November 3, 2023
49 mins read

የመለስ-ሌንጮ የዘጠኝ ክልል የውሸት ዲሞክራሲያዊ ፌደሬሽንና የቀሩት አገር-ክልል-የለሾቹ 74 ብሔር ብሔረሰቦች

ሰመረ በላይ

download 11ምፅዋትና በልመና የጦር መሳሪያ የአገዛዝ ስልጣን ለማቆየት የእርስ በእርስ ጦርነት እያፋፋሙ ለመግዛት ስለመረጡ፣ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ፣ ሰላምና ዕድገት እርቋታል:: ኦሮሞ መሩ የብልጽግና አገዛዝ ከወያኔ መሩ የኢህአዴግ አስከፊ ውድቀት መማር አለመቻሉ፣ ሁለተኛም በበጭፍን ወገናዊው የሁለት ጎሳ ሕገ መንግሥት ተብየው ውስጥ ለሕግ አፍራሽ ሹሞች ገዳቢ ተቋምና (constitutional court) የተጠያቂነት ድንጋጌም ባለመኖሩ፣ አገራችን እንደ ጋለሞታ ቤት ሕግና ስርአት አልባ ሆና የሕዝብ ውክልናም ሆነ ክብር በሌላቸው ቡድኖች በተከታታይ አመታት መፈንጫ መሆኗ የዛሬው አስከፊ ትርምስ መንስኤ ነው። የሕወሀትና ኦነግ መሪዎች የ UNITED KINGDOM፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ መስኮብ፣ አሜሪካና ሌሎችም ሀብታም መንግስታት ሁሉ በደምና አጥንት መገንባታቸውን ሳያገናዝቡ፣ ለአገር ግንባታ የተከፈለውን የአገራችንን የብዙ ሺ ዘመናት መስዋዕት ለግልና ለማያዛልቅ ጥቅም ሲሉ በመካድ፣ ቆምንለት ብለው የሚያታልሉትም ወገናቸው ሳይቀር አሳፋሪ ኋላ ቀርነታችን ሳይቆጫቸውና ሳያሳስባቸው፣ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መሆናችንም ተረስቶ፣ ደናቁርቱ ወደ 15ኛው ክፍለ ዘመን ሊመልሱን እየተውተረተሩ ነው።

 

የሕገ መንግሥት ክለሳ መነሳቱ ስለማይቀር፣ ይህ አስተያየት ለቅን ውይይት ተዘጋጅቷል። 32 ዓመት ሙሉ በውሸት የፌደራል ሕገ መንግሥት ስንገዛ ስለኖርን፣ ጉድለቱን በከፊል በመተንተን ያለፈውና የዛሬውም ፍዳችን እንዳይደገም ክለሳውን ለማጠናከር ይረዳ ይሆናል። ሕገ መንግሥት ተብየው ባለ-አገርነትም ሆነ ተጠያቂነት የሌለበት ለፈላጭ ቆራጭ ጠባብ የወያኔ አገዛዝ የተዘጋጀ ነው። በዲሞክራሲያዊ አገሮች የገዢ ፓርቲ ተጠያቂነት በሕገ መንግሥት ውስጥ ሲኖር፣ በተለይ የገዢው ፓርቲ ዋና ተቆጣጣሪው ሕዝብ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅርብ ሕጋዊ ተቆጣጣሪ ናቸው። በኢትዮጵያ ግን ይህን ሚና መጫወት እንዳለባቸው የሚረዱና የሚችሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሉም። ስለሆነም አገራችን በጎሣና በነፍጥ ላይ ተፈናጥጦ ሥልጣን ለያዘ ጠባብ አገዛዝ አመቺ በመደረጓ፣ ከሚነግድበት ጎሣ ውጭ ማሰብ በማይችልና ኋላ ቀርነት በማይቆጨው እየዳከረች ምን ጊዜም አድሮ ጥጃ ሆናለች ።

 

ሥልጡን የፖለቲካ ባሕል ሲኖርማ፣ በቅርቡ በእንግሊዝ (UNITED KINGDOM) ሁለት መምራት ያቃታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሮች በዓመት ውስጥ በፖለቲካ ሥርዓቱ አስገዳጅነት በተከታታይ ተባርረዋል። በአሜሪካም እአአ በ1974 ፕሬዚደንት ሪቻርድ ኒክሰን ሕገ መንግሥት በመጣሱ፣ ከፕሬዚደንትነት ተሰናብቷል። በእኛ አገር ግን መሪዎች ምንም ዓይነት የከፋና የከረፋ ወንጀል ቢሠሩም፣ ራሣቸው ኢዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት አርቅቀው በማጽደቃቸው ሊከሰሱና ሊወቀሱ ስለማይቻል አውሬ መሪም ተሸክመን መኖር ለምደናል። በዛሬው የወያኔ-ኦነግ ሕገ መንግሥት ተጠፍረንና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ትርጉም ያለው የፖለቲካ ኃይል የመሆን ተስፋ ስለማይታይባቸውና እስካልሆኑ ድረስ፣ ኢትዮጵያ በሰላምና እድገት ጠል አመራር እየደማች መቀጠሏ አይቀርም። ለአገርና ለወገን የሚያስቡ ፖለቲከኞችና የሚኒስትሮች ም/ቤት ቢኖሩንማ ኖሮ፣ ጃፓን በ19ኛው ክፍለ ዘመን በ30 አመት ውስጥ እንደበለጸገችው፣ ኢትዮጵያንም ባለፉት 32 ዓመታት መንጥቆ ከድህነትና ኋላቀርነት የሚያወጣ መንግስት እንመሠርት ነበር።

 

አኩሪ የነፃነት ታሪካችንን የማያውቁ ጎሰኞች ደጋግመው በፖለቲካው ማማ ላይ ተቀመጡና ዕጣ ፈንታችን የዛሬ 2000 ዓመት ባገኘነው የግብርና መሣሪያ እየጫርን መራብ፣ ራሳቸው በ V8 እየተንፈላሰሱና በምርጥ ቤተመንግሥት እየኖሩ ዛሬም ምርት ወደ ገበያ በቅምባ በእናቶች ጀርባ እየቀረበላቸው መብላቱ ከአመት አመት ሳይቀፍፋቸው ዶክቶርና ፕሮፌሶር የተባሉ ጉድ ጉድቅምጥሎች የሚመሯት ኢትዮጵያም በስንዴ ምዕዋትና በልመና ዶላር መኖሯን የአመራር መርህ አድርገውታል። ምናልባት የጎሣ ልሂቃኑም ለሕዝባችን ደህንነትና ዕድገት በጋራ መቆሙ ላይ ከተስማሙ፣ ወደፊት ሁላችንም ወደን ፈቅደን በምናሻሽለው ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግየሥት ላይ ተመሥርተን ፣ መከላከያንም ከቡድን ሥልጣን ጠባቂነትና ከመንደር ፖሊስነት ወደ አገራዊ መከታነት አሸጋግረን፣ የአገር ሰላም የሚጠበቅበትን ሕጋዊ ሥርዓት ከፈጠርን፣ እንደ ምዕራብያኑም፣ የማያሻማ የተጠያቂነት ድንጋጌና እድገትም ሊኖረን ይችላል።

 

የዛሬው ሕገ መንግሥታችን የሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች ስምምነት ያላገኘ፣ በተለይም አማራውን ከውሱኑ የሕወሀት-ኦነግ መር የ1983 ዲስኩርም ያገደ፣ ለአምባገነን የህወሀት-ኦነግ ጠባብ መሪዎች አገዛዝ እንዲያመች ሆኖ በጥቂት ሃፍረተ ቢስና የአገርና የወገን ፍቅር በሌላቸው የሕወሀትና የኦነግ መሪዎች ተረቅቆ የጸደቀና አገርአልባ ያደረገንም በመሆኑ፣ ከሥልጣን እስከ መሻርና ማሰር የሄደ የተጠያቂነት ድንጋጌ የለበትም። ስለሆነም፣የአገርን ሰላም አስጠብቆ ለማያቋርጥ ዕድገትም ለመብቃት፣ ባለአገር መሆናችንን ካረጋገጠ ሥርዓት ጋር የገለልተኛ ፍ/ቤት (INDEPENDENT CONSTITUTIONAL COURT) እና የ”ተጠያቂነት” ድንጋጌ በሁሉም ሕዝባችን ስምምነት በሚሻሻለው ሕገ መንግሥት ውስጥ ተጨማሪ አካል ሆነው፣ የሚከተሉትንም አንቀጾች ማስተካከልም ይጠቅማል፦ “ፌደራላዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ” የሚለው የውሸት ሐረግ መጠቀስ የጀመረው በአንቀጽ 1 ነው። በእውነተኛ ፌደራል አገሮች፣ እንደሚታየው፣ አንድ ሥርዓተ መንግሥት “ፌደራል“ ለመባል፣

 

የፌደራል ሥርዓተ መንግሥት ለመመሥረት በተስማማው ጠቅላላ ሕብረተሰብ ዘንድ የፌደራሉ አባል የሆኑት ንዑሳን መንግሥታት/አስተዳደሮች የነፍጠኛ ቡድኖች ምርኮኞች ስብስብ ሳይሆኑ፣ዳር ድንበራቸው በሁሉም ሕዝብ የታወቀና በአከላለላቸውም ላይ ምንም የወሰን ክርክር የሌለበት፣ የፌደራሉ መሪ ምን ጊዜም ንዑሳን መንግሥታትን የመምራትና የማዘዝ ስልጣን ሳይኖረው ሁሉም የራሳቸው ነፃና ዲሞክራሲያዊ መስተዳድር ያላቸው፣

 

መስተዳድራቸውም በዲሞክራሲያዊ የውክልና ሥርዓት የተመረጠና ለፌደራል ሥርዓት ምሥረታው ጉባዔ ሕጋዊ ወኪል መሰየም የቻሉና የጉባዔ ወኪሎቻቸውም በፌደራል ሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ጉባዔ ውስጥ በእኩልነት ተሳትፈው፣ የፌደራል ሕገ መንግሥት ረቂቅ ሲመጣላቸውም እያንዳንዱ ንዑስ መንግሥት/አስተዳደር ያለማንም ተጽዕኖ ረቂቁን ማጽደቅ ወይም መሻር የሚያስችል ሉዓላዊ ሥልጣን ያለው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተወከሉ አባላት ያሉበት ም/ቤት ሲኖራቸው ነው።

 

የእኛ ክልሎች ግን ሁለቱ ጦረኛ ቡድኖች፣ ሕወሀትና ኦነግ፣ የየራሳቸውን ፊውዳላዊ ግዛት ለማስፋት ሲሉ እንደ ተመኙት አገሪቱን ቆራርጠው የከለሉ በመሆኑና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርም የትም አካባቢ ተመሥርቶ ስለማያውቅ፣ ያልታወቀ ወሰን ካላቸው ክልሎች ሕዝብ እውቅናና ድጋፍ አላቸው በተባሉ ምልምሎችና ምርኮኞች ጭብጨባ ሕገ መንግሥቱም በነዚያው ሁለት ጦረኛ ቡድኖች የተረቀቀ በመሆኑና የጸደቀውም አንድም ዲሞክራሲያዊ ውክልና በሌላቸው ምልምሎች በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት “ፌደራላዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ” ን ለመመሥረት የበቃ አይደለም። ስለሆነም፣

ዋናው ችግራችን፦ (ሀ) ብዙ ወገናችንን አገርየለሽ ያደረጉት የክልሎችም ዳር ድንበር የጥቂቶቹ ነፍጠኞች ፈጠራ መሆኑ፣ (ለ) ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁትና ያጸደቁት፣ ዕውቅ አድራሻና ውክልና የሌላቸው የጦረኞቹ ምልምሎችና ምርኮኞች መሆናቸው፣ (ሐ) ተረቀቀ የተባለውም ሕገ መንግሥት በአንድም ታዋቂና ዲሞክራሲያዊ የክልል/መስተዳድር ስላልጸደቀ ሥርዓተ መንግሥታችን ፌደራልም ሆነ ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑ ነው። በጠመንጃ ኃይል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጫነና ለዛሬውም አገር አቀፍ ትርምስ ያበቃን የሁለት ሥልጣንና ሀብት ጥመኛ ቡድኖች ፈጠራ ነው። ሁለቱ ጦረኞች የፈለጉትን ለም አገር ሁሉ ለራሳቸው ክልለው ሁለት የተለጠጡ ክልሎች ለመግዛት ከተስማሙ በኋላ፣ ያገኙትን ነፃነትና የፈጠራ ክልል ባለቤትነት መብት ለቀሩት 81 በመንፈግ እስከ ዛሬም አገር-የለሽ አድርገዋቸው፣ ለነዚህ ለተፈረደባቸው ለቀሩት 81 ብሔሮችና ብሔረሰቦች 7 ተጨማሪ ክልሎችን ያለ ሕዝብ ፈቃድ በመከለል፣ በጠቅላላው ለ 83 ብሔሮችና ብሔረሰቦች በፈጠሯቸው 9 ክልሎች፣

 

1ኛ/ ቢበዛ 9 ጎሳዎችን አንግሰው የቀሩትን 74 ጎሳዎች አገር-የለሽ ከማድረጋቸው በላይ ዘጠኙም እንኳ በክለላው ባለመስማማታቸው የአማራ-ትግራይ፣ የአማራ-ቤኒሻንጉል፣ የአማራ-ኦሮሞ፣ የትግራይ-አፋር፣ የኦሮሞ-ደቡብ፣ የኦሮሞ-ሶማሊ፣ የሶማሊ-አፋር የወሰን ክርክርና ጦርነት ተፈጥሯል።

 

2ኛ/ ከ83 ብሔር ብሔረሰቦች መካከል, ክልል ያላቸው ቢበዛ 9 ብሐሮች ብቻ በመሆናቸው የቀሩት 74 ብሔር ብሔረሰቦች ወገኖቻችን ያለፈቃዳቸው በዘጠኙ ስር እንዲረገጡ ስለተከለሉ ፣ አገር እንደድሮው የጋራ መሆኑ ቀረና የዜግነት መብትም ሆነ ነፃነት ስለሌላቸው የራሳችን ክልል ይኑረን ጥያቄ አስከትሏል።

 

3ኛ/ ክልል ካላቸው ዘጠኙ ጎሣዎች ውጭ ያሉት ቢያንስ 74 ብሔር ብሔረሰቦች አገር-የለሽ መሆን፣ የ ”ቀዮች” እና “ የክልል ባለቤቶች” የሚለው ዓይነት የቤኒሻንጉል ክልል ድንጋጌ፣ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ለመፈናቀል፣ ለመሳደድ፣ ለጦርነትና ለሞትም ዳርጓል። በሺ የሚቆጠሩ ዘመናት የኖሩበትን አገራቸውን በወያኔ ነፍጥ የተቀሙትና አገር=የለሽ የተደረጉት የራያ፣ ወልቃይትና ሁመራም ሕዝብ እጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው።

 

እነዚህ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ነው እያሉ ለዘመናት ደም ሲያፈስሱ፣ ሲጮሁና ሲነግዱ የኖሩት ኦነግና ሕወሀት ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመመስረቱ ስልጣንና እድል እጃቸው ላይ ሲወድቅ፣ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ በሚለው የስግብግብ መርህ በመጠመቃቸው ምርጫቸው ብዙሀኑን ዜጎች አገር-የለሽ ያደረገ ጸረ ዲሞክራሲ ክለላና የውሸት ሕገ መንግስት መፈብረክ ሆነ። ቀድሞውንም ደጉን የትግራይና የኦሮሞን ሕዝብ ሲያታልሉ ነው እንጂ የዘመናት የመብት ጫጫታቸው የውሸት እንደነበረ በፌደራልና በየክልላቸውም በራሳቸው ሕዝብ መፈናቀል፣ ስደትና ሞት መጥለቅለቅ እንደማይቸገሩ ታይቷል ።

 

በአንቀጽ 45 እንደተጻፈው፣ ሲጀመር ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ ውክልናና ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ስለሌሉን ሁሉም የፓርላማ አባላት ሕዝብን የማይወክሉ፣ ተጠያቂነት የሌለባቸው፣ በእኩልነት ተወያይተውም መወሰን የማይችሉ በመሆናቸው የአገር መሪም ሆነ ሚኒስትር የመምረጥ ስልጣን የላቸውም፣ እኩልነትና ነፃነትም ስለሌሉ ሥርዓተ መንግሥቱም ፓርላሜንታዊም አይደለም። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትርና የሚኒስትሮች ም/ቤት ሕጋዊ ስልጣን የላቸውም። የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ድንጋጌዎች ከዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ድንጋጌዎች የተገለበጡ በመሆናቸው እንከናቸው ባይበዛም፣ የቀሩት ብዙ ድንጋጌዎችን ግን ለ32 ዓመት ብንሸከማቸውም፣ የአንዳንዶችን አንቀጾች አስከፊ ድክመት እንደሚከተለው መተቸት ይቻላል።

 

አንቀጽ 47(1)፣ የፌደራል መንግሥት አባላት ከቁጥር 1 እስከ 6 እና በቁጥር 9 ላይ ያሉት ያለአግባብ አንዳንድ ሕዝብ የሚኖርባቸው ሲያስመስል፣ በቁጥር 7 እና 8 ያሉት ብዙ ሕዝቦች ያሏቸው ናቸው ይላል። የ83 ጎሣዎች አገር በ9 ክልል ሸንሽኖ በዘጠኝ ጎሣዎች ብቻ እንዲመሩ መደንገጉ፣ የወያኔንና የኦነግን ክልል ፈጣሪዎችና ሕገ መንግስት አጽዳቂዎች ጠባብነት፣ አይን አውጣነት፣ ራስ ወዳድነትና ዲሞክራሲ ጠልነት ምስክር ነው።

 

እንደሚታወቀው፣ በኦሮሚያ ከ 75 በላይ ጎሣዎች፣ በአማራ ከ55 በላይ ጎሣዎች፣ በሌሎችም ብዙ ጎሳዎች ያሏቸው 9 ክልሎች ፈብርኮ በእያንዳንዳቸው ውስጥ አያሌ ብሔሮች መኖራቸው እየታወቀና ብዙሀኑን 74 ጎሳዎች ለ 9 ምርጥ ጎሳዎች ተገዥና አገር-የለሽ አድርጎ በአንቀጽ 8(1) ላይ “ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ብሎ ማታለሉ የሁለቱን ጦረኛ ቡድኖች ( አርቃቂ፣ አጽዳቂና የክልል ብዛትና ዳር ድንበር ፈጣሪም ወያኔና ኦነግ ብቻ ስለነበሩ።) አይን አውጣነትና ጭፍን ራስ ወዳድነት ጠቋሚ ነው።

 

በአንቀጽ 8(2) ላይም “ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸ ው መግለጫ ነው።” ማለቱ ምንም ድምጽ ባልነበራቸው 81 ብሔር ብሄረሰቦች መብትና በ74 አገር- የለሽ ጎሳዎችም ላይ ማፌዝና የሁለቱን ነፍጠኛ ቡድኖች የንቀት አመለካከትና የስግብግብነት ልክ ጠቋሚ ነው። በአንቀጽ 47(4) የዘጠኙ ክልሎች ገዢ ብሔሮች (ኦሮሞ፣ ጋምቤላ፣ አማራ፣ ሶማሊ፣ ትግሬ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐራሪ፣ አፋር) እኩል መብትና ሥልጣን አላቸው ብሎ ሲደነግግ፣ ክልል የሌላቸው የቀሩት 74 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከዘጠኙ ክልሎች እኩል የሆነ መብትና ሥልጣን እንደሌላቸውም ይህ ሕገ መንግሥት ደንግጓል። ለምሳሌ፣ በኦሮሚያ ክልል ስር ያሉት ከ 75 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከኦሮምኛ ቋንቋና ከኦሮሞ ባህል ውጭ ሌላ ቋንቋና ባህል የለም ተብለው ታፍነው እንዴት ነው በአንቀጽ 8(1) ላይ 83“የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔርተሰቦች፣ ሕዝቦች

 

የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ሊባል የሚችለው ? ንቀት ነው ወይስ ድንቍርና ወይስ እውር እብሪት?

 

ዛሬ ያለው ትርምስ ዋና መንስኤ ሁለቱን ፈላጭ ቆራጭ ጎሣዎችን የበላይና የአገር ባለመብት፣ የቀሩትን ብዙሀኑን የበታችና መብት የለሽ አድርጎ የደነገገውና የኢትዮጵያውያን ሁሉ እኩልነት፣ ሌላው ቀርቶ በሕገ መንግሥትም ደረጃም የሌለ፣ ቢበዛ ጥቂት ጎሣዎችን ያነገሠ ሥርዓተ መንግሥት ስላለን ነው። ይህን በደል ሳንወድ በግድ ተሸክመን 32 ዓመት መዝለቃችን እልበቃ ብሎ ዛሬም ይህን ጎደሎ ሕገ መንግስት ያረቀቁትና ያጸደቁት የህወሃትና የኦነግ ዲቃላዎች ይህ በድፍን አገራችን ፣ በትግራይና በኦሮሞም ድሀ ላይ የተፈጸመ ሕገ መንግስታዊ በደል እንዲቀጥል ድርቅ ብለው ይወተውታሉ:: የረሱት ግን ከእንግዴህ ወዲያ፣ 74 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አሽከር አድርገው የኦሮሞና ትግሬ ልሂቃን ሊገዙ እንደማይችሉ አለመረዳታቸው ነው። ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር፣ እኩልነትን ፣ዲሞክራሲና ልማትን ለማስፈን ቆርጠው ተነስተዋል።

 

በአንቀጽ 46(2) ላይ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው።” ቢባልም ይህ አንድም ቦታ ያልተተገበረ ድንጋጌ ዛሬም የደቡብ ኢትዮጵያ ወገኖቻችንም ክልል የመመሥረት ጥያቄ ደጋግመው ሲያቀርቡ፣ በተለይም ወላይታና ጉራጌ የተሰጣቸው መልስ ሞትና እስራት ነው። በአንቀጽ 48(1) ላይም የወሰን ክርክር ሲነሳ መፍትሔ በ 2 ዓመት ውስጥ እንደሚሰጥ በአንቀጽ 48(2) ቢደነገግም፣ የወልቃይት፣ ጠገዴና የራያ ሕዝብ ፍላጎትና መብት በወራሪውና በሕገ መንግሥት አርቃቂና አጽዳቂው እብሪተኛ ቡድን ዳኝነት ፍትህ ተጨፍልቆ ውሳኔ ባለመገኘቱ፣ ለዛሬው የአገር ትርምስና እልቂት አንዱ መነሻ ሆኗል። ስለሆነም የፌደሬሽን ም/ቤት የሕገ መንግሥቱ ጥሰት ማእከል በመሆኑ፣ ተጠያቂ እንዲሆን ድንጋጌም ባለመኖሩ፣ ችግሩ ለ32 ዘመናት አብሮን ኖሯል።

 

አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ ሆነና፣ የፌደሬሽን ም/ቤት አባላት ሕገ መንግሥቱን ጥሰው አንቀጽ 48(1) በራሳቸው ላይ መተግበሩን ስለማይቀበሉ፣ በፌደሬሽን ም/ቤት የወያኔና የኦነግ እብሪተኛ አባላት ወሳኝ ድምጽ ያላቸው በሆኑበት የሕዝብ ጥያቄ ተደጋግሞ ቢቀርብም፣ ጥያቄው ወደ ጎን በመገፋቱ፣ የሕዝብ ጥያቄ ፍትሐዊ ውሳኔ ሊያገኝ አልቻለም። ይህን ሕገ መንግሥት ሲጀመር ጀምሮ የጣሰው ክልል ዳኛ ሆኖ የሚቀመጥበት ም/ቤት ለወቅቱ ሰላም መጥፋት አንዱ ዋና ምክንያት በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48(1) ሊተገበር ስላልቻለ፣ የፌደሬሽን ም/ቤት ሥልጣንና አባልነት እንደገና በጥንቃቄ ሊጠናና ሊስተካከል የሚገባው ነው። በዚህ ላይ፣ አዲስ አበባና ድሪዳዋም በምክር ቤቱ አልተወከሉም።

 

አንቀጽ 49 ስለ አዲስ አበባ የተደነገገ ሲሆን፣ አንቀጽ 49(5) ከኦሮሚያ ጋር በሀብት አጠቃቀምና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ድንጋጌ በእብሪት ተጣምሞ በኦሮሞ አገዛዙ ተተርጉሞ፣ ዛሬ ዛሬ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ከተማ ነች በማለትም የኦሮሞ ርዕሰ መስተዳድርም መስተዳደራቸውን በከተማዋ ውስጥ አደላድለው፣ ቤተ መንግስትም በመገንባት ላይ ሆነው፣ ከተማዋ የፌደራል ርዕሰ ከተማ ብቻ ሳትሆን የኦሮሚያም ዋና ከተማ ተብላ የታወቀ ስሟንም እንኳ የመቀየር ፍላጎት አለ። በዚህ ላይ፣ በተከታታይ ዓመታት የኦሮሚያ ገዢ መደብ አባል ከንቲባ ሆኖ መሾሙና በፌደራል ጠቅላይ ሚኒስትርም በመመራቷ፣ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሽታ እንዲርቃትና የኦሮሚያ ገዢዎች እብሪት እንዲነግስባት ተደርጓል። የሁላችንን የጋራ ከተማ እንደ ግል የኦሮሞ ንብረት በመቁጠር የጎሳ ት/ቤቶችና ቤተ መንግስትም እየገነቡ ነው። በአንቀጽ 47(4)እውቅና የተነፈጋት ከፌደራል ዋና ከተማነት ወደ ክልል ከተማነት ለመለወጥ ይሆን ?

 

በተሻለ የኢዲስ አበባ የጤናና የንፁህ ውሀ አገልግሎት፣ በተሻሉ ት/ቤቶች፣ በስልክና ኢንተርኔት፣ በብዙሀኑ ባንኮች፣ በመንገድና ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በሰፊ የግብርና ምርት ገበያ አገልግሎትና በፌደራል መንግሥት ማዕከል ቅርበቷም ከማንም ክልል የበለጠ ተጠቃሚ ብትሆንም፣ ኦሮሚያ ክልል አልጠግብ ባይ ሆነችና ከተማዋም የኔ ነች እስከማለት በመድረሷ፣ ይህን ጥቅም ከማያገኙትና ለዕድገቷ በድምር ከኦሮሚያ ይበልጥ ከሚያዋጡት ሌሎች ክልሎች ሕዝቦች ጋር ሊያግባባት አልቻለም።

 

የኢትዮጵያ 83 ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦች ከተማ ከመሆኗ ጋር በኦሮሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን መሪነትና ሿሚነት የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አመራር አባል ከንቲባ ሆነው ያለምንም ይሉንታ በኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እብሪት የምትገዛ ከተማ ሆናለች ። ስለሆነም፣ ርዕሰ ከተማችን የፌደራል መንግሥትም ሕገ መንግሥቱን ያላከበረበትና የብዙ ግጭት መንስዔ አንዷ ማዕከል ነች። የከተማዋን ችግር ያባባሰው የከተማው የበላይ ተቆጣጣሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሮሞ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት የሚያደርጉት ከንቲባዋና የፖሊስ አዛዥም ኦሮሞ መሆንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኦሮሞ ብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ አባል መሆናቸው ከተማዋ ገለልተኛና ለከተማው ሕዝብ ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር የላትም። እንደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ አገሮች የተጠያቂነት ድንጋጌ ቢኖረን ኖሮ የኦነግንና የወያኔን ግብስብስ ሕገ መንግስት ተብየ በመጣሳቸው ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከንቲባዋም እንደ ቦሪስ ጆንሰን ቢያንስ ከስልጣን በራሳቸውም ፓርቲ ይባረሩ ነበር::

 

አንቀጽ 50 ስለ ሥልጣን አካላት አወቃቀር ሲደነግግ ፣ የክልል ም/ቤት የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል ነው ካለ በኋላ፣ በተግባር ግን የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመለመለው ርዕሰ መስተዳድሩ ሆኖ ይታያል። በአንድ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩም አለቃቸውን ፓርላማውን ሊጠይቀኝ አይችልም ማለታቸው የሚታወስ ነው። ዶ/ር ይልቃል ከፋለ መከላከያ ወደ ክልሉ እንዲገባ ሲጠይቁ የክልል ም/ቤቱን ሉዓላዊ ሥልጣን የቀሙ ይመስላል። የክልል ም/ቤትም በአንቀጽ 50(5) መሠረት የክልል ሕግ ማርቀቅና ማጽደቅ ሲገባው፣ ብዙ ክልሎች የተጠቀሙት በአንቀጽ 52(2)(ለ) መሠረት በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ የሆነ የክልል ሕገ መንግሥት በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ሲያረቅቁና ሲያጸድቁ፣ ሕግ መንግሥት መጣሱን የሚያግድ ፓርላማ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ድንጋጌ የለም። ስለሆነም፣ አገሪቱ በአንድ ሕገ መንግሥት ሥር መተዳደሯ ቀርቶ፣ ተማርን የሚሉ የጎሣ ሹሞች በፈለጉት መልክ በቀረጹት ሕግ አገር መምራታቸው ሌላው የወቅቱ የሀገር ትርምስ መንስኤ ነው። በእርግጥ የተማረና አገር ወዳድ ዜጋ ቢመራን ኖሮማ የዛሬው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዲሁም የወንድማማቾች የእርስ በእርስ መተላለቅ መፈናቀል ሞትና ውርደት ቀርቶ ባለፉት 32 አመታት አገራችን ተባብራ ብትሰራ ትበለጽግ ነበር ።

 

በክልል የጸጥታ መደፍረስ ሲከሰትና ሕገ መንግሥት ሲጣስ፣ (ሀ) በአንቀጽ 51(14) መሠረት በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ የፌደራል መንግሥት የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፣ (ለ) በአንቀጽ 55(16) የተወካዮች ም/ቤትና የፌደሬሽን ም/ቤት በጋራ በወሰኑት መሠረት ለክልሉ ም/ቤት መመሪያ ይሰጣል፣ (ሐ) በአንቀጽ 62(9) የፌደሬሽን ም/ቤት ብቻውን የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል የሚሉት የተለያዩ ዝብርቅርቅ ድንጋጌዎች አሉ ። በክልል ም/ቤት ጥያቄስ መከላከያ ገብቶ ከራሱ ሕዝብ ጋር ምንና እንዴት ዓይነት የፖሊስ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ካልተወሰነና አቶሚክ ቦምብም ካለው በራሱ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ መወርወር ከተፈቀደለት፣ የገዢው ፓርቲ/ቡድን የሥልጣን ግብግብ የትግል መሣሪያ ሊሆን ይችላል። የአሜሪካና የ UK ገዢ ፓርቲዎች ዛሬ ላይ ከፍተኛ ግብግብ በየክፍለ ሀገሩ ይታይባቸዋል፣ በቀበሌ ሰላም ቢነሱና ሕገ መንግሥትም ቢጥሱ፣ ዳር ድንበር ጠባቂው መከላከያ፤ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብልጽግና እንደተደረገው፤ የራሱን ታማኝ ዜጋ ለመግደል ለአገር መከላከያ የተገዛለትን ከባድ መሳሪያ ደግኖ ወገኑን እንዲያድን አይፈቀድም። የኢትዮጵያ ትርምስ መነሻው ከሕገ መንግስቱ ኢዲሞክራሲያዊነት ጀምሮ ማዕከላዊ መንግሥቱም ራሱም ሕገ መንግሥቱን ባለማክበሩና የዜጎች መብት በየቀበሌው ያለከልካይና ተጠያቂነት መጣሱ ነው።

 

አንቀጽ 52 የክልል ሥልጣንና ተግባር ድንጋጌ ሲሆን፣ አንቀጽ 52(2)(ለ)፣ አንቀጽ 52(2)(ሐ) እና 52(2)(ሰ) ሳይከበሩ ለዘመናት ቆይተዋል። የፌደራል መንግሥት ስንዴ ዝሩ ካለ፣ ሁሉም ክልል ስንዴ ይዘራል፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ክልሉ ፖሊስ ያቋቁማል ብሎ ቢደነግግም፣ የፌደራል መንግሥቱ የክልሉን የተለየ ባህል፣ ችግርና የደህንነት ስጋት ሳያመዛዝንና ሚዛናዊ አገር አቀፍ አፈጻጸምም ሳይኖረው፣ በአንቀጽ 50(8) እና በአንቀጽ 52(2)(ሰ) የተደነገገውን የክልሎችን ሥልጣን በመጣስ፣ የፖሊስ አደረጃጀት መመሪያ ለየክልሎች መስጠቱ ከፌደራልነትም ሆነ ከዲሞክራሲያዊነት ጋር አይጣጣምም። አንቀጽ 52(2)(ሀ) ላይ “… የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል …” ይበል እንጂ፣ የክልል ሕገ መንግሥት የፌደራል ሕገ መንግሥቱን መጣሱ ገና ከፌደሬሽን ምሥረታው ጀምሮ እየታየ፣ ዜጎች በብዙ ክልሎች በማንነታቸው ሲታረዱ፣ ሲታፈኑ፣ ሴቶች ሲደፈሩ፣ ሲፈናቀሉና ሲሳደዱ፣ የፌደራል መንግሥቱ የአንቀጽ 51(1) ኃላፊነቱን ባለማክበሩ፣ በዛሬው ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ገብተናል። ይህ ችግር የመጣው የመንግሥት አካላት ተጠያቂነት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ስለሌለም ነው።

አንቀጽ 55 የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሥልጣንና ተግባር ድንጋጌ ሲሆን፣ በአንቀጽ 55(9) የተወካዮች ም/ቤት የጦርነት አዋጅ ያወጣል ቢልም፣ ጦርነቱ ከአዋጁ የሚቀድም ይመስላል።

በአንቀጽ 55(10) የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ፖሊሲ የማውጣት ሥልጣን ሲኖረው፣ ይበልጥ ከባድ የሆነው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመቅረጽ ሥልጣን በአንቀጽ 77(8) ለሚኒስትሮች ም/ቤት መሰጠቱ የውጭ ግንኙነታችንን ክብደት ያቃለለና አደገኛም ድንግጋጌ ነው።

 

በአንቀጽ 55(7) የሰብአዊ መብትና የሀገር ደህንነት ጥሰት እንዲቆምና በአንቀጽ 55(16) ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ሲያቅታቸው እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ቢኖረውም በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉልና በደቡብ ችግሩ ሲከስት እርምጃ አለመውሰዱ ለሰላም መናጋት አበርክቷል።

 

ንዑስ አንቀጽ 16፣ 17 እና 18 ለስም ይኑሩ እንጂ፣ ተግባር ላይ ውለው አያውቁም። በአንቀጽ 55(17) እና አንቀጽ 55(18) የተወካዮች ም/ቤት ሹሞችን የመጠየቅ ሥልጣን ቢሰጠውም፣ ሕገ መንግሥቱም እንዲከበር በአንቀጽ 12(2)፣ 50(8)፣ 51(1)፣ 62(9)፣ 74(13) እና 77(9) ቢደነገግም፣ በአንቀጽ 50(3) እና በዚህ አንቀጽ 55 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥትን የሕግ ጥሰት ሊቆጣጠር አልሞከረም። እነዚህ አንቀጾች፣ 55(17) እና 55(18)፣ የመጠየቅ እንጂ፣ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ መቅጫ ሥርዓት ስላልደነገጉ፣ የሕግ አስፈጻሚው ዘርፍ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ እንዳልሆነ ብዙ ምሣሌ ማንሳት ይቻላል።

 

በክልሎች የንፁሐን ግድያ ሲበረክት፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ሲሄድ፣ የክልሎች ሕገ መንግሥቶች ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ያልተጣጣሙ ሲሆኑና ሕገ መንግሥቱን ሲጥሱ፣ ፍ/ቤት የለቀቀውን ፖሊስ መልሶ ሲያስር፣ የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ክልል ሲመራና ሲሾም ፣ የብሔር ብሔረ ሰቦች ራስን በራስ ማስተዳደር መብት በወላይታና በጉራጌ ዞንና በብዙ ክልሎች ሲጣስ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የበላይ ሥልጣኑን አልተጠቀመበትም። አንድ ሹም ሕገ መንግሥት ቢጥስ ወይም ባያስከብር እንደሚባረርና ከዚያም ለፍርድ እንደሚቀርብ ቢደነገግ ኖሮ፣ የዛሬ ደም መፋሰስና ሌሎች ብዙ ችግሮቻችን አይኖሩም ነበር።

 

አንቀጽ 61 ስለ ፌደሬሽን ም/ቤት አባላት ኢዲምክራሲያዊ አመጣጥ ይደነግግና፣ በአንቀጽ 62 የፌደሬሽንን ም/ቤት ሥልጣንና ተግባር በመወሰን፣ ይህ የሕዝብ ውክልና የሌለው ጥርቅም፣

1ኛ/ በአንቀጽ 48(1) የወሰን ክርክር የመወሰን ሥልጣን አለው፣ ግን በአንቀጽ 48(2) በ2 ዓመት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ቢባልም፣ ለዘመናት አልወሰነም። አማራጭ ድንጋጌም የለም። በአንቀጽ 62(6) ላይም ለክልሎች አለመግባባቶች መፍትሔ ይፈልጋል ተብሎም፣ በአያሌ ክልሎች መካከል ለተፈጠሩ አለመግባባቶች ከፌደሬሽን ም/ቤት መፍትሔ መጥቶ አልታየም። ችግሩ አጥፊው ዳኛ መሆኑ ነው ። ስለሆነም፣ የሚጠራቀም አለመግባባት ፈጥሯል።

 

2ኛ/ በአንቀጽ 83(1) መሠረትም የሕገ መንግስቱም ተርጓሚ ነው። አባላቱ የሕግ ጥሰት ማእከል ሆነው የሙያ ብቃትና የወገናዊነት ችግር ቢኖርባቸውም የሕግ ተርጓሚና ዳኛም በመሆናቸው፣ እንዲሁም በአብዛኛው የሕጉም ጥሰት ደራሲ በመሆናቸው ከባድ የፍትሐዊነት ጥያቄ ይነሳበታል።

 

3ኛ/ የፍትሐብሔርን ሕግ ተፈላጊነት ወስኖ ለሕግ አውጪው የመጠቆም ሥልጣንም አለው።

 

4ኛ/ በሕዝብ ተመረጠ ተብሎ በአንቀጽ 50(3) የመንግሥቱ የበላይ አካል ነው የተባለለት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቶበት፣ በአንቀጽ 62(9) አንድ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ፣ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚያዝዘው በሕዝብ ያልተመረጠውና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለው ክልል ያለበት የርዕሳነ መስተዳድሮች ምልምል ስብስብ የሆነው የፌደሬሽን ም/ቤት ነው። ርዕሳነ መስተዳድሮች ችግሩን ራሳቸው ፈጥረው፣ በራሳቸው ላይ ይፈርዳሉ ብሎ መጠበቅ በአገርና በሕዝብ መቀለድ ነው። መንግሥታዊ ሥርዓቱ ብዙ ፈተና ቢደርስበትም፣ ይህ ድንጋጌ ተተግብሮ አያውቅም።

 

የድንጋጌ አንቀጽ 62(9) አስፈጻሚዎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በመሆናቸው በራሳቸው ላይ ስለማይፈርዱ፣ አንዱ በሌላው ጉዳይ ሳይገባ ክልላቸውን እንደፈለጉ ረግጠው እንዲገዙና የክልል ትርምስ እንዲሰፍን ማድረጋቸው በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአማራና በደቡብም እየታየ ነው። ይህን ቁልፍ ሥልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ም/ቤትም ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መተራመስ አንዱ ዋና ተጠያቂ የመንግስት አካል ነው።

 

በአንቀጽ 74(13) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል ያለው ድንጋጌ ተከበረ ለማለት አይቻልም። በአንቀጽ 77(9) የሚኒስትሮች ም/ቤት ሕግና ሥርዓት መከበሩን ያረጋግጣል ያለውም ተፈጻሚ ሆኖ አያውቅም። ይህም ችግር መሰረቱ ተጠያቂነት አለመኖሩ ነው።

 

አንቀጽ 82(2) የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን አባላት ይወስናል። የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንትና ምክትሉ በሰብሳቢነትና ምክትል ሰብሳቢነት፣ ከፌደሬሽን ም/ቤት 3፣ ከሕግ አውጪው 6፣ በጠቅላላው 11 አባላት አሉበት ። ብዙሀኑ.ከሕግ አውጪው ስለሆኑ ያወጡትን ሕግ ተርጉሙ እየተባሉ ነው። ከፌደሬሽን ም/ቤት የመጡት ምናልባትም የሕጉ ጥሰት የሚመለከታቸው ክልላት መሪዎች ወይም ረዳቶቻቸው ናቸው። ሁሉም የአንድ ፓርቲ ስዩማን ሲሆኑ ደግሞ የሕገ መንግሥት ትርጓሜው ቀልድ ይሆናል።

 

ማጠቃለያ፦

ዋናው የአገራችን ችግር፦ 1ኛ/ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ካለፉት 6 የሽንፈት ምርጫ ተብየዎች ባለመማር የሕብረት ቅንቅን በልቷቸው፣ በማንኛውም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚደረገው፣ ገዢውን ፓርቲ መቆጣጠር አለመቻላቸው፣ 2ኛ/ ሕገ መንግሥቱ የሁለት ጦረኞች የቡድን ጥቅም ማስጠበቂያ በመሆኑ የፌደራልም ሆነ የዲሞክራሲ ሽታ ስለሌለበት፣ 3ኛ/ ለዘጠኙ ብሔር ብሔረሰቦች ፈላጭ ቆራጭ የሆኑበት ክልል ሰጥቶ 74 ብሔር ብሔረሰቦችን አገር-የለሽ ያደረገው የክልል ስርአት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል ባለ አገር ባለማድረጉ፣ 4ኛ/ የሚኒስትሮች ም/ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ የፌደሬሽን ም/ቤት፣ የክልል ም/ቤቶችና በጠቅላላ የአገሪቱ ተቋማት ሹማምንት ሕገ መንግስት ተብየውን ስለማያከብሩና ስለማያስከብሩ፣ 5ኛ/ ሕገ መንግስት ሲጣስ የሚዳኝ እንደ ፌደሬሽን ም/ቤት የምልምል ስብስብ ተከሳሽና ዳኛ የሆነበት ሳይሆን ገለልተኛ (INDEPENDENT) የባለሙያ የዳኝነት ተቋም (constitutional court) ባለመኖሩ፣ 6ኛ/ ሹሞቻችን እንደ አሜሪካና አውሮጳ ሹሞች፣ ከሥልጣን የመባረርና የመከሰስ ተጠያቂነት ስለሌለባቸው በሕዝብ የተሰጣቸውን የአደራ ሥልጣን ያለምንም የቅጣት ስጋትና የሕዝብ አክብሮት ስለሚጠቀሙበት ነው። ስለሆነም የዛሬው ገዢ ፓርቲ ፍጹም ወገናዊና አገር-አልባ ያደረገንን ሕገ መንግስት ተብየውን ም ማክበርና ማስከበር ስላልቻለ በሽግግር መንግስት ተተክቶ፣ የሙሉ ሕዝባችን እኩል ተሳትፎና ስምምነት ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርአት መመስረት ይገባል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ። የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ የሐዘን መግለጫ ታጋይ ይሰዋል ትግል ይቀጥላል !

January 22, 2025
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ “ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና

ጀልባዋ አትሰምጥም፤ የሚሰምጥ ግን አለ!

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] (https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/) ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

Go toTop