“ዋርካ ምድር ነካ ንገሩት ለዋንዛ
ፍቅር ለባለጌ ይመሥለዋል ዋዛ። “
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
ዋርካ ትሑት ነወ። የፍቅር አሥተማሪ ነው። ዝቅ በማለት ለምድር ያለውን አክብሮት ገለፀ።እንዲህ በማለት ፥
” ምድር ሆይ! ሥለሰጠሺኝ ማዕድን ፣ ሥለአጠጣሺኝ ውሃ በእጅጉ አመሰግናለሁ።እኔ ያለአንቺ ፍቅር ና እንክብካቤ ምንም ነኝ። ሳትሰስቺ ሥለሰጠሺኝ ፍቅር ይኸው ዝቅ ብዬ አመሰግንሻለሁ።” አለ።ከልቡ።
” ዋንዛ ” ግን ትዕቢተኛ ነው።ከቶም ምንም ምስጋና አላቀረበም።”አንቺን ማየት ደብሮኛል።”በማለት ሰማዩን ማየት ተያያዘው።
ዋንዛ ቦጥራራነቱን ያኔ አሳወቀ። ጉረኛና አይሩቤ መሆኑንም በተግባሩ አረጋገጠ። ።በጨው ደንደስ በርበሬ እንደሚወደስ የማያቅ መሆኑ ታወቀ። ዋንዛ ከነቱ ና የከንቱ ከንቱ ነው ፣ የተባለው የዛን ጊዜ ነው።ነፋሥንም የሚከተል በዋል ፈሰስነቱም ተረጋገጠ። በህዝበ ጫካ ውሥጥ ለብቻው የተኳፈሰ ና በግብዝነት የሚመፃደቅ ሞኝ መሆኑንም በተግባሩ መሠከረ። ። ፈረስ የበሬን ውለታ ( ቀድሞ በመገኘት ብቻ) በጮሌነት ሲቀማ እንደኖረ ሁሉ ዋንዛም እንደዛው ነው።
ፈረስ ፣ከሰው ፊት ለፊት በመገኘቱ በአሸንክታብ በመሽቀርቀሩ በግብዝነት የሚመፃደቅ ነው። ያሥጌጦትን ፣ያሥዎቧትን እነዛን ጥበበኞች የሚረሳ ብቻ ሣይሆን እንደቆሻሻ የሚቆጥር ነው።የዋንዛም ባህሪ ተመሣሣይ ነው።እጅግ ሲበዛ ግብዝ ነው።
እውነት፣እውነት እላችኋለሁ ፣በህዝብ ጫካ ውስጥ ያለ ዋንዛ የባቢሎን ግንበኞች ተምሳሌት ነው።የግብዝነቱን ጠርዝ መርገጥ የምናሥተውለው፣ የተሰጠው ህይወት ከምድር መሆኑን ዘንግቶ ወደሰማይ ሲንጠራራ ነው።…
የእኛ ሀገር የሰው ጫካ በዋርካ ና በዋንዛ ብቻ የተሞላ አይደለም። በተፈጥሮ ጫካ ውሥጥ ሀገር በቀል ና ከውጪ ሀገር አምጥተን የተከልናቸው ዛፎች አሉ ። (ለምን እነ ወይራ እነ ባህር ዛፍን ከሀገራችን ሂዱልን እንዳላሏቸው ባይገባኝም።) በእርግጥ የቢርቢራ፣የወይራ፣የዝግባ፣የኮሶ፣ ወዘተ ዛፎችን የሚመሥሉ ሰዎችም ፣በሰው ጫካ ውስጥ አሉ። (ህዝብ በበዛባቸው የሀገራችን ከተማዎች።)ሥለነዚህ እና ሥለመሳሰሉት በሰው ጫካ ውሥጥ ሥለሚኖሩ፣የሰው ዛፎች መፈላሰፉን ለአንባብያን ትቻለሁ።
(በበኩሌ ሁላችንም ሰው እንጂ ፣ ብሔር፣ቋንቋ፣ወዘተ ያለመሆናችንን እና ሁሉም ሰው ወንድሜ ና እህቴ እንደሆነ የማምን እና ዛሬ የምንሰማቸው ዝባዝንኪዎች ሰዎች የፈጠሯቸው ግላዊ ፍረጃዎች ናቸው ።ባይ ነኝ።.)
እንደ ዋርካ ና ዝግባ የሚቆጠሩ የዚች ወርቅ ሀገር ሰዎች በይበልጥ በከተማ የሰው ጫካ ውሥጥ ወይም ደን ውሥጥ ትላንት የነበሩ ፣ ዛሬም ያሉ፣በማህበራዊው፣ኢኮኖሚያዊው ፣በፖለቲካው መሥክ አንቱ የተባሉ ፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ… ረዳት በማጣትም ጭምር ፤ በዓለም ፖለቲካ አሠገዳጅነትም ይሁን ፣ደግ መካሪ በማጣት ፣ሀገርን ሲያሉሙ ና ሲያጠፉ ነበሩ።ዛሬም እያለሙ ና እያጠፉ ናቸው። …..
ከነዚህ በተቃራኒ የቆመ፣ ዋንዛ መሣይ ሰው ደግሞ አለላችሁ።ትምህርት በቅጡ ሣይማር ፣ በገንዘብ ኃይል ዲግሪውን ይዞ ፣ልክ እንዳወቀ ሰው፣የራሱ የሆኑ ዘባዝንኪሃሳብ ሳይኖረው፣የዝግባ ና የዋርካን ሃሣብ እየጦለበ የራሱ ሃሳብ እንደሆነ ፣ የሚያናፍስ።
ተምሬለሁ፣አውቄለሁ፣ምሁር ነኝ የሚል። ነገር ግን ፣ሰውነቱን ረስቶ፣ራቁቱን መሆኑን ዘንግቶ፣ ሥለመማሩ ፣ሥለማወቁ ፣ ሥለምሁርነቱ፣ ከሱ ሌላ መሥካሪ ሣይኖረው ” ቂጡን ገልቦ ተከናንቤያለሁ” ባይ። ፣ ያ ሰው በዋንዛ እመሥለዋለሁ።አብራራለሁ።
በእኔ እምነት ትምህርት ዕውቀት በመሆኑ ከሌሎች ያወቅነውን በትክክል የምንተገብር ከሆነ ያንን የተማርነውን አውቀናል ማለት ነው። የተማርነውን ፈፅሞ የማናቅ ዲፕሎማ፣ዲግሪ ና ማሥትሬት በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች ያለን ወይም የተሰጠን በዚች ሀገር፣ እንደአፈር ነን። ትርፋችን ግን የምርቃት ፎቷችን ቤታችንን ማድመቂያ ና ሥንሞት ማሥለቀሻ ና ነፍሳችን በሰላም እንዳታርፍ ማድረጊያ ነው። ከዚህ በዘለለ ምንም ፋይዳ አይኖረውም።
አንድ መምህር የሆነ ሰው ያወቀውን ፣ለማሳወቅ የበኩልን ሲጥር ፣ከንቱ የመንጠራራት አባዜ ያለበት የማይሰማው ና ፍላጎቱ ና የልቡ ሃሳብ እውቀትን ለመሸመት ሳይሆን ፣ የውሸት ካባ ለብሶ በከንቱነት ለመመፃደቅ ከሆነ ፣ ያ ሰው በሰው ጫካ ውስጥ የሚኖር ግብዝ ዋንዛ ነው። …
ግብዝ ዋንዛዎች፣ በማሥመሰል፣ በብልጣ ብልጥነት ፣ በተንኳል፣በአይን አውጣነትና በፈጣጣነት የተካኑ ናቸው።የእነሱ ዓላማ መሰላል የሆነውን የሰው ጫካ ረጋግጠው ሰማይ መንካት ነው። የዘወትር ፍላጎታቸው፦
” ዳቦ ልገዛልህ ነውና ተረግጬህ ወደ ዳቦ ቤት ልሂድ፣ፍቀድልኝ” በማለት በትህትና አሥፈቅዶህ ሲያበቃ ፣ ባንተ ጫንቃ ላይ ተረማምዶ ፣እላይ ከተሰቀለ ፣ በኋላ “ዳቦዬሥ???”ብትለው፣ ” አራት እግርህን ብላ።” ነው የሚልህ። ወዳጄ ያአንተን ድርሻ ሸጦ እርሱ ኬክ መብላት ሥለጀመረ አይሰማህም።
እሱ ና መሰሏቹ ፣እዛ ላይ ተሰቅለው፣ዘወትር ሥለአንተ ድህነት እያወሩ ፣የአንተ ድርሻ ያለበትን የሀገር ቤት ያለአንዳች ሀፍረት ዘወትር ይበላሉ።
ዋዛዎቹ ያልተገነዘቡት ቢዘገይም፣ ተሸክሞ የሰቀላቸው ከንቱነታቸውን ሲረዳ ፣ በወጉ እንኳን ካሉበት ከፍታ፣እንዳይሰበሩ ተጠንቅቆ እንደማያወርዳቸው ነው።እየረገጡት በጫቃው ላይ ተረማምደው ፣እንደወጡት ፣እየረገጡት ከቶም አይወርዱም። … (የፕሮ መስፍንን ወ/ማርያምን “መሠላል” የተሰኘውን ግጥም ያነቧል።)
በማጭበርበር እና በሽውዳ፣ ሰዎችን በመሸንገል ና ኃቀኛ ፣የላቀ ዕውቀት ፣የሚገርም የተለየ ገንቢ አተያይ እና ፈጠራ ፣ ያላቸውን በማንኳሰስ፣ብሎም በሐሰት ወሬ ሥም በማጥፋት ፣ በምላሥ ጉልበት ዓዋቂ በመባል፣ ዛሬ፣ዛሬ በየፈርጁ የተመቻቸ ኑሮ ኗዋሪው በዝቷል።በየደረጃው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ና በመንግሥት መሥራቤቶች ና በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውሥጥ ሳይቀር “ዋንዛዎች” በዝተዋል።…
በግብዝነት ራሱን አንጠራሪ ፣ ግብዙ ዋንዛ ፣ አቋራጭ መንገድ ፈላጊ ፣ ከትላንት እስከዛሬ የዚች ሀገር ችግር ፈጣሪ እንደሆነ ታሪክን ዋቢ አድርገን መመሥከር እንችላለን።
ታሪክ ፣እንደሚመሰክረው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደህዝብ ፣ ተጣልቶ ና ተከፋፋሎ ፣ ዘር ቆጥሮ ተባልቶ አያውቅም። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ታሪክ አብዛኛውን ጊዜ ሰው በሆነው ጫካ ውስጥ በዝግባ የሚመሰሉ ሰዎች ወደሥልጣን በመምጣታቸው ነው።
ታሪክ እንደሚነግረን፣ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የዚች ሀገር ጠላቶች ፣ ገዢዎች እና እናውቃለን የሚሉ ፣ ሆኖም ሰዎችን ከመኮነን እና ትንኝ የምታህለዋን የአምሳያቸውን (ምሁር፣ባለሥልጣን ና መሪም ቢሆን )ትንኝ የምታክል ጉድፍ ፣ ከራሳቸው ቋጥኝ ከሚያህል ጉድፍ ጋር የማያሥተያዩ ናቸው።
መልካም፣ ቅን ፣በጎነት የተሞላ መሪን ፤ አገርን ወደብልፅግና የሚያሸጋግር ራእይ የሠነቀውን ና ራእዩንም የማሣካት ብቃት ያለውን የ ትላንትም ሆነ የዛሬ መሪዎችን ፣ እያደናቀፉ ያሉት በተግባር ሲመዘኑ የሚቀሉ ግብዞቹ ዋንዛዎች ናቸው። ከራሳቸው ብልፅግና እና የሥጋ ምቾት ነጋ ጠባ ከመጨነቅ ይልቅ አንዳችም፣ አንዳችም ለህዝብ የሚጠቅም ራእይ የሌላቸው።
ዋንዛዎቹ ፣ በቃላት በማሳመንና ሱሪ በአንገት በማውለቅ ያምናሉ። አሁን ያለው ገዢ ፖርቲ ( የኢህአዴግ መንግሥት የተሰራበትን ሥሬት ለመቀየር ደርጋዊ አካሄድን መሄድ እንዳለበት ያምናሉ።ትላንት ደርግ ወታደራዊ መንግሥት መሆኑን እና ከጋለ የሀገር ፍቅር ሥሜት ውጪ፣እንደ ዶ/ር ሠናይ ልኬ ፣እንደ ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ፣እንደ ፕሮ መሥፍን ፣እንደ ነገደ ጎበዜ ፣እንደ አሰፋ ጫቦ፣ እንደ በዓሉ ግርማ ወዘተ ዓይነቶች በቅብብሎሽ እገዛ ባያደርጉለት 17 ዓመት በጦርነት ውሥጥ ሀገር እየመራ መቆየት ይቅር፣ና ለአንድ ዓመት በሥልጣን ላይ እንደማይቆይ እያወቁ ፣ የዛሬውን ጥገናዊ ለውጥ ያጣጥሉታል።
በመሰረቱ በአንድ ቀን ጀንበር ይህንን የ27 ዓመት መንግሥት ፣ እንደለበሥነው ኮት በማውለቅ አሽቀንጥረን የትም መወርወር አንችልም።እንዲህ ማድረግ ወያኔ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሠራዊት ” የደርግ” ነው ብሎ የፋሺሥት ተግባር እንደፈፀመው ፣ እኛ ተመሣሣይ ሀገር የሚያፈርሥ ተግባር ለመፈፀም የሚያሥችል ጨካኝ ልብ አለን ማለት ነው።
ይህንን ለማድረግሥ በዚች ሀገር ፣” ይሄ ለኢትዮጵያዊያን ይመጥናል… ዋርካ ነው ! ” የምንለው ፖርቲ ከቶስ አለ ወይ ?(የሰሞኑ የምርጫ ቦርድ አዲስ መሥፈርት እንደአሸን የፈሉትን እና እንደ ምልታዘዙ “ልጥ ፖርቲ ” ዓይነቶችን ያንገዋልላል ፣በሚል ፍራቻ ፣ የተፈጠረው ጫጫታ ይህንኑ ያረጋግጥልናል።።)
በውስጣቸው ግብዞችን ያላሰባሰቡ። በወንዝ ልጅነት ያልተጠራሩ። በተግባር አንድም ቀን በአዳራሽ አባሎቶቻቸውን ያልሰበሱቡ ።…በሥርዓት የተመዘገቡ ፣መታወቂያ ያላቸው፣ የዓባልነት መዋጮ የሚከፍሉ የፖርቲ ዓባላት የሌላቸው።ዓባል ሥለሆኑበት ፖርቲ፣ የተለያዩ ፖሊሲዎች አንዳችም ዕውቀት ያላገኙ። ሆኖም ያላአንዳች ኃፍረት ፖርቲ እናየፖርቲው የበላይ አመራር ነን ያሉ… ፣ አዳም ረታ እንዳለው ” የበዙ ፊት አውራሪ መሸሻዎች ” ፖርቲ ነን።ሀገር መምራት እንችላለን ። ቢሉስ ፣ ህዝብ ይሰማቸዋልን???……………
በእርግጥ ዋንዛዎቹ፣ ዓይን ቀቅለው የበሉ ናቸውና ህዝብ ባይወዳቸውም ” ውድድድድ” ነው ህዝባችን የሚያደርገን በማለት፣ለዓይኑ የጠላቸውን ህዝብ ፍፁም ሳያፍሩ፣መቶ በመቶ መርጦናል በማለት” በትረ ሥልጣኑን ” ከመያዝ ወደኋላ አይሉም።
ለዚች ሀገር ፣በአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ፣የጠገበ ሆዱን የበለጠ ለመሙላት ሣይሆን ፣ በጠኔ የሚማቅቁትን ፣በከፋ ድህነት ውሥጥ በመላው ሀገሪቱ የሚኖሩትን በግምት ከ50 ፐርሰንት በላይ የሆኑትን ዜጎች፣ ወደ ብልፅግና የሚያመጣ ” የዋርካ ስብስብ ” የሆነ መንግሥት ያሥፈልጋል። እንዲህ ዓይነቱን መንግሥት ለማወለድ ደግሞ ዜጎች ሁሉ፣ ጭንብላችንን አውልቀን ሰው መሆናችንን በመገንዘብ እንደዜጋ በህብረት ለሀገራችን ብልፅግና በቅንነት ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለሥራ መነሳት አለብን።
ከትዕቢት እና ከግለኛ ሥሜት ካልተላቀቅን ወደ ዋርካነት ለመቀየር አንችልም።ነገ ሟች መሆናችንን እስካላወቅን ድረስ፣ ሥላልተወለደው ህፃን አይጨንቀንም።በዛሬው ቀን የሚወለዱ እና በተመሳሳይ ሰዓትም የሚሞቱ አያሌዎች እኮ ናቸው፣ ትውልድ እንደሚመጣ ና ።ትውልድም ላይመለሥ እንደሚሄድ አንዘንጋ።(የወለድከው ልጅ ፣ያ ሰው ነው፣ አንተን ዘላለማዊ የሚያደርግህ።)
ኢትዮጵያ ሀገራችን ለዘመናት በትዕቢተኛ መሪዎች እየተመራች፣ትውልዶችን አፈራርቃለች።ዛሬ ግን፣ ትሁት እና ዝቅ፣ዝቅ ማለትን በተግባር የሚያሳይ ፣ፍትህ ገንዘቡ የሆነች ፣በህግ የበላይነት የሚያምን እና ይኽንን የህግ የበላይነት ፣ ደግሞ በተግባር የሚያረጋግጥ ዋርካ የሆነ መሪ ያሥፈልጋታል።…
ይህንን ዋርካ መሪ ለማዋለድ፣በሚደረገው ሠላማዊ ትግል ውስጥ የነፃ ፕሬሥ ሚና ከፍተኛ ነው። ከአጨብጫቢነት እና ከአለቅላቂነት የፀዳ ብዕር ያለው ጋዜጠኛም ይህ መሪ ቶሎ እንዲወለድ ያደርጋል።ወርካ ለፍቅር ብሎ አጎንብሶ ምድርን እንደነካ ፣ለባለጌው እና ለዋዘኛው ዋንዛ በድፍረት እየነገረ እና ዋዘኛ ና ባለጌውን ዋንዛ እያጋለጠ።…