June 5, 2018
11 mins read

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንበሮች – ሙሃዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጠዋት ወደ ቢሯቸው ማልደው ሲገቡ የእንግዳ መቀበያ ክፍሉ ወንበሮች ተሰልፈው ጠበቋቸው፡፡ ነገሩ እንግዳ ሆነባቸው፡፡

የዚህን ቤተ መንግሥት ባሕል ገና አልለመዱትም፡፡

የተለመዱ ችግሮችን ባልተለመደ መንገድ እፈታለሁ ብለው ለተነሡት ጠቅላይ ሚኒስትር ነገሩ ከተለመደውም የወጣ መሰላቸው፡፡

‹ምንድን ነው?› አሉ ሳቅ ይዟቸው፡፡

‹አሰናብቱን› አለ ደንዳሳ ትከሻ ያለው የቆዳ ወንበር፡፡በታሪኩ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ እንግዶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡

‹ለምን? የት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ

‹በቃ እኛንም ጡረታ ያውጡና› አለ ሌላ እምቡር እምቡር የሚል ወንበር፤

የባለሥልጣን መቀመጫ መሆኑን የሥላሴን ዙፋን ከተሸከሙት ኪሩቤል በላይ ይኮራበታል፡፡

‹እንትናኮ እኔ ላይ ነው የሚቀመጠው› እያለ መጎረር ይወዳል፡፡

‹ምን ሆናችሁ› አሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጃቸውን አገጫቸው ላይ አድርገው፡፡

‹እኛ ከመጀመሪያው ስንገዛ ለዚህ ዓይነት ነገር መሆኑን የነገረን የለም፡፡ አሁን እየተሠራ ያለው ከለመድነው ውጭ ነው፡፡

ከተገዛንበት ዓላማ ውጭ ነው፡፡ የመርሕ መደባለቅ እያየን ነው› አለ ባለ ደንዳሳ ትከሻው ወንበር፡፡

‹ለምን ዓላማ ነበር የተገዛችሁት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልሰሙት የቤተ መንግሥት ምሥጢር መኖሩን እየጠረጠሩ፡፡

‹እኛኮ እዚህ ቦታ ብዙ ጊዜ ኖረናል› አለቺ አንዲት ቆንጠር ቆንጠር የምትል ድፉጭፉጭ ወንበር፡፡

‹እዚህ ስንኖር እነማን ይታሠሩ፣ ይባረሩ፣ አገር ጥለው ይጥፉ፤ ምን ዓይነት አሣሪና ጨምዳጅ ሕግ ይውጣ፣ እነማን ይመቱ፣ እነማን ይገለሉ፣

እነማን ይታገዱ፣ እነማን ይወገዱ፣ እነማን ይውደሙ፣ እነማን ይጋደሙ የሚል ነገር ነው ስንሰማ የኖርነው፡፡

እኛ የተገዛነው ይሄን የመሰለ ምክር ሊመከርብን ነው፡፡ እኛ እዚህ ቢሮ ስንኖር የተቀመጡብን ሰዎች በጣም የተከበሩ ናቸው፡፡

እዚህ እኛ ላይ በተመከረ ምክር ስንት አገር ተተራምሷል፤ ስንቱ ታሥሯል፣ ስንቱ ተገድሏል፤ ስንቱ ቀምሷል፣ ስንቱ ነፍዟል፡፡

አሁን የምንሰማው ነገር ግን የሚያዛልቀን አይደለም› አለቺ መሬቱን በስፒል እግሯ እየፈተገች፡፡

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን እርስዎ የሚናገሩት ቋንቋ እኛን ሊገባን አልቻለም፤ ለዚህ ቢሮ አዲስ ቋንቋ ነው፡፡ ለኛም ለወንበሮቹ አዲስ ልሳን ነው፡፡

ስናየው በልሳን እየተናገሩ ይመስለናል› አለ፤ ሁለት ሰው እንዲይዝ ሆኖ የተሠራው አጭሬ ወንበር፡፡

‹እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ፡፡ የማወራው አማርኛ ነው፤ ትግርኛ ነው፤ ኦሮምኛ ነው፤ እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ወደ ውስጠኛው ቢሮ መግባቱን ተዉትና በሩ ላይ ቆሙ፡፡

የጽ/ቤት ኃላፊያቸውና አጃቢዎቻቸው በአግራሞት የሚሆነውን ሁሉ ይከታተላሉ፡፡

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ባለ ደንደሱ ትከሻ፡፡ ‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ይሄ የምናውቀው ቋንቋ አይደለም፡፡

በእርስዎ ደረጃ ሰምተንም አናውቅም፡፡ ምናልባት ዶክተር ሲባሉ ሰምተናልና ከውጭ ተምረውት ያመጡት ይመስለናል፡፡ እዚህ ሀገር እዚህ ቢሮ በዚህ ቋንቋ ሲወራ ሰምተን አናውቅም፡፡

ጭራሽ ማሠር እንጂ መፍታት የሚባል በዚህ ቢሮ መዝገበ ቃላት ውስጥ የለም፡፡

ውጡ እንጂ ግቡ የሚል ቃል አዲስ ነው ያመጡብን፡፡ ተለያዩ መባል ሲገባው ታረቁ፣ ተስማሙ፣ አንድ ሁኑ የሚባል መጋኛ እየመጣብን ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ካሉ ለምን እስከዛሬ እዚህ ቢሮ ውስጥ አልሰማናቸውም?› ባለ ደንደሱ ትከሻ የአንገት መደገፊያውን በኀዘን ነቀነቀው፡፡

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫነት የተዘጋጀው ወንበር፡፡

‹ጭራሽ አሁን ስንሰማማ በሽብር የተከሰሰን ሰው፣ ሞት የተፈረደበትን ሰው መፍታት ሳያንስዎት እዚህ ጠርተው እጁን ሊጨብጡት፤ እኛ ላይ አስቀምጠው ሊያናግሩት ነው አሉ?

ይኼንን ከምናይ ምነው ድሮ ተቀዳደን በወደቅን ወይም በሐራጅ በተሸጥን?

እና ይሄ ሰውዬ መጥቶ የት ሊቀመጥ ነው? ከኛ ማናችንም ብንሆን እንዲቀመጥብን አንፈቅድም፡፡

ለእርስዎም ለስምዎ ጥሩ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርኮ እቆርጣለሁ፣ እፈልጣለሁ፣ አሥራለሁ፣ እቀፈድዳለሁ፣ ሲል ነው የሚያምርበት፡፡

‹እና እንዋጋለን፣ እንሸፍታለን፣ መንግሥት እንገለብጣለን፣ ሲሉ የኖሩት ሁሉ ብረታቸውን እያስቀመጡ እየመጡ ሊቀመጡብን ነው?

ትናንትና እኛ ላይ ቁጭ ባሉት ባለ ሥልጣናት አሸባሪ፣ አደናባሪ፣ አቀናባሪ፣ ሲባሉ እንዳልነበር ዛሬ ዘመን ተቀየረ ብለው መጥተው ሊቀመጡብን?› ሞት ይሻለናል› አለ ሁለት ሰው የሚይዘው አጭሬ ወንበር፡፡

‹ክብራችን ተነክቷል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለቺ ድፉጭፉጯ ወንበር፡፡

‹ጭራሽኮ አሁንማ ቤተ መንግሥቱን ሰው መጎብኘት አለበት እያሉ ነው፡፡

ታድያ በኛና በሰፊው ወንበር መካከል ምን ልዩነት አለው? የቤተ መንግሥት ወንበር በመሆንና የቤት ወንበር በመሆን መካከል ምን ልዩነት ሊኖር ነው?

መከበራችን፣ መታፈራችን፣ መፈራታችን፣ ሊቀርኮ ነው፡፡

ተራውን ሕዝብ ሁሉ ቤተ መንግሥት ጠርተው መጋበዝዎት ሳያንስ ጭራሽ የቤተ መንግሥቱን ቆሌ ገፍፈው ሊያስጎበኙት?

እና የየሠፈሩን ሰዎች እዚህ ግቢ ውስጥ በመስኮት ልናያቸው? ሞተናላ!›

‹ሲደበደብ ከኖረ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ዜማው ሁሉ በለው በለው ይመስለዋል› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

‹አባቶቻችን ድንበር ሲያስከብሩ ኖሩ፤ እርስዎ ግን ድንበሩን ሁሉ ናዱት› አለ ዝም ብሎ ሲመለከት የነበረ በአገልግሎት ብዛት አርጅቶ አናቱ የተላጠ ወንበር› ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውስጥ የሚሰሙትን የስልክ ጥሪ የጽ/ቤት ኃላፊያቸው እንዲያነሣ አዝዘው ማዳመጥ ቀጠሉ፡፡

‹የቱን ድንበር ነው የናድኩት?› አሉት ፈገግ ብለው በትዕግሥት ቆመው፡፡

‹በተቃዋሚና በደጋፊ፣ በገዥና በተገዥ፣ በውጭና በውስጥ መካከል የጸናውን ድንበር ናዱትኮ፡፡ እግዜር ያሳይዎና ኢቲቪና ኢሳት አንድ ዓይነት ዜና እንዲያቀርቡ አደረጓቸውኮ፡፡

አሁን ጭራሽ ውጭ ሊሄዱ ነው አሉ፡፡ ዕንቁላል መወርወሩ ቀርቶ የዕንቁላል ሳንዱች ሊቀርብልዎት ነው አሉ? ከዚህ በላይ ድንበር መናድ የት አለ?› የተላጠ አናቱን አነቃነቀ፡፡

‹እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያሰናብቱን፤ አመለካከታችንን ከምንለውጥ ጾታችንን ብንለውጥ ይሻለናል፡፡

ዐርባ ዓመት ያልሰማነውን ቋንቋ ከምንሰማ – ጡረታ ወጥታችኋል የሚለውን ብንሰማ ይሻለናል፡፡

አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌው አቁማዳ ማስቀመጥ አቁማዳውንም መቅደድ ወይኑንም ማፍሰስ ነው፡፡›

ባለ ደንደሱ ትከሻ ወንበር ወደ ውጭ ሲወጣ ሌሎችም ተከትለውት ወጡ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ብዕሮችና ወረቀቶች ግን ጤና አልተሰማቸውም፡፡

‹እነዚህ ወንበሮች እውን በጤናቸው ነው ቢሮውን ለቅቀው የወጡት? ወይስ በበር ወጥተው በመስኮት ሊመለሱ ነው?› አለ አንዱ እስክርቢቶ፡፡

‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል› አለና ሌላኛው እስክርቢቶ መለሰለት፡፡

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop