መግቢያ፤
ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው የፈረስ ስማቸው “አባ ናዳ” ስለ ተሰኘው ስለ ቀኛዝማች ድልነሣሁ ጠንፉ የሕይወት ታሪክ ነው። በቤተዘመዳቸውና በሌሎችም ሰዎች ይታወቁ የነበረው እራሳቸውም በድርሳነ ሚካኤላቸው መግቢያ የተጠቀሙት በፈረስ ስማቸው ስለነበረ ከዚህ ቀጥሎ አባ ናዳ በሚለው ስያሜያቸው እጠቀማለሁ።
ቀኛዝማች ድልነሣሁ ጠንፉ
የአባ ናዳ ትውልድ፤ ሸዋ ውስጥ ሲጠር በሚባለው አካባቢ እንደሆነ ይነገራል። የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዝርያ ናቸው። የልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ቁጥር በትክክል ባይታወቅም በመቶዎች እንደሚቆጠር ይገመታል። ለጊዜው የተገኘው የዘር ሐረግ ሰንጠረዥ አባሪ ሆኖ ቀርቧል። አባ ናዳ የልዑል ራስ መኰንን አባት የደጃዝማች ወልደ ሚካኤል አብሮ አደግ ነበሩ። ልዑል ራስ መኰንን፤ አባ ናዳን ያከብሯቸውና “አጎቴ” ይሏቸው ነበረ። ሁለቱ በሚነጋገሩበትም ጊዜ ልዑል ራስ መኰንን አባ ናዳን “አያ” ይሏቸው እንደ ነበረና አባ ናዳም ልዑል ራስ መኰንንን “አንተ” እንደሚሏቸው እንመለከታለን።
አባ ናዳ ከቅርብ ዘመዳቸው ከልዑል ራስ መኰንን ወልደሚካኤል ጋር በመዝመት ሐረርጌ በቅኝ ገዥዎች እንዳትያዝ ካደረጉት ጀግኖች አንዱ ናቸው። ዓረቦች፣ እንግሊዞች ፣ ፈረንሳዮችና ኢጣልያኖች ሐረርጌን ለመያዝ አሰፍስፈው በነበረበት ጊዜ በአጼ ምኒልክ ብልሕና ፈጣን እርምጃና አመራር በነራስ መኰንንና አባ ናዳ ቆራጥነት ሐረርጌን ለማዳን ችለዋል። አባ ናዳ መኖሪያቸውን ጃርሶ ጎሮ አድርገው በልዑል ራስ መኰንን መሪነት ሐረርጌ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍለ-ግዛት ጋር የነበራት ትስስር እንዲጠናከር አድርገዋል። ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) የተወለዱትና እድሜያቸው ሶስት ዓመት እስኪሆን ድረስ የነበሩት በአባ ናዳ የበላይ ጠባቂነትና አሳዳጊነት በጃርሶ ጎሮ ነበር።
አባ ናዳን አስደናቂ የሚያደርጋቸው ሌላው ከፍ ያለ ቁምነገር በ1889 ዓ/ም ከራስ መኰንን ጋር ኢጣልያ ተጉዘው ከልዑካኑ ጋር በመሆን በጊዜው ከነበሩት ከንጉሥ ኡምቤርቶና ከኢጣልያ መንግሥት ጋር በመደራደር የውጫሌው ውል እንዲጸድቅ መደረጉ ብቻ ሳይሆን ከኢጣልያኖቹ በተገኘው ብድር ብዙ የጦር መሣሪያዎች ለኢትዮጵያ ያስገኙ መሆኑ ነው። የውጫሌው ውል ጠንቅ የአድዋ ጦርነትን ሲያስከትል እነአባ ናዳ ያስገኙት የጦር መሣሪያ ለኢትዮጵያ ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ መሆኑ የታወቀ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነልዑል ራስ መኰንንና የነአባ ናዳን ግሩም የሆነ የዲፕሎማሲ ውጤት ሁልጊዜም ሊያስታውሰው የሚገባ ነው።
እነአባ ናዳ ኢጣልያ በነበሩበት የሶስት ወር ጊዜ 11 ከቶሞችን በመጎብኘት ብዙ ኢንዱስትሪዎችንና ድርጅቶችን ለመመልከት ችለዋል። ከኢጣልያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም በኢየሩሳሌም አልፈው በእቴጌ ጣይቱ ትእዛዝ መሠረት ንብረት ገዝተዋል።
ከታሪክ በማጣቀስ የጥንቷ ኢትዮጵያ ግዛት ሰፊ እንደ ነበረና ከውስጥና ከውጪ በደረሰባት እክሎች ስለ ተከሰተው ሁኔታ ጽሑፉ ባጭሩ ይዳሳል። እንደሚታወቀው፤ አጼ ቴዎድሮስና አጼ ዮሐንስ በቀደዱት ፈር አጼ ምኒልክም በመቀጠል የኢትዮጵያን አንድነት ያጠናከሩና ግዛቷንም እንደ ጥንቱም ባይሆን ያስፋፉ ታላቅ መሪ ነበሩ። በጊዜው ከነበሩት የአጼ ምኒልክ አጋሮች አንደኛው ልዑል ራስ መኰንን ሲሆኑ የርሳቸው ቅርብ ዘመድና ደጋፊ ደግሞ አባ ናዳ ነበሩ። ስለዚህ እነአባ ናዳ ለኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ በተለይም በኢጣልያኖች ከተሰነዘረባት የቅኝ አገዛዝ ጠንቅ ያዳኗት ጀግኖች መሆናቸውን ከታሪክ ጠቀስ በማድረግ ለማስገንዘብ እሞክራለሁ።
አባ ናዳ በጊዜው ከነበሩት ታላላቅ መኳንንት አንዱ የነበሩ መሆኑንና ለሐገራቸው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱ ጀግናና ዲፕሎማት እንደ ነበሩ በማስረጃ የተደገፈ ሐተታ ከዚህ ቀጥሎ ይቀርባል።
ምሥጋና፤
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረበው የዘር ሐረግ ሰንጠረዥ የተገኘው በወ/ሮ የምሥራች በዛብህ እርዳታ ፎቶግራፎቹ ደግሞ በሮቤርቶ ባሩቲ ከፍ ያለ ድጋፍ በመሆኑ ለሁለቱም ጥልቅ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም ጽሑፉን ተመልክተው ጠቃሚ ሐሳቦችን ያቀረቡልኝን ዶር. ግርማ ዓለማየሁንና አቶ ፈቃደ ሥላሴ በዛብህን አመሠግናለሁ።
1.የአባ ናዳ ትውልድ፤
1.1 “ዛቲ ጦማር ዘቀኛዝማች አባ ናዳ” በማለት ብራና ላይ በድርሳነ ሚካኤል መጽሐፋቸው መቅድም የሚገኘው ጽሑፋቸው ትውልዳቸውን ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ይጀምርና እንደሚከተለው ይዘረዝራል፤ (1)
“አጤ ዘርእየ ያዕቆብ አጤ በእደ ማርያምን ወይዘሮ ከላላን ንብለ ድንግልን ወለዱ። ጅን ከለላ የማማን ልጅ እራስ ድልድይን አገባችና አብተ ገብርኤልን ወለዱ፤ አብተ ገብርኤል ዘጌን ወለደ፤ ዘጽጤናን አገባና ይማኖን ልብሰን ወልዩን ሰናን ጣያን ወለደ።
ይማኖ የተጉለቴን ልጅ ሰናን አገባና መንበሮን እመት ውስቴናን መሥዋዕትን መልከ ማርያምን ቃለ አብን ጊኔን ወለደ። ዓመቴን ተሌላ ወለደ። መንበሮ እሩትን ይኩኖን ቅድስቴን ኢሳይያስን ተአውቆን ወክሰሰን ሸበጧትን ወለደ። እሩት አቅሎምን ወለደ፤
እኩት ያስራትን ልጅ ወልዶ ሳላን አገባና ሳለሞትን ወለደ። ሳለሞት ጥዱን አገባና አደሩን አይቼሽን ወለደ። አደሩ አማከለችን አገባና ጠንፉን አየልሃቸውን ሴፉን ወለደ ጠንፉ አባ ናዳን ንግሩን በሻህ ውረድን ወለደ።
1.2 የአባ ናዳ ጽሑፍ ይቀጥልና በጊዜው ስለ ተከሰተው የወንድማማች የአመራር ይገባኛል ንትርክና ስለ ተደረገው ውሳኔ እንደሚከተለው ይገልጻል።(2)
“ለዘጌ ልጆች አለቃ ይማኖ። ለይማኖ ልጆች አለቃ መንበሮ። ለመንበሮ ልጆች አለቃ እሩት። ለእሩት ልጆች አለቃ አቅሎም። ለአቅሎም ልጆች አለቃ እኩት፤ ለእኩት ልጆች አለቃ ሳለሞት። ለሳለሞት ልጆች አለቃ አደሩ። ለአደሩ ልጆች አለቃ ጠንፉ። ለጠንፉ ልጆች አለቃ አባ ናዳ።”
1.3 የአባ ናዳን ተወላጆች ዝርዝር የሚያሳየውን ሰንጠረዥ ለማየት የሚፈልግ የሰምናወርቅ አዘጋጆችን በመጠየቅ ማግኘት ይችላል።
1.4 አባ ናዳ የሞቱት መስከረም 12 ቀን 1895 ነበር።(4) የሞቱት በ115 አመት አድሜያቸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ይኸውም፤ ይህ ጸሐፊ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥራ በመጋቢት 1964 ዓ/ም ወደ ሌሶቶ ሊሄድ ሲል በክቡር አቶ እንዳልካቸው መኰንን፤ በጊዜው የመገናኛና የትራንስፖርት ሚኒስትርና የቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ ሊቀመንበር፤ አማካኝነት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ለመሰናበት ቀርቦ ስለነበር አባ ናዳ ያረፉት በ115 ዓመታቸው መሆኑን በቃላቸው አረጋግጠውለት ስለነበር ነው። በዚህ መሠረት አባ ናዳ የተወለዱት በ1780 ዓ/ም ነበር ማለት ይቻላል።
. እ.አ.አ. በ1889 ወደ ኢጣልያ የተጓዘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ናፖሊ ከተማ የተነሳው ፎቶ
- ኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎች በነበሯት በአንደኛው ሺ ዘመነ ምሕረት፤
እነአጼ ካሌብን የመሳሰሉ ጠንካራ መሪዎች በነበሩዋት ዘመን የኢትዮጵያ ግዛት ያሁኑን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የመንንና የዛሬዋን ሳውዲ ዓረቢያን እስከ መካ ድረስ ያጠቃልል ነበር። በሶስተኛው ምእት ዓመት በጊዜው ከነበሩት የዓለም አቀፍ ሃያላን አንደኛዋ ኢትዮጵያ ነበረች።(5) ሌሎቹ ታዋቂ ኃያላን ቢዛንቲየም እና ፋርስ (ያሁኗ ፐርሺያ) ነበሩ። የኢትዮጵያ ጦር አሁን ሳውዲ ዓረቢያ በሚባለው ሐገር፤ ዛእፈርና ናግራን በተሰኙ ከተሞች ውስጥ ይገኝ ነበር።(6)
በመጀመሪያው ሺ ዘመነ ምሕረት፤ የኢትዮጵያን ኃያልነት ከሚያመለክቱት ክስተቶች፤
(ሀ) በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት፤ እ.ኤ.አ. በ523 እና በ525 ዓ.ም በ230 መርከቦች በመጠቀም ከ70፣000 እስከ 120፣000 ጦር አዝምተው፤ ዛእፈርና ናግራን ከተሞች ውስጥ 3000 ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈውን ወደ አይሑድነት የተለወጠ የዓረብ ልዑል ያንበረከኩበት ታሪክ ነው(7)
(ለ) ሌላው ታሪካዊ ተግባር፤ የጦር ሰፈሩንና የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛቱን ሰንዓ፤ የመን አድርጎ የነበረው አብርሃ የተባለው የጦር መሪ በመካ ከተማ ላይ ያከናወነው ወረራ ነው። ስለዚህ ወረራ፤ ባሁኑ ዘመን እንኳ ዓረቦች የሚተርኩትና በሌሎች ጸሐፊዎች የተዘገበው ሐቅ የተለያዩ ናቸው። እነሥርግው ሐብለ ሥላሴ የዘገቡት (8) የወረራው ምክንያቶች፤
– አንድ ከመካ የመጣ ዓረብ ሰንዓ በነበረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያሰጸይፍ ተግባር በማከናወኑ፤
– መካ ውስጥ ተስፋፍቶ የነበረው የጣኦት ማምለኪያ እንዲወድም እና
– የመካ ንግድ ወደ ሰንዓ እንዲዛወር ለማድረግ ነበር።
በዝሆን ታጅቦ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር መካ ሲደርስ ሊቋቋመው የሚችል ኃይል አልነበረም። ሆኖም ጦሩ ጠንቀኛ በሆነ ተላላፊ በሽታ ስለ ተጠቃ ወደ ሰንዓ ለመመለስ ተገደደ። በዓረቦቹ በኩል እስካሁን እየተነገረ ያለው “አም አልፊል” በተሰኘው የቁራን ምእራፍ ተዘግቦ ይገኛል። በዚህ መሠረት፤ ኢትዮጵያዊው ጦር መካ እንደ ደረሰ በወፎች አማካኝነት በዘነበበት ጠጠሮች ጦሩ እንደ ተጨፈጨፈ ተተርኳል።(9) መታሰብ ያለበት ትልቅ ቁም-ነገር፤ በዚያን ጊዜ፤ ኢትዮጵያውያን በአንድ አምላክ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሲሆኑ የመካ ሰዎች ጣኦት አምላኪዎች የነበሩ መሆኑን ነው። ወረራው የተከናወነው፤ ነቢዩ መሐመድ በተወለደ እ.ኤ.አ በ570 ነበረ። ለማንኛውም፤ የመንና አካባቢዋን ይቆጣጠር የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ማእከሉን ሰንዓ አድርጎ ለ50 ዓመት እዚያ እንደ ቆየ ተዘግቧል።(10)
- የኢትዮጵያ ሕብረት መላላትና ያስከተለው ጠንቅ፤ በ2ኛው ሺ ዘመን፤
የአክሱም መንግሥት እየተዳከመ ሲሔድ፤ መጀመሪያ በፋርስ መንግሥት አማካኝነት ኢትዮጵያ ከየመንና ከአካባቢዋ ተባረረች። ከዚያ ቀጥሎም የእስላም ሃይማኖት ተከታይ ዓረቦችና ቱርኮች ዙሪያዋን ከበቧት። በ1030 ዓ.ም የዛግዌ ዘመነ መንግሥት ተተክቶ፤ እስከ 1270 ዓ/ም ቆየ። ከዚያም ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ተተክቶ በእነ ንጉሥ ይስሐቅ (1413-30)፤ ንጉሥ ዳዊት (1380-1412)፤ እና ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ (1434-68) አማካኝነት የኢትዮጵያን ግዛት ያስፋፋ መሆኑ ቢታወቅም፤ የመሳፍንት አገዛዝ ሲተካ ያስከተለው መከፋፈልና መዳከም ለኮሎኒያሊስቶች፤ ማለትም ለኦቶማን ቱርኮች፤ ከዚያም ወደ ሁለተኛው ሺ ዘመነ ምሕረት መገባደጂያ ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች፤ በተለይም ለእንግሊዞች፣ ለፈረንሳዮችና ለኢጣልያኖች ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ኢትዮጵያ ጠረፎችዋን ተነጥቃ ጅቡቲ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የተሰኙ አዳዲስ ሃገሮች ተፈጠሩ። ይህ አልበቃ ብሏቸው፤አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ መሪነታቸውን የጀመሩት ኮሎኒያሊስቶች ኢትዮጵያን በሙሉ ቦጫጭቀው ለመያዝ በሚሽቀዳደሙበት ጊዜ ነበር
- ሐረርጌ በኮሎኒያሊስቶች ከመያዝ ስለ መዳኗ፤
ሐረርጌን ለመያዝ ቋምጠው የነበሩት፤ ዓረቦች ብቻ ሳይሆኑ በአካባቢው ያንዣብቡ የነበሩት፤ ኢጣልያኖች፤ ፈረንሳዮችና እንግሊዞች ነበሩ። ይህንኑ ቀድመው የተገነዘቡት፤ አጼ ምኒልክ፤ በስተደቡብና በስተምሥራቅ በኩል የነበረው የኢትዮጵያ አካል በቅኝ ገዢዎች እንዳይያዝ በወሰዱት ፈጣን እርምጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት ዋና ዋና መሪዎች ውስጥ ልዑል ራስ መኰንንና አባ ናዳ ይገኙበታል።
“አጤ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሐፉ፤ ጳውሎስ ኞኞ እንዲህ ይላል፤
“ግብጾች ሐረርጌን የያዙት በ1867 ነው። ኢትዮጵያ በመሳፍንት አገዛዝ ተከፋፍላ ሁሉም የእለት ጥቅሙን ያሳድድ በነበረበት ጊዜ ክፍት በር ያገኘው በራኡፍ ፓሻ የሚመራው 1200 ወታደሮች ያለበት የግብጽ ጦር በቀላሉ ሐረር ገባ።”(11) በ1879 ዓ/ም በንጉሥ ምኒልክ በራሳቸው የተመራው፤ በላምበራስ መኰንን (በኋላ ልዑል ራስ) የነበሩበት ጦር ወደ ሐረር የገሰገሰው ሐረርጌ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኗን ለአውሮፓ መንግሥታት ለማሳወቅና አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ባላቸው እቅድ መሠረት ወደ ሐረርጌ ጦር ቢልኩ ውጊያው ከምኒልክ ጋር መሆኑን ለማሳወቅ ጭምር ነበር። ለማንኛውም፤ ንጉሥ ምኒልክ የሐረርጌን ግዛት ኢትዮጵያውነት አረጋግጠው፤ ጥር 18 ቀን 1879 ዓ/ም ለበላምበራስ መኰንን የደጃዝማችነት ማእረግ ሰጥተው፤ “የሐረርጌ የበላይ ገዢና የወታደር ሹም” ብለው ሾሙዋቸው። ከዚያ በሗላ የካቲት 1 ቀን ከሐረር ተነስተው የካቲት 28 ቀን 1879 ዓ/ም ዋና ከተማቸው አዲስ አበባ ገቡ።(12) አባ ናዳም ከራስ መኰንን ጋር ከዘመቱት መኳንንት አንዱ ስለ ነበሩ ሥራቸውንና ኑሮአቸውን በሐረርጌ፤ በተለይም በጃርሶ ጎሮ (13) አካባቢ አድርገው ቀጠሉ።
- ቀኛዝማች አባ ናዳ በሐረርጌ፤
“ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)” በተሰኘው የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት መጽሐፍ ስለ አባ ናዳ የዓይን ምስክርነት ያለው ማስረጃ ቀርቧል። ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ከጻፉት(14) የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች መገንዘብ ይቻላል፤
(ሀ) ቀኛዝማች አባ ናዳ የራስ መኰንን ዘመድና አጋራቸው ነበሩ። “ከከምቦልቻ እስከ አብዱላ ሠረርታ ድረስ ያለው የደጋው አገር በቀኛዝማች አባ ናዳ እጅ ሆኖ፤ ፊትም የራስ ፈረሶችና በቅሎች ማስቀለቢያ፤ በሗላም ለእመይቴ (ወይዘሮ የሺመቤት፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እናት) መኖሪያ፤ ቆይቶም ለተፈሪ (በሗላ አጼ ኃይለ ሥላሴ) ማሳደጊያ እንደጉልት ተደርጎ ነበር።”(15)
(ለ) ወይዘሮ የሺመቤት (የራስ መኰንን ባለቤት) ተፈሪን (በኋላ አጼ ኃይለ ሥላሴ) የተገላገሉት ጃርሶ ጎሮ ነበር። የሞቱትም በሚወልዱበት ጊዜ፤ እንግዴ ልጁ አልወጣ ብሎ በአለቃ ሀብተ ማርያም ትእዛዝ፤ አዋላጃቸው በእጇ ጎትታ ለማውጣት ስትሞክር በደረሰባቸው ሥቃይ ነው።(16)
(ሐ) ተፈሪም እድሜያቸው ሶስት ዓመት እስኪሞላ ድረስ ያደጉት በአባ ናዳ ጥበቃ ነበር። ፊ/ተክለ ሐዋርያት እንደ ጻፉት፤
“ተፈሪ የሚባለው የራስ ልጅ ሊመጣ ነው፤ ቀኛዝማች አባ ናዳ ቤት የሚያሠሩት ለሱ ነው እየተባለ ሲወራ ሰማሁ። ልጁን እስከ ዛሬ ድረስ ቀኛዝማች አባ ናዳ ደብቀው ሲያሳድጉት ቆይተው አሁን ካባቱ ጋር ለመኖር ሊመጣ ነው ተባለ።” (17)
(መ )አባ ናዳ ይምሉ የነበሩት በአጼ ሣህለ ሥላሴ የነበረ መሆኑንና ሲናገሩ አፋቸውን ያዝ ያደርጋቸው እንደ ነበረ ፊ/ተክለ ሐዋርያት እንደሚከተለው ዘግበዋል፤
ራስ መኰንን፤ “አያ፤ የተፈሪ ቤት አለቀለት?”
አባ ናዳ፤ “ዬ ዬ ዬ ማለቁ ነው፤ በቶሎ እንዲገባበት አደርጋለሁ።
ሣ ሣ ሣ ሣህለ ሥላሴ ይሙት አላቆይበትም።”
(ሠ) አባ ናዳ ሰው ሲጠቃ የማይወዱ፤ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ርህሩህ ሰው ነበሩ። (18)
“ራስና አብዩ የማይስማሙ ሆኑ…….አንድ ቀን ለጃንሆይ (ለአጼ ምኒልክ) ደብዳቤ ሲያጽፉት፤ ሁለቱ ብቻ ተቀምጠው ሲነጋገሩ፤ ራስ ከተቀመጡበት ስፍራ እመር ብለው ተነሡ፤ ከፊታቸው የነበረውን ትንሽ ደወል (ያሽከር መጥሪያ) አንሥተው ወረወሩበት፤ ራሱን ሊፈነክቱት ነበር። ለጥቂት አመለጠ።……….”ና ማናዬ ዝም ትለኛለህ፤ በልልኝ ጣለው ግረፈው!” የግቢው ሰዎች አብዩን ይወዱታል። ተጨነቁ። አቶ ማናዬ እጁን ያዘውና ጭፍሮቹን ጠራ። አብዩን ሊገርፉት ከመሬት ላይ ጣሉት። እኔ ሲገረፍ
ዐይኖቼ እንዳያዩብኝ ጆሮቼ እንዳይሰሙብኝ ሸሸሁ። ቀኛዝማች አባ ናዳ በቶሎ ደረሱ። አብዩ ጀርባ ላይ ታዘሉና እላዩ ተጋደሙ። “ዬ ዬ ዬ እኔን ግረፉኝ…” እያሉ ጮሁ። ቀኛዝማች አባ ናዳ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሎሌ ነበሩ። የደጃዝማች ወልደ ሚካኤል አብሮ
አደግ ናቸው። ራስ ያከብሯቸዋል። (አያ ይሏቸዋል። አቋራሽ ናቸው። ራስን አንተ ይላሉ) መናገር ሲጀምሩ አንደበታቸው በጣም አይታዘዝላቸውም። ስለዚህ “ዬ ዬ ዬ” ብለው ይጀምራሉ፤ ልማድ ሆኖባቸዋል። ወዲያው ፊታውራሪ በንጉሤም ደረሱ። ……… እንደዚህ አብዩ በገላጋዮች ብርታት ከመገረፍ ዳነ።…..”
(ረ) ራስ መኰንንና አባ ናዳ በጣም ይቀራረቡ ነበር።
“ጧት ጧት ራስ መጽሐፋቸውን ደግመው ሲጨርሱ ቀኛዝማች አባ ናዳ
እየገቡ ይገናኛሉ።”
- የአባ ናዳ የዲፕሎማሲ አስተዋጽኦ፤
6.1 ሰኔ 24 ቀን 1857 ዓ/ም፤ ወጣቱ ምኒልክ (በኋላ አጼ) በአቶ ገርማሜ (በኋላ ደጃዝማች) አማካኝነት ከአጼ ቴዎድሮስ እሥር ቤት ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ ከገቡ በሗላ ተቀናቃኞቻቸውን አሸንፈው ሥልጣናቸውን አደላድለው ያዙ።
6.2 መጋቢት 3 ቀን 1881 ዓ/ም አጼ ዮሐንስ መተማ ላይ በደርቡሾች ከተገደሉ በኋላ ከራስ መንገሻ በተቀር ሌሎቹ፤ እንደ ንጉሥ ሚካኤል፤ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፤ ራስ ወልደ ሥላሴ፤ ወዘተ. የነበሩት ዋና ዋናዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ገቡላቸው።
“ከዚህ በሓላ ያጤ ዮሐንስ የነበረ መኳንንት ሁሉ፤ ከራስ መንገሻ ዮሐንስና ከራስ አሉላ በቀር ተመተማ እየገሰገሰ ላጤ ምኒልክ ገባ።”(19)
አጼ ምኒልክ፤ የኢትዮጵያ መሪነታቸው የሰመረላቸው ቢሆንም፤ የቀሩትን ተቀናቃኞቻቸውን ለመቋቋም መሣሪያና የውጭ ድጋፍ ስላስፈለጋቸው፤ “የውጫሌ ውል” የተሰኘውን ሀያ አንቀጾች የነበሩትን ሰነድ በኢጣሊያኑ በፒዬትሮ አንቶኒሊ አማካኝነት ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ/ም ተፈራረሙ።(20) አጼ ምኒልክ ወዲያውኑ ጊዜ ሳይወስዱ ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ/ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው ዘውዳቸውን ተቀዳጁ።(21)
6.3 ከውጫሌው ውል በስተጀርባው የነበረው ዓለማ፤ በአጼ ምኒልክ በኩል የኢትዮጵያ መሪነታቸውን በኢጣልያ ድጋፍ ለማረጋገጥ ሲሆን፤ በሗላ በአድዋ ጦርነት እንደ ተረጋገጠው፤ በኢጣልያኖች በኩል ግን ኢትዮጵያን በሙሉ (ኤርትራን ጭምር) የነሱ የቅኝ ግዛት ለማድረግ ነበር። በተለይ፤ የውጫሌው ውል፤ አንቀጽ 17፤
“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከኤውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ፤ በኢጣልያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል።” ተብሎ በአማርኛው የተዘገበውን በኢጣልያንኛው ትርጉም፤ ኢትዮጵያ የኢጣልያኖችን የበላይነት የተቀበለች አስመስለው ዓላማቸውን ለመፈጸም እርምጃ መውሰድ ጀምረው ነበር።
6.4 አጼ ምኒልክ፤ የውጫሌውን ውል በፈረሙበት እለት አባ ናዳም ከራስ መኰንን ጋር እዚያው ውጫሌ ነበሩ። ፔትሪዲስ እንደ ጻፈው፤(22)
አጼ ምኒልክ፤ “…..ከሰዎቻችን ሁሉ የበለጠውን ሰው መርጠን መላክ አለብን። ምክንያቱም ጉዳዩ ጥበብ የሚያስፈልገውና በጣምም አስቸጋሪ ነው። አጎት የምንሆነውን ሰው፤ ወንድማችንና ወዳጃችን የሆነውን ደጃዝማች መኰንን ወልደ ሚካኤልን እንሾማለን። …..ሌሎቹንም አብረውት የሚሔዱ መልእክተኛ(ኞች) እሱ ራሱ ይምረጥ። እነዚህን ያጸድቁ ዘንድ እኛ ለኢጣልያ ንጉሥ ደብደቤ እንጽፋለን”….ከዚያም በሗላ ሁለቱ (አጼ ምኒልክና ደጃዝማች መኰንን) በጣም ዝቅ ባለ ድምፅና በለዘበ አንደበት ንግግር ጀመሩ።
ደጃዝማች መኰንን ውጪ ከወጡ በኋላ፤ “…..ወደ ኢጣልያ በማደርገው ጉዞ ከናንተ ሠላሳ ሰዎች ተከትለውኝ ይሔዳሉ። የነፍስ አባቴን ወልደሚካኤልን፤ አጎቴን አቧዳን (አባ ናዳን)(23)፤ አጎት የምሆነው ዘመዴን ቢራቱን፤ ቀኛዝማች ናደውንና ባላምበራስ ደሳለኝን ቶሎ መንገድ ይገቡ ዘንድ አስጠንቅቋቸው። በተቻለ መጠን ቶሎ እንነሳለን።”6.5 ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደ ዘገቡት፤ (24)
ከደጃዝማች መኰንን ጋር ወደ ኢጣልያ የተጓዙት ዋነኞቹ የሚከተሉት ነበሩ፤
1ኛ. አባ ወልደ ሚካኤል – የንስሐ አባት
2ኛ. ቀኛዝማች አባ ናዳ (የደጃዝማች መኰንን የቅርብ ዘመድ)
3ኛ. ፊታውራሪ ቢራቱ
4ኛ. ግራዝማች ዮሴፍ (አስተርጓሚ)
5ኛ. ግራዝማች ደሳለኝ (በዓድዋ ጊዜ ፊታውራሪ ናቸው)
6ኛ. ባላምበራስ ነገሜ (በሗላ ቀኛዝማች ቀጥሎ ደጃዝማች)
7ኛ. ባሻ ቆለጭ (በሗላ ፊታውራሪ ተብለው የቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ ሞግዚት የነበሩት)
6.5 አባ ናዳ በኢጣልያ፤
6.5.1 አባ ናዳ፤ ደጃዝማች መኰንንን አጅበው ከሐረር እ.አ.አ. ሐምሌ 20 ቀን 1889 በመጓዝ ነሐሴ 2 ቀን ዘይላ፤ እና ነሐሴ 21 ቀን ናፖሊ፤ ኢጣልያ ደረሱ። በየደረሱበት ታላቅ የክብር አቀባበል ተደረገላቸው።(25) ከዚያም፤ ወደ ሮማ ተጉዘው እ.ኤ.አ. ነሐሴ 28 ቀን 1889 ልዑካኑ ከኢጣልያ ንጉሥ ኡምቤርቶ ጋር ተገናኙ። የጉዞው ዋና ዓላማ የውጫሌው ውል በኢጣልያ መንግሥትና ንጉሥ ኡምቤርቶ አንዲጸድቅ ለማድረግና በተጨማሪም፤ ከኢጣልያ መንግሥት ብድር በማግኘት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን የጦር መሣሪያ ለመግዛት ነበር።(26)
6.5.2 ለደጃዝማች መኰንንና ለነአባ ናዳ በሮም ስለ ተደረገላቸው እጅግ አስደናቂ አቀባበል ብዙ ተጽፏል። ነገር ግን በዚህ ጸሐፊ አሰተያየት፤ ሥፍራው ተገኝተው የዓይን ምስክርነታቸውን ያቀረቡት አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ (በሗላ ቢትወደድ) ከሁሉም የደመቀና በጥንቱ የተዋበ አማርኛ የተዘገበው እንደሚከተለው ይነበባል።(27)
“…..ደጃች መኰንን አርባ ሰው አስከትለው ወደ ኢጣልያ አገር ተሻገሩና
የኢጣልያ ንጉሥ በክብር ሮማ ላይ ተቀበላቸው። ያቀባበሉ ነገር በቃል
ተናግሮ የሚጨርሱትና ጨርሶ በቃል የሚአስረዱት ነገር አይደለም። ግሩም
እጹብ ድንቅ ነበረ። እስከ ረፋድ መንገድ ከሁለት እልፍ የበለጠ ጦር
ተሰልፎ በጣልቂአ በጣልቂአው ባለ ሙዚካ ተሳክቶ ቁሞ መለኸቱ ነጋሪቱ
እምቢልታው ሁሉ እየተነባበረ እየተመታ በመካከሉ ደጃች መኰንን እስከ
ሰዋቸው በባለ በባለ ብር ጥሩር ሽልሜ ሰቀላ ሰቀላ በሚአካክል ፈረስ
ተቀምጦ ተቀምጦ ደንገላሳ እየጋለበ ከንጉሡ አዳራሽ ደረሰ። ያ ሁሉ
የንጉሥ ሽልሜ ከናት ማሐፀን እንደ ሰው የወጣ አይመስልም ነበረ።
ብቻ በተለየ ሁለት ሁለቱን መዘዞ አንድነት እየጨፈለቁ ያበጁት ይመስል
ነበረ። በግራ ክንዱ ጎሽ በቀኝ ክንዱ ዘሆን ለግቶ አላግቶ የሚጥል ይመስል
ነበረ። ይሄው ሽልሜ የንጉሡ ዘበኛ ከንጉሡ ዙሪአ የማይለይ ምርጥ ሎሌ
ነው። ይሄው ምርጥ ዘበኛ ደረቱ በክንድ ቁመቱ በገመድ የሚሰፈር የመሳሰለ
ሽልሜ ነበረ። ከንጉሡ አዳራሽ ሲደረስ ከደጃፉ ላይ ግራና ቀኝ የየጁን
በርበሬ የመሰለ ጁህ ጁሁን ለብሶ ቅዱና ቅጡ ባበሻ ያልታወቀ ኩፍታ
ኩፍታውን አድርጎ የብር የብር ጐመዱን ይዞ አጋፋሪ ቁሞ ነበረ። ደጃች
መኰንን እስከ ሰዋቸው ተሰረገላ ወረዱና ከዚያ ሁሉ ሰልፍ መካከል
ወዳዳራሹ ገቡ። ካዳራሹ ጥልቅ ሲገባ ከበረዶ የነጣ የዕብነ በረድ ደረጃ
ወለል ብሎ ይታይ ነበረ። በዚያ ወለላ ሰፊ ደረጃ ላይ በመካከሉ ተመልካም
ከፈይ የለሰለሰ ወላንሳ ተነጥፎበት ነበረ። ከደረጃው መካከል ብቅ ሲባል
የሰማይ ስባሪ የመሳሰለ መስተሀት ዙሪአ ዙሪአውን እንቁጣጣሽ በመሰለ
ወርቅ ተጣፍጦ ላይን ያሰክር እራስ ያዞር ነበረ። የቀረውን ታገራችን ታይቶ
የማይታወቀውን ሕብር የሌለውን ሁሉ ላይን እንደሳት የሚፋጀውን እንደ
ጮራ የሚዋጋውን ደፍሮ ለማየት የሚቸግረውን በየገጹ በየሳንቃው
በየመስኮቱ በየወለሉ በየምኑም ሁሉ ያለውን ጌጥ ላየም ይግረመው ላላየም
ይቍጨው ለሰማም ይጭነቀው እንጂ በስሙ ለማስረዳት ላገራችን
አይታወቅም። በዚህ መሀል ለመሀል ደጃች መኰንን ሙሉ መሳርያቸውን
አድርገው ሰዎቻቸውም አጊጠው አምረው ሄዱ ሄዱና የጉግሥ መጫወቻ
ከሚአህል ወለል በደረሱ ጊዜ ሁለት ሶስት ጊዜ ለጥ፣ ለጥ ብለው እጅ ነሱ።
ከዚያ ካዳራሽ ወለል መሀል የኢጣልያ ንጉሥ በሽልሜው ታጥሮ በመኳንንቱ
በሹማምቱ ተከቦ የመንግሥት ልብሱን ለብሶ ከመንበረ መንግሥቱ ላይ
ተቀምጦ ነበረና እንዴት ዋላችሁ እንኳን ደህና ገባችሁ! አሰኘ። ከዚህ ወዲያ
ከመንበረ መንግሥቱ እንደ ተቀመጠ የኢትዮጵያንና የኢጣልያን ፍቅር ነገር
ቃሉን በወረቀት አድርጎ ይዞ ነበርና አንብቦ ለደጃች መኰንን አሰማ። ንጉሡ
ወዲያው አፈፍ ተነሣና ለደጃዝማች መኰንን እጁን ሰጠ ቀጥሎም
ለፊታውራሪ ቢራቱ ሰጠ። ያ ግርማው የሚአንቀጠቅጥ ፍቅሩ የሚአሳስብ
ደግ ንጉሥ ኡምበርቶ ቀዳማዊ ደስ ብሎት ደስ አሰኝቶ ያበሻን መልክተኛ
ተቀበለ። ደጃች መኰንን ወዲአው ጃንሆይ የሰደፉትን ቀጸ በረከት ሁሉ
አቀረቡ። ንጉሡ እስከ መኳንንቱ ያን በረከት ከበው ደስ ብሏቸው አዩ።
ተሁሉ ደስ ያሰኛቸውና እንደ ግሩም ያሰደነቀ አንድስ አንድስ ያህል ታይቶ
የማያውቅ ሁለት የዝሆን ጥርስ ነበረና ያ ነው። ደጃች መኰንን ከኢጣልያ አገር እስከ ሰዎቻቸው እየተ(ን)ከበከቡ በደስታ ሮማ ላይ ተነሐሴ እኩሌታ እስከ ህዳር ድረስ ተቀመጡ።”
6.5.3 አባ ናዳና የቀሩት ልዑካን ኢጣልያ በቆዩባቸው ሶስት ወሮች (ከነሐሴ 1889 እስከ ሕዳር 1890) 11 ከተሞችን፤ ማለት ሚላኖን፤ ኮሞን፤ ቱሪኖን፤ ጀኖቫን፤ ፒያችንካን፤ ቪቼንሳን፤ ቬኒስያን፤ ቦሎኛን፤ ላስፒዝያን፤ ፊሬንሴንና ፒሩጅያን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ጊዜ፤ የኢጣልያንን የመሣሪያ ዓይነት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎቻቸውን ለማየት ችለዋል።(28)
6.5.4 ልዑካኑ በኢጣልያ ያደረጉት ጉዞ በሚገባ ተሳክቶላቸው፤ ደጃዝማች መኰንን ተጨማሪ ስምምነት አከናውነው፤ የ4 ሚሊዮን ሊሬ (29) ብድር ካገኙ በኋላ “28 ባለሰባ ሚሊ ሜትር ጠመንጃዎች፤ 38 000 ጠመንጃዎችና፤ 2 500 000 ጥይቶች የሚገኙበት የጦር መሣሪያዎች ለመግዛት ችለው ጉብኝታቸውን ፈጽመው ከኢጣልያ ተነሱ።
6.6 አባ ናዳ በኢየሩሳሌም በኩል ወደ ኢትዮጵያ መመለስ፤
እነአባ ናዳ ኢጣልያ የሔዱበትን ተልእኮ በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላ፤ “እቴጌ ጣይቱ ኢየሩሳሌም ከጌታችን መቃብር ከጎልጎታ አጠገብ መሬት በ8 000 ብር እንዲገዙ ቀደም ብለው አዘዋቸው ስለነበረ፤ ኢየሩሳሌም ሔደው ነበር።(30) የታዘዙትን ካከናወኑ በኋላ በዚያን ጊዜ አጼ ምኒልክ ይገኙ በነበሩበት መቀሌ ከተማ የካቲት 23 ቀን 1890 ዓ/ም በሰላም ደርሰው ስለ መልእክታቸው ውጤት ዝርዝር ገለጻ አደረጉ።(31) እነአባ ናዳ ባከናወኑት ጉዞ ሁሉ ኢጣልያኑ ካውንት ፒየትሮ አንቶኒሊ አብሮዋቸው ነበረ።
6.7 የውጫሌ ውልና የአድዋው ድል፤
6.7.1 ቀደም ብሎ እንደ ተጠቀሰው፤ ኢጣልያኖች የውጫሌን ውል ሲፈርሙ ዓላማቸው ኢትዮጵያን በሙሉ የቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ ነበር። ይህንንም ለማሳካት የተጠቀሙበት በውሉ በአንቀጽ 17 በአማርኛ የተጻፈው በኢጣልያንኛው ቋንቋ የሰፈረው የተለያየ እንዲሆን በማድረግ ነበር። ለዚሁም መሠሪ ተግባር ተባባሪ እንዲሆኑ ለአስተርጓሚው፤ ለግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ ጉቦ በመስጠት ነበር ቢባልም ምንም ማስረጃ አልተገኘለትም። ለማንኛውም፤ አንቀጽ 17 በአማርኛው ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከሌሎች መንግሥታት ጋር ለምትዋዋለው ጉዳይ በኢጣልያ መንግሥት አማካኝነት መላላክ ትችላለች ሲል፤ በኢጣልያንኛው ቋንቋ ግን በኢጣልያ መንግሥት አማካኝነት ለመጠቀም ተስማምታለች የሚል ነበረ። በዚህም መሠረት፤ የኢጣልያ መንግሥት ለሌሎች ሐያላን መንግሥቶች በሙሉ ኢትዮጵያ በኢጣልያ ጥበቃ ሥር መሆኗን የሚገልጽ ደብዳቤ አስተላለፈ።(32)
6.7.2 እነአባ ናዳ ኢጣልያ በነበሩበት ጊዜ፤ ደጃዝማች መኰንን አንድ ተጨማሪ ውል ፈርመው ነበር። በዚህ ውል መሠረት በኢጣልያና በኢትዮጵያ መሐከል የሚኖረው ወሰን በጊዜው ባላቸው ይዞታ መሠረት ይሆናል የሚል አንቀጽ ነበረበት። ውሉ ሲፈረም ኢጣልያኖች የሚያውቁት እነደጃዝማች መኰንን ያላወቁት፤ የኢጣልያ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ ገስግሶ ደርሶ አድዋን ጭምር የያዘ እንደ ነበር ነው። በዚህ ምክንያት እነአባ ናዳ መቀሌ ሲደርሱ፤ የጠበቃቸው ሁኔታ ዘብረቅ ያለ ሁኔታ ነበረ። ባንድ በኩል፤ አጼ ምኒልክ ደጃዝማች መኰንንን ራስ ብለው ሲሾሙና ሲደግፉ በሌላ በኩል፤ በኢጣልያኖች በኩል የተፈጸመውን ተንኮልና ወረራ ያወቁ ሰዎች፤ በተለይ በራስ መኰንንና በግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ ላይ ወቀሳ አድርሰውባቸው እንዲያውም ጉቦ ወስደው በኢትዮጵያ ላይ ክሕደት ፈጽመዋል እስከ ማለት ደርሰው ነበር።(33)
6.7.3 ስለ አንቀጽ 17፤ በኢጣልያን ቋንቋ የተዛባና አደገኛ ሁኔታ ስለ መከሰቱ በጊዜው ሮም በትምሕርት ላይ የነበሩት አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ (በሗላ በጅሮንድ)፤ የሚከተለውን ዘግበዋል፤
“…..ኢትዮጵያ በኢጣልያ መንግሥት ውስጥ ልትኖር ውል ተደረገ የሚል ወሬ በጋዜታ ላይ ተጣፈ።……ለደጃች መኰንን፤ በኢትዮጵያ ምነው እንዲህ ያለ ክፉ ነገር ተደረገባት ብሎ ነገረ። ደጃች መኰንን ቶሎ ብለው፤ ይሄ ነገር ፍቅራችንን ያደፈርስብናልና ቶሎ ይታረም አይሆንም ብለው ለኮንት አንቶኒሊ ተናገሩ። ወዲያው ደጃች መኰንንና ኮንት አንቶኒሊ ተጣሉ………ኮንት አንቶኒሊ…..በገንዘብ ዝም እንዲል አባበለው የማይሆንለት በሆነ ጊዜ
ግን አይቶ ባደባባይ ከፍና ዝቅ አድርጎ ሰደበው አዋረደው።”(34)
6.7.4 ጳውሎስ ኞኞ በዘገበው መሠረት፤(35)
“…በኢጣልያ አገር ስዕል እንዲማሩ ተልከው የነበሩት ልጅ አፈወርቅ ገብረየሱስ (በኋላ ፕሮፌሰር የሆኑት) በጋዜጣ ያነበቡትን ለራስ መኰንን ነገሩዋቸው። ራስ መኰንንም አስጎብኚያቸው የነበረውን አንቶኒሊን ቢጠይቁት “…..ያ ደደብ ኢትዮጵያዊ ተማሪ ትርጉም ስላልገባው ነው” ብሎ ተሳደበ። ራስ መኰንንም ተቃውምአቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የውሉን መበላሸት ለአጤ ምኒሊክ አሳወቁ።”
6.7.5 ለማንኛውም፤ አጼ ምኒልክ፤ እቴጌ ጣይቱና መኳንንቶቻቸው ስለ ኢጣልያ ተንኮል ግንዛቤ ካገኙ በኋላ ተቃውሟቸውን ለአውሮፓ መንግሥታት አሳወቁ። ክሪስ ፕራውቲ እንደ ጻፈቺው፤ እቴጌ ጣይቱ በአንድ ስብሰባ ላይ፤ “ተነሱ የትግሬና የጎንደር ሰዎች፤ ከኢጣልያኖችጋር ልንዋጋ ነው” ብለው ሲናገሩ ወንድማቸው (ራስ) ወሌ ቁጭ ብለው ስለ ነበር “ቀሚሴን እንካ እኔ ሱሪህን እለብሳለሁ” አሉዋቸው ተብሏል።(36)
6.7.6 እንደሚታወቀው፤ የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ጠንቅ የአድዋን ጦርነት አስከትሎ፤ በአጼ ምኒልክና በነራስ መኰንን አመራር፤ ኢትዮጵያ አንድ ሐያል የአውሮፓ መንግሥት፤ ኢጣልያን፤ ድል አድርጋ ነጻነቷን ለመጠበቅ ቻለች።
6.7.7 በዚህ ጸሐፊ ግንዛቤና አሰተያየት፤ በተለይ ሊተኮርበት የሚገባው ነጥብ፤ ኢጣልያኖች፤ የውጫሌን ውል እንደ ምክንያት ሊጠቀሙበት ሞከሩ እንጂ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ ወስነው ከዚሁ ዓላማቸው ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ። እነራስ መኰንንና እነአባ ናዳ ያስገኙት ትልቁ ቁምነገር በደጃዝማች መኰንን ጥበባዊ ዲፕሎማሲ ባገኙት ብድር በኢጣልያኖች በራሳቸው ገንዘብ የጦር መሣሪያና ጥይት በአስደናቂ ጀግንነት አድዋ ላይ ድል ማድረጋቸው ነው!
ስለ አድዋው ጀግንነት፤ በጊዜው ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ ከተደረሱት ብዙ ግጥሞች፤ ጥቂት ስንኞች፤
“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይኸን ጊዜ አበሻ።
በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈጠመ ጣልያን አበሻ እንዳይደርስ።
መድፉን መትረየሱን ባድዋ መሬት ዘርቶ
እንክርዳዱን ነቅሎ ስንዴውን ለይቶ
የዘራውን እህል አጭዶና ወቅቶ
ላንቶኒሊ አሳየው ፍሬውን አምርቶ።
እንዳቀና ብሎ ለምኖ መሬት
ንግድ ሊያሰፋበት ሊዘራ አትክልት
እየመጣ ሊሰጥ ግብሩን ለመንግሥት
ለጓዙ ማረፊያ አገር ቢሰጡት
ተጠማኝ ሰንብቶ ሆኖ ባለርስት
ወሰነ እየገፋ ጥቂት በጥቂት
እውነት እርስት ሆነው ተቀበረበት።
ባሕር ዘሎ መምጣት ለማንም አትበጅ
እንደ ተልባ ስፍር ትከዳለች እንጂ
አትረጋምና ያለተወላጅ።”(37)
7. መደምደሚያ፤
7.1 ቀኛዝማች አባ ናዳ (ድልነሣሁ ጠንፉ)፤ ትውልዳቸው ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ የሆነ፤ የራስ መኰንን አጎት እና የቅርብ አጋር የነበሩ ሰው ናቸው።
7.2 ቀኛዝማች አባ ናዳ ከሚታወቁባቸው ዋና ዋና ተግባሮች ውስጥ፤
• ከራስ መኰንን ጋር በመዝመት ሐረርጌን በኮሎኒያሊስቶች ከመያዝ
ማዳናቸው፤
• በኢጣልያ በተሳተፉበት አስደናቂ ዲፕሎማሲና በተገዛው የጦር መሣሪያም የአድዋው ድል በመገኘቱ፤ ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ቅኝ ተገዢነት ማትረፋቸው፤
* ተፈሪ መኰንን (በኋላ አጼ ኃይለ ሥላሴ) እድሜያቸው ሶስት ዓመት
እስኪደርስ ጃርሶ ጎሮ አሳድገው በኋላም ከምቦልቻ (ሐረርጌ) ቤት
አሠርተው አባታቸው ራስ መኰንን አጠገብ እንዲያድጉ ማድረጋቸው
ነው።
7.3 ቀኛዝማች አባ ናዳ ለሃገራቸው ያከናወኑት አስተዋጽኦ ጀግናና ዲፕሎማት የሚያሰኛቸው ነው። የ115 እድሜ ባለፀጋ ስለ ነበሩ ከራስ መኰንን ጋር ለኢትዮጵያ የሚበጁ ሌሎች ቁምነገሮች ሳያከናውኑ እንዳልቀሩ ይገመታል። ስለዚህ በሕይወት ካሉት ሌሎች የልጅ ልጆቻቸው ማስረጃ ከተገኘ መጋራቱ በጣም ይጠቅማል።
ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ፤ የአባ ናዳን ነፍስ ይማርልን።
የግርጌ ማስታወሻዎች፣
(1) ግልባጩ አባሪ ሆኖ ቀርቧል። በብራና የተዘጋጀው መጽሐፍ ዋናው በታደሰ ሐይሌ እጅ ነበረ።
(2) ስለዚህ ውሳኔ በአንዳንድ የአባ ናዳ ተወላጆች ይነገር የነበረ ሐተታ አለ። በልጅ ኢያሱ ዘመን ደጃዝማች ተፈሪ (በኋላ አጼ ኃይለሥላሴ) የሲጠርን አመራር አለአግባብ ይዘዋል በማለት የአባ ናዳ ልጅ ሐብተ ሚካኤል ክስ አቅርበውባቸው ነበር። ነገር ግን ልጅ ኢያሱ ተወግደው ንግሥት ዘውዲቱ ሲተኩ ደጃዝማች ተፈሪ አልጋ ወራሽ ሆነው የመንግሥቱን ሥልጣን ስለያዙ ጉዳዩ ደብዛው ጠፋ። ሐብተሚካኤልም ራስ እምሩ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ሊያስማሟቸው ቢሞክሩም አሻፈረኝ እንዳሉ አቃቂ ኖረው አረፉ።
(3) ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ፤ “ዜናሁ ለራስ መኮንን”፤ 1965 ዓ/ም (ፈቃደሥላሴ በዛብህ ከጠቀሰው)
(4) Levine, Donald, “Greater Ethiopia”, 1974, ፤ ገጽ 7::
(5) Hable Selassie, Sergew, “Ancient and Ethiopian History to 1270”, 1972, ገፅ 121::
(6) ዝኒ ከማሁ ገፅ 128-137::
(7) ዝኒ ከማሁ ገፅ 151-153::
(8) Ali, Yusuf A., “The Holy Quran”, 1934, ገፅ 1791::
(9) Miles, S.B., “The countries and Tribes of the Persian Gulf”, ገፅ 2::
(10) ጳውሎስ ኞኞ፤ “አጤ ምኒልክ”፤ ገጽ 40:: የግብጾቹ ዓላማ ሐረርን ብቻ ለመያዝ ሳይሆን ከዚያ ለጥቀው፤ በሸዋ አቋርጠው የአባይ ወንዝን ምንጭ ሁሉ ለመቆጣጠር ነበር። (Rubenson, Sven, “The Survival of Ethiopian Independence”, 1976, ፤ ገጽ 317)
(11 ) ዝኒ ከማሁ ገጽ፣42-45::
(12) ይህ ጸሐፊ፤ በ1941 ዓ/ም፤ ከአባቱ ከአቶ ዓለማየሁ ገብረ ሚካኤል ጋር ሆኖ አባ ናዳ ይኖሩበት የነበረውን ጃርሶ ጎሮን ጎብኝቶ ነበር።
(13) ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም፤ “ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)”፤ 1998፤ ገጽ 45-53::
(14) በቅንፎቹ ያሉት ቃላት የዚህ ጸሐፊ ናቸው።
(15) ተክለሐዋርያት ተክለማርያም: ገጽ 46::
(16) ”ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ”፣ በተሰኘው መጽሐፋቸው (ገጽ 1-5)፤ ቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ ስለ ሕጻንነታቸው ጊዜ ሲጽፉ ሐምሌ 16 ቀን 1884 ኢጆርሳ ጐሮ መወለዳቸውን እንጂ ከቀኛዝማች አባ ናዳ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አልጠቀሱም። በሗላ ስለ ሲጠር ጉዳይ ባጋጠመው ንትርክ ምክንያት ይሆን?
(17) ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም፤ “ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)፣ 1998፤ ገጽ 42-5::.
(18) አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፤ “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ”፣ 1901፤ ገጽ 57::
(19) ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ “ዐጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” 1983፤ ገጽ46::
(20) ዝኒ ከማሁ ገጽ 70::
(21) ፔትሪዲስ፤ ኤሰ. ጴጥሮስ፤ “የአድዋው ጀግና የልዑል ራስ መኰንን ታሪክ” 1961፤ ገጽ 86-87
(22) ዝኒ ከማሁ ገጽ፣. 87; (ፔትሪዲስ “አቧ ዳን” ያለው በሕትመት ስሕተት ወይም በጸሐፊው አለማወቅ ሳይሆን አይቀርም። ለማንኛውም አባ ናዳን ማለቱ እንደ ነበረ ግልጽ ነው።)
(23) ተክለጻድቅ መኩሪያ፤ “አጸ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” ፤ ገጽ 54::
(24) op.cit, p. 90::
(25) Battalia, Roberto, “La prima Guerra d’Africa”, 1958, ፤ ገጽ 285::
(26) አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፤ “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ”፤ 1901፤ ገጽ 66-69::
(27) ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ “አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” ገጽ 57::
(28) አበበ ሐይለመለኮት፤ “The Victory of Adowa and what we owe to our heroes”, 1998, p. 74
(29) Op. cit., p. 58; (እንደዚሁም፤ ፔትሪዲስ፤ “የአድዋው ጀግና”፤ ገጽ 103.)
(30) ዝኒ ከማሁ ገጽ፣59. (አንቶኒሊ ወደ ሮማ ካስተላለፈው ቴሌግራም)
(31) ዝኒ ከማሁ ገጽ 79::
(32) Prouty, Chris, “Empress Taytu and Menilek II”, 1986, pp. 69-70
(33) አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፤ “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ”፤ 1901፤ ገጽ 70-71። (በዚህ መሠረት፤ አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ፤ ደጃዝማች መኮንን ስለ አንቀጽ 17 የኢጣልያኖች ተንኮል አላወቁም ነበር ያሉት ትክክል አይመስልም። “አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት”፤ ገጽ 83)
(34) ጳውሎስ ኞኞ፤ “አጤ ምኒልክ”፤ 1984፤ ገጽ 143::
(35) Prouty, Chris, “Empress Taytu and Menilek II”, ፤ ገጽ 71 ::(ወደ አማርኛ እንደ ተረጎምኩት)
(36) ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት”፤ 1983፣ ገጽ 506::
Abstract:
Abba Nada: Ethiopian Diplomat and Hero/ አባ ናዳ (የኢትዮጵያ ዲፕሎማትና ጀግና)
The article is produced in Amharic with the following main contents by Kidane Alemayehu.
Abba Nada is the nom de guerre of Kegnazmach Dilnessahu Tenfu. He also used “Abba Nada” to refer to his name in his prayer book. Members of his family also refer to him as Abba Nada.
Abba Nada was a close relative and friend of Emperor Haile Selassie’s grandfather, Dejazmach Woldemikael. HH Prince/Ras Mekonnen, Emperor Haile Selassie’s father, used to refer to him as “Aggotae” meaning my uncle.
Abba Nada is known for his heroic service to Ethiopia during the reign of Emperor Minelik II in the successful campaign for saving the Harer province from being colonized by the British, the Italians and other aspiring colonialists.
He also rendered a historic and an important diplomatic service as a member of the Ethiopian delegation that had travelled to Italy following the signing of the Wuchale Treaty by Emperor Minelik II and Italy’s representative, Pietro Antoneli, in 1889. An important result of that diplomatic visit to Italy was the fact that a loan of 4 million Lire was obtained part of which was used to purchase military equipment that was eventually applied in the war of Adwa and the historic Ethiopian victory against the Italian invasion.
Another important service rendered by Abba Nada was to host HH Prince/Ras Mekonnen’s wife, HH Princess Yeshimebet, who gave birth to Teferi (later Emperor Haile Selassie I) at Abba Nada’s residence at Ejersa Goro. Teferi was under the care of Abba Nada at Ejersa Goro until he was three years old after which a house was constructed for him by Abba Nada at Kembolcha (also known as Melkarafu), a small town not far from Harer.
The article also provides some insights about Abba Nada’s personal characteristics using various reliable sources.