February 16, 2014
18 mins read

Health: ጨው ከደም ግፊት፣ ከስትሮክ፣ ከስኳር እና ከኩላሊት ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል?

ለምግብ ከሚውለው ጨው ጋር በተያያዘ ብዙ ሰው ብዙ ጥያቄ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ ከጥያቄዎቹም፣
– ጨው የበዛበት ምግብ በማዘውተሬ ለደም ግፊት ያጋልጠኛል ወይ?
– አልፎ አልፎ ሰውነቴ ያብጣል ከምግብ ጨው ጋር የሚገናኝበት ሁኔታ አለው?
– ጨው ያለበት ምግብ መመገብ ካቆምኩ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሆኖኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ያለማቋረጥ ጭንቅላቴን ያዞረኛል፡፡ ጨው ካለመመገቤ ጋር ይገናኛል ወይ?
ቀስ በቀስ ከምግብ ስርዓት ጨውን ለማስወገድ ጥረት እያደረኩ ነው፡፡ ምናልባት የሚያጋጥመኝ የጤና እንከን ይኖር ይሆን?
የሚሉት የበርካቶች ጥያቄ ናቸው፡፡ እነዚህን እና ሌሎች ከእናንተ የደረሱንን ጥያቄዎች ይዘን አንድ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ምላሽ እንዲሰጡን አነጋግረናቸዋል፡፡ ለምግብ ማጣፈጫነት ከምንጠቀምበት ጨው ጋር ተያይዘው በተነሱ ጥያቄዎች ዶክተሩ በቂ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጥያቄ፡- ጨው ከምግብ ማጣፈጫነት የዘለለ ጤና ነክ ጥቅሞች ይኖሩት ይሆን?
ዶ/ር ፡- ከአጣፋጭነት ይልቅ ጤና ነክ ጥቅሙ ነው የሚያመዝነው፡፡ ጨው ሶድየም ክሎራይድ የሚባል ማዕድን የያዘ ነው፡፡ በሰው ልጆች ህይወት ጤናማነት መቀጠል የሚያስፈልጉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ ጨው አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም በሰውነት ውስጥ ያሉ ነርቮች፣ ልብ፣ የጡንቻና ሌሎች ሴሎች ምንም እንኳን መጠኑ ዝቅተኛ ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይልን በመጠቀም ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ሌሎች የሚንቀሳቀሱበትን የኤሌክትሪክ ኃይል በመስጠት ደግሞ ከጨው የሚገኘው ሶድየም ፍሎራይድ ማዕድን ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ የጨው ጠቀሜታ አንዱ ይህ ሲሆን በሌላም በኩል ኩላሊታችን በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ፈሳሽ እንዲቆጣጠር ጨው በሰፊው ያግዛል፡፡ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር በመሆን የሰውነታችን አጠቃላይ ሁኔታ መሰረታዊ የሚባሉ ማዕድናት ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ከፍ ያለ ጥቅም ይሰጣል፡፡ በተለይም እንቅርትና ደም ማነስ በማህበረሰብ ደረጃ ደም ማነስን ለመከላከል ጨውን በአዮዲን፣ በብረት እና በሌሎች ማዕድናት ማበልፀግ ጤና ነክ ጥቅሙ የጎላ ነው የሚሆነው፡፡

ጥያቄ፡- በምግብ ስርዓት ውስጥ ጨውን አስወግዱ የሚሉ ሐኪሞች ገጥመውኛል፡፡ ጨውን አለመመገብ ከላይ የተዘረዘሩትን ጤና ነክ ጥቅሞች አያሳጣም?
ዶ/ር ፡- ጨውን ጭራሽ አትመገቡ ብሎ መምከር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ የጨው አጠቃቀማችን ሚዛናዊ መሆኑ ላይ ነው መተኮር ያለበት፡፡ ጨውን መመገብ አቁመን በሰውነታችን ውስጥ እጥረት ቢፈጠር ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርሱ የጤና ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ለምሳሌ ራሳችን ለመቆጣጠር እስከምንቸገር ድረስ ማዞር፣ የጡንቻ ችግር፣ ጠቃሚ ማዕድናት ሚዛን መዛባትና በሰውነት ውስጥ አላስፈላጊ ውሃ ተከማችቶ መመረዝን ያመጣል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጨውን ከሚፈለገው መጠን በላይ አብዝተን የምንመገብ ከሆነ እስከ ሞት የሚዘልቅ የጤና ችግር ሊያጋልጠን ይችላል፡፡

ጥያቄ፡- በተለምዶ አሞሌ ጨው ተብሎ የሚታወቀው በተለይ የገጠሩ ህብረተሰብ በብዛት ሲጠቀምበት ይታያል፡፡ ለመሆኑ አሞሌ ጨው በጤና ተስማሚነቱ በፋብሪካ ከተመረተው ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ፡- በፍፁም አይቻልም፡፡ አሞሌም ሆነ ሌሎች በፋብሪካ ውስጥ ያላለፉና በተለያዩ ንጥረ ነገሮች ያልበለፀጉ የጨው አይነቶች ለምግብነት የሚመከሩ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ከሶድየም ክሎራይድ በተጨማሪ ማግንዥየምን፣ ካልሽየምንና ሌሎች ተለይተው ያልታወቁ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ነው፡፡ በፋብሪካ ተመርቶና በንጥረ ነገሮች በልፅጎ ጥቅም ላይ የሚውለው የገበታ ጨው ግን ከ90 እስከ 97 በመቶ ለጤና ተስማሚ የሆነውን ሶድየም ክሎራይድን የያዘ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ሰው የሚመከረው በፋብሪካ የተመረተውንና በአዮዲን እንዲሁም በአይረንና በሌሎች ንጥረ ነገሮች የበለፀገውን የገበታ ጨው እንዲጠቀም ነው፡፡

ጥያቄ፡- በፋብሪካ የተመረተውንም ሆነ የአሞሌ ባህሪ ያላቸውን የጨው አይነቶች አብዝቶ በመመገብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ዋና ዋና የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?
ዶ/ር ፡- ጥሩ! ጨውን ካስፈላጊው መጠን በላይ አብዝቶ መመገብ የሚያስከትለው የጤና ችግር ሰፋ ያለ ቢሆንም ዋና ዋና የምንላቸውን ስንዘረዝራቸው፣ ከቁጥጥር የወጣ የደም ግፊትን ያመጣል፣ ስትሮክ የማምጣት ዕድሉ ሰፊ ነው፣ የደም ስሮች መሰንጠቅን ያመጣል፣ የልብን የግራ ክፍል ቧንቧ እንዲዳብር እንዲሆን በማድረግ ለልብ ጤና ችግር መቀወስ ምክንያት ይሆናል፣ ኩላሊት ሰውነታችን ከሚጠቀመው በላይ የሆነውን ውሃ ማውጣት ባለመቻሉ እብጠት ይከሰታል፣ ጨውን አዘውትረው በብዛት የሚጠቀሙ ሰዎች ለጨጓራ ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸውም ሰፊ እንደሆነ በጥናት የተደገፉ ማስረጃዎች ያጋልጣሉ፡፡ እንዲሁም ሰውነታችን ከሚፈልገው በላይ ከተጠቀምን በሴሎቻችን ውስጥ ያለው ፈሳሽ ተመጦ በማለቅ ድንገተኛ የሴሎች ሞትን ያመጣል፡፡

ጥያቄ፡- አንድ ሰው በቀን ምን ያህል የጨው መጠን ቢጠቀም ነው ለጤናው ተስማሚ የሚሆነው?
ዶ/ር ፡- ከጨው ውስጥ የሚፈለገው ንጥረ ነገር ሶድየም የሚባለው ነው፡፡ አንድ ሰው በጨው አማካኝነት ማግኘት የሚገባውን የሶድየም ንጥረ ነገር መጠንን በተመለከተ የተለያዩ አገሮች የተለያየ የመጠን ስታንፎርድ ያወጣሉ፡፡ በብዙ አገራት ሙያተኞች ተቀባይነት ያለውን የእንግሊዝን እና የአሜሪካንን ብናየው ለጥያቄህ ምላሽ 㜎ይሆናል፡፡ የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኩላሊት እና ሌሎች መሰል የጤና ችግር ያለባቸው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆነ ሰዎች በቀን መውሰድ የሚገባቸውን የጨው መጠን አስመልክቶ በእንግሊዝ አገር የተቀመጠ አንድ ሰው በቀን 1600 ሚሎ ግራም ሶዲየም መጠቀም እንዳለበት ነው የሚገልፁት፡፡ በአሜሪካ ደግሞ በተጠቀሱት የጤና ችግሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች የአንድ ሰው የጨው የቀን ፍጆታው ከ1500-2300 ሚሊ ግራም ቢሆን ጉዳት የለውም ይላሉ፡፡ ለማንኛውም ጤነኛ ሰው ደግሞ በቀን 4000 ሚሊ ግራም ሶድየም መጠቀም እንዳለበት ሲመክሩ አሜሪካውያን ደግሞ 5750 ሚሊ ግራም ሶድየም ድረስ አንድ ሰው በቀን ቢጠቀም ምንም አይነት የጤና ችግር አያመጣበትም ይላሉ፡፡

ጥያቄ፡- አንድ ሚሊ ግራም ሶድየም ለማግኘት ምን ያህል መጠን ያለው ጨው መመገብ ይኖርብናል?
ዶ/ር ፡- አንድ ሚሊ ግራም ሶዲየም በ2.55 ሚሊ ግራም ጨው ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ 1000 ሚሊ ግራም ሶዲየም በ2.55 ሺህ ሚሊ ግራም ጨው ውስጥ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የአንድን ሰው የቀን የጨው ፍጆታን ለማወቅ ከላይ በሶዲየም መጠን የገለፅናቸውን መጠኖች በ2.55 በማባዛት ትክክለኛውን ስሌት ማወቅ ይቻላል፡፡

ጥያቄ፡- ይህ ስሌት በተዘዋዋሪ መንገድ ከተለያዩ ምግቦች የምናገኘውን ጨው መጠን የሚጨምር ነው?
ዶ/ር ፡- ጨውን በፋብሪካ ውስጥ ከሚመረተው ብቻ አይደለም የምናገኘው፡፡ የምንመገባቸው ጥራጥሬዎች፣ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች እና የእንስሳት ተዋፅኦዎች ውስጥ በተፈጥሮ መጠኑ ይለያይ እንጂ በውስጣቸው ሶድየም አላቸው፡፡ ከላይ ለመግለፅ የሞከርኩት የቀን የሶዲየም መጠን ስሌት በተለያዩ ምግቦች ውስጥ ልናገኝ የምንችለውን የሶድየም መጠን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ አጠቃላይ የጨው አጠቃቀማችን ከምንመገባቸው ልዩ ልዩ ምግቦች ውስጥ የምናገኘውን የጨው መጠን ታሳቢ ማድረግ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡
የአገራችን ባህላዊ ምግብ የሆነው በርበሬ ሲፈጭ በዛ ያለ ጨው ይገባበታል፡፡ ለታካሚዎቻችን ብዙ ጊዜ የምንመክረው በርበሬ ያለውን ጨው መጠቀም በራሱ በቂ ነው ብለን ነው፡፡ በተለይም ክሮኒክ የሚባሉ የጤና ችግሮች ያለባቸውን ሰዎች ምክሩ ያግዛቸዋል፡

ጥያቄ፡- በመጨረሻ ሙያዊ ምክርዎን እንውሰድና ውይይታችን እናጠቃለው፡፡
ዶ/ር ፡- ማናችንም በግልፅ መገንዘብ እንደምንችለው የአገራችን የአመጋገብ ስርዓት ከዘመናዊነት ይልቅ ልማዳዊነት የተጫነው ነው፡፡ በዘመናዊው አስተሳሰብ የሰው ጤና የተሟላ ሆኖ የሚጠበቀው ሐኪም በሚሰጠው ህክምና ሳይሆን እያንዳንዱ ግለሰብ በአመጋገብና በአኗኗር ዘይቤው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ሲችል ነው፡፡ አመጋገባችን ከአካላዊ ዕድገታችን፣ ከጤናችንና በየጊዜው ከምናወጣው ኃይል ጋር የተገናዘበ (የተጣጣመ) መሆን ይኖርበታል፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ አይነት ምግብ በብዛት ከመመገብ ይልቅ ከኃይል ሰጪ፣ ከፕሮቲን፣ ከበሽታ ተከላካይ እና ከንጥረ ነገሮች መገኛ ምግቦች በትንሽ በትንሹ ቀላቅሎ (አመጣጥኖ) መመገብ ተመራጭ ይሆናል፡፡ ምግቦቻችን በይዘትም ሆነ በአይነት አመጣጥኖ የመመገብ ባህላችንን ብናሳደግ ሁል ጊዜም ጤነኞችና ደስተኞች መሆን እንችላለን፡፡ በእኛ አገር ስጋ ተመጋቢ መሆን ብቻውን የጥሩ ተመጋቢነት መገለጫ (ማረጋገጫ ማህተም) አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን መስተካከል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ጥሩ የአመጋገብ ስርዓት ተብሎ የሚወሰደው የእንስሳት ተዋፅኦ ተመጋቢ መሆን ሳይሆን አትክልትና ፍራፍሬና ጥራጥሬ መመገብ ማዘውተር ነው፡፡ ለዚህም ነው አመጋገባችን ሚዛኑን የጠበቀ ይሁን የሚባለው፡፡
ጉዳዩን ቀደም ሲል ከተወያየንበት ጨው ጋር አያይዘን ስናየውም አካሄዱ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡ ጨውን ከመጠን በላይ አዘውትሮ መመገብ ቀስ በቀስ አጠቃላዩን የጤና ሁኔታችን ወደ ቀውስ ውስጥ የሚያስገቡ ስር ሰደድ ህመም ነክ ነገሮችን ያመጣል፡፡

ለምሳሌ አንድ ስር ያለው የለመለመ ተክልን ጨው ውስጥ ብንነክረው በአትክልቱ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሙሉ በሙሉ ተመጥጦ አልቆ አትክልቱ ወዲያውኑ ነው የሚጠወልገው (የሚደርቀው) የሰዎች ሁኔታም ከአትክልቱ ክስተት የሚለይ አይደለም፡፡ የአመጋገብ ስርዓታችን ጨውን በብዛት የምንጠቀም ከሆነ በሴሎቻችን ውስጥ ያለው ውሃ በሙሉ ተመጥጦ ያልቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ሴሎቻችን ባልተጠበቀ ሁኔታ ይሞታሉ፡፡ ጤናችንም ይቃወሳል፡፡ በሌላኛ ገፅ ደግሞ በቀጥታ ከገበታ አልያም ደግሞ ከተለያዩ ምግቦች የምናገኘው ጨው ዝቅተኛ ከሆነና ሰውነታችን ከሚፈልገው መጠን በታች ከሆነ አላስፈላጊ ፈሳሽ (ውሃ) በሰውነት ውስጥ ይከማቻል፡፡ የተከማቸውን ውሃ ኩላሊት በማሶገድ አቅም ያጣል፡፡ ሚዛን የሚጠብቅ ንጥረ ነገር ስለሌለ ሴሎች ከአቅም በላይ በሆነ መንገድ ከውጭ ወደ ውስጥ ውሃን እየመጠጡ ያስገባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሴሎች ያብጣሉ፡፡ በኋላም የደም ስሮች መተርተር ይፈጠራል፡፡ የደም ስሮች ሲፈነዱ (ሲተረተሩ) ከውስጥ ደም ስለሚፈስ ስትሮክ ይከሰታል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከቀላል እስከከባድ ተብለው የሚገለፁ የጤና ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ በአንፃራዊነት ሲታይ ግን ከጨው መብዛት ማነስ ይሻላል፡፡ ከሁሉም ተመራጩና ውጤታማው የሚባለው የምንጠቀመውን ጨው ትኩረት ሰጥቶ ሚዛናዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በተለይም ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ማለትም ከ40 ዓመት በላይ ሲኮን የገበታ ጨውን በጣም መቀነስ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከምግቦች የምናገኘው ሶድየም (ጨው) በቂ ስለሚሆን ነው፡፡
ጥያቄ፡- እናመሰግናለን፡፡S

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop