አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)
ከተማ ይፍሩ የተባሉ የደርግ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር(?) ለሥራ ጉብኝት ወደ ውጭ ሄደው በዚያው ቀሩ አሉ፡፡ ለምን እንደቀሩ ሲጠየቁ በርዕሴ የጠቆምኩትን የእንግሊዝኛ ዐረፍተ ነገር እንደተናገሩ ይወሳላቸዋል – “አጋጣሚ ባገኘህ ጊዜ (ሁሉ) ከኢትዮጵያ አጥብቀህ ሽሽ!” ተብሎ ቢተረጎም ያስኬዳል- ህልምና እንግሊዝኛ ደግሞ እንደፈቺው ነው አሉ፡፡
ሀገራችን ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለይ ለይቶላት ባለቤት አልባ ሆናለች፡፡ አሁን ያለው የዶ/ር አቢይ መንግሥትም ምን እያደረገ እንደሆነ እንኳንስ ሌላው ራሱ አቢይም የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ሀገሪቱ መሽቶ ይነጋላታል እንጂ ያለመሪና ምናልባትም ያለ ሕዝብ በደመነፍስ እየተውገረገረች ነው – አለች ለመባል ያህል፡፡
ይህን የሚያስብሉ ጥቂት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
- የኑሮ ውድነት – ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ኑሮ ከመንኮራኩር በሚልቅ ፍጥነት ወደ ሰማየ ሰማያት ሲመጥቅ “ይህ ሕዝብ የኔ ሕዝብ ነው፤ በኑሮ ውድነት ሲጠበስ፣ ከገቢው ጋር በማይመጣጠን ሁኔታ የኑሮ ውድነት በእሳት አለንጋ ሲገርፈው እኔን በዋናነት ይመለከተኛልና ገበያውን ላረጋጋ፤ ንግዱን ልቆጣጠር፤ የንግዱን ማኅበረሰብም ንቃተ ኅሊናውን አሳድጌ ተመጣጣኝ ትርፍ እንዲያገኝ ላስችል፤ ኢኮኖሚውና ሕዝብ እንዲገናኙ ላድርግ….” የሚል መንግሥትም ሆነ የመንግሥት አካል አልተገኘም፡፡ ሁሉም ሩጫው የራሱን ኑሮ ለማመቻቸት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ሕዝቡም ሆነ ሀገሪቷ የኔ ናቸው የሚላቸው አካል አለመኖሩን ነው፡፡ የመኪና ባትሪ በ10 ዓመታት ውስጥ ከብር 300 አሁን ወደ ብር አምስት ሽህ ሲገባ፤ አንድ ዕንቁላል ከስሙኒ ወደ 6 ብር ሲገባ፤ ኩንታል ነጭ ጤፍ ከብር 1000 ገደማ ወደ ብር 4000 ሲጠጋ፣አንድ ሊትር ዘይት ከብር 12 ወደ ብር 90 ሲሽቀነጠር፣ የ20 ብር የቀን ሠራተኛ (ወዛደር) ወደ ብር 400 እና ከዚያ በላይ ሲመነደግ፣ የቤት ሠራተኛ ከ50 እና 60 ብር ወደ ብር 2500 ሲያሻቅብ፣ ለትንንሽ የመኪናም ሆነ የቤት ጥገናዎች ይወጣ የነበረው ብር 300 እና 500 አሁን ከአሥር ዕጥፍ በላይ አድጎ ብር 3000 እና 5000 ሲገባ (በጣም ትንሽ ጥገና ነው! ሞተር ላውርድ ካልክ የዛሬ 10 ዓመት መኪናውን የገዛህበትን ዋጋ የሚያስከነዳ ዋጋ ትጠየቃለህ፤ የቀን ጅብ ሆኗል እያንዳንዱ ባለሙያና የንግድ ድርጅት፡፡ አቢይ ሲያቀብጠው “የቀን ጅብ” አለ ያኔ፡፡ እነዚያኞች መቀሌ ሲመሽጉ ሌሎች የቀን ጅቦች በየቀኑ እዚሁ ይፈለፈሉ ገቡ)….. ይህ ሁሉ ምስቅልቅል በሀገር ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ሲከሰት ታዲያ የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ ባዩ የአቢይ መንግሥት እየታዘበ ቁጭ ከማለት ወይም ምናልባትም ለተለዬ ውስጣዊ ተልእኮ ሲባል ለኑሮው መመሰቃቀል የበኩሉን አስተዋፅዖ ከማድረግ ውጪ ሊያደርግ የሞከረው አንድም ነገር የለም፡፡ “የኔ ነው” የምንለው መንግሥት እንደማጣት ያለ ቁጭት የሚለቅ ነገር ደግሞ የለም፡፡ እኔ ቤተሰቤ ሲራብና ሲጠማ የማይሰማኝ ከሆነ ደደብና ደንቆሮ ነኝ ማለት ነው፡፡ ኃላፊነቱን የማያውቅ ወላጅና መንግሥት አንድ ናቸው፡፡ ስለሆነም ነው የአቢይ መንግሥት የኔ መንግሥት የማይመስለኝ፡፡ ደንቆሮና ዕውር መንግሥት ካላቸው ሀገሮች ቀዳሚዋና ምናልባትም ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት – “አክሰሱ” ያላችሁ አንድ ዜጋው እንዲህ ማለቴን ንገሩት፡፡ ይሄ ነገር በጣም ይገርመኛል፡፡ በርሀብና በርዛት፣ በበሽታና በቄሮ ማለትም በህግ-አልባዎች የዝርፊያና ግድያ ቡድን አንቀጥቅጦ መግዛት ወንጀል ነው፡፡ ኋላ ማጣፊያው እንደሚያጥረው ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም አሁን ሀገርና ሕዝብ ክፉኛ እየተሰቃዩ መሆናቸውን በመገንዘብ መፍትሔ መሻት ጊዜ የማይሰጠው ነው፡፡
- ሥርዓት አልበኝነት – አሁን ይህችን ማስታወሻ እየጸፍኩ እንኳን በመስኮት መንገዱን ስመለከት መሀል አዲስ አበባ ላይ ወጣቶች መንገዱን ዘግተው በኦሮምኛ ቋንቋ እየዘፈኑና እየጮኹ ነው፡፡ መጮኻቸውን አልቃወምም፤ መብትም የለኝም፡፡ ግን መንገድ እየዘጉና የትራፊክ እንቅስቀሴን እያወኩ በሥራ ሰዓት እንዲህ መሆን አግባብ አይደለም፡፡ ይሄ “ጊዜው የኛ ነው!” የሚሉት ዘመን አመጣሽ ፈሊጥ ሀገራችንን የለየላት ሦርያና ሶማሊያ ሳያደርጋት በሀገራችን ህጋዊና ብሔራዊ ስሜት የሚሰማው ሕዝባዊ መንግሥት መቆም ይኖርበታል፡፡ በየክልሉ ሄደን ብናይ መንግሥት ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም ባፈተተው ይጓዛል፡፡ የማኅበረሰቡ ሕይወት በጎረምሦችና በወጠጤዎች የምሕረት እጅ ውስጥ ነው፡፡ አዲስ አበባም እንደዚሁ ናት፡፡ በህጋዊ መንገድ ጉዳይን ማስፈጸም ታሪክ ሆኗል፡፡ ጉቦና ሙስና ጫፍ ወጥተዋል፡፡ በሰላም ከቤት ወጥቶ በሰላም መመለስም ብዙዎች የሚናፍቁት እየሆነ ነው፡፡ በጠራራ ፀሐይ በሚደረግ ዝርፊያና ንጥቂያ የብዙ ሰው ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡ ለሀገርና ለወገን ማሰብ ዕርም በመሆኑ ሥራንና የሥራ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ቀርቷል፡፡ ሙስና የደም ሥር ከሆነ ሰነበተ፡፡ ምናልባት ሰዎች በእውነተኛ ገቢያቸው መኖር አለመቻላቸው ለዚህ ዓይነቱ ህገ ወጥ ድርጊት ዳርጓቸው ሊሆን ይችላል፡፡ መንግሥት ቢኖር ይህን ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት ከኑሮው ጋር የሚመጣጠን ደሞዝ እንዲከፈል ህግ ያወጣ፣ አዲስ የደሞዝ አስኬልም ይቀርጽ ነበር፡፡ አሁን ግን ሀገራችን ባለቤት ስለሌላት እንዲያውም ይባስ ብለው ካለችንም ትንሽዬ ገቢ እንዴት እንደሚዘርፉ አዳዲስ ሥልቶችን ያውጠነጥናሉ እንጂ ለኛ ኑሮ ግዴላቸውም፤ ባልተወለደ አንጀት ይገርፉን ይዘዋል፡፡ በዚህ ረገድ ነጋዴው በዓመት በሚሊዮኖች ለሚያስገባበት ንግድ በሙስና ትስስር ጥቂት ሽዎችን እንዲከፍል ሲደረግ የኔ ዓይነቱ ምሥኪን ደሞዝተኛ ላይ ቫትን ጨምሮ ከ50 በመቶ በላይ ከደሞዛችን ይቆረጣል፡፡ ጊዜው ሲደርስ የምናወራው የገቢዎች ሚኒስቴር በተለይ በሠራተኛው ላይ የሚፈጽመው ግፍና በደል እጅግ ብዙ ነው፡፡ ገና ለገና የመንግሥትን ገቢ አሳደግን ብለው የቅጥር ሠራተኞችን ደሞዝ ከየትኛውም የዓለም ሀገር በማይወዳደር የቀረጥ ዓይነትና የአቀራረጥ ሁኔታ እየመዘበሩንና ኑሯችንን መቅኖ እያሳጡት ይገኛሉ፡፡ ለነገሩ ቀረጥና ግብሩ እነሱን ስለማይነካ ምን ያድርጉ፡፡ እነሱ እኮ ደሞዝ የሚከፈላቸው ለስሙ እንጂ የኑሯቸው መሠረት ሌላው ቀርቶ አንዱ ነጋዴ ብቻም ሊሆን ይችላል፡፡
- የባለሥልጣናት ድንቁርና – ልብ አድርጉ፤ አጎቴና አክስቴ በባዶ እግራቸው የመሬት እሾህና የዛፍ ላይ ቆንጥር እያሰቃያቸው ተርበውና ታርዘው በሚከፍሉት ግብር በስምንትና አሥር ሚሊዮን ብር ቪ-8 መኪና መንግሥት ይገዛና ለየባለሥልጣናቱ ያድላል፡፡ እነሱም በነዳጁ፣ በአበሉ፣ በምኑም በምናምኑም የዚህን ምሥኪን ሕዝብ ገንዘብ ያሟጥጡታል፡፡ ለሕዝቡ ግን አንድም ነገር አይሠሩለትም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ውኃ የለውም፤ መንገድ የለውም፤ ትምህርት ቤት የለውም፤ ህክምና የለውም – (“ነቲንግ!” አለ ያ መንጌ በአንድ ንግግሩ – በጣም ተናዶ )፡፡ ገበሬው ከዛሬ 100 ዓመት በፊት የነበረውን ሕይወት እየመራ ባለሥልጣናቱ ግን የ21ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓዊ ሕይወት ይቀጫሉ – ቀንቼ እንዳይመስላችሁ – ነገረ ሥራቸው ስለሚያናድድ እንጂ፡፡ በዚህም ቅንጣት አይሰማቸውም፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ድንቁርና ጆሯቸውንም ልቦናቸውንም የፊጥኝ አስሮታልና፡፡ ትንሽ መልካም ሥራ ቢሠሩ እንኳን እሰዬው ነበር፡፡ ግን አንዳችም የለም፡፡ ቢሯቸው እንኳን የሚገኙት ከስንት አንድ ናቸው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሚባክነውን ገንዘብና ሀብት ስታዩ፣ ላልተሠራ ፕሮጀክት ሳይቀር ብዙ ሚሊዮን በብድርና በምጽዋት የተገኘ ገንዘብ በሀሰት ሠነድ እየተወራረደ የሚጠፋውን የገንዘብ መጠን ስትሰሙ እንደ ኢትዮጵያዊ ከማሣፈሩም በተጨማሪ እንደ አንድ ጤናማ ዜጋ ያሳብዳችኋል፡፡ ይህን ኢትዮጵዊነት ምን እናድርገው ይሆን?
- የመንጋ ፍርድ – በየአካባቢው የሚታዬው የመንጋ ፍርድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንዲትም ደቂቃ ቢሆን እንድትኖር አያደርግህም፡፡ መውጫ ቀዳዳ ቢኖር ብዙ ዜጎች በአንድ ጀምበር ከኢትዮጵያ ውልቅ ብለው በተገላገሉ ነበር፡፡ በየትም ሥፍራ ብትሄድ እንደ ዘመነ ክርስቶስ “ስቅሎ፣ስቅሎ” ነው መመሪያው፡፡ ሰውን ዘቅዝቆ መስቀል፣ ሰውን ገድሎ ሬሣን ዘመድ እንዳይወስድ በመከልከል የግፍ ግፍ በጀብ ማስበላት፣ አባትን ከቤት ጠርቶ በልጆች ፊት መሀል አናትን በጥይት መፈጥፈጥ፣ ልጅን ገድሎ በሬሣው ላይ እናትን ማስጨፈር፣ ተደራጅቶ ገንዘብና ንብረት በመቀማትና በመዝረፍ የራስን ኑሮ ማበልጸግ፣ ጭቁን ዜጋ በላቡ የሠራውን ኮንዶምንየም ቀምቶ ለራስ ጎሣ ማደል፣ ከአንዱ አካባቢ ወደሌላው አካባቢ እህልና ጥራጥሬ እንዳይገባ ማገድ፣ “ይህ የኛ ቦታና መሬት ነው” በሚል ነባር ባለይዞታን ከኑሮውና ከይዞታው ማፈናቀል፤ በዘር ተሰባስቦ ከተሞችን መውረር፣ ወዘተ. የሀገራችን ዘመናዊ ባህል ከሆኑ ሰነበቱ፡፡ ይህም የመንግሥትን ደካማነት ወይም ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት የወንጀል ተባባሪነት ከማሳየት ባለፈ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ይህችን የመሰለች ሀገር እየመራሁ ነው ማለትም በእጅጉ ያሣፍራል፡፡ እኔ አቢን ብሆን በሚደረግልኝ የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል እሸማቀቅና ደብቁኝ እል ነበር፡፡ የዚህች ሀገር መሪ መሆን በምንም መንገድ ሊያኮራ አይችልም፤ አይገባምም፡፡ ኢትዮጵያ ያለች የምትመስለው አርትስ ቲቪን በመሳሰሉ አንዳንድ ገራገርና ጥሩ የሚመኙ ሚዲያዎች ውስጥ ብቻ እንጂ በእውን ኢትዮጵያ በቀደመው ይዘቷ አለች ማለት በፍጹም አንችልም፡፡ ልቀጥል ? ጊዜ የላችሁም መሰለኝ … መልስ ለመስጠት ተጓደዳችሁብኝ፤ ስለዚህ ይቅርብኝ፡፡ … ግን ሀገራችን እንዳለች የማትቆጠር መሆኗን ያዙልኝ፡፡