July 28, 2019
ጠገናው ጎሹ
ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለኢንፎርሜሽን ተክኖሎጅ መዘመን ምሥጋና ይግባውና በዓለም ዙሪያ የሚሆነውን ደግ ወይም ክፉ ነገር ከመደበኛው (ከተለመደው) የኮምፒዩተር ላይ አጠቃቀም አልፎ በየኪሶቻችን በምንይዛቸው ስልኮች እጅግ ከሚገርም ፍጥነት ጋር ለማወቅ አስችሎናል ።
እንደማነኛውም የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ እንደሚፈልግ ግለሰብ እና በተለይ ግን ተወልዶ ያደገባትና በተፈጥሮ ሥጦታውም ሆነ በጠንካራ ሠርቶ አዳሪ ዜጎቿ ያልጎደለባት ምድር (ኢትዮጵያ) እየተፈራረቁ በሚገዟት እኩያን ፖለቲከኞች እና ከዚሁ ክፉ ልክፍት እናተርፋለን ባይ ግለሰቦችና ቡድኖች ምክንያት የምድር ሲኦል የመሆኗ ጉዳይ ከምር እንደሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ ይህኑ ዘመን አመጣሽ የኢንፎርሜሽን መረብ ያለማሳለስ እጎበኛለሁ ።
ጉብኝቱ ህሊናን እፎይ የሚያሰኝ ሳይሆን ለመግለፅ የሚያስቸግር እጅግ ከባድ የህሊና ፈተና የተሞላበት መሆኑን የገዥዎችንና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን ተራና ባዶ ፐሮፓጋንዳ እየተቀበለ ከሚያስተጋባው በስተቀር የአገሩ (የወገኑ) ጉዳይ ከምር የሚያሳስበው የአገሬ ሰው ይስተዋል የሚል ጥርጣሬ የለኝም ። በተለይ በጨካኝ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችና ግብረ አበሮቻቸው ወደ ጭንጋፍነት ከተለጠው የ1997ቱ መልካም ዴሞክራሲያዊ እድል ወዲህ ህሊናው በፀፀትና በቁጭት ሲተራመስ የኖረ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው አሁንም ሌላ ታላቅ መልካም እድል ወደ አስከፊ ጭንጋፍነት (ምናልባትም በባሰ አኳኋን) እየተለወጠ ይሆን? በሚል ብርቱ ሥጋት ህሊናው እፎይታ ቢያጣ ከቶ የሚገርም አይሆንም።
ከሰሞኑ ዩ ቲዩብ ( YouTube) የተሰኘውን የቪዲዮ መጫኛና ማጫወቻ መረብ ስጎበኝ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አፋልጉኝ” የሚል ርዕስ ያለው የቪዲዮ ጥሪ ተመለከትኩ ። የማጫወቻውን ምልክት ጠቅ ሳደርገው በአሜሪካ የካልፎርንያ ግዛት ኗሪ ከሆኑና ዶ/ር ዳኛቸው ተሾመ ከተባሉ ሰው የተላለፈ መልክተ አፋልጉኝ መሆኑን ተረዳሁ ።
የአፋልጉኝ ጥሪው ዋና መልእክት “መንበረ ሥልጣኑን እንደተረከቡ ባደረጉት እጅግ ስሜትን የሚመስጥ ዲስኩርና በወሰዷቸው አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎች መነሻነት ‘የእግዚአብሔር ጣቶች ያረፉበት ኢትዮጵያዊ ሙሴ’ ተብለው እስከ መሞካሸት የደረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙም ሳይራመዱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠፍተውብኛልና (በቃላቸው ያለመገኘት ከባድ ስህተት ውስጥ ወድቀዋልና) ያንን የመጀመሪያውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አፋልጉኝ” የሚል ይዘት ያለው ነው ። መልእክቱ ይህ መሆኑን ገና ከመግቢያው ለመገንዘብ ብችልም እኔስ/እኛስ? ለሚለው እራስን የመፈተሽ ጥያቄ ሂሳዊ አቀራረብና ትንታኔ (critical approach and way of analysis of self-searching) እጠብቅ ስለነበር በትእግሥት አደመጥኩት ። አድምጨም ጨረስኩ ።
ይህ ” ሥልጣኑን ሲረከብ ለአስተጋባቸው ድንቅ ቃላት ህይወት መዝራት በሚመጥን አኳኋን መዝለቅ እየተሳነው ያለውን ኢትዮጵያዊ ሙሴ አፋልጉኝ “ የሚለው ጥሪ የእውነተኛ ለውጥ ህልሙ እውን መሆን ወይም አለመሆን ከሚያሳስበው ቅን ዜጋ የቀረበ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙም ማሰብ አልጠየቀኝም ።
ጥርሱን ነቅሎ ያደገበትን የዘመናችን ፈርኦኖች ሥርዓተ መንግሥት አውግዞና ንስሃ ገብቶ “‘በብርቱ የተጎሳቆለችው ምድር (ኢትዮጵያ) የነፃነትና የፍትህ ምድር ትሆን ዘንድ የማልከፍለው መስዋዕትነት የለምና ተከተሉኝ’ የሚል ድንቅ የውዴታ ግዴታ ቃል ኪዳን የገባው ‘ኢትዮጵያዊው ሙሴ’ በአካል ሳይሆን ሆኖና አድርጎ ከመገኘቱ ዓለም ጠፍቶብኛልና አፋልጉኝ” የሚል ጥሪ ማቅረብ ቢያንስ ልክ ከሌለው ስሜታዊነትና የጭፍን ድጋፍ ክፉ አባዜ ለመውጣት ይቻል ዘንድ ቆም ብሎ ለማሰብ ይረዳልና ይበል የሚያሰኝ ነው ማለት ይቻል ይሆናል ።
ከላይ እንደጠቀስኩት የአፋልጉኝ ጥሪው አንድ ትልቅ ቁም ነገር እንደሚጎለው ግን ግልፅ ነው ። የጥሪው ሂሳዊ ጎደሎነት የሚመነጨው ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የሚመሩትን መንግሥተ ኢህአዴግ ለተጀመረው የለውጥ ሂደት መሳካት ወይም መጨንገፍ በዋናነት ተጠያቂ የማድረጉ ተገቢነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ እኔስ/ እኛስ እንደ ግለሰብ ዜጋ (በተለይ ፊደል እንደቆጠረ ) ፣ በፖለቲካና በልዩ ልዩ የሲቭልና የሙያ ማህበራት እንደ ተደራጀ የዜጎች ስብስብ አባልነት እና በአጠቃላይ እንደ ህዝብ “ኢትዮጵያዊ ሙሴ” ብለን የተቀበልንበትና ያስተናገድንበት ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሁኔታ ትክክል ነበር ወይ? የሚለውን እራስን የመፈተሽ ጥያቄ ለመመለስ ካለመቻል ወይም ካለመፈለግ ነው።
የለውጥ ሽታ በሸተተን ቁጥር “የለውጥ አራማጅ ነን” የሚሉትን ፖለቲከኞች የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሁኔታ በእጅጉ የወረደ (ልክ በሌለው ግልብ ስሜት የተሳከረ ) በመሆኑ ምክንያት መልሰንና መላልሰን አይውድቁ ውድቀት እየወደቅን ከመጣንበት የፖለቲካ ታሪካችን (ተሞክሯችን) አሁንም አለመማራችን በእጅጉ ያሳስባል ። እንደ ዜጋም አንገት ያስደፋል ፤ እንደ አገርም በእጅጉ ያሳፍራል ። ቆም ብሎና ትንፋሽ ወስዶ የእንቆቅልሹን ሚስጥር ከምር ለመረዳት ፈቃደኛና ዝግጁ የሆነ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው ማለቴ ነው።
በዓለማዊው ወይም በሃይማኖታዊው እውቀት ልሂቅ ብቻ ሳይሆን የልሂቃን ሁሉ ልሂቅ ነኝ እያለ የሚመፃደቀው የአገሬ ሰው ፖለቲከኞችን የተቀበለበትንና ያስተናገደበትን ማርሽ (የፍጥነት መቆጣጠሪያ) ምን? ለምን? እንዴት ? ለማን? በነማን? መቼ ? የትና ወደ የት? ከዚያስ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እያዘለለ በመጨረሻው ማርሽ በመክነፉ ወደ ትክክለኛውና ጤናማ የማርሽ አጠቃቀም ለመመለስ ተቸግሮ እራሱን ብቻ ሳይሆን ህዝብንም ግራ ሲያጋባ ማስተዋል በእጅጉ ህሊናን ያቆስላል ።ከምር የሚሞግት ህሊና ላለው።
ከመከራውና ከውርደቱ መጠንና መሪርነት የሚመነጨውን እጅግ ስስ የሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ሥነ ልቦና ከቆዩበት የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ክፉ ሥርዓት አሳምረው የተማሩት ፖለቲከኞቻችን “የለውጥ አራማጅነታቸውን” ትርክትና ዲስኩር በዚህ ስስ ሥነ ልቦና መወድስ መጀመራቸው ጨርሶ የማይጠበቅ ወይም የሚገርም አልነበረም። ሊቀ ሊቃውንት ወይም የልሂቆች ሁሉ ልሂቅ ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል በአሳዛኝ አኳኋን እራሱን ወደ ታች ያወረደው ይህን ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች አካሄድ ሂሳዊ በሆነ አቀራረብ ( critical approach) ከመቀበልና ከማስተናገድ ይልቅ ፊደል ካልቆጠረው ወገኑ በባሰ አኳኋን ልክ በሌለው ግልብ ስሜት ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞችን “ክንፍ አልባ መላእክት” ብሎ ያሞካሸ እለት ነው። ለመሆኑ “የዘመኑ ሙሲዎች ፣ ከሰማየ ሰማያት የተላኩ ፣ ክንፍ አልባ መላእክት ፣ ወዘተ” በሚል ፖለቲከኞችን ያወደሰ (የሚያወድስ) ልሂቅ ወይም ሊቀ ልሂቃን ስለ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን መሞገትና መሟገት እንዴት ይቻለዋል ? ለዚህም አይደል እንዴ ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር መንበረ ሥልጣን ላይ የሚወጡ ፖለቲከኞች ሁሉ በየአዳራሹና በየአደባባዩ ታዳሚያቸው እያደረጉ ክንዱ እስኪዝል የሚያስጨበጭቡት ?
ታዲያ የአፋልጉኝ ጥሪ የሚያስፈልገው ድሮም የህዝብን ስስ ሥነ ልቦና በማማለል የፖለቲካ ተቀባይነት ለማግኝት ሲሉ ድንቅ ቃላትን ለዲስኩሮቻቸው ማሳመሪያነት ለተጠቀሙት ፖለቲከኞች ሳይሆን የዚህ እጅግ አሳሳች የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ ለሆነው ተማርኩና ተመራመርኩ ለሚለው ወገን አይደለም ወይ?
የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኛ ገዥዎች አደንቁሮ የመግዛት ፖለቲካ ሰለባ ሆኖ የቆየው ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህ አይነት ከንቱ መወድስ ተጠቂ ቢሆን ከቶ የሚገርም ወይም የማይጠበቅ አልነበረም ። አይደለምም ።
በእውነት እየተነጋገርን ከሆነ ሳይማር ያስተማረን ህዝብ መልሶ ሳያስተምሩ ወይም የመሠረታዊ እውቀት ባለቤት እንዲሆንና ይህንኑ እውቀት ነፃነትንና ፍትህን ወደ የሚያረጋግጠበት ድርጅታዊ ቁመና እና አቅም ይለውጠው ዘንድ ትርጉም ያለው ሥራ ሳይሠሩ በየመደስኮሪያ መድረኩ ድንቅ ዲስኩር እያስተጋቡ ፣ ከስሜታዊነት በሚነሳ የሙገሳ ጭብጨባ እየተሳከሩ እና ብሶቱን ብቻ እያራገቡ መከረኛው ህዝብ ተአምር እንዲሠራ ከመጠበቅ የከፋ ተማርኩ ብሎ የመደንቆር አባዜ የለም ።
ከዚህ መሠረታዊ የፖለቲካ ግድፈት በመነሳት ነበር የአፋልጉኝና የእንፈላለግ ጥሪው “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመጀመሪያውም የተቀበልንበት ሁኔታ በእጅጉ ግልብና የወረደ መሆኑ ትምህርት ይሁነንና ከዛሬ ጀምሮ በጠንካራ ምክንያታዊነትና ዘላቂ በሆነ የዓላማ ፅእኑነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አውድ ውስጥ እራሳችንን ፈልገን ለማግኘት ጥረት እናድርግ ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደ አንድ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን በህወሃት/ኢህአዴግ የጎሳ/የዘር/የመንደር አጥንት ሥርዓተ ፖለቲካ ጥርሱን ነቅሎ እንደ አደገ ፖለቲከኛ በጥሞና እና ሂሳዊ በሆነ አቀራረብ ለማየት ያለመፈለጋችን ወይም ያለመቻላችን ውድቀት ይበልጥ ለከፋ አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሞራላዊ ቀውስ እየዳረገን ነውና የጠፋብንን የእራስን ነፃነት በራስ ተጋድሎ የማረጋገጥ መንፈስና መንገድ ፈልገን እናግኘው “ የሚል ግልፅና ቀጥተኛ ጥሪ የኖረዋል ብየ የጠበቅሁት ።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ይባልልኝ ። እያልኩ ያለሁት እሮሮውና የአፋልጉኝ ጥሪው ትክክል አይደለም ወይም አይጠቅምም ሳይሆን ደረጃውና መጠኑ ሊለያይ ቢችልም ማነኛችንም ተነሳን ስንል ተመልሰን አዙሪት ውስጥ የመዘፈቅ ክፉ አባዜ የፖለቲካ አውድ ወጭ ልንሆን አንችልምና በዚህ ረገድ የምናደርጋቸው የሃሳብ ልውውጦችም ይህኑ ሃቅ የሚያንፀባረርቁ መሆን ይገባቸዋል ነው ። እነዚያ ወይም እነርሱ ስንል እኔስ ወይም እኛስ ? ብሎ መጠየቁን አውቀንም ሆነ ሳናውቅ እየሸሸን የተሟላ የመፍትሄ ሃሳብና ትርጉም ያለው የተግባር እርምጃ እውን ለማድረግ ጨርሶ የሚቻለን አይሆንም ። በሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ውስጥ በተራ ካድሬነት (በደቀ መዝሙርነት) እና ከዚያም በላይ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉ ፖለቲከኞችን ስሜት ኮርኳሪ የህዝባዊነት ዲስኩር (excessively emotional populist political rhetoric) ምን? ለምን? ማን? በማን/በነማን? መቼና እንዴት? ከየትና ወደ የት ? ብለን ሳንጠይቅና ሳንሞግት “ከሰማየ ሰማያት የተላኩ ሙሴዎች” ብለን የተቀበልንበት ሁኔታ ያለንበትን ዘመን የገሃዱ ዓለም ፖለቲካ ጨርሶ የሚመጥን አልነበረም ። አይደለምም። የገሃዱ ዓለም እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉት ፖለቲከኞችን ምክንያታዊና ሂሳዊ በሆነ አቀራረብ ሳይሆን ልክ በሌለው ግልብ ስሜታዊነት አቀራረብ እንዲባልጉ ካደረግን በኋላ እነዚያ የመልካም ቃላት ፖለቲከኞችን ምን ነካብን? እባካችሁ አፋልጉን ? የሚል ጥሪ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም ።
መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክረራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ይሆን ዘንድ ግዙፍና መሪር መስዋዕትነት የተከፈለበትን የረጅም ዘመን ትግል የለውጥ አራማጅ ከምንላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞች የሸፍጥ ተሃድሶ ሰለባነት የሚታደግ የፖለቲካ ድርጅት (ሃይል) ለመፍጠርና ለማዘጋጀት ያለመቻላችን ሁኔታ ምን አይነት ውድቀት ሊያስከትል እንደሚችል መሬት ላይ ካለው መሪር ሃቅ በላይ ሊነግረን የሚችል መረጃ (ዋቢ) የለም።
ይህ እየሆነ ያለው ከመቶ በላይ ተቀዋሚ (ተፎካካሪ ፉገራ ነው) ፓርቲ ተብየ በሚተራመስባት እጅግ ደሃ አገር ውስጥ መሆኑን ልብ እንበል ። እጅግ ወደ ኋላ በመቅረቱ የግለሰቦችና ቡድኖች መጫወቻ እንደሆነ ከቀጠለው የአገራችን የፖለቲካ አውድ (political arena) እይታ አንፃር ባይገርምም በእጅጉ የሚያሳዝነው እራሳችንን አከሰምን ካሉ ቡድኖች የተወለደውን ኢዜማን ጨምሮ ከዚህ እጅግ አስከፊ አዙሪት ለመውጣት ያስችሉ ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ የተቀዋሚ ድርጅቶች እራሳቸው የአዙሪቱ ሰለባ መሆናቸው ነው።
አዎ! እንደ ሰብአዊ ፍጡርና እንደ ዜጋ በነፃነት ተከብሮና ተከባብሮ የሚኖርበት ሥርዓተ ፖለቲካ መሽቶ በነጋ ቁጠር ከመቅረብ ይልቅ እየራቀበት በእጅጉ የተቸገረውን መከረኛ ህዝብ “ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ በመለስ ያለውን የፖለቲካ ትግል ግብ አጥበቀን የምንፀየፈው መሆኑን እንደፈጣሪህ እመነን” ሲሎት እንዳልነበር አሁን ጠቅልለው ሲዘፈቁበት ማየት የማያሳስበን ከሆነ ስለ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ታገልን ወይም እየታገልን ነው ማለታችን ጨርሶ ትርጉም አይኖረውም ።
ታዲያ ድሮውንም ለረጅም ጊዜ በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ የተካኑትን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች “ቃላቸውን አጥፈውብኛልና አፋልጉኝ” ከማለት ይልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ የተቀዋሚ ድርጅቶች ፖለቲከኞችን አፋልጉኝ ማለት ትክክል አይሆንም ወይ?
በእውነት ከተነጋገርን ከቃላት ወይም ከዲስኩር አልፎ የሄደና ከባድ መስዋእትነት ከተከፈለበት የሥርዓት ለውጥን እውን የማድረግ ዓላማ አንፃር ሲታይ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ለውጥ ወይም እርምጃ (political paradigm shift) የሚሳይ እውነታ ባልታየበት ሁኔታ “ያ ድንቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጠፍቶብኛልና አፋልጉኝ ። አሁንም ተስፋ አልቆርጥም” የሚለው የአፋልጉኝ ጥሪ የሚፈለገውን የህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ እውን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ጨርሶ አይመጥንም። የራስን ነፃነት በራስ ጥረትና ወሳኝነት እውን ማድረግ እንጅ በቃላቸው ለመዝለቅ የሚያስችል እውነተኛ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሰብእና በእጅጉ የሚቸግራቸውን የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞች “እባካችሁ የአፋልጉኝ ጥሪዬን ሰምታችሁ ወደ ገባችሁት ቃል ኪዳን ተመለሱ” የሚል የተማፅኖ አይነት ፖለቲካ ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ አይደለም። ከዚህ አይነት የኮሰመነ የፖለቲካ ሥነ ልቦና በቶሎ መውጣት ይኖርብናል ።
ከዚህ የመውጣቱ እርምጃ መጀመር ያለበት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን “የዘመናችን ሙሴ ወይም የፈጣሪ ጣቶች ያረፉበት” እያልን የተቀበልንበት ሁኔታ ጨርሶ የተሳሳተ መሆኑን አምኖ ከቀበልና ተገቢውን እርምት ከማድረግ ነው ። በሌላ አገላለፅ ያለብን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንጭጭነት (naivety of political thinking) ለላንበት እውነታ የማይመጥን መሆኑን አውቀን ቀጣይነት ያለውና በኢህአዴግ የተሃድሶ ፖለቲከኞች የሸፍጥ ፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር የማይወድቅ የፖለቲካ ሥራ መሥራትን ግድ ይለናል።
“ያንን የኢትዮጵያ ሙሴ ምን ነካብን? እባካችሁ አፋልጉን” ለሚለው ጥሪ ወይም አዋጅ ፈጣሪም ጀሮውን የሚሰጠው አይመስለኝም ። ምክንያቱም ሰውን ከነሙሉ ነፃነቱ ሲፈጥረው ያንኑ መብቱን ለማስከበር ከሚያስያስችለው የአካልና የአእምሮ ብቃት ጋር ነውና ። ረቂቁን አእምሮ ያደለውም የሚፈልገውንና የሚወደውን ከማይፈልገውና ከማይወደው ለይቶ እንዲተገብርና እንዲጠቀምበት ነው ። የአካሉን ብቃት ያደለውም ረቂቁ አእምሮ በጥሞና የተረዳውንና ለተግባራዊነት ያዘጋጀውን ሃሳብ ከሌሎች ደመ ነፍስ እንስሳት በተለየ አኳኋን እውን እንዲያደርግና ለህልውናው ብቻ ሳይሆን ለማያቋርጥ ነፃነቱና እድገቱ እንዲጠቀምበት ነው ። የፈጣሪ ሃላፊነትና ተግባር የሰው ልጅ መሆን ያለበትን ሆኖና ማድረግ ያለበትን አድርጎ ለመገኘት በሚያደርገው ቁረጠኝነት ፣ቅንነትና ጥበብ በተሞላበት ጥረት ውስጥ እገዛውንና በረከቱን መለገሥ ነው ። ከአእምሯዊና አካላዊ ብቃት ጋር ተፈጥረን የራሳችን ሃላፊነትና ተግባር ሥራ ላይ ለማዋልና ለምድርም ሆነ ከሞት በኋላ ተስፋ ለሚደርገው ህይወት የሚበጀውን ለማድረግ ባቃተን (ስንፍና በተጫጫነን) ቁጥር የምናሰማውን የድረስልኝ እግዚኦታ እየተቀበለ መፍትሄ የሚያድል (የሚያከፋፍል) ፈጣሪ ያለ አይመስለኝም ።
እናም ቀድሞውንም ቢሆን ቃል የመታመን እዳ እንደሆነ ከምር አምነው ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ በድንቅ ቃላት ቅንብር የተዋቡ ዲስከሮቻቸውን ያስደመጡን ፖለቲከኞችን “አፋልጉኝ” እያሉ ከመቸገር ፈጣሪ ሲፈጥረን ከሌሎች እንስሳት በተለየ የሰጠንን አካላዊና አእምሯዊ ብቃት ለምንና እንዴት በአግባቡ ለመጠቀም እንደተሳነን ፈልገን ማግኘትና እስከአሁን ከኖርንበት የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ነፃ መውጣት ይኖርብናል ።
ተነሳን ስንል ተመልሰን የምንወድቀው ፖለቲከኞችንን ምንነታቸውንና ማንነታቸውን በተግባር እየመረመርንና እያረጋገጠን እንድንራመድ የሚያስችለንን አእምሮ ወደ ውስጥ እያመቅን በስሜት የሚጋልበውን እኛነታችንን ያለ ልጓም የመልቀቃችን ክፉ ልማድ ነው ። አካላችንም የሚታዘዘው ለዚሁ ልክ የሌለው የስሜታዊነት እኛነታችን በመሆኑ ወደ የምር የጨዋታ ሜዳ ደፍሮ ለመግባት ይሳነዋል ። ቢገባም የተነሳበት የአስተሳሰብ አውድ ስሜታዊነት እንጅ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ሰለባ ከመሆን አያመልጥም። በአገራችንም እየሆነ ያለው ይኸው በዚሁ ክፉ የፖለቲካ አዙሪት ዙሪያ የመሽከርከር አባዜ ነው ። ከዚህ በተሻለ አገላለፅ መግለፅ ቢቻል እንዴት መልካም ነበር ። ነገር ግን ፊት ለፊት ያፈጠጠውን እውነታ በአገላለፅ ለማስታመም መሞከር እራስን እየሸነገሉ ወደ ማይቀረውና ሊመልሱት ወደ ማይቻል የቁም ሞት መውረድ ነው የሚሆነው።
ለዚህ ነው “የኢህአዴግን የለውጥ አራማጅ ፖለቲከኞች ቃላቸውን አጥፈው (በልተው) እየጠፉብኝ ነውና እባካችሁ አፋልጉኝ” የሚለው ጥሪ ከቅንነት የሚመጣ ነው ሊባል ቢቻልም በእጅጉ እንጭጭ (seriously naïve) ነው ማለት ትክክል የሚሆነው።
እናም ጠፋብን የምንለውን ፖለቲከኛ ከመጀመሪያውም የተቀበልንበትንና አብረን ዳንኪራ የረገጥንበትን የፖለቲካ አስተሳሰብ እጭጭነት ፈልገን በማግኘት ይበልጥ ሳያበላሸን ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብና አካሄድ መመለስ አለብን ።
አዎ! ይህ ግዙፍና መሪር እውነታ እንኳን ከእለት እለት ህይወቱ ጋር እየኖረው ላለው የአገሬ ህዝብ በየትኛውም የሰለጠነና የተሳካላት የዓለም ክፍል ለሚኖረው የአገሬ ሰውም ግልፅና ግልፅ በመሆኑ ለምን? የሚለውን ማብራራት የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም።
“ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተከፈለበትን መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ ወርቃማ ተሃድሶ እያካሄድን ነው” የሚሉትን ኢህአደጋዊያንና በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጎሳ ላይ የተመሠረቱ መንደሮች ንጉሦች ወይም ንግሥቶች በመሆን ምኞት እብደት ውስጥ የሚገኙ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነን ባዮች እያወቁ የጠፉ ስለሆነ የአፋልጉኙን ጥሪ በጥሞና አድምጠው እንዴት በጎ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ለማመን ቀርቶ ለማሰብም ያስቸግራል።
እናም ከምር ፈልገን ማግኘት ያለብን እያወቁ የጠፉትን አጥፊ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ነን ባዮች ሳይሆን እንዲህ አይነቱን አስቸጋሪ የፖለቲካ እንቆቅልሽ ለመፍታት የሚያስችለንን የአርበኝነት ሞራልና ጥበብ ለምን? እንዴትና መቼ ? እንዳጣነው (እንደጠፋብን) ነው ።
ጠንካራ አማራጭ ሃይል ሆነው አለመገኘት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ወደ የኢህአዴግ የተሃድሶ ፍርፋሪ ለቃሚነት (ተመፅዋችነት) በቀየሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ምክንያት መሽቶ በነጋ ቁጥር የአገራችን ሁለንተናዊ ቀውስ መጠንና ጥልቀት እየከፋ መሄዱን ቀጥሏል ። እናም እነዚህንም “ምነው ስንፈልጋችሁ የት ጠፋችሁብን?” እያሉ ከመጨነቅ አሁን እያሳዩ ያሉትን ወደ ለየለት የኢህአዴግ “የለውጥ አራማጅ” ቡድን ተለጣፊነት (ካድሬነት/አሽቃባጭነት) የመጠቃለል አሳፋሪ አስተሳሰብና አካሄድ ቆም ብለውና በቅጡ አጢነው ለበርካታ ዓመታት ከበሬታንና ድጋፍን ወደ አስገኘላቸው ለመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ በፅናት የመቆም አቋማቸው እንዲመለሱ በግልፅና በቀጥታ መናገር (መሞገት) የግድ ነው ። የምንነጋገረው በፖለቲካ ወንጀል የተዘፈቀው ኢህአዴግ ስለሚመራው የሸፍጥ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሳይሆን ስለ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ከሆነ ።
በየአዳራሹ፣ በየአደባባዩ፣ በየመገናኛ ብዙሃኑ እና በየሃይማኖት አውዱ መሬት ላይ ጠብ የሚል ቁም ነገር የሌለውን ንግግር ወይም ሰበካ ስናዥጎደጉድ “ምን እያላችሁና ምን እየሆናችሁ ነው ?” ብሎ ሳይጠይቅ በሚያጨበጭብልን ታዳሚ በተሳከርን ቁጥር የግብዝነቱን አባዜ ይበልጥ እየተለማመድነው በመሄድ ላይ እንገኛለን ።
እንደ አንድ የአገሩን የፖለቲካ ታሪክና ባህል ለማወቅ የሚያስችል መሠረታዊ አቅምና ጉጉት እንዳለው ኢትዮጵያዊ ከአንድ ዓመት በፊት “የለውጥ አራማጅ” የምንላቸውን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች የተቀበልንበትን ሁኔታ በዚሁ ዘመን አመጣሽ ድንቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ያላማሳለስ ተከታትያለሁ ። ምንም እንኳ ከምክንያታዊነትና ከሂሳዊ አቀራረብ ይልቅ በግልብ የስሜታዊነት ፈረስ የመጋለብ ሁኔታ በአሳሳቢ ደረጃ የተስተዋለ ቢሆንም የለውጥ ፍንጭ የታየባቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ከሥጋት ይልቅ የተስፋ ስሜት የጫሩ እንደ ነበሩ መካድ አይቻልም ።
በግዙፍና መሪር መስዋእትነት የመከራና የውርደት ፖለቲካ ምዕራፍ ተዘግቶ እንደ ሰውም ሆነ እንደ ዜጋ ተከብሮና ተከባብሮ መኖር የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለመክፈት የሚያስችለውን መልካም እድል በመሪነት የተቀላቀሉትን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች የተቀበልንበትና ያስተናገድንበት ግልብና ሂስ አልባ ፖለቲካዊ ድባብ ይኸውና ከአንድ ዓመት በኋላ “የዘንድሮው ጠቅላይ ሚኒስትር ቃላቸውን አጥፈዋልና እኒያን የአምናውን ጠቅላይ ሚኒስትር አፋልጉኝ “ የሚልና ብዙም ፋይዳ የሌለው ጥሪ ለማቅረብ ተገደናል ። ልክ በሌለው የስሜት ፈረስ የጋለብንበት አካሄድ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከመጣንበት በባሰ ሁኔታ ወደ ክፉው የቁልቁለት አዙሪት ይዞን እየነጎደ መሆኑ የእለት ከእለት ዜና መሆኑን ተለማምደነዋል ።
እናም ያለምንም ሂሳዊ አቀራረብ “የሰላምና የፍቅር ቀንዲሎች” ብለን የተቀበልናቸው የኢህአዴግ ተሃድሶ (reform) ፖለቲከኞች እያደር እውነተኛ ባሀሪያቸው ሲገለጥ አዲስ ባህሪ የተጠናወታቸው ይመስል “ተለውጠውብኛልና አፋልጉኝ” የሚል ጥሪ ማቅረብ ሲያንስ የፖለቲካ የዋህነት ነው ፤ ሲበዛ ደግሞ የፖለቲካ ድንቁርና ነው ።
የህወሃት የበላይ ፈላጭ ቆራጭነት መወገድን እና አንዳንድ ለለውጥ አጋዥ የሆኑ አወንታዊ ክስተቶችን በማየት እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ የተካሄደ እስኪመስል ድረስ የተጎሰመውን ነጋሪት ፣ የተጨፈረውን ጭፈራ፣ የተደሰኮረውን የዲስኩር ጋጋታ ፣ የተበረከተውን ቅኔና ዝማሬ ፣ የተዘፈነውን ዘፈንና የተደነሰውን ዳንስ፣ የተጠቀሰውን የሃይማኖት እና የፍልስፍና ጥቅስ ፣ የተነገረውን ትንቢተ ለውጥ ፣ወዘተ አሁን ከምንገኝበት በፍጥነት ተመልሶ የመውደቅ አደጋ ጋር ለሚያጤን የአገሬ ሰው መቼና እንዴት ነው ከዚህ አይነት ከባድ የእንቆቅልሽ አዙሪት የምንወጣው? የሚል ጥያቄ ህሊናውን ቢያናውጠው የሚገርም አይሆንም ።
ይህን አይነት እንቆቅልሽ ለመፍታት ከተቸገርንባቸው አይነተኛ ምክንያቶች አንዱ ገና ወደ ለውጥ (ለውጥ ማለት ለእኔ የሥርዓት ለውጥ ነው) የሚወስደውን የመጀመሪያ ምእራፍ በቅጡ ሳንጀምረው የድል ነጋሪት መደለቃችን ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት ለምን ? እንዴት? በነማን? ለነማን? በምንና በየት በኩል? የትስ ለመድረስ? ብለን ሳንጠይቅ ፖለቲከኞችን “ክንፍ አልባ መላእክት” ብለን የተቀበልንበት ሁኔታ ብዙም ሳቆይ አላስፈላጊ ዋጋ አስከፍሎናል ። እያስከፈለንም ነው።
እናም “ያንን የአምናውን የእግዚአብሔር እጅ ያረፈበት ኢትዮጵያዊ ሙሴ አፋልጉኝ” የሚለው ጥሪ ተገቢና ጠቃሚ ነው ብንልም እንኳ ከምንምና ከማንም በፊትና በላይ ፈልገን ማግኘት ያለብን የተሰወረብንን የራሳችንን እንቆቅልሽ በራሳችን የመፍታት ቅንነትና ጥበብ ነው ።