ከመተንፈሻ አካል ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የአስም ህመም ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለበት በዚህ በክረምት ተባብሶ የመታየት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ቀዝቃዛማ ወቅት እኛ ላይ ይበረታሉ እንጂ ቀዝቃዛማ አየር በሚኖርበት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ችግሩ ተባብሶ መታየቱ አይቀርም፡፡ ይህ ችግር እንዳለ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ታዲያ አስምን ለማከም በየጊዜው የተለያዩ ነባርም ሆኑ አዳዲስ መድሃኒቶች ህክምናውን መሰረት አድርገው በስራ ላይ ውለዋል እየዋሉም ነው፡፡ የአስም መድሃኒቶች የህመሙን መከሰትና የምልክቱ ሁኔታ በማየትና እነሱንም ለመቆጣጠር ይውላሉ፡፡ እነዚህም መድሃኒቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ህመሙን ሊያስታግሱ (በደቂቃ ውስጥም) ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን የአስም መድሃኒቶች በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በመድሃኒቶቹ አሰራር ላይና በሚፈጥሩት የጎንዮሽ ጉዳት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው የሚጠቀምባቸው መድሃኒቶችም ለአጭር ጊዜ ማገገምን ለማግኘት ወይም የረዥም ጊዜ ህመሙን ለማግኘት ወይም የረዥም ጊዜ ህመሙን ለማከም በሚል የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በተቀናጀ መልኩ መድሃኒቶቹን ይጠቀሙባቸዋል፡፡ የአስም ህመም በየጊዜው እንደመለዋወጡ ህመሙን ለመቆጣጠር ከቅርብ የህክምና ባለሙያ ክትትል አለመራቅ ይመረጣል፡፡ ታዲያ የአስም ህክምናዎች ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በዕድሜ፣ በሚያሳየው ምልክትና አስቀድሞ ውጤታማ በሆነው የመድሃኒት አሰጣጥ ላይ የተመረኮዘ ይሆናል፡፡
የረዥም ጊዜ የመድሃኒት አወሰዳደድ
የአስምን ህመም ለመቆጣጠር የረዥም ጊዜ መድሃኒት አጠቃቀማችን በየቀኑ ሊፈፀም የሚችልና ህመሙን በማስታገስ ብቻ ሳይሆን በማከም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህመሙን ከመቆጣጠርና ከመፈወስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነዚህ ህክምናዎች ራሳቸውን የቻሉ ሆነው በተለያዩ ክፍሎች የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የአስም ህክምናዎች በአየር መልክ የሚሳቡ (inhalers) እንደዚሁም ብሮንካይት አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን መከፋፈት ላይ (bronchodilators) ያተኮሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የመድሃኒቶቹን አከፋፈል ግን ቀጥለን እናያቸዋለን፡፡
– በትንፋሽ የሚሰጥ ኮርቲኮስቴሮይድ መድሃኒቶች (Inhaled corticosteroids) ከእነዚህም መድሃኒቶች መካከል ፍሉቲካሶን፣ ቡዲሳያናይድ፣ አዝማኮርት፣ ኤሮቢይድ የመሳሰሉትን የያዘ ነው፡፡ ይህ የመድሃኒት አይነት የመተንፈሻ አካላትን የመለብለብና የመቆጣት ስሜትን ለመቆጣጠር የሚውል ነው፡፡ ይህ በአፍ ከሚሰጠው የኮርኮስትሮይድ የተለየ ሲሆን የጎንዮሽ ጉዳቱም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ መድሃኒት ታዲያ ለረዥም ቀናት ከህመም ለማገገም የሚወሰድ ነው፡፡
– ቤታ-2 አጎኒስትስ (Long-acting bets-2 agonists) ይህ ምድብ ደግሞ ሳልሜቴሮል፣ ፎርሞቴሮል የመሳሰሉትን የያዘ ነው፡፡ ይህም በትንፋሽ የሚወሰድ ሲሆን የመተንፈሻ አካላትን በመከፋፈትና የሴሎችን መቆጣት በመቀነስ ዘና በማድረግ እረፍትን የሚያሰጥ (bronchodilators) ነው፡፡
– ሌኮተሪን ሞዲፋየርስ (Leukotrine modifiers) በዚህ ምድብ ውስጥ ሞንቲሉካስት፣ ዛፊይሉካስት፣ ዛይሊውተን የመሳሰሉትን ያካተተ ሲሆን የአየር ቧንቧን በመክፈት የመከርከርና የመታፈን እንደዚሁም የንፍጥ መሰል ፈሳሽ (mucous) የበዛ ምርትን መቀነስ የሚያስችል ነው፡፡
– ክሮሞላይን እና ኔዶ ክሮማይል (cromlyon and nedocromil) ይህ ደግሞ የአስም ሕመም በተለያዩ አለርጂክ በሆኑ ነገሮች ሲቀሰቀስ የአስምን የህምም ምልክቶች ከመቀነስ ጀምሮ የአለርጂክ ችግሮቹንም ያስወግዳቸዋል፡፡
– ቲዎፓያሊይን፡- ይህ የመድሃኒት ምድብ ደግሞ የመተንፈሻ አካላትን በመከፋፈትና በዙሪያው ያሉ ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ የሚያደርግ ነው፡፡
ፈጣን የማገገሚያ መድሃኒቶች አወሳሰድ
እነዚህ የመድሃኒቶች ምድብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን የማገገም ሂደትን የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ እነዚህም የአስም ህመም ድንገት ሲመጣና አጣዳፊ ሲሆን አስቸኳይ መፍትሄን ከመስጠት አኳያ የሚውሉ ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
– ቤታ-2 አጎኒስትስ (shoprt-acting beta-2 agonists) ከዚህ የመድሃኒት ምድብ ውስጥ አንዱ አልቡቴሮል ሲሆን ጊዜያዊና ፈጣን ምላሽን በደቂቃ ውስጥ መስጠት የሚችል ነው፡፡ የአስም ህመሙ የጠነከረ ከሆነ ግን የማገገሙ ሁኔታ ለ6 ሰዓት ብቻ ይሆንና ከዚህ ሰዓት በኋላ ተመልሶ የመምጣት ሁኔታን ሊያሳይ ይችላል፡፡
– ኢፕራትሮፒየም (Ipratropium/Atrovent) ይህ የመድሃኒት ጥቅም ደግሞ ፈጣን በሆነ መልኩ የህመሙን ምልክት የሚያጠፋና አየር በቀላሉ መውጣትና መግባት እንዲችል የሚያደርግ ነው፡፡ በተለይም የብሮንካይ ችግሮች ካሉ እንዲቀረፉ ያደርጋል፡፡
– በአፍ ወይም በደም ስር የሚሰጥ ኮርቲኮስቶሮይድስ (Oral and in travenous corticosteroids)፡- ፕሪዲናዩሲን እና ሜታይል ፕሪዲናዩሰን በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ የመተንፈሻ አካላትን ዘና በማድረግ መታፈንን በማስቀረት የአየር ቧንቧን በቅፅበት የሚከፋፍቱ ናቸው፡፡ ይህን መድሃኒት አብዝቶ መውሰዱ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚያመጣ የሚመከር አይደለም፡፡
አለርጂ ላይ ያተኮረ የአስም ህክምና /Allergen Immunotherapy/
ይህ የመድሃኒት ህክምና የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ለሚሆኑባቸው ነገሮች የመቆጣት ስሜትን እንዳይፈጥሩ ወይም የሰውነት በሽታን የመከላከል ስርዓት ለአለርጂ መነሻ ለሆኑ ነገሮች ምላሽ እንዳይሰጥ በማድረግ የሚሰሩ ናቸው፡፡
– ኢሙውኖቴራፒ (Immunotherapy)
ይህ ለተወሰኑ ሳምንታት ለጥቂት ወራት የሚሰጥና በቀጣይነትም ለወራት የሚሰጥ ነው፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች ከጊዜ በኋላ አለርጂክ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች የሰውነታችንን የመከላከያ ኃይል በማብዛት ወደ አስም የሚሄዱበትን አጋጣሚ ይቀንሳሉ፡፡
– አንቲ-አይጂ.ኢ ሞኖክሎናል አንቲቦዲይስ (Anti-IgE Mono-clonal antibodies) ኦማሊዙማብ (ዞሌር) የሚባል መድሃኒትን የያዘ ሲሆን በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን ከላይ ካየነው ጋር በተመሳሳይ መልኩ የሚሰጥ ነው፡፡ ልዩነቱ የሚሰጥበት የጊዜ ሁኔታ መለየት ብቻ ነው፡፡ እስከ አሁን የተቀስናቸው መድሃኒቶች አሁን ባሉበት ሁኔታ ጥቅም ይስጡ እንጂ በከፍተኛ የጥናት ምርምር ውስጥ የተሻለ ግኝትም ላይ እንዲገናኙ ለማድረግ ጥረቶች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡