የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ በውጥረትና በክፍፍል ውስጥ ሲያደርገው የነበረውን ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ የፓርቲውን 45 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አካሄደ። በተራሮችን ያንቀጠቀጠው ትውልድ መጽሐፍ ላይ ለሕወሓት ትግል ሲባል “ቅማል እንደበሉ የተጻፈላቸው” አቶ ስዩም መስፍን፣ የአቶ አርከበ እቁባይን እህት አግብተው በመሃል ላይ ከወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ጋር ነበራቸው በተባለው ግንኙነት የተነሳ ትዳራቸው ችግር ውስጥ ገብቶ በባለቤታቸው ክስ የተነሳ በስማቸው ተመዝግቦ የነበረውን የሕወሃትን ገንዘብ በኒውዮርክ እስከማሳገድ ደርሰው ነበር የሚባልላቸው አቶ ብርሃነ ገ/ክርስቶስን፤ በአዲስ አበባ ላይ ጥሩ ለውጥ አምጥተው በምርጫ 97 ወቅት ኢሕ አዴግ በመሆናቸው ብቻ የተሸነፉትና በዚህም የተነሳ በአቶ መለስ “ቀለም ከመቀባት ሌላ የተሻለ ሥራ አልሰራህም” በሚል የተዘለፉትና ከወ/ሮ ሐዜብ ጋር በከፍተኛ ጸብ ውስጥ እንደከረሙ የሚነገርላቸው አቶ አርከበ እቁባይ ከድርጅቱ መሰናበታቸው ተዘግቧል።
መንግስታዊው ሚድያዎች ሳይቀሩ እንደዘገቡት ለዓመታት ፓርቲውን በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያገለገሉት አምባሳደር ስዩም መስፍን ፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ፣ አቶ አርከበ ዕቁባይና አቶ ዘርዓይ አስገዶም ባቀረቡት ጥያቄና ፓርቲው እየተገበረ ባለው የመተካካት ሂደት መሰረት በአዲስ አባላት እንዲተኩ የወሰነ ሲሆን አንጋፋ አባላቱ በክብር ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ተሰናብተዋል ቢባልም ስንብታቸው ሕወሓት ውስጥ ተፈጥሮ ከነበረው የውስጥ ችግር ጋር ይያያዝ አይያያዝ የታወቀ ነገር ባይኖርም አቶ ስዩም መስፍን በተደጋጋሚ ከሕመም ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ እንዳሉ የዘ-ሐበሻ ምንጮች ጠቁመው ከፓርቲው ራሴን አግልያለሁ ቢሉ እንኳ እንደማይገርም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ሕወሓት እነዚህን ነባር አባላት ያሰናብት እንጂ ብ አዴን አሁንም አቶ በረከትን እና አቶ አዲሱን በማ ዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ይዞ እንደሚቀጥል እየተጠበቀ ነው። ከደህዴን በኩል ደግሞ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አሁንም የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ የኦህዴድ ምርጫ ውጤት ግን ለነገ ቢራዘምም ለድርጅቱ ማ ዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ከ ጉባኤተኛው እጩ አድርጎ ካቀረባቸው መካከል አቶ አባዱላ ገመዳ ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ ፣ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ፣ አቶ ድሪባ ኩማ ፣ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ፣ አቶ ግርማ ብሩና ደግፌ ቡላ ይገኙባቸዋል ተብሏል።