(ትናንት በተቀመጡበት ድፍት ብለው በደቂቃዎች ውስጥ (እንደሀኪሞቹ አባባል) በስትሮክ ሞቱ የተባሉትን የመሥሪያ ቤቴ ባልደረባ ነፍስ ይማር በዚህ አጋጣሚ፡፡) የሞተ ተገላገለ፡፡ የሞቱ በለጡን፡፡ “በዚያን ዘመን ሞትን ይመኟታል፤ ነገር ግን አያገኟትም” የሚለው ነባር መጽሐፍ ቅዱሣዊ(?) ቃል እውን ሆነ፡፡ ወግ ሆነና ሰው ሞተ ሲባል ይለቀሳል፡፡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የምገኝበት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይም ይህንኑ ማየቴ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ባህልና ወግ ነውና፡፡ ግን ደፋር ቀባሪ ጠፋ እንጂ ሁላችንም በቁም ሞተናል፡፡ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የሚል የዱሮ መጽሐፍ ነበር ልበል? አዎ፣ ትክክል ነው – እንደትንቢት ወሰድኩት፡፡
ዛሬ ጧት ከቤቴ ወጥቼ በአንድ ሚኒባስ ታክሲ ሦስት ኪሎ ሜትሮችን ያህል ወደ መሀል አዲስ አበባ አካባቢ መጣሁ – ወደ መሥሪያ ቤቴ ለመሄድ፡፡ ሚኒባሱ በህግ የተፈቀደለት የተሣፋሪ ብዛት ሹፌርና ረዳትን ሣይጨምር 11 ሰው ነው፡፡ እኛን የጫነን ሚኒባስ ግን ማንን ፈርቶ ከነሹፌሩና ረዳቱ 21 ነን – ልክ እንደዛሬዋ የእመብርሃን ዕለት – መስከረም 21 (ያደለው ግሸን ደብረ ከርቤ ሄዶ ይቺን ቀን ያከብራል እኔ እዚህ በንዴት እንጨረጨራለሁ)፡፡ ልብ በሉ – የመኪናው የመጫን አቅምና የተጫነው ሰው ብዛት በፍጹም አይመጣጠንም፡፡ ይህ ደግሞ አደጋን ከሚያበዙ አጋጣሚዎች ቀዳሚው ነው፡፡ ሀገራችን በመኪና አደጋ ምናልባት ከአንደኞች ተርታ ብትሠለፍ አንዱና ዋናው ምክንያት ይህ ከተሸከርካሪዎች አቅም በላይ የሚደረግ ጭነት ነው፡፡ ሌላው እንዲሁ እንደጠበል ጠዲቅ የሚረጭ መንጃ ፈቃድ ነው – በገንዘብ ወይም በሙስና፡፡ ሌላው ሀሽሽና ጫት እንዲሁም መጠጥ ነው፡፡ ሌላም ይኖራል፡፡ …
ወደ መ/ቤቴ ለመጓዝ ታክሲና ሃይገር ለማግኘት ዐይኖቼን ሳማትር የሠልፉ ነገር ወሽመጥ ይበጥሳል – ሰዓቱ ገና ከጧቱ 1፡15 ላይ መሆኑን ያዙልኝ፡፡ ወዲህ ብል ወዲያ ብል ምንም አማራጭ የለም፡፡ ስድስት ኪሎ ሜትሩን የመሥሪያ ቤቴን መንገድ በእግሬ አስነካው ገባ፡፡ ሄደት እያልኩ በመኪኖች በመጥለቅለቁ ሳቢያ እንደኤሊ የሚጎተተውን የመንገድ ላይ ተሸከርካሪ ቆም ብዬ ቃኘት አደርጋለሁ – ምናልባት አንዱ የሚያውቀኝ ቢያቆምልኝና ቢጠድቅብኝ፡፡ ተስፋ ያደረግሁት አልቀረም – አንዱ ወዳጄ ካለፈኝ በኋላ የኋሊት መጥቶ “አምቢቹ፣ ና ግባ!” አለኝና ገላገለኝ፡፡ የሀገራችንን አስጨናቁ ጉዳይ እያወራን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ ስታወራው ይቀንስልሃል፡፡
ግን ግን ወዴት እየሄድን ነው? በሀገራችን ሁኔታ እንደዛሬ ደንግጬ አላውቅም፡፡ የማየው ነገር ሁሉ በፍርሀት እያራደኝ ነው፡፡ መሄጃ ቢኖረኝ እንደወፍ በርሬ ከዚህች አገር በጠፋሁ – እስኪ የምትችሉ ጥደቁብኝ! ከላይ ታገኙታላችሁ፡፡ እውነቴን ነው፡፡
ለዳቦ ሠልፍ፣ ለህክምና ሠልፍ፣ ለትራንስፖርት ሠልፍ፣ ለግብርና ቀረጥ ክፍያ ሠልፍ፣ ለቅጣት ክፍያ ሠልፍ፣ ለቀበሌ ሉካንዳ ቤት ሠልፍ፣ መኪና ስታሽከረከር ሠልፍ፤ ልትጠበል ሠልፍ፣ ለጥንቆላ ቤት ወረፋ፣ ለሙስና ክፍያ ወረፋ፣ ለምግብ ወረፋ፣ ለፓስፖርት ወረፋ፣ ለቦሎ ሠልፍ፣ ለመጠጥ ሠልፍ፣… ሠልፍ… ሠልፍ…. ሠልፍ…፡፡ ሠልፉ ደግሞ ዙሪያ ጥምጥም ነው፡፡ የመስቀል ለት ሥጋ ልገዛ ወደ ቀበሌ ብሄድ ሠልፉ የመስቀል አደባባዩን የዚያን ሰሞን የእሬቻ ሩጫ ሊያክል ምንም አልቀረውም፡፡ (እናንተዬ ምሥጢሩን ሰማሁ – ለካንስ 50 ሽህ ሯጭ እንደተሣተፈ የተነገረው ውሸት ነው፤ 5 ሺም አይሞላም አሉ፤ በዚህ ዓይነት ምርጫውን እንዴት ልናምን ነው?(ይላሉ ሰዎች)) ይህ የሚያመለክተው አንድም የሸቀጥና የአገልግሎት ሰጪው ወይም አቅራቢውና የተጠቃሚው ብዛት አለመመጣጠኑን ነው፡፡ አንድም የሕዝቡ ብዛት ከቁጥጥር ውጭ መውጣቱን ነው፡፡ አሳሳቢና አስጨናቂ ዘመን፡፡
ከምር ወዴት እየሄድን ነው?
አዲስ አበባ ውስጥ አሥርና ሃያ ደቂቃ የማይፈጅ መንገድ ሰዓታትን ይወስድብሃል፡፡ ይህ ብቻውን የጎንዮሽ ጉዳቱ ቢተነተን በጣም ብዙ ነው፡፡ የነዳጅ ፍጆታን ይጨምራል – በዚያም ምክንያት ገንዘብን አላግባብ ማባከንን ያስከትላል፡፡ ጊዜን ይጨረግዳል- በዚያም ሰበብ ቀጠሮን ማጓተትና የሥራ ሰዓትን ማቃጠልን፣ ከሥራ ኃላፊዎች ጋርም መጋጨትንና ሥራን ሁሉ ማጣትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሀገር ሀብትን ያሟጥጣል – ነዳጅ ለማስመጣት ብዙ ዶላር እንደማስፈለጉ ለሌላ ጉዳይ ይውል የነበረን የውጭ ምንዛሬ ለነዳጅ በማዋል ያባክናል፡፡ የመለዋወጫ ፍጆታን ስለሚጨምር ይህም ጉዳቱ ትልቅ ነው፤ በዚያ ላይ ለፍጥነት መቀነሻ ተብሎ በየመንገዱ አለዕውቀት የተጎበረው ግንዲላ ግንዲላ እሚያካክል የአስፋልትና የስሚንቶ ንጣፍ መኪኖችን ከጥቅም ውጭ እያደረጋቸው ነው፡፡ ሀገርን በጥበብ ማስተዳደር ዕርምና እንደወንጀልም የሚቆጠር ሳይሆን አይቀርም፡፡ የመንገድ መጨናነቁ በዚህ ብቻ አያቆምም፡፡ ወደ ጭንቅላት ይወጣና ትግስትንም ይፈታተናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼስ እነዚህ የ “Q” ዘሮች መላም የላቸው፡፡ ከዚህ አንጻር AQ, BQ, IQ, SQ, CQ,… ፍዳቸውን እየበሉ ከዜሮ ጋር ወደ መደመር ተቃርበዋል፡፡ EQ (Emotional Quotient)ም በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት አሣሩን እየበላ ነው፡፡ አዳሜ ከፊቱ የተገተረው መኪና ምን ገጥሞት እንደተገተረ ባለማስተዋል የመኪናውን ጥሩምባ ዕረፍት እየነሣ አካባቢን ከማደንቆሩም በተጨማሪ በቡጢ የመኪናውን መሪ እየደለቀ ንብረቱ ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ያደርሳል፡፡
ምን አለፋህ – አዲስ አበባ ትርምስምሷ ወጥቷል፡፡ በረንዳ አዳሪውን፣ ለማኙን፣ ሥራ አጡን፣ ሥራ ፈቱን፣ ጠጪና ሰካራሙን፣ ዘሟቹን፣ ሴተኛ አዳሪዋን፣ ወንደኛ አዳሪውን፣ ቀማኛውን፣ ቦዘኔውን፣ ደላላውን፣ የማርካቶና ፒያሣ እንዲሁም አራት ኪሎና መገናኛ አካባቢ ወከባን፣ የሃይማኖት መላላትና ከናካቴው መጥፋትን፣ የሰዎችን አስመሳይ ባሕርይ፣ የሞራልና የባህል ክሮችን መበጣጠስ፣ በሀገራችን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቀውን ራስ ወዳድነት፣ በንግዱና ኢኮኖሚው የሚፈጸመውን ማጭበርበር፣ የብሔራዊ ስሜት መጥፋትን፣ በጥቅሉ የዜጎችን ስሜት አልባነትና ብዙዎች የሚመሩትን ሜካኒካዊ የሮቦት-መሰል ሕይወት ስትመለከት ጭንቅላትህ ሊፈነዳ ይደርሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር አንጎልህን ከሥራ ውጪ ማድረግ ይኖርብሃል፡፡ ከቻልክ ማበድ፡፡
ባይገርምህ በሀገራችን ውስጥ – በአሁኑ ዘመን – ሥራ ያለው የጎዳና ተዳዳሪ ቤተሰብ እኮ በብዛት ታገኛለህ፡፡ በየትኛው ደመወዙ ቤት ይከራይ? የአንድ ሽህና ከዚያም በታች ደሞዝተኛ እንዳለ ታውቃለህ? የቤት ኪራይ ከ2000 ብር በታችስ እንደማይገኝ ታውቅ ይሆን?(በተለይ በመሀል ከተማ?)፡፡ አንቺም አስቢው – ከአንድ ሽህና ሁለት ሽህ ብር ደሞዝ ምኑ ከምን ሆኖ ለቤት ኪራይ ይከፈል? ለምግብም እኮ አይበቃውም፤ ለትራንስፖርትም እኮ አይበቃውም፤ ለህክምናም እኮ ያስፈልገው ነበር፤ ለልብስና ለልጅ ምግብ፣ የትምህርት ቤት ክፍያና የደምብ ልብስም እኮ ይጠበቅበታል፤ ለመንቀሳቀሻ እኮ ያስፈልገዋል፤ ለተቀማጭማ አይታሰብም፤ እንዴት ይኑር ይህ ሰው? ራሱን ያጥፋ? መተሳሰብንና መተዛዘንን ከሀገራችን ምድር ሙልጭ አድርጎ ያስወጣቸው ማን ይሆን?
ይህች ሀገር ታዲያ በኪነ ጥበቡ አይደለም እየኖረች ያለችው? መንግሥት የት ነው ያለው? ፈጣሪንስ ማን አገተው? በርግጥም ወዴት እየሄድን ነው? እኛን ከተመቸን – በቃ – ሀገር እንደፍጥርጥሯ ትሁን? ቅንጡዎቹና ስለሀገር ችግር አይሞቄ-አይበርዴዎቹ እነበቀለና እነጃዋር ታዲያ ይህንን ችግር ለማስወገድ ነው መሯሯጥ የሚገባቸው ወይንስ ለማባባስ ነው መራወጥ ያለባቸው? የዚህችን አገር ሕዝብ እንኳንስ በጎሣና በሃይማኖት አለያይተን በሁሉም ነገር አንድ አድርገንም ወደ ትክክለኛው የሰውነትና የዕድገት ፈር ማስገባት በቻልን፡፡ እንኳንስ ተጣልተንና ተመነቃቅረን ተፈቃቅረንም በሆነልን፡፡ እዚያና እዚህ ፎቅና የሚያማምሩ ሴቶችን ማነው ቤቶችንና የአስፋልት መንገዶችን ስላየህ ብቻ ኢትዮጵያ አለች አትበል፡፡ ከሌለን ቆየን ወንድማለም፡፡
ለዚህ ሁሉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ያደረሰን ሕወሓት ግን እግዜር ይይለት፡፡
ለማንኛውም አስተያየት [email protected]