የሃገራት መሪዎች ሁሉንም መሆን ስለማይችሉ የመንግስታቸውን ሽራፊ በእውቀት የዳበረ፤ሃገር ወዳድነቱ ከግምት የገባ ፤በተግባር የተፈተነና የተመሰከረለት ፤ውጤታማ ልምድ ያለው ዜጋ እየመረጡ ስራውን በሚኒስቴር፤ በመመሪያ ሃላፊነት፤ በኮሚሺነርነት፤ በአምባሳደርነት እንደየደረጃው እየመለመሉ የመንግስታቸውን ስራ ያሳልጣሉ፡፡ ይህ ለሹማምንቱ የተሰጠው ቦታና ሃላፊነት እንደ ንግስና የእድሜ ልክ ሳይሆን በሩቅና በቅርብ ጊዜያቶች እየተገመገመ መልካም የሰሩ በቦታቸው ይቆያሉ፤ለከፍተኛ ስልጣን ይታጫሉ በአንጻሩ ስራን የበደሉ ፤ በተመደቡበት ቦታ ብቃት ሳይኖራቸው በነሱ አመራር ኪሳራ ከደረሰ፤ ስራ ከተጓተተ፤ ከአቅም በታች በመስራት ድርጅታቸው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ካልተወጡ በህግ ተጠያቂ ሁነው ለፍርድ ይቀርባሉ ቅጣታቸውንም ያገኛሉ እንደ ቻይና ባለው አገር በጥይት ሲደበደቡ እንደ ጃፓን ደግሞ በውሻ ሰንሰለት ታስረው የህዝብ መሳቂያ ይሆናሉ፡፡
በአፍሪካ መሪዎች ከላይ የታተተው የማይታሰብ ቢሆንም በብዙ ሃገሮች መሪዎች ሃገራቸውን በብቃት መምራት ካቃታቸው ተገፍትረው፤ በህግ ተገደው ወይ እራሳቸው መልቀቂያ ጠይቀው ከሃላፊነታቸው ይነሳሉ፡፡ መሪዎችም በስልጣኔ ከመጣህ ወደ ግልጽ ጦርነት እንሄዳለን ብለው ዜጋን አያስፈራሩም ፤ በታክስ ከፋዮች የተቋቋመውን የመከላከያ ተቋምም እንደ ግል አሽከራቸውና ድርጅታቸው ዜጋን ተኩሶ እንዲገድል ትእዛዝ አይሰጡም፡፡ ቢሰጡም ተአለቃዬ አዞኝ ገደልኩ የሚለው በሲቢል አስተዳደር ተቀባይነት አያገኝም ይህን ያደረገም በህግ ይጠየቃል:: ዛሬ በሃገራችን ፋይላቸው ያልተዘጋ የኢንጅነር ስመኘው፤የጄነራል አሳምነው፤በተለያየ ጊዜ በህወአትም ሆነ በብልጽግና፤ በኦነግ የተግደሉት ዜጎቻችን፤በፋኖ ስም እሰር ቤቱን የሞሉት ወጣቶች ጉዳይ ወንጀሉን ይርጋ ስለማያግደው የዶሴው አቧራ ተራግፎ ወንጀለኞች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ጥርጥር አይኖርም፡፡
ከላይ መሪዎች ሊያደርጉ የሚገባቸውን ቀላል ነገር በመጠኑ ከጠቆምን በኋላ ኢትዮጵያ ሃገር ነች የሚለውን እሳቤ ለጊዜው ትተነው ኢትዮጵያ ትርፍ የምታመጣ የዶክተር አብይ የግሉ ኩባንያ ብትሆን አካባቢውን በወንጀለኞች፤አራጆች ከእውቀትና ልምድ በራቁ ባለስልጣኖች ይሞላዋልን ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡ አያድርገውም የራሱ ለሆነው ነገር ውሳኔው የሚመሰረተው economical, effective and efficient በሆነ ልኬት ነው፡፡ ጠሚኒስትሩ በአንድ ንግግሩ ካሁን በኋላ ሹመት በጎሳ ነው ብሎ የተናገረው ከግምት ይግባልን በችሎታ አላለም፡፡ በፈረንጆች 2012 የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ የብሄራዊ ባንኩን ገዥ አድርጎ የሾመው የካናዳውን ዜጋ ነበር ፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የማርክ ካርኔይ ካናዳዊው የእንግሊዝ ባንክ ገዥ ልምድና ችሎታ ተገምግሞና ታምኖበት ነበር፡፡በኢትዮጵያ ግን የፈለገው ልምድ ቢኖርም እውቀትና ሃገር ወዳድነት ቢታከልበትም ዋናው መለኪያው ብሄሩ በመሆኑ ከኦሮሞ ተወላጆች ውጭ ይህ ቦታ ሊታሰብ አይችልም፡፡ እስቲ በወቅቱ የእንግሊዝ ቻንስለር ኦዝቦርን ስለዚህ ተሿሚ የሰጠውን ምስክርነት ለእኛ ሹመኞች አይን ይከፍታል ብለን ስለገመትን እንዳለ አቅርበነዋል Chancellor George Osborne said Carney was “the outstanding candidate to be Governor of the Bank of England and help steer Britain through these difficult economic times”. “He is quite simply the best, most experienced and most qualified person in the world to do the job,” Osborne told Parliament ይህ ነው እንግዲህ የሰለጠነ ህዝብ ከምሽጉ ወጥቶ አለም አቀፍ ግንዛቤ ሲያገኝ የሚደርስበት የግንዛቤ ልኬት የሚያሳየን ፡፡ እንደው ወደ ፈረንጅ ምሳሌ ሄድን እንጅ በተለያየ የአለም ክፍል በተለያየ ተቋም የሚሰሩ የኢትዮጵያ ልጆች መች በሃገራቸው ውስጥ የተጠየቁትን ያልተያያዘ ጥያቄ ተጠየቁ? የተጠየቁት ብቃታቸውን ብቻ ነበር (ጥላሁን ይልማ፤ጌታቸው ሃይሌ፤ብሩክ ላቀው፤ዮናስ ገዳ፤ተስፋዬ ቢፍቱ፤ኪዳኔ አለማየሁ እያለ ይቀጥላል ህወአት እግዜር ይይልህ መጨረሻህን አያሳምረው ….)፡፡
እንዲህ ካልሆነ ብቃት ባላቸው በዘር ባልተቧደኑ ለሃገር አሳቢ ሰዎች ካቢኔውንና ሌላውን የሰራ ዘርፍ መሙላቱ አማራጭ ሳይሆን ግዴታም በመሆኑ ጠሚኒስቴሩ በሚሰምጥ መርከብ ላይ መሆኑን አውቆ ባስችኳይ እርምት እንዲያደርግ ዛሬም እናሳስባለ ጆሮ ጠባቂያቸውም ይህንን እንዲያደርሱላቸው እንጠይቃለን፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታየሃገራቸው ጉዳይ እረፍት የነሳቸው ዜጎች በተደጋጋሚ ቢጽፉም ቢጮሁም ዶር አብይ ምን ያመጣሉ በሚል እብሪት በዚህ ሃገርን በሚያጠፋ አሰራር በርትቶ ቀጥሎበታል፡፡
በቅርቡ ከባጥ በላይ የተጮኸለት ብርሃኑ ነጋ በጀት ተመድቦለት የኢትዮጵያ ተስፋዎች በሚፈለፈሉበት ትልቁ ተቋም (ትምህርት ሚኒስቴር) ተመድቦ ሲሰራ (ሲያጠፋ) ቀደም ሲል አማራዎች ናቸው በማለት የ13000 ተማሪዎችን የወደፊት ተስፋ ሲያጨልም በሚዲያው ቀርቦ ጎሽ እንደገደለ አዳኝ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ጠ/ሚኒስቴሩ ምንም እንዳልሆነ ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጠው ታልፏል፡፡ ይህ በዚያ ሳያበቃ ሚኒስቴሩ በራሱ ሰዎች ሲገመገም የ12ኛ ከፍል ተፈታኞች ከጠቅላላው 3% ብቻ ማለፉን ሰምተን በእጅጉ ከማዘን አልፈን አገሪቱ ወዴት እያመራች ነው ብለን መጠይቅ ተገደናል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እንዲህ ያለ የአመራር በደል ያደረሰ ባለስልጣን በሌላው አገር ቢሆን ጆሮውን ተይዞ ከስልጣን ከመባረሩ በተጨማሪ ባስከተለው ጥፋት፤ ቀውስ፤ኪሳራ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ሁኖ ጉዳዩ በፍረድ ተይዞ ወደ እስር በተጋዘ ነበር ቦታውም ጎሳን ሳይሆን ሃገርን በሚወዱና ስራን መስራት በሚችሉ ዜጎች በተሸፈነ ነበር፡፡ ብርሃኑ ግን ዛሬም ምንም እፍረት ሳይሰማው በየሚዲያው ቀርቦ ሲታይ ህሊና ላለው ሰው ያሰቅቃል፡፡
መአዛ አሸናፊ የፍርድ ተቋሙ የበላይ ሰዉ፡፡ ይህች ሴት በውነቱ እንደ አለም አቀፍ ሱፐር ሞዴል ስትናገርም ሆነ ስትራመድ (ካት ዎክ) እንደሚሉት ሙሉ ትኩረቷን በራስዋ ላይ አድርጋ በስልጣን ዘመኗ ስታላግጥ ከርማ የአብይ መንግስት መጨረሻው ስላላማራት ቀድማ የሾለከች ጩሎሌ ሴት ናት፡በበታች እርከን የሚገኙ ዳኞች አለአግባብ ታስሮ የሚሰቃየውን፤ የተበደለውን ዜጋ ነጻ ነህ ብለው ሲያሰናብቱት ነጻነቱ የታወጀለት ፍርደኛ በዳኛው ፊት እየተዳፋ እንደገና ወደ እስር ቤት ሲወረወር የዛን ጊዜ ከስልጣን መልቀቅ ሲገባት ቦታው የሚሰጣትን ጥቅም ስታጣጣም ከርማ አሁን ከአብይ ውድቀት በፊት እጇን ያወጣች የኦሮሙማ ስርአት አሳላጭ ነች፡፡
አዳነች አቤቤ/ታከለ ኡማ እነዚህ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተወረወረሩ መቅስፍቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች አዲስ አበቤ ሳይሆኑ በአብይ እጅ ጠምዝዝ ሹመት አዲስ አበባን እንዲቀጡ ኦሮምያን እንዲያዋልዱ ወምበሩ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡ አዳነች አቤቤ ከዚህ በፊት በስብሰባቸው ላይ ወደ ሂሳቧ ስለገባው 40 ሚልዮን ብር ብትጠይቅ የማውቀው ነገር የለም ብላ መመለሷን በአንድ ሚዲያ ላይ ሰምተናል የማታውቀው ሰው 40 ሚሊዮን ብር ሂሳቧ ውስጥ ሲያስገባላት፡ ይህች ጩሉሌ ሴት ቅዳሜ ለምትመርቀው ህንጻ ሀሙስ ተቃጠለ ሲባል ምን ተብሎ ይገለጻል እንግዲህ የሂሳብ ሰነዶቹም አብረው ተቃጥለዋል ወይም ደግሞ ታከለ ኡማ አቃጥሎት ሄድ ቢሉን ሊገርመን አይገባም፡ የኦሮምያ መስፍን የጊዜው የአብይ ተገዳዳሪ በግልበጣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው ሽመልስ አብዲሳ ከሻሸመኔ እስክ ወለጋ ፈልገውና መርጠው አማራ ባልሆኑት ዜጎች ላይ ይህን ያህል መርገም ሲያወርድባቸው የኖረው እንኳንስ ከስልጣኑ ሊባረር በነብስ ግዳይ ሊጠየቅ፤ በህዝብ ጭፍጨፋ ሊወገዝ ፤በንብረት ውድመት ሊከሰስ፤ ከስልጣኑ ሊባረር ቀርቶ ዛሬ ክልሉን እያለፈ በአማራ ክልልና በሱማሌ ክልል መመሪያና ማስፈራሪያ እየሰጠ የሚመለስ ሲሆን አብይም በፍርሃት ይሁን የሚፈልገውን ስለሚሰራለት ስራውን በማድነቅ ወንጀሉን ደግፎ ድምጹን አጥፍቶ ቁጭ ብሏል የቃዬል ደም ወደ አምላኩ እንደጮኸ የነዚህ ንጹሃን ደምም በወንጀለኞች መቀሰፍት እንደሚያመጣባቸው ለቅንጣት አንጠራጠርም፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር አብርሃም በላይ አብረሃም በላይ እንደ አብይ ሁሉ በህወአት ተኮትኩቶ ለዚህ የደረሰ ሰው ነው፡፡ አብርሃም በላይ በህወአት ዘመን ተክለ ሰውነቱን የገነባ ከህወአት እሳቤ ውጭ ሊያስብ ቢፈልግም የተሰራበት የማይፈቅድለት በህወአት የተጠመቀ ሰው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስቴሩም ሀወአትን የመከላከያ ሚኒስቴር አድርጎ ህወአትን እየወጋሁ ነው ይለናል፡፡የኢትዮጵያ ጦር በህወአት የጭዳ በግ ሲሆን አብይም ሆነ አብረሃም በላይ ብዙም ያልሞቃቸው ያልበረዳቸው ነበሩ፡፡ የዶ/ር አብረሃም ትይዩ ዶር ሙሉ ነጋ የትግሬ አገር ገዥ ሁኖ ሲመደብ ትግራይ ውስጥ ምን ሰርቶ እንደወጣ የቅርብ ትዝታ ነውና እዚህ መድገም አያስፈልግም አብረሃም በላይ እንደ ሙሉ ነጋ ሁሉ በትግራይ ህወአትን አጠናክሮ የወጣ የህወአት የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የ130 ሚሊዮን ህዝብ አገር ነች ካልጠፋ ሰው በኢትዮጵያዊነት ላይ ያመጹትን ዜጋ የገደሉትን በእነ ሌንጮ ለታ/ባቲ፤አረጋዊ በርሄ፤ዲማ ነገዎ፤ቀጀላ መርዳሳ፤ሃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ሬድዋን ሁሴን፤አገኘሁ ተሻገር……. ተከብቦ መቀመጥ ለዶክተር አብይ የሚያመጣለት ፋይዳ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሾሙት ሚኒስተሮቹ ዲፕሎማቶቹ ኮሚሺነሮቹ ከጥቂቶቹ በስተቀር ልምድ እንዲያዳብሩ ስራ እንዲያበላሹ ካልሆነ በስተቀር ለዚህ ታላቅ ሃገር ይፈይዳሉ ተብሎ አይታሰብም የታየውም ይኸው ነው፡፡ እስቲ ለዚህ ማያያዣ እንዲሆነን የሃይለ ማርያም ደሳለኝን ብቃት ቲም ሰባስቲያን ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ ብቃቱን እንፈትሸው ይህ ነው እንግዲህ የአባይ ተደራዳሪ እንዲሆን ከታጩት ሰዎች መሃል በትግሬዎች ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድር ሙሉ ስልጣን በነ በረክት የተሰጠው (200) Former Ethiopia PM: Labeling me a dictator is wrong | Conflict Zone – YouTube፡፡ ዶር አብይ በአንድ ስብሰባ ካሁን በኋላ የቀደመው ትውልድ ወደስልጣን ዝር አይልም የተሰጠውን እድል አልተጠቀመበትም ብሎ ጠረቤዛ እየደበደብ ሲናገር ተስተውሏል ከላይ እንዳመላከትነው የከበቡት ወጣት ትውልዶች ያመጡለትን አይተናል እንደው እሱ እንዳለው ብንቀበለው እንኳ ቀጀላ መርዳሳ፤አረጋዊ በርሄ፤ዲማ ነገዎ፤ሌንጮ ለታ/ባቲ፤አባዱላ ገመዳ፤…….. የመሳሰሉ ተሿሚዎችና አማካሪዎች ፍንዳታዎች ሊላቸው ነው? መሪ ተበሳጭቶ ንግግር ባያደርግ መልካም ይሆናል ንግግሩ በብዙ ሰው ስለሚስተዋል፡፡
ለማጠቃለል ሹመት ስራን ለማሳለጥና ፕሮግራም የተደረገውን ስራ ከግብ ለማድረስ ነው ይህንን ማድረግ ያልቻሉትን ስራን ለረጅም ጊዜ እንዲያበላሹ መፍቀድ የኋላ ኋላ ዳፋው ለሿሚው ስለሆነ ዶ/]ር አብይ ብሽሽቅ የሚመስለውን አሰራሩን ትቶ አግባብ ባለው መልኩ ይህችን አገር እንዲመራ እንጠይቃለን ማንኛውም ስለ ሃገሩ የሚጨነቅ ዜጋ ከሱ ያነሰ ወይም የበለጠ ባለመሆኑ ጭንቀቱን ሊካፈለው ያለበት ቦታ ያስገድደዋል፡፡በታሪክ መሪዎች ከ 3 ሰአት እስከ 44 ቀን በስልጣን ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ ሊዝ ትረስ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስቴር በ 6 ሳምንቷ አልቻልኩም ስራ ይበላሻል አገር ይጎዳል ብላ ስራዋን በፍቃዷ መልቀቋ ለሃገራችን ትክል ባለስልጣኖች ትምህርት ይሰጠናል ብለን እንገምታለን፡፡
አማራ ክልል ከአንዴም ሶስቴ በግድያና በሌላም መልኩ መሪዎችን እያጠለሸ ጠ/ሚኒስቴሩ ሲለወጥ ይህ አሰራር ኦሮምያንም ያለመጎብኘቱ ለምን ያስብላል፡፡ ] በተረፍ ኮሽ ሲል የሚደነግጥ መንግስት የለም የሚለው የእብሪት አካሄድ የትም እንደማያደርስ የሌሎች ሃገር ተሞክሮች ሳይሆኑ የሃገራችንም ልምድ በቂ ማሳያ ስለሚሆን መሪዎቻችን ካለፈው ይማሩ እንላለን፡፡ከላይ ምስሉ ግልጽ ያልሆነው በአራተኛ ረድፍ የምታዩት የሰላሙ ታጋይ ማህተማ ጋንዲ ሳይሆን የህወአት መስራችና የወታደር ክንፉ ሃላፊ ሁኖ ብዙ ዜጎችን ያጨደ ሃገርን ላጠፋበት የህዳሴ አስተዳዳሪ ሁኖ በአብይ አህመድ የተሾመ የኢትዮጵያ መቅሰፍት ነው ቀሪዎቹም አብይ ፍንዳታ የሚላቸው ወንጀለኞች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሰመረ አለሙ [email protected]
(ፍትህ ለክቡር ታዲዎስ ታንቱ)