ክፍል ሁለት፡
ከኦሮሙማው የፋሽስት መንግሥት ጋር ድርድር አይሞከር፤ ለፋሽስቶች ድርድር ጠላቶቻቸውን አዘናግቶ ማጥፊያ መሳሪያ ነውና!!!!!!
በዶ/ር አሰፋ ነጋሽ – በሆላንድ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ
E-mail -àDebesso@gmail.com – አምስተርዳም (ሆላንድ) ሃምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም.
ፋሽስቶች ያሉትን ሁሉ በጭፍንነት የሚያደርጉ ናቸው – የዶ/ር ዲማ ነገዎ ንግግርና የእሱ ትንቢትና ምኞት ዛሬ ላይ እየተፈጸመ መሆኑ።
ዓቢይ አህመድ ሥልጣን ላይ እንደወጣ በህገወጥ መንገድ አቶ ታከለ ኡማ የተባለ አንድ በዘረኝነት አስተሳሰብ የሰከረ የኦሮሙማን ፓለቲካ በቅጡ ሊያስፈጽም የሚችል የኦሮሞ ካድሬ በከንቲባነት ሾመ። ታከለ ኡማ ከተነሳ በኋላ ደግሞ የኦሮሙማው መንግሥት ወ/ሮ አዳነች አበቤ የተባለችውን የኦህዴድ ካድሬ ከንቲባ በማድረግ የአዲስ አበባን ከተማ የህዝብ ስብጥር ሥር ነቀል በሆነ መንገድ የመቀየር እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። እነዚህ ሁለት ከንቲባዎችና በስራቸው ያሰለፏቸው የኦሮሙማ ፋሽስታዊ ፓለቲካ አራማጆች ባለፉት አምስት ዓመታት የፈጸሟቸው ድርጊቶች፤ የተገበሯቸው ዘረኛ ፓሊሲዎች በአዲስ አበባና አካባቢዋ ባሉ ከተሞችና ክፍለ ከተማዎች ዛሬም የቀጠለው የዘር የማጽዳት ድርጊት (በሱሉልታ፤ ሰበታ፤ አቃቂ፤ ቦሌ ቡልቡላ፤ ለገጣፎ፤ አሁን ደግሞ ሸገር ብለው በሰየሙት የአዲስ አበባ ክፍል ወዘተ) ከዚሁ የፋሽስታዊ አገዛዝ መሰረት ከሆነው የሶሻል ዳርዊኒስት አስተሳሰብ የሚነሳ ነው። እነ ሀጂ ጀዋር መሃመድ ዓቢይ አህመድ ሥልጣን ላይ በወጣ ማግስት ሃሮምሳ ኦሮሚያ (Resurgence of a Dominant Oromo Nationalism and Consciousness) በሚል ሥም በአዲስ አበባ ያሉትን የኦሮሞ ተወላጆች በዜግነት ሳይሆን በአዲስ የኦሮሞን የበላይነት፤ የኦሮሞን ልዕለ-ሰብዕና የሚሰብክ ፋሽስታዊ አስተሳሰብና አመለካከት በመቅረጽ (super-man status of Oromos) ያከናወኑት ሰፊ የሆነ የፓለቲካ ሥራ፤ ተስፋፊነትን፤ ድንበር-ገፊነትን፤ እብሪተኛናትን ጦረኛነትን የሚያበረታታ፤ የኦሮሞን ልዩ ጥቅምና የኦሮሞን የበላይነት የሚሰብክ ፋሽስታዊ የሆነ በሶሻል ዳርዊንዝም አስተሳሰብ የተቃኘ አደገኛና ጽንፈኛ እንቅስቃሴ ነበር። የአዲስ አበባ አካል የነበረን ሰፊ አካባቢ “ሸገር” በሚል ሥም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በማካተት አሁን ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጽዳት ድርጊት (እስካሁን 112000 ቤቶች ፈርሰዋል፤ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኦሮሞ ያልሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች (አማራዎች፤ ደቡቦች፤ ጉራጌዎች ወዘተ) መንገድ ላይ እንዲበተኑና ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ አድርጓል። ናዝሬትና ደብረዘይትን በመሳሰሉ ከተሞችም ተመሳሳይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የማፈናቀል ድርጊት በስፋት እየተፈጸመ ነው። የአዲስ አበባን ኦሮሞነት ለማረጋገጥ በፍጥነት እየተገነቡ ያሉት የኦሮሚያ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ግንባታ፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን የአስተዳደር፤ ቢሮክራሲና የፓሊስ ተቋሞች በኦሮሞ ተወላጆች የሙሙላት ግልጽና ሰፊ እንቅስቃሴ ወዘተ ከዚህ ፋሽስታዊ የኦሮሙማ የአፓርታይድ ሥርዓት መስፋፋት ጋር የተገናኙ ናቸው። የኦሮሞ ቋንቋን ትምህርት በግዴታ ኦሮምኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ባልሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የመጫኑ ድርጊት፤ ነባር የሆኑና ህብረ-ብሄራዊ ቀለም ያላቸው ሀገራዊ ምልክቶችን፤ ህንጻዎችን፤ ተቋሞችን፤ ታሪካዊ ስፍራዎችን በታላቅ ፍጥነት የማፍረስና የማጥፋቱ ዘመቻ የፋሽስታዊው የኦሮሙማ እቅድ አካል ነው። ይህ የኦሮሙማ የፓለቲካ ንድፍ ወይም ፕሮጄክት ታሪካዊ ስፍራዎችና ምልክቶችን የማፍረስና የማውደም ዘመቻን የሚያካትት ሲሆን በተጨማሪም ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣን የአንድ ሀገር ህዝብ የወል ትውስታ ሥር-ነቀል በሆነ መንገድ (destroying the collective memory of a people in a radical manner) በማጥፋትና በመደምሰስ ኦሮሙማ የተባለውን የኦሮሞን ነገድ የበላይነት የሚሰብክ ፋሽስታዊና ጽንፈኛ የሆነ የአፓርታይድና የአድሎ ሥርዓት ለመተካት የሚደረግ አደገኛና ሀገር-አፍራሽ የሆነ ድርጊት ነው። እዚህ ላይ አንባቢ እንዲረዳ የምፈልገው ፋሽስቶች እነሱ የራሳቸውን ጥቅም በተመለከተ እናስከብራለን የሚሉትን ዓላማ ሁሉ በጭፍንነት ለማሳካት ከፍተኛ ቁርጠኛነትና የዓላማ ጽናት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡
ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ዲማ ነገዎ የተባለው (ዛሬ የዓቢይ አህመድ አንዱ ዋነኛ አማካሪና የፓርላማም ተወካይ የሆነ ሰው የኦነግ ዋና ሊቀመንበር በነበረበት ወቅት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር መስከረም 1990 ዓመተ ምህረት (ማለትም ከዛሬ 33 ዓመት በፊት) ሙላሃየም (Mulheim) በምትባል ትንሽ የጀርመን ከተማ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ ላይ የተናገረውን ነገር ላስታውሳችሁ። ከ33 ዓመት በፊት በዚች የጀርመን ከተማ የኢትዮያ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች (ኢህአዴግ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶንና ኦነግ) በጀርመን የኢትዮጵያ መንግስት አምባሳደር (አቶ ጥበቡ በቀለ) ጭምር በተገኙበት ስብሰባ ላይ የኦነግ መሪ የነበረው ዲማ የሚመራውን ኦነግ የተባለውን ድርጅት የፓለቲካ መዳረሻና ግብ በተመለከተ “የኦነግ የፓለቲካ ዓላማ ምንድነው” ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የሚከተለው ነበር። “የኦነግ ዓላማ ኦሮሚያን ነጻ አውጥቶ ፊንፊኔ ላይ የኦሮሚያን ነጻነት ማወጅ ነው”። በዚህ ስብሰባ ላይ እንደኔው ተገኝቶ አዳማጭ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ “አቶ ዲማ አንተ ፊንፊኔ የምትላት የዛሬው አዲስ አበባ ናት። በዛሬዋ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው ነዋሪ ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደለም። ታዲያ እናንተ ኦነጎች ፊንፊኔ የምትሏት አዲስ አበባ ላይ ነጻነታችሁን ስታውጁ፤ የኦሮሞ ነገድ ተወላጆች ያልሆኑት የዚች ከተማ ነዋሪዎች ምን ይሆናሉ? እጣ ፈንታቸውስ ምንድነው” ብሎ ጠየቀው። ዲማ ነገዎም “ኦሮሞ ያልሆኑትን ኮሪዶር ከፍተን እናስወጣቸዋለን” ብሎ መልስ ሰጠ። በወቅቱ እዚያ ስብሰባ ላይ የነበርነው ብዙዎቻችን ይህንን የዲማን ምላሽ እንደ አስቂኝ ነገር ወይም የእብድ ንግግር አንድርገን ቆጥረን ያለፍነው ይመስለኛል። በወቅቱ በዚህ የዲማ ንግግር ሲስቁ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁኝ። ግን ዲማ የሚናገረው ነገር አስቂኝ አልነበረም፤ አስቂኝ እንዳልነበረም ባለፉት አምስት ዓመታት ዲማ ይናፍቀው የነበረው የኦሮሞ መንግሥት ሥልጣን ላይ ወጥቶ ያደረጋቸውን ነገሮች ማየቱ በቂ ነው። ፋሽስቶች የራሳቸውን ጥቅም በተመለከተ እናደርገዋለን፤ እንፈጽመዋለን ለሚሉት ቃል ታማኝ ስለሆኑ ዲማ ከ33 ዓመት በፊት የተናገረውን ነገር ዛሬ እሱ የሚሳተፍበት የኦሮሙማው መንግሥት በተግባር እየፈጸመው ነው። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን የኦሮሙማው መንግስት ዛሬ በሸገር፤ በሱሉልታ፤ በለገጣፎ፤ በሰበታ፤ በናዝሬት፤ በደብረዘይት፤ በአዲስ አበባ ወዘተ ሥልታዊ በሆነ መንገድ እያካሄደ ያለው የዘር ጽዳት ነው። ይህንን ከእዚህ በላይ ዲማ ነገዎ የተናገረውን ሁሉ እሱ መናገሩን የሚመሰክሩ በርካታ ሰዎች ዛሬም በጀርመን ሀገር ይኖራሉ ብዬ አስባለሁኝ። እኔ በምኖርበት በሆላንድ ሀገር የሚኖርና እንደ እኔው እዚያ ስብሰባ ላይ የነበረ ሀገሬ ሃዲስ የተባለ ግለሰብ በህይወት ስላለ ምስክርነቱን ሊሰጥ ይችላል።
እንደምታሳውሱት የወያኔ ትግሬዎች መንግሥት ከትግራይ ክልል በታች በሚኖረውና በዚህ የፋሽስታዊ ሥርዓት በተመረረው ህዝብ ትግል በሚንገዳገድበት ወቅት እነ ዲማ ነገዎ ግንቦት ሰባትን ሽፋን በማድረግ ጥቂት ለዝናና ለታይታ በየቦታው ጥልቅ ብለው የሚገቡ የአማራ ተወላጆችን በአጃቢነትና በአጫፋሪነት ይዘው ግንባር Formation of Alliance of Arbegnotch Ginbot 7 & Oromo Democratic Front
ፈጠርን ብለው ኢሳት በሚባለው የግንቦት ሰባት ልሣን በነበረው የፕሮፓጋንዳ ቴሌቪዥን ሰፊ ሽፋንና ህዝብን የማደናገር ሥራ ይሰሩ ነበር። በተለይም ብርሃኑ ነጋን በመሳሰሉ እጅግ ጸረ-አማራ የሆኑ ግለሰቦች ሲዘወር የነበረው ግንቦት ሰባት ኦነግ ከተባለው በአማራ ጥላቻ ጥርሳቸውን ነቅለው ባደጉ የኦሮሞ ፋሽስቶች ጋር በማበር አማራ የተባለውን ሰፊ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አካል ከማናችውም የኢትዮጵያ ፓለቲካ ለማግለል በብርቱ ሰርተው ጥረታቸውም ሰመረላቸው። ወያኔን አሽቀንጥሮ የአማራዎች አስተዋጽዖም ተረስቶ አማራን ጭራሹኑ የማያቋርጥ የጥቃት ዒላማ ያደረገ የኦሮሙማ መንግሥት ወደ ሥልጣን ላይ መጣ። የዚህን የኦነግና የግንቦት ሰባት ጥምረት በማምጣት ዋና አስተባባሪ በመሆን ኦነግ ውስጥ ለውጥ መጥቷል እያለ ድንቁርናና የእውቀት-እጥረት በሚፈጥረው ግትርነት በየመድረኩ ሲሰብክ የነበረውና በተለይም በእነ ኢሳት ላይ ሰፊ ሽፋን ይሰጠው የነበረው ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ነበር። ጌታቸው ኦነግ ውስጥ ለውጥ መጥቷል እያለ በአደባባይ ሽንጡን ገትሮ ይከራከር የነበረው በቃል ብቻ ሳይሆን በጽሁፍም ነበር። ለማስረጃም ጌታቸው በ2011 የጥናት ጽሁፍ ብሎ በስብሰባ ላይ ካቀረበው ጽሁፍ ጠቅሼ የዚህን የሁለተኛውን የጽሁፌን ክፍል እቋጫለሁኝ። ይህንን ዛሬ ለአንባቢዎች የምጽፈው ጌታቸውን የመሳሰሉ ግለሰቦች የአክራሪ ብሄረተኛነትን ሀሁ እንኳን በቅጡ ያልተረዱ፤ ለመረዳትም አንዳችም ጥረት ሳያደርጉ ባገኙት መድረክ ሁሉ የአክራሪ ብሄረተኞችን በማር የተለወሰና አማላይ ቃላት እንዳለ በመቀበል ህዝብን በማደናገርና በማሳሳት ያደረጉት ጥረት የኦሮሙማን መንግሥት አንግሶ ምን ያህል ጉዳት እንዳመጣ ለማሳየት ነው።
የኢትዮጵያ ፓለቲካ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ እንደ ጌታቸው በጋሻው ባሉ በእውቀት ሳይሆን በስሜት በሚመሩ፤ ስለኢትዮጵያ ታሪክ፤ ማህበረሰብ፤ ባህል ትላንትም ሆነ ዛሬ በቂ ግንዛቤ በሌላቸው ሰዎች ይመራ የነበረ ህዝባዊ እንቅስቃሴን ወልዶ አልፏል። ይህ በተማሪዎች እንቅስቃሴ የተጀመረ እውቀት-አጠርና ስሜታዊነት የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ በግራ ፓለቲካ አሸጋጋሪነት ባለፉት 32 ዓመታት ደግሞ ለፋሽስታዊ አገዛዝ እንደዳረገን ማንም ህሊና ያለው ኢትዮጵያዊ መረዳት የሚችል ይመስለኛል። ላለፉት 60 ዓመታት በጮርቃው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተለኩሶና የግራ ፓለቲካን መፈናጠጫው አድርጎ “በብሄር-ብሄረሰቦች ነጻነትና መብት” ሥም ሲገፋ የነበረው ፓለቲካችን ባለፉት 32 ዓመታት በሃሰተኛ ትርክት ላይ መሰረታቸውን ያደረጉ አክራሪ ብሄረተኛና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ ተራማጅ ኃይሎች ይቆጠሩ የነበሩ ፋሽስታዊ ኃይሎችን በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥትን ሥልጣን እንዲጨብጡ አስችሏል። በነገራችን ላይ እኔም በእድሜም ሆነ በአስተሳሰብ ጮርቃ በነበርኩበት የህይወት ዘመኔ የግራ ፓለቲካ ተከታይ ሆኜ በጀሌነት ለሶስት ዓመታት ያህል ኢህአፓ ውስጥ ቆይቻለሁኝ። በዚህም ምክንያት ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱት ችግሮች የራሴም ድርሻ አለበት እያልኩ እቆጫለሁኝ። ስደት በፈጠረልኝ አጋጣሚ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ታሪክና ባህል ለማወቅ ሙከራ አድርጌያለሁኝ። ቢያንስ ይህ የፈጠረልኝ ግንዛቤ በነጻነት ሥም ዘረኛና በጥላቻ የሚመሩ የብሄር ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ድሮ የኢህአፓ ጀሌ በነበርኩበት ዘመን እንዳደረግሁት ሆ ብዬ እንዳልደግፍ አድርጎኛል። የብሄረተኛ ድርጅቶችንም የጥፋት አጀንዳና ግብ በመረዳት ባለፉት 39 ዓመታት ያህል እነዚህንም ዓይነት የጥፋት ኃይሎች ስቃወም ቆይቻለሁኝ። በሚያሳዝን ደረጃ ግን ከግራው ኃይል መፈረካከስ በኋላ የተረፉ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የእኔ ትውልድ ሰዎች እነዚህን የጥፋት ኃይል የሆኑ አክራሪ ብሄረተኛ ድርጅቶችን ከመታተል ይልቅ እንደ ተራማጅ የህብረተሰብ ኃይሎች በማየት ሲታገሱ፤ ሲያሽኮረምሙ አይቼአለሁኝ። ይህ ያሳዝነኛል፤ ባለፉት 32 ዓመታት ሀገራችን በአክራሪ ብሄረተኛ ድርጅቶች እጅ ወድቃ ዛሬ ለደረሰችበት ፋሽስታዊ ሥርዓትም ይህ የእኔ ትውልድ ዝምታና ቸልታ (በተለይ በነጻው የምዕራቡ ዓለም በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ) የራሱ አስተዋፅዖ አድርጓል ብዬም አምናለሁኝ።
ፋሽዝም አንድ ህዝብ ከራሱ ማንነት ጋር እጅግ የተጋነነ ፍቅር ይዞት የራሱን የወል ማንነት እንደ ጣዖት እንዲመለከተውና እንዲሰግድበት የሚያደርግ መርዘኛ ፍልስፍና ነው። በትግራይ አክራሪ ብሄረተኛነት የማዕዘን ድንጋይ ላይ መሰረቱን የጣለው አዲሱ አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛንት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የራሳቸውን የነገድ ማንነት በአምልኮ መልክ እንዲሰግዱለትና እንደ ጣዖት እንዲያመልኩት በማድረግ አክራሪና ጽንፈኛ የሆነ ፋሽስታዊ የሆነ የፓለቲካ ሥርዓትን በትግራይ ውስጥ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ ለመዘርጋትና ለመጫን ችሏል። በእኔ የግል ምልከታ፤ ንባብና ድምዳሜ ወያኔዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የዘረጉት ትግራዋይነት የሚባለው አክራሪ ማንነት ትግሬዎች ህይወታቸውን የሚመሩበት አዲሱ የፓለቲካ ኃይማኖት ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ ትግራዋይነትን ተክቶ በኢትዮጵያ ሰማይና ምድር ላይ የጽልመት ኃይል ሆኖ ያለው ብቅ ያለው ኦሮሙማ የሚባለው ሁሉን ሰልቃጭና ተስፋፊ (expansionist)፤ ሁሉን ልቆጣጠር (totalitarian)፤ ከእኔ ውጭ ያሉ ነገዶችን ማንነት ላጥፋ (genocidal)፤ የሌሎችን ነገዶች ታሪክና ቅርሶች አጥፊ (historicide or one who perpetrates the erasure of the history of other people outside its ethnic group)፤ ሁሉን ላጥፋ ብሎ የተነሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያለው የኦሮሞ አክራሪ ብሄረተኛነት እንደ ትግራዋይነት ሁሉ የፋሽስት ፍልስፍና መገለጫ ነው። እንደ ማንኛውም የፋሽስት ፍልስፍና አዲሱ የዚህ አስተሳሰብ ተከታዮች የሚያመልኩት የፓለቲካ ኃይማኖት የእያንዳንዱን ግለሰብ ማንነት በማክሰም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እንደ መንጋ በአንድ መንገድ እየተጓዙ አድርጉ የተባሉትን ሁሉ በደመነፍስ (instinctively) የሚፈጽሙ የአንድ ፋሽስታዊ ድርጅት ጭፍን ተከታዮች አድርጓቸዋል። በእኔ የግል እምነት ኦነግን፤ ኦዴፓን፤ ኦፌኮን የመሳሰሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኛ ድርጅቶችን የሚከተሉ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆችና በተለይ ቄሮ የሚባሉት ወጣቶች የዚህ አዲሱ ኃይማኖት ተከታዮች ናቸው። እነዚህ የኦሮሙማ ፋሽስታዊ የሆነ አዲሱ የፓለቲካ ኃይማኖት ተከታዮች ህይወታቸው የሚመራው ቀደም ሲል በሚያምኑባቸው የክርስትና፤ የእስልምናም ሆነ ሌሎች ኃይማኖቶች ሳይሆን እነዚህን ነባር ኃይማኖቶችና እምነቶች ተክቶ የህይወትና የሥነ ምግባር ወዘተ መመሪያ ሆኗቸው ብቅ ባለው ኦሮሙማ በሚባለው አዲሱ የኦሮሞን የበላይነት፤ የኦሮሞን ልዩ ፍጡርነት፤ ልዩ ጀግንነት፤ ልዩ ጥበበኛነት፤ ልዩ ባለመብትነት ወዘተ በእብሪትና በማን አለብኝነት መንፈስ የሚሰብክ አክራሪና ጽንፈኛ የሆነ የፋሽስት የፓለቲካ ኃይማኖት ነው። የእነዚህን እጅግ አደገኛ የሆኑ ፋሽስታዊ የነገድ ማንነት አራማጅ ድርጅቶች የፓለቲካ ዓላማም፤ ግብ፤ ባህርይና ተፈጥሮ ሳይረዱ ኦነግን አትናገሩ፤ ኦነግ ወደ ኢትዮጵያዊነት እየመጣ ነው እያሉ የራሳቸውን በድንቁርናና በስሜታዊነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ሲሰብኩ ከነበሩት “ምሁራኖች” ውስጥ አንዱ የሆነውን የፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻውን ንግግር ከዚህ በታች አስፍሬያለሁኝ። አንባቢ ጌታቸው በጋሻው ከዚህ በታች ስለ ኦነግና ሌሎች ኦነግን የመሰሉ ብሄረተኛ ድርጅቶች የጻፈውን የመሰለ ግልብ (superficial) እና እውቀት-አጠር (ill-informed) የሆኑ ድምዳሜዎች ኢትዮጵያን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉ ያለፉትን 32 ዓመታት የኢትዮጵያ ሁኔታ በአንክሮ መለስ ብሎ በመመልከት የራሱን ፍርድ እንዲሰጥ እጠይቃለሁኝ። ኦነግ ዐጼ ምንሊክ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞዎችን ፈጅተዋል ብሎ ከዛሬ 43 ዓመት በፊት Gadda Melbaa በሚል የብዕር ሥም በሃሰት ትርክት ላይ የተመሰረተ አንዲት መርዘ|ኛ መጽሃፍ በጻፈው ዶ/ር ታደሰ ኤባ (መሬት ይቅለለውና) በመሰሉ የፈጠራ ትርክት እየጻፉ የኦሮሞን ወጣት ትውልድ አይምሮ ይመርዙ በነበሩ ሰዎች ይመራ የነበረ ድርጅት ነው። ታደሰ ኤባ በዚህ አነስተኛ መጽሃፍ ውስጥ በጻፈው አንድ ሃሰተኛ የሆነ የፈጠራ ትርክት አማካይነት ዐጼ ምንሊክና ተከታዮቻው የሆኑት (የአማራ ነፍጠኞች) አምስት ሚሊዮን ንጹሃን የኦሮሞ ተወላጆችን ፈጅተዋል ብሎ መርዘኛ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በአማራ ህዝብ ላይ ነዝቷል። ባለፉት አምስት ዓመታት በኦነግና ሥልጣን ላይ ባለው የኦሮሞ መንግስት ታጣቂዎች በወለጋ የተጨፈጨፉት አማራዎች የዚህ ሃሰተኛ ትርክት ሰለባዎች ናቸው። ጌታቸው በጋሻው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2011 ብዙ ርቀት ሄዶ በበደኖ፤ በአርባጉጉ፤ በሙጊ (ወለጋ)፤ በሂርና፤ በደደር፤ በጉርሱም፤ በመቻራ፤ በገለምሶ፤ በዴሳ ወዘተ በርካታ ንጹሃን የአማራ ተወላጆችን የጨፈጨፈውን ኦነግን የመሰለ ፋሽስታዊ ድርጅት በዚህ ደረጃ ቢያንቆለፓፕስም ጭራቁ ኦነግ ግን ከፋሽስታዊ ድርጊቱ አለመቆጠቡን ያለፉት አምስት ዓመታት ድርጊቶቹ ፍንትው አድርገው አሳይተውናል። ኦነግ ከወያኔ ጋር የሽግግር መንግሥት መስርቶ ሥልጣን ላይ በቆየበት በ1984 ዓ. ም አካባቢ እኔ ተወልጄ ባደግሁበት በሀረርጌ ክፍለ ሀገር እንደዚሁም የሀረርጌ አጎራባች በሆኑት የአርሲና የባሌ ክፍለ ሀገሮች ውስጥ ታጣቂ አባሎችና አፍቃሪዎቹ “ያ ጀሩ ጀረርቲ አማርቲቲን ነመ ሚቲ” እያሉ በኦሮምኛ ያዜሙ ነበር። የዚህ የኦነግ ተዋጊዎች መፈክር ትርጉም “አማራ ሰው አይደለም፤ ከሰው በታች የሆነ ፍጡር ነው” የሚል ሲሆን አንድምታውም ከሰው በታች ለሆነ ፍጡር ህይወት አትሳሳ፤ አትራራ፤ ግደለው የሚል ነው። ይህ መፈክት ኦነግ እንደ መንጋ የሚከተሉት ተከታዮቹ የሚፈጇቸውን አማሮች እንደ ሰው ፍጡር ሳይቆጥሩ ካለርህራሄ ህይወታቸውን እንዲያጠፏቸው ያደርግበት የነበረ የጭፍን ጥላቻ መፈክር ነው። ይህ የኦነግ መፈክር የጀርመን ናዚዎች ይሁዲዎችን ከሰብዓዊ ፍጡር ያነሱ (unter-mensch=subhuman) ናቸው እያሉ ካለርህራሄ እንዲፈጇቸው ያደረጉበትን፤ ሁቱዎች ቱትሲዎችን (cockroach) ወይም በአማርኛው በረሮ እያሉ እንደ ነፍሳት እንዲፈጇቸው ከቀሰቀሱበት መፈክር ጋር ተመሳሳይነትና አቻነት ያለው ነው። ኦነግም ተከታዩቹ የአማራን ተወላጆች በጅምላ እንዲጨፈጨፉ ያደረገበት ፋሽስታዊ መፈክር ነው። ጌታቸው በጋሻው ኦነግ ከወያኔ ጋር የሽግግር መንግስት ከመሰረተ በኋላ ዛሬ ኦሮሚያ ተብሎ በተከለለት ሰፊ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ኦነግ ስለፈጸማቸው ድርጊቶች ሳይሰማ አልቀረም። ቢያንስ በአርባጉጉና ሀረርጌ ስለተፈጸመው የኦነግ ድርጊት ጌታቸውና እኔ እንሳተፍበት በነበረ Ethiopian Electronic Distribution Network (EEDN) መድረክ ላይ የተለያዩ መረጃዎችን ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ ተርጉሜ የዛሬ 30 ዓመት አካባቢ አሰራጭ ስለነበረ እነሱን እንዳነበበ እገምታለሁኝ። እንግዲህ ይህንን ፋሽስት ድርጅት ነበር ጌታቸው በጋሻው ኦነግ ውስጥ ለውጥ ይታየኛል፤ ኦነግን የመሰለ የዘር ድርጅት ብላችሁ አትቃወሙ፤ አደብ ግዙ በማለት እራሱ ተደናብሮ ሌሎችን ያደናብር የነበረው። ይህንን ድርጅት ነበር ሽንጡን ገትሮ ኦነግ በተባለ ድርጅት ላይ ተስፋ አይቼአለሁኝ እያለ ከ12 ዓመታት በፊት በጽሁፉ ይቀሰቅስ የነበረው። ጌታቸው በ2011 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ባቀረበው ጽሁፍ ውስጥ በበጎ ሥሙን ያነሳውን ኢብሳ ጉተማ የተባለውን ጽንፈኛና በጥላቻ ያበደ ግለሰብ መጽሃፍ እንኳን አገላብጦ ያነበበ አይመስለኝም። ለማንኛውም የቅርቡን ነገር እየረሳን ሥቃያችንን ስላበዛነው ጌታቸው በጋሻው እውቀት ላይ ያልተመሰረተ ድፍረት በሚፈጥረው እርግጠኛነት ህዝባዊ መድረክ ላይ ወጥቶ ኦነግን ለዲሞክራሲና ለእኩልነት የሚታገል ድርጅት አድርጎ የተናገረውን ከዚህ ቀጥሎ በማቅረብ አንባቢ እንዲመለከተው እጠይቃለሁኝ። ይህንን የማደርገው አንድን ግለሰብ ለማብጠልጠል ሳይሆን ለምንናገረውና ለምናደርገው ነገር ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባን ለማሳወቅ ጭምር ነው። ይህ ከተማሪዎችና የግራ ፓለቲካ እንቅስቃሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የቀጠለ ሂደት ነው። ተጠያቂነት (accountability) መቀበልና፤ ለምንለውና ለምናደርገው ነገር ኃላፊነት ልንወሰድ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
“In a nationalist age, societies worship themselves brazenly and openly, spurning the camouflage ጌታቸውም ሆነ ማንም ሌላ ሰው ከዚህ በላይ ለጻፍኩት ተቃውሞ ቢኖራቸው ወይም በግንባር ቀርበው በሰነዘርኳቸው ሃሳቦች ላይ ሃሳባቸውን በክርክር መልክ መግለጽ ቢፈልጉ በፈቀዱበት መድረክ ቀርቤ በሃሳብ ልሞግታቸው ዝግጁ መሆኔን አሳውቃለሁኝ።
እነሆ ጌታቸው በጋሻው በ2011 እ.አ.አ. በመድረክ ላይ ወጥቶ ካደረገው ንግግር ኦነግን የመሳሰሉ የነገድ ድርጅቶችን አስመልክቶ የተናገረው የሚከተለው ነው።
“ሁለተኛ፡ የዘር ድርጅቶች የትግሉ አካል እንዲሆኑ መጣር ያስፈልጋል:: ይህ አዲስ ሀሳብ አይደለም፣ ያልተጀመረ ሙከራም አይደለም። በዚህ ረገድ ድርጀት ለድርጅት ውይይት ለጀመሩትና አንዳንድ ትብብሮችን እያሳዩ ላሉት የፖለቲካ ኃይሎች፣ ማለትም ለግንቦት 7፣ ለኦነግ፣ ለኦብነግ፣ ለአፋር ድርጅትና ተባባሪ ለሆኑት ሌሎችም ያለኝን ምስጋናና አድናቆት ለመግለጥ ይፈቀድልኝ።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የዘር ድርጅቶችን፣ በተለይም ኦነግን፣ እንደ ፀረ-አንድነትና እንደ ጠላት በመፈረጅ፣ ምናልባት ወንዝ ለማታሻግር ትንሽ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ለመሸመት ባዶ የመግለጫ ጋጋታና ፍሬ-ቢስ ጫጫታ የሚረጩ እንዳሉ መገንዘብ ይበጃል። በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሕዝብ መሀል ጥላቻን የሚዘሩና በድርጅቶች መሀል ሊኖር የሚችለውን መግባባትና መተባበር ለማደፍረስ የሚያከሄዱት ኃላፊነት የጎደለው ተግባራቸውም ሊጋለጥ ይገባል።
(ሀ) አደብ ይገዛ
በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ድርጅቶችንና ድርጅቶቹ እንወክላቸዋለን የሚሏቸውን ዜጎች ያላካተተ እንቅስቃሴ ከጅምሩ የከሸፈ ሙከራ ይሆናል። የዘር ድርጅቶች ትግላቸውን የጀመሩባቸው ታሪካዊ ምክንያቶች እንዳሏቸው አለመገንዘብና እንኝህን የዘር ድርጅቶች የመግፋትና የመተንኮስ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አንድነት ከሁሉም የባሰ አደጋን ያረገዘ ቀቢፀ ተስፋ ፖለቲካ መሆኑን መረዳት የግድ ይሆናል። አሁን፣ በዚህች ሰዓት፣ ይህችን ጽሁፍ በምናነብባት ሰዓት እንኳን፣ ወያኔ በኢትዮጵያ መንግስትነት፣ ሲያስቡት የሚሰቀጥጥ ግፍና ጭቆና፣ ግድያና ማፈናቀል በኦጋደን፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ ውስጥ ባሉ ወገኖቻችን ላይ እያካሄደ ባለበት ሰዓት፣ ረሀብንና ምግብን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ በሕዝባችን ላይ እየተጠቀመ በዜጎች ስቃይ እየተደሰት በሚገኝበት ሰዓት፣ ሳይቸግር የዘር ድርጅቶችን ማውገዝና በጠላትነት መፈረጅ የዘመኑ ታላቅ የፖለቲካ ክስረት ከመሆኑ ሌላ የጨካኝ አረመኔ ባህሪይ ሆኖ ይታያል።
ለመሆኑ፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነኝህ “በኢትዮጵያ አንድነት” ስም ይህንን ያህል የዘር ጥላቻ የሚነዙ ከፋፋይ ኃይሎች ዛሬ ማን ሆነው ነው፣ ዬት ቆመው ነው፣ ማንን ይዘው ነው የዘር ድርጅቶችን እንዋጋቸዋለን የሚሉት? ለአገር አስባለሁ የሚለው ወገን እውነት ለአገር አሳቢ ከሆነ በመጀመሪያ የራሱን ድርጅታዊ ድርሻና አቅም ከነዚህ ሁሉ የዘር ድርጅቶች ጋር አነጻጽሮና አወዳድሮ ይመለከታል፤በዚያም የሚናገረውን ይመጥናል፤ የሚጽፋቸውና የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች በሕዝበ የወደፊትና የዛሬ ህይወት ላይ ምን የፖለቲካ ውጤት እንደሚኖራቸው ይመረመራል፣ በዚህም ኃላፊነትን ይወስዳል። እስቲ ስለ እውነት እንጠይቅና ከእነኝህ ድርጅት ኮናኞች ውስጥ ዬትኛው “የአንድነት ኃይል” ነው፣ ዛሬና ወደፊት፣ ይህን የሚቀፈቅፈውን የጠላትነት አቋሙን ይዞ ኦሮሚያና ኦጋዴን ተብለው በተከለሉ ግዛቶች ውስጥ ሄዶ ለማደራጀት፣ ለመመልመል ለማስታጠቅና የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ የሚችለው? ምነው ሁኔታዎችን ቢለዩና የሚናገሩትን ቢያውቁ፤ ምነው አቅማቸውን ቢመዝኑና አደብ ቢገዙ።”
ክፍል ሶስት ይከተላልና ይጠብቁኝ።