በርናባስ
(ለሎሚ መጽሔት እንደጻፈው)
በኢትዮጵያ ውስጥ ጥበብ በሁለት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የመጀመሪያው በአሁን ሰዓት ደራሲዎችም ሆኑ የጥበብ ባለሙያዎች አዲስ ነገር ይዘው መምጣት ካለመቻላቸው ጋር በተያያዘ በህብረተሰቡ ዘንድ ቦታ እያጣ መምጣቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ ጥበብን ንግድ ያደረጉ አርቲስቶች መበራከት በራሳቸው አንገት ላይ ሸምቀቆ በማሰር ጥበቡን እየገደሉት ይገኛሉ፡፡ በአሁን ወቅት ምናልባትም ጥበብ ያለ ንግድ የታባቱ ያለ የጥበብ ሥራን ከተመለከትን ያለምንም ጥርጥር ‹‹ሠው ለሠው›› ድራማን በግንባር ቀደምትነት ማየት ይቻላል፡፡ ሲጀመር በርካቶች ለመመልከት የተሻሙበት ዛሬ ላይ ግን ‹‹ይህ ነገር አያልቅም እንዴ?›› ተብሎ የተለያየ ሂስ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ ውስጥ እንደ ሠው ለሠው የዘመኑ ማለቂያ አጥቶና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም መረን የለቀቀ ዕድል የሰጠው የለም፡፡
መቼም በየሣምንቱ እንደምንመለከተው ከሆነ የሠው ለሠው ድራማ ሃሣብ አልቆበት እዛው በዛው መዳከሩ ብቻ ሣይሆን፣ ገንዘብ የማባከንና የመዝናናትንም ነገር እየተመለከትን ነው፡፡ ከድራማው መውረድ ጐን ለጐን ካላስፈላጊ ታሪኮችም ጋር ተደማምሮ አሁን በተለይ ተዋናዮቹ እራስን የማዝናናት ጊዜ ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ምናልባትም ለሌሎች ባይገባም መስፍን ጌታቸውና ሠለሞን አለሙ ግን ይህ ለምን እንደሚደረግ ልባቸው ያውቃል፡፡
የሠው ለሠው ድራማ ሲጠናቀቅ ፋይሉ ያልተዘጋ የክስ ሂደት ከመኖሩም በላይ በእነርሱ ላይ ክስ የመሠረቱት ወገኖች ሂሳብ ሊካፈሉ የሚችሉበት ሁኔታ በመኖሩ ከወዲሁ ብሩን በተለያየ ምክንያት በማባከን ‹‹የለንም›› ካሉ የከሳሾቻቸውን አንጀት የማሳረርና በዚህ መልኩ የማምለጥ አጋጣሚም እያመቻቹ ነው፡፡ አንድ በውጭ ሃገር የዳይሬክትንግ ትምህርት የተከታተለ ባለሙያ ሠው ለሠው ድራማን አብረን ስናይ፣ ‹‹ይህ ድራማ ማስታወቂያ ባይኖረው እኔ ዳይሬክት ባደርገው በአንድ ምሽት ላይ የሚታየው ከሰባት ደቂቃ አያልፍም ነበር›› ሲል አስገርሞኛል፡፡ በዚህ መልኩ በባለሙያ ሳይቀር የተገመገመው ሠው ለሠው አሁን በባንክ ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ የተገኘበት ይመስላችኋል?
78 ብር /ሠባ ስምንት ብር/ ምናልባት ዓይናችሁን እያሻችሁ ደግማችሁ ደጋግማችሁ ልታነቡና ልታስቡት ትችሉ ይሆናል፡፡ ብዙም ሩቅ መሄድ የሚያስፈልገው አይደለም ወይም የጽህፈት ስህተትም አይደለም፡፡ ባለፈው ሠሞን የፊልሙ ዳይሬክተር በአጋጣሚ ባገኛቸው ሚዲያዎች ላይ ሁሉ ‹‹ሠው ለሠው አትራፊ አይደለም›› እያለ ሲባዝን ነበር፡፡ ይህ የእርሱ ድርጊት ወይም አባባል ግን ምናልባትም በሂደት የሠው ለሠው አካውንት ሲታይ ይህ 78 ብር ይፋ ይሆንና ከመጋለጥና ህዝቡንም ግራ ማጋባቱ ስለማይቀር ሳልቀደም ልቅደም በሚል መልኩ የህብረተሰቡን አዕምሮ ለመለወጥ ወይም ተጠቃሚው እነርሱ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ቴሌብዥን ነው የሚለው ግንዛቤ ለማዘጋጀት ሆን ብሎ ያደረገው ነው፡፡
እንደ መረጃዎቹ ጠቋሚነት ከሆነ የሠው ለሠው ድራማ ዳይሬክተሮች ባለፉት ሦስት ዓመታት እንዲሁም ወራትም ተጨምሮበት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወስደዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በተለያዩ ጊዜያት ድራማው ሲቀረጽ ወደ ክልሎችም የሚወጣበት አጋጣሚም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም የክልሉ መስተዳድር ለሠው ለሠው ዳይሬክተሮች በስፖንሰር መልክ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ከዛም ሌላ ከዋሪት ቁሳቁሶች /ፈርኒቸርም/ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በዚህ መልኩ ታላቅ ገቢ ማግኘት የቻለው ድራማ እንዴት በባንክ ሂሣብ ውስጥ 78 ብር ሊገኝ ቻለ? ከተባለ ግን ከዚህ ጀርባ ከድራማው መጠናቀቅ በኋላ ካለው ክስ ጋር ተያይዞ ምንም ገንዘብ ባለማስቀረት ወይም እነርሱ ተጠቃሚ ላለማድረግ ሲባል ዳይሬክተሮቹ ገንዘቦቹን በተለያዩ ባንኮች ውስጥ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለአንድ ድራማ ከዚህ ቀደም ከአንድ ዓመት በላይ እንዲጓዝ ዕድሉን የሰጠበት ሁኔታ አጋጥሞ አይታወቅም፡፡ የሰው ለሠው የዚህን ያህል ዓመት እንዲጓዝ የተፈቀደው በምን ምክንያት ነው? ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ኢ.ቲ.ቪ ከዚህ ቀደም በድራማዎች ላይ የተለያዩ የመጠጥ ምርቶችን በምስል ተቀርጸው ተካተው ሲመጡ በግምገማ እንዲወጡ አሊያም ምርቶቹ ሳይታዩ መቀረጽ አለባቸው የሚል ፖሊሲ ነበረው፡፡ አሁን በሰው ለሠው ድራማ ግን ሁሉም ምርቶች እንደልብ እየተቀረጹው ይገባሉ፡፡ ምናልባት በኢቲቪ በኩልም ከነመስፍንና ሠለሞን ጋር በጋራ በመሆን የሚቀጠቀም አለ፡፡ የሠው ለሠው የዳይሬክተሮች የአስናቀን መረን የለቀቀ የዘራፊ ተግባር እያሳዩን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ድራማ ታሪክ ውስጥ የድራማ ተዋናይ ለመመረጥ ‹‹በጡት ማስያዣና ፓንት ፎቶ ተነስታችሁ አምጡ›› ብለው የጠየቁት መስፍንና ሠለሞን በመሆን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ አንዱ ለድራማ መመዘኛ ዲያሎግ በቃል የመያዝ ብቃት የመጀመሪያው መመዘኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሚፈለገው ገጸ ባህሪም የምትሆነውን ተዋንያን በርካታ ገምጋሚዎች ባሉበት ይመረጣል እንጂ ‹‹በፓንትና ጡት ማስያዣ የተነሣችሁትን ፎቶ አምጡ›› ብሎ መጠየቅ ምናልባት ‹‹ምን እየተሰራ ነው?›› ብሎ የሚያስጠይቅም ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያም ፎቶ ከተጠየቁት ሴቶች መካከል ወደፊት በስፋት የምናየው ነጥቦች ይኖራል፡፡ የሠው ለሠው ድራማ ከተጀመረ በኋላ ሁለት ዓመታት ያህል ‹‹ሎሚ ፒክቸርስ በሚል ሲሰራ የቆየው ባልታደሰ ፈቃድ ነው›› ቢባልም በኋላ ላይ ነገሮች እየከረሩና በህግ የተያዘ በመሆኑ ለውጥ ተደረገ፡፡ የሠው ለሠው የዳይሬክተሮች በተለያዩ ጊዜያት ከራሳቸው ተዋናዮች ጋር የሚጋጩበትም አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚህም ከፍ ሲል ከተዋንያኖቹ ጋር በፍርድ ቤት ድረስ እስከመካሰስ ተዳርሰው ነበር፡፡ የክሳቸው መጠን ከመብዛቱ የተነሳ በሣምንት አንድ ቀን የግድ ችሎት ላይ ለመገኘት ተገደዋል፡፡
ባለፈው ሠሞን የኢትዮጵያ ቴሌብዥን ‹‹የሠው ለሠው ድራማ እስከ መጋቢት 30/2006 መጠናቀቅ አለበት›› በሚል ማሳሰቢያ የሰጠ ሲሆን፣ ዳይሬክተሮቹ ግን ‹‹ይህ የጊዜ ገደብ ፈጽሞ ሊጨመርልን ይገባል›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በርግጥ አሁን የድራማው ታሪክ ቢያልቅም ዳይሬክተሮቹ በግድ ታሪኩን እየለጠጡ የአንድ ሰው መጨረሻ የማታይበት እንጂ የዚህን ያህል የተለየ ነገር ታይቶበት አይደለም፡፡ ዳይሬክተሮቹን ከአስናቀ መጨረሻ ይልቅ ያጓጓውና ድራማው ባለለቀ እያሰኘ ያለው ዋናው ጉዳይ ከሠው ለሠው የሚገኘው ደለብ ያለ ጥቅም ነው፡፡ ለተዋናዮቹ አንድም ልብስ የማይገዛውና የተለየ ክፍያ የማያደርጉት የሠው ለሠው ዳይሬክተሮች ይህንን ድራማ ለማቆየት ሲሉ አሁን ደግሞ ወደ ‹‹ልማታዊ ቋንቋዎች›› ገብተዋል፡፡ ገንዘብ ይገኛል፤ ገንዘቡ ግን የት እንደሚገባ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሠው ለሠው በክብር ተጀምሮ በውርደት ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜም ቢኖር የቀናት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ግን ከቴሌቪዥን ጀርባ የተፈፀመው የመስፍንና የሠለሞን ተግባር ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡ በርካቶች ያዘኑባቸውንና ያለቀሱባቸው ዳይሬክተሮች ዛሬ ላይ የደለበውን ገንዘብ ይዘው የተወሰኑትን በጥቅም ለመግዛት ቢሞክሩም፣ ይህ ነገር ያለቀለትና ምናልባትም ሠው ለሠው ከዚህ በላይ እንዳይዘልቅ የሚል ውሳኔ እስከመስጠት ተደርሷል፡፡ እናም 78 ብር አካውንቱ ላይ የተገኘውን ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ያሸሹት የሠው ለሠው የዳይሬክተሮችን መጨረሻ በቅርብ የምናየው ይሆናል፡፡