February 11, 2013
13 mins read

ስለ ታምራት ሞላ ጥላሁን ገሰሰ እና ማህሙድ አህመድ ምን ብለው ነበር?

“ስለ ታምራት ብጠየቅ የቱ ነው ጫፉ የቱስ ነው መጨረሻው በአጠቃላይ ፍቅር ነው”
ጥላሁን ገሠሰ
“ትንሹም ትልቁም ለታምራት እኩል ናቸው”
ማህሙድ አህመድ


(ዘ-ሐበሻ) ተወዳጁ ድምጻዊ አርቲስት ታምራት ሞላ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ከአዲስ አበባ የመጡ ዜናዎች አመለከቱ። በተለይ “ታምሜ ተኝቼ ትላንትና ሌሊት በህልሜ መጣችሁብኝ አይኔ ሲንከራተት” በሚለው ዘፈኑ የምናውቀው ተወዳጁ ድምጻዊ ታምራት ሞላ የተወለደው በጎንደር ክፍለሃገር ነበር።
በሙዚቃ ሕይወቱ በነበረበት ዘመን ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ጉልህ ሚና የተጫወተው አርቲስ ታምራት ሞላ የቀብር ስነ-ሥርዓቱ ዛሬ ሰኞ እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚፈጸም ጨምሮ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በደም ካንሰር ክፉኛ ተጠቅቶ የነበረው አንጋፋው ድምፃዊ ታምራት ሞላ “በእግዜአብሔር ረዳትነት፣ በእመቤቴ ጠበልና በኢትዮጵያ ሕዝብ ጸሎት ተፈውሻለሁ” በአንድ ወቅት በሃገር ቤት ይታተም ለነበረው መሰናዘሪያ ጋዜጣ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ መናገሩ አይዘነጋም። በወቅቱም “ከሞት አፋፍ ተመልሻለሁ” የሚለው ድምፃዊው “በአሁኑ ሰዓት መጠነኛ ከሆነ ጉንፋን ውጭ ሌላ በሽታ የለብኝም” ሲል ተናግሮ ነበር። “እኔ ዕድሜዬን ሙሉ ስዘፍንና ሳዘፍን፣ ስደንስና ሳስደንስ የኖርኩ ኀጢያተኛ ነበርኩ፣ ከእንግዲህ ወዲህ እኔና ዘፈን በሕግ ተፈራርመን ተለያይተናል፤ ከዚህ በኋላ ምናልባት ማይክሮፎን ይዤ ብታየኝ መዝሙር ለመዘመር ነው፡፡ ዕድሜ ልኬን የበደልኩትን አምላክ የምክስበት ወቅት ነው” በሚል ተናገሮ የነበረው ድምጻዊው ታምራት ሞላ በሙዚቃ ሕይወቱ የማይረሳውን ትዝታ ተጠይቆ ሲናገር “በአንድ ወቅት ከመድረክ ሳልወርድ አንዲት ሴት ከባሏ ተነጥላ ወደ መድረኩ በመምጣት የአንገቷን ሀብል አውጥታ ከሸለመችኝ በኋላ ጉንጬን ስማኝ ከመድረክ ስትወርድ የተቀበላት የባለቤቷ ጥይት ነበር” ብሎ ነበር።
በወቅቱ ከደም ካንሰር በሽታ እንዴት ሊፈወስ እንደቻለ ሲናገር “ለህክምና አሜሪካ ሄድኩ፤ ኬሞቴራፒ የሚባል መድኀኒት ነበር የታዘዘልኝ፡፡ መድኀኒቱ የእባብ መርዝ ያህል ከባድ ነው፡፡ ልክ ስትወስደው ፀጉርህ፣ ቅንድብህ፣ ሽፋሽፍትህ፣ ጢምህ መርገፍ ይጀምራል፡፡ ስቃዩን ተመልከት፡፡ እኔ ግን መድኀኒቱን ከመውሰዴ ከአራት ሰዓት በፊት ጸሎት አደርግና ከሀገሬ የመጣልኝን ጠበል ጠጥቼ ጥቂት አርፋለሁ፡፡ ከዚያ መድሃኒቱን እወስዳለሁ፡፡ …ፀጉሬ እንደምታየው ሙሉ ነው፣ ቁስለትም የለብኝም፣ ሐኪሞቹ መገረም ጀመሩ፡፡ በወቅቱ የእኔ መድኀኒት የእመቤት ጠበል፣ ባለቤቴም ጿሚ ነበረች፣ የእርሷና የኢትዮጵያ ሕዝብ ፀሎት ነበር፡፡ አሁን ስለዚህች የቃል ኪዳን ሀገር ነው የምጨነቀው፡፡ ኢትዮጵያ በአምላክ ኪዳንና በረከት ያለች ሀገር ናት፡፡ እስቲ ተመልከት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉም ነገር በተወደደበት ጊዜ እንኳን በአብዛኛው ፆሙን አያድርም፡፡ ይህ የእግዚአብሄር የቃል ኪዳን ምድር መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡ የዚች አገር ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበኛል፣ በስስት ነው የማያት፣ የትም ብሄድ ጠረኗ መልሶ ይጠራኛል፣ ስለሷ ባሰብኩ ቁጥር አለቅሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እኮ በንጉሡ ጊዜ ለሳኡዲ አረቢያና ለእንግሊዝ ስንዴ ትረዳ የነበረች ሀገር ናት፡፡ አሜሪካ የምትባል አገር ሳትታወቅ፣ በዘመናዊ መርከብ ትነግድ የነበረች የሥልጣኔ ማማ ነበረች፡፡” ሲል ተናገሮ የነበረው ድምጻዊው ታምራት ሞላ አሁን ለሞት ያበቃው ህመም ከዚህ የደም ካንሰር ጋር ይያያዝ አይያያዝ የታወቀ ነገር የለም።
ዶ/ር ጥላሁን ገሠሰ ስለ ታምራት ሞላ ምን ብሎ ነበር?
“ስለ ታምራት ብጠየቅ የቱ ነው ጫፉ የቱስ ነው መጨረሻው በአጠቃላይ ፍቅር ነው። እንደማስታውሰው ታምራትና አለማየሁ እሸቴ የ1954 ዓ.ም የክቡር ዘበኛ ቅጥረኞች ናቸው። ታምራት በትርፍ ሰዓቱም አዲስ አበባና ሹፌሮች ሆቴል ይሰራ ነበር። ሁላችንም አሪዞና ክለብ እንሰራ ነበር። በዚህ ወቅት አንድ የመንግስት ሰራተኛ የሆነ ሰው ሌላ ቦታ መስራት ሰለማይችል በጣም እየተሳቀቅን እርስ በርሳችን በመሸፋፈን ነበር የምንሰራው። ሌላው የማይረሳው በዚሁ ወቅት ታምራት ደሞዜ ወደ 347 ብር ተቆራርጦ እንዲደርሰኝ ተከራክሮ ያስጨመረልኝ እሱ ነው። ታምራት ለኔ ብቻ አይደለም ለሁሉም ወንድሞቹ ተቆርቋሪ የሆነ ወንድም ነው። እኔማ ደሞዝ ይጨመርልኝ ስል አለቆቼ የጠየቁኝ ዲግሪ ነው። እባካችሁን
እንደውም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሁለት ስንኝ ፅሁፍ እንድፅፍ ይፈቀደልኝና ዲግሪዬን ህዝቡ ይስጠኝ ብዬ በተናገርኩ እስር ቤት ገብቼ ነበር። በዚህ ሰዓት ታምራት እኔን ለማስወጣት ያልገባበት ቦታና ያልቆፈረው ጉድጓድ ያልሄደባቸው ባለስልጣናት ጋር አልነበሩም። ኮረኔል ሞላልኝ አማቹ ስለበሩ። አማቼ እንዴት እንደዚህ ያደርጉታል ብሎ በአማርኛ ለመስደብ “ግርማዬ ተገፎ ካሳን ጠራሁኝ ሞላጎደል ሆኖ እያበሳጨኝ” እያልን ወደ ንፋስልክ አካባቢ ባትሪሲዮን ቦታ ላይ እንጫወት ነበር። ኮረኔል ሞላልኝ በመነፅራቸውና በባርኔጣቸው ተሸፋፍነው መጥተው ያስተውላሉ። በኋላም በጥፊ. . . በርግጫ. . . ፍዳችንን አሳይተውን ነበር። እንዲህ እንዲህ እያልን እሱ ሲያዝ እኔ ስሰራ እኔ ስያዝ እሱ ሲሰራ ብዙ ነገር አሳልፈናል። አንድ ሰሞን መኪና የገዛሁ አካባቢ መኪናዬ ውስጥ ትራስ ፣ አንሶላና ፍራሽ ነበር ይዤ የምዞረው። ምክንያቱም ተደብቄ ነበር የምሰራው ትርፍ ስራ እንደሆነ በአደባባይ መስራት አንችልም። ምናልባት ለምን ሃብታም አልሆናችሁም? እንባል ይሆናል። ችግራችንን ግን እኛው እራሳችን ነን የምናውቀው። ለአሁኖቹ ትውልድ ቀደምትና ፈር ቀዳጆች ነን ብንል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ከተሳሳትኩም እታረማለሁ። በኋላም መከረኛው ታህሳስ ሲመጣ ልንለያይ ሆነ። ከጦሩ ጋር ወደ ኦጋዴን ሊልኩት ሆነ። በዚህ ወቅት ነበር ከሻለቃ ወንድሙ ዘውዴ እና ሻለቃ ተስፋዬ መኩሪያ እንዲሁም እኔም ጭምር በመሆን ኮረኔል አሽኔንና ሻለቃ ደስታን መክረንና አሳምነን ከጦሩ ውስጥ እንዲቀር ተደረገ። እግዚአብሔር ይስጣቸው። እኔና ታምራት አብረን ብዙ ክፉና ድግ ቀኖችን አሳልፈናል። መጠጥ የሚባል እንኳን አያውቅም። የሱ መጠጥ ውሃ ነው። ይቅርታ አድርጉልኝና እኔ ብቻዬን በጣም ብዙ እጠጣ ነበር። እንዲህ ያለ ጥንቃቄ የሚወስድ ሰው እንኳን ያመዋል ብዬ አላስብም ነበር። ለካ ወንድሜ ተይዞ ነበር። ሌላው እሱም ወታደር ነበር እኔም ለሁለት ዓመት ወታደር ነበርኩ። ታምራት በጦር ሜዳውም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ከወንድም ወንድ እና ሞራል ያለው ሰው ነው። ለወገኖቹም ተቆርቋሪ ጥሩ አርቲስት ነው። እኔ ለታምራት እችኑ ያለችህን አንድ ሃገር ፈጣሪ ፍቀድልኝና ልግዛህ ቢለኝ አሜን ብዬ የምቀበል ሰው ነኝ። ታምራት ለኔ ልጄም ወንድሜም ጓደኛዬም ነው። ይሔው ነው ብዬ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ አልችልም። በአጠቃላይ መለኪያዬ ነው።”
ማህሙድ አህመድስ ምን ብሎ ነበር?
« ስለታምራት ለመጀመር ቢከብድም እኔ መቼም ሁላችሁም እንደሰማችሁትና በታሪክም እንደምታውቁት አሪዞና ክለብ ውስጥ ወጥ ቤት እሰራ ነበር። በ1954ዓ.ም ነው አባታችን ፣ ወንድማችን ፣ የጉሮሮ መክፈቻችንና አምባሰደራችን የሆነው ጥላሁን ገሠሠን ጨምሮ ታምራት ሞላ ፣ አባይ በለጠ ፣ እሳቱ ተሰማ ፣ ተፈራ ካሳ ፣ አሰፋ ሚካኤልና የመሳሰሉት
በመሆን እየመጡ በሚጫወቱበት ወቅት ነው የተዋወቅነው። በኋላም ክቡር ዘበኛ በምንቀጠርበት ወቅት በነ ታምራትና በሌሎቹም ዘፋኞች ስራ በመዝፈን ነበር ያለፍኩት። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ይሄው እስከ ዛሬ ወዳጆች ሆነናል። ታምራት በጣም ጠንካራ ሰው ነው። ነገርን በትክክል በጭንቅላቱ አስቦ የሚመልስ መካሪ ፣ እስኪ እንነጋገር የሚል ሰው አክባሪ ነው። ሌላው ይቅርና እርስ በርሳችንም ብንሰዳደብና ብንኮራረፍ ገበናችን ግን ወደ ውጪ አይወጣም። ትንሹም ትልቁም ለታምራት እኩል ናቸው። መቼም ወታደር ቤት ያለን ሰዎች ሲቪሎችም ብንሆን ወታደር ነን። ለትንሹም ለትልቁም«አቤት ጌታዬ ነው» እርስ በርሳችንም ቢሆን መሃሙድዬ ሲለኝ«አቤት ጌታዬ» ታምራትዬ ስለው “አቤት ጌታዬ” ነው የሚለኝ። ይህንን
ለልጆቻችን ሁሉ ሳይቀር አውርሰነዋል።”
ዘ-ሐበሻ የታምራት ሞላ ነብስን በገነት እንዲያኖራት ትመኛለች።

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop