May 23, 2024
25 mins read

ልዕልት ሂሩት ደስታ ምን አይነት ሰው ነበሩ?

ከአንሙት ስዩም

ልዕልት ሂሩት ደስታ
ልዕልት ሂሩት ደስታ

እስካሁን በኖርኩባቸው አመታት የተረዳሁትና የገባኝ አንድ ነገር አለ፡፡ በዝህብ ላይ መጥፎ ስራ የሰሩትን ወንጀለኞች ለፍርድና ለቅጣት የማቅረብና የማስፈረድ ልምድ ያለንን ያህል፤ መልካም ለሰሩት ግለሰቦች ግን ተመጣጣኝ የሆነ የስማቸው ማስታወሻ የሚሆኑ ነገሮች የማናደርግ መሆናችንን ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ፤ የአንድን አካባቢ ህዝብ ህይዎት፤ በትልቅ ሁኔታ የለወጡትን ገልሰቦች፤ በአቅም ማነስ እንኳን ምንም ነገር ማድረግ ባንችል፤ ስራቸውን በጽሁፍ መልክ ሌሎች ሰዎች እንዲያውቁት ማድረግ የዜግነት ሃላፊነት ነው፡፡

እኔ በበኩሌ፤ የማውቀውን ላልሰሙና ላላወቁ ኢትዮጵያውያን ግልጽ ማድረግ የምፈልገው፤ የልዕልት ሂሩት ደስታን የበጎ አድራጎት ስራ ነው፡፡ ልዕልት ሂሩት፤ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የልጅልጅ ናቸው፡፡ እናታቸውም የጃንሆይ ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ ሲሆኑ አባታቸው ደግሞ ስመጥሩው አርበኛ ክቡር ራስ ደስታ ዳምጠው ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ሊያስታውሱት የሚችሉት፤ ልዕልት ሂሩት የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገላቸውን ይሆናል፡፡ በዚያን ወቅት፤  ለትምህርትቤቱ አስተዳዳሪዎች፤ መምህራንና ተማሪዎች ስለነበራቸው እህታዊ ፍቅርና ላሳዩትም መልካም የአስተዳደር ችሎታ፤ በትምህርት ቤቱ የተማሩና የተመረቁ ሴቶች ሁሉ የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡

አሁን እኔ ግን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቸ ማካፈል የምፈልገው፤ ልዕልት ሂሩት፤ ከንጉሣዊ ቤተሰቦቻቸው ተለይተው፤ የቤተመንግስትን የድሎት ኑሮ ትተውና የወጣትነታቸውንና ትዳር የመያዣቸውን ጊዜ ሰውተው፤ ተረስቶ ወደነበረው የገጠር ከተማ፤ ላሊበላ፤ ሄደው የብዙ ሰዎችን ህይዎትና የከተማውን ውበት ከፍ ያደረጉበትን በጎ ስራቸውን ነው፡፡ ይኧውም፤ የቅዱስ ላሊበላ ቤተክርስቲያናትን ለማየትና ለማድነቅ የሚጓዙ የውጭ አገር ጎብኝዎች ማረፊያና ማስተናገጃ ስላልነበረ፤ ሆቴል ለማሰራት ወስነው ላሊበላ በ1951 ዓ.ም መምጣታቸው ነው፡፡ ልዕልቷ ይህን ለማድረግ የወሰኑበት ምክን ያት፤ በመጀመርያ መንፈሳዊ ስለነበሩ፤ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ፤ የቦታውን ቅዱስነት በደንብ አደርገው ስለሚያውቁ ነበር፡

የአካባቢው አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አበበ ስዩም፤ ለልዕልት ሂሩት ማረፍያ ቤት ላሊበላ ውስጥ ለማግኘት ተቸግረው በነበረበት ጊዜ፤ በከተማው የተሻለ ሆኖ የተገኘው የእኔ አጎት ምድርቤት ያለው የፎቅ (የደርብ) ቤት ነበር፡፡ አጎቴ አባ ይልማ ስንቄም፤ ቤታቸው ለልዕልቷ ማረፍያ እንዲሆን በአስተዳዳሪው ሲጠየቁ፤ በደስታ ለቀቁላቸው፡፡ ማረፍያቸውን ካስተካከሉ በኋላ፤ ልዕልት ሂሩት ሰባት ወይራ ሆቴል ተብሎ የሚጠራውን ማሰራት ጀመሩ፡፡

እንግዲህ ሆቴልን ያህል ስራ ሲታሰብ፤ ብዙ የተለያዩ ሙያ ያላቸው ሰራተኞች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለሆነም ብዛት ያላቸው ሰራተኞች ከላሊበላና ከአካባቢው ተቀጠሩ፡፡ በተጨማሪም ከሩቅ ቦታዎች፤ በተለይም ከትግራይና ከአዲስ አበባ ብዙ የሆቴል ስራ ባለሙያዎች ማለትም ግንበኞችና አናጺዎች ወደ ላሊበላ እንዲመጡ ተደረገ፡፡ ታዲያ ብዙ የሆቴል ሰራተኞች ወደ ላሊበላ ሲመጡ፤ የክራይ ቤቶችና የምግብ ቤቶች በብዛት መሰራት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም፤ ያች ቀዝቃዛ  የነበረችውና አዲሽአዴ የሚባል መዝናኛ ቦታ ብቻ የነበራት የላሊበላ ከተማ፤  ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች በብዛት እየተከፈቱ አገግልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ የሰባት ወይራ ሆቴል ስራም ካለቀ በኋላ፤ ከላሊበላና ከአካባቢው የተቀጠሩት ሰራተኞች፤ የሆቴሉ ቋሚ ሰራተኞች ሆነው ተቀጥረው ማገልግል ጀመሩ፡፡

በዚህ አጋጣሚ፤ ልዕልት ሂሩትን ስላጋጠሟቸውና ስለሰሯቸው ሎሎች ነገሮችም በመጠኑ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ልዕልት ሂሩት ሆቶሉን ለማሰራት ላሊበላ በመጡ ጊዜ፤ በጣም ወጣትና ቆንጆ ነበሩ፡፡ ይህንንም የተገነዘበ አንድ ሀብታም ነኝ የሚል የአካባቢው ኗሪ ሰው፤ ልዕልቷን እንጋባ የሚል ደብዳቤ ጽፎ፤ የልዕልቷ ጠባቂ ለነበሩ ሁለት የክብር ዘበኞች መልእክቱን እንዲያደርሱለት ይሰጣቸዋል፡፡ እነሱም ይህን ሰው “እንዴት ንቀት ቢኖረው ነው ልዕልቷን ላግባሽ ብሎ የሚጠይቀው” ብለው ሊገርፉት ማሰባቸውን ልዕልት ሂሩት ሰምተው፤ ለክቡር ዘበኞቹ የሰጧቸው መልስ የሚደንቅ ነበር፡፡ “እንዴ እኔ እኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ማንም ላግባሽ ብሎ እኔን መጠየቅ መብቱ ነው፡፡ ከፈለግኩ እሽ እለዋለሁ፤ ካልፈለግኩ ደግሞ አይሆንም እለዋለሁ” የሚል ነበር፡፡ የክብር ዘበኞችንም ይህን ስው ምንም ነገር እንዳያደርጉት ሲነግሯቸውና ሲቆጧቸው አስታውሳለሁ፡፡ ልዕልት ሂሩት እንደዚህ ያሉ መልካም ሰው ነበሩ፡፡

ከሆቴሉ ስራ ጋር ተያይዞ ብዙ መሰረተ ልማቶች በላሊበላ ከተማ ተከናውነዋል፡፡ በላሊበላ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ ለቤተክርስቲያናትና ለከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክቲሪክ መብራት ገባ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የቧንቧ ውሃ ገባ፡፡  የመኪና መንገድም ተሰራ፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያው በዘመናዊ ሁኔታ ተሰራ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ፤ የሌሎች ከተሞች ወግ ደረሳት፡፡የከተማውም ህዝብ ከስልጣኔ ጋር ተዋወቀ፡፡

ስለሆነም ለልዕልት ሂሩት እንደዚህ ተብሎ ተዘፈነ፡፡

እያረበረበች እያረበረበች

የእኔ ሂሩት ደስታ ላስታ ላይ ዘነበች፡፡

በሂሩት ደስታ

ተቀደሰች፤ ተባረከች ላስታ፡፡

ልዕልት ሂሩት ላሊበላ በቆዩባቸው ስድስት አመታት ውስጥ፤ አንዳንድ በአካባቢ የሚገኙትን ድንቅ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት ይጎበኙ ነበር፡፡ ለምሳሌ አሸተን ማርያምን፤ አቡነ ዮሴፍን፤ ናኩቶላብንና ይምርሀነ ከርስቶስን ጎብኝተዋል፡፡ ልዕልቷ በመጀመርያ የጎበኟት፤ የአሸተን ማርያምን ገዳም ነው፡፡ የአሸተን ማርያም ገዳም የተሰራችው፤ ከላሊበላ አጠገብ ከሚገኘው ተራራ ጫፍ ላይ ነው፡፡ በድሮ ዘመን፤ የገዳሟ አገልጋዮች ጸሎት የሚያደርጉት ሌሊትና ቀን ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን፤ የሆኑ መንገደኞች በዚያ ሲያልፉ፤ እጣን ይሽታቸዋል፡፡ በጣምም ተገርመው፤ የእጣኑን ሽታ እየተከተሉ ሲሄዱ ገዳሟ ውስጥ ይደርሳሉ፡፡ የገዳሟም አገልጋዮች ከመንገደኞች በሰሙት ነገር ተገርመው፤ ከዚያ ቀን በኋላ ገዳሟ አሸተን ማርያም ተባለች ይባላል፡፡

ልዕልት ሂሩት በሌላ ጊዜ ደግሞ የአቡነ ዮሴፍን ቤተክርስቲያን ጎበኝተዋል፡፡ አቡነ ዮሴፍ፤ ከአሸተን ማርያም፤ ከደጎሳይና ከመዳጌ በላይ ያለ ታላቅ ታሪካዊ ገዳም ነው፡፡ ከተራራው ከፍተኛነት የተነሳ፤ በአሁኑ ጊዜ ለአካባቢው ህዝብ አገልግሎት የሚሰጠው ሳተላይት የተሰቀለው እዚያ አካባቢ ነው፡፡ ልዕልት ሂሩት ወደ አቡነ ዮሴፍ ገዳም ሲሄዱ፤ እኔም ከሌሎች ሰዎች ጋር አብሮ የመሄድ እድል አግኝቸ ነበር፡፡ ልዕልቷ፤ ሞላ በሚባለው የሚያምር ቀይ ፈረሳቸው ላይ ሆነው፤ እኛ ደግሞ በእግራችን እየተጓዝን፤ ረዥምና አድካሚ የሆነውን መንገድ አቆራርጠን ወደማታ አካባቢ ደረስን፡፡ የገዳሙ አካባቢም ህዝብ፤ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎንና መስተንግዶ ካደረገልን በኋላ በድንኳኖቻችን ውስጥ አደርን፡፡ ገዳሙ የተሰየመው፤ አባ ዮሴፍ በሚባሉት የበቁ መነኩሴ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንድ ቀን አባ ዮሴፍ ከዋሻቸው ወጥተው ባሉበት ጊዜ፤ የአካባቢው ዝንጀሮ የህዝቡን አዝመራ እየበላ ማስቸገሩንና አርሶአደሮችም ዝንጀሮዎችን በድንጋይና በጩኧት ሲያባርሩ ያያሉ፡፡ እኒህም መነኩሴ፤ አርሶአደሩንና ዝንጀሮዎችን ማስማማት ፈልገው፤ የሚከተለውን ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ አርሶአደሮችን የመከሯቸው፤ እህል ስያጭዱና ሲሰበስቡ፤ መሬት የወደቀውን ከመልቀም ፋንታ፤ ለዝንጀሮዎች እንዲተዉ ሲሆን፤ ለዝንጀሮዎች የሰጧቸው ምክር ደግሞ፤ አዝመራ ከመታጨዱ በኋላ እንጂ ከዚያ በፊት ከአርሶአደሩ ማሳ እንዳይደርሱ ነበር፡፡ በአባ ዮሴፍም ምክር ሁለቱም ወገኖች ተስማምተውና ተከባብረው ኖሩ ይባላል፡፡ ይህን ገድል፤ ልዕልት ሂሩት ሲስሙ በጣም ተደንቀው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪኩን እንዲያውቀው አደርጋለሁ ብለው፤ ከግዕዝ ወደ አማሪኛ አስተረጉመውና አጽፈው፤ ወደ አዲስ አበባ መውሰዳቸውን አውቃለሁ፡፡

በአቡነ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን እሁድ ቀን ካስቀደስን በኋላ፤ ወደ ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አመራን፡፡ መቸም ይምርሀነ ክርስቶስ ስንደርስ ያየነውን ሁሉ ለመግለጽ በጣም ያዳግታል፡፡ ለምሳሌ ትልቅ የመቃብር ጉድጓድ ውስጥ፤ ብዙ የሆኑ፤ አፈር ያልበላቸው የሙታን አፅሞች ማየታችን አስደንቆኛል፡፡ ከሰአት በኋላ ስለደረስን፤ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ገብተን ለመሳለም ግን አልቻልንም፡፡ በሚቀጥለው ቀን፤ ቤተክርስቲያኑን ተሳልመንና ጎብኝተን ትንሽ እረፍት ካደረን በኋላ፤ በብልባላ ጊዮርጊስ በኩል አድርገን፤ ወደ ላሊበላ ጉዟችንን ጀመርን፡፡ ከብልባላ እስከ ደጎሳይ፤ መንገዱ ጥሩ ነበር፡፡ ከደጎሳይ በኋላ ያለው መንገድ ግን ዳገት ስለነበር፤ ለልዕልት ሂሩት የፈረስ ላይ ጉዞ እንኳን በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ የአስር አለቃ ክፈተው ሞላ የሚባል ክቡር ዘበኛና ሌሎች ሰዎች፤ ፈረሱን እየደገፉ እንደምን ብለን ዳገቱን ወጣነው፡፡ ላሊበላ አፋፉ ላይ ስንደርስ፤ የአካባቢው አስተዳዳሪ አቶ አበበ ስዩም፤ ባትሪ ይዘው በአጀብ ተቀበሉን፡፡ ስለቆየንም በጣም አስበው እንደነበረ ነገሩን፡፡ ከዚያም በሰላም ወደየቤታችን ገባን፡፡

ልዕልት ሂሩት ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳቸው በፊት የጎበኟት ቤተክርስቲያን ሸጎላ ማርያም ትባላለች፡፡ የሽጎላ ማርያም ቤተክርስቲያን ሀላፊ፤ ላሊበላ በመጡ ቁጥር፤ ልዕልት ሂሩትን ሁልጊዜ ወደዚያ መጥተው ታቦቷን እንዲሳለሙ ይጠይቋቸው ነበር፡፡ ሸጎላ ማርያም የምትገኘው፤ ከላሊበላ በስተምእራብ ሲሆን፤ የእኔን የትውልድ ቦታ ሰራብጥ ካህናተ ሰማይን አቋርጠን መሄድ ነበረብን፡፡ የሸጎላ ማርያም መንገድ ሜዳ ስለነበር፤ እንደሌሎቹ ቦታዎች ለጉዞ አስቸጋሪ አልነበረም፡፡

የሰባት ወይራ ሆቴል ስራ፤ ከስድስት አመታት በኋላ ተጠናቆ ካለቀ በኋላ፤ ልዕልት ሂሩት፤ ጃንሆይን ላሊበላ መጥተው ሆቴሉን እንዲመርቁላቸው ጠየቋቸው፡፡ ጃንሆይም ላሊበላ መጥተው፤ የልጅልጃቸው የደከሙበትን ሆቴል አድንቀው በየካቲት ወር በ1957 ዓ.ም መረቁላቸው፡፡ ልዕልት ሂሩትም፤ ሆቴሉ የቤተክርስትያናት መተዳደርያ እንዲሆን ወስነውና ለቅዱስ ላሊበላ ቤተክርስቲያናት አስተዳደር አስረክበው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ይህ ሆቴል፤ የቅዱስ ላሊበላ ቤተክርስቲያናት ንብረትና መተዳደርያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡

በመጨረሻም አንድ ሌላ የልዕልት ሂሩትን አብይና ቅን ስራ ልግለጽ፡፡ ልዕልቷ፤ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ዘጠኝ ወጣት ልጆችን፤ ከቤተሰቦቻቸው ፈቃድ ካገኙ በኋላ፤ አዲስ አበባ ወስደው እየረዱ ዘመናዊ ትምህርት አስተምረዋቸዋል፡፡ ከዘጠኙ ወጣቶች ውስጥ ስምንቱን አዳሪ ትምህርት ቤት አስገብተው ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ፤ ከዚያም ክቡር ጀኔራል ነጋ ተገኝን ሲያገቡ፤ ወደ ጎንደር ይዘዋቸው ሄደው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አድርገዋል፡፡ ከዘጠኙ ወጣቶች ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ምንም እንኳን ልዕልት ሂሩት ወደ አዲስ አበባ ቢያመጡኝም፤ በአንድ አጋጣሚ ደብረዘይት በልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ ግቢ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ አይተውኝና ወደውኝ፤ አዲስ አበባ ከወሰዱኝ በኋላ ትምህርቴን ያስተማሩኝ፤ እህታቸው ልዕልት ሰብለ ደስታና ባለቤታቸው ክቡር ደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም ናቸው፡፡

ታዲያ ይህን ሁሉ መልካም ስራ ለሰሩ ጥሩ ሴት፤ ላሊበላ ውስጥ የስማቸው መጠርያ አንድ ነገር መኖር ነበረበት፡፡ ግን እስካሁን የተደረገ ነገር የለም፡፡ መቸም የላሊበላ ህዝብ በዚህ ነገር ባይስብበት ነው እንጂ፤ በልዕልቷ ስም፤ አንድ አብይ ነገር ማድረግ ተስኖት አይደለምና እስቲ ይህችን ጽሁፍ ለማንበብ እድል ያገኛችሁ ሁሉ፤ አስቡበትና አንድ ቁም ነገር እንስራ፡፡ በእርግጥ፤ ልዕልት ሂሩት፤ የወጣትነት ጊዜአቸውንና ትዳር መያዝ የሚችሉባቸውን ስድስት አመታት ሰውተው፤ ይህን የመሰለ ቁም ነገር ላሊበላ ወስጥ የሰሩት፤ ጥቅም ወይም ዝና ፈልገው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ቢሆንም እኛ ደግሞ ውለታችንን ለመመለስ እንድንችል እናስብበት፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት በ1966 ዓ.ም ከፈነዳ በኋላ፤  ልዕልት ሂሩት፤ ከሌሎች ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር ለ17 አመታት፤ በደርግ በከርቸሌ ታስረው ተንገላቱ፡፡ በኢህአዴግ ጊዜ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ፤ በደርግ መንግስት ተወርሶ የነበረውን የሰባት ወይራ ሆቴል፤ በፍርድ ቤት ከሰውና ተከራክረው በእሳቸው ስም አስደርገው ካስመለሱት በኋላ፤ እንደገና ለቅዱስ ላሊበላ ቤተክርስቲያናት መተዳደርያ እንዲሆን አድርገውና ለቤተክርስቲያናቱ አስተዳደር አስረክበው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ከዚያም ወደ ታላቋ ብሪታንያ ሄደው በለንደን ከተማ ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ፤ በተወለዱ በ84 አመታቸው በ2006 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የእኒህን ቅድስት ሴት ነፍስ ቸሩ አምላክ ይማር!

6 Comments

  1. የሰው መልካም ሥራ ከመቃብር በላይ ይኖራል የሚባለው እንዲህ ያለው ተግባር ሲወሳ ነው። ይሁን እንጂ ከመከራ ወደ መከራ እየተላለፈች የምትሰጠው ውዲቱ ሃገራችን መልካም የሚሰሩ ሰዎች እያለፉ ክፉዎች ለጊዜውም ሲለመልሙ ማየት ከፈጣሪ ጋር ያጋጫል። ያም ሆነ ይህ የታሪኩ ጸሃፊ እንዳለው እኔም በቅርብ የማውቀው ሰው በጄ/ነጋ ተገኝና በልዕልት ሂሩት ደስታ ከተረድት አንድ ነው። አይ ጊዜ እንዲህ ይሻግት? በዘርና በጎሳ በቋንቋና በሃይማኖት ተከፋፍለን በድንጋይ ዘመን እንኑር?
    ሌላ አንድ እውነተኛ ታሪክ ልጨምርና ይብቃኝ። አንድ የገጠር ተማሪ በጣም ከድሃ ቤተሰብ በመሆኑ ሁሌ ወደ ገጠር በግሩ እየተጓዘ ስንቅ እያመላለሰ ይማራል። አንድ ቀን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አንድ በዛሬው አጠራር ኤርትራዊ ሰው ንፋስ ለመቀበል ከከተማ ወጣ ብለው ስለነበር በመንገድ ይገናኛሉ። መኪናቸውን አቁመው የት እየሄድክ ነው ይሉታል። ወደ ከተማ የ 10ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ ይላቸዋል። እሳቸውም ግባ ይሉና እያወሩ ወደ ከተማ ሲደርሱ የምኖረው እዚህ ነው እየመጣህ ጠይቀኝ ይሉታል። እሱም እጅ ነስቶ ሲመቸው እየሄደ እየጠየቃቸው ከቤተሰብ ጋር ሁሉ ተዋውቆ ሲኖር ማትሪክን ከፍተኛ ነጥብ አግኝቶ ህክምና ለመማር ይመርጣል። ያሰበውም ተሳክቶ ይማራል። በመመረቂያው ቀን እናትና አባቱ በህይወት ባለመኖራቸው እንደ ቤተሰብ ሆነው በሥፍራው ተገኝተው ያስመረቁትና በጎደለው ሁሉ የረድት እኝህ ኤርትራዊ ዛሬ በህይወት የሉም ሥራቸው ግን በከተማው ሁሉ የታወቀ ነበር። ያዘው ጥለፈው በለው ከማለት ይልቅ የምንችለውን ኢምንትም ቢሆን መልካም ነገር ሰርተን እንለፍ። የዘር ፓለቲካውን በሰውኛ እይታ እንተካው። በቃኝ!

    • ተስፋ ምን ሆንክብን? ያሳደጉህ አንተ ወደዚያው ልትሄድ ነው በህይወት የሉም ትላለህ እንዴ? ከልብህ ሁን እንጅ። ሰውየው በወቅቱ ከንጉሱ እኩል ሊሆኑ ይችላሉ ንጉሱ በህይወት የሉም የማለት ያህል ነው። ሞትን ሳትረሳ አልቀረህም

      • ወስላታ! ነገር አታማታ፡ ባለህበት አትርገጥ። ጊዜ እየሮጠ ነው።

    • ወንድሜ ተስፋ ምን ልል እንደፈለግሁ ስገባህና አንተም የምታዉቀዉን ስለአካፈልኸን ከልብ አመሰግናለሁ::ሁላችንም እምናዉቀዉ ብዙ መልካም ነገሰር አለ:: እንናገርዉና ሰዎ ይወቀዉ::

  2. Dear Anmut, This is a great memorial. We Ethiopians should learn a lot from your initiative and I hope a good memorial in the form of Statue may be erected in Lalibela for Princess Hirut.

  3. በእውነት ልብ ይነካል እግዚአብሄር የለም አልን መልካም ሰዎችን አጠፋን ቀጥሎ የመልካም እሴቶች መገለጫ ክፋት፣ጭካኔ፣የመዋእለ ንዋይ ፍቅር ሆነ ይህን ፕሮጀክት ለማስፈጸም ትግሬን ላከብን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Fano 2 2 1
Previous Story

ከአማራ ፋኖ በጎጃም፣ ከአማራ ፋኖ በጎንደር፣ ከአማራ ፋኖ በሸዋ ዕዝና ከምስራቅ አማራ ፋኖ የተሰጠ የጋራ መግለጫ 

190327
Next Story

ስለተከሰ-ከሰው ድሮን የተሰማው ምስጢር | ከፍተኛ የብልፅግና ሰው ተያዘ | ጎንደር ሰራዊቱ እያለቀ ነው |

Latest from Blog

blank

አርበኛ አስረስ ማረ እና ምርኮኞቹ | ስለ ፋኖ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ያልተጠበቀ ንግግር |

#ሰበር_ዜና #AmharaFano ➢መሰከረም 29/01/2017 ዓ.ምብዙ ድሎችን አግኝተናል፣➢1️⃣115 ምርኮኛ ➢2️⃣70 እስረኞችን አስለቅቀናል➢3️⃣ 7 ብሬን➢4️⃣2 ድሽቃ➢5️⃣ 4 ስናይፐሮችን➢ለትግል የሚጠቅሙ የነፍስ ወከፍ ክላሾችንተተኳሾችን መኪኖችም ገቢ… pic.twitter.com/GbYaOAtFtr — ትዝብቱ🔔 (@Geteriew1) October 12, 2024 በፋኖ የተማረኩት ኮሎኔል
blank

ትግሉ ይጥራ – ከጥሩነህ ግርማ

የህልውና ትግሉን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር የኦይዶሎጂ ብዥታን ማጥራትና በመሬት ላይ ያለውን ተንኮል መጋፈጥና ማፅዳት ያስፈልጋል የህልውና ትግሉ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ያጠነጠነ እንደመሆኑ የመኖር አለዚያም እንደ ህዝብ  የመጥፋት ትግል ነው: ሌላው ኢትዮዽያዊ ወገን
blank

የፋሽስቱ አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ላይ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ከመስከረም 13 እስከ 27/2017 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የደረሰ የጉዳት !!!መረጃ:

ሸዋ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መርሀቤቴ አውራጃ በደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ኮሉ በተባለ አካባቢ ላይ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከኦሆዴዱ ጥምር ጦር ጋር ቅንጅት በመፈጠር መስከረም 22 ቀን 2017ዒ.ም ከለሊቱ
Go toTop