ቦሌ ለሚ ኮብልስቶን በሚሰሩ ሰዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 8 ሰዎች ሞቱ

 

በአዲስ አበባ ከተሰሩ የኮብልስቶን ሥራዎች መካከል (ፎቶ)

በአዲስ አበባ በሚገኘው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ ቦሌ ለሚ  በሚባል አካባቢ ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2005ዓ.ም. ኮብልስቶን በሚሰሩ  ሰዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች  መካከል በተፈጠረ ግጭት 8 ሰዎች  መሞታቸውንና በርካታ ሰዎች  መቁሰላቸው ተጠቆመ፡፡
በፍኖተ ነፃነት ዘጋቢዎች የተጠናቀረው  መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ  የግጭቱ መንስኤ የሞባይል መጥፋት  እንደሆነ እና በዚህም ኮብልስቶን  ትሰራ የነበረችን የአንዲት የአካባቢው  ነዋሪ ሴት ጡት ሌላው ሰራተኛ  በመቁረጡ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ  በአካባቢው ነዋሪዎችና በኮብል ስቶን  ሰራተኞቹ መሀከል ግጭት ተነስቷል፡፡ በዛው ዕለት ፀቡን ለማረጋጋት  የሞከረ ፖሊስም በኮብልስቶን  ተመቶ ወዲያው ህይወቱ ማለፉን  ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ወደ ብሔር  ግጭት ተለውጦ ፀቡ እስከ ሐሙስ  መጋቢት 5 ቀን መዝለቁንና ህይወቷ  ያለፈው ወጣት የአካባቢው (ኦሮሚያ) ተወላጅ በመሆኗ ጉዳዩ ወደ ማኀበረሰቡ  በመድረሱ በርካታ የአካባቢው ሰዎች  ከአያት ኮንዶሚኒየም እስከ ቦሌ ለሚ  ድረስ ከበባ በማድረግ በሰራተኞች  መካከል የኢህአዴግ አደራጅና ሰላይ
ናቸው የተባሉ 6 የወላይታ ተወላጆችን በመግደልና በርካታ ሰዎችን በማቁሰላቸው በአካባቢው ከ3 ተሸከርካሪ  ያላነሱ የፌደራል ፖሊሶች ግጭቱን  ለማረጋጋት ቢገኙም ለማረጋጋት  እንዳልቻሉ ሆኖም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን ወስደው እንዳሰሩ የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ከፖሊስ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫ
የለም፡፡
የዝግጅት ክፍሉ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተዋል ወደ ተባለው ቦሌ  ክፍለ ከተማ ፖሊስ መረጃ ክፍል ስለጉዳዩ ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ዘገባው ወደ ህዝብ እንዲደርስ እስከተደረገበት መጋቢት 7 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ ቀደም ሲል በርካታ ሰዎች የኮብልስቶን ስራ ይሰሩበት የነበረው አያት ጨፌ እና ቦሌ ለሚ
የሚባል አካባቢ ማንም ሰው እንዳይገባ የተደረገ ሲሆን ከሰራተኞች ጋር እዛው በሚገኝ ቀበሌ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ የመንግስት ባለስልጣናት እያወያዩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ችግሩ እስኪፈታም በአካባቢው እስከ ሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ ስራ እንደለሌም ምንጮቻችን ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከጎጃም ፋኖ ዕዝ ዋና አዛዥ ጋር የተደረገ ቆይታ

(ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ከአዲስ አበባ)

Share