July 22, 2024
5 mins read

እስክንድር ነጋ ይብቃው፣ ገለል ይበል

ታጋይ እስክንድር ነጋ፣ ከነአርበኛ ጋሽ ምንተስኖት ጋር ሆኖ፣ የተወሰኑ ነፍጥ የያዙ ወጣቶችን ከጎኖ አድርጎ፣ የሰጠውን መግለጫ፣ የስታሊን ገብረስላሴ ዛራ ሜዲያ ላይ አየሁት፡፡ ተደረገ የተባለው “ምርጫ” የፈጠረውን ክስተት ተከትሎ የተነሳውን ትልቅ ውዝግ በመመልከት ፣ አንዳንዶች ምን አልባት እስክንድር ነጋ ትሁት ሆኖ፣ ነገሮችን ያረጋጋል የሚል እምነት የነበራቸው አይጠፉም፡፡ ሆኖም እንደጠበቁት አልሆነም፡፡
ብቃት ያለው፣ ሃቀኛ የህዝብ መሪ፣
– 1ኛ ከራሱ ፍላጎት በፊት የህዝብን ጥቅም ያስቀድማል፡፡
– 2ኛ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ በማሰብ ጥንቃቄዎችን ያደርጋል፡፡
– 3ኛ ችግሮች ሲፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ ቀዳዳዎችን ለመድፈን ቅድሚያ ሰጥቶ ይሯሯጣል፡፡ ችግሮችን ይፈታል፡፡
– 4ኛ ችግሮችና አለመስማማቶች ሲኖሩ፣ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ይኖራልም፣ ሁሉንም አስታራቂና አሰባሳስቢ በመሆነ መልኩ መፍትሄዎችን በማምጣት፣ እመራቸዋለው የሚላቸውን ወገኖች አንድነት አስጠብቆ ይጓዛል፡፡
– 5ኛ ትግሉ ወደፊት እንዳይሄድ፣ እርሱ መሰናክልና ችግር ከሆነ፣ ወይም ከርሱ የበለጠ ትግሉን ወደፊት ሊያስኬዱ የሚችሉ ሰዎች ካሉ፣ ገለል ብሎ ቦታውን ለሌሎች ይሰጣል፡፡
እስክንድር ነጋ የራሱን ድምጽ ለራሱ ሰጥቶ፣ 5 ለ 4 ድምጽ፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አሸነፍኩ ብሎ መግለጫ ሲሰጥ፣ ለተፈጠረው ቀውስና ችግር ደንታም የሰጠው አይመስልም፡፡ መግለጫው እንደወጣ በከፍተኛ ደረጃ ነው ትልቅ ውዝግብ የተነሳው። ይህ ሊያስደነግጠውና ቆም ብሎ እንዲያስብ ሊያደrገው ይገባ ነበር፡፡ በርሱ መመረጥ ዙሪያ ብዙዎች ከተቃወሙ፣ “በፋኖዎች መካከል ንትርክ መኖሩ ማንን ነው የሚያስደስትነው? ማንን ነው የሚጠቅመው ?” ብሎ መጠየቅ ነበረበት፡፡ መሪ ነኝ ሲል፣ የተቃወሙትን ለማነጋገር በመሞከር የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መሯሯጥ ነበረበት እንጂ ሜዲያ ላይ ቀርቦ፣ የጨረባ ምርጫው ተመርጫለሁ ብሎ አብይ አህመድ እንደሚደነፋው፣ተመርጫለው ብሎ ደረቱን ነፍቶ መውጣት አልነበረበትም፡፡
እስክንድር ወደሰጠው መግለጫ ስንመጣ፣ መግለጫውን የሰጠው ሸዋ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ከሸዋ ጠቅላይ ግዛት እዝ አንድ አመራር፣ ከጋሽ ምንተስኖት በቀር፡፡ ለእስክንድር ነጋ ድምፅ የሰጠው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እዝ መሪ ሻለቃ መከታውን ጨምሮ፣ ሌሎች የሸዋ ጠቅላይ ግዛት አመራሮችና የክፍለ ጦር አዛዦችን አላየሁም፡፡ ምን አልባት በሸዋ ጠቅላይ ግዛት እዝ አመራሮች መካከል ነገሮችን እንደገና ለማጤን የፈለጉ ይመስላል:: ይሄ ጥሩና ተስፋ ሰጪ ምልክት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ጽፊያለሁ፣ እስክንድር ነጋ የመሪነት ብቃት ይለውም፡፡ ገለል ማለትና፣ በሞያው፣ በችሎታው ሊያበረክት የሚችለውን ስራ ቢሰራ ጥሩ ነው፡፡ ትግሉ የህዝብ እንደመሆኑ ግለሰቦችን ማምለክና ማግነን፣ የግለሰቦችን ተክለ ሰውነት መገንባት መቆም አለበት፡፡ የግልሰብ ተከታዮች ሳይሆን የመርህ ሰዎች መሆን አለብን፡፡ ማንም ሰው መሪ ይሁን አይሁን ጥሩ ሲሰራ፣ ጥሩ ህሳብ ሲያመጣ መደገፍ፣ ማባረታት፣ ማመስገን አስፈላጊ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ መሪም ሆነ ሰው ስህተቶች ሲሰራ ፣ መውቀስ፣ መተቸት፣ ለማረምና ለማስተካከል መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡ ያ ሰው አልታረም ብሎ የበለጠ ጥፋት እየፈጸመ ከሆነ ደግሞ ያንን ሰው መቃወምና መታግል ያስፈልጋል፡፡
ግርማካሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop