የታቀደው የመንግሥትና የሕወሃት ንግግር፣ መሰናክሎቹና የሚጭረው ተስፋ – ባይሳ ዋቅ-ወያ

bayisa wak woya `
ባይሳ ዋቅ-ወያ

*****

ከሁለት ዓመት መገዳደል በኋላ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላም ለመቋጨት አሸማጋዮች ተሳክቶላቸው በደቡብ አፍሪካ ሊደረግ የነበረው ንግግር ሳይሳካ መቅረቱ ብዙዎችን አሳስቧል። በተለያዩ ምክንያቶች። አንዳንዶች ከመጀመርያውም “ከከሃዲ ጁንታ” ጋር ሰላማዊ ንግግር አያስፈልግም፣ ወሳኝ ወታደራዊ መፍትሔ እንጂ የሚሉ ወገኖች በንግግሩ መክሸፍ ተደስተዋል። ሌላው ደግሞ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚደረገው ንግግርና ብሎም ስምምነት ብቻ ነው ብለው የሚያምነው ወገን በንግግሩ መክሸፍ አዝኖአል። የንግግሩ (ድርድር ደረጃ ላይ ገና አልተደረሰም) ሂደት ምን ይመስል ነበር? አሸማጋዮችስ ሁለቱን ወገኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ ለማምጣት ለምን ይህ ሁሉ ጊዜ ፈጀባቸው? ሁለቱን አካላት በደቡብ አፍሪካ ለማገናኘት እያጋጠማቸው ያሉ መሰናክሎችስ ምን ይመስላሉ? በጠረጴዛ ዙርያ ከተቀመጡም በኋላ ሊያጋጥም የሚችለው የስምምነት ነጥብ (ቦች) ምን ይመስሉ ይሆን? በለስ ቀንቷቸው ከተስማሙና አንዳች ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አስፍረው ወደ ኢትዮያ ከተመለሱ በኋላ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሊያጋጥም የሚችለው መሰናክልስ ምን ሊመስል ይችላል ለሚሉ ተገቢ ጥያቄዎች በከፊልም ቢሆን ለማስረዳት ከማለት ይህንን በግል ተሞክሮዬ ላይ የተመሠረተውን ጽሁፍ ላካፍላችሁ ወሰንኩ።

 

ድርድር በተለምዶ ማሟላት ያለበት አጠቃላይ ቅድመ ሁኔታ አለው። ሁሉንም ድርድር ሊመራ የሚችል ሁሉን አቀፍና አንድ ወጥ የሆነ ፍኖተ ካርታ ግን የለም። እያንዳንዱ ግጭት ከሌሎች ግጭቶች የሚለየው የራሱ የሆነ የግጭት መነሻ ታሪካዊ ምክንያት አለውና! ስለዚህ ዛሬ ሊካሄድ እየታሰበ ያለውን ንግግር (ቀጥሎም ድርድር) መገምገም የምንችለው በኢትዮጵያዊነት መነጽር ብቻ ነው። አንዳንዶቻችን ሁለቱም አካላት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው ለመነጋገር ከወሰኑ በኋላ ጦርነቱ ለጊዜውም ቢሆን ለምን አልቆመም የሚል ቅሬታ እያቀረብን እንገኛለን። ቅሬታው ተገቢ ነው። ሆኖም ግን፣ በድርድር ወቅት ጦርነትን መቀጠል ያልተለመደ ነገር አይደለም። በተለይም አንደኛው ወገን የበላይነትን እየተቀዳጀ ባለበት ሁኔታ። ንግግሩን ለማስጀመር ረጅም ጊዜ የፈጀውስ ለምንድነው? የምንልም አለን። በኔ ግምት የኦባሳንጆ የአንድ ዓመት ሙከራ ረጅም ጊዜ ነበር ሊባል አይቻልም። የግጭቱን መንስዔና የተጋጩ አካላትን ማንነትና ትውልድ ዘለል “የጀግንነት ባሕላችንን” ጠንቅቀን እናውቃለንና!

 

በውጪ ወራሪ ኃይልና በየርስ በርስ ጦርነት ወቅት የሚካሄድ ድርድር በቅርጽም በይዘትም ይለያል። የውጪ ውራሪ ኃይልን አሸንፎ የአገር ኅሊውናን ለማስጠበቅ ከጥቂት ባንዳዎች በስተቀር መላው የአገሩ ሕዝብ በሙሉ ልቡ እንደየሙያውና ችሎታው ይሳተፋል። የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ በአንድ አገር ሕዝቦች መካከል የሚከሰት ስለሆነ ሕዝቡ ለሁለት ተከፍሎ ነው የሚወጋጋው።

 

የውጪ ወራሪ ኃይልን አሸንፎ ከወሰኑ ከወጣና ብሔራዊ ሉዓላዊነት ከተጠበቀ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላምን ለማስፈን ቀላል ነው። በየርስ በርስ ጦርነት ወቅት ግን ሰላም እንኳ ከተፈጠረ በኋላ ተፋላሚዎቹ በአንድ አገር በአንድ መንግሥት በአንድ አገር ሕገ መንግሥት ሥር መተዳደር ቢቀጥሉም፣ ተደማምተዋልና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እጅግ በጣም ከባድ ይሆናል። በየርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት የጠፋው ነፍስና ተከታታይ ኃዘን የብዙዉን ዜጋ ቤት ያንኳካ ስለሆነ ቂም በቀሉ በአንድ ትውልድ ብቻ ሊወሰን አይችልም። (በዩጎዝላቪያ፣ በሩሲያና በኡክሬይን እንዲሁም ዛሬ አንዳንድ የኢትዮጵያ ብሔሮች የሚያነሱት የብሔር ጭቆና / ቅራኔ ከብዙ ዓመታት በፊት የተፈጸም መሆኑን ልብ ይሏል)። በዚያውም ልክ በቅርቡ የኤርትራና የሶማሌ ወረራዎችን በጉልበት አሸንፈን ብሔራዊ ሏዓላዊነታችንን ካስከበርን በኋላ ዛሬ ከኤርትራም ሆነ ክሶማሌ ሕዝብ ጋር አንዳች ዓይነት ቂም ስናስተናግድ አንስተዋልም።

 

በድርድር ወቅት ከውጪ ውራሪ ኃይል ተወካዮች ጋር መደራደር ይቀላል። ተፎካካሪ አገራት አደራዳሪዎችን ወይም አሸማጋዮችን እንጂ ተደራዳሪዎችን ለመምረጥ እድል የላቸውምና። ተደራዳሪዎቹ በበፊተኛው የሥራ ሕይወታቸው አብረው ያልሠሩ ወይም የማይተዋወቁ ስለሆነ የተደራዳሪዎቹ ማንነት እምብዛም ችግር አይመጣም። በየርስ በርስ ጦርነት ወቅት ግን የተደራዳሪዎች ማንነት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። የአንድ አገር ልጆች ስለሆኑና በበፊተኛው ሕይወታቸው በግልም ሆነ በሥራ ዓለም ሊተዋወቁ ስለሚችሉ በድርድሩ ወቅት የመናናቅ ወይም ያለመተማንን ሊኖር ስለሚችል በድርድሩ ሂደት ችግር ሊያስከትል ይችላል። በተለይም በመጀመርያው ዙር በዲፕሎማቶች መካከል በሚደረገው ውይይት/ድርድር አንዳች ዓይነት ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ የተደረሰበትን ስምምነት በተግባር ለመተርጎም የሚችለው በአብዛኛው መለዮ ለባሹ ስለሆነ፣ ብዙ ችግር አለበት። በዛሬው የአገራችን ሁኔታ ለምሳሌ የቀድሞው የመከላከያ ኃይላችን ኤታ ማጆር ሹሙ ጄኔራል ጻድቃንና ያኔ የበታች መኮንን የነበረውን የዛሬው ፌልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በእኩልነት ደረጃ ተቀምጠው የድርድሩን ውጤት በተግባር ለመተርጎም በእኩልነት ደረጃ ሲወያዩ ማለት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሀገርን ትንሣኤ ለማፋጠን ፋኖን ከሠርጎ ገቦች ሤራ መጠበቅ - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

 

በኔ ግምት፣ የዛሬው የሰሜኑም ሆነ በምዕራብ ኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው የርስ በርስ ግጭት፣ የፖሊቲካ ሥልጣን ጥያቄ እንጂ የድንበር ወይም ተገንጥሎ የራስን አገር የመመሥረት ስላልሆነ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው ባይ ነኝ። የዲሞክራሲ ጥያቄ ደግሞ በምንም መልኩ ጠብመንጃ የሚያማዝዝ አይደለም። ስለዚህ፣ ሳያድለን ቀርቶ አለመግባባትን በጠብመንጃ እንጂ በሠለጠነ መንገድ በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ የመፍታት ባሕል ስለሌለን ነው እንጂ የዛሬው የሰሜኑ ግጭት ገና ከመጀመርያው በሰላም ልንፈታው የምንችለው ጉዳይ ነበር። ግን አልሆነም። ያለሆነበትም ምክንያት፣

 

ሀ) አለመግባባትን በሰላም ለመፍታት ሃሳብ ማቅረብ የድክመት ወይም የሽንፈት ምልክት መስሎ ስለሚታይ፣ ከሁለቱም ወገን ማንም ደፍሮ ከልብ “ችግራችንን ያለ ጠብመንጃ እንፍታ” ብሎ ሃሳብ የሚያቀርብ አልነበረም።

 

ለ) በባሕላችን ተሸናፊ ከአሸናፊው እኩል አብሮ በእኩልነት ሊኖር የሚያስችል ልምድና ባሕሉ ስለሌለን ሁለቱም ወገኖች የግድ ማሸነፍ አለብን ብለው ይገምታሉ። ከሽንፈት በኋላ በሰላምና በክብር እንዲሁም በእኩልነት አብሮ የመኖር ዋስትና ስለሌለ፣ እንደ ምንም ብሎ ማሸነፍ፣ ካልተቻለ ደግሞ በአቻ ለመለያየት እንጂ መሸነፍን በጭራሽ አንቀበልም። በታሪካችን ቀደምት መሪዎቻችን ከአጼ ቴዎድሮስ፣ ጀምሮ እስከ መለስ ዜናዊ ድረስ ያላንዳች ማሻሻል የወረስነው ባሕል ቢኖር ተሸናፊን ማሸማቀቅ፣ ማዋረድ፣ አካለ-ስንኩል ማድረግ፣ ለግዞት መዳረግ፣ ማሠቃየትና ስብዕናን የሚነካ ድርጊት በተሸናፊው ላይ መፈጸም ስለሆነ፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ማንም ተፎካካሪ ሽንፈትን ሊቀበል ፈቃደኛ አይሆንም። ለዚህም ነው፣ “እስከ መጨረሻው ጥይትና እስከ መጨረሻው ሰው” ወይም አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፣ “ለትግራይ ሕዝብ መሸነፍ ማለት መጥፋት ማለት ነው” የሚለውን አባባል በተደጋጋሚነት የምንሰማው!

 

ያሁኑን የድርድር ሂደት ከጅምሩ ሊያወሳስቡ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከውጪ ለሚያየው ተመልካች ተደራዳሪዎቹ ፊት ለፊት ቁጭ ብለው ሲነጋገሩና በቴሌቪዥን ቀርበው ሲያዩአቸው በጣም ቀላል ሂደት ይመስላል። ግን ሁለቱን ወገኖች በአንድ ጣራ ሥር አምጥቶ እንዲነጋገሩ ለማድረግ አሸማጋዮቹ የሚያዩት ፍዳ ቀላል አይደለም። ሁለቱን ለንግግር መድረክ ለማብቃት ዓመት መፍጀቱ በኔ ግምት፣ በተለምዶ ከሚደረገው ተመሳሳይ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አንጻር የዘገየ ነው አይባልም። ዓመት ድረስ የሚያቆይ ምን ነገር እንደ ተፈጠረ ባናውቅም፣ የሚከተሉት ጥቂት ነጥቦች ግን ለንግገሩ መዘግየት የራሳቸው አስተዋጽዎ እንደ ነበራቸው እገምታለሁ።

 

ሀ) ሁለቱም ወገኖች “በወኔ ተሞልተው ስለነበርና ጦርነቱ ሊያልቅ የሚችለው በአንደኛው ወገን አሸናፊነት ብቻ ነው” ብለው ይገምቱ ስለነበር፣ “ከጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ቆራጥ ውጊያ በኋላ አሸንፌ ከማንበረክከው ጠላት ጋር ምን ገዶኝ እደራደራለሁ” በሚል ግምት ራሳቸውን ስላሳመኑ በቅንነት ከልባቸው ለመደራደር ዝግጁ አልነበሩም።

 

ለ) የአሸማጋዮቹ (mediators) እና የአደራዳሪዎቹ (negotiators) ማንነት ምርጫ ወሳኝ ነበር። ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙባቸው መሆን ነበረበትና። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ሕወሃት ኬኒያታን ሲመርጥ መንግሥት ደግሞ ኦባሳንጆ ካልሆነ ይላል። ሕወሃት አሜሪካ ትግባበት ሲል መንግሥት ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት መሆን አለበት ይላል። ስለዚህ ለሁለቱም የሚጥም አሸማጋይ ማግኘት ቀላል አልነበረም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጦርነት ጋንግስተሮች!!! ጦርነት ሲኦል ነው!!! የጦርነት ሚሊየነሮች ትርፍ!!! ሰንደቅ-ዓላማው ዶላሩን ይከተላል፣ እናም ወታደሮቹ ሰንድቅ ዓላማውን ይከተላሉ!!!

 

ሐ) አሸማጋዮችን (ወይም አደራዳሪዎችን ) ብቻ ሳይሆን የንግግሩ (የድርድሩ) ተሳታፊዎችና ታዛቢዎችም ምርጫ እንደዚሁ የተወሳሰበ ነው። አንዳንዶቻችን እንደምናስበው ሳይሆን፣ የድርድሩ ተካፋዮችን የመምረጥ መብት ያላቸው የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ብቻ ናቸው። አሸማጋዮችና አደራዳሪዎች ምናልባት ሃሳብ ይሰጡ እንደው እንጂ የድርድሩ ተካፋዮችን በተመለከተ አንዳችም ወሳኝ ሚና አይኖራቸውም።

 

ሐ) የቦታ ምርጫ ሌላው ችግር ነው። ንግግሩ (ድርድሩ) የሚካሄደው በተቻለ መጠን ሁለቱም ወገኖች ቤተኝነት በሚሰማቸው ቦታ መሆን አለበት። ይህን መሰል አገር ማግኘት ደግሞ ቀላል አይደለም። ለዚህ ነው ከኢትዮጵያ ቅርብ ጎረቤት አገሮች ለሁለቱም የሚስማማ ቦታ “ጠፍቶ” ደቡብ አፍሪካ ድረስ የሚሄዱት ።

 

መ) የንግግሩ (ድርድሩ) ተካፋዮች ጉዞ (logistics) ራሱን የቻለ ችግር አለበት። የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች በፈለገው አቅጣጫ መብረር ሲችሉ የሕወሃት ዴሌጌሽን ጉዞ ግን ውስብስብ ያለ ነው። በአዲስ አበባ በኩል ለመብረር ዋስትና ያስፈልጋቸዋል። በቀጥታ አዲስ አበባን ሳይረግጡ የውጭ አገር አውሮፕላን መጥቶ ከመቀሌ ይውሰዳቸው እንዳይባል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ኮሪዶሩን ካልፈቀደ የሚሳካ ሙከራ አይደለም። ዞሮ ዞሮ ለሕወሃት ዴሌጌሽን ጉዞ ስኬት የመንግሥት ፈቃድ አስፈላጊ ነው ማለት ነው።

 

ሁለቱ ወገኖች በድርድሩ መደምደሚያ ላይ ጦርነቱን ለአቁሞ ሰላምን ለማስፈን ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ይሆናሉ ወይስ እንደው የተበታተነና የተዳከመ ጦራቸውን አሰባስበው በአዲስ ኃይል ውጊያ እስከሚጀምሩ ጊዜ ለመግዛት ነው ብለው የሚጠይቁ ብዙ ናቸው። ተገቢ ጥያቄ ነው። ያለፈው እንዳለ ሆኖ፣ በኔ ግምት ዛሬ ሁለቱም ወገኖች ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ ናቸው ብዬ እገምታለሁ። ምክንያቱም፣ ጦርነቱ ሁለቱም ወገኖች ባላሰቡት አኳኋን ተራዝሞባቸዋል። በአጭር ቀናት ወይም ሳምንታት እንጨርሰዋለን ብለው የጀመሩት ግጭት ይኸው ሁለት ዓመት ሆነው። ጦርነት ሲራዘም ደግሞ፣

 

ሀ) ብዙ ተዋጊ ኃይላት ይገደሉና የውጊያውን ግለት ይቀንሱታል።

 

ለ) አብዛኛው ዘማች በሰላም ስለማይመለስ ፈቃደኛ የሆኑ ተተኪ ተመልማዮችን ማግኘት እየከበደ ይመጣል።

 

ሐ) ወላጆች ልጆቻቸውን ለመላክ ፈቃደኛ አይሆኑም። ልጆቻቸውን ይደብቃሉ ወይም ያሸሻሉ።

 

መ) በሁለቱም ወገን የጦርነት ኤኮኖሚ ስለሚካሄድ ተዋጊውን ራሱን መቀለብ እስከማይቻልበት ደረጃ ይደርሳል፣ ቀለብ የሌለው ተዋጊ ደግሞ የመዋጋት ብቃቱ ይቀንሳል።

 

ሰ) አብዛኛው የአገሪቱ አንጡራ ሃብትም ሆነ በብድርና በዕርዳታ የሚገኘው ገንዘብ ለጦርነቱ ስለሚውል፣ የኑሮ ውድነት ይከተላል። በመሆኑም፣ ገቢና ወጪውን ማመሳከር ያቃተው ሰፊው ሕዝብም ማጉረምረም ብሎም መቆጣት ይጀምራል። ሕዝብ ሲቆጣ ደግሞ የመንግሥትን ሕልውና ይገዳደራል።

 

ሠ) ሁለቱም ወገኖች የስንቅና ትጥቅ መተላለፊያ ድልድዮችንና ቁልፍ መንገዶችን “ጠላትን ይጠቅማል” ከማለት አስቀድመው ስለሚያወድሙ፣ ለተዋጊ ኃይላቸው በቂ ትጥቅና ስንቅ በወቅቱ ለማድረስ ይቸገራሉ።

 

በኔ ግምት፣ ይህ ሁሉ ተዳምሮ ነው እንግዲህ ሁለቱን አካላት ወደ ድርድር መድረክ እንዲመጡ ያስገደዳቸው።

 

የድርድሩን ይዘትና ተጓዳኝ መፍትሔን ለማምጣት በሚደረገው ውይይት ውስጥ ወሳኙ በዛሬው ሁኔታ በውጊያው ሜዳ ማን የበላይነትን እየተጎናጸፈ ይገኛል የሚለው ነው። ሁለት ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ሕወሃት ሁለንተናዊ ሽንፈት አይቀሬ መሆኑን አምኖበት፣ ግን ደግሞ ተሸንፎ ከመዋረድ አሁን እንዳደረገው “በእኩልነት” ለመደራደር ፈቃደኛ ሆኖ ይቀርባል። በፈረንጅኛ dignified exit የሚባለው ነው። በኔ ግምት ሕወሃት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰ ይመስለኛል። የዚህ ውሳኔ ጥቅሙ፣ ሕወሃት በድርድር ጠረጴዛው ዙርያ እንድ አንድ እኩል ተደራዳሪ ሆኖ መቅረቡ ነው። ሌላው ምርጫ ደግሞ የተለመደውን “አንዲት ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር ድረስ እንዋጋለን” መፈክር አንግበው እስክ መጨረሻው ሲዋጉ መደምደሚያው ያው አይቀሬው ሽንፈት ይሆንና የጦርነቱን ድምዳሜና የድኅረ ጦርነቱን ሁኔታ የሚወስነው አሸናፊው ወገን ይሆናል። ጦርነቱ በዚህ ሁኔታ ካለቀ ደግሞ በሁለቱ መካከል ሊኖር የሚችለው “ንግግር” ወይም “ድርድር” ሳይሆን በአሸናፊው መልካም ፈቃድ የሚወሰን የ ”እጅህን ስጥ” ትዕዛዝ (capitulation) ብቻ ነው። ሁለቱም ወገኖች እዚያ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ለድርድር ፈቃደኛ መሆናቸው ብስለታቸውን ይጠቁማል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በመስቀል ሰሞን የመስቀል ወሬ

 

በድርድሩ ሂደት ሊነሱና አወዛጋቢ ሊሆኑ ከሚችሉ ብዙ ነጥቦች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፣

 

ሀ) የወልቃይትና የራያ የወደፊት ዕጣ እጅግ በጣም አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል። ሕወሃት እንደሚለው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታ ወይስ ያለፈውን ታሪካዊ ቦታቸውን እንደ መረጃ ወስዶ መፍትሔ ይፈለግላቸዋል?

 

ለ) ከሰላሙ ስምምነት በኋላ የትግራይ ክልል ሠራዊት ሚና ምን ይሆናል? እንደ ሌሎቹ የክልል ልዩ ኃይላት የክልል ሚናውን ብቻ እንዲጫወት ተፈቅዶለት በሕልውናው ይቀጥላል ወይስ ማስተማመኛ ስለሌለ እንዲከስም ይደረጋል?

 

ሐ) ከሰላሙ ስምምነት በኋላ ትግራይን ማን ያስተዳድረዋል? ሕወሃት? አዲስ ጊዜያዊ መንግሥት? ጊዜያዊ መንግሥቱስ ተመራጭ ነው ወይስ ተሿሚ ነው የሚሆነው? የትግራይ ተቃዋሚ ኃይላት ሚናስ ምን ይሆናል?

 

መ) የጦርነትን ሕግና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ጥሰው ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት የትግራይ አመራር አባላት ተጠያቂነትስ እንዴት በተግባር ይውላል? ወይስ ሁለቱም ወገኖች “ያለፈው አልፎአልና ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለን ማንም ማንም ሳይወነጅል አዲስ ትዳር እንጀምር” ብለው ይቀጥላሉ። (ልብ በሉ! የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ተመሳሳይ ክስ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ እያቀረቡ ነው)። ወንጀሉ እንደ ተፈጸመ ሁለቱም ወገን ቢያምኑበትስ ፍርዱን የሚሠጠው ዳኛስ ማን መሆን አለበት?

 

ያሁኑ ንግግር ወደ ድርድር ይሻገራል የሚል እምነት አለኝ። ድርድር ደግሞ ሰጥቶ መቀበል ቢሆንምና ሁለቱ ወገኖች ምን እንደሚሰጣጡ ባላውቅም፣ ራሱ ፊት ለፊት ለመገናኘት መወሰናቸው ትልቅ ውሳኔ ነው። በግሌ ከድርድሩ ባሻገር አንድ እጅግ በጣም የሚያሳስበኝ ጉዳይ አለ። የእርስ በርስ ጦርነት በወንድማማች መካከል የሚከሰት ግጭት ስለሆነ አንደኛው ወገን ወታደራዊ የበላይነትን ይጎናጸፍ እንደው እንጂ አንዳቸውም አንዳቸውን አያሸንፉም። የተገደሉት፣ የተፈናቀሉት፣ የቆሰሉትና የደሙት፣ በሙሉ የአንድ አገር ልጆች ስለሆኑ፣ ቁጥሩ ይበላለጥ እንደው እንጂ፣ ኃዘኑ የሁለቱንም ቤት እኩል ጎድቷል። ከሁለቱም ወገን ብዙ ደም ፈሷል፣ ብዙ ነፍሳት ጠፍተዋል፣ ሴቶች ባሎቻቸውን፣ እናቶች ልጆቻችውን አጥተዋል። አብዛኛው ወላጅም የገዛ ልጁን እንኳ ቀብሮ እርሙን ሊያወጣ ያልቻለበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ነው የእርስ በርስ ግጭት ዋነኛው ችግር፣ ጦርነቱም ቆሞ ሰላም ከሰፈነ በኋላ በትውልድ መካከል ለሚቀጥሉት ዓመታት ወይም ዘመናት በሕዝቦች ልብ ተቀርጾ የሚቀረው ቂም በቀልን የሚያስከትለው።

 

ወገኖቼ፣ ዛሬ ተኩስ አቁሞ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ስምምነት ላይ ቢደረስም፣ ሕዝቡ በአንድ አገር ውስጥ በፍቅርም ባይሆን እንደ ጥሩ ጎረቤት አብሮ ለመኖር ሰፊውን ሕዝብ ማስታረቅና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚጠበቀው የቤት ሥራ እጅግ በጣም አታካች ይሆናል። ስለዚህም ነው የኢትዮጵያ ኅልውናና የሕዝቦቿ ሰላም ያሳስበናል የምንል ዜጎች በተለይም ምሁራንና ፖሊቲከኞች እንዲሁም አክቲቪስቶች ይህንን ታሪካዊ ተግዳሮት (challenge) አሸንፈን ለመውጣት ከወድሁ መዘጋጀት አለብን የምለው። ከሁሉ በላይ ራሳችንን ማሳመን ያለብን ጦርነቱ በፖሊቲካ ሥልጣን ጥያቄ ዙሪያ በአንድ ቤተሰብ መካከል የተከሰተ ጊዜያዊ ጠብ እንጂ በኢትዮጵያ ኅልውናም ሆነ በሕዝቦቿ አብሮነት ላይ ያነጣጠረ አለመሆኑን ነው። የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ከሁለቱም ወገን የተገደለውና የተፈናቀለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ደግሞ ከዚህም ግጭት በኋላ ልክ እንደ ድሮው በአንድ አገር በአንድ ሕገ መንግሥት ሥር መተዳደሩን ይቀጥላል። ስለሆነም፣ ሁሉም ነገር እንዳልተፈጸመ አድርገን ዛሬውኑ ተቃቅፈን በፍቅር እንክነፍ ሳይሆን፣ በሂደት አንዳችን ሌላውን እየተረዳን፣ ይህ ዓይነት ሁለንተናዊ ጥፋት ዳግመኛ እንዳይከሰት በጋራ የምንተጋበትን ፍኖት ካርታ እናዘጋጅ። ፈጣሪ አስተውሎትን አብዝቶ ይስጠን።

 

******

 

ጄኔቫ፣ 20 ኦክቶቤር 2022 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com

 

 

 

2 Comments

  1. በምንም አይነት ስሌት ቢሆን ወያኔ በሰላም ድርድር ነገሮችን አስልቶ አያውቅም። በ1968 ዓ. ም ትግራይ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ብድን ኑ ለአንድ ጉዳይ ነው የምንታገለውና እንታረቅ በማለት አብልቶ አጠጥቶ ነው በተኙበት የጨረሳቸው። ይህ ባህሪው ከ 40 ዓመት በህዋላ ተከስቶ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት በኢትዪጵያ መንግስት በዝርዝር የተገለጠ ባይሆንም ከጥቃቱ የተረፉና የቅርብ የአይን ምስክሮች የሰጡትን ምስክርነት ላዳመጠ የድር አራዊት እንጂ የሰው ልጅ እንዲህ ያስባል ብሎ መገመት ይከብዳል። እኔን በጣም የሚያሳዝነኝ ዛሬም በትግራይ ህዝብ ስም መነገዳቸው ነው። በተለይ በውጭ ሃገር ያሉ አፍቃሪ ወያኔዎች (ብዙዎቹ በወያኔ ድጋፍና ልዪ ልዪ ጥቅማ ጥቅም እርዳታ ከሃገር የወጡ ናቸው) በመሪዎቻችን እናምናለን፤ ትግራይ ታሸንፋለች ሲሉ ግርም ይለኛል። ማን ማንን ነው የሚያሸንፈው? ወንድም እህት አባትና እናት ተገዳድሎ ማን ነው የሚያተርፈው? ግን ውሻ በበላበት ይጮሃል ነውና እንተዋቸው ይንጫጩ።
    አሁን በደቡብ አፍሪቃ የሚደረገውም የሰላም ድርድር ዋጋቢስና በአሜሪካ ገፊነት የሚደረግ ተልካሻ ድርድር ነው። ሲጀመር አሜሪካ በታሪኳ ሃገሮችን አስማምታ አታውቅም። ማፍረስ፤ መሪዎችን መግደል፤ የሴራ ወሬ ማሰራጨትና ሰውን ማስጨነቅ እንጂ። ሰው ግን ቆም ብሎ አሜሪካና አውሮፓውያን ይህን ያህል ከተመድ ጋር አብረው ለወያኔ የተጨነቁት ሌላ የሚያስጨንቃቸው ጠፍቶ ይሆን ወይስ ለሃበሻ ፓለቲከኞች ግልጽ ያልሆነ ሰውር ደባ አለ? ይህን መርምሮ የደረሰበት ወገን ይኖር ይሆን? ባጠቃላይ ላንድ ተገንጣይ ቡድን አንድ ትልቅ ሃገር ቋሚ ጠበቃ የሆነበት እንዲህ እንደ አሜሪካውና እንደ ወያኔው ያለ ጥምረት በአለም ፓለቲካ ላይ ታይቶ አይታወቅም። ግን ያው ወያኔ ሰርቆም ያባላቸው ስለነበርና (በተለይም በዓለም ባንክና በመሳሰሉት እርዳታ ሰጭ ነን ባይ ድርጅቶች በኩል) አልፎ ተርፎም እንደ ፈለጉ የሚጋልቡት ወያኔ በመሆኑ ይኸው የክፋታቸውን ጥግ ሁሉ ሞክረው ዛሬ ላለንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ስለ ዲሞክራሲ፤ ስለ ሰዎች መብት፤ ስለ ሃገር ልዕልና ሁሉ የሚያወሩትና የሚያስወሩት ውሸት ነው። ተንኮላቸው በምድር ተርመስማሽ፤ በአየር ላይ ተንሳፋፊ ነው። ይህ የጥላቻ ወሬ ነው ለምትሉ The Secret History of the American Empire by John Perkins አንቦ ዋቢ የሆኑትንም መጣጥፎች ማገላበጥ አይን ይከፍታል። ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን ለ30 ዓመታት እርስ በእርስ እንዲገዳደሉ ንጉሱን በመገፋፋት ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስና የቃኘው ስቴሽን በአሜሪካ እጅ እንዲገባ ያደረጉት ለማንም አዝነው ሳይሆን ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነው። ያው ሁሉም እንደሚረዳው ደርግ በራሺያ ሻቢያና ወያኔ በአሜሪካና በነዳጅ በሰከሩ የአረብ ሃገሮች አይዞአቹ እየተባሉ እልፍ ወገኖቻችን ከሁለቱም በኩል ረግፈዋል። ባጭሩ የወያኔ ለሰላም ቁጭ ማለትም ያው አሜሪካን ደስ ለማሰኘት ተብሎ የሚደረግ እንጂ ምንም አይነት መፍትሄ አያመጣም።
    ደርግን ደመሰስን ገለ መሌ የሚሉት ደርግን የጣለው ወያኔም ሻቢያም አይደሉም። ጊዜ ነው ደርግን የጣለው። የፓለቲካ ነፋስ መለወጥ። አሁን በዪክሬንና በራሺያ የሚደረገው ፍትጊያም የዚሁ ንፋስ እፍታ አንድ አካል ነው። ያውቃሉ ጆርጅያ ሲሶ የሚሆነውን መሬቷን በራሺያ እንደተነጠቀች? ግና ፍትጊያው ይቀጥላል። ወደ ሃገራችን ጉዳይ ስንመለስ አብዪት ልጆቿን ትበላለች እያለ ደርግ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደራዊ አመራሮችን በጭፍን ያለምንም ፍርድ አፈር ስለመለሰባቸው የቀረው ጀሌና ነጭ ለባሽ ስለሆነ ነው የአሜሪካ ሴራ ተጨምሮበት ሻቢያ በአስመራ ወያኔ በአዲስ አበባ የእድሜ ልክ አለቆች ለመሆን የበቁት። ይኸው ወያኔ ተፈንግሎ ሊመለስ እየታገለ ነው። ባጭሩ የሚያገዳድሉን የሚያደራድሩን ተራቡ ብለው ስንዴ የሚሰፍሩልን ናቸው። በቅርቡ ከአንድ ጓደኛ ጋር ስናወራ ለምንድነው አይርላንድ ከወያኔ ጋር የጠበቀ ፍቅር ያላቸው አለኝ። አይ አንተ ያኔ እኮ ደርግ በከተማ ወጣቶችን እያፈሰ ሲያስርና ሲገድል የአይርላንድ ተወላጅ የሆኑ የውጊያ አዋቂዎች፤ የክምና ሰዎች በረሃ ከወያኔ ጋር ተሰልፈው ይዋጉ ነበር። ከዚያ ወያኔ የሃገር መሪ ሲሆን ደግሞ ንግድና ሌላውንም የዝርፊያ ስልት አብረው ነው የተካፈሉት ስለው ለደቂቃዎች ጸጥ ብሎ ከቆየ በህዋላ አንድ ዳብሊን ውስጥ የተፈጠረ በራሱ አይን ያየውን ተርኮልኝ ወደ ቀረበልን ምግብ ተመለስን። የሃበሻ ፓለቲካ አሽዋ ላይ ያረፈ የጫማ አሸራ ነው። የዛሬው ግብ ግብ በሌላ ይተካል፤ የዛሬው የፓለቲካ ቋንቋ ሌላ ሃሳብ ይተካዋል። The The International መዝሙር ስታንዛ እንዲህ ይላል።
    So comrades, come rally
    And the last fight let us face
    The Internationale unites the human race.
    አሁን ደግሞ ያ ቀርቶ ሌላ ዘፈን ሆኗል ነገሩ ሁሉ። ክልል፤ ቋንቋ፤ ዘር፤ ሃይማኖት፤ ድንበር፤ መጤ ገለመሌ እያልን እንዣለጣለን። የታለ የሰው ዘር የተሳሰረው የተፋቀረው? በቀዝቃዛው ጦርነት ከነበረው ሹኩቻ እና ዛቻ ይልቅ ዓለም አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አስጊ ነው። ይበልጦቹ የዓለም ፍልሚያዎች የተቋጩት በጦርነት ድል በማድረግ ነው። ወያኔ መልሳችሁ እንኳን ቤተመንግስት ብታስገቡት ከክፋቱና ከብቀላው የዘር ፓለቲካ ፈቀቅ አይልም። ሲጀመር እነዚህ ሰዎች የማሰብ ችሎታቸውን ተቀምተዋል። የሰው ሞት ምንም አይመስላቸውም። ይህን ታውቃላችሁ? የሰሜን እዝን በወጉ ማግስት የገደሏቸውን ሬሳ አይሱዙ ሞልተው መቀሌ ከተማ እየተዘዋወሩ ያሳዪ እንደነበረ? ይህ ትውልድ ቆሞ ይሂድ እንጂ የሞተ ትውልድ ነው። ግፍን እንደ ውሃ የጨለጠ ትውልድ ቆሜለታለሁ ለሚለውም ሆነ ለራሱ ዋጋ የለሌው ነው። በደቡብ አፍሪቃም የሚደረገው ድርድር ወንጀለኛን በኩልነት አስቀምጦ እሰጣ ገባ ለማስገጠም እንጂ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታን አያመጣም። ድሉ መጠናቀቅ ያለበት መቀሌ በመግባት ለትግራይ ህዝብ ምርጫ በመስጠት ነው። ሌላው ሁሉ አሻሮና ወፎች የሚበሉት ዘር ነው። በቃኝ!

  2. እዚህ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ ትህነግ በመጀመሪያ አማራን ቀጥሎ አብይን ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መገስገሱን እናውቃለን፡፡ ታዲያ ዋናው ተደራዳሪ አማራ መሆን ሲገባው ምንም ችግር ላልደረሰበትና እስከ አሁንም የሚያላግጡት የኦሮሞ መሪዎች በአንድም ሆነ በሌላ ለዚህ ድርድር ማን ማንዴት ሰጣቸው፡፡ ትግሬ እራሱን ችሎ ከተደራደረ አማራውም እራሱን ችሎ መተዳደር አለበት፡፡ የአማራ ተደራዳሪዎች እነ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፤ አቻም የለህ ታምሩ፤የወልቃይት ኮሚቴ እና መሰሎች ከባህር ማዶ ከሃገር ውስጥ ደግሞ እነ ጄነራል ተፈራ፤ዶ/ር ጫኔ፤ ሌሎችም የአማራው በደል ያንገፈገፋቸው መሆን ሲገባቸው የችግሩ ገፈት ቀማሾች ያልሆኑ ከብልጽግ ና ወምበር አኳያ የሚመለከቱ ለድርድሩ ብቃት አላቸው ብዬ አልገምትም ቋንቋ እራሱን የቻለ መስፈርት ነው ለትግሬዎች ማይክል ሃመር ነው ማነው የሚሉት አብሮ ያሳክርላቸዋል ለአማራው ማን አለው፡፡ ከሃገር ቤት ብልጽግና በሽመልስ አብዲሳና በጁዋር መራራ በኩል በሸኔ መከራውን ያበላዋል ከዚህ እኛ እናውቅልሃለን ብለው ያላግጡበታል፡፡ ድርድሩ ወደ ክረምቱ ገፋ ቢል ጥሩ ነበር የትግሬ ተንከባላዮች ሰው እንዳያሳስቱ መንደባለሉ ፈረንጅን እጅ እጅ ስላለው አሁን ስልት ቀይረው በአንድ እግር ቢቆሙ መልካም ነበር፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share