የመለስ ሞት የኢትዮጵያን ህዝብ ለምን አስለቀሰው?

‘አዲስ ራዕይ ጥቅምት 2005 ልዩ እትም’ን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ፡ ክፍል 1

በደሳለኝ ቢራራ

መግቢያ

አቶ መለስ ዜናዊ በዋና አዘጋጅነት ሲፅፋት የነበረችው በራሪ መፅሔት ዛሬ ስለአዘጋጇ መታሰቢያ ተደርጋ ታትማለች። የዚች እትም ትኩረት የአቶ መለስ አስተምህሮዎችና ስራዎቸ እንዲሁም በግለሰብ ስብእናው ዙሪያ ነው። እናም “አቶ መለስ ማነው?” ሲሞትስ “በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ሚሊዮኖች ያለቀሱለትና በእንባ እየተራጩ የሸኙት ማን ቢሆን ነው?” ብሎ በማጠየቅ ይጀምራል። የመለስን ለቅሶ “በዓለም ታይቶ የማይታወቅ” የሚለውን ግርድፍ ድምዳሜ መሞገቱን ልዝለለውና አዘጋጆቹ ለጠየቁት ጥያቄ እራሳቸው ወደሰጡት መልስ እና ሀተታ ልቀጥል።

“እኛ የአዲስ ራዕይ ዝግጅት ክፍል አባላት ይህን ጥያቄ በማንሳትና መልሱንም በማፈላለግ መፃፍ የመረጥነው በመለስ ማንነትና ስብእና ላይ ብዥታ ስላለን አይደለም!” በማለት ስለመለስኮ አናውቅም ቢሉ ኖሮ ከሚመጣባቸው ዱላ እራሳቸውን ለመከላከል ይጥራሉ። በተለይ ‘ብዥታ አለብኝ’ ማለት አለማወቅን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ አፈንጋጭነት ሊተነተን የሚችል ችግር ስለሆነ የገባውንም ያልገባውንም ነገር ‘ፍንትው ብሎ ታይቶኛል፤ አብጠርጥሬ አውቀዋለሁ’ ለማለት ያስገድዳል። በህወኃት ወይም ኢህአዴግ ቤት እስካለ ድረስ አንድ ሰው ብዥታ ገጥሞኛል፥ አልገባኝም ማለት አይችልም። በጥርጣሬ ዐይን መታየትን የሚወድ አይኖርምና በግድም ቢሆን የተሞሉትን ትርክት ‘እውነት’ ብለው ተጠምቀውት እንደነበረ የሚያስተባቃ ሰውየው ሙቶም የሚገዛቸው መንፈስ ነበር። በመሆኑም አዘጋጆቹ ስለሚፅፉት ታሪክ እውነትነት ሳይሆን እራሳቸውን ከአደጋ ስለመከላከል አበክረው ማብራራታቸው የአገዛዙን ባህሪ አስረጅ ነው።

“መለስ በዘመን ላይ ተፅዕኖ ያሳረፈ የዘመን ውጤት” ነው በማለት ሀተታ የጀመሩት አዘጋጆች ለጥቀው “በአርአያ ስላሴ ተፈጠርን ከምንል ሰዎች ልቀውና መጥቀው ታሪካዊ ዓለማዊ ስብእና ያላቸው. . .” እያሉ ይገልፁታል። ወደ አምላክነት ያጋሽቡታል። እነዚህ ሰዎች የመለስን ታሪክ ሰውየው በህይወት እያለ አዘጋጁ ተብለው ቢሆን ኖሮ ‘ከስላሴም በላይ ልቀውና መጥቀው’ ሊሉ እንደሚችሉ ጥርጥር የለኝም።

ቀጥሎም ፍሬደሪክ ሄግልን በማጣቀስ እንደ መለስ አይነት ሰው “የዚህ አይነት ታሪካዊ ዓለማዊ ምጡቅ የታሪክ ስብእና ከአፍሪካ አይፈልቅም!” በማለት አጉራ ዘለል ድምዳሜ ይከምራሉ። ለዚህ የስብእና ደረጃ መለኪያ አድርገው ያስቀመጧቸው ጉዳዮችም አሉ። የአቶ መለስን ስብእናና ታሪክ ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ ለመግለፅም እንደተለመደው በሀገራችን ታሪክ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ነገስታት በማጠልሸት ከጥቁር ታሪክ ላይ በነጭ ፅፈው ለመጉላት ይሞክራሉ።

“ግለታሪካቸውን በስንክሳርና በዜና መዋዕል ፀሐፊዎች እየታገዙ በመጻፍ ታሪካቸውን የሚያስጠርዙ መሪ አልነበሩም አቶ መለስ” ይላሉ አዘጋጆቹ ምስክርነት ሲሰጡ። በሀገሪቱ ያሉ የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሀን እንዲሁም በሀገራችን ፈቃድ ተሰጥቷቸው የሚዘግቡ የውጭ ሀገራት ሚዲያ አካላት በመለስ ዙሪያ ማይኮቻቸውን አጥረው የሚውሉትን በድሀ አጥር ላይ የተንዠረቀቀ የኮሽም ቅጠል ነው ሊሉን ይዳዳቸዋል። ከስንክሳርና ዜና መዋእል በበለጠ እነዚህ አዘጋጆች በአፍጢም እየተደፉ የሚጽፉበት አዲስ ራእይ አይበልጥሞይ? ከመለስ በላይ ታሪኩን ለማስጻፍ ድርጅቶች የከፈተስ ማነው? የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን በሙሉ የማን ዜና መዋዕል ሆኑና! ከህገመንግስት እስከ ቀበሌ መንግስታዊ ቡድን ቃለጉባኤ ድረስ የማን ስንክሳር ሆነና!

የመለስን ምጡቅነትና ስብእና ለመግለፅ ቃላት ከቁፋሮ ግኝት ተፈልገው የተገጣጠሙበት በሚመስል ደረጃ “ድንበርና ጠፈር ሳይከልላቸው፥ ዘር፥ ብሔር፥ ዕድሜ፥ ፆታ፥ ሐይማኖት፥ እምነት፥ ቦታ እና ጊዜ ሳይገድባቸው ለሁሉም ህዝቦች የሚመቹ፥ የሚጥሙና በልቡናቸውም ውስጥ የሚቀመጡ መሆናቸው ነው” ይላሉ። በእንተ እግዝትነ ማርያም መሀረነ ክርስቶስ!!! ሌላ ምን ይባላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብአዴን ሆይ! ነፍስ ይማር!!

ሀቁማ ቢያንስ ቢያንስ መለስ የብሔር ፖለቲከኛ ነው። የአንድ ብሔር ነጻ አውጭ ግንባር ሊቀመንበርም ነው። ስለዚህ ሰውየው ከሌሎች ሰዎች ሁሉ እጅግ በጣም የተለዬ ፍጡር ቢሆን እንኳ በዘር፥ በብሔር፥ በድንበር፥ በቋንቋ፥ ወዘተ የተገደበ አላማና ተልእኮ ነው የነበረው። በተጨማሪም ሰውየው እንደማንኛውም ሰው ደግሞ ሰው በመሆኑ በጊዜ እና በቦታ የተገደበ ተጽዕኖ ነው ያለው። ለዚህም ነው የሞተው፤ ለዛውም በድንጋጤ ነው የሞተው። አልፋና ኦሜጋ የሚመስላቸው ለአዲስ ራእይ አዘጋጆች ነው።  እንደዛ አይነት ሰው የለም። ሁሉም ሰው ዘላለማዊነትና ሁለኑባሬያዊነት የለውም። ሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ ብቻ የሚገኝ ህይወቱም በተወሰነች ጊዜ ገደብ የተወሰ ነው። መለስ አጋንንት ካልሆነ በስተቀር ከሰዎች ተለይቶ በተመሳሳይ ሰአት በሁሉም ቦታ ሊገኝ አይችልም፤ ዘላለማዊም ስላልሆነ ሙቷል። ዘረኛ ስለነበረም በቋንቋ ከፋፋይ ስርአት ተክሏል። ክፉ ስለሆነም ህዝቦችን በብሔር ለያይቶ የሚገደሉበትን የጥላቻ ትርክት ስር እንዲሰድ አድርጓል። ጠባብ ጎጠኛ ስለሆነም ከትግራይ ለመጡት የራሱን ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች እንኳ በእኩል አይመለከትም። ቅድሚያ የሚሰጣቸው የአድዋ ተወላጅ፥ ከዛ በኋላ የእንደርታ ተወላጅ፥ ከዛ ቀጥሎ የአክሱም ተወላጅ እያለ ደረጃ ያወጣ ነበር። በተዘረዘረው የአዘጋጆቹ ቃል ሁሉ መለስ ይሰደብበታል እንጅ አይሞገስበትም። ለአንዱም መገለጫ የሚሆን ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም።

ነገር ግን መለስን “ለሁሉም ህዝቦችና ብሔሮች የሚመቹ፥ የሚጥሙና በልባቸው የሚቀመጡ ናቸው” ያሉት ዋናውን ቁም ነገር ያዘለ ሁኖ አግንቸዋለሁ። ከሰውየው የሞት ዜና መነገር በኋላ ከተስተዋለው የህዝብ ለቅሶና ሲወረድ የነበረ ሙሾ ምን እንደሆነ እና ለምን እንደሆነ ለመመርመር አስችሎኛል። እናም ‘የመለስ ሞት ሀገርን በሙሉ ያስለቀሰው ምን አይነት ሰው ቢሆን ነው’ የሚለውን ለመረዳት ሀቁን እይታ አክለንበት ወደ አዘጋጆቹ ዲስኩር እንመለሳለን።

የመለስ ሞት የኢትዮጵያን ህዝብ ለምን አስለቀሰው?

አቶ መለስ በሞተ ጊዜ የተደበላለቀ ስሜት ተፈጥሮ ነበር። መጀመሪያ ላይ መሞቱን ማመን ከባድ ነበር። ምክንያቱም አቶ በረከት በሚሰጠው መግለጫ “ጠሚሩ በጥሩ ደህንነት ላይ ናቸው፤ በቅርቡም ወደ ስራ ይገባሉ” ምናምን እያለ ህዝቡን ያወናብደው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ የነበረው ኢሳት ቴሌቪዥን የአቶ መለስን መሞት ዘግቦታል። በወቅቱ ማንኛውም የኢትዮጵያ ባለስልጣን ከሚሰጠው መግለጫ ይልቅ የኢሳት ዜና ተአማኒነት ነበረው። እውነትና ንጋት መገለጡ አይቀርምና የኢሳት ዜና የአቶ በረከትን መግለጫ ትቢያ ደፍቶበት፡ የአቶ መለስ መሞት እውን ሁኖ እሬሳው ወደ ሀገር ሲገባ ለማየት ቻልን። ነገር ግን የባለስልጣኑን መግለጫ ላለማቃለል ይሁን የኢሳትን ዜና ለማስተባበል ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት እሬሳው ወደ ሀገር የገባው ብዙ ቀናትን ቆይቶ ነበር። ሆኖም በዓለም ዙርያ ያሉ ትግሬዎች ሁሉ በመሪር ሀዘን አልቅሰዋል። አዲስ አበባም በየቀበሌው ድንኳን ጥለው፥ በየመንደሩ ጥሩንባ እየተነፋ እና በመኪና ሞንታርቦ ጭነው እየዞሩ በመልፈፍ ለቅሶ ጠርተዋል። በእየድንኳኖቹም አቴንዳንስ እየተያዘ (ለቅሶ የተገኘ ሰው ለመገኘቱ ማረጋገጫ ፊርማውን እያስቀመጠ) ተለቀሰ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መንግስት የሙት ዓመትና ተዝካር ማለት ትቶ ትኩረቱን ለሐገራዊ መግባባት ቢሰጥ – ግርማ ሠይፉ ማሩ

ይህ በአዲስ አበባ እና በትግራይ የተደረገው የለቅሶ መርሃግብር በሌሎቹም ሁሉም ክልሎችና ከተሞች እንዲከናወን በየቀጠናው የተቀመጡ የህወኃት እንደራሴዎች በአስፈጻሚነት ተሰማሩ። ለበታቾቻቸው የወረዳና ቀበሌ ተላላኪዎችም ህዝቡን ለመቀስቀስና ለማስተባበር አቅጣጫ ተሰጣቸው። እነዚህ ኃይሎች ተጣምረው ህዝብን የፍጥኝ በመያዝ የሚፈልጉትን ነገር ለማስደረግ ባላቸው ልምድ ልቅሶውን በየአደባባዩ እየተዞረና ደረት እየተደቃ ሲለቀስ በቪዲዮ ተቀርጾ ለታሪክ እንዲቀመጥና በቴሌቪዥንም ቀጥታ ስርጭት እንዲተላለፍ አደረጉ።

ብዙ ሰዎች ከልባቸው አለቀሱ። በርካቶች የቀበሌያቸውን፥ የጎረቤታቸውን፥ የቤተሰባቸውን እንኳን ሳይቀር ደህንነትና ጥቅም አሳልፎ በመስጠት በህወኃት ጥላ ስር ተጠልለው ኑረዋል። የመለስ ሞት ደግሞ የዚህ ጥላ መገፈፍ ነውና መድረሻ የሚያጡ ባህር የሚውጣቸው፤ ሲያስገድሉት የኖሩት ህዝብ በአንዴ ቆራርጦ የሚጥላቸው ስለመሰላቸው ሆዳቸው ባብቶ ነበርና አምርረው አለቀሱ።  በ8ኛ ክፍል ትምህርት በተለያዬ መስሪያ ቤት የክፍል ኃላፊዎች ተደርገው፥ በፎርግድ ማስረጃ ተቆልለው እንዳሉ ውስጣቸው ያውቃልና፥ ህወኃት ከወደቀ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት በያዙት መደብ የሚያስቀጥላቸው የለምና፥ ከሞቀ ከተደላደለ ኑሮ ወደ ተጠያቂነትና ዘብጥያ ሲወርዱ ይታያቸው ነበርና፥ በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ስለፈጸሙት ግፍና በደል ለፍርድ መቅረባቸውን ባሰቡት ጊዜ በየመንደሩ ጥቁር ተከናንበው ሙሾ እያወረዱ መሪር ለቅሶ አልቅሰዋል።

ሁለተኛው የአልቃሾች አይነት በሰፊ አውድ በጥልቀት የሚታይ ይሆናል። አቶ መለስ “አከርካሪውን ሰብሬ እንደ ሲጋራ ቁሮ ረግጨ ገድየዋለሁ፤ ቀብሬው ከመቃብሩ ላይ ቁሜአለሁ” ያሉት ህዝብ ገዳዩን ሲሞት አዬና አለቀሰ። ዕብሪተኛ ተመጻዳቂና በቀለኛ ገዳይን ከሁሉም በላይ የሚበቀል፥ የመግደል አቅም ስላለው የእግዚአብሔር ኃይል አለቀሰ። አንገቱን ደፍቶ የኖረ ህዝብ ቀና ብሎ አለቀሰ። ይህም ከልብ የመነጨ ለቅሶ ነበር።

ትግሬዎች እንደሚሉት “እግዚአብሔር ዘፈን ሲያምረው ትግሬን ያጠግባል፡ ለቅሶ ሲያምረው ደግሞ አማራን ይገድላል” እየተባለ የአማራን ሞት መሳለቂያ ከማድረግ አልፎ አማራን መግደል እግዜርን ማዝናናት እንደሆነ በሚያስረዳ ደረጃ ሞታችንን ያረከሱትን ሰዎችም ገድሎም ለቅሶን አሳዬን። በአማራ ሞት ብዙ ተዘብቷል፤ ብዙም ተተርቷል። ከሁሉም በላይ ግን የአማራ ሞት የአምላክ መደሰቻ ነው የሚል ትርጉም በስሪት ደረጃ መለማመዳቸው የህልውናችን ውጋት ነበር። የማን ሞት ከማን ሞት ያንሳል? ለቅሶ ለአማራ የተመደበ ማህበራዊ እውነታ ስለነበር ለቅሶን ለእኛ የመደበልን ሰው ሲሞት የእኛም ነባራዊ ሁኔታ ሊገለበጥ እንደሚችል ባሰብን ጊዜ ብዙዎቻችን የእምነት ተስፋ እንባ አስገንፍሎብናል። በርካቶችን ያስለቀሰው ለማልቀስ የተሰጣቸው ትእዛዝ ሳይሆን የዚህ ስርአት መልክ ሊቀየር ነው የሚል ተስፋ ነበር። የህዝቡን ለቅሶ በዚህ ልክ ካየነው ወደ አዘጋጆቹ ቀጣይ ጥያቄ ደግሞ እናምራ።

“መለስ ምን አይነት ሰው ነበር?”

ከህዝቡ ማልቀስ በመቀጠል አዘጋጆቹ በጥያቄ ማዳበር የፈለጉት የመለስ ማንነት የሚለቀስለትና ድጋሜ ሊገኝ የማይችል ምጡቅነቱን ነው። አዘጋጆቹ “መለስ ሁሉንም ሰው የሚወዱና የሚወዳቸው፡ ለሁሉም የሚመቹ፥ በሁሉም ዘንድ ከልብ የታተሙ ናቸው” ይሉታል።

ወደ እውነታው ሲገባ፡ አቶ መለስ ስለሚጠላው ነገር እንጅ ስለሚወደው ነገር አንዴም ተናግሮ አያውቅም። እራሱ ስለሚወደው ነገር ሳይናገር አዘጋጆች ከየት አምጥተው “የሚወደው ነገር” እንዳሉ፡ ለዛውም ግለሰቡ አምርረው የሚጠሉትን የኢትዮጵያን ህዝብ ይወዱት እንደነበር ለማብራራት መሞከር ‘ከባለቤቱ በላይ ያወቀ ቡዳነት’ ነው።   እነ አቶ መለስ የሚጠሉት ነገር እንጅ የሚወዱት ነገር ትኩረት ስለማይሰጠውም ነበር ከአይዲዮሎጅ እስከ ፖሊሲና ስትራቴጅ ድረስ የጥላቻ ማስፈጸሚያ መዋቅሮች፥ ስሪቶችና እሴቶች የተንሰራፉት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦ - ብልፅግና. . . . አ - ብልፅግና (ኤፍሬም ማዴቦ)

አቶ መለስ በሚመሩት ህወኃት ድርጅታዊ ሰነድ (የትህነግ ማኒፌስቶ) በስፋት ተብራርቶ የተቀመጠው ስለሚጠሉት ነገር ነው። ስለሚወዱት ነገር የተጻፈ ምን አለ? ይህ ድርጅታዊ ጥላቻ በመለስና በጓዶቹም ልብ ተኮትኩቶ አድጎ፥ ታትሞ እንደኖረ ገሀድ ነው። በእርግጥ አዘጋጆቹ ይህን እውነት እንዲጽፉት አይጠበቅም፤ ቢበዛ እንዲዘሉት እንጅ። በመለስ ልብ ታትሞ ስለኖረው ጥላቻ እና የበቀል ሴራ እንጅ እርሱ በሌሎች ልብ ላይ ስለመታተሙ የሰነድም ሆነ የአካል ማስረጃ አያቀርቡም።

ስለዚህ መለስ ጥላቻን የጻፈ፥ ለበቀለ የዘመተ ገዳይና አስገዳይ አውሬ ከመሆኑ የተለዬ ስለስብእናው መጻፍ ይቸግራል። ሰውየው ለብዙ ሽህ ዘመናት አብሮ ይኖር የነበረን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ፡ የሌላ ዘውግ ብሎ ያሰበውን አንጡራ እና መሬት በመዝረፍ የራሱን ዘውግ ለማበልጸግ የተጋ፥ የነጻነቲቱን ምድርና ህዝብ ደፍሮ ያስደፈረ፥ የባንዳ ውላጅ፥ የታሪክ አተላ ነው። የአቶ መለስ እና የነስብሀት ነጋ ቤተሰብ ከቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ ጠላትን እየመሩ ወደ መሀል ሀገር በማስገባት ኢትዮጵያዉያንን ሲያስጠቁ ስለነበር ማህበራዊ መገለል ተደርጎባቸው፤ ከነርሱ የተጋባም “ውሻ ይውለድ” ተብሎ ተገዝቶ መኖሩ የታሪክ እውነት ነው። የልጅ ልጆቻቸው ህወሃትን ከመሠረቱት ጀምሮ የበቀል አላማ የሰነቁ ናቸው። ከፍተኛ ጥላቻ አለባቸው። እራሳቸውንም ዝቅ አድርገው ነው የሚያዩት፥ ሊፍቁት የማይችሉት የባንዳ ልጅነት ነውና ምንነታቸው። እናም መቼም ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን አይቀበሉትም።

የአቶ መለስ ባህሪም ከዚህ ታሪካዊ ዳራ ጋር የተሰናሰለና አመክንዮአዊ ግንኙነት ያለው ስለሆነ ነው ስለሚጠላው እንጅ ስለሚወደው ነገር እንዳይናገር ያደረገ፡ እድሜልክ አፍኖ ያኖረው ጥላቻ ቂምና የበቀል መንገድ የተከተለው። የባንዳ ታሪካቸው የሚፋቅ ይመስል ታዲያ ረጅሙን የኢትዮጵያ ታሪክ በአጭሩ ቁርጥ አድርጎ በመጣል ‘ተራራ ከሚያንቀጠቅጥ’ – የውሸት ጀብዳቸው የኢትዮጵያ ታሪክ እንዲጀምር ያስደረገ ደፋር ነው። ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፡ እነዚህ የባንዳ ልጆች ኢትዮጵያን ጠላት ያደረጓትና ሁሌም የሚበቀሏት የአባቶቻቼውን መገለል ለመበቀል ነው። ነገር ግን ይህ የሁሉም ትግሬ አላማና ፍላጎት አልነበረም። በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው በወርቅ የሚጻፍ አርበኛና አይተኬ የነበሩ የትግሬ ተወላጅ ጀግኖች አሉ። አሁን የትግራይ ህዝብ ታዲያ እውነተኛ ጀግኖቹን ትቢያ አልብሶ የባንዳዎቹን ልጆች መገለጫው ካደረገ ወይንም ደግሞ እነዚህ ሰዎች መላውን ትግሬ የእነርሱን ታሪክ ጭነው ሲጋልቡት “እሺ” ብሎ ህዝቡ ከተቀበለ ምን ይደረጋል?! እንደ አንድ ወገን የመምከር እድል ካለኝ፡ እባካችሁ ብዙሀን ትግሬወች በፈቃዳችሁ የባንዳ ልጆች ነን አትበሉ። በህወኀዓት አስተምህሮ ተመርታችሁ የበደላችሁትን አጎራባቻችሁን ህዝብ ክሳችሁና ይቅርታ ጠይቃችሁ ወደራሳችሁ ተመለሱ።

ማሳጠሪያ

በመለስ መታሰቢያ አዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ የቀረበው ሀተታ ሲጠቃለል ስለመለስ ግላዊ ባህሪ፥ አስተዳደግና አመራር በተለይ ደግሞ ህዝብን፥ ብሔርን፥ ነጻነትን፥ ሐይማኖትን፥ ድንበርን ወዘተ ጠቅሶ በነዚህ ረገድ የሚጠቀስ አንድም በጎ ገጽታ ሊጠቀስ አይችልም። እራሱ ሰዎየው በሕይወት በነበረበት ወቅት ቢጠየቅ እንኳ አንድም ስለራሱ በጎነት የሚያነሳው ዋቢ የሚኖር አይመስለኝም። አዘጋጆቹ ግን የጎባጣ አሽከሮች ናቸውና የሟች ቤተሰብ ለሙሾ በሚመች መልኩ ግለታሪኩን መንግስታዊ ቅርጽ አስይዘው እንዲያዘጋጁት ባዘዟቸው መሰረት መልአክ አድርገው አቅርበውታል። አዘጋጆቹን ልምጥ ወይም አድርባይ ብዬ በተፈጥሯዊ ባህሪያቸው አልሰድባቸውም፤ ከስነምግባር አንጻር ስንኩልን “ስንኩል” አይባልምና። እነዚህ አዘጋጆች  በዋናነት እነ አቶ አገኘሁ ተሻገርና ተመስገን ጥሩነህ ያሉበት የብአዴን ክበብ፡ የሚገርሙኝ አሁንም መለስን ሲያመልኩ እንደነበረው ሁሉ የአብይ አህመድ ደቂቃን መሆናቸው ነው።

 

ክፍል 2 ይቀጥላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share