አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት ሰዎች ራሳቸውን/አቋማቸውን በቅጡ ሊፈትሹ ይገባቸዋል?! (በዘርዓያዕቆብ)

 

  1. እንደመንደርደሪያ

‘‘ወያኔ/ትግሬ ከሚገዛኝ ሳጥናኤል ቢገዛኝ ይሻለኛል?!’’

(አቡነ ጴጥሮስ/የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ)

ዋልድባ የማን ነው… እዚህ ቁጭ ብላችሁ ጣላችሁን ከምትጠጡ ግንባር ዘምታችሁ አንድ እፍኝ የማይሞሉ ሰዎችን መደምሰስ አቅቷችሁ ነው …?!

(አቡነ መቃርዮስ/ሊቀ ጳጳስ)

‘‘በዚህ ጦርነት ላይ የሰማይ ሰራዊት ጭምር ሊሳተፉና ከጎናችን ሊቆሙ ይገባቸዋል፤’’

(አቶ አበባው አያሌው፤ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር)

‘‘… ወያኔ/ሕወሓት ከምድር-ገጽ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ አእምሮም ሊሰረዙ ይገባል …’’

(የተከበሩ የፓርላማ አባል፣ ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት)

‘‘የወያኔ ባንዳነት፣ ክህደት የታሪክ መሠረት ያለው ነው… ለአብነትም የትግራዩ ዐፄ ዮሐንስ ዐፄ ቴዎድሮስን አሳልፎ በመስጠት …፤’’

(ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ/የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል)

‘‘… የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነውርግጠኛ ነኝ አሁን የትግራይ ሕዝብ ‘እገነጠላለኹቢል እዚህ ምክር ቤት ውስጥ ያላችሁ ሁላችሁም መጮኻችሁ አይቀርም፤ ስለዚህ ለሕዝቡ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደርሰው መንገዶች መከፈት ይኖርባቸዋል …’’

(ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ በጦርነቱ ወቅት ለፓርላማ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)

  1. አነጋጋሪውየአንዳንድ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት ሰዎች አቋም       

ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ ባለፈው ሰሞን ከቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ ‘‘ርዕዮት ሚዲያ’’ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ አንድ ነገር ተናግሮ ነበር፡፡ ይኸውም የሰማዕቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የግፍ አሟሟት የተመለከተ ነበር፡፡ ደረጄ በዚሁ ቃለ-መጠይቁ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መንግሥት የመገደላቸው ምክንያት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ ጋር ደብዳቤ ሲጻጻፉ ተደርሶባቸው እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡

በጊዜው ይህን ቃለ-መጠይቅ የሰሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ካህን የኾኑ ሰው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ የተናገሩት ነገር ፍጹም ስሕትት መሆኑን እንደነገሩት ከሰለሞን ሹምዬ/ገበያኑ ጋር በነበረው ቆይታ አንስቷል፡፡ ስለሆነም ደረጄ ቅዱስነታቸውን በተመለከተ ላስተላላፈው የተሳሳተ መረጃ ይቅርታ ለመጠየቅ እንደወሰነ ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ለማለት ይህንን ዕድል በጉጉት ሲጠባበቅ እንደነበር ገልጾልናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በ19 ዓመቴ ወልጄው ሞቷል ያልኩት ልጄን አገኘሁት (ከዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ ጅግሳ0

ዶ/ር ደረጄ አክሎም፤ ‘‘ይቅርታ ማለት ካለብኝ ግን ይቅርታ ለማለት የምፈልገው የቅዱስነታቸው የሥጋ ዘመዶች እንጂ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ለመጠየቅ ፍላጎቱም ሐሳቡም እንደሌለው፤’’ ከሰለሞን ሹምዬ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ በግልጽና በድፍረት ነግሮናል፡፡

ዶ/ር ደረጄ ለዚህ አቋሙ ምክንያቱን ሲገልጽም፤ ‘‘… ወያኔ/ትግሬ ከሚገዛኝ ሳጥናኤል ቢገዛኝ ይሻለኛል …!!’’ የሚል ጳጳስን ተሸክማ የምትኖር ቤተክርስቲያን ከእኔ ይቅርታን የምትሻበት የሞራል መሠረትም፣ ሆነ የሞራል ተጠየቅ ሊኖራት አይችልም፤’’ ሲል በአጽንኦት ተናግሯል፡፡

ዶ/ር ደረጄ በቃለ-ምልልሱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አባቶች ላይ የሰነዘረውን ወቀሳ መሠረት አድርግንና የሐሳቡን ፈር እንደያዝን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት- የአንዳንድ አባቶችና የመንግሥት ሰዎችን አቋም ምን ይመስል እንደነበር መፈተሽና መነጋገር ግድ ይለናል፡፡

በዚህ የጦርነት ወቅት ዘንባባ ይዘው፣ አሊያም እንደ ጋሞ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለምለም ሳር ወይም የወይራ ዝንጣፊ ይዘው ስለዕርቀ-ሰላም መናገር የነበረባቸው የሃይማኖት አባቶች ጦርነቱን በመደገፍ መልእክት ሲያስተላልፉ በመገርምና በኀዘን ውስጥ ሆነን ሰምተናቸዋል፡፡ ለአብነትም ያህል፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት የግንቦት 7 የአርበኞች ሰራዊትን በረሃ ድረስ ወርደው ሲያበረታቱ አብረው ፎቶ ተነስተው ምሰላቸውን ያየናቸው አባት አቡነ መቃርዮስ፣ በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ባደረጉት ንግግራቸውም፤

‘‘… እነዚህን እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች ተዋግታችሁ ጠላቶቻችሁን መደምሰስ ነው እንጂ እዚህ ቁጭ ብላችሁ ጠላችሁን እየጠጣችሁ ምን ታደርግላችሁ…?!’’ የሚል ዝምት፣ ተዋጋ… የሚል ንግግራቸው በመገናኛ ብዙኃን ተመዝግቦ አለና እናስታውሰዋለን፡፡

በተመሳሳይም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በትምህርት ረገድም እስከ ፒ.ኤች.ዲ. ድረስ ዘልቀው ተምረዋል የሚባሉት ሌላው አባት አቡነ ጴጥሮስ/ሊቀ ጳጳስ በጦርነቱ ወቅት፤ ‘‘… እነርሱ/ወያኔ ከሚገዛን ሳጥናኤል ቢገዛን ይሻላል!’’ የሚል አባታዊ መልእክትን/ምክርን አስተላልፈዋል፡፡

ከሃይማኖት አባቶች ባሻገርም፤ ከመንግሥት ሹመኞች መካከልም፤ የቅርስ ጠበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር የኾኑት አቶ አበባው አያሌው በብሔራዊ ቴያትር- ለመከላከያ ድጋፍ በተጠራ አንድ መድረክ ላይ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዉጭ ያሉ ተቃዋሚዎችን ለማሰባሰብ የሚረዱ ነጥቦች - ክፍል አንድ

‘‘… በዚህ ጦርነት የሰማይ መላእክትም ሊሳተፉና ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል!’’ ሲሉ… የጦርነቱን ፍትሐዊነትና ቅዱስ ጦርነት መሆኑን ጭምር፤’’ በአጽንኦት ሊያረጋግጡልን ሞክረዋል፡፡

የዕርቀ-ሰላም ሰባኪና መምህር ሊሆኑ የተገባቸው አባቶች ስለሰላም ለመስበክ ባይቻላቸው እንኳን አደባባይ ወጥተው ጦርነትን የሚያበረታታ እንዲህ ዓይነት መልእክት ማስተላለፋቸው ብዙዎችን አስገርሟል፣ አስደንግጧልም፡፡ ኮሜዲያን እሸቱ በቅርቡ በተለቀቀው ስታንዳርድ የኮሜዲ ሥራው ጦርነቱን ‘‘የብሩካን ጦርነት’’ ሲል በኀዘኔታ መንፈስ ገልጾታል፡፡ ሌላኛውና ‘‘የጠቅላይ ሚ/ሩ አማካሪ’’ ናቸው የሚባሉት ሰው ዲ/ን ዳንኤልም፤ በመረረ ጥላቻና ምሬት ውስጥ ኾነው፤

‘‘… ወያኔ/ሕወሓት ከኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ መደምሰስ ብቻ ሳይህን ለወደፊቱም እንደ እነርሱ ዓይነት ሰዎች በምድሪቱ እንዳይፈጠሩ ማድረግና በትውልድ አእምሮ ውስጥ ምንም ዓይነት መታሰቢያ እንዳኖራቸው አድርጎ ማጥፋት፣ መደምሰስ ይገባል …፡፡’’ የሚል መልእክትን አስተላልፈዋል፡፡

የሚገርመው ነገር ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ከአንጀታቸውም ይሁን ከአንገታቸው ጦርነቱ የእርስ በርስ ጦርነትና የወንድማማቾች እልቂት መሆኑን በፓርላም ጭምር ተናግረው፣ ለሰላማዊ መፍትሔ መንገዶችን፣ አማራጮችን ማፈላላግ ይኖርብናል እያሉ በሚወተውቱበት ጊዜ እንኳን- ጠቅላይ ሚ/ሩ አብራዋቸው ያሉ ሹመኞቻቸውና የቅርብ ሰዎቻቸው ጭምር ከእርሳቸው ሐሳባቸው ተቃራኒ የኾነ አቋም ነበር ሲያራምዱት የነበረው፡፡ እንደውም እነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ፤

‘‘ሕወሓት/ወያኔ ጠላት፣ የሕዝብና የሀገር ዋና አደጋ በመሆኑ ያለን የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው መፍትሔ እነርሱን ከኢትዮጵያ ምድር መደምሰስ፣ ማጥፋት ነው፤’’ በሚል አቋማቸው ጸንተው- ‘‘ጦርነቱ ለምን ሲባል ይቆማል?!’’ በማለት በየሚዲያውና በየዩ ቲዩብ ነጋዴዎች ዘንድ ይህን አቋማቸወን ሲያራምዱ በአግራሞት ታዘበናቸዋል፡፡

የመንግሥት ሰዎችም ሆኑ ምሁራኑ ሕወሓትን ከኢትዮጵያ/ከትግራይ ምድር ስለማጥፋት ሲናገሩ አንድ የሳቱት ሐቅ አለ፡፡ ይኸውም፤ ሕወሓት/ወያኔ የትግራይ ሕዝብ አካል ብቻ ሳይሆን የትግራይ እናቶችና አባቶች የልጆቻቸውን ደምና አጥንት የገበሩለት ግማሽ ምዕተ ዓመታት ለማስቆጠር የቻለ ድርጅት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ጦርነት ሕወሓት ከትግራይ ሕዝብ ጋር መቼም ላይለያይ የመንፈስ ውሕደትን ጭምር ዕውን ያደረገ ድርጅት ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ ይህ የታሪክ ሐቅ፤ ‘‘ሽብርተኛ፣ የሀገር፣ የሕዝብ ጠላት ነው’’ ተብሎ ለተፈረጀው ለኦነግና ለኦነጋውያንም የሚሠራ ነው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ወራሪው ማን ነው? ተወራሪዎቹስ? – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

በኦሮሞ ሕዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ ኦነግ ትልቅና የከበረ ስፍራ እንዳለው መዘነጋት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ይህን የታሪክ ሐቅ የአሁኖቹ የኦሕዴድ ብልጽግና ሰዎች አሳምረው ያውቃሉ፤ ያምናሉም፡፡ አብዛኞቹ የኦሮሞ ባለሥልጣናትም ለኦሮሞ ሕዝብ የመብትና የእኩልነት ትግል ታሪክ ውስጥ ከነክፍተቱም ቢሆን ደማቅ አሻራ ያለውን ኦነግን መቼውንም ቢሆን ከልባቸው ሊፍቁት እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹም የድርጅቱ የትግል አጋርም ናቸው፡፡ ስለሆነም የሕዝብን ትግል መቼውንም ቢሆን ማዳፍን እንደማይቻል ማወቅ ይበጃልና መፍትሔው ሰላማዊ አማራጭ የኾነው- በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር፣ መወያየት ብቻ ነው፡፡

  1. እንደመውጫ

ላለፉት ሁለት ዓመታት ባደርግነው ጦርነት እንደታዘብነው- የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራንና ምሁራን ሚናቸውና ምክራቸው ሊሆን የሚገባው ሰላማዊ መፍትሔ እንጂ በወንድማማቾች ጦርነት መካከል የጦርነት ነጋሪ መጎሰም ሊሆን ባልተገባው ነበር፡፡ ‘‘ለይቅርታ፣ ለፍቅርና ለሰላም ሐዋርያ፣ አምባሳደር ናቸው’’ ተብለው የተጠሩ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን ትልቁ ሥራቸው ሊሆን የሚገባው ሰላምን በቃልም በተግባርም ማስፈን ነው፡፡ እነዚህ አባቶቻችን መመሪያ አድርገው የተቀበሏቸው የሃይማኖት መሠረት የኾኑት መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርአን ትልቁ መልእክታቸውም ‘‘ሰላምና ሰላም’’ ነውና፡፡

እንዲሁም ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍላ ያስተማረቻቸው ምሁራኖቻችንም ከጦርነት ይልቅ ለሕዝቦች አንድነት፣ ሰላምና ኅብረት የሚበጁ የታሪክ ሰበዞችን እየመዘዙ ወደፊት እጅ ለእጅ ተያየዘን የምናድግበትን የሰላም ጎዳና ሊያሳዩን ነው የሚገባቸው … እንጂ እንዴት ታሪክን እያወላገዱ አንድን ሕዝብ በባዳነት ፈርጆ በወንድማማች ሕዝብ መካከል ጠላትነትንና የመለያየትን ግምብ ለመገንባት ይደፍራሉ፡፡

ምሁራኖቻችን ሀገር በጭንቅና በመከራ ውስጥ በገባች ጊዜ የመውጫ መንገድ የሚያሳዩን ብልሆች፣ አስተዋዮች፣ ሩቅ አሳቢና አላሚ ሆነው በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የብርሃን ወጋገን፣ የተስፋን ጨላንጭል የሚያሳዩን መሆን አለባቸው እንጂ- በመከራችንና በሰቆቃችን ጊዜ አብረውን የሚያለቅሱና የሚያላቅሱ ሊሆኑ ባልተገባቸው ነበር፡፡ ስለሆነም አንዳንድ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራኖች ራሳቸውን፣ አቋማቸውን በቅጡ በመፈተሽ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሕዝብ መካከል መቀራረብ፣ አንድነት፣ ሰላም፣ ልማት… እንዲሰፍን በቃልም በተግባርም ሊሠሩ ይገባቸዋል እላለኹ፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!

1 Comment

  1. ዶ/ር ደረጀ ለርዮት ሚዲያ የሰጠውን ኢንተርቪው አዳምጨዋለሁ። አቡነ ቴዎፍሎስን እና ቄስ ጉዲና ቱምሳን አምታቷል። ሁለቱ የተገደሉት አንድ ላይ ነው። ደርግ ቄስ ጉዲናን የገደልኩት “ለኦነግ ወረቅት ሲያመላልሱ ነው” ብሎ ግድያውን ጀስቲፋይ ለማድረግ አስወርቷል። ስለአቡነ ቴዎፍሎስ አላውቅም። የደረጀ ስህተት ሰዎቹን ማምታቱ ሳይሆን ለርዮት ሚዲያ የተናገረው ሲተረጎም “ደርግ የሃይማኖት አባቶች ቢሆኑም መግደሉ በምክንያት ስለሆነ ስህተት አይደለም” ማለቱ ነው።
    በነገራችን ላይ አንድ ቀን ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ያማያውቀው ሁሉ የሃይማኖት አባቶችን ሲሳደብ እና ሲረግም ማየቱ የሚገርም ነው። የሃይማኖት አባቶች መዋረድ የጀመሩት ከአብዮቱ ጊዜ ጀመሮ ነው፣ ጥራዝ ነጠቅ ኮሚኒስት ነኝ ባይ ተማሪ ሁሉ ሊቀመንበር ማኦ “religion is the opium of the society” ብሏል ‘ታቦት እንጨት ነው” እያለ ቤተ ክህነትን አዋርዷታል። የደረጀ ይቅር (ህጻን ስለሆነ!) በተለይ “ያ ትውልድ” የሚባለው ዉስጥ የነበራቾሁ የህይማኖት አባቶቻችንን የመናገር አንድም ሴንቲሜትር የሞራል ከፍታ እንደሌላችሁ ማስታወሱ ተገቢ ነው። መተቸትም ካለባችሁ በግለሰብ ደረጃ “ያጠፋውን” የሃይማኖት አባት ስም ጠርታችሁ እንጅ በጅምላ መሆን የለበትም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share