ሰው ሁሉ ኃይማኖቴ ነፃ ያወጣኛል እያለ ፣ዘላለማዊ ህይወትን በመሻት ወደ አምልኮ ሥፍራው መመላለሱን እሥከ ፍርድ ቀን አያቋርጥም።
ሰው ሁላ ከ70 ዓመተ ዓለም ጀምሮ ሀይማኖት እንዲህ ዓይነት ተሞክሮ አለው። በአንድ ፈጣሪ ፈጣሪነት ከማመኑ በፊት፣ የፓጋን እምነት ነበረው።
በዛን ዘመን ፓጋኒዝም በራሱ ኃይማኖት ነበር።የግሪክ ፈላሥፎችም የኃይማኖቱ መሠረቶች ናቸው።ሁሉ ነገር ከጥያቄ እና ከመልሱ እንደገና ከጥያቄው ነው እየታወቀ እና እየተለየ የመጣው።ዛሬም ይጠየቃል።ይመለሳል።”እውነቱ የቱ ነው?” ይባላል።ዛሬምቢሆን።
ዛሬም ቢሆን ፣ ሰው ልጅ በተለያዩ የማምለኪያ ሥፍራዎች፣ቤተ መቅደሶችና መሥጂዶች የሚመላለሰው ለገዛ ጥቅሙ እንደሆነ በእውነት ይመሠከራል። “ለገዛ ሃጃው እንጂ ለማንም ሲል ማንም በየማምለኪያ ሥፍራ አይመላለሥም…።”ቢባልም እውነቱ ይህ ብቻ እንዳይደለም ፈላሥፎች ያለፍራቻ ይናገራሉ። “ለቅሚያ፣ለዝርፊያ ለዝሙት እና ሌብነቱን ለመደበቅ በየኃይማኖት ተቋማቱ የሚመላለሥም እንዳለ አትዘንጉ።”ይሉናል።…
እርግጥ ፤አማኝ ሁሉ፣በተመረጠለት እና በመረጠው ኃይማኖት፣ በተፃፈ የአምልኮ ሥርአት አማካኝነት ፣ በተሠመረለት መሥመር ወይም የእምነት መንገድ ተጉዞ የማይሞትበትን እና በሥቃይ ለዝንት ዓለም ከመሠቃየት የሚያመልጥበትን ሥፍራ በማግኘት እፎይ ለማለት ይተጋል። ይህ አማኝ የሚኖረው” የማመልከውን በምድራዊ የአምልኮ ሥርአት እያመለክሁ እና እያገለገልኩ ለዘላለም ዓለም ፈጣሪዬ በአዘጋጀልኝ ሠማያዊ ሥፍራ ነገ እኖራለሁ።” የሚል ተሥፋ ሰንቆ እንደሆነ ይታወቃል።
“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እና ንሥሐ ግቡ ” ብሎ እንደ መጥመቁ ዮሐንሥ ፣ ሰውን ከተኛበት አንቅቶ ወደንስሐ እንዲገባ ያሥገደደው ባይኖርም፣ የዛሬ እምነቱ ነገ መንግሥተ ሰማይ በተሰኘው ሀገር፣ ዘላለማዊ ደሥታ ና የህሊና ምቾት ያሥገኝልኛል፣ ብሎ ነው ፣ጥቂት የማይባለው አማኝ እንደ እምነቱ በየማምለኪያ ሥፍራው ሥርዓተ አምልኮውን ተከትሎ የሚማፀነው።ደጅ የሚጠናው። የሚፀልየው እና የሚፆመው።…ማለት እንችላለን።
ብዙሃኑ አማኝ ደግሞ፣ የእምነት ክብረ በዓል ቀን የእምነት ሥፍራዎችን የሚያጨናንቀው መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ አይደለም።(መ/ቤቶች የሚዘጋባቸው የኃይማኖት በዓላትን የምናከብረው ለፅድቅ ነው ባዮች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።) በዓሉን ተከትሎ የሚደረገው የፈንጠዝያ እና የመብልና መጠጥ ሥርዓት ማርኳት የክት ልብሱን ለብሶ በአደባባዩ የሚታየው ከልቡ ከሚያምነው በእጅጉ ይበልጣል።(…)
እርግጥ ነው፣የበዛው አማኝ የሚከተለውን ኃይማኖት የአምልኮ ሥርአትን በጥልቀት አያውቅም ።ፈጣሪን፣ አላህ፣ዋቃ፣ ወዘተ እያልን በየቋንቋችን የዓለም ህዝቦች ሁሉ እንጥራው እንጂ፣ፈጣሪያችን የተቋራኘው ቀጥታ ከህሊናችን ጋራ ነው።እናም ፈጣሪ ለሙሴ በገሃድ እንዳልታየው ሁሉ፣ ለእኛም በገፅ ሊታየን ከቶም አይችልም።
እርግጥ ነው፣ ሙሴም ድምፅና እሣት እንጂ የፈጣሪ መልክ አልታየውም።ኢየሱስም በፈጣሪነቱ ሥለ ፈጣሪ (ሥለራሱ) ተረኳል። ቁርጥ አድርጎ በመልክ እና በአምሣል እንመሳሰላለን ብሏል።”ወልድን ያየ አብነ አይቶታል።”በማለት።
አሥረጂ:-
(John 14 )
————
1 ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።
2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤
3 ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።
4 ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።
5 5 ቶማስም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው።
6 ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።
8 8 ፊልጶስ- ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።
9 ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ?
10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።
11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።
12 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥
13 እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።
14 ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።
15-16 15-16 ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤
17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።
18 18 ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።
19 ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።
20 እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።
21 ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።
22 22 የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ፦ ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው።
23 ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።
24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።
25 25 ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤
26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።
27 27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።
28 እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር።
29 ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን ነግሬአችኋለሁ።
30 ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤
31 ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።
“(John 15 )
————
1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው።
2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።
3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤
4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።
5 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።
6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።
7 በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።
8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።
9 አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ።
10 እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።
11 ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ።
12 እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።
13 ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።
14 እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።
15 ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።
16 እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።
17 እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ።
18 18 ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ።
19 ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።
20 ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።
21 ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።
22 እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም።
23 እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል።
24 ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል።
25 ነገር ግን በሕጋቸው። በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
26 ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤
27 እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።”
በላይ ባለው በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 14 እና 15 በተፃፈው፣ የክርስቶስ ወልድ ገለፃ እና በእኔ መረዳት እያንዳንዱ ሰው ገና በእናቱ ማህፀን ሣለ ከፈጣሪ ጋር በፈጣሪ መረብ (GOD net) የተሳሰረ ነው ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል።ልክ እንደ ኢንተር ኔት ማለት እኮ ነው።
ሰው ልጅ፣ ሲፀነስ ጀምሮ ከፈጣሪ ጋር በተሳሰረው የመልካምነት ድር አማካኝነት በህሊናው ተሳስሯል። ሰው በዚህ መረብ አማካኝነት እያደገ ሲሄድ፣ ” ክፉና ደጉን” እየተገነዘበ ይሄዳል። ይላል የእኔ አሥተምህሮ።በእርግጥ የራሴን ቤተ እምነት ገንብቼ በዚህ አሥተምህሮ መግፋት እና ብዙ ተከታዮች ማፈራት ራእዬ አይደለም።ይሁን እንጂ ቀላል ተደራሽነት ያለውን ይህንን መድረክ መርጫለሁ።(የበየነ መረብን እና የመገናኛ ብዙሃንን መድረክ ማለቴ ነው።) ይህ መድረክ በቀላሉ ሃሳቤን ተደራሽ ያደርግልኛል። ደግሞም የተለየ የእምነት አሥተሳሰቤን እንዳልቀማ ምሥክር ሆኖ ያገለግለኛል።በዚህ እምነቴም ለመጀመሪያ ጊዜ የኃይማኖቴን ፍልሥፍና ይፋ እንዲያደርግልኝ “ዘ ሐበሻ” ድረ ገፅን መርጫለሁ።…(በመግቢዬ ላይ ያነሳሁት ውግዘት እንደማያጋጥመኝም ተሥፋ አደርጋለሁ።)
እንደሚታወቀው፣ በሰው ህሊና በተቃራኒነት የሚቆሙ ሁለት ተፃራሪ ሃሳቦች ሁሌም ይመላለሳሉ።እነዚህን ሃሳቦች መልካም ሃሳቦች ወይም የፅድቅ ሃሳቦች እና ክፉ ወይም የሐጥያት ሃሣቦች በማለት ለሁለት እንከፍላቸዋለን።ሰው ልጅም ሁለቱን በማመዛዘን የተሻለውን ወይም መልካሙን እና የፅድቁን ድርጊት እንዲፈፅም ከፈጣሪው ይሁንታ ተሰጥቶታል። ወደ ድርጊት የመቀየር ፈቃድ ፈጣሪ የሰጠው ግን ለመልካሙ ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል።
ሁኔታዎችና ነገሮች ሁሉ በፈጣሪ ሲታወቁ፣ሰው ግን በፈጣሪ ዘንድ ሁለት አማራጮችን ይዞ ከመጓዝ መልካሙን ይዞ መጓዝ እንደሚበጀው ይመከራል። ይኸውም
ክፉ ከመሆን ደግ መሆንን ፤ ውሸታም ከመሆን ይልቅ እወነተኛ መሆንን፤ ከመጥላት ይልቅ ማፍቀርን ፤ከብልግና ጨዋነትን ፤ከሥንፍና ሥራን ፤ከመርገም መመረቅን፤ ከመሥቆንቆን መሥጠትን፤ከጥመት ቅን መሆንን፤ከሃሜት ግልፅነትን፤ ከድህነት ብልፅግናን ፤ከመለፍለፍ ማዳመጥን፤ ካለማመን ማመንን፤ከሃይማኖተ ቢሥነት ኃይማኖተኛ መሆንን፤ከሞት ህይወትን ፤ ወዘተ ።
ፈጣሪ በቁጣውና በእያንዳንዳችን ሀይወት ላይ በግልፅ በሚታይ ኑሮና ህይወት መልካም እና ክፉ መሥራታችንን ይነግረናል።የአበራሽን ጠባሳ አይተን ግን አንማርም።በእሳት መጫወታችንን እንቀጥላለን።
ይሁን እንጂ፣ከመልካም ነገሮች በተቃራኒ የሚጎዝ ሰው ሁሉ፣አንደኛ ለራሱ አይሆንም። ሁለተኛ ለቤተሰቡ አይሆንም። (ልጆቹ በእርሱ መልካምነት እና ታታሪነት ላይ የተመሰረተ ቀጣይ ህይወት ቢኖራቸውም ፣አባት እና እናት የመጥፎ መንገድ ተከታይ ሥለሆኑ ብቻ ልጆች ድህነት እና አበሳን አይወርሱም።ልጆቻቸው፣ በአጋጣሚ የሚያገኙትን መልካም እድል በበጎነት ከተቀበሉ የሚያሥደንቁ፣ የተሻሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።)ሦሥተኛ ለሀገሩ የማይጠቅም ከንቱ ፍጥረት ነው የሚሆነው።ይህ ከንቱነት እንዳያጋጥመው ሰው ህይወቱ እሥካለ ድረሥ ከመጥፎዎቹ የህይወት መንገዶች ይልቅ ከመልካሞቹ የህይወት መንገዶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ማድረግ ይጠበቅበታል።ጥብቅ ቁርኝትም የሚኖረው፣ለመጥፎ ነገር ሁሉ፣”እንቢ”በማለት ዘወትር በፍልሚያ ውሥጥ ለመኖር ሢችል ነው።
ማንኛውም አማኝ ከዚህ ዓለም የኑሮ ፍልሚያ ነፃ አይደለም። አፍሪካዊው ለእለት ጉርስ ለዓመት ልብስ ሌት ተቀን ሲለፋ፣የዕለት ጉርስም ሆነ የዓመት ልብስ ችግራቸው ያልሆነ፣ በቁሥ የታጀበ የተዝናኖት ኑሮ ለመኖር ሲሉ፣ አሥራ ሥድሥት ሰዓት ተግባራዊ በሆነ ሥራ ተሰማርተው ኑሯቸውን ለመለወጥ የሚተጉ በተቃራኒው አሉ።እነዚህም የበለፀጉት ሀገራት ዜጎች ናቸው።
ይህንን እውነት፣ አእምሮ ያለን እና የዓለምን ተጨባጭ የኢኮኖሚ እውነታ የምንረዳ በቀጡ እንገነዘባለን።ይሁን እንጂ በነዚህም ባለፀጋ ሀገራት መጥፎ ነገሮች በህሊናው ታጭቀው፣ከሰው በታች እንዳያደርጉት እንቢ የሚል ሰው በዝቷል አንልም። ከሥነ ምግባር አንፃር በርካታ አጓጉል ድርጊቶች በበለፀገው ሀገር ነው ያለው። እንደውም ከብልግና አንፃር መልካሞቹን የፈጣሪ ሃሳቦች በህሊናው የሚያሥተናግድ በበለፀጉት ሀገሮች የበዛ አይደለም።
እውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ኢሲያ በላሃጫምነት እና በቅርሻታምነት የሚታወቁ አያሌ ህሊና ቢሥ ወጣት እና ጎልማሶች እንዳሏቸው እሙን ነው።
“በብልግና እና በክፋት ተሞልቶ በነውር ከሚኖር ባለፀጋ ይልቅ አለነውር የሚኖር ደሃ በፈጣሪ ዘንድ የተሻለ ነው። “የተባለው የፈጣሪ የዘላለማዊነት መሥፈርት መልካም ነገር ብቻ ሥለሆነ ነው።(ኢየሱስ ክርሥቶሥ እኔ እውነት ህይወትም፣መንገድ ነኝ ሢል፣መልከም ነገሮችን ያሥተማረው በእነዛ መልካም ነገሮች ብቻ መንግሥተ ሠማይ እንደምትገኝ ሰው ሁሉ እንዲያውቅ እንደሆነ እሙን ነው።የሰው ህሊና ከክፉ አሥተሥሠብ እሥካልነፃ ጊዜ ድረሥም ከፈጣሪ ጋር ህብረት አይኖረውም። በሰው ህሊና መጥፎ አሥተሳሰብ ከታጨቀ ደግሞ መልካሙ ህሊና በበጎነት የተሞላው የፈጣሪ መረብ በመጥፎው ሰውን በሚጎዳው ቫይረሥ ተጠቅቶል ማለት ነው። አጥቂው ቫይረሥም ከመልካሙ የፈጣሪ መረብ የሚፃረረው የክፋት ሰራዊት ቫይረሥ ነው። ይህ አውዳሚ ቫይረስ ነው። ቀሥ፣በቀሥም እየገዘገዘ ፣አሳሥቆ ወደሞት የሚወሥድ አደገኛ ቫይረሥ ነው።
ይህ ቫይረሥ አእምሮአችንን ከመቆጣጠሩ በፊት ፣መልካምነት ሁሉ በውስጡ አጭቆ በያዘ ፀረ -ቫይረሥ ልናጠፈው ይገባናል።ቶሎ ብለን ካላጠፋነው፣እጣ ፈንታችን ጥርሣችንን እያፎጨን ወደ መቀመቅ መውረድ ነው።
መቀመቅ ላለመውረድ ይመሥላል ሰው በቡድን ሆኖ የሚያምንበትን ዶግማ እና ቀኖና ለምእመናኑ ቀርፆ ፣የተፈቀደ እና የተከለከውን ይፋ አድርጎ፣ጥቅምና ጉዳቱን አሣውቆ፣ከሞት በኋላ ገነት እና ሲኦል እንዳለ አሥገንዝቦ ፣ለኃይማኖቱ ሥም ሰጥቶ ፣ቤተ እምነት ገንብቶ ኃይማኖቱን ማሥፋፋት የጀመረው።(የብሉይ ኪዳኑን ፣ነብዩ ሙሴን፣እና 10ቱን ትዕዛዛት ይጠቅሷል።)
ሰው ልጅ፣ ኃይማኖቱን ማሥፋፋት መብቱ ቢሆንም ፣ አንድ ግለሰብ በራሱ አእምሮ መጠንም ይሁን በሌላው አእምሮ ግፊት የአንድ ሀይማኖት ተከታይ የሚሆነው፣ ኃይማኖተኛ መሥሎ ለመታየት ከሆነ በቫይረሱ እንደተጠቃ ይወቀው።
በቫይረሱ ከተጠቃህ ኃይማኖተኛ ባትሆንም፣ ኃይማኖተኛ መምሰል ታበዛለህ። በተግባር ግን ህሊናህ በመጥፎ ነገሮች ተወሯል። ተግባርህም ሲፈተሽ ከአሥርቱ ትዕዛዛት ውሥጥ 0 (ዜሮ)ነጥብ የሚሰጥህ የመጥፎ ነገሮች ሁሉ ተገዢ ነህ።
የመጥፎ ነገሮች ውቅር በሆነው በዚህ ቫይረሥ የተያዙ፣ ብዙዎቹ ኃይማኖተ አለኝ ባይ ሰዎች በማሥመሰል የተካኑ እና የዋሆችን በአሥመሣይ ባህሪያቸው በማጥመድ ከፅድቅ መንገድ የሚያሥቷቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። “ጥቁሩን ቡና ካልተጋራው ፣ አምሳያዬ ያገለኛል።” ብሎ ፣የጀበና ቅራሪ የማያቀር እና ከዕድር ና ከባልትና ላለመውጣት ብሎ ብቻ ቤተ ክርሥቲያን እና መሥጊድ የሚመላለሥ ሁለቱም ህሊና ቢሶች ናቸው።ይህ ማለት ደግሞ በመጥፎ ቫይረሥ ህሊናቸው ተጠቅተዋል ማለት ነወ።
እነዚህ እና እነዚህን መሰል ሰዎች፣ በቀን ሰው አየኝ አላየኝ እያሉ ፣በሌሊት ደግሞ አለባበሳቸውን አሳምረው በማይታወቁበት ከተማ ና መንደር “አሥረሽ ምቺው”እያሉ የሚያነጉ ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹን በየቤታቸው ዓመላቸውን የሚያውቁ “ውሥጡን ለቄሥ” ይሏቸዋል።
ሰው ምሥጢራዊ ነው። በመሆኑም ውሥጡን ለቄሥ ለፓሥተሩ፣ለነብዩ፣ለኃይማኖት አባቱ ብቻ ፣ይናዘዛል።ለዚህ ነው ውሥጡን ለቄሥ የተባለው።
እምነት ያለው ሰው፣ለቄሥ ሲናዘዝ ብቻ ነው ኃጥያቱ የሚታወቀው።ያውም ለቄሱ ብቻ።እርግጥ ነው፣ ሁሉም እንደ ሃይማኖቱ የህሊናው ሙገት እንዲቀለው ለኃይማኖቱ መሪዎች ይናዘዛል። የኃይማኖቱ መሪዎቹም እንደ ሃጥያቱ ክብደትና ቅለት ፣ ሃጥያቱ እንዲሰረይለት ይፀልዩለታል።(በዚህ ባላምንም።ድርጊቱን ሆን ብሎም ሆኖ በሥህተት ሥለመፈፀሙ ከገዛ ህሊና ጋር ለተቆራኘው ፈጣሪ እንዴት መካድ ትችላለህ።አንተን ነፃ የሚያወጣህ በመጥፎው ቫይረሥ ህሊናህ ያለመወረሱ ብቻ እና ብቻ ነው ። እላለሁ።)
በዓለም ላይ ከሃያ ሺ በላይ ኃይማኖት አለ ይላሉ ሥራዬ ብለው በዓለም ያለውን ኃይማኖት ያጠኑ።…
ሃያ ሺ ሃይማኖት እኮ በጣም ብዙ ነው።ይሁን እንጂ ሁሉም የሚያጠነጥኑት ሃሳብ በሤጣንና ወይም በሰው ዓምላክ ወይም ፈጣሪ ላይ ነው ።(በእግዚአብሔ) በፅድቅና ኩነኔ ዙሪያ ነው።ከሞት በኋላ ዘላለማዊ ህይወት በተለያየ መንገድ መኖሩን ነው የሚሰብኩት ። የየኃይማኖቱ መሪዎች እና በተዋረድ ያሉ ኃይማኖቱን አሥፋፊዎች፣ ፣ዘላለማዊ ህይወት በእነርሱ ኃይማኖት አሥተምህሮ እና ህግጋት በኩል እንደሚገኝ አጥብው ይሰብካሉ።”የእኔ ኃይማኖት እውነት ና ወደመንግሥተ ሰማይ የሚያሥገባ ብቸኛ መንገድ ነው፣ ያለእኔ ኃይማኖት ፈፅሞ ወደመንግሥተ ሰማይ አትገቡም ይላሉ።
አንዳአንድ ኃይማኖቶች በሰባኪያኖቻቸው አማካኝነት ደግሞ ፣ለሰው፣የዕውቀት ማነስ፣ሱሰኝነት የጎላ ሚና አለው ፣ብሎ በመደምደም፣ሰው ከሁሉም ሱሶችና መጥፎ ልምዶች ነፃ ካልሆነ ከወንጀል ነፃ አይሆንም ብለው ይሰብካሉ።ይህ ግን ብዙን ጊዜ እውነት አይሆንም።
እነዚህ ሰባኪያን ፈጽሞ ያላወቁት ፣ዕውቀት ቢኖር እቺ ዓለም እራሷ እየኖረች ያለችው “ፍፁም የሰው አእምሮ ተመራምሮ በማይደርስበት ከተፈጥሮ ኃይል በላይ በሆነ ፈጣሪ መሆኑን ነው።ይህ ኃይልም በእርግጥ እንዳለ ፣ሞሞታቸው ከተረጋገጠ ና ከሞት ወደህይወት ከተመለሱ ሰዎች ምሥክርነት ተረጋግጧል።
ከሞት በኋላ በህይወት መኖር እንደሚቻል ፣”ሞተዋል። ነፍሰቸው ወጥታለች።እስትንፋሳቸው ተቋርጣለች።ልባቸው መምታቷ አክተሟል የተባሉ፣በኃኪሞች ተረጋግጦ ወደአሥከሬን ቤት ሲወሰዱ የነቁ፣በኩነቱ ኃኪሞችን ያሥደነገጡ መኖራቸውም እርግጥ ነው። እኔ ከሞት በኋላ ህይወት የለም ኃይማኖትም ከንቱ ነው አልላችሁም።
የራሴ የተለየ እምነት እና ኃይማኖት እንዳለኝ ይህም በሺ ከሚቆጠሩት ኃይማኖት እንደ አንዲ እንዲመዘግብልኝ እፈልጋለሁ።
እምነቴም፣ኃይማኖቴም ከሁሉም ሰው ቢለይ እናንተን አያገባችሁም ።የኃይማኖቴን ፍልሥፍና ግን መመርመር ትችላላችሁ።እኔ የጥቂቶቻችሁን ኃይማኖት መርምሬያለሁ ። ኃይማኖታችሁ ሰዎችን ቅነ፣በጎ እና ለባልጀራው ታማኝ እንዲሆን እና ፈጣሪውን አጥብቆ እንዲፈራ እና በተቀደሱት መፅሐፍ ህግጋት መሠረት እንዲጎዝ አጥብቆ ይመክራል። ብዙዎች ተመችቷቸው ከእናንተ ኃይማኖት ጋር በየፀሎት ቤቱ እዬዬ ሥላሉ እና እቤታቸው ቁጭ ብለው፣ ሥለተፀለየላቸው መንግሥተ ሰማይን ይወርሳሉ ትላላችሁ። የልደላቸውስ፣ምንዱባኖቹስ? “እዬዬም ሲዳላ ነው።”እንዲሉ በየጎዳነው ፣በየጢስ ናፋቂው ጎጆ ያሉ ፣ ሥለፈጣሪ የታወቀውን ወይም የተዳላላቸው ያወቁትን ያላወቀውስ?እንጦሮጦስ ለመግባቱ ምን ማረጋገጫ አላችሁ።”ቅዱሥ መፅሐፋ” እንኳን ፣ የናንተን ሥብከት የሚያወግዝበት አያሌ ምዕራፎች እያሉት ፣በዛ በእውነት ሃሳብ ለመሥበክ ብዙዎቻችሁ አትፈልጉም።ይልቁንስ እንዲህ ዓይነት ፅሑፍ ሥታዩ ና ሠታነቡ ፀሐፊውን የሉሲ ፈር ወይም የሣጥናኤል ደቀመዝሙር እንደሆነ እንዲታመን ከፍተኛ ቅሥቀሳ ታካሂዳላችሁ።አንዳንዶቻችሁ ህሊናችሁ መጥፎነትን ያነገሠ ሴጣን ሆኖ ሣለ ሌሎች መልካም ህሊና ያላቸውን ሰዎች እንደሴጣን እንዲታዩ ታደርጋላችሁ። ፣እኔ ግን እላችኋለሁ ፈጣሪ ለፈጠረው ይሁዳ እንኳን ያዝናል።
ታቃላችሁ ይሁዳ፣ ሳኦል( የፃፎችና ፈሪሳውያን አገልጋይ የነበረው ሣኦል እንዴት ድንቅ ሐዋርያ እንደሆነ እና ጳውሎስ እንደተባለ አሳምራችሁ ታውቃላችሁ።) ቀያፋ ፣ ፃፎች ና ፈሪሳውያን ባይኖሩ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሰረተ ቤተ እምነት እና የክርሥትና ኃይማኖት አይኖርም ነበር።እነዚህን ዋናዋና የቅዱሥ መፅሐፉን ትርክት አሳማሪ ፣የራሱ የፈጣሪ ፍጥረቶች ባይኖሩ ኖሮ ሐዲሥ ኪዳንም አይፃፍም ነበር።
እውነት እውነት እላችኋለሁ ፣ ከእኔ የባሰ ሐጥያተኛ የለም።ራሴን ፃድቅ አድርጌ እናንተን ለመኮነን ወደዚች ዓለም እናንተንም እኔንም የፈጠረ ፈጣሪ አላመጣኝም።ልክ እንደበርባን ማለት ነው። እናንተን የፈጠረ እኔንም ፈጥሮኛል።
ኃይማኖቴ ፣ ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ፣ከረቂቆ ነፍሥ ጋር የተጣበቀ ፈጣሪን ማምለክ ይባላል።ያ አንድ ፈጣሪ ምንጊዜም ከሰው ጋር የተቆራኘ ድር ያለው ነው።በፅንስ ውስጥ እንኳን ሆነን ከፈጣሪያችን ከዘላለማዊው ድር ጋር ተቆራኝተናል።
ከርሱ ጋር ያለን ድር በእንቅልፍ ሰዓትም ሆነ በሞት ሰዓት አይቋረጥም።በዓለም ሥንኖር መገንዘብ ያለብን ግን ፈጣሪ በህይወት ሥንኖሮ በጎና ክፍውን ማገናዘብያ አእምሮ እንደለገሰን እና ከትክክለኛው በተቃራኒ የቆሙት ሁሉ ለሰው ልጅ ያለመጥቀማቸው ነው።
የሰላም ተቃራኒው ጦርነት ነው።የበጎነት ተቃራኒው ክፋት ነው።የህይወት ተቃራኒ ሞት ነው።የእውነት ተቃራኒ ውሸት ነው።የጽድቅ ሥራ ተቃራኒ፣ የኃጢያት ሥራ ነው።የማዳን ተቃራኒ መግደል ነው።የማመሥገን ተቃራኒ መርገም ነው።የትህትና ተቃራኒ ትዕቢት ነው።የነፃነት ተቃራኒ ባርነት ነው።የምርቃት ተቃራኒ እርግማን ነው።የጨዋነት ተቃራኒ ብልግና ነው።የፍቅር ተቃራኒ ጥላቻ ነው።የመዋደድ ተቃራኒ መጠላት ነው።የመቀራረብ ተቃራኒ መራራቅ ነው።የንፁህ ተቃራኒ ቆሻሻ ነው።…ሰው ልጅ ህሊናውን በበጎ ሃሳቦች በመሙላት መጥፎ ሃሳቦች ህሊናው ውሥጥ ቦታ እንዳያገኙ እሥካላደረገ ድረስ በምድርም ሆነ ዘላለማዊ ሆኚ እኖርበታለሁ ባለው ሰማያዊ ሥፍራ በሰላም፣በደሥታና በፍቅር ሊኖር ከቶም አይችለውም።ምክንያቱም እዛም ህሊና የምትባለው ነፍስ አለችና ከእርሷ እንዴት መሸሽ ይችላል???