በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ..! ከሁሉም በፊት

July 31, 2023

T.G

ከሁሉም በፊት ሁሌም የማምንበትን አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ። የተሳሳተ አስተሳሰብና አካሄድ ሰለባ ሆኗል ብለን በምናስበው ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ ሂሳዊ አስተያየት ለመስጠት (ለመሰንዘር) የግለሰቡ ወይም የቡድኑ አባላት የእድሜ ቁጥር (አዛውንትነት)፣ የዓለማዊውም ሆነ የሃይማኖታዊ እምነት ምሁርነት (ዶክተርነት/ፕሮፌሰርነት/ልሂቅነት/ሊቀ ሊቃውንትነት) ፣ ፓትርያርክነት፣ ሊቀ ጳጳስነት ፣ ጳጳስነት፣ ፓስተርነት፣ ካርዲናልነት፣የመጅሊስ መሪነት፣ ፕረዝደንትነት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ ወዘተ በራሳቸው መመዘኛዎች ሊሆኑ አይገባም የሚል ፅዕኑ እምነት ካላቸውና ከሚኖራቸው ወገኖች አንዱ ነኝና ይህ ሂሳዊ አስተያየቴም ከዚሁ አንፃር እንዲታይ ለማስገንዘብ እወዳለሁ።

“ኮሜዲያን” እሸቱ በማህበራዊ ሚዲያው (ዶንኪ ቲዩብ) ለ11 ቀናት (በትክለኛው አቆጣጠር 15 ቀናት ነው) ሲካሄድ ከሰነበተው የገዳም እዳ ክፍያ ገንዝብ ማሰባሰብ ዘመቻ  “በረከት” እንድንወስድና አስተያየታችንም እንድንሰጠው ደጋግሞ ጠይቋል። ጥያቄውና ግብዣው በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ መልካምና ተገቢ ነውና ለመቀበል አያስቸግርም።

የአስተያየቴ ትኩረትና ማጠንጠኛ የትኛው ግለሰብ ወይም ቡድን አገራዊና ተቋማዊ የሆኑ የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ምን አይነት ሃሳብ አራመደ? ምን አይነት ስህተት ሠራ? ለምንና እንዴት? ምንስ መደረግ አለበት? እንጅ የግል ማንነትንና ህይወትን የሚመለከት እስካልሆነ ድረስ አካፋን አካፋ እስከማለት መሄድ ትክክል ነው የሚል ነው።

በየትኛውም የሙያና የሥራ መስክ ፍፁምነት (ምልዑነት) የማይጠበቅ የመሆኑ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖታዊውም ሆነ የዓለማዊው እውቀት ባለቤትነት ማለት ከመማር፣ ከተግባራዊ ተሞክሮ እና ከህይወት ልምድ የተገኘውን እውቀትና ክህሎት በአጥጋቢ ሁኔታ የመረዳት ፣ የማስረዳት እና ለሰው ልጅ ህይወት የማያቋርጥ ደህንነትና እድገት የሚበጁ የመፍትሄ ሃሳቦችንና ዘዴዎችን አምጦ የመውለድ ፍላጎትና ዝግጁነት ማለት ነው።ለዚህም ነው ትምህርት አስከፊ ሁኔታን ለመዋጋት አይነተኛ መሣሪያ (education is the means to fight against catastrophe) ነው የሚባለው።

ይህ ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሠረተን የቅድሚያ ቅድሚያ ርብርብንና አርበኝነትን (priorities -focused and patriotic operation) ይጠይቃል በእንዲህ አይነት በእጅጉ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኝ ህዝብ (ማህበረሰብ) ከሚያስፈልጉት እጅግ ወሳኝ (extremely critical) የድጋፍ አይነቶች  መካከል በሃይማኖት ተቋማት የሚቀርቡ የማቴሪያል፣ የመንፈሳዊና የሞራል ድጋፎች  የመሆናቸው እውነታ የሚያጠያይቅ አይደለም።

እናም ራሳችንን ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ  ስም እያታለልን ለመቀጠል ካልፈለግን በስተቀር  ወድቀናልና በቶሎ ራሳችንን እንመርምር ።

እጅግ ፈታኙ ጥያቄ በአንድ በኩል አገር (ህዝብ) በባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች እና እነዚህኑ ጨካኝ ቁማርተኛ ዥዎች ለመገሰፅ (አደብ ግዙ ለማለት) ወኔው በከዳቸው አድርባይ (መስሎና አስመስሎ አዳሪ) የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ምክንያት እጅግ  አስከፊ የውድቀትና የመከራ ዶፍ ውስጥ የመገኘቱን መሪር እውነታ እና በሌላ በኩል ደግሞ በአሜሪካ የሚኖረው ዳያስፖራ እንደማነኛውም የማህበረሰብ ክፍል በራሱ ድክመትም ይሁን ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት የሚያጋጥሙትን ማህበራዊ ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ህፀፆች በእጅጉ በመለጠጥ (በማጦዝ) ገዳም መገደምን ፋታ የማይሰጥ ጉዳይ እያስመሰሉ ዶላር ካልሰጣችሁን የገነት በር ይጠረቀምባችኋል የሚለው ዘመቻ የሚነፃፀሩ ናቸው ወይ ? የሚለው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከግብረሰዶማውያኑ ጀርባ  (አርአያ ተስፋማሪያም)

በአሜሪካ (ካሊፎርኒያ) ይሠራል ለተባለው ገዳም ለ15 ቀናት በእሸቱ ሚዲያ (ዶንኪ ቲዩብ) የተካሄደው የዶላር ስጡና በረከት ውሰዱ ዘመቻ መታየትና መገምገም ያለበት ከዚሁ መሠረታዊና ፈታኝ እውነታ አንፃር ነው። ከዚህ እጅግ ግዙፍና መሪር የአገር ቤት እውነታ አንፃር ነው ዘመቻው የተሳካ አልነበረም ማለት ትክክል የሚሆነው።በአምሳሉ የፈጠረው ህንፃ (የሰው ልጅ) በግፈኛ ገዥዎችና አደራ የተሰጧቸውን በጎችን ነቅቶ ለመጠበቅና አስፈላጊም ከሆነ መስዋእትነት (ሰማእትነት) ለመክፈል ወኔው በከዳቸው የሃይማኖት መሪዎች ምክንያት እንዳልነበረ  በመሆን ላይ በሚገኝበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት ታሪካዊ ለሚሆንና ኢትዮጵያን ለሚያስጠራ የባህር ማዶ ገዳም የቅድሚያ ቅድሚያ ሠጥተን እንሠራለን ማለት የውድቀት እንጅ የስኬት መንገድ አይደለም። የፅድቅ መንገድም አይደለም!

ለነገሩ ይህ ዘመቻ አቅጣጫውንና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረቱን የሳተ እንደነበርና እንደሚሆን የታወቀው የገዛ አገራቸው ምድረ ሲኦል ሆናባቸው በየጎዳናውና በየመጠለያው የሚባዝኑትን ንፁሃን ወገኖች ተዘዋውሮ ያላፅናና እና የመከራውን ስፋትና አስከፊነት ከምር ተረድቶ የምሥክርነቱን ቃል ለማሳወቅ ያልሞከረ የሃይማኖት መሪ አዲስ አበባ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ውስጥ ” እዚህ ያለው ወገንህ ብቻ ነው የሚገድህ? አሜሪካ ያለው ወገንህ አይገድህምን? በሚል ጨርሶ ሊነፃፀሩ የማይችሉ ነገሮችን (ጉዳዮችን) በማነፃፀር የተበሠረ እለት ነበር ።

ልብ በሉ ወገኖቼ!  ለሩብ ምእተ ዓመት የሰቆቃ ህይወት ውስጥ ሆኖ የኖረውንና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኛና እጅግ ጨካኝ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች ለመግለፅ በሚያስቸግር የመከራና የውርደት ዶፍ እየተመታ ያለውን መከረኛ ህዝብ አሜሪካ የሚኖረው ዳያስፖራ ከሚያጋጥሙት ማህበራዊና መሰል ችግሮች ጋር እኩል በማወዳደር እኩል ሊገደን ይገባል ማለት ምን ማለት ነውይህንንስ በእውን ባርኮና ቀድሶ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ አለ ወይ?

መቸም የገዛ ራሳችንን እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ በሰንካላ የሰበብ ድሪቶ እየሸፋፈን በውድቀት አባዜ ውስጥ መጓጓጎጥን ተለማምደነው በመቸገራችን ነው እንጅ አገር ወይም ህዝብ  ለማመን በሚያስቸግር የመከራ ዶፍ እየተመታ በቀጠለበት እግዚኦ የሚልባቸው የሃይማኖት ተቋሞቹ በባለጌና ጨካ ተረኛ ገዥ ቡድኖች እና ሃይማኖታዊ ሃላፊነታቸውን ረስተው የእኩይ ፖለቲከኞች ሰለባ በሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ምክንያት እየተጠቁና መሳለቂያ እየሆኑ ባሉበት እና በአጠቃላይ አገር ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል በሆነችበት  በዚህ አስጨናቂ ወቅት ለባህር ማዶ ገዳም እንቅልፍ ያሳጣ ዘመቻ ማድረግ በፍፁም ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም። በዚህ ሁኔታ የሚመሠረትን (የሚሠራን) ገዳም የሚባርክና ማደሪያው የሚያደርግ እውነተኛ አምላክም የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች የቅስቀሳ ስራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

በአምሳሉ የተፈጠሩ አያሌ ንፁሃን ህይወቶች (የሰው ልጆች) በእኩያን ገዥ ቡድኖች እንዲወድሙ (እንዲፈራርሱ) ሲደረግ ከምር በመቆጣት ከመገሰፅና ከማውገዝ ይልቅ የፖለቲከኞች ሰለባዎች የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ለባህር ማዶ የገዳም ምሥረታና “ልማት” እንቅልፍ አጥተው ሲሰነብቱ መታዘብ ሚዛናዊና ቅን ህሊና ላለው የአገሬ ሰው በእጅጉ ይከብዳል።

ሂሳዊ አስተያየታችን ከግል አልፎ ሰዎችን ወይም ማህበረሰብን ወይም አገርን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚጎዱ ጉዳዮች ላይ እስከሆነ ድረስ እና ተገቢ በሆነ አቀራረብ (በግለሰባዊ ሰብዕና እና ህይወት ላይ ያላነጣጠረ እስካልሆነ ድረስ) የትኛውንም ስህተት ሰርተዋል የምንላቸውን ሰዎች ወይም ቡድኖች በግልፅና በቀጥታ ተሳሳስታችኋልና  አደብ ግዙ ለማለት በፍፁም የተለየ መመዘኛ አያስፈልገንም። ማቆሚያ ላጣው የውድቀት አዙሪት ሰለባዎች ሆነን እንድንቀጥል ካደረጉ ምክንያቶች አንዱም በዚህ ረገድ ያለብን ሽባነት ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የገዛ ራሳችንን የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነት፣ የፅዕኑ መርህ አልባነት ፣ የሞራል ዝቅጠት፣ የሥነ ልቦና ኮስማናነት፣ የመንፈሳዊነት ጎስቋላነት፣በራስ ያለመተማመን ቀውስ ፣ ወዘተ በአርበኝነት አቋምና ቁመና ተጋፍጠን ራሳችንን ነፃ ማውጣት ሲሳነን ለነፃነት፣ ለፍትህ ፣ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለብልፅግና ፣ ወዘተ እውን መሆን እጅግ ታላቅ ኀይል የሆነውን ሃይማኖታዊ እምነት መደበቂያችን ብቻ ሳይሆን የድክመታችንና የውድቅታችን ማስተባበያ አድርገነዋል። አዎ! በእንዲህ አይነቱ የተዛባ ሃይማኖታዊ ማንነታችንና እንዴትነታችን ምክንያት ነው ፈጣሪም በጭንቀታችንና በመከራችን ፈጥኖ ለመድረስ የተቸገረው።

አዎ! በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እና ግብረ በላዎቻቸው ፣ የቁም ሙት በሆኑ የተቀዋሚ ፖለቲካ መሪዎች፣ ፈጣሪን የእኩይ ገዥዎች ቤተ መንግሥት አማካሪ ለማድረግ በማይገዳቸው የሃይማኖት ነጋዴዎች ፣ የመማርን ትክክለኛ ትርጉምና ዓላማ ስንኩል ባደረጉ ልሂቃን ተብየዎች ፣ ወዘተ ምክንያት በፈጣሪ አምሳል የተፈሩ ንፁሃን ወገኖች ህይወት እንዳልነበረ እየሆነ ባለበት እጅግ አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ ወቅት የሚገነባን የገዳም ህንፃና የሚዋብ ግቢ ማደሪያዬ ነው ብሎ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ ይኖራል ብሎ ለማሳመን የሚያስችል አንዳችም እውነታ የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ

እሸቱ ዘመቻውን ሲጀምር የዩቲሊቲን (የልዩ ልዩ አገልግሎቶችን) ጨምሮ ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ በብዙ ሳምንታት ሳይሆን በተወሰኑ ሰዓታት ወይም ቢበዛ በተወሰኑ ቀናት ውስጥ ማስገኘት በጣም ቀላል እንደሆነ ራሱንና አስተባባሪዎችን (የሃይማኖት መሪዎችንም ጨምሮ) አሳምኖ የጀመረው በመሆኑና ይህ ግን ከብዙ ቀናት የ24 ሰዓት የተማፅኖ ዘመቻ በኋላም ባለመሳካቱ ቢያንስ 5 ሚሊየን ካልሞላችሁ የእግዚአብሔረ በረከት አይጠጋችሁም በሚል የአቀራረብ ስልት ዘመቻው እንዲቀጥል በማድረግ ወደ 5 ሚሊየን ለማስጠጋት ሞክሯል።

ጉዳዩ ከብሩ ማነስና መብዛት ላይ ብቻ አይደለም። የመከረኛ ወገንን የድረሱልኝ ጩኸት “ውራጅ ልብስና ለተወሰኑ ቀናት የሚሆን ደረቅ ዳቦ ሰጥተን እያለንና  ወደ ፊትም ልንሰጥ እንደምንችል  እየተናገር  የእግዚአብሔር ማደሪያ ለሚሆን ገዳም  ቅድሚያ ሰጣችሁ ብላችሁ አትጠይቁን” የሚል አይነት መከራከሪያ ማስተጋባት የአስቀያሚው ወለፈንዲነታችንን ( our own ugly paradox) ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የለውም። የባእዳንን የምፅዋእት እጆች በመጠባበቅ ላይ እያለች ማደሪያ ሥጋ አጥታ ነፍሱ የምትለየውን ወገን “ትናንት ይህንን ያህል ሳንቲም ሰጥቸልሃለሁና ዛሬ የገዳም ምሥረታ ተራ ነው” የሚል የሃይማኖት መሪና አስተማሪ የራሱን ህሊና ከምር ሊመረምር ይገባል።

በዚሁ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ሂደት ወቅት የማያቋርጥ የግፍ አሟሟትና የቁም ሙት የሚሆኑትን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችን ሁኔታ የሚያወሳ (የሚያሳስብ) አንደበት አልሰማንም ። እናም የመከረኛ ወገኖችን የድረሱልን ጩኸት የቁራ ጩኸትን ያህል እንኳ ሳይገደን የእግዚአብሔር ማደሪያና ለራሳችንም ማረፊያ ገዳም ለማሠራት በነፍስ ውጭና በነፍስ ግቢ ዘመቻ ላይ መሠማራታችን የሚነግረን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚባል ነገር አለማወቃችንን ወይም እያወቀን በራሳችን ግልብ ስሜትና ፍላጎት የምንነዳ የመሆናችን መሪር ሃቅ ነው።

መወለድ ሳይፈልግ ከመከረኛ እናቱ የተወለደውና የሠርቶ አዳሪ ባልደረቦቹን መበት ለማስከበር ባደረገው ጥረት ተወንጅሎ የሞት ፍርድ የተፈረደበት የአቤ ጎበኛው አልወለድም “በቤተ ክርስቲያናችን መካነ መቃብር አይቀበርብንም” እያሉ ላጉረመረሙት ቄሶች የማያወላዳ ምላሽ ከሰጣቸው በኋላ ለተራው ህዝብ (አማኝ ወገኑ) ያስተላለፈው መልክእክት ” ወዮላችሁ ተራህዝብ ለሆናችሁወገኖቼ! በጡንቻውናባበጠቦርሳው የሚመካሁሉ ለባርነት ለሚያጫችሁ ምስኪኖች ወዮ!” የሚል ነበር ነበር ።

ዛሬስ? መልሱን ለአንባቢ ትቸዋለሁና ልብ ያለው ልብ ይበል!

 

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share