የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበረዉ ታዬ ደንደአ በህግ ቁጥጥር ሥር ዋለ
ታህሣሥ 2/2016 (አዲስ ዋልታ) የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ፤ በህግ ቁጥጥር ስር የዋለዉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበረዉ ታዬ ደንደአ ከለውጡ በፊት የኦነግ አባል የነበረና በእስር ቤት የቆየ ሲሆን፤ የለውጡ መንግስት ባደረገለት ምህረት ከማረሚያ ቤት ተለቆ በተሰጠዉ እድል በተለያዩ የክልል እና የፌደራል መንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰራ ነበር ብሏል።
ይሁን እንጂ ታዬ ደንደአ ከህዝብና ከመንግስት የተሰጠዉን ኃላፊነት በተለይም ደግሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ ሰላምን ለማስፈን መሥራት ሲገባዉ፤ በተቃራኒዉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰራ ተደርሶበታል ብሏል መግለጫዉ።
መግለጫዉ አያይዞም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ በነበሩ የሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ እጁ እንዳለበት የተደረሰበት መሆኑን አስታዉቋል።
ይህንን እኩይ ዓላማ ሲያራምድ የነበረዉ ተጠርጣሪ ታዬ ደንደአ፤ በመንግስት ቁጥጥር ስር ሊዉል እንደሚችል ሲገምት ታጋይ ለመምሰል በራሱና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አፍራሽና ፀረ ሰላም ፅሁፎችን፣ ንግግሮችንና መግለጫዎችን በማን አለብኝነት ሲያስተላልፍና ሲሰጥ ቢቆይም ከተጠያቂነት ማምለጥ ባለመቻሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን መግለጫዉ አመልክቷል።
በተጨማሪም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንደገለፀዉ፥ ታዬ ደንደአ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ተቀብሎ እየሰራ በነበረበት ወቅት መንግስታዊና የፓርቲ መዋቅሩን በሴራ ለመናድ በህቡዕ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን በመረዳት ያላሰለሰ ጥናትና ክትትል ሲደረግበት ነበር ብሏል፡፡
በተደረገው ክትትልም ታዬ ደንደአ ከኦነግ ሸኔ አመራሮችና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግስትን በአመጽ፣ በሽብርና፣ በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴር እንደ ተደረሰበት መግለጫዉ ጠቁሟል፡፡
ተጠርጣሪዉ ታዬ ደንደአ በህግ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅትም በመኖሪያ ቤቱ ዉስጥ በተደረገ ፍተሻ፤ ግለሰቡ በህቡዕ ለሚያደርገዉ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ ሲገለገልባቸዉ የነበሩ የተለያዩ 9 ሞባይሎች፣ 4 ላፕቶፖች፣ 3 አይፖዶች፣ በርካታ ፍላሾች፣ 4 የተለያዩ ተሸከርካሪ ሰሌዳዎች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም የኦነግ ሸኔ አርማዎችና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ የኦነግ ሸኔ መታወቂያዎች፣ ሰነዶችና ማስታወሻዎች እንደተገኙ ግብረ-ኃይሉ በላከው መግለጫ አረጋግጧል፡፡
ከዚህም ባሻገር በብርበራ ወቅት በመኖሪያ ቤት ውስጥ በሶስት መታወቂያዎች የሚጠቀም አንድ የኦነግ ሸኔ አባል ተደብቆ መገኘቱንና በቁጥጥር ሥር መዋሉንም መግለጫዉ ጨምሮ ገልጿል።
ታዬ ደንደአ በተመደበበት ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ሆነ በተደጋጋሚ መንግስትን ገዳይና ጨፍጫፊ እያለ ሲወቅስ የሚደመጥ ቢሆንም፤ በተግባር ግን ከሽብርተኞች፣ ጽንፈኛችና ነፍሰ ገዳዮች ጋር የጥፋት ትስስር የነበረው ራሱ መሆኑ በተደረገ ክትትል መረጋገጡን የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል።
በመጨረሻም በመንግስትና በፖርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነዉ በተመሳሳይ እኩይ ዓላማ በተሰማሩ አካላት ላይ በጥናት የተመሰረተ ጥብቅ ክትትል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እያደረገባቸዉ እንደሚገኝና እንደአስፈላጊነቱ የሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎችን በተከታታይ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን መግለጫዉ አስታዉቋል።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
ታህሳስ 2/2016 ዓ.ም