‹‹… ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል፤››
(ጌታችንና አምላካችን፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእስራኤል ከተናገረው ቃል)
የዓለማችን፤ የምድራችን የፖለቲካ ትኩሳት ‹የስበት ማእከል› ተደርጎ በሚቆጠረው በመካከለኛው ምሥራቅ- ጽዮናዊቷ እስራኤልና ሐማስ የገበቡበት ጦርነት/እልቂት የብዙዎችን ስሜት ሰቅዞ እንደያዘ ነው፡፡ በዛ ስፍራ ስለሆነውና እየሆነ ስላለው ነገር ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ያለመታከት በየሰዓቱና በየደቂቃው ዜናዎችንና ትንታኔዎችን እንደ ዶፍ እያዘነቡብን ነው፡፡ (መቼም ጉዳዩ የአፍሪቃ ቢሆን ኖሮ ከጥቂት ደቂቃ የዜናዎች ሽፋን እንደማያልፍ ግልጽ ነው) እናም የዜና አውታሮቹ ያሉትን ጉዳይ በመድገም እንዳላታክታችሁ በቀጥታ ባለፈው ወደ ጀመርኩት ኢትዮጵያንና እስራኤልን ወደተመለከተው የታሪክ-ነገራ ወጋችን ልመለስ፡፡
ለመሆኑ፤
1. የቋራው ካሳ/ዐጤ ቴዎድሮስ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ባል፤ የኢየሩሳሌም እጮኛ/ውሽማ›› ይሉ እንደነበር ሁሉ ከዐጤ ቴዎድሮስ በኋላ ወደ ንግሥናው ዙፋን የመጡት ካሣ ምርጫ/ዐጤ ዮሐንስም ማሕተማቸው ላይ፤ ንጉሠ ኢትዮጵያ ከሚለው በሻገር ‹‹ንጉሠ-ጽዮን›› የሚል ሐረግ እንደነበረው ምን ያህሎቻችን እናውቅ ይሆን…፤
2. የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ ብሎ 66 ዓመታትን ያንቀላፋ ኢትዮጵያዊ የንጉሥ ባለሟል ስለመኖሩስ…፤
3. ፋሽስት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወረው በያዙበት 5 ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያንን/አይሁዳውያንን ኢትዮጵያ ላይ ለማስፈር፣ በኢጣሊያና በአውሮፓ ከሚገኙ አይሁዳውያን እና እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የአይሁድ ማህበር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውን። በኋላም እስራኤላውያኑ ከቀደሙ አባቶቻችን ከፍልስጤም ምድር ውጪ የትም ምድር/ሀገር መስፍር አንፈልግም በማለታቸው ይህንን እስራኤላውያንን በኢትዮጵያ የማስፍር ዕቅድ መሰረዙንስ እናውቅ ይሆን…፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ዝርዝር መረጃ የሚፈልግ ሰው ካለ፤ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ The Jewish Settlement በሚል የጻፉትንና ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘውን ጥናታዊ ጽሐፍ እንዲመለከት እጋብዛለሁ)።
እነዚህ ከላይ ያነሳኋቸውን አንኳር ጉዳዮች ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ የምመለስበት ይሆናል ግን ለዛሬው ቀጣይ ወጋችን፤ ‹‹አበው ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ›› እንዲሉ ለመሆኑ ሕዝበ-እስራኤል ከ1000 ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ፤ ሀገር አልባ የሆኑበት ምክንያቱ ምን ነበር… በሚለው ሐሳብ ለመንደርድር ወደድኹ፡፡ እናም የዛሬውን መጣጥፌን በአንድ የወንጌል ኃይለ-ቃል ለመጀመር ወደድኹ፡፡
(የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 19)
———-
‹‹41፤ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ 42፤ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል።
43፤ ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤
44፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና፡፡››
‹‹ሕዝበ-እግዚአብሔር›› የሚል ቃል ኪዳን ከአባቶቻቸው ያላቸው /የወረሱት/ እስራኤላውያኑ /አይሁዳውያኑ/ ከዓመፀኝነታቸው፣ ካለመታዘዛቸውና ከበደላቸው ጠንቅ የተነሳ በተደጋጋሚ በምርኮና በፍልሰት ከሀገራቸው ተሰደዋል፤ በገፍና በግፍ ተፈጅተዋል፤ ተጨፍጭፈዋል፤ ባሪያ ሆነው ወደ ባቢሎን ምድር ተግዘዋል፡፡ (በነገራችን ላይ ከላይ የጠቀስኩት ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ባለሟል አቢሜለክ 66ት ዓመታትን ያንቀላፋው ይህን ባቢሎናውያን የአይሁዳውያን ላይ ያደረሱትን ጥፋትና የኢየሩሳሌምን ውድመት አታሳየኝ ብሎ አምላኩን/ያሕዌን በመለመኑ የኢትያጵያ ቤ/ክ ሉቃእንትና መተርጉማን ይናገራሉ)፡፡
ይህን የኋለኛውን ባቢሎናውያን ለ70 ዘመናት አይሁዳውያኑን ከምድራቸው አፍልሰው ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰዱ የተደረገበትን ታሪክ ለጊዜው እንተወውና በ70 ዓ.ም. እስራኤል የምትባል ሀገርና መንግሥት የጠፉበትን ታሪካቸውን በጥቂቱ ለማየት እንሞክር፡፡ ምናልባት ይህ የአይሁዳውያን ታሪክ ለእኛ ምናችን ነው፤ ኢትዮጵያ እና እስራኤልስ ምንድ ናቸው… የሚል ሰው ቢኖር ሁለቱ ሀገራት ‹የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ምድር› በመሆናቸውና በዋናነት ደግሞ የእስራኤላውያን ታሪክ ለምድራችን፤ ለመንግሥታትና በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ‹የድነትም ሆነ የጥፋት ታሪክ ትልቅ ትምህርት ቤት› ስለሆነ ነው፡፡
ለመውጫ ያህልም፤
‹‹… ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል፤››
ይህ በእንባ ጭምር የተገለጸ የመጽሐፍ ቃል/መለኮታዊ መልእክት/የጌታችን ቃል፤ አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለችበት ሰቆቃና መከራ፤ እልቂትና ፍጅት ገላጭ ኃይለ-ቃል/ምክር አይሆንም ይሆን…?!
ሰላም፤ ሻሎም!!