በላይነህ አባተ ([email protected])
አንድ አሜሪካዊ የሥራ ባልደረባዬ ተሁለት ሳምንታት በፊት አለወትሮው ቆጣ ብሎ ጸጉሩን እየነጨ ሲትከነከን አገኘሁት፡፡ “ምነው በመላጣህ ምክንያት የቁንጅና ውድድር ወደክ ወይስ የቀጠርካት ጉብል ቀረቺብህ!” ብዬ ልቀልድ ብሞክርም አለወትሮው ከንፈሮቹ አልሳሳ ጥርሶችም አልታይ አሉ፡፡ ሁለቴ ጠበቅ አድርጎ “እፍፉ…” ብሎ ታምቆ የቆዬ እስተንፋስ ከተነፈሰ በኋላ “ይህ ትራንፕ እሚባል ሰው ተቀናቃኙን ለማጥቃት ስልጣኑን መጠቀሙ ቅደመ አያቶቻችን የመሰረቱትን የአሜሪካ መሰረት የሚንድ ነው!” አለና ብሶቱን ደጋግሞ ገለጠ፡፡
አቶ ትራንፕ ተቀናቃኛቸውን በፖለቲካ ለማጥቃት የስልክ ንግግር ማድረጋቸው ይኸንን ጓደኛዬን እንደ ሽንኩርት ቁሊት ማትከንከኑ ገርሞኝ አይኔን አፍጥጬ ሳለሁ አንድ አገራችን እሰማው የነበረ ተረት ቁልጭ ብሎ ተፊቴ ተደቀነብኝ፡፡ “ማን? መቼ? የት? ” እያላችሁ ነፍሰ-ገዳይ ገዥዎቻችሁን ጠይቃችሁ በማታውቁት ጥያቄዎች እንደ ንፍፊት አትወጥሩኝ፡፡ ተረት ነው እማወራው ብያለሁ፡፡ አንድ ሰው መቶ ብር ይጠፋበታል፡፡ ይህ ያልታደለ ሰው በጠፋበት ገንዘብ ልቡ እንደ እባጭ ቆስሎና አንጀቱ እንደ ስንበር ተመትሮ ወገቡን በግራ እጁ ደግፎና በቀኝ እጁ የሚንዠቀዠቀውን እንባውን እየጠረገ እናቱ የሞተችበትን ያህል ያለቅሳል፡፡ “መቶ ብር ይኸንን ያህል ያስለቅሳል?” በሚል ከንፈራችሁን እንደ እማማ የሻረግ አሸራማችሁ አታሽሟጡ፡፡ በተረቱ ጊዜ የነበረው መቶ ብር የዛሬው ግማሽ ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ ሰው አንዴ ጎንበስ ሌላ ጊዜ ቀና እያለ፣ በእጁ አንዴ ወደ ፊት አየሩን እየገፋ፤ ሌላ ጊዜም ማጅራቱን ጠፍንጎ እየያዘ ሰፈር መንደሩ ድብልቅልቅ እስከሚል ድረስ “ኡኡኡ!” እያለ ወዮታውን ያቀልጠዋል፡፡
መቶ ብር የጠፋበት ሰው ኡኡታውን በሚለቅበት ሰዓት ተዚያው ሰፈር ሌላ ያልታደለ ሰው “ወይኔ ገንዘቤ! ወይኔ ንብረቴ፣ ወይ..ወይኔ!!” እያለ እንዲያውም ከመጀመሪያው ሰውዬ ይበልጥ እንደ ክረምት ዝናብ እንባውን እያዘነበ፣ ፊቱን እየነጨ አገሩን በለቅሶ ማናጋት ይጀምራል፡፡ ነጋዴ እሚበሳጨው እራሱ ስለከሰረ ሳይሆን ሌላው ስላተረፈ ነው ይባላል፡፡ ይህንን የተመለከተ መቶ ብር የጠፋበት ሰውየም “ለካስ ተእኔም የባሰ በዚች ምድር አለ!” ብሎ በመጽናናት ለቅሶውን ገታ አደረገና ወደዚህ ወደ ሁለተኛው ሰውዬ ጠጋ ብሎ “የኔ ወንድም እንዲያው ምን ያህል ገንዘብ ቢጠፋብህ ይሆን ይህንን ያህል ፊትህን የምትነጨው?” ብሎ የሚመልሰውን ለመስማት ጆሮውን እንደ ሙሰኛ ኪስ ቦርግዶ ይጠይቀዋል፡፡ ሁለተኛው ሰውየም አጽናኝ በማግኘቱ ልቡ ረጋ ብሎ ነገር ግን ሳግ እየተናነቀው “ እንደ ወርቅም… እንደ…አልማዝም የሚ..ያበራ የሰው እጅ ያልነካው ስሙኔ” ብሎ ይመልሳል፡፡ መቶ ብር ያጣው ሰውየም ቆጣ ብሎ “የኔ ወንድም እንካ ስሙኔህን! ለቅሶዬን አታበላሽብኝ!” ብሎ ሃያ አምስት ሳንቲሙን ለሁለተኛው አልቃሽ ሰጥቶ ዝም ካሰኘ በኋላ ትቶት የቆየውን ለቅሶውን እንደገና ማቅለጥ ጀመረ ይባላል፡፡
የሥራ ባልደረባዬ በአቶ ትራንፕ ይትከነከን የነበረው የሚሊዮኖችን ነፍስ በመደዳ እንደ ትንኝ ያጠፉ፤ እግር እንደ ግንድ የቆረጡ፤ ጥፍር እንደ ስንጥር የነቀሉና ቆዳ እንደ ሌጦ የገሸለጡ አረመኔዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በድሎት ስልጣን ተንፈላሰው በሚገኙበት ሰዓት ነው፡፡ የሥራ ባልደረባዬ በአቶ ትራንፕ ስልክ ጥሪ ይትከነከን የነበረው በእኛዋ አገር ተላይ በተገልጡት ወንጀሎች ተሳታፊና ተባባሪ የነበሩት ጭራቆች “ተሰማይ የወረዱ ሙሴዎች!” እየተባሉ በሚመለኩበትና በሚሸለሙበት ሰዓት ነው፡፡ የሥራ ባልደረባዬ ተራ ወንጀልም ባልተገኘባቸው የሕዝብ ተመራጭ ይትከነክን የነበረው የእርሱ አገር አስራ አምስት እጥፍ የእድሜ ታላቅ በሆነችዋ የእኛዋ አገር መንጋዎች በዘር ማጥፋት ወንጀል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፉትን የሂትለር ደቀመዛሙርት እንደገና እንደ ቅርቀብ ሊጫኑ ድብዳባቸውን ተጀርባቸው እያስቀመጡ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ መስማት ላልታከተው ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡፡
ስሙኔ የጠፋብህ የሥራ ባልደረባዬ ሆይ! ጩኸትህ የእኛን በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ ያጣነውን ጩኸት እያበላሸው ነው፡፡ እንካ ስሙኔህን! ልቅሷችንን አታበላሽብን!
ታህሳስ ሁለት ሺህ አስራ ሁለት ዓ.ም.