ሃገሬ ናፈቀኝ ወንዟ ሸንተረሯ
ናፈቀኝ ሃገሬ ነፃነቷ ክብሯ
ትዝታ ኑሮዋ ባህል ቁም ነገሯ ።
ያሳለፍኩት ሁሉ እየመጣ በእውኔ
እንቅልፌንም ነሳኝ ተሰማኝ ኩነኔ ።
መንደሬ ሰፈሬ አስፋልት ኮረኮንጁ
ቂማውና ጨብሲው > ጠላውና ጠጁ ።
ከረንቦላው ኳሱ ድራፍት ካቲካላው
ብትለው ብትጠጣው ሆድን የማይሞላው።
ጣፋጭ ትዝታዋ ሃገሬ ናፈቀኝ
እራቀኝ ሄደብኝ ከቶውን ላይገኝ ።
ከቤላ ፈረንሳይ ስድስት ኪሎ ሄጄ
ጭንቀት ሳይኖርብኝ ሽቅብ ታች ወርጄ።
የኖርኩበት ዘመን ላይገኝ መልሶ
ሊታለፍ የማይችል ፍፁም ተደባብሶ ።
ሃገሬ ናፈቀኝ ሰላምሽ ትዝታሽ
ቀድሞ የነበረው ወዘና ቁመናሽ ።
ከቶ ይናፍቀኛል እንዴት ልሁን ታዲያ
አልፈልግም ልትሆኝ ብቻ መቀበሪያ ።
ስደት የተባለ ወረርሽኝ ውጦኝ
ከሰፈር ቀበሌ ከጓደኛ አርቆኝ ።
ሃገሬ ናፈቀኝ ሆድ ባሰኝ ዘንድሮ
የማይወጣ ነገር ልቤ ውስጥ ተቀብሮ ።
ጭራሽ አይረሳም ፈረንሣይም ቤላ
ፍቅር የሞላበት ያደግኩበት ሁላ ።
ዜሮ አምስት ውቅያኖስ ቀጭ ቀጭ ሃሰን ሱቅ
በቡዜ ቀብራራው የነበረንን ሳቅ
እንዴትስ ይረሳል ለምንስ አይናፍቅ ።
ጃልሜዳ ወጥቼ ቅሜ ተጫውቼ
ጨፋናው ቴዲዬን ሃረሩን አግኝቼ
በቁኮ እና ለጌ ሻለቃን አውርቼ ።
የሽፌ ጨዋታ ጌቾ ትህትናው
የፈረንጅ አፉ የቋንቋ ችሎታው
ወልድዬ ወላሞ ነብስህን ይማረው ።
ሳቅና ጨዋታው ተካፍሎ መብላቱ
ትዝ አለኝ ሃገሬ ትዝ አለኝ የጥንቱ
ሃገሬ ናፍቆቱ ሃገሬ ስስቱ
ርቆ የሄደን ሰው ወይ ማሰቃየቱ ።
ጃልሜዳ አራት ኪሎ ቶታል ስድስት ኪሎው
የነ አይሰጬ ፈድሉ ሺሰማ ትዝታው
የጊቢው ተማሪ መጥተው ተኮልኩለው ።
ጠረባ ትረባው በአረንጓዴ ምላስ
ያ ጊዜ ተገኝቶ ምነው ባይበላስ ።
ለመርሳት ብሞክር ዜሮ አምስትን ከልቤ
ጃልሜዳ ጉልትን ላወጣው ከቀልቤ
አልሆንልህ አለኝ መጣ በምናቤ ።
ነበረኝ ብዙ ሙድ መገናኝ ገርጂ
ብዙ የሚናፍቀኝ የኖርኩበት ደጅ ።
ጉለሌ ጋሽ መጋል ወርቁ ሸክላ ሄጄ
ጳውሎስን አልፌ ኳስ ሜዳ ወርጄ ።
ኢዲዩን ጎብኝቼ ስሄድ ዳትሰን ሰፈር
የክትፎውን ጣባ ዮሃንስ ስንሰብር ።
በቅዳሜ ጠዋት ሾሌ ነጭ ጠላ በዞረ ጢንቢራ
ጨጓራው ተበልቶ ደልቶን ስናጓራ
ሃገሬ ናፈቀኝ የአራት ኪሎ ቢራ ።
ሰብለ ቤት ጨልጬ ሶሎ ቤት ስሸና
ይገቤ አልማዝ ቤት የጆሊ ባር ቡና ።
ካሳንቺስ ክትፏችን ከተማ ቤት ቢራ
የመጨረሻዬን ቺርስ ያልኩበት ተራ ።
ከወዳጆቼ ጋር የመለየት ለቅሶ
በአረቄና ቢራ ፍፁም ተለውሶ ።
ከቶ አይረሳኝም ነብስ ይማር መንግስቱ
ተጫዋች አሳቢ አንተ የኔ ከንቱ ።
ተቃቅፈን ተላቅሰን የሸኛችሁኝ ግዜ
ተክሎብኝ የቀረው ሃሳብ ከትካዜ።
ሼህ ዑመር ባህሩ ብሬ እና ውዶቹ
ከቶ እንዴት አድርጌ ከልቤ ላውጣችሁ ።
አርቆ የሸኘኝ ላይመልሰኝ ግዜ
ሃገሬ ናፈቀኝ ተጫነኝ ትካዜ።
የኤጀርሳ ጎሮ የጎድን ጥብስ ሽታ
የታምራትን ቤት ኡኡታ ጫጫታ ።
ትዝ አለኝ ሃገሬ ናፈቀኝ መንደሬ
ስጎነጭ ስጨልጥ ከናፋቂው ወሬ ።
ፍፁም አይረሳም የአራት ኪሎ መንገድ
ከሥራ በኋላ ያለው መንጎራደድ ።
በሞት ያጣዋቸው ወዳጅ ዘመዶቼ
ከቶ ላልረሳችሁ በልቼ ጠጥቼ
ከነጫጮቹ ምድር ጠፋሁኝ ሰስቼ ።
ጥዬው እንዳልመጣ እሩጬ ፈርጥጬ
የያዘው ይዞኛል ዝቅ አርጎኝ ከአገጬ ።
አይመስለኝም ነበር ልቆይ እንዲህ እርቄ
በሃገር በህዝቤ ሁሌ ተጨንቄ ።
ልብ አቅም ሲደክም ሲወርህ እርጅና
ይናፍቃል ቀዬ የሰፈር ጓደኛ ።
ግና ለምን በኔ ስደት ጨከነሳ
ወይስ እኔ ፈራው አበዛው ወቀሳ ።
ሃገሬ ናፈቀኝ ወንዟ ሸንተረሯ
ናፈቀኝ ሃገሬ ነፃነቷ ክብሯ
ትዝታ ኑሮዋ ባህል ቁም ነገሯ ።
ሜይ 2019
ግርማ ቢረጋ / ስቶክሆልም