February 13, 2013
33 mins read

‹‹እኔ ብዙ ግርግር አልፈልግም፤ ብዙ መታየትም አልወድም›› – (ኃይሌ ሩትስ)

ቺጌ› በተሰኘ አልበሙ ታዋቂነትን እያተረፈ የመጣው ድምፃዊ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) ከአንድ በኢትዮጵያ ከሚታተም መፅሄት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ለአንባቢዎቻችን በሚስማማ መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ጥያቄ፡- በመጀመሪያ አልበምህ ጥሩ አቀባበል አግኝተሃል፡፡ ይህን መሰል አቀባበል አገኛለሁ ብለሀ ጠብቀህ ነበር? ከአድማጮችስ ምን አስተያት አገኘህ?
ኃይሌ፡- እንዲህ አይነት አቀባበል ይኖራል ብዬ አልጠበቅኩም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሙዚቃው ላይ የተለመደው የመዝናኛ እና የፍቅር ዘፈን ስለሆነ አንተ ሲሪየስ ነገር ነው ይዘህ የመጣኸው የሚሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የሚገርም ነገር ነው የተፈጠረው፡፡ ከእኛ መሀል ኤልያስ መልካ ብቻ ነው እንደዚህ ጠብቆ የነበረው፡፡
ጥያቄ፡- አልበምህን ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ኃይሌ፡- በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን ለመጨረስ ረዥም ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ጠቅላላ ፕሮጀክቱን ለማነቃነቅ ነው ትልቅ ጊዜ የወሰደው እንጂ አንዳንዶቹ ዘፈኖች ከተሰሩ ቆይተዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ቅርብ ጊዜ የተሰሩ ናቸው፡፡ እናም በአጠቃላይ ከአምስት ዓመት በላይ ፈጅቷል፡፡
ጥያቄ፡- ኤልያስ መልካ ከሰራው ከአንዱ ግጥም ውጪ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ያንተ ስራ ነው፤ የሌሎችን ሰዎች ግጥሞች መቀበል ያልፈለግህበት ምክንያቱ ምንድነው?
ኃይሌ፡- ሬጌ መዝፈን ስጀምር ሬጌን እኛ እንደምንፈልገው የሚጽፍልን ሰው አልነበረም፤ ሁላችንም የሬጌ ዘፋኞች ራሳችን ነን ግጥሙን የምንጽፈው፡፡ በወቅቱ የነበረው አማራጭ ይህ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ አንፃር ራሴ ነበር የሰራሁት፤ የሰው ግጥም አልፈልግም በሚል ግን አይደለም፤ ደስ የሚል ስራ ከተገኘ ከሌላ ሰው ባገኝ ደስ ይለኛል፤ እኔ መሰራት አለበት ብዬ የማስበውን ነገር ነው የሰራሁት፡፡ ስለዚህ ራሴ መስራት ስለነበረብኝ ነው እንደዚያ የሆነው፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹ቺጌ›› የሚለው ስልት በማንና እንዴት ተፈጠረ? ከኤልያስ መልካ ጋር ‹‹ቺጌ››ን በመፍጠር ረገድ የነበረህ ሚናስ ምን ይመስላል?
ኃይሌ፡- ሀሳቡ የኔ ነው፡፡ የጃማይካን ስልት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ነገር ጨምሬበት መስራት ፈለግኩ፡፡ ቺክቺካንና ሬጌን ቀላቅዬ መስራት እፈልግ ስለነበር ለኤልያስ እንደዚህ መስራት እፈልጋለሁ አልኩት፡፡ የተወሰነ ሪትም ሞከርን፣ ከዚያም ኤልያስ እንደዚህ ነው ሚክስ መደረግ ያለበት ብሎ ሬጌውንና ቺክቺካውን ቀይጦ ሰራው፡፡
ጥያቄ፡- ይህ ስልት የተቀላቀለ ነው ወይንስ አዲስ ኢትዮጵያዊ ስልት ሊባል ይችላል?
ኃይሌ፡- እንግዲህ እኛ ለራሳችን አዲስ ስልት ነው ብለናል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ሬጌንና ቺክቺካን ቀላቅሎ የሰራ ሰው እስካሁን አልሰማሁም፡፡ ስለዚህ አሁን እንደ አዲስ መንገድ የውጪውንም ሰው ጆሮውን ቀረብ ታደርገዋለህ፡፡ ሪትሙ አራት በአራት የሚሄድ ስለሆነ የበለጠ ቀለል ያለ ሆኗል፤ ቺክቺካው ላይ ሬጌ መግባቱ ደግሞ ለጆሮ አዲስ እንዳይሆን የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለውጪው አድማጭ፡፡
ጥያቄ፡- ከአገር ውጪ ለመስራት ስምምነት ያደረግክበት ሁኔታ አለ?
ኃይሌ፡- አዎ! ከፋሲካ በኋላ የኛ ቱር ይጀምራል፤ ከሀገር ውስጥ ይጀምርና ከዚያ በኋላ በውጪ ይቀጥላል፡፡ ከመጀመራችን በፊት ለሰው ግልፅ እንዲሆን ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅተን አካሄዳችንን በወቅቱ እናብራራለን፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ጀምሮ ኮንሰርት አለ፡፡
ጥያቄ፡- በቴዲ ስራዎች ላይ በፊቸሪንግ ገብተህ የምትናገራቸው ቃላት የምን ቋንቋ ናቸው? ትርጉም አላቸው ወይንስ ዘፈኑን ለማድመቅ ያህል ነው? ለምሳሌ፡- ግርማዊነትዎ በሚለው ዜማ ላይ በፊቸሪንግ የምትገባበትን ትርጉሙን ልትነግረኝ ትችላለህ?
ኃይሌ፡- ግርማዊነትዎን እኔ አይደለሁም የገባሁት፤ ጆኒ ራጋ ነው የገባው፡፡ ከቴዲ ጋር ላምባዲና እና ቦብ ማርሌይ ላይ የምዘፍናቸው፤ ሁለቱም ትርጉም አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹ላምባዲና›› የሚለው ‹‹Every body says lambadina…››የሚለው በተለይ የእውቀትን ብርሃን አዕምሮዬ ላይ አብራልኝ፤ ‹‹Light on the fire…›› ማለት ‹‹በዚህ ዓለም እንዳስተውል አዕምሮዬን የጥበብ ብርሃን አድርግልኝ›› ነው የሚለው፡፡
‹‹ቦብ ማርሌይ›› የሚለው ደግሞ ‹‹we need fire… we don’t need water…›› ይላል፡፡ በራስታ ውስጥ አንድ እምነት አለ፤ ሁሉም ነገር በእሳት ውስጥ ማለፍ አለበት ይላሉ፡፡ ለምን? እሳት ወርቅን ያጠራል፤ ለማንኛውም ነገር እሳት ማጥሪያ ነው የሚል ይዘት ያለው ነው ያአባባል፡፡ እናም በቦብ ማርሌይ ዘፈን ‹‹we need fire… we don’t need water…›› ያልኩት ለዚያ ነው፤ ትርጉም አለው፡፡ ውሃን ሳይሆን የምፈልገው የሚያፀዳንን እሳትን ነው፡፡
ስለዚህ ብዙዎቹ ትርጉም ያላቸው እንጂ ዘፈን ለማድመቅ ተብለው የገቡ አይደሉም፡፡ በነገራችን ላይ የጃማይካ ቋንቋ በይበልጥ ለአገላለፅ የሚመች… በተለይ ደግሞ እንደ አማርኛ ቅኔ ተቀኝተህ መግለፅ የምትችልበት አይነት ቋንቋ ነው፡፡ ስለዚህ ነው እንጂ ዝም ብዬ ዘፈን ለማድመቅ አንድም ነገር አልተጠቀምኩም፡፡ ብዙ ዓመት የኖርኩት ከጃማይካዎች ጋር በመሆኑ ለቋንቋውም አዲስ አይደለሁም፡፡
ጥያቄ፡- ከኤልያስ መልካ ጋር የጠበቀ ጓደኝነት እንዳላችሁ አውቃለሁ፤ ለምድነው በበገና ሪከርድስ ሙዚቃህን ያላሳተምከው? ስለ ጓደኝነታችሁ ንገረኝ፤
ኃይሌ፡- እኔና ኤልያስ ጓደኛ ሳይሆን ወንድማማቾች ነን፡፡ ብዙ ዓመት አንድ ላይ ነው የኖርነው፡፡ ጎረቤት ነን፤ እርሱ ቦሌ አካባቢ እያለ እኔም እዚያው አካባቢ ነበር የምኖረው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው ጓደኝነታችንን በስራ ላይ እንደ ስራ ነው ቅርበቱ፡፡ ጓደኝነታችን ደግሞ ለብቻ ነው፡፡ ከበገና ሪከርድስ ጋር መስራት እፈልጋለሁ፡፡ ግን አንዳንድ የወረቀት ስራዎች ይቀሩናል፡፡ ከውጪ ድርጅቶች ጋር የምንሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ስለሚዘገይ ነው ከአዋድ ጋር ተነጋግረን እንዲወጣ ስምምነት ያደረግነው እንጂ እኔም በዚያ በኩል ቢሆን ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ጊዜው ስለሄደ ነው ያልተሳካው፡፡ ኤሌክትራ ጋርም ደክሜ አለቀ ሲባል፣ ናሆም ጋርም እንዲሁ ተጀምሮ ተቋርጦ ነበር፤ እና ያንን ስራ ጨርሶ ለማውጣት እንጓጓ ነበር፡፡ በመጨረሻ ከአዲካዎች ጋር በፍጥነት ነው ሰርተን ያወጣነው፡፡
ጥያቄ፡- በገና ሪከርድስ ሙዚቃ የማሳተም ስራውን መቼ እንደሚጀምር ተነግሮሃል?
ኃይሌ፡- አይታወቀውም፤ እኛ በበኩላችን ውስጣዊውን ስራ እየሰራን ነው፤ እኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ነገሮች እንደታሰቡት አይደለም የሚጓዙት፡፡ ዋናው ከባዱ ነገር ውስጥ ለውስጥ የኮምዩኒኬሽን ስራውን መስራቱ ነው፤ ብዙ ጊዜ የሙዚቃው እንጂ የወረቀት ስምምነት ልምዱ ስለሌለን በዚህ የተነሳ ጊዜ ፈጅቷል፡፡
ጥያቄ፡- ከአዲካ ጋር በምን አጋጣሚ ተገናኛችሁ?
ኃይሌ፡- ጭንቀት ነዋ! (ሳቅ) የመጨረሻ ጭንቀት ሲጨንቀኝ ወደዚያ ሄድኩ፡፡ አሁን ምክንያቶችን መግለፅ አልፈልግም፤ ማለትም የኔ ሙዚቃ ለመውጣት ብቁ ሳይሆን ቀርቶ ሳይሆን ሌሎች ምክንያቶች ነበሩ፡፡ እኔ ሰርቻለሁ፤ ደክሜያለሁ፡፡ ግን ነገሩ እንዳሰብኩት አልሆነም፡፡ መጨረሻ ላይ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር እያወራን ለምን አዋድን አናነጋግረውም ተባባልን፤ እኔም አዋድን በቴዲ በኩል አውቀው ነበርና ጠርቼ አሰማሁት፡፡ አንዴ እንደሰማው ነው የወደደው፤ ከዚያ በኋላ መቼ እንደሚያልቅ ወዲያው ተነጋግረን ጨረስን፡፡ ያው እግዚአብሔርም ቀኑን ሊያሳካው እንዲያ ሆኖ ወጣ እንጂ የተለየ አካሄድ ሄደን አይደለም፡፡
ጥያቄ፡- ከአዲሱ አልበምህ ምን ያህል ክሊፖችን ሰርተሃል?
ኃይሌ፡- ሶስት ሰርቻለሁ አሁን ደግሞ ሌሎች ሶስት ፕሮጀክቶች ላይ ያሉ አሉ፡፡ ‹‹ጨው ለራስሽ››፤ ‹‹ንፁህ ቋንቋዬን›› እና ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚሉትን ዘፈኖች ክሊፕ ሰርቻለሁ፤ ሌሎችን ለመስራት ደግሞ ስክሪፕት በመስራት ላይ ነን፡፡
ጥያቄ፡- ከአልበሙ ጋር በተያያዘ ከሞዴል ኤልሳቤጥ ጋር የሰራኸው ዘፈንና ክሊፑ እኩል አልሄደልኝም፡፡ በዚህ ላይ ያንተ አስተያየት ምንድነው?
ኃይሌ፡- በመጀመሪያ ስክሪፕቱን አይቼው ጉዳዩን እንደገለፀው ስለገባኝ ነው የሰራሁት፡፡ ስክሪፕቱን የሰራው ያሬድ ሹመቴ ነው፡፡ እኔ ባየሁት ነገር ደስተኛ ነኝ፡፡ እኛ የተቻለንን ያህል እንዲገልፅ ሞክረናል፡፡ ስክሪፕቱን የሰራሁት እኔ አይደለሁም፡፡ ከኔ ስክሪፕቶች መካከል ‹‹ቺጌ›› የሚለው አዲስ እየተሰራ ያለ ፕሮጀክት አለ፡፡ ይህኛው ስክሪፕት የኔ ነው፡፡ መጀመሪያ ስንሰ ራም አምነንበት ነው የሰራነው፤ እኔም ኤልያስም ስክሪፕቱን አይተነዋል፡፡ ግጥሙን የጻፈው ኤልያስ ስለሆነ ሀሳባችንን ይገልፃል ወይ ብዬ መጀመሪያ ወስጄ ያሳየሁት ለርሱ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ፀጉርህን ድሬድ ማድረግ የጀመርከው መቼ ነው? ጓደኛህ ኢዮብ ፀጉሩን ተቆርጧል፤ አንተስ ወደ ፊት ሀሳብህ ምንድነው?
ኃይሌ፡- ፀጉሬን ማሳደግ ከጀመርኩ ብዙ ቆይቷል፤ 8 እና 9 ዓመት ይሆነዋል፡፡ ራስ ውስጥ ድሬድን ከእምነቱ ጋር የሚያያይዙ አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ የግድ ድሬድ ሁን የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ ግን ሬጌ ውስጥ እንዳለኝ ልምድ ዋናው ነገር ስራ ነው፡፡ ፀጉር ማሳደግ አለማሳደጉ ከስራ ጋር የሚያያዝ ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡ ከውስጥህ፣ ከምትሰራው እና ከማንነትህ ጋር ነው መያያዝ ያለበት፡፡ አንድ ሰው ፀጉሩን ከመሰለው ያሳድገዋል፤ ካልመሰለው ይቆርጠዋል፡፡ እኔም በዚያ ደረጃ ነው የማስበው እንጂ ለሆነ ነገር መጠቀሚያነት አድርጌ ከዚያ በኋላ ደግሞ ያ ነገር ሲሳካ መቆረጥ አይነት ነገር አላስብም፡፡ ኢዮብ ጓደኛዬ ነው፡፡ በህይወቴ ከማከብራቸው ሰዎች አንዱ ኢዮብ ነው፡፡ በብዙ ነገር የሚያማክረኝ፣ ‹‹ይህ ጥሩ ነው፤ ይህ መጥፎ ነው›› የሚለኝ ሰው ነው፡፡ እና ኢዮብ ምን አይነት አስተሳሰብ እንዳለው አውቃለሁ፡፡ ከፀጉሩ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለውም፡፡ እኔ አሁን ለመቆረጥ እቅዱ የለኝም፡፡ ግን ነገ ከነገ ወዲያ ምን እንደሚሆን አላውቀውም፡፡ አሁን ባለኝ አስተሳሰብ ግን የመቆረጥ እቅዱ የለኝም፡፡
ጥያቄ፡- ከልጅነትህ ጀምሮ ለሬጌ ሙዚቃዎች (ስልቶች) ፍቅር ነበረህ፤ ፀጉርህን ያሳደግኸው ያ ተፅዕኖ አሳድሮብህ ነው?
ኃይሌ፡- በፊት ራስ ተፈሪያንን ነበር የማስበው፤ የምከተለውም፡፡ በዚያ ውስጥ ደግሞ ድሬድ በጣም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ አንደኛ ከዚያ አንፃር ነው፤ ቤተሰብም ይከለክል ስለነበር የማሳደግ እልሁ ነበረኝ፡፡ በፊት ማህበረሰቡ ከባድ ስለነበር የማሳደግ ጉጉቱ ነበር፤ የበለጠ ደግሞ ከስልጣኔ በፊት የነበረው የአፍሪካውያንን አይነት ጊዜ የነበረውን ቡሽማን (የገጠር አይነት ሰው) የሚለውን ነው የሚገልፀው፡፡ ከቴክኖሎጂው በፊት የነበረውን ኦርጅናል አካሄድ ነው የሚያሳየው፡፡ ከዚያ ውጪ የተለየ ነገር ሰጥቼ በህይወቴ ውስጥ እንደዚህ መቆረጥ አለበት፣ የለበትም ብዬ አላስብም፡፡ እንደ ውበትና እንደ ፋሽንም አይደለም የምጠቀመው፣ ለምን? ፋሽን የሆነ ጊዜ ላይ ያልፋል፤ ሌላ አዲስ ፋሽን መምጣት አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ ፋሽን አይደለም፤ የምንወደውን ነገር ነው የምናደርገው፡፡ ለዘመናዊነትና ከሰው ለየት ለማለት ብዬም አይደለም፡፡
ጥያቄ፡- የቤተሰቦችህ ሁኔታ ምን ይመስላል? የት ተወለድክ? የት አደግክ? የት ተማርክ? ከቤተሰብ ያንተን ፈለግ የተከተለ አለ?
ኃይሌ፡- ዘጠኝ ወንድማማቾች ነን፡፡ ሁለት እህቶች አሉኝ፡፡ ከመጨረሻ ሁለተኛ ልጅ ነኝ፡፡ እናቴ በህይወት የለችም፡፡ አባቴ አለ፡፡ አባታችን ነው ያሳደገን፡፡ ያደግሁት እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃን ስላሴ ካቴድራል፤ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ዳግማዊ ምኒልክ  ነው የተማርኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ትምህርት አልሆነኝም (ሳቅ)፡፡ እግርኳስ ተጨዋች ነበርኩ፤ እግርኳስ በጣም ነበር የምጫወተው፤ ከዚያ እርሱን ተውኩና ወደ ሙዚቃው ገባሁ፡፡
ሙዚቀኛ በዘሬም የለም፤ እኔ ብቻ ነኝ በድፍረት የወጣሁት፡፡ ለዚያ ነው በወቅቱ ሙዚቃ ስጀምር ተቸግሬ የነበረው፡፡ መግባባት አልነበረም፤ ቤተሰብ የሚፈልገው የሃይማኖት እና ሌላ ሌላውን ሙያ ስለነበር ይህን አይደግፉትም ነበር፡፡ እና በወቅቱ ችግር ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ለሙዚቃ እድገት በናይት ክለብ መስራት ምን ያህል አግዞኛል ትላለህ? በቅርቡስ ወደ ናይት ክለብ ትመለሳለህ?
ኃይሌ፡- ናይት ክለብ በጣም ጠቅሞኛል፤ አንደኛ የኮንሰርት ልምድ እንዳገኝ ረድቶኛል፤ ከልጅነታችን ጀምሮ ብዙ የሙዚቃ መሰረት የለንም፡፡ በውጪ ሀገር አንዳንድ ጥሩ ነዋሪዎች ግራንድ ፒያኖ ቤታቸው አላቸው፡፡ አብዛኛው ቤት ውስጥ አንድ የሙዚቃ መሳሪያ ያውቃሉ፡፡ እኔ እንደዚያ አይነት የሙዚቃ መሰረት የለኝም፡፡ ሬጌ ሰማሁ፤ ሬጌ መዝፈን ፈለግሁ፤ ያኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨረስኩ ስነሳ አላማዬ ስለ ኢትዮጵያ የሚያወራውን ጠንካራ መልዕክት በአማርኛ ማድረስ ነው፡፡ እና ምንም መሰረት ስላልነበረ ልምድ ለማግኘት ናይት ክለብ የግድ ያስፈልግ ነበር፡፡ በየሳምንቱ ብዙ ዘፈን ነው የሚሰራው፤ መድረክ ለመልመድ፤ ድምፅ እንዲስተካከል፤ ከባንድ ጋር ያለን ሁኔታ ለመለማመድ ያግዛል፡፡ እኔ ስጀምር ባንድ ሬት አላውቅም፤ ኪይ አላውቅም ነበር፡፡ እነዚህን እነዚህን ነገሮች ተምሬያለሁ፡፡ በእርግጥም ጠቅሞኛል፡፡ ለኑሮም ይረዳል፤ እኛ ሀገር በተለይ ካሴት ካላወጣህ ልትሰራና ገንዘብ ልታገኝ የምትችለው ክለብ ሲሰራ ነው፡፡ በዚያ ገንዘብ ይገኝበታል፤ በዚያ ሕይወትህን ትመራለህ፤ ትኖራለህ፡፡ ስለዚህ እኛ ሀገር ባለው ሁኔታ ክለብ መስራቱ ወሳኝ ነው፡፡
እስካሁን ብዙ ክለብ ነው የሰራሁት፡፡ ከኦፊስ ባር ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ አሪፍ የተባሉ ቦታዎች ሰርቻለሁ፡፡ ዝርዝሩን መጥቀስ ይከብዳል፡፡ ከዜማ ላስታስ ጋር ቡፌ ደ ላጋር ነው የጀመርኩት፡፡ በአዲሱ አልበሜ በወር አንድ ቀን መርጠን ጃም ማድረግ ስላሰብን እቅድ እያወጣን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ የሬጌ ባንድ እያደራጀን ነው፤ የባንዱንም ስም ‹‹ቺጌ›› ልንለው ነው፡፡ ሁለት ጃማይካዎች አሉበት፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት ብለው ኢትዮጵያ የሚኖሩ ጃማይካውያን ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሐበሾች ናቸው፡፡ ጥሩ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በቅርቡ ስራችንን ሰው የሚያየው ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ወደ ፊት ክለብ መስራቱ ብዙም አይታየኝም፡፡ ብዙ ዓመት ክለብ ውስጥ ስለሰራሁ ህይወትን ቀየር አድርጌ የመኖር እቅድ አለኝ፡፡
ጥያቄ፡- ወደ ሬጌ ስልት ልታደላ የቻልክበት ምክንያቱ ምንድነው?
ኃይሌ፡- የፖለቲካም ይሁን የፍቅር ጉዳይ የሚያነሱ አብዛኞቹ ትልቅ የሬጌ አርቲስቶች ናቸው፡፡ ስለ ህብረተሰቡና በማህበራዊ ጉዳይ ዙሪያ ነው የሚያቀነቅኑት፤ እኔንም የመሰጠኝ ይህ ነው፤ እንደምዘፍንና የመዝፈን ችሎታ እንዳለኝ እንኳን አላውቅም ነበር፡፡ ይህንን ነገር ስሰማ ይህ መልዕክት ለእኛ ሰው መድረስ አለበት፤ ይህንን ነገር ህዝቡ አልሰማውም ከሚል ነው አነሳሴ፡፡ የሚቀርበው መልዕክት ጠንካራ በመሆኑ ለህዝባችን በጣም ያስፈልገዋል በሚል መነሻ ነው ሬጌን ለመዝፈን የተነሳሁት፡፡
ጥያቄ፡- የሕይወት ፍልስፍናህ ምንድነው?
ኃይሌ፡- በፍልስፍና ሳይሆን በእውነታ ነው የምኖረው፤ በፍልስፍና መኖር አልፈልግም፤ ፍልስፍና ማለት አንተ የምትኖረው ህይወት ነው፤ እኔ የምኖረው ህይወት እንደማንኛውም ማህበረሰብ አይነት ህይወት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ጤነኛ ህይወት ነው የምኖረው፡፡ እውነቱን ተከትዬ መኖር ነው የምፈልገው፡፡ በራሴ ሀሳብ ብቻ ተመርኩዤ ብዙ መጓዝ አልፈልግም፡፡ ከሁሉም በላይ ይህቺ ምድር የእግዚአብሔር ምድር ናት፡፡ ስለዚህ እርሱንም አክብሬ መጓዝ ነው የምፈልገው፡፡ እና በእውነታ ውስጥ መጓዝ ደስ ይለኛል፡፡ ያው ለመኖር እውነታ ከባድ ነው፤ የሰው ልጅ ይሳሳታል፤ ያጠፋል፤ ግን አሁንም በእውነታው መንገድ ውስጥ መኖር እና ይበልጥ የራሴን መንገድ ነው የምከተለው፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹በየመሀሉ›› በሚለው ዘፈንህ ላይ የተደጋገመ ‹‹እናስብ አንዳንዴ›› የሚል ገለፃ አለ! የሰው ልጅ ማሰብ ያለበት አንዳንዴ ነው ወይስ ሁልጊዜ?
ኃይሌ፡- (ሳቅ…) እናስብ አንዳንዴ ማለት ለምሳሌ የሆነ ነገር ስታጠፋ አንዳንድ ሰዎች ‹‹እንዴት! ኧረ አንዳንዴማ እንደዚህ እናድርግ፤ ተዉ እንጂ!›› ይላሉ፡፡ ያ ማለት አንዳንዴ ብቻ ጥሩ ሰው ሁን ማለት ሳይሆን ‹‹አስብ እንጂ›› አይነት መልዕክት አለው፡፡ እንጂ አንዳንዴ ብቻማ ለምን እናስባለን፤ ሁልጊዜም ነው እንጂ፡፡ አገላለፁ ግን ‹‹እናስብ አንዳንዴ›› ማለቱ ጓደኛህ ‹‹አንዳንዴማ ይሉኝታ ይኑርህ›› ይልህ የለ? ልክ እንደዚያ እንደማለት ነው፡፡ ሁሌም ይሉኝታ ሊኖረን ይገባል አንዳንዴ ብቻ አይደለም፡፡
ጥያቄ፡- እንደ ቦብ ማርሌይ በልጅነትህ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልም ነበረህ የሚባለው እውነት ነው? ቦብ ማርሌይንስ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ኃይሌ፡- ቦብ እኮ የሙዚቃው መሰረታችን ነው፤ ቦብ ማለት የማህበረሰብን ትክክለኛ ህይወት እና መንገድ ይዘህ ከሄድህ ምን ያህል ማሸነፍ እንደምትችል ያሳየ ነው፡፡ ቦብ ለእኛ ጆሮአችን ሰምቶ የማያውቀውን አዲስ ስታይል ነው ያመጣው፡፡ ከዚያ በፊት ‹‹ስካ›› የተባለው የጃማይካ ሙዚቃ ስልት ነው የነበረው፤ ያንን ቀይሮ ነው ሬጌ ያደረገው፡፡ ኢትዮጵያ መጥቶ 14 ቀን ቆይቷል፡፡ ብዙ የሬጌ አርቲስቶች አሉ፤ ነገር ግን የተወሰኑት ናቸው ቃላቸውን አክብረው ኢትዮጵያ የመጡት፡፡ ቦብ በብዙ መልኩ ስታየው ለኢትዮጵያ የነበረው ፍቅር በጣም የሚያስገርም ነው፤ ስለ ኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ስለ አፍሪካም የነበረው አስተሳሰብ ትልቅ ነበር፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር የቀባው ሰው ነበር፤ በሙዚቃው ተሰጠው ስጦታ ልዩ ነው፡፡ በአስተሳሰቡ፤ በአመለካከቱ፣ በአብዛኞቹ ስራዎች አይከን ነው፡፡
ጥያቄ፡- ቀለል ያለ ህይወት መምራት ይመቸኛል ብለህ ስትናገር ከዚህ ቀደም ሰምቻለሁ፤ ቀለል ያለ ህይወት ላንተ ምን ማለት ነው?
ኃይሌ፡- ምንም ሳታካብድ መኖር፡፡ እኔ ብዙ ግርግር አልፈልግም፤ ብዙዎች ታዋቂ ሰዎች እንደሚኖሩት አይነት ህይወት መኖር አልፈልግም፡፡ ያ ለእኔ ህይወት አይደለም፡፡ እኔ ከዚህ በፊት የኖርኩት ህይወት አለ፡፡ ከህዝቤ ጋር፣ ከዝቅተኛው ህብረተሰብ ጋር እርሱን ሕይወት ነው መኖር የምፈልገው፡፡ በስራህ ሰው ሊወድህ ሊያከብርህ ይችላል፡፡ ህይወቴ ግን ብዙም የምወጣ የምታይም ሰው አይደለሁም፤ ብዙ መታየት አልወድም፤ ‹‹Behind the Scene›› ይለዋል እንግሊዝኛው፡፡  የተለየ ሰው ለመሆን ፈልጌ ሳይሆን እኔ የምፈልገው እንደዚህ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አሁን የምትኖረው ከማን ጋር ነው? ጓደኛስ አለችህ?
ኃይሌ፡- የምኖረው ከጓደኞቼ ጋር ነው፡፡ ለረዥም ጊዜያት ከጓደኞቼ ጋር አብረን ነው የምንኖረው፡፡ ትዳርና ጓደኛን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ ግን ይለፈኝ፡፡
ጥያቄ፡- ለመሰነባበቻ ለአንድናቂዎችህ ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ?
ኃይሌ፡- እኛ ሙዚቀኞች ነን፡፡ ለማህበረሰቡ በተለይ ለወጣቶች ማስተላለፍ የምፈልገው ሁል ጊዜ ራሳችንን መመልከት እንዳለብን ነው፡፡ መነሻችንን፣ ባህላችንን፣ ማንነታችንን አውቀን በዚያ ውስጥ ነው መሰልጠን ያለብን፡፡ የራሳችንን ነገር ይዘን ስልጣኔ ውስጥ ብንገባ፣ ስልጣኔ ነው ብለን ያለንን ነገር በሙሉ ጥለን የሌላ ነገር ውስጥ ባንገባ ጥሩ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በወጣቱ ትውልድ ላይ ማየው ያን ነገር ነው፡፡ አካሄዱን፣ አለባበሱን፣ አደናነሱን፣ ክሊፖች ላይ እንዴት እንደሚደንሱ ስናይ፣ አንዳንዶቹ ነገሮች ፍፁም ከእኛ ማንነት እየወጡ ነውና ወደ ራሳችን እንመለስ ነው የምለው፤ ምክንያቱም ሁሌ የራስህን ነገር ነው ልዩና አዲስ የሚያደርግህ፡፡ ስለዚህ ያራሳችንን፣ ማንንም የማይመስለውን፣ አዲስ የሆነውን ነገራችንን ይዘን ነው ወደ ዓለም ስልጣኔ መግባት ያለብን፡፡ በመጨረሻ በገና ስቱዲዮን፣ አዲካ ኮምዩኒኬሽን ኤንድ ኢቨንትስን እንዲሁም ከጎናችን በመሆን የተባበረንን ህዝብ በእጅጉ አመሰግናለሁ፡፡S

Go toTop