የአደባባይ በዓሎቻችንና እኛ 

October 1, 2023

T, G

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሳይሆን በዘመን አቆጣጠር ቀመር ምክንያት በዚህ ዓመት ሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች (ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና እስልምና) በዓሎቻቸውን (መስቀል እና መውሊድን) ተመሳሳይ ሊባል በሚችል ቀን አክብረዋል።

መከረኛው ህዝብ ከሚገኝበት አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ አንፃር በትክክል ለሚገነዘበው ግን በበዓላቱ (በመስቀልና በመውሊድ) መድረክ ላይ ተገኝቶ የተለመደ ዲስኩር ከማድረግ አልፎ ወደ ሥልጣነ መንበር የሚወጡ እኩያን ገዥዎች ሃይማኖትን እንደ አንድ ዋነኛ የፖለቲካ መጫዎቻ ካርድ የሚጠቀሙበትን አስቀያሚና አደገኛ ስልት ቢቻል ለማስቆም ቢያንስ ግን  ለመቀነስ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከር በተገባ ነበር። ይህ ግን እንደ አለመታደል ወይም የፈጣሪ ፈቃድ ባለመሆኑ ሳይሆን በአመራር ድክመት እና አሜን ከማለት ያለፈ ተሳትፎ እንዳይኖረው በተደረገው ምእመን ወይም አማኝ ወይም ተከታይ የእውቀት ፣ የአቅም እጦትና እጥረት ምክንያት እውን ሆኖም አያውቅም። አሁንም ሊሆን አልቻለም።

ሁለቱም ግን እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ በንፁሃን የደም ጎርፍ፣ የቁም ሰቆቃ፣ ማህበራዊ ቀውስ (ርሃብ፣ ጥማት፣ በሽታ፣ የሥነ ልቦና ቀውስ) ፣ የመንፈስ ስብራት፣ የሰቆቃ ድምፆች፣ ተስፋ ማጣት፣ ወዘተ በተከበበ አደባባይና አውራ መንገድ ላይ ለቱሪስት ማሳቢያ በሚሆን ገፅታ ተሰልፈውና አሰልፈው “እግዚአብሔር ወይም አላህ የታደመባቸው በዓላትን አከበርን” ሲሉን እውነተኛው ፈጣሪ ይታዘበናል እንኳ አይሉም።

በእውነተኛው አምላክ ስም በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ፈጣሪ/አላህ የዋለው አካባቢያቸውና መንደራቸው ምድረ ሲኦል ሆኖባቸው እንደየምነታቸው ፈጣሪን ሲማፀኑ ከነበሩት (ከዋሉት) ምንዳባንና ንፁሃን ጋር እንጅ አማኞችን በአስፈሪ ማስጠንቀቂያ ጠርንፈው በአደባባይ ከእኩያን ገዥዎች  ጋር ሲተሻሹ ከዋሉት ጋር በፍፁም አልዋለም።

ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን እንደ መርገም ወይም ሃጧአት ወይም ድፍረት ወይም ፀረ ሃይማኖታዊ እምነት በመቁጠር የእርግማንና የውግዘት ናዳ ሊያወርዱ የሚችሉ የዋህ አማኝ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን በሚገባ እረዳለሁና ቢያሳዝነኝም አይገርመኝም። የሚያሳዝነኝ እንዲህ አይነት የውድቀት አዙሪት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመቀጠሉ መሪር እውነት ሲሆን የማይገርመኝ ደግሞ እውነት መናገርንና ከውድቀት አዙሪት እንውጣ ማለትን እንደ ኩነኔ ወይም ሃጢአት የሚቆጥር እውነተኛ አምላክ በፍፁም ስለሌለ ነው።

መቸም የአእምሮ ችግር ወይም ጭፍን ጥላቻ ክፉኛ የተጠናወተው ሰው ካልሆነ በስተቀር እንኳንስ የሃይማኖታዊ እምነት ሌሎችም አገራዊም ይሁን አካባቢያዊ በዓላት አፍራሽ የሆነ ዓላማና ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚያሳይ ግልፅና ግልፅ   ምክንያት እስከሌለ ድረስ በደመቀ አኳኋን ሲከበሩ እሰየው ይላል እንጅ ከቶ አይጎረብጠውም። ሊጎረብጠውም አይገባም።

እርግጥ ነው የአስከፊነቱ መጠንና አይነት ይለያይ እንደሆነ እንጅ በዚህ ሂሳዊ አስተያየቴ የማነሳቸው ጉዳዮች ከረጅሙ የሃይማኖታዊ እምነት ታሪክ ጋር ተያይዘው የመጡና በሰው ልጅ ተፈጥሮና ባህሪ ምክንያት ወደፊትም በፍፁምነት (መቶ በመቶ) ሊወገዱ የማይችሉ ፈተናዎች ናቸው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እናትዋ ጎንደር እና አደይ ትግራይ፡- ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት!! - በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

ከታሪክ አንፃር ያለውን ለጊዜው እናቆየውና በአለንበት በዚህ ዘመን እዚህ እጅግ ጥልቅና መሪር ከሆነ የውድቀት አዙሪት ውስጥ ራሳችንን ለምንና እንዴት አገኘነው? ከፖለቲካው ቀውስና ውድቀት አልፎ የሃይማኖታዊ እምነቶቻችን ወይም እሴቶቻችን ለምንና እንዴት ተጎሳቆሉ?  ብለን እንጠይቅ።

ከመልሶቻችን አንዱ እንኮራበቸዋለን (እውነትም ነው) ከምንላቸውው የረጅም ዘመን የአገራዊነትና የክርስትና እና የእስልምና እምነቶቻችን አንፃር ላለንበት ዘመን የሚመጥን እና የሃይማኖታዊና ሌሎች መሠረታዊ መብቶች የሚከበሩበት ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚደረገውን የተቀደሰ የህዝብ ተጋድሎ በሚጠበቅባቸው ሃላፊነትና ተልእኮ መጠንና አይነት ለመወጣት በተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎቻችን ምክንያት መሆኑን ለማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም።

አዎ! የረጅም ጊዜው ይቅርና በዚህ በምንገኝበት ክፍለ ዘመን እየያነው፣ እየሰማነውና እየታዘብነው ያለው መሪር እውነታ የሃይማኖት መሪዎቻችን በራስ ወዳድነትና ልክ በሌለው ፍርሃት በመጠርነፋቸው እየተፈራረቁ ዙፋን ላይ ከሚወጡ እኩያን ገዥዎች ጋር እየተሻሹ እና ህዝብ የተቆጣ ሲመስላቸው ደግሞ የይመሰል እሮሮና ጩኸት እያስተጋቡ እና አንዳንዴም ከፖለቲካ ሥርዓቱ ካድሬዎች በማይተናነሰ ሁኔታ ህዝብን ግራ የሚያጋቡ መሆናቸውን ነው።

ለዚህ ደግሞ በመስቀል በዓል ዋዜማ ዝርዝር በሆነና አስፈሪነት ባለው አቀራረብና ይዘት ያስተላለፉትን መግለጫ (መቸም ትርጉም አልባ እየሆነብን ከተቸገርን ቆየን)  በጥሞና መረዳት በቂ ነው።

እጅግ አስከፊ ከሆነው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን መውጣት በእውን የምንፈልግ ከሆነ በዚህ መጠንና አይነት ነው መነጋገር ያለብን። አዎ! እኩያን ገዥዎች ሲገድሉትም፣ ሲያስገድሉትም እና ሲያገዳድሉትም መልሼ ልግደል ሳይል እጅግ እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግሥት የተማፀናቸውን ህዝብ ይፋ ጦርነት ሲያውጁበት ተፈጥሯዊ የሆነውን መብቱን በመጠቀም ራሱን ከመከላከል አልፎ የረጅም ጊዜ ገዳዮቹን  ለመቅጣት የተገደደውን ህዝብ በሰላም ስም ከገዳዮቹ ጋር እኩል ለመውቀስ የሚዳዳቸው የሃይማኖት መሪዎችን ቢያንስ  ኢሞራላዊ ነው ማለት ካለብን ወቅት ላይ ነንና ከምር ልብ እንበል።

አዎ! ይህ አይነት ደካማነታቸው ሳያንስ “አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” በሚል የማሸበሪያ አዋጅ ሥር የዋሉትን የመስቀል እና የመውሊድ በዓላት “እጅግ በሚደንቅ ሰላምና ደህንነት አክብረን በሙዋላችን ፈጣሪ ወይም አላህ በረከቱን አርከፈከፈን” ብለው ሊያበስሩን ሲሞክሩ መታዘብ የበለጠ መሪር ትዝብትን ይፈጥራል።

ክርስቶስ እንኳንስ በከባድ መከራ ወቅት በማነኛውም የማስተማር ተልእከው ቢችል በአካል ካልሆነም በመንፈሱ ሃያልነት ከጎስቋሎች የራቀበት ቀንና ሰዓት አልነበረም። ጎስቋሎች በያሉበት የእርሱን ሃያል ድጋፍ ፈልገው በሚማፀኑበት ወቅት በተመቻቸ አዳራሽ ውስጥና አደባባይ ላይ  እየሰበከ አልነበረም የሰውን ልጅ ጨርሶ ከመጠፋፋትና ከመጥፋት የታደገው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰው መሆናችንን አውቀን ለፍቅር ከተገዛን  ኢትዮጵያን  ኃያል እናደርጋታለን።  - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የእኛዎቹ የሃይማኖትመሪዎች ግን ሌላው ቢቀር ዋና ጽ/ቤታቸው በሚገኝበት ከተማ (አአ) ዙሪያ መጠለያቸው በግሬደር ተደርምሶባቸው ከእነ ቤተሰባቸው የምድር ላይ ሲኦል ሰለባ የሆኑትን ንፁሃን ወገኖች ጉዳይ በአካል ተገኝተውም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን መስኮት በታቀደና በተደራጀ አቀራረብ አልነገሩን አልደፈሩም ፤ እነዚያን ንፁሃን ዜጎች ለዚህ ያበቋቸውን ጨካኝ ፖለቲከኞችንም ከምር ሲገስፁም አላየንም ወይም አልሰማንም። እንግዴህ ይህ ሁሉ የሃላፊነት ጎደሎነት በነበረበት እና ባለበት መሪር እውነታ ውስጥ ነው ከእነዚያው ገዳይ፣ አስገዳይ፣ አገዳዳይና አፈናቃይ ባለሥልጣናትን ጋር ወንበር እየተጋሩ ያከበሯቸውን የመስቀልና የመውሊድ በዓላት “ፈጣሪ የታደመባቸው እና በሰላምና በፍቅር መንፈስ የተንበሸበሹ ነበሩ” ሲሉን ጨርሶ ህሊናቸውን የማይኮሰኩሰው።

የሃይማኖታዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የፈጣሪን ስም እየጠሩ ፍትህና ርትዕ አልባ በሆነ እና የእኩያን ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን ዘመን ጠገብ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የመነጋገሪያ አጀንዳ በማያደርግ ሁኔታ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ወይም እፎይታ ይመጣል ማለት የአገርን መሪር እውነታ አለመረዳት ወይም ለጊዜውም ከሠራ የኢትዮጵያ ህዝብ ቶሎ የመርሳት “ፀጋ” አለው በሚል መልሶ በህዝብ መሳለቅ ነው።

የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎች ለሰማዊውም ሆነ ለምድራዊው ዓለም (የሰማያዊው መንገድ የሚወሰነው በዚህ ገሃድ ዓለም በምንሆነውና በምናደርገው ነውና) ለዚህ እንቅፋት ከመሆን አልፎ የፖለቲካ ወለድ ሰይፋቸውን በመከረኛው ህዝብ ላይ ያሳረፉትንና አሁንም ከምንጊዜው በከፋ እያሰረፉበት የቀጠሉትን እኩያን ገዥ ቡድኖችንና ግብረበላዎቻቸውን የክርስቶስን ያህል ባይጠበቅበቸውም የእርሱ ሃዋርያት ነን እያሉ ከሚነግሩን አንፃር ሆነውና አድርገው ሊያሳዩን በተገባቸው ነበር።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን አብዛኛው ነገረ ሥራችን ሁሉ ከቀደምት ወገኖቻችን አንፃር ሲታይ እንኳን ወደ ፊት ልንገሰግስ በነበርንበት ቆመን ለመገኘትም በእጅጉ ተስኖናል። ይህ ደግሞ የሃይማኖት መሪዎችንም ሲጠናወት የሚያሳድረውን አሉታዊና ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ለመረዳት ከእኛው ከራሳችን የተሻለ ምስክር (ዋቢ) የለም።  የራሳችንን መሪር የሆነ ደጋግሞ የመውደቅ አባዜ፣ ማቆሚያ ካላበጀንለት የአገራችን (የህዝባችን) መከራና ውርደት፣ የሃይማኖት ተቋሞቻችን/አገልጋዮቻቸው/ተከታዮቻቸው ከገጠማቸውና እየገጠማቸው ካለው ፖለቲካ ወለድ ውድመትና ውርደት ፣ በዚህ ከቀጠልን ሊገጥመን ስለሚችለው አስከፊ የነገ (የወደፊት) እጣ ፈንታ አስፈሪነት፣ ወዘተ ያለመማር ክፉ አዙሪት ውስጥ እየተሽከረከርን ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ፆምና ፀሎት፣ ስለ ክርስቲያናዊ ባህሪና ተልእኮ፣ ከሞት በኋላ ተስፋ ስለምናደርገው ዓለም የምንፅፈውም ሆነ የምንናገረው የተለምዶ ከሆነ ንግግር/ትርክት አያልፍም።

በገዳይና አስገዳይ ገዥ ቡድኖች ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት የአስቃቂ አሟሟት ሰለባ በሆነ፣ ከመቃብር በላይ ከሆነ ሞት ጋር በተፋጠጠ ፣ በየማጎሪያ ቤቱ ሰቆቃ ላይ በሚገኝ ፣ በርሃብና እርዛት ጠኔ ምክንያት የመፅዋች ያለህ እያለ በሚጮህ  አየሌ ሚሊዮን ህዝብ በተከበበ አደባባይ ላይ ከእኩያን ገዥ ቡድኖች ጋር እየተሻሹ በተከበሩ በዓላት ላይ  እውነተኛው አምላክ ወይም አላህ በእውነት ደስ እንዳለው መተረክን  እውነተኛው ፈጣሪ አወንታዊ  ምሥክርነት የሚሰጥበት አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:    በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ  ውሳኔ መወሰን ያለበት ማነው?  - ኤፍሬም ማዴቦ

ኢህአዴጎች (ብልፅግና እና ህወሃት) በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ባካሄዱት ጦርነት ልጆቻችው የሞቱባቸው የትራይ ወላጆችና ቤተሰቦች በመርዶ ማእበል በሚናወጡበትና በዚያው ጦርነት የሞቱበትን ልጆቹን በቅጡ ሳይረዳ (እርሙን ሳያወጣ) ሌላ አስከፊ ጦርነት ተከፍቶበት በማያቋርጥ መከራ ላይ በሚገኘው የአማራ ማህበረሰብ መሪር እውነታ ውስጥ የተካሄዱትን በዓላት “በሰላምና በመረጋጋት ተጀምረው ተጠናቀቁ” በሚል ጮቤ መርገጥን እንኳንስ የሚያደንቅ በትእግሥት የሚያዳምጥም እውነተኛ አምላክ የለም። አዎ! ንፁሃን ፍጡሮቹ የምድር ላይ ሲኦል ተደፍቶባቸው እያየ ከገዳዮችና አስገዳዮች ጋር በአንድ አደባባይ እያሸረገድን ወይም እየተውረገረግን አከበርን የምንላቸው በዓላት እውነተኛውንና የንፁሃንን አምላክ እንዴት ሊያስደስቱ እንደሚችሉ ለመረዳት ከራሳችን ግልብ ስሜት መውጣን ይጠይቃል ።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ሀ) በአሁኖቹ ባለጌ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እገዛ መፈንቅለ መጂሊስ በማድረግ ሥልጣኑን በቁጥጥራቸው ሥር ባደረጉ ወገኖች ሥር የተካሄደ የሃይማኖታዊ በዓል በረከትትነትን ለመረዳት ያስቸግራል። ለ) የውስጣቸውን ድክመት (ቀውስ) ቢቻል ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ቢያንስ ደግሞ በንፃራዊነት ይበል የሚያሰኝ መውጫ መንገድ ለማበጀት ስለ ተሳናቸው ከእኩያን ፖለቲከኞች የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባነት ሰብረው ለመውጣት ባቃታቸው የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች የተካሄደን ሃይማኖታዊ በዓል በደስታና በእልልታ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል። ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት እውነተኛው አምላክ ወይም አላህ ያለውና የሚኖረው በየአካባቢያቸው፣ በየመንደራቸውና በየመጠለያው የፖለቲካ ወለድ ሰቆቃ ሰለባ ሆነው የደም እንባ ከሚያነቡት እና የእርሱን (የፈጣሪን) እገዛ ከሚማፀኑ ንፁሃን ጋር ነውና።

እናም የሚሻለው ከርሞና ከዚያ ወዲያም በተመሳሳይ የውድቀት አዙሪት ውስጥ እንዳንገኝ መሪር የሆነውን ያራሳችንን እውነታ አምነን በመቀበል የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ የምናደርገውን ተጋድሎ እውነተኛው አምላክ ወይም አላህ እንዲባርክ ከልብ እየተማፀን ተገቢ የሆነውን የየራሳችንን የቤት ሥራ መሥራት ነው።

አቻ በማይገኝለት ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ በወረደበትና እየወረደበት በሚገኝ ብዙሃን ህዝብ ፣ በአየሌ ሽዎች በሚቆጠሩ ንፁሃን የደም ጎርፍ፣ በአያሌ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ወገኖች የቁም ሟችነት ፣ እና በአጠቃላይ የራሱ ምድር ምድረ ሲኦል በሆነችበት መከረኛ ህዝብ መካከል እየኖርን እና ዘመንና ወቅት እየቆጠርን በምናከብራቸው በዓላት “እየረካን” ነገር ዓለሙ ሁሉ እፁብ ድንቅ እንደሆነ አድርገን ራሳችንን የማታለሉ ጎጅ ልማድ ይበቃናል ።

 

እናም ልብ ያለው ልብ ይበል! 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share