Ghion/March 22, 2019 [email protected]
አገራችን አሁን ያለችበት ወቅት አገር አቀፍ ሆነ የወረዳ ምክር ቤት ምርጫ ማካሄድ አገሪቱን ለከፋ አደጋ መጋበዝ ነው:: የሚቀጥለውን አገር አቀፍ ምርጫ እንዲተላለፍ በማድረግ የሽግግር መንግስት ማቋቋም መፍትሄ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: ምርጫው የሚተላለፍ ከሆነ ገዢው ፖርቲ ፖርላማውን መበተን እና የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት እና ስልጣን ለማጋራት ሥራ ቢጀምር::
እንደ አንድ የጨነቀው ኢትዮጵያዊ የሚከተለውን ሃሳብ ማቅረብ እወዳለው:: ይህ ሃሳብ ዳብሮ ለአገራችን አማራጭ መፍትሄ ከሆነ ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው:: በተጨማሪ የውይይት ሃሳብ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: በተረፈ አገራችን በምርጫ ምክንያት ከሚመጣ የከፋ አደጋ ይጠብቃታል::
1. አንጋፋ ፖለቲከኞችን (ከ 60 አመት እድሜ በላይ የሆኑ) በክብር እንዲሸኙ ማድረግ:: አንጋፋ ፖለቲከኞች በገዛ ፈቃዳቸው ከፖለቲካ አመራርና አባልነት ጡረታ እንዲወጡ ማበረታታት:: • ከውጪ ወደ ሃገር የተመለሱ እና አገር ውስጥ ላሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች (ከ 60 አመት እድሜ በላይ የሆኑ) ከፖለቲካ በገዛ ፈቃዳቸው ጡረታ ከወጡ o የአገራችን አቅም ባገናዘበ መልኩ መንግስት ጡረታ የሚጦሩበት ገቢ መስጠት o ቤት ለሌላቸው በሕይወት እስካሉ ድረስ የሚኖሩበት የመንግስት ቤት ወይም በስጦታ መልክ መኖሪያ መስጠት ቢቻል:: ይህንን መንገድ ለሚከተሉ ከ2-3 ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ከፖለቲካ አመራር ለቀው ለመንግስት ማሳወቅ አለባቸው:: በዚህ ጊዜ ውስጥ ያላመለከተ ከእድሉ ተጠቃሚ አይሆንም::
2. የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በየክልሉ ብዙ ደጋፊ ይኖራቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ከ 2-3 ፓርቲዎች ለምሳሌ : • ትግራይ – 2 ፓርቲ (ሕወአት (TPLF), አረና (ARENA)) • አፋር – 2 ፓርቲ (የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ANDP), የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (ARDUF)) • አማራ – 2 ፓርቲ (የአማራ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ADP), አብን (NAMA))
• ኦሮሚያ – 3 ፓርቲ (የኦሮሞ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ODP), የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (OLF), ኦፌኮ (OFC)) • ሶማሌ – 2 ፓርቲ (የሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ESPDP), ኦጋደን ብሔራዊ ነጽነት፡ ንባር (ONLF)) • ቤን ሻንጉል ጉሙዝ – 2 ፓርቲ (የቤንሻንጉልና ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ አንድነት, 2nd Party) • ደቡብ (የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ, 2nd Party) • ጋምቤላ – 2 ፓርቲ (የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ, 2nd Party) • ሐረር – 3 ፓርቲ (Harari People’s Democratic Party (HPDP), የኦሮሞ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ODP), የዜግነት ፖለቲካ ፖርቲ) • ድሬ ዳዋ – 3 ፓርቲ (የሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ESPDP), የኦሮሞ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ODP), የዜግነት ፖለቲካ ፖርቲ)) • የዜግነት ፖለቲካ – 1 ፓርቲ (በምሥረታ ላይ) • አዲሳ አበባ – ሁሉም ፖርቲዎች
3. የወረዳ, የህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤት ወንበር ድልድል
• የክልል እና ወረዳ ምክር ቤት መቀመጫ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እኩል ወንበር:: እዲሁም የዜግነት ፖለቲካ ለሚያራምዱ 5% መቀመጫ መስጠት::
• ለፌድራል ህዝብ ተወካዬች በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ፖርቲዎች እኩል ወንበር:: ክልሉ ከ100 በላይ የፌድራል ወንበር ካለው የዜግነት ፖለቲካ ለሚያራምዱ 5% መቀመጫ መስጠት::
• አዲስ አበባን በተመለከተ የከተማውን ህዝብ ብሔር ስብጥር በሚመጥን መልኩ የከተማው ምክር ቤት, የፌድራል እና ወረዳ ምክር ቤትን ወንበር ማከፋፈል:: ለእያንዳንዱ ብሔር በክልላቸው ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እኩል ማካፈል::
• ድሬ ዳዋ: 3 የፌድራል መቀመጫ አላት:: ለሶማሌ (ESPDP), ኦዴፓ እና የዜግነት ፖለቲካ ፖርቲ ማካፈል:: የከተማና ወረዳ ምክር ቤት ወንበር ለሶማሌ (ESPDP), ኦዴፓ እና የዜግነት ፖለቲካ ፖርቲ እኩል ማካፈል::
• ሐረር: 2 የፌድራል መቀመጫ አላት:: Harari People’s Democratic Party (HPDP) ኦዴፓ ማካፈል:: የከተማና ወረዳ ምክር ቤት ወንበር ለHPDP, ኦዴፓ እና የዜግነት ፖለቲካ ፖርቲ እኩል ማካፈል::
• ደቡብ ክልል: የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በክልሉ ለሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝብ ብዛትን ያማከለ ተመጣጣኝ የክልል እና የፌድራል ምክር ቤት መቀመጫ እንዲሰጥ:: እዲሁም የዜግነት ፖለቲካ ለሚያራምዱ 5% መቀመጫ መስጠት::
4. መንግስትን ማን ይምራ የፌድራል ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ያገኘ ግንባር ወይም ጥምረት ምክር ቤቱ የሚጠይቀውን ወንበር መጠን ካሟላ ካቢኔ ማዋቀር ይችላል:: በተጨማሪ ይህ ግንባር ወይም ጥምረት የግድ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የአማራና ኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ ሊኖሩት ይገባል:: የአማራና ኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ የሌለው ግንባር ወይም ጥምረት መንግስት እንዲመሰርት መፈቀድ የለበትም:: መንግስትን የሚመራው ካቢኔ አወቃቀር የእያንዳንዱን የግንባሩን ወይም ጥምረት አባል ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫ ቁጥርን ያማከለ ሊሆን ይገባል::
5. ፓርላማው አገሪቷ የተሟላ ዲሞክራሲያዊ ተቋም እንዲኖራት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በተቀመጠው ጊዜ መንግስት ፍኖተ ካርታውን መተግበሩን መቆጣጠር ከዋና ስራዎቹ አንዱ እንዲሆን::
6. የፌድራል ምክር ቤት፣ የከተማና ወረዳ ምክር ቤት የ5 አመት እድሜ እንዲኖረው ቢደረግ::
7. የአዲስ አበባ የስራ ቋንቋን በተመለከተ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮሚኛ፣ ትግሪኛ እና ሶማሊኛ እንዲካተቱ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት::
አመሰግናለው Ghion2008