July 11, 2019
16 mins read

አምናና ዘንድሮ – ነፃነት ዘለቀ

ነፃነት ዘለቀ ([email protected])

የ97ን የከሸፈ ምርጫ ተከትሎ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አንድ ድንቅ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ እርሱም “ኢቲቪን ማየት ካቆምኩ ጀምሮ ጤንነቴ ተመለሰ” ያሉት ነው – በትክክል ካላስቀመጥኩት ይቅርታ፡፡ እኔም ከርሳቸው ልዋስና ጤንነቴ ስለሚበልጥብኝ ኢቲቪን አላዘወትርም፤ እንዲያውም አላይም ነበር፡፡ ካለፈው ዓመት ለውጥ ወዲህ ግን በመጀመሪያ አካባቢ በደምብ፣ ቆየት እያልኩ አንዳንዴ፣ ከቅርብ ጊዘያት ወዲህ ደግሞ በጭራሽ አላይም፡፡ ትናንት ሲያቀብጠኝ የነእስክንድርን ውሎ ከዘገቡት እንዴት እንደሚዘግቡት ለማየት ለተወሰነ ጊዜ ብከፍት ኢቲቪ የሚባለው ጉድ ሕገ መንግሥታችንን በጉልበት ሲደፈጥጠው ታዘብኩ፡፡ ይህ ጣቢያ አለፈለት ስል እንደለመደበት ለእውነት ሣይሆን ለተረኛ ገዢ አሸርጋጅነት ቀጥሏል፡፡ የሚገርም ጣቢያ ነው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የአምናም የዘንድሮም መልቲ ሲስተም የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን በየነ ዜና እያነበበ ነው፡፡ የዜናው ምንጭ ደግሞ ኢዜአ ወይም ኢቢሲ ሣይሆን ኦቢኤን ነው – ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ፡፡ እሱ ባልከፋ – ላለው ይጨመርለታል ነው፡፡ ይሁንና ተሜ “በፊንፊኔ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች…” በማለት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ንብረት የአንድን ክልልና የአንድን መሪ ድርጅት የስያሜ አቋም ሲናገር ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሙከራ እያደረገ እንደሆነ ማንም አልገባውም፡፡ ሕገ መንግሥታችን ተንዷል፡፡ ፍርድ ቤት ቢገኝ መክሰስ ነበር፡፡ ነገሩ እየሆነ ያለው አፄ ቴዎድሮስ ለካህናት እንዳሉት – አሁንም እዋሳለሁ – “አንዱ አንባቢ አንዱ ተርጓሚ” እየሆኑ ይህችን ሀገር መቀመቅ መክተት ነው – በግላጭ፡፡

እርግጠኛ ነኝ – በፌዴራል ሕገ መንግሥታችን “የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዋና ከተማ አዲስ አበባ ናት፡፡” ማለቱ አይቀርም – ባላነበውም፡፡ ታዲያ አማራውን ጨምሮ ይህ ሁሉም ቤርቤረሰቦች በእኩል ተሣታፊነት “ሆ!” ብለው ያጸደቁት  ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥታችን በደምቡ መሠረት ለውጥና ማሻሻያ ሳይደረግበት ማንም የመጣ የሄደ ሁሉ በመንግሥትነት ስም ከደረመሰው የመኖር ዋስትናችን እንዴት ሊከበር ይችላል? ለዚህ ድፍረትና ግልጽ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰትስ ተጠያቂው ማን ነው? እነእስክንድርስ ፈጸሙት የተባለውስ ጥፋት ከዚህ ይበልጣል ወይ? የሚመለከተው አካል ካለ ይታሰብበት፡፡ ሕገ መንግሥታችን ይከበር! እነኢንጂነር ታከለ ኡማ ወዴት አሉ? ፖሊስና መከላከያስ በሶ ጨበጠ ወይ?

የአምናውን የሚዲያ ሽፋን ስከታተል ለገለጻና ማብራሪያ የሚቀርቡት ባለሥልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች በአብዛኛው ከየትኛው ጎሣ/ብሔረሰብ ይመደቡ እንደነበር በግልጽ እረዳ ነበር – በስማቸው ብቻ ሣይሆን ባነጋገር ቅላጼያቸው፡፡ ያ የአምናው ሥርዓት መተታዊ በሆነ ፍጥነት በአንድ ዓመት ውስጥ ጥግ ይዞ አሁን ደግሞ ማንኛውንም ዓይነት መንግሥታዊ ሚዲያ ከፍቼ ስከታተል የሚቀርቡትና መግለጫና ማብራሪያ የሚሰጡት ባለሥልጣናት ከአንድ ጎሣ ምንጭ የተቀዱ ለመሆናቸው ካላንዳች ጥርጥር መረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር እንዲያው የአጋጣሚ ነገር ቢሆን ደስ ባለኝ፡፡ ግን አይመስለኝም፤ አይደለምም፡፡ እንደዚች ያለችው የቁጭ በሉ ተግባር ከቀጠለች የሰይጣን ጀሮ ይደፈንና ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከናካቴው ልትጠፋ ትችላለች፡፡

በዘረኝነት ቅኝት ተጉዞ የጠፋ እንጂ የለማ ሀገር በዓለም ታሪክ የለም፡፡ ሰውነትና የጋራ ዜግነት ያሳድጋል፡፡ ጎሠኝነትና ዘረኝነት ከምድረ ገጽ ያጠፋል፡፡ በዘረኝነት ጦስ በሚቀሰቀስ ጦርነት ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ የለም – ዩጎዝላቪያንና ሦርያን አስቡ፡፡ ተያይዞ መጥፋት ዕቅድና ፍላጎታችን ከሆነ እሰየው ባይባልም በተጀመረው መንገድ መትመምና የጋራ መቃብርን መቆፈር ነው፡፡ የሚያዋጣን ግን ከዚህ ሸፋፋና ወልጋዳ አካሄድ፣ ከዚህ ሕወሓትን እንጦርጦስ ከከተተ የዲያቢሎስ ጎዳና በአፋጣኝ መውጣት ነው፡፡ ዛሬ ሁሉንም ነገር ልትቆጣጠር ትችላለህ፡፡ በዚያም ደረትህም እግርህም ሊያብጥ ይችላል፡፡ ያለ ነው፡፡ ያጋጥማል፡፡ ግን ግን ነገ ሌላ ቀን መሆኑን ከረሳህ ተሞኝተሃል፡፡ በጓዳ ምን እየተሰናዳልህ እንደሆነ አታውቅም፡፡ የደመሰስከው ከመሰለህ የጠላትህ ኃይልና ጉልበት የበለጠ ነገር በሥውር ተዘጋጅቶ ከገባህበት እየገባ የሚመነጥርህ ታሪካዊ መቅሰፍት እንደሚገጥምህ ከወዲሁ ተረድተህ ወደኅሊናህ መመለስ ነው ብቸኛው የመዳኛ መንገድ፡፡ “ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም” ወንድሜ፡፡ ጎልያድ በትዕቢቱ አልዳነም፡፡ ሦምሦን ጉራው አልጠቀመውም፡፡ ጀግናው በርግጥም ጊዜ እንጂ ሰው አይደለም፡፡ አየነው፤ ለየነው፡፡ ከታሪክም ተማርን፡፡ ከመለስና ከመንግሥቱ፣ ከሂትለርና ከሙሶሎኒ፣ ከቢዝማርክና ከእስታሊን፣ ከኃየሎምና ከአሣምነው፣ ከአብዲሣና ከጃጋማ ኬሎ፣ ከታዬ ባልኬርና ከደምሤ ቡልቶ… የበለጠ ጀግናና ጠንካራ ነኝ ካልክ ይቅናህ፤ በጅምርህ ግፋበት፡፡ ነገር ግን መጥፎ አጋጣሚ ወይም ዕድሜ ከዚህች ከምትወዳት ዓለም ባላሰብከው ቅጽበት ይለዩሃል፡፡ መነጽርህን አስተካክልና ዙሪያህን ቃኝ፡፡ እንደመጽሐፉ ኅያው ቃል ሁሉም ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው ወንድማለም፡፡ ከማዕበሉ ማዶ መገናኘት ከቻልን ያኔ ይህንና ሌላውንም በዝርዝር  እናወራዋለን፡፡

(በነገራችን ላይ የወያኔ ጊዜ ቀስ በቀስ እየመጣች ነው፡፡ ኢንተርኔት በፕሮክሲ መጠቀም ጀምረናል፤ በገፍ መታሰር ጀምረናል፣ እሥር ቤቶችን በተረኛ የጎሣ ኮታ መሙላት ጀምረናል፤ በየመዝናኛውና መጠጥ ቤቱ አምና በተረኛው ቋንቋ ሰዎችን እስክናደነቁር እንጮህ ነበር – (ትልቅ የማነስና የዝቅተኝነት ምልክት!) –  አሁንም በዚያው ፋሽን አጠገባችን ለሚገኝ ሰው ከቤት ውጪ ላለ ሰው እንደምንናገር ያህል በተረኛ ልሣን እየጮህን አካባቢን በትዕቢትና በማን አለብኝነት መበጥበጥና ማወክ ጀምረናል፤ ብዙ ነገሮችን ከወያኔ እያስታወስን በተሻሻለ መንገድ መገረብ ጀምረናል፡፡ ገና ደግሞ ብዙ ይቀረናል፡፡ ሁሉንም ሳንኮርጅማ እንዴት ተደርጎ!  የገደሉም የባህሩም፣ የምድሩም የሰማዩም አጋንንት ለምን ይክፋቸው!)

በአምናው ዘመን በአንድ ወቅት በአንድ ወታደራዊ ቫን(ተሸከርካሪ) ተሣፍሬ የመሄድ ዕድል ገጥሞኝ ነበር – ከ18 ዓመት በፊት፡፡ ከሹፌሩ በስተቀር ከአሥር የሚበልጡት ተሣፋሪዎች የሚነጋገሩበት ቋንቋ የአንድ ጎሣ ሆኖ እነሱም ሙሉ በሙሉ ከዚያ ጎሣ የወጡ ነበሩ፡፡ በጣም ነበር የገረመኝ፡፡ በዚያው ዘመን በብዙ የፖሊስና የመከላከያ ቢሮዎች ሄጃለሁ፡፡ ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር፡፡

አሁንስ? ያው ነው፡፡ የሚገርመው ግን የጊዜው ፍጥነት ነው፡፡ የአምናው ሥርዓት ትንሽ ይሉኝታ ነበረው ማለት ነውና ያን የመሰለ የራሱን ሰዎች የመሰግሰግና ሌሎችን ከጨዋታ ውጭ የማድረግ አስቀያሚ ድርጊት ለማናወን 20 ምናምን ዓመታትን ፈጅቶበት ነበር፡፡ የዘንድሮ ግን ምን እንደታየው አላውቅም አፋጠነው፡፡ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ የትም ግባ ከየትም ውጣ ከላይ እስከታች የምታገኘው በተለይ በኃላፊነት ቦታ የሚገኝ ሰው የአንድ ጎሣ አባል ነው፡፡ ነገሩ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ማውረድ ያቅታል ማለት አሁን ነው፡፡እንዲህ የምለው እውነቱን ለመናገር እንጂ አንዱን ከአንዱ ለማጋጨት ወይ ለማጣላት አይደለም- ፈጽሞ፡፡ እውነትም እንደውበት እንደተመልካቹ ናትና ብትቃወመኝ አልፈርድብህም፡፡ ግን ልብ ይስጥህ፡፡

እባካችሁን – ወደላይ ስትወጡ አወራረዳችሁ እንደሚያምር አድርጋችሁ ውጡ፡፡ ቀን ሰጠኝ ብሎ መጃጃል ለተጃጃለና መልክ ለሌለው አወዳደቅ ይዳርጋልና ጊዜ አገኘን ብላችሁ የምትፈነጥዙና አይሠሩ ሥራ የምትሠሩ ወገኖች ረጋ በሉ፤ ትንሽ ሰከን በሉ፡፡ ሱቅ እንደገባ ሕጻን አትሁኑ፡፡ ሁሉ ነገርም አይመራችሁ፡፡ ጥቂት እንኳ ለመሰንበት ግራና ቀኝን አይቶ መጓዝ ጠቃሚ ነው፡፡ ሁሉን የወደደ አንዱንም ሊያገኝ የማይችልበት መጥፎ ሁኔታ እንደሚገጥመው ተረዱ፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባልና በጀመራችሁት መንገድ ያዋጣናል ብላችሁ ከቆረጣችሁ እንደመለስ ዜናዊ “መንዳቸሁን ጨርቅ ያድርግላቸሁ” ብዬ ከመመረቅ በስተቀር ሌላ ምርጫ የለኝም፡፡ መጨረሻችሁን ግን እኔ ብቻ ሳልሆን ጡትና ጡጦ ያልጣለ ሕጻንም ያውቀዋል፡፡ የአምባገነኖችን የመጨረሻ ዕጣ ለመገንዘብ በግድ 60 እና 70 ዓመታትን በምድር ከክፉዎች ጋር እየኖሩ መሰቃየት አያስፈልግም፡፡ ማስተዋል ጠፋ’ይ ግልጽ ነው፡፡

በተቃውሞም ይሁን በድጋፍ፣ እርስ በርስ በመጠላለፍም ይሁን በሤራ ፖለቲካ፣ በእንፍጠንም ይሁን በእንዘግይ የአካሄድ ሥልት ልዩነት፣ በውጫዊም ይሁን በውስጣዊ መቺ ኃይል… በየትኛውም ጎራ ተሠልፈውና የተባለውም ይሁን ያልተባለው – የተገለጠውም ይሁን የተደበቀው – ብቻ የትኛውም ዓይነት ግድያ ተፈጽሞባቸው በሰው እጅ ሕወታቸው ያለፈ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር፡፡ እኛም ወደነሱው ነን፡፡ ነገር ግን የዓለም መሣቂያ ከመሆን ፈጣሪ ይታደገን፡፡ በቶሎ ደርሶልንም እንደድንጋይ የደደረውን ልባችንን እንደበሰለ ፓፓያ ያላላልን፡፡ “በቅሎ ‹አባትሽ ማን ነው?› ቢሏት እናቴ ፈረስ ነች” እንዳለችው ቢጤ – በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እኛው በኛው እየተጨራረስን በ12ኛው ክፍለ ዘመንና ከዚያም በፊት በተሠራ ታሪክ መኩራራትና ትንሽ ሆነን ሳለ ትልቅ ነን ማለት ዕብደት እንጂ ጤንነት አይደለምና የአመራር ቦታውን አለዕውቀትና አለጥበብ የያዛችሁ ዜጎች እባካችሁን – ስለእግዜር ብላችሁ – በየሥርቻው ለሚገኙ የተማሩና የበቁ ዜጎች ስጡ፡፡ ጣማችሁም መረራችሁም ለዛሬ ይህን አልኩ፡፡

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop