አንበሳው ተነሳ

አባቱ ውድማ የተኛውን በሬ፣
ነካክተው ቆስቁሰው አደረጉት አውሬ።”


የሕዝብ ስንኝ

____________________

ልባችሁ ተደፍኖ በትዕቢት ጮማ
አትነካኩት ስንል ብላቸሁ አልሰማ
እየነካካችሁ በሚያቃጥል ሳማ
አንገብግባችሁት ቆሽቱ እስከሚደማ፣
ሲጠናበት ጊዜ ሲበዛበት ቂያማ
በደረቀ ሌሊት በድቅድቅ ጨለማ
አንበሳው ተነሳ ከተኛበት ውርማ።

ብዙ ሲታገሰው መስሎት ሙት እሬሳ
እየፈነጨበት ባፍቂጡ እየፈሳ
የቀሰቀሰውን በትቢት ትንኮሳ
ጅብም ሆነ አነር፣ ተኩላም ሆነ ሰሳ
አሳዶ በመያዝ እያሳየ አበሳ፣
ዳግም ላይረበሽ ሰላም ላይነሳ
ምሎ ተገዝቶ ሦስት ጊዜ ሲያገሳ፣

አደበላለቀው አስራ አራቱን ማሳ
በአንድነት ሰማው ሰማኒያ ሶስት ጎሳ።
 
ጦሙን እንደዋለ ጡሙን ስላደረ
ጨጓራው ተቃጥሎ አንጀቱ እንዳረረ
ሆዱ ተቆራምዶ አፉ እንደከረረ፣
በገባችሁበት ገብቶ እያባረረ
በክንዱ ደቁሶ እየዘገረረ
ቁርስ ያረጋችኋል እየሰባበረ።

 
መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጋዜጠኞችና ጦማሪያን ጊዜ ቀጠሮ በመደበኛ ችሎት እንዲታይ ታዘዘ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share