በሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የተጠለፉ አገራዊ ጉዳዮቻችን

June 17, 2023
23 mins read
Oromo 2 1
#image_title

June 10, 2023

ጠገናው ጎሹ

 

ለዘመናት በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የአገዛዝ ቀንበር ሥር እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ከወደቅንበት እጅግ አስከፊ ሁኔታ ሰብረን ለመውጣት እንኳንስ ሊሳካልን ትርጉም ያለው የማስታገሻ እርምጃ ለመራመድ ካልቻልንባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ አገራዊ (የጋራ) ጉዳዮቻችንን አሳልፈን የመስጠታችን ከፉ ውድቀት ነው።

ከመከረኛው ግብር ከፋይ ህዝብ እየነጠቁ እና በተሃድሶ ስም ከለጋሽ አገሮችና ድርጅቶች እርዳታ እየለመኑ ለርካሽና ጨካኝ የፖለቲካ ሥርዓት ሽፉን ሰጭነት የሚያገለግሉ ኮሚቴዎችን፣ ኮሚሽኖችን፣ ቦርዶችንና መሰል አካላትን በአዋጅና በመመሪያ ማቋቋም የባለጌና የጨካኝ ገዥዎች  የተለመደ ዘዴ ነው።

የምርጫ ቦርድን፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋምን ፣ የእርቅና ሰላም ኮሚሽንን፣ የማንነትና የወሰን ጉዳይ ኮሚሽንን፣ የሰላም ሚኒስቴርን፣ እና ይሙት ይኑር ሳይታወቅ ቆይቶ አሁን ተአምር እየሠራሁ ነው የሚለውን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተብየን፣ ወዘተ ለዘመናት በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው እጅግ መሪርና አስፈሪ እውነታ አንፃር ለሚያነፃፅር ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው አገራዊ ጉዳዮቻችን ምን ያህል ከባድና አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ ለመረዳት አይቸግረውም።

ለማሳያነት ያህል ሂሳዊ ነጥቦቼን እንደሚከተለው ላቅርባቸው፦

 

1)    ዘመን ጠገቡና እጅግ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳያችን (our overdue and extremely burning national issue) በቀደሙት ትውልዶች የአርበኝነት ተጋድሎ (በቁሳዊ ዋጋ ጨርሶ የማይተመን የደምና የአጥንት ዋጋ) የቆየችውን የጋራ አገር በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ አማካኝነት ለዚህ ለእኛው ዘመን የምትበጅ ማድረግ  የሚያስችል የፖለቲካና የሞራል አቋምና ቁመና ላይ መገኘት ሲገባን  እንዲያውም ይባስ ብለን ለማፈራረስ እንቅልፍ ስናጣ መታዘብ ከኢትዮጵያዊነት አልፎ ሰው የመሆንን ትርጉም በእጅጉ ይፈትናል።

2)     አዎ! ታላቁ አገራዊ ጉዳያችን  የተቀደሰው የጋራ ራዕያችን ፣ ዓላማችንና ግባችን እውን እንዳይሆን መግደልንና ማስገደልን  ጨምሮ እጅግ ለመግለፅ የሚያስቸግሩ የግፍና የሰቆቃ እርምጃዎችን በመጠቀም የመከራውና የውርደቱ ዘመን ማብቂያ እንዳይኖረው ያደረጉትን የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ገዥ ቡድኖችን በጋራ አስወግዶ መልካም የጋራ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንጅ እጅግ አሳሳችና አደገኛ የክስተቶች ትኩሳት ጋር እየሞቅንና እየቀዘቀዝን የገዛ ራሳችንን የመከራና የውርደት ዘመን ለማራዘም መሆን አልነበረበትም።

3)   አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ወደር የሌለው አገራዊ ጉዳያችን መልሰንና መላልሰን ከወደቅንበት እጅግ ወራዳና አዋራጅ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብረን በመውጣት ከእኛው ከገዛ ራሳችን ሁለንተናዊ ጉስቁልና አልፎ በዓለም ፊት ከንፈር መምጠጫ፣ መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆን ያደረገንን የባለጌና ጨካኝ የጎሳ/የጎጥ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ፖለቲከኞችን ሥርዓት እንደ ሥርዓት አስወግደን መሠረታዊና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አምጦ የመውለድ ጉዳይ እንጅ በዚያው በበሰበሰና በከረፋ ሥርዓት መልካም ፈቃድ  በሚፈጠሩና በሚሽከከሩ ኮሚቴዎች፣ ኮሚሽኖች፣ ቦርዶች፣ እንባ ጠባቂዎች ፣ወዘተ መፍትሄ ይወለዳል የሚልእ ጅግ አስቀያሚና አደገኛ  ቂልነት (ድንቁርና) ወይም አድርባይነት ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ዝቅጠት  መሆን አልነበረበትም።

4)    አዎ! አገራዊ ጉዳያችን ዘመን ጠገብና አስከፊ ከሆኑ ውድቀቶቻችን ተምረን መሠረታዊና እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያጠኑና የሚቀምሩ አርበኛ ወገኖችን አምጦ ለመውለድ እንጅ እጅግ ሥር የሠደደንና እንደ አስከፊ ወረርሽኝ የተንሰራፋን የፖለቲካ ሥርዓት በሚዘውሩ ተረኛ የጎሳ/የጎጥ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞች የተሾሙ (የተቀቡ) ኮሚሽነሮችን ወይም የቦርድ ጠርናፊዎችን ወይም የኮሚቴ አበጋዞችን ወይም የጥናት ጠበብት ተብየዎችን የለየለት የአድርባይነት (ህሊናን ሸጦ የመኖር /መኖር ከተባለ) ባህሪና ተግባር እየተከታተልን የእዚህ ሞላችና እዚያ ጎደለች አደገኛ ጨዋታ ሰለባዎች ለመሆን አልነበረም ።

5)   አሁንም ታላቁና እጅግ አንገብጋቢው አገራዊ ጉዳያችን ከዘመን ጠገቡና እጅግ መሪር ከሆነው ተሞክሯችን ከምር ተምረን በትክክለኛው አቅጣጫና ተግባር ላይ ማተኮር እና የእኩያን ገዥዎችንና የግብረ በላዎቻቸውን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓትን እንዴትና መቼ ማስወገድ እንችላለን? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ በመመለስ ላይ ማተኮር ሲገባን  ለርካሸና ጨካኝ የፖለቲካ ሥርዓት ሽፋን ሰጭነት የተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን “በፕሮፌሰር እገሌ/እገሊት ስለሚመራ  ታሪክ ይሠራል” የሚል የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት ውስጥ መገኘታችን በእጅጉ አሳፋሪና አስፈሪ ነው።

6)    አዎ! አገራዊ ጉዳያችን በየዘመኑ በሥልጣነ መንበር ላይ አየተፈራረቁ በመከረኛው ህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ካወረዱትና ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ በማውረድ ላይ ከሚገኙ እኩያን ገዥ ቡድኖች ጋር እየተሻሹ የህዝብን የነፃነትና የፍትህ ትግል በማኮላሸት መሣሪያነት የሚያገለግሉ ምሁራንና ሽማግሎዎች ነን ባዮች ወደ ትክክለኛ ህሊናቸው እንዲመለሱና ከገቡበት መርዘኛ የፖለቲካ አረንቋ እንዲወጡ በግልፅ ፣ በቀጥታና በአግባቡ መናገርንና መንገርን ማበረታት ሲገባው “ለሰላም ሲባል” በሚል እጅግ የተሳሳተ ወይም እንጭጭ (wrong and naive)  የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ  ሰለባ  ሆኖ ቀጥሏል ።

አለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን በገዛ ራሳችን ልክ የሌለው የውድቀት አባዜ  ምክንያት የሆነውንና እየሆነ ያለውን ለመግለፅ በእጅጉ ከባድና አስፈሪ ሆኖብናል። አሁንም ይህንን እጅግ አደገኛ ሁኔታ በቶሎ ልናርመው ካልቻልን የእኩይ ገዥዎች እና የግብረ በላዎቻቸው አደገኛ ሴራና ሸፍጥ ሰለባዎች ሆነን እንቀጥላለን ።

የዚህ ክፉ የፖለቲካና የሞራል ደዌ ተሸካሚና መሣሪያ በመሆን ያገለገለውና አሁንም በማገልገል ላይ የሚገኘው በዓለማዊው ወይም በመንፈሳዊ ወይም በሁለቱም እውቀት (ትምህርት) እና ተሞክሮ ብዙ ርቀትና ጥልቀት እንደተጎዘ የሚነግረን የተማረው የህብረተሰብ ክፍል የመሆኑ መሪር እውነትነት ደግሞ እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ህሊናን በእጅጉ ያስጨንቃል (ያሳምማል)።

እኩያን ገዥዎች መሠረታዊና ዘላቂ የሆኑ የሥርዓት ለውጥ ጥያቂዎችና እንቅስቃሴዎች እንዲኮላሹ (እንዲጨነግፉ) ከሚጠቀሙባቸው የማታለያ (የማዘናጊያ) ዘዴዎች መካከል ኮሚቲዎችን ፣ ኮሚሽኖችን ፣ ቦርዶችን፣ እንባ ጠባቂዎችን ወዘተ በአዋጅ ፣ በመመሪያና ደንብ እየፈጠሩ (እያቋቋሙ) አደንቁረውና መከራንና ውርደትን እንዲለማመድ አድርገው ሲገዙት የኖሩትንና አሁንም እየገዙት ያሉትን መከረኛ ህዝብ ለሥርዓታቸው ምቹ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው።

የአሁኖች ኮሚሽኖች ፣ ቦርዶች፣ ኮሚቴዎች፣ ወዘተ የእኩያን ገዥዎች መሣሪያነትም ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ እጅግ የከፋ እንጅ ከቶ የተሻለ አይደለም። የተሾሙላቸው (የተቀቡላቸው) ኮሚሽነሮችና ሊቃነ መናብርትም የእራሳቸውን ህሊና ከመሸጥ አልፈው  በሁለንተናዊ ፈተና ናላው (እርሱነቱ) አየዞረበት በእጅጉ በተቸገረው ትውልድ ላይ የሚያሳድሩት የመጥፎ አርአያነት ተፅዕኖ ከቶ  ቀላል አይደለም።

መቸም የትናንቱን ብቻ ሳይሆን ከሰዓታት በፊት የሆነውን ልክ የለሽ ሁለንተናዊ ሰቆቃ እየረሳን ማቆሚያ ያላበጀንለትን እጅግ አስከፊ ማህበረሰባዊና አገራዊ ህመም (ስቃይ) መታመሙን ተለማምደነው ብዙም ልብ አንለውም እንጅ ከሶስት አሥርተ ዓመታት በላይ ዘልቀው ወደ አራተኛው አሥርተ ዓመታት የተሻገሩት የኢህአዴግ ወሮ በሎች (ባለጌና ጨካኝ ስብስቦች) በፈጠሩት ልክ የሌለው የሥልጣን ሽኩቻ ከሁለት ተሰንጥቀው ካስከተሉት የመከራና የውርደት ዶፍ በላይ መሪር ማስረጃ  ጨርሶ የለም።

አገር በባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ለልጆቿ የለየላት ምድረ ሲኦል በሆነችበት አገር ውስጥ በእነዚሁ ገዥዎች ተሹሞ ፣ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ተሰጥቶት እና መመሪያ ወርዶለት አገርን ከገባችበት እጅግ ጥልቅና ሰፊ የውድቀት አዙሪት ለማውጣት የሚያስችል አገራዊ አጀንዳ፣ ምክክርና እውነተኛ ፍኖተ  መፍትሄ ያስገኛል ብሎ ከማመን የባሰ የፖለቲካ እንጭጭነት ( እንከፍነት) እና የሞራልና የመንፈስ ኮስማናነት ፈፅሞ የለም።

 

የመልካም ዜግነት ህሊናን በእጅጉ የሚያቆስለውና እንደ ማህበረሰብም ወይም እንደ የአንድ አገር ህዝብም ለመግልፅ በሚያስቸግር ሁኔታ የሚያሳፍረው (የሚያሸማቅቀው) ደግሞ እነዚሁ እኩያን ገዥ ስብስቦች ያንን ሁሉ የመከራና የውርደት ናዳ (ዶፍ) ከማውረድ ባልተገቱበት መሪር እውነታ ውስጥ በምንገኝበት በዚህ ወቅት ያለምንም ተጠያቂነትና ያለምንም ይፋዊ ይቅርታ () ለማታለያ መሣሪያነት በአዋጅ ድርሰት ያቋቋሟቸውን የኮሚቴ፣ የኮሚሽንና  የቦርድ ቁጥርና አይነት እየጠቀሱ እየጠቀሱ “የምንሠራውን ተአምር ከቻላችሁ በመደመር አግዙ ካልሆነ ግን አርፋችሁ ተቀመጡ” አይነት ቀጭን ትእዛዛቸው ነው።

 ይበልጥ ተጨባጭና ግልፅ ለመሆን በሚከተሉት ማሳያዎች አስተያየቴን ልቋጭ ፦

·         “አገርን የንፁሃን ልጀቿ ምድረ ሲኦል ያደረጉና እያደረጉ ያሉ እኩያን ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ለርካሽና ጨካኝ ፖለቲካቸው ሽፋን ሰጭነት ያገለግል ዘንድ የፈጠሩትን (ያቋቋሙትን) አካል የሰላም ሚኒስቴር ብለው በመሰየም “የምሥራች” ሲሉን ከምር በመቆጣት እውነተኛ ሰላም እውን የሚሆንበትን ሥርዓት አምጠን ለመውለድ ወኔ ያጣን እለት ነበር ታላቁና ወርቃማው አገራዊ ጉዳያችን በክፉዎች ጠለፋ ውስጥ የወደቀው፤

 

·         የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህሪና ገፅታ አንዱ የሆነው የምርጫ ሥርዓት   አስፈፃሚ ነው የሚባለው የምርጫ ቦርድ ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች በሚሾሟቸውና በሚያዟቸው ደካማና አድርባይ ግለሰቦች ቁጥጥር ሥር ሲውል ከምር በሆነና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ለምንና እንዴት? ብለን ባለመጠየቃችንና ባለመሞገታችን ምክንያት ነበር አገራዊ ጉዳያችን በክፉዎች መዳፍ ሥር የወደቀው።

·          የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየው ኮሚሽነር  ዳንኤል በቀለ ኢህአዴግን በተረኝነትና ከህወሃት የበላይነት ዘመን እጅግ በባሰ ሁኔታ ያስቀጠሉትን ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን/ብልፅግናዊያን ሹመትና ጥቅማጥቅም ተቀብሎ ህዝብ በመስማት ሳይሆን በመኖር (በገሃዱ ዓለም የኑሮ ተሞክሮው) የሚያውቀውን የመከራና የውርደት ህይወት ከጋዜጠኝነት ባልተሻለ አኳኋን ሪፖርት (ዜና ትንታኔ) እያዘጋጀና ከማቅረብና ከማስነበብ ያለፈ ሥራ ባይሠራ ያሳዝን እንደሆን እንጅ አይገርምም። እኛም ነፃና ሚዛናዊ የሆነ አካል እየመራ እንደሆነ ሊያሳምነን ሲሞክር ከምር ነውር ነው ለማለት ወኔ ያጣን እለት ነበር እጅግ አንገብጋቢው አገራዊ ጉዳያችን በባለጌና ጨካኝ ፖለቲከኞች ተጠልፎ የመከራውና የውርደቱ ዘመን እንደሚረዝም ግልፅ የሆነው።

·         የመንግሥት ሠራተኛ የደም እንባ የሚያስነቡ እኩያን ገዥ ቡድኖች እንባ ጠባቂ (ombudsman) የሚባል አካል (ክፍል) ፈጥረው “የግፍ እንባን እናብሳለን” ሲሉን በየትኛው የፖለቲካ ተፈጥሯችሁና ባሀሪያችሁ? ብለን ከምር ለመጠየቅና  ለመቆጣት የተሳነን እለት ነበር ትክክለኛ አገራዊ ጉዳዮቻችን በእኩያን ገዥዎችና ሸሪኮቻቸው ተጠልፈው የመከራና የውርደት አገዛዙ ዘመን የተራዘመው።

·         ከፖለቲካ ተፈጥሯቸው ፣ ባህሪያቸውና ተግባራቸው ጋር ፈፅሞ ተቃራኒ የሆኑ የሰላምና እርቅ ኮሚሽን እና የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን አቋቋምን ብለው ሲያቄሉን (ሲያጃጅሉን) ለምን? እንዴት? በማንና ለማንብለን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታቸውን ለመሞገት (ለማጋለጥ) እና ከምር ለመታገል አቅም ያጣን እለት ነበር ብዙ የምንተርክለት አገራዊ ህልማችንና ጉዳያችን በክፉዎች መዳፍ ሥር የወደቁት።

·         በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሁሉ መሪር ተሞክሮ ትምህርት አልሆነን ብሎ አሁንም ለተመሳሳይ ዓላማና ግብ በእነዚሁ እኩያን ገዥ ቡድኖች ተገጣጥሞ የተሠራው (የተቋቋመው) የአገራዊ መክክር ኮሚሽን ተብየ ከሌሎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ ተአምር ይወልድ ይመስል የትንታኔና የትርክት ድሪቶ በመደረት ሥራ ላይ የመጠመዳችን አባዜ ነው።

በአጠቃላይ  ከእባብ እንቁላል የዶሮ ጫጩት መጠበቅ የለየለት ቂልነት ወይም ራስን ማታለል እንደሆነ ሁሉ ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች  የብልግና እና የጭካኔ አገዛዛቸውን ለማራዘም ሲሉ ከሚፈጥሯቸው (ከሚያቋቁሟቸው) ከሚሽን፣ ኮሚቴ፣ ቦርድ፣ እንባ ጠባቂ ፣ ወዘተ ከሚሰኙ  አሻንጉሊቶች በጎ አገራዊ ራዕይና  እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ  ይወለዳል ብሎ መጠበቅም የለየለት የፖለቲካ ቂልነት እና የሞራል ኮስማናነት ነውና ብቸኛውና ትክክለኛው መውጫ መንገድ የሥርዓት ለውጥ ተጋድሎ ነው!

እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

183645
Previous Story

እኛ እና እናንተ በምንም አንገናኝም| ኮ/ል ደመቀ ስለወልቃይት | COLONELL DEMEKE ZEWDU | WELKAYIT AMHARA | ETHIOPIA

Oromo Tergnaw 1 1 1
Next Story

እኔ የምለው….Part 10 ….እኛ ረሀቡን ችለን እነሱ ጥጋቡን መቻል አቃታቸው

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop