ህወሃትን የተካው ኦነጋዊያን በበላይነት የሚያሽከረክሩት የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት ይችላል
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ክፍል ሁለት የአራት
ክፍል ሁለት
ኢትዮጵያ ወደ የት እያመራች ነው? የሚለውን የቀድሞው ጠ/ሚንስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ግልጽ በሆነ ደረጃ አስቀምጠውታል። የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያንና 120 ሚሊየን ሕዝቧን ከድጡ ወደ ማጡ እያሸጋገሯቸው ነው።
“አማራና ኤርትራን ካስከፋን ተበላን” ጃዋር ሞሃመድ ለኦሮሞ ብልፅግና አመራር የሰጠው ማስጠንቀቂያና መልእክት።
የብልጽግና ፓርቲ፤ ከዚያ በፊት ህወሃት ለራሱ የበላይነት የመሰረተው ኢህአዲግ ሥልጣን ከያዘበት ጀምሮ አማራው በራሱ አገር የከፋው መሆኑን መስዋእት እየከፍለ ይፋ አድርጓል። ሰሚ ግን አላገኘም።
“ኬኛንት” ተባባሰ እንጅ ዛሬ አልተጀመረም። በቅርቡ አዲስ አበባ በተካሄደው የብልፅግና መሪዎች ጉባኤ የኦሮሞ ብልፅግና መሪዎች ተራ በተራ ያቀረቡትን መረን የለቀቀና አደገኛ “የኬኛነት” ትርክት ስሰማ ይህ ህወሃትን የላቀ ቡድን በአማራው ሕዝብና በመሪዎቹ ላይ “ከመተናኮስ” አልፎ በአዲስ አበባም ሆነ በቀረው ኢትዮጵያ ላይ አዛዢዎቹ እኛ ብቻ ነን የሚል ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ የአማራ ብልፅግና የበላይ አመራር በተቀነባበረ ድምጽ ለኦሮሞ ብልፅግና አመራር ያልጠበቀውን ማስጠንቀቂያ አቅርቧል። ተራውን የአማራ ሕብብ ብሶትና ጩኸት ሰምቷል ማለት ነው። ይህ አቋም ተገቢ ስለሆነ እንዲቀጥል እመክራለሁ።
ይህንን ሃተታና ምክረ ሃሳብ የምጽፈው የእልቂት ኢላማ ለሆነው ለአማራው ሕዝብ አይደለም። ህወሃትን ለተካው ለኦሮሞ ብልጽግ ፓርቲም አይደለም። በህወሃትና በኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ግፍና በደል ለሚጠቃው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ፤ በሰብእነቱ፤ በፍትህ-ርተእ ለሚያምነው፤ የኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ ለሚያስጨንቀው ለሰፊው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ነው።
ሮኬት ሳይንስ አይደለም። ዛሬ በአማራው ላይ የሚካሄደው ጭካኔ ነገ በወላይታው፤ በጉራጌው፤ በሶማሌው፤ በአኟኪ ወዘተ ሕዝብ ላይ እንደሚደርስ እንመን። “ኬኛነት”፤ ተስፋፊነት፤ የበላይነት፤ ኢ-ሰብአዊነትና ኢ-ፍትሃዊነት ዳር ድንበር የለውም። የፖለቲካ፤ የመከላከያ፤ የደህንነት፤ የባጀት፤ የባንክ አገልግልግሎት ስርጭት፤ የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር፤ የከተማ መሬት ስርጭት የበላይነትን የያዘው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑ ሊካድ አይችልም።
በህወሃት ዘመነ መንግሥት ሁሉን አቀፍ የበላይነት የያዘው ህወሃት እንደ ነበረ እናስታውሳለን። አንድ ዘውግ የበላይነት ሲይዝ ሌብነት፤ አድልዎ፤ ሙስና የተለመደ መሆኑን በህ ሃት ዘመን አይተናል። በተመሳሳይ፤ ዛሬ ብልግና፤ የአስተዳደር ብልሽት፤ ሙስናና አድልዎ ፈር ለቀዋል። ሙስና ስል የባጀት፤ የገንዘብ፤ የውጭ ምንዛሬ ና ተዛማጅ ጉዳዮችን ብቻ ማለቴ አይደለም። በእነዚህና በመሬት አጠቃቀም የተከሰተው ሙስና በፖለቲካም እንደተከሰተና እንደሚከሰት ማሰብ አለብን እላለሁ። እንዲያውም ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው የፖለቲካው ሙስና ነው። ተቋማትን ያመክናል። የሕግ የበላይነትን፤ ተጠያቂነትንና ሃላፊነትን ቀፎ ያደርጋል።
በሰባዊ መብትና ደህንነት መስፈርት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የተከሰተውን ጭካኔ ማየቱ ይበቃል። በሰሜን ህወሃትና የውጭ ግብረ አበሮቹ አፋሩን፤ አማራውን፤ ትግራዩንና ኤርትራዊያንን ሲያዋክቡ “ኬኛዎቹ/ ተረኞቹ” በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እጅግ በጣም የሚዘገንን እልቂትና ውድመት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
- በወለጋ፤ ኦሮምያና በአዲስ አበባ ዙሪያ በተደጋጋሚ መንገዶች፤ የመጓጓዣ አገልግሎቶች፤ የዜጎች እንቅስቃሴ ተዘግተዋል፤ ተጓጉለዋል፤ አስጊ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። የሕግ የበላይነት ዜሮ ሆኗል።
- ባለፉት ሁለት ዓመታት በምስራቅ ወለጋ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ሰብአዊ አገግሎት(Basic human services)–የባንክ፤ ንግድ፤ የመገናኛ፤ የመጓጓና ሌላ መሰረታዊ አገልግሎት እንዳይካሄድ አድርጓል። ይህ የሚያስታውሰኝ ለአስርት ዓመታት ህወሃት በወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ ያደረገውን አፈናና ጫና ነው።
- ከህወሃት ባላነሰ ደረጃ የታጠቀው የኦሮሞ ክልል ልዩ ኃይል በወለጋ የሚኖሩትን የንጹሃን ኢትዮጵያዊያን ደህንነት በመታደግ ፋንታ ከኦነግ ሸኔዎች ጋር በማበር የእልቂቱ አካል ሆኗል። ሁለት ሸኔዎች አሉ የሚለው ማዘናጊያ እንጅ የአማራው ፋኖ ወይንም ሚሊሽያ ወይንም ልዩ ኃይል ታጥቆና ድጋፍ አግኝቶ በኦሮሞ ወይንም በሌላው ወገኑ ላይ ጭፍጨፋና ዝርፊያ ያካሄደበት አንድም መረጃ አላገኘሁም። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ “ሁለቶ ሸኔዎች አሉ” ብለው መናገራቸው ከእሳት ላይ ቤንዚን እንደ መጨመር ሆኖ ይታያል። ይህ ከማዘናጊያ በላይ አደጋውን አባብሶታል።
- የኦሮሞ ብልጽግና መንግሥት በወለጋ፤ ኦሮምያ ብቻ ከ 200 በላይ የሚገመቱ የአማራ ብሄር አባላትን አስሮ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የሚያጉር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።
- የኦሮም ብልጽግና ፓርቲ በበላይነት የሚያሽከረክረው የፌደራል መንግሥት መከላከያ ኃይል በምስራቅ ወለጋ የሚካሄደውን ኢ-ሰብአዊ፤ ኢ-ፍትሃዊ ጭፍጨፋና አፈና ለማቆም እርምጃ አለመውሰዱ በራሱ በአማራ ሕዝብ ላይ በየትም ቦታ የሚካሄደው ግፍና በደል የማያቆም መሆኑን ያሳያል።
- በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ “ኬኛዊንትና” የበላይነት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ የአንድ ብሄር አገር ለማድረግ ከሚደረገው አደገኛ ሴራ ለይች ለማየት አልችልም።
ሰሚ የለም እንጅ ሰሚ ቢኖር ክቡር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “ብልጽግናዎች አማራን በመተናኮስ ሊወጡት ወደማይችሉበት ገደል ውስጥ እንዳይገቡ” የመከሩትን ቢተገብሩ ይሻላል። ወደ ገደል ከገባን ማንም አትራፊና የበላይ ሊሆን አይችልም። እኔ በበኩሌ የምመኘው ህወሃትን አስወግዶ በኦሮሞ ብልጽግና መተካትን አይደለም። ይህ አዝማሚያያ ባስቸካይ እንዲቆም ካልተደረገ ኢትዮጵያን ወደ ገደል እንደሚወስዳት አልጠራጠርም።
እትዮጵያ በአማራው መቃብር ላይ ልትቀጥል ወይንም ልትመሰረት አትችልም።
አማራውን ከባሰ እልቂት ለመከላከል ራሱን የማደራጀትና ከሌሎች አገር ወዳዶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት የመመስረት ግዴታ አለበት። ለምሳሌ ከአፋር፤ ከሶማሌ፤ ከጉራጌ፤ ከትግራይ፤ የኦሮሞን “ኬኛነት” ከማይደግፉ ኦሮሞዎች፤ ከወላታው ወዘተ ሕዝብ ጋር።
ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ከመኖር ይልቅ አለመኖርን የሚመኙ ብዙ ሚሊየን ንጹሃን መኖራቸው በራሱ ራሳችንን እንድንገመግም ያስገድዳል። መሰረታዊ የአሳተሳሰብ እና የስርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል። የኦሮሞ ብልፅግና አላማው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊንትን መታደግ አለመሆኑን በአይናችን እያየን ነው።
ስርዓተ መንግሥቱን በመሻሻል ፍትሃዊ፤ ሁሉን አቀፍ አና ዲሞክራሳዊ በመሆን ፋንታ ወደ ገደል ጫፍ መድረሱ ለምን ይሆን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የታወቁት ምሁር አማርትያ ሴን እንዳሉት( The question is no longer whether a state is fit for democracy; but how to make a state fit through democracy.” Amartya Sen
ኢትያጵያን እንዴት እናሻሽላት፤ እንዴት ፍትሃዊ እናድርጋት እንጅ እንዴት እንቀራመታት የሚል የፖለቲካ ሂደት አያዋጣም።
ኢትዮጵያ ወደ የት እየተጓዘች ነው? (Quo Vadis Ethiopia?) የሚለውን ጥያቄ የኢትዮጵያ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ የፖለቲካ መሪዎች ወዘተ ሲነጋገሩበት ውሎ አድሯል ብል አልሳሳትም። ከመወያየት ውጭ ግን አመርቂ የሆነ፤ ሁሉን ኢትዮጵያዊያን የሚወክል፤ እትዮጵያንና 120 ሚሊየን ሕዝቧን ፍትሃዊ በሆነ ደረጃ የሚመጥንና የሚያገለግል አማራጭ ለመስጠት አልቻሉም። ቢችሉም ኢትዮጵያን በበላይነት የሚገዙት ስርዓቱ ኮልኩሎና ተንከባክቦ እድል የሰጣቸው ኃይሎች አያዳምጡም። አይፈቅዱም።
በአሁኑ ወቅት በማንኛውም የኢትዮጵያ መንግሥት አገዛዝና አስተዳደር መስፈርቶች ብልሹነት–የፍርድና የፍትህ አሰጣጥ ግድፈት፣ የዜጎች ደህንነትና ሰብእነትና ዋስትና ማጣት፤ የባጀት አመዳደብ ኢ-ሚዛናዊነት፤ የገቢና ወጭ ቁጥጥር ግድፈትና ግልጽነት አለመኖር፤ የሌብነት፤ ጉቦና ሙስና ቁጥጥር ጥልቀትና ስፋት መያዝ፤ የአዲስ አበባ የቤት፤ የመሬት ነጠቃ፤ መስፋፋት እና የነዋሪዎች መፈናቀል፤ የኢትዮጵያን መለያ ሰንደቅ ዓላማ በሌላ ባንዲራ ለመተካት የሚደረገው ጫና፤ በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ እምነት አለመኖር ወዘተ መስፈርቶች ሲገመገም ኢትዮጵያ እንደ ሃገርና እንደ ሃገረ መንግሥት ጤናማ አይደለችም ለማለት ያስደፍራል። ለምሳሌ፤ በአዲስ አበባ ቤታቸው እንዲፈርስና የመንገድ አዳሪ እንዲሆኑ ያደረጋቸው አካል በሃላፊነት የሚጠይቅ የበላይ አካል አለ? ለምን? እነዚህ ዜጎች ለማን አቤቱታ ያቅርቡ?
በኔ ግምገማ፤ ጠባብ ብሄርተኛነት፤ የብሄር ጽንፈኛነት፤ የዘውግ ፖለቲካ፤ በዘውግና ቋንቋ የተዋቀረ ሕገ መንግሥት፤ ስርአትና አስተዳደር ከእውነተኛ፤ ፍትሃዊ፤ ሁሉን አሳታፊ፤ የእያንዳንዱን ዜጋ መብትና ግዴታ ከሚያስተናግድ ፌደራል ስርአት እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ጋር አብረው ሊሄዱ አይችሉም።
ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት ሃገረ መንግሥት ሲመሰርቱና ፓርቲዎቻቸውን ሲያዋቅሩ “እኛ ለሕዝባችን እናውቃለን” በሚል ሰበብ ከላይ ወደ ታች የመመስረት ልምድ አላቸው። ዛሬም ከዚህ ልምድ ለመውጣት ተቸግረናል። ለሕዝብ ተገዢና ተጠሪ ያልሆነን መንግሥት በሃላፊነት የሚዳኘው ማነው? የሚለው ጥያቄ ፊታችን ላይ ተደቅኗል። ሕግ አውጩ፤ ሕግ አስተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው የአንድ ሳንቲም ግልባጭ አባላት ናቸው።
በተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ልዩነት የለም ለማለት አልችልም። ግን በሕዝቡ መካከል ያለው ልዩነት በሽምግልናና በምክክር ሊፈታ ይችላል።
ሆኖም፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነት/እህትማማችነት ላይ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወተው የገዢው ክፍል አካል የሚከተለው መርህ ሕዝብን ማእከል ያላደረገ፤ መርሁ ከላይ ወደታች እንጅ ከታች ወደ ላይ ሆኖ ሕዝቡን የስልጣን መሰረት ያደረገ ሆኖ አላገኘሁትም።
በሕዝብ ተሳታፊነትና ጫና ፈጣሪነት መስፈርት ስገመግመው ሕዝብን የሥልጣን መሰረት አድርጎ አቅሙን ማጠናከር አስፈላጊ ነው የሚለው መርህ ፈር ለቋል ለማለት እችላልሁ። ይህ ሁኔታ ኮሚሽን በማቋቋም፤ በልሂቃን ምክክርና እና በሰበካ ብቻ ሊፈታ አይችልም። ውይይቱ ከታች ወደላይና ጎነ ለጎን (Grassroots level and horizontal) ቢሆን የተሻለ ውጤት ይገኛል የሚል እምነት አለኝ።
አፋሩና ኦሮሞው፤ ኦሮሞውና ትግራዩ፤ ሶማሌውና አማራው ወዘተ እንዲነጋገር ማድረግ እንዴት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል? ኦነግ ሸኔ ንጹሃን አማራዎችንና ኦሮሞዎችን ለመጨፍጨፍ የሚችለው የክልሉ ባለሥልጣናትና ተራው የኦሮሞ ሕዝብም መሸሽጊያ ሆነው ስለሚሰሩ ነው የሚሉ ደፋር ኢትዮጵያዊያን አሉ። እነሱ የሚሉትን ሃቅ የሚሰማ ባልሥልጣን ግን አላይም።
አንድ የስርአተ መንግሥትና የአስተዳደር ጥያቄ ለኢትዮጵያ መሪዎች ላቅርብ።
ይኼውም፤ ለመሆኑ መቸ ነው ሕዝቡን ፈርታችሁ፤ ከሕዝብ ርቃችሁ፤ የሕዝቡን የመግዛት አቅም አዳክማችሁ፤ በምትሄዱበት ሁሉ ሕዝብ በሚሰጠው ታክስ በመሳሪያ ታጅባችሁ፤ የባጀት ክፍተት ሲከሰት ቀረጥ እየጨመራችሁ፤ ሕዝቡ የመሬቱና የቤቱ እውነተኛ ባለቤት እንዳይሆን ሰበብ እየፈጠርፋችሁ ለመግዛት የምትችሉት? ይህ የአስተዳደር ብልሹነት ካልተፈታ የጨነቀው ሕዝብ ቢነሳ ይፈረድበታል?
ይቀጥላል
January 17, 2023