መርህ አልባነት ፣ የጭፍን ወይም የጨለማ ጉዞ!

የአቢይ አህመድ ጨለማ ጉዞ!
የአቢይ አህመድ ጨለማ ጉዞ!

መርህ  መመሪያ፣ ዓላማ፣ግብ፣ምክንያት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።መርህ አልባ በተቃራኒው ዓላማ ቢስ፣መመሪያ ቢስ፣ምክንያተቢስና ግብ የለሽ መሆን ማለት ነው። በሌላም አባባል መርህ አልባነት መነሻና መድረሻውን ሳያውቁ፣የጉዞ አቅጣጫን ሳይነድፉ በዘፈቀደና ስሜታዊነት ተነስቶ የጭፍን ወይም የጨለማ ጉዞ መሄድ ማለት ነው።ብዙውን ጊዜ የጨለማ ወይም የጭፍን ጉዞ ካላዩት ገደል ወይም ጉድጓድ ውስጥ ይከታል።ለዚያም ነው የሰው ልጅ መርህ ሊኖረው ይገባል የሚባለው።

ህይወት ያለው ፍጡር ሁሉ ለመኖር፣የሚያስፈልጉት ቁሳዊና አካላዊ ግብአት መሟላት አለባቸው።የእነዚያን ማሟላት እንደ ዓላማው ቆጥሮ ለማግኘት ጥረትና ትግል  ማድረግ፣ብልሃትና መንገዱን ማወቅና መከተል አለበት። ህይወት ካላቸው ፍጥረታት ሁሉ በመርህ ለመመራት የላቀ ግንዛቤና የመፍጠር ችሎታ ያለው የሰው ልጅ ነው።የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ለመኖር ሲል ብዙ ውጣ ውረዶችን የማለፍ ግዴታ ተቀብሏል። ለብዙ አይነት ችግሮች ተጋልጧል።ከውጭና ከውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ተጠቅቷል።በተፈጥሮና በራስ ሰራሽ ችግርም ተፈትኗል።በርሃብ ፣በበሽታ፣በተፈጥሮ አደጋ፣በድንቁርና፣ በጦርነትና በእርስበርስ ግጭት ውስጥ መግባት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።ታዲያ ከችግሮቹ ለመውጣት ትግልና  ጥረት አደረገ እንጂ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠበት ጊዜ የለም።አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሌላ ጊዜ ሲሸነፍ አሁን ካለበት ዘመን ላይ ደርሷል።አሁንም ትግሉን አላቆመም፤ጊዜና ሁኔታ የሚወልዳቸውን ችግሮች ለመቋቋም ጥረቱና ትግሉ ቀጥሏል።ለዚያም ነው የሰው ልጅ ታሪክ የትግል ታሪክ ነው የሚባለው።በሚያደርገው ትግል በተደጋጋሚ አለመሳካት ወይም ችንፈት ገጥሞታል።ለዚያ  የዳረገው ዋናው ምክንያት ዓላማውንና መድረሻውን  በቅጡ አለማወቁ እንዲሁም ከግቡ ሊደርስበት የሚችለውን መንገድና አቅጣጫ አለመረዳቱ ወይም የአቅም ማነስ ሲሆን በተጨማሪም በጉዞው መካከል በጥቃቅን ግኝቶች እረክቶ ከግቡ ሳይደርስ ዓላማውን ዘንግቶ በማቋረጡ ይሆናል።ያም የመርህ አልባነት ውጤት ነው።መርህ ሙሉነት እንጂ ግማሽነት የለውም።በግማሹ መርካት ከጠቅላላው ችግር መውጣት ወይም መላቀቅ ሳይሆን የፍለጋ ጥረቱን ወይም ትግሉን አቋርጦ ነባሩን ችግር እዬተለማመዱ  በቀጣይነት የሚመጣውንም ተሸክሞ ለመኖር ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው።

የሰው ልጅ የገጠሙት ችግሮች ብዙ ቢሆኑም፣ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው ትንቅንቅ አያሌ ቢሆንም ከነዚያ ውስጥ በጣም የከፋው ሰው በራሱ የሚፈጥረው ችግር ነው። የጥቂቶችን  ስግብግብነትና እራስ ወዳድነትን ተከትሎ የተፈጠረው ችግር ብዙሃኑ ኑሮው እንዲዛባና ተስፋው እንዲጨልምበት አድርጓል።የተወሰነችለትን ትንሽ የዕድሜ ገደብ በወጉ ሳያጣጥማትና ኑሮ ሳይኖር በመከራና በስቃይ እንዲያሳልፍ፣ በለጋ ዕድሜውም  በሞት እንዲቀጭ አድርጎታል።ጥቂቶቹ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ብዙሃኑን በደካማ ጎኑ እዬገቡ እርስ በራሱ እንዲተላለቅ አድርገው የሃብትና የሥልጣኑ ባለቤት ሆነዋል፤ያንንም ላለማጣትና  ዘለዓለማዊ ለማድረግ ብዙ ሴራና ተንኮል ይተበትባሉ።ግን ዘለዓለማዊ  አይሆንም።የማይሆንበትም ምክንያት የሰው ልጅ ዝም ብሎ የተኛ፣የጫኑትን ተሸክሞ የሚኖር፣የማይንቀሳቀስ ግኡዝ አካል ሳይሆን ለዋጭና በለውጥ ጉዞ የሚንቀሳቀስ ፍጡር ስለሆነ ነው።ጥያቄው የጊዜ ጉዳይ ነው።ይዋል ይደር እንጂ ጊዜው ሲደርስ የነበረው ባልነበረው ይለወጣል።ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ለውጥን የሚያቆመው ሃይል አይኖርም።

በዓለም ላይ የተከሰቱት  ግጭቶችና ጦርነቶች ጥቂት ስግብግቦችና አልጠግብ ባዮች  በጠነሰሱት ተንኮልና ሴራ ምክንያት ነው።በዚህም የዬአገሩ ዜጎች በጠላትነት ተሰልፈው በጦር ሜዳ ሞተዋል ፣ቆስለዋል። የአንድ አገር ዜጎችም ግንኙነታቸው ሊሻክርና ለእርስ በርስ ጥላቻና ግጭት፣ለመከፋፈልና በጠላትነት ጎራ ለመሰለፍ ችለዋል።ከሰውነት ስነምግባር ወጥተው ወደ አውሬነት የብላ ተባላ ልማድና ተግባር ውስጥ ገብተዋል። ይህንን ክስተት ለማሶገድ ከሰው ልጆች መካከል የነቃ አይምሮ ባለቤት የሆኑት ጠቢባንና ፈላስፎች ያሉትን ውስብስብ ችግሮች ተረድተው መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ  ለህብረተሰቡ ለማበርከት ጥረት አድርገዋል።ከእራብ ለመዳን፣ከበሽታ ለመፈወስ፣ከድንቁርና ለመላቀቅ፣ከጭቆና ለመገላገል፣ከብዝበዛ ለመጽዳት፣ከእርስ በርስ ግጭት ለመውጣትና በፍትሃዊ መንገድ ሁሉም የጋራ ተጠቃሚ ሆኖ  በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ያደርጋል ያሉትን የመፍትሔ ንድፈ ሃሳብ ወይም ራዕይ በፍልስፍና ደረጃ በማቅረብ ምሑራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሞክረዋል። ሁሉም ይሆናል ባሉት መንገድ  የህብረተሰቡን ችግርና ምክንያቱን እንዲሁም መፍትሔውን የሚጠቁም መመሪያ ወይም ፍኖተካርታ በርዩተዓለም (አይዲዎሎጂ)መልክ  አቅርበዋል።በመነጩት ሃሳቦች ላይ በሚነደፈው ፍኖተ ካርታ ወይም ራዕይ  አኳያ እያንዳንዱ የህብረተሰብ አካል ለዓላማዬ ይሆነኛል ወይም ከችግሬ ያወጣኛል ብሎ ያመነበትን ፍልስፍና(አይዲዎሎጂ) ለመከተል ችሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለይቶና አቅዶ የገጨንን ዘር ጨፍጫፊ ሾፌር ለቀው ተሽከርካሪውን (የነጂውን) እንዴት እንክሰሰው? - ወንድእጥር መኮነን 

ከላይ እንደተገለጸው የሰው ልጆች ህይወት ከትግል ጋር የተሳሰረ ነው።ለመታገል የገፋፋው ደግሞ ዓላማ ሲኖረውና ያንን ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ነው።ለሚያደርገው ትግል የሚመራበት መንገድና አቅጣጫ ጠቋሚ ወይም ኮምፓስ ሊኖረው ይገባል።ያም  በንድፈሃሳብ (ፍልስፍና) ላይ ያረፈ፣ መነሻውን ብቻ ሳይሆን መድረሻውንም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የትግል መነጽር ወይም ራዕይ ነው። የችግሩን ምንጭ፣የሚፈልጉትንና መድረሻ ግባቸውን ሳያውቁ ትግል ቢጀምሩት ውጤቱ ከባሰ ችግር ላይ መውደቅ፣በሌላ ካባ  ለተመሳሳይ ችግር መዳረግ ይሆናል።

ይህንን እንደ መመሪያ አድርገን ወደ አገራችን ፣ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰን የገጠመንን ችግርና ችግሩንም ለማሶገድ የተጠቀምንበት ዘዴና የተከተልነው መንገድ ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን መመርመር ይገባናል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ከሌላው አገር ሕዝብ ችግር የተለዬ አይደለም።የሁሉም አገር ሕዝብ በሚኖራት አጭር ዕድሜው፣ሳይራብና ሳይጠማ፣ጤናው ሳይጓደል፣ሰላሙ ሳይናጋና እርስ በርሱ ሳይጋጭ ለመኖር ቢሻም ካለነዚህ ውጣ ውረዶች የቻለበት ጊዜና ዕድል የለም።ነገር ግን ችግሮቹን ተቋቁሞና አሶግዶ የሚፈልጋቸውን ለማግኘት ጥረት አድርጓል።የተሳካላቸው አገሮች እንዳሉ ሁሉ ያልተሳካላቸውም የእኛ አይነቱ አገሮች ብዙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረጅም ዘመን ከአምባገነኖች መዳፍ ለመውጣትና የችግሩን ጫና አሸንፎ በተሻለ ደረጃ በህይወት ኖሮ ለማለፍ ፍላጎት አለው፤ለዚያም ብዙ ትግልና ጥረት አድርጓል።ሆኖም ግን ውጤቱ ከድጡ ወደማጡ ሆነበት እንጂ ለተሻለ የኑሮ ደረጃ አላበቃውም።ላለመሳካቱ ምክንያት የሆነው እራስ ወዳድነትን  ባለማሸነፍ ፣በጋራ አለመቆሙ፣ጠላትና ወዳጁን ለይቶ አለማወቁ፣የችግር ማሶገጃ መንገዶችን ባለማወቅና ባለመረዳት፣መርህ አልባ ሆኖ መነሻና መድረሻውን ባለማወቅ፣የሚመራበት ግልጽ ፍልስፍና ባለመኖሩ፣ ድብልቅልቅ ካለ ብዥታ ውስጥ ገብቶ በመዳከሩ ነው።መዳከርም  ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ተያይዞ  ለሚጠፋበት አደጋ ማለትም ለእርስበርስ ጥላቻና ግጭት ተጋልጦ መገኘቱ ነው።ይህንን የጥፋት መንገድ ሕዝቡ ፈቅዶና ወዶ ያመጣው ሳይሆን በውጭ ሃይሎች የሚነዱ፣ በሕዝቡ ስም የሚነግዱና ከጥፋት እናተርፋለን በሚሉ በጥቂት ከይሲዎች የጥፋት መርዝ ተጠንስሶ በመሰራጨቱ ነው።እነዚህ ከይሲዎች መረማመጃ መሰላልና መሣሪያ ያደረጉትም የተወለዱበትን ቦታና ጎሳ፣የሚናገሩትን ቋንቋና የሚከተሉትን ሃይማኖት ነው።

እያንዳንዱ አገር የአንድ ጎሳ ብቻ ሳይሆን የብዙ ጎሳዎች ድምር ውጤት ነው።ኢትዮጵያም እንደሁ።አንዱ ጎሳ ከሌላው ጎሳ ጋር እዬኖረ በሚፈጠረው መስተጋብር አንዱ ሌላውን ሆኖ በጋራ ማንነት የአንድ አገር ዜጋ ሆኖ ለመኖር በቅቷል።ተዋልዶ በእትብት ገመድ ተሳስሯል።ባለንባት ዓለም እንኳንስ የአንድ አገር ዜጋ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ተጋብተውና ተዋልደው ከሚኖሩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ከሌላ አገር ዜጎች ጋር ተጋብተው  የተዋለዱ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም።የአንድ ነጠላ አገር ዜግነትንና ድንበርን አፍርሰው በሰው ልጅነታቸው ዓለም አቀፋዊነትን ተክተዋል።በጣም የሚያሳዝነው ግን በዚህ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትና ማንነት ውስጥ ያሉና ያለፉ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወገናቸውን በጎሳ ማንነቱ ለያይተው እንዲጫረስ የሚያደርጉት መሆናቸው ነው።ለዚህ ትልቅ ምሳሌ የሚሆኑት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ኦነጋውያን ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሕፃን ካቦካው - ልጅ ያቦካው ይሻላል” (ለተክለሚካኤል አበበ አስተያየት የተሰጠ ድጋፍ)

በአገራችን በኢትዮጵያም የተለያዩ ጎሳዎች አብረው በመኖር ተቀራርበውና ተስማምተው የመኖር ባህል አዳብረዋል፣ጠባብ ጎሰኝነትን በመዋለድና በመቀራረብ አዳክመውታል።ለጋራ ጥቅም አብረው ተሰልፈዋል፣የመጣባቸውን የጋራ ጠላት በአንድነት መልሰዋል።ይህንን ሰላማዊ የጎሳ ስብጥር በመናድና በማቆሸሽ ጸረ አንድነት የሆኑት አገር በቀልና የውጭ ሃይሎች ለጥፋት ዓላማቸው ሊጠቀሙበት ሞክረዋል።እዬሞከሩም ነው።

በጦር ሜዳ  የተዋረዱት ወራሪዎች ለበቀል ከጠነሰሱት ሴራ መካከል የሕዝቡን አብሮነት ለመናድ  ደካማ እራስ ወዳዶችን መልምለው  የወጡበትን ጎሳ ተገን በማድረግ  ሥልጣን ላይ እንዲወጡ ከማድረግም በላይ ሕዝብ በጎሳ ማንነቱ እርስ በርሱ እዬተዋጋ በድህነት አሮንቃ ውስጥ ገብቶ የነሱን እጅና ቡራኬ እያዬ እንዲያድር፣በአገሩ ተስፋ እንዲቆርጥና ፣አገርም ተበታትና በትናንሽ መንደሮች ልክ ተሸንሽና በመዳፋቸው ሥር እንድትወድቅ  የማድረጋቸው ዓላማ ነው።ይህ አንዱና ዋናው የችግራችን መነሻ ነው ማለት ይቻላል።

የሰው ልጅ ከሰው አብራክ የተፈጠረ ስለሆነ ካለሰው አይኖርም።ጎሰኝነትና ግለኝነት የሰውነት ጸርና ጠላት ነው።ያም ማለት እራሱን የሚበላ አሲድ ነው ማለት ነው።በጎሰኝነት አስተሳሰብ የሚነዳ ማህበረሰብ የሚፈልገውን አግኝቶ መኖር ሳይሆን ፈልጎ ለማግኘት የሚችልበትን አገሩን፣ ነጻነቱንና ዕድሉን ያጣል።መዳረሻው አጥፍቶ መጥፋትይሆናል።

በአገራችን የጎሰኞች ፊታውራሪ የሆኑት የወያኔና የኦነግ እንዲሁም ሌሎቹ ቆመንለታል ለሚሉት ማህበረሰብ ተጠቀሙበት እንጂ አልጠቀሙትም።ከሰውነት ደረጃ አውርደው አውሬ አደረጉት እንጂ አላሻሻሉትም። በሚቀሰቅሱት የጥቅምና የሥልጣን ጦርነት ህይወቱን ቀጠፉበት እንጂ የሰላማዊ ኑሮና የትልቅ አገር ባለቤት አላደረጉትም። እነሱ ግን የሃብትና የንብረት ባለቤቶች ሆነዋል።

እነዚህ ሁለቱ የቀዬሱት የጎሰኞች ሥርዓትና አስተሳሰብ  የጥፋት ጎዳና መሆኑን ከተገነዘብን መፍትሔው ሥርዓቱን ከነአስተሳሰቡ ማሶገድ ነው ማለት ነው። ያለውን ሥርዓት በጥገና ማስተካከል አይቻልም። በጥቃቅን ማታለያ ዘዴዎች መርካትም ተገቢ አይደለም። አንዳንዶች አብይ ይውረድ፣ወይም ስርዓቱን ያስተካክል፣ሕገመንግሥቱ ይሻሻል ሲሉ ይደመጣሉ።አልፈው ተርፈውም ሁሉንም ያካተተ ውይይትና ስምምነት በሚል ሽፋን በከተማና  በጫካ  የሕዝቡን ሰላም የነሱና የሚያሸብሩ፣ገዳዮች፣በተመሳሳይ  ዓላማ የሚነዱ ቡድኖች የሥልጣኑ ተካፋይ ይሁኑ ይላሉ። ይህ የችግሩን መነሻና መፍትሔውን ካለማወቅ የሚመነጭ ብዥታ ነው።የትግል መነሻውንና መድረሻውን  ያለመረዳትና  መርህ አልባነት ነው።

ችግራችን ምንድን ነው?እንዴትስ ይወገዳል፣ጠላትና ወዳጅ ማን ነው?ሥርዓቱስ የማን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነሳ የምናገኘው መልስ  በውጭ ሃይሎች የሚታገዝ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የጎሳ ፖለቲካና ጎሰኝነትን የሚያራምደው በሥልጣን ላይ የተቀመጠ ቡድንና መሰሎቹ ዋናዎቹ የችግራችን ምንጮች ሆነው እናገኛቸዋለን። የጠላት ና ወዳጅ አሰላለፉ በነዚህና በአገር ወዳዱ ጎራ መካከል የሚኖረው አሰላለፍ መሆኑን እንረዳለን።በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን የውጭ ሃይሎች ተላላኪ፣ኢትዮጵያን ለመበታተንና ሕዝቧንም ለማጫረስ የሚሠራ የጎሰኞች ስብስብ ስለሆነ ከጠላት ወገን የሚመደብ እንጂ በአጋርነት ሊመደብ አይችልም፣የጥፋት እንጂ የልማት ሃይል ተደርጎ ሊቆጠር አይገባውም።ስለሆነም መወገድ አለበት።ተወግዶም ሌላ ተመሳሳይ ቡድን ለሥልጣን እንዳይበቃ ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሊኖር ይገባል።የተበታተነው አገር ወዳድ በአንድ ጣራ ስር ተሰልፎ  መታገል ይኖርበታል። ግባችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ማዳን ሲሆን የምንመራበት ፍልስፍና ኢትዮጵያዊነት ይሆናል ማለት ነው።በኢትዮጵያዊነቱ የማያምን የትግሉና የመፍትሔው አካል ሊሆን አይገባውም።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአዬር ላይ የተንጠለጠለ መንፈስ ሳይሆን በሰው አይምሮ የተወለደና በሰው ማንነት ላይ ተዳብሎ የሚኖር፣ሰብአዊና መንፈሳዊ ጥምረት ያለው፣ ትውልድ ተሻጋሪ የመኖር ጥበብና ዘዴ ነው።ይህንን ጥበብና  የማንነት ፍልስፍና የተሸከመ ማህበረሰብ ወይም ማህበረሰቦች እንዳሉ ማወቅ ተገቢ ነው።ካሉት ማህበረሰቦች መካከል አማራው አንዱና ዋናው ነው።ቤት ያለምሰሶ እንደማይቆም ሁሉ ለኢትዮጵያ እንደ አገር ለመኖር የኢትዮጵያዊነትን ፍልስፍና በዋናነት የሚከተል ሕዝብ መኖር አስፈላጊ ነው።ጠላት ሊያጠፋ የሚፈልገውን አገር ለማጥፋት ሲያስብ ኢላማ የሚያደርገው ምሰሶ ወይም የስበት ማእከል(Center of Gravity) የሆነውን ሕዝብ ወይም ማህበረሰብ ነው። ለዚያም ነው አማራውን ጠላት አድርገው  በዬጊዜው ተረባርበው የሚነሱበት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያን ከሚያስተዳድራት ኃይል ጋር እንተዋወቅ - ግርማ በላይ

ሌላው የአገር የስበት ማእከል ከሚሆኑት መካከል፣ባሕል፣እምነት፣ቅርስ፣የተፈጥሮ ጸጋዎች፣የሚግባቡበት ቋንቋና ስነጽሑፍ—ወዘተ  ሲሆኑ ሥልጣኔን ተከትሎ የተመሠረቱ ከተማዎችም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።ያንንም በሆነ ባልሆነው ዘዴ ማዳከምና ማንበርከክ ሌላው የጠላቶች ስልት ነው።ለዚያም ሲባል ነው የኦነግ ስብስብ በታሪካዊ ከተማዋ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን መንደሮች አሰባስቦ ሸገር የሚለውን  ጥንታዊ ስሟን ነጥቆ ሌላ ከተማ ለመመስረትና በሂደት ከጥቅም ውጭ (Irrelevan,te)አድርጎ ለመዋጥ ሽር ጉድ የሚለው።በራስ ፊደል የዳበረን የተሟላ የጋራ ቋንቋን አሶግዶና አዳክሞ በባዕዳን (በላቲን) ፊደል የሚታገዝ ኦሮምኛ ለመጫን ፣የሁሉም አርማ የሆነ፣የውጭ ጠላቶችን ለመዋጋትና ድል ለማድረግ በጦር ሜዳ ሳይቀር የተውለበለበ ፣ለሌሎቹም አገሮች የነጻነት ምልክት ሆኖ አክብረው የተቀበሉትን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ጥሎ በታሪካዊ ጠላት በሆነችው በግብጽ ባንዲራ ለመለወጥ  ሙከራ የሚያደርገውም የዚያው አገር የማፍረሱ ሙከራ አካል ነው።

የጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ የግድ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ መርህ መከተል ይገባል።ያም ኢትዮጵያዊነት ነው።ኢትዮጵያዊነት እንደ ፍልስፍና ተደርጎ የሚወሰድበት ምክንያት፣የሞራል ልእልናንና ፈሪሃ አምላክን ስለሚከተል፣የነጻነትና የአልበገሬነት ምልክት ስለሆነ፤የብዙ ዘመን ታሪክና የሥልጣኔ ባለቤትነትን ስለሚገልጽ፣ጸረ ባርነትና ቅኝ አገዛዝን መቃወም ብቻም ሳይሆን ተዋግቶ ድል ስላደረገ፣ ፣ለጥቁር ሕዝብ አርነት ምሳሌና ፈር ቀዳጅ በመሆኑ፤ለአፍሪካ አንድነትና ለፓን አፍሪካኒዝም መፈጠር የፋና ወጊነትን ሚና ስለተጫወተ፣ከዛም በላይ ብዙ ሕዝብ ቋንቋና ባህል፣እምነትና ጎሳ ሳይለያዬው ተዋልዶ  በአንድነት ለመኖር ያበቃው የጋራ ማንነት መገለጫ ስለሆነ ነው።

የጎሰኞች የእርስ በርስ ግጭትና ተደራድሮ መስማማት  ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና ለሕዝቧም አብሮነት ዋስትና የለውም።የወያኔና የኦነግ ኦሕዴድ ብልጽግና እርቀ ሰላም ለዳግም የተባበረ ዘረፋና የእርስ በርስ ጦርነት፣ብሎም ለአገር መፈራረስ የሚያበቃ የሌቦች ስምምነት ነው።እውነተኛና ዘላቂ ሰላም በሕዝቡ አንድነትና በነዚህ መንታ ጠላቶች መቃብር ላይ ይመሠረታል እንጂ በነሱ የሥልጣን ወንበር  መከፋፈል አይረጋገጥም። ፍትሕም በጸረ ፍትህ ሃይሎች አይሰፍንም።በኦነግ ኦሕድድ ብልጽግና ና በወያኔ ፈቃድና ፍላጎት የሚገኝ ሰላም፣ አንድነትና ፍትሕ አይኖርም።የነሱ መንገድ ሁሌም የጥፋት መንገድ ነው።ሕዝቡን ያጫረሱ ወንጀለኞች፣አገር የከዱና ለባእዳን ያደሩ በመሆናቸው በሕግ ይጠየቃሉ እንጂ በነጻና በይቅርታ እንዲኖሩ መፈቀድ የለበትም። እንዲያ ከሆነ ፍትሕን ባፍጢሙ መድፋት ይሆናል።

የስርአትና ያስተሳሰብ ለውጥ እንጂ የመሪዎች መቀያዬር፣ መውጣትና መውረድ፣መሻርና መሾም የተሻለ ለውጥ ወይም መፍትሔ አያመጣም።ያለፉት መቀያዬሮች ማስረጃዎች ናቸው። ከሃምሳ ዓመት ወዲህ አምስት ሥልጣኑን የያዙ መሪዎች ነበሩ።ከነሱም ጋር ብዙ ሚንስትሮችና  ባለስልጣኖች መጥተው ሄደዋል።በነሱ መለዋወጥ የሕዝቡ ችግር አልተወገደም።አሁንም በተመሳሳይ የአስተሳሰብ በረት ውስጥ ያሉ ቦታ ቢለዋወጡ ወይም ሥልጣን ላይ ቢወጡ ውጤቱ ያው በገሌ ነው።ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ!ስለሆነም የምንፈልገውን ለውጥ ማወቅ አለብን።ያንንም መርህ አድርገን እስከመጨረሻው ድረስ እንያዘው፤ለዚያም እንታገል! በጥቃቅን ሽንገላና ማጭበርበር አንታለል።መርሃችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማዳን ነው።የሕዝቧንም አንድነትና አብሮነት ብሎም እኩልነት ማረጋገጥ ነው።ለዚያም የጠላት ጎራ ሊያጠፋው የሚረባረብበትን ዋናውን መሰሶ አማራውንና ከጎኑ የሚሰለፉትን በኢትዮጵያዊ,ታቸው የሚኮሩትንና የማይደራደሩትን ማህበረሰቦች ማዳንና ማጠናከር ተገቢና አስፈላጊ ነው።ያ ነው መርህ ማለት!

አገሬ አዲስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share