October 1, 2023
5 mins read

የጠለምት አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ መምህር ፀጋዬ እሸቴ በግፍ መታፈን አስመልክቶ ከልሳነ ግፉዓን ድርጅት የተሰጠ መግለጫ

Lisane Gufuan 2 1ፋሽስቱ ትህነግ/ወያኔ በኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ብርቱ ክንድ ተደቁሶና እጁ ተጠምዞ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት እንደፈረመ ይታወቃል። ይህ ባለ 15 አንቀፅ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ አመት ሊሞላው ከወር ያነሰ እድሜ የቀረው ቢሆንም የስምምነቱ ክፍሎች በሙሉ ተጥሰውና ትህነግ/ወያኔ ዳግም የህዝባችን የህልውና ስጋት ወደ መሆን እንዲሸጋገር የተደረገበት የክህደት ቁልቁለት ላይ እንገኛለን።

በአሁኑ ወቅት በዘር ማጥፋትና በሀገር ክህደት ወንጀሎች የሚፈለጉት የትህነግ/ወያኔ መሪዎች በተለየ ጥበቃና እንክብካቤ አዲስ አበባ ላይ እየተንጎማለሉ፤ በአንፃሩ ደግሞ ንፁሃን የአማራ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ባለሃብቶችና፣ በተለይም ወጣቶች በጅምላ እስር እየተሰቃዩና መከራን እየተቀበሉ ይገኛል። የአማራ ልጆች በገፍና በግፍ መታሰርና መሰቃየት ዋነኛው ምክንያት የብልፅግና መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀመውን ታሪካዊ ክህደትና ከትህነግ/ወያኔ ጋር የገባበትን መርህ አልባ ግንኙነት ያደናቅፋሉ በሚል እንደሆነ ልሳነ ግፉዓን በፅኑ ያምናል።

የመምህር ፀጋዬ እሸቴ አፈና የብልፅግና መንግስት የገባበትን የአማራ ፖለቲከኞችንና መሪዎች የማሳደድና ብሎም የማጥፋት ዘመቻ አንዱ ማሳያ ነው። መምህር ፀጋዬ እሸቴ በግፍ እስከ ታፈኑበት እለት ማለትም መስከረም 3/2016 ዓ.ም. ድረስ የጠለምት አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ። መምህር ፀጋዬ እሸቴ የታፈኑበት ምክንያት በውል ባይታወቀም በአዳርቃይ ከተማ መከላከያ ጦር ሰፈር የቴክኒክ ሞያ ውስጥ በግፍ ታስረው እንደሚገኙና ቤተሰቦቻቸውም በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶናል።

የመምህር ፀጋዬም ሆነ የሁሉም የአማራ ልጆች የጅምላ እስርና ስቃይ የሚመነጨው የብልፅግና መንግስት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያና አካባቢውን ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጭ ለትህነግ/ወያኔ አሳልፎ ለመስጠት የሸረበውን ሴራ ያደናቅፋሉ በሚል እንደሆነ እናምናለን። ለዚህም ዋና ማሳያው እነ መምህር ፀጋዬን የመሰሉ የአማራ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች እንዲያፍኑና እንዲያሰቃዩ ተላልፈው የተሰጡት በቅርቡ ወደ ሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀሉ ለተደረጉ የትህነግ/ወያኔ ነባር ታጋዮች መሆኑ ነው።

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት ደግሞ ደጋግሞ እንደሚያሳስበው የብልፅግና መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ የጀመረውን የጅምላ እስርና ማሰቃየት በአስቸኳይ ካላቆመ ሀገር ወደ ከፋ ምስቅልቅልና ቀውስ ውስጥ ትገባለች የሚል ስጋት አለን::

ይህ ሀገራዊ ምስቅልቅል ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በከፋ ሁኔታ የሚጎዳና የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ከመጣው ሀገራዊ አደጋ ተለይቶ እንደማይተረፍ ማስገንዘብ እንወዳለን።

ስለሆነም የብልፅግና መንግስት በግፍና በማን አለብኝነት ያፈናቸውን መምህር ፀጋዬ እሸቴንና ሁሉንም የአማራ ልጆች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈታና ለሀገራዊ መረጋጋትና ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ እናሳስባለን።

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!

በአማራ ህዝብ ላይ የተከፈተው የዘር ፍጅት በአስቸኳይ ይቁም!

Lisane Gufuan 1 1

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት

መስከረም 29/2016 ዓ.ም.

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop