ስኬታማ ፌደራሊዝም በመድብለ-ዘውግ ማሕበረሰብ፣ ጠቃሚ የሕንድ ተሞክሮዎች – ተበጀ ሞላ

ብዝሃነት በራሱ ችግር አይደለም፣ እንደ ህንድ ያሉ መድብለ-ዘውግ እና ባለ ብዙ ሃይማኖት ሃገራት በዓለም ግዙፉን የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት ችለዋል። በሌላ በኩል በሃይማኖትም ሆነ በቋንቋ አለመለያየት ለአንድነት ዋስትና አይሆንም። በሶማሌ ጎረቤቶቻችን የሆንዉን ላስተዋለ ይህን እዉነታ አይስተውም። የዚህ አጭር ፅሁፍ ዓላማ ከህንድ ተሞክሮ አንፃር በፌዴራላዊ የመንግስት አስተዳደር መድብለ-ዘዉግ ዴሞክራሲን ለማጠናከር ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ነጥቦች መጠቆም ነው።
 
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ህንድም ባለ ብዙ ቋንቋ እና አምልኮ ህዝቦች መኖርያ ነች። በህንድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች የሚነገሩ ሲሆን 60 የሚሆኑት ቋንቋዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተናጋሪ ሕዝብ አላቸው፣  23 የሚሆኑት ደግሞ በሕገ-መንግስቱ እዉቅና የተሰጣቸው ክልላዊ ቋንቋዎች ናቸው። አብዘሀኛው ሕዝብ የህንዱዝም ተከታይ ቢሆንም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእስልምና፣ ክርስትና፣ ሲክሂዝም እና ቡዲዝም አማኞች በህንድ ይኖራሉ። የቀደምት ስልጣኔ ባለቤቶች ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያን እና ህንድን የሚያመሳስላቸው ሌላው ጉዳይ ፌደራላዊው የመንግስት መዋቅራቸው ነው። የህንድ ፌደራላዊ ስርዓት በስኬታማነቱ በምሳሌነት ተጠቃሽ ነው። በተቃራኒው እኛ ደግሞ ገና በሙከራ ላይ ነን፣ ከወዲሁም በርካታ ፈተናዎች ገጥመዉናል። ፈደራላዊ አስተዳደራችን ከገጠመው ዉስብስብ ችግር አንፃር በዚህ ክፍል ለኛ ይጠቅሙ ይሆናል ያልኳቸውን አምስት የህንድ ተሞክሮዎችን ባጭሩ እጠቅሳለሁ።
 
(1) ለዉጥ አስተናጋጅ ፌደራሊዝም ለሀገር ሕልዉና ወሳኝ ነው
 
ለውጥ ተፈጥሯዊ ነው። በማህበራዊዉ ዓለም አንድም ቋሚ ነገር የለም፣ ከለውጥ ዉጪ። በ1956 ህንድ 13 ክልሎች ብቻ ነበሯት።  በሂደት ዘዉግ-ተኮር የራስ-ገዝ ጥያቄ እየገፋ ሲመጣ የፌደራል መንግስቱ አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት ነበረበት። ስለዚህ ባለፉት 60 ዓመታት ዉስጥ 16 ተጨማሪ ክልሎች ተፈጥረዋል። የዘርፉ ባለሙያዎች ህንድ እንደሀገር ለመዝለቅ ያስቻላት ቁልፍ ነገር ቢኖር ከሀገር ሕልዉና በመልስ ያለን ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል አሰራር ዘርግቷል ነው ይላሉ። በየዘመኑ አማፅያን ብሄርተኞች ኃይላቸውን አጠናክረው ሲነሱ ህንድ የራስ-ገዝነት መብት በማጎናፀፍ ማዕበሉን ታበርዳለች። ለዉጡ ህገመንግስቱንም ይጨምራል። ባለፉት 70 ዓመታት ህንድ 150 የህገ-መንግስት ማሻሻያዎችን አድርጋለች።   ህገ-መንግስት ሕይወት እንዳለው ነገር ሁሉ የሚወለድ እና የሚለወጥ ለመሆኑ የህንድ ተሞክሮ ጠቃሚ ዋቢ ነው።
 
እኛም ከዚህ የምንማረው ቁምነገር ቢኖር የፖለቲካ ኃይሎች የሕገ-መንግስት ማሻሻያም ሆነ የክልልነት ጥያቄ ቢያነሱ ሊያስጨንቀን አይገባም።  በተንኮሻኮሸ ቁጥር መበርገግ የለብንም። በዋናነት የሚያስፈልገን አስቸጋሪ ጥያቄዎች ሲነሱ በግዜና ባግባቡ መመለስ የሚያስችለንን ተቋማዊ ብቃት መፍጠር እና ሕጋዊ አሰራር መዘርጋት ነው።
 
(2) ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም በልዩነት አብሮ መስራትን ይቀበላል 
 
አስፈላጊው ሕጋዊ እና ተቋማዊ አሰራር ከተዘረጋ በርዕዮተ-ዓለም ዋልታ የረገጡ የፖለቲካ ኃይሎች በአንድ ፌደራላዊ መንግስት ስር መስራት ይቻላሉ።   ህንድ ገና ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ወጥታ የዴሞክራሲ ተቋማትን እያጠናቀረች እያለ በደቡባዊቷ የኬራላ ክልል የኮሚንስት ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ ወደ ስልጣን ወጣ። በወቅቱ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው የህንድ ብሔራዊ ሸንጎ ሂደቱን ለማንኮላሸት ቢሞክርም፣ የኬራላ ኮሚንስቶችን ግን ማቆም አልተቻለውም። ባለፉት 60 ዓመታት በክልሉ ስምንት ግዜ በምርጫ አሸንፈው ለስልጣን በቅተዋል። ኮሚኒስቶቹ የክልል መሪዎች ከሊበራል ዴሞክራቶቹ ሀገር-ዓቀፍ ፓርቲዎች ጋር ተግባብተው መስራት ችለዋል። ህንድ በቀኝ-ዘመሙ የናሬንድራ ሞዲ ፓርቲ በምትመራበት በአሁኑ ግዜ እንኳ በጥምር መንግስት ኬራላን የሚያስተዳድሩት ግራ-ዘመም የፖለቲካ ኃይሎች ከፌደራል መንግስቱ ጋር ተናበው ይሰራሉ። የኬራላ ግዛት ከሁሉም የህንድ ግዛቶች በተራማጅነቷ ግንባር ቀደም ነች። በሰብዓዊ ልማትም ከአዉሮጳ ሃገራት ጋር ትወዳደራለች። ለዚህ ስኬት ደግሞ የኮሚኒስት ፓርቲው ድርሻ ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገራል።
 
ወደኛ ሀገር ሁኔታ ስንመጣ፣ በርዕዮተ-ዓለም የማይገናኙ ኃይሎች በሃገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩ በቅንጅት የሚሰሩበት ጊዜ እንደሚመጣ መጠበቅ አለብን። ለምሳሌ በቀጣዩ የምርጫ ዉጤት የብልፅግና ፓርቲ የላቅ ድምፅ አግኝቶ መንግስት ለመመስረት ከበቃ፣ ተቃዋሚ ቡድኖች ቢያንስ ከትግራይ እና ከአዲስ አበባ ተወክለው ወደ ፓርላማ ሊገቡ ይችላሉ። ያ ከሆነ ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲያን እና ሊበራል ዴሞክራሲያን በሚያገናኛቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ይገደዳሉ። ስለዚህ በግዜያዊ ግለትና ብስጭት በርቀት የቃል ድንጋይ የሚወራወሩ ኃይሎች ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው አሁን ነው።  የጋራ ሀገር እስካለ ድረስ የማያገናኝ የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት፣ የማይታለፍ የፖለቲካ ወጀብ የለም። በእልህ እና በግል ቁርሾ ሕዝብን ማንገላታት፣ ሃገርን ወደ ፖለቲካ ቀውስ መክተት በትዉልድ ያስጠይቃል።
 
(3) እውነተኛ ፌደራላዊ ስርዓት ሃገራዊ ሉዓላዊነትን ለድርድር አያቀርብም
 
የህንድ ህገ-መንግስት ለሀገራዊ ሉዓላዊነት ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣል። በአንቅፅ 51A መሰረት የመንግስት ዋና ኃላፊነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና አንድነት መጠበቅ ነው። ህንዶች ህገ-መንግስታቸውን ሲያረቁ በምሳሌነት ያጠኑት የፈረንሳይን፣ ካናዳን፣ ስዊዘርላንድን፣ እና አሜሪካን ነበር። ከፈረንሳይ ዉጭ ሁሉም ጠንካራ የፌደራል ስርዓት የገነቡ ስኬታማ ሃገራት ናቸው (በአንፃሩ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት በምሳሌነት የወሰደው እንደ ዮጎዝላቪያ እና ሶቬት ህብረት የመሳሰሉ የከሸፉ ኮሚኒስት ሃገራትን ነበር)። ለሕንዶች መገንጠል አማራጭ አይደለም። ማንኛም የፖለቲካ አጀንዳ እና ክርክር ከሀገሪቱ ሉዓላዊነት በታች ነው። በ1946 (እአአ) የብርታኒያ መንግስት የህንድን አስተዳደር ወደ ህንዳዉያን ለማዞር የሚያስችለውን ሥራ ሲያጠናቅቅ አንድ ቁልፍ ዉሳኔ አቅርቦ ነበር። እሱም በአዲሱ የህንድ ህገ-መንግስት የመገንጠል መብት እንዲካተት የሚል ነበር። ሕዳዉያን ሃሳቡን አልተቀበሉም። መገንጠል የሚፈልጉትን ከሕገ-መንግስቱ በፊት አሰናብተው ትኩረታቸውን በፍትህ እና ዴሞክራሲያዊነት ላይ አደረጉ።  ከዚህ በመነሳት አንዳንዶች “ሃገራዊ ልዑላዊነትን በተመለከተ የህንድ የፖለቲካ ስርዓት በቅርፅ ፌደራላዊ በመንፈስ አሃዳዊ ነው” ይላሉ። 
 
የኛን ፌደራላዊ ስርዓት ከህንድ ተሞክሮ በመሰረታዊ መልኩ የሚለየው ኢትዮጵያን እንደ ሉዓላዊ ሀገር አለመቀበሉ ነው። በሕገ-መንግስቱ (አንቅፅ 8) በግልፅ እንደተቀመጠው በኢትየጵያ ሉዓላዊው ዘውግ ነው። ይሄው ሉዓላዊ ዘውጌም ባሻው ግዜ የመገንጠል መብት አለው (አንቅፅ 39[4])። ሆኖም ታሪክ እንደሚያስተምረን መገንጠልን መብት ያደረገ ሀገር ይዉል እንደሆን እንጂ አይከርምም። ዮጎዝላቪያ በ1974 የብሔሮችና ብሔረሰቦች የመገንጠል መብት በሕገ መንግሥት እንዲረጋገጥ አድርጋ ነበር። የሶቭየት መሪዎችም በ1977 ባሻሻሉት ሕገ መንግሥት የኅብረቱ አባላት ባሻቸው ጊዜ የመገንጠል መብት እንዳላቸው አዉጀው ነበር። ሁለቱም ሃገራት ዛሬ በሕይወት የሉም፣ ተበትነዋል። በርግጥ  
ሀገራዊ ብሔርተኝነትና የዘውጌ (Ethnic) ማንነት መሰረታዊ ቅራኔ እንደሌላቸው የህንድ መድብለ-ዘዉግ ዴሞክራሲ ሁነኛ ማሳያ ነው። ፑንጃቢው ህንዳዊነቱን ሳይጥል በዘዉጌ ማንነቱ ኮርቶ ይኖራል። እኛ ግን የዘውጌ ማንነትን የተረዳንበትና ፖለቲካዊ ጥያቄውን ምላሽ ለመስጠት የሄድንበት መንገድ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያልተዛመደ ነው፤ ምንጩም ግራ-ዘመሞቹ የ ‘ያ ትዉልድ’ ሰዎች በክፉ ቀን ሳያላምጡ የዋጡት የባዕድ ፖለቲካ ለመሆኑ አያጠያይቅም። የእኛ ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ ሃሳቡን ካመጣንባቸው ዩጎዝላቪያና ሶቭየት ኅብረት ፍርስራሽ አዳዲስ ሃገራት እየተመሠረቱ ነበር። ሐሳቡ እነሱን እንዳጠፋቸው እያወቅን ራሳችንን ለማዳን ሌላ አማራጭ መንገድ አለመከተላችን ግራ ያጋባል። በዚህ ዘመን በዓለም ራሷን ሉዓላዊ አድርጋ የማታይ፣ መገንጠልን መብት ያደረገች ብቻኛ ሀገር ኢትዮጵያ ነች። አሁን የሚታየው ፖለቲካዊ ጡዘት እና ፅንፈኝነት በግዜ እልባት ካላገኘ፣ ከታሪክ ሳንማር መሽቶብን እንዳንበተን እሰጋለሁየሀገሪቱን ሕልዉና ለማረጋገጥ፣ የተረጋጋ የፖልትቻል ሂደት እዉን ለማድረግ ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ለነገ የማይባል የጋራ አጀንዳ መሆን አለበት። ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ከሀገሪቱ ሕልዉና በታች መሆኑን በሕግ ማረጋገጥ አለብን።
 
(4) ጠንካራና ዘላቂ ፌደራሊዝም ራስ-ገዝ የብሔራዊ መዲና ግዛት ይፈልጋል 
 
የፌደራል ስርዓት የክልሎች ህብረት እንደመሆኑ ለሁሉም ማዕከል የሆነ የትኛውም ክልል በተለየ የባለቤትነት መብት የማያነሳበት ነፃ ዋና ከተማ ያስፈልገዋል። ከዚህ እዉነታ በመነሳት ህንዶች 
በ1956 የሕገ-መንግስት ማሻሻያ አድርገው ደልሂን ነፃ የብሔራዊ መዲና ግዛት አድርገው አቋቋሙ። ይህን በማድረጋቸው በክልሎች መሃል ሊፈጠር የሚችለውን ያልተገባ ሽኩቻ አስቀርተዋል። የሌሎች ፌደራላዊ ስርዓት አራማጆች ተሞክሮም ከዚህ የተለየ አይደለም። የአዉስትራሊያ መንግስት በስድኒ (ኒው ሳውዝ ዌልስ ክልል) እና ሜልቦርን (ቪክቶሪያ ክልል) መካከል የተፈጠረውን አላስፈላጊ ፉክክር ለመፍታት ዋና ከተማውን ከሁለቱም አርቆ፣ ከየትኛውም ክልል ነፃ የሆነ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር አዉስትራልያን ካፒታል ተሪተሪ (Australian Capital Territory) የሚል ግዛት መስርቷል። በካናዳም ኩቤክ እና ቶሮንቶ ያለ ልክ ፉክክር ዉስጥ ቢገቡ ንግስት ቪክቶሪያ በሁለቱ መሃል የምትገኘውን ኦታዋን ለዋና ከተማነት መረጡ። አሜሪካኖችም እንዲሁ የፌደራል መንግስቱን ዋና ከተማ የመሰረቱት ከሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ ክልሎች ተዋጥቶ በተሰጠ ነፃ መሬት ላይ ነው። ቦታው የተመረጠው የሰሜኑን የኢኮኖሚ ኃይል ከደቡቡ የፖለቲካ ኃይል አማዝኖ ለመያዝ እንደሆነ ይነገራል። 
 
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቅፅ 49(5) በፌደራሉ ዋና ከተማ ሌላ ቡድን ልዩ ጥቅም እንዳለው ያስቀምጣል። ይህ ቀያጅ እና ተጋፊ ድንጋጌ ነው። መንግስት የአዲስ አበባን ባለቤትነት የአዲስ አበባዉያን እና የመላው ኢትዮጵያዊያን ብቻ መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ ለማረጋገጥ የታሪክም የፖለቲካም ድጋፍ አለው ብዬ አምናለሁ። በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ የሚገኝ ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል የሚዋሰን የብሔራዊ መዲና ግዛት ያስፈልገናል።
 
(5) ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ዉህዳንን ከጨፍላቂዎች ይጠብቃል
 
በአንድ የህንድ ክልል ዉስጥ አናሳ ቁጥር ባለው ሕዝብ የሚነገር ቋንቋ ቢኖር እንደተናጋሪዎቹ ፍሎጎት፣ የክልሉ መንግስት እውቅና የመስጠት ግዴታ አለበት፣ የቡድኑ አባላትም ልጆቻቸው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን ባፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማስተማር መብታቸው በሕግ ተረጋግጧል (አንቅፅ 30[1])፣ በተግባርም ህንድ ረጅም ርቀት ተጉዛለች። የ ዉህዳን ቡድኖችን መብት ባግባቡ በማያከብሩ ክልሎች የሀገሪቱ ርዕሰ-ብሔር በቀጥታ ጣልቃ እንዲገቡ ህገ-መንግስቱ (አንቅፅ 350A) ይፈቅዳል።  
 
በኛ ሀገር ግን መሰል መብቶች በወረቀት (በሕገ-መንግስቱ አንቅፅ 39[2] እና በትምህርት ፖሊሲው) ቢሰፍሩም በወጥነት ሲተገበሩ ግን አይታይም። ለምሳሌ የአማራ ክልል በዉስጡ ያሉ አናሳ የዘዉጌ ቡድኖች (ኦሮሞኛ ተናጋሪዎችን ጨምሮ) በቋንቋቸው እንዲማሩ ሲያደርግ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ በርካታ አማርኛ ተናጋሪዎች ግን ልጆቻቸውን ባፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር አልቻሉም። በትግራይ ክልል እንዲሁ በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጠው በራስ ቋንቋ የመማር እና የመዳኘት መብት በይፋ ተጥሷል። በመሆኑም ወደ ትግራይ የተካለለ የራያ ሰው ባፍ መፍቻ ቋንቋው ሳይሆን በትግርኛ እንዲማርና እንዲዳኝ ይገደዳል።  የአናሳ ቡድኖችን መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት በዋናነት ለክልሎች ተሰጥቶ ለትግበራው በፌደራል መንግስቱ ልዩ ክትትል ቢደረግበት አሁን በየአቅጣጫው የምንሰማው ብሶት እና ምሬት እዚህ ደረጃ ባለደረሰ ነበር። ወደ እዉነተኛ ዴሞክራሲያዊ የፌደራል ስርዓት የምናደርገው ጉዞ ይህን መሰል ጉልህ ኢፍትሃዊ አሰራር በማረም መጀመር ይኖርበታል።
 
ሃሳቤን ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ነጥብ ላንሳ። በህንድና መሰል አገሮች ተተግብሮ እንዳየነው ፌዴራላዊ ስርዓት መድበለ-ዘውግ ዴሞክራሲን ለመገንባት ምቹ ነው። ሀገራዊ ማንነትን እና የዘውጌ ማንነትን ሚዛን ጠብቆ የመያዝ ብቃት አለው። የግለሰብና የቡድን መብቶችን አጣጥሞ ያስተናግዳል። መርሆው ተጓዳኝና ተደራቢ ማንነት ያላቸውን የተለያዩ የማኅበረሰቡ አባላት በእኩል ዜግነት የሚያስተናግድ የፖለቲካ ሥርዓት ዕውን ማድረግ ነው። አካታችነቱ እንዳለ ሆኖ ስኬታማ መድበለ-ዘውግ ዴሞክራሲ ለጋራ እሴቶች ግንባታና ጥበቃ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በስምምነት የሚፈጠር የጋራ እሴት ማዕከላዊ ይሆንና የዳርቻውን ማንነት በአዝጋሚ ስበት ያስገባል። በሒደቱም በማንነት ላይ ሳይሆን መርህ ላይ የቆመ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን አመዝኖ የሚያስተናግድ የዜግነት ፖለቲካ ዕውን ይሆናል። እኛም እንደ ሀገር ይሄኛውን መንገድ ብንመርጥ በአንድነት ለተሻለ ብልፅግና እንበቃለን። 
 
ቸር እንሰንብት! 
———————
ተጨማሪ ያንብቡ:    " በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው... " መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 
Share