May 16, 2018
34 mins read

ሀይማኖት እና ፖለቲካ በኢትዮጵያ – ሰሎሞን ጌጡ

ሰሎሞን ጌጡ ፤ ግንቦት 2018

ሀይማኖት እና ፖለቲካ፡- ለአንድ ማህበረሰብ ብሎም ህብረተሰብ ውጤታማነት እና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም ያላቸው ማህበራዊ ተቋማት ናቸው፡፡ ስለሆነም የነዚህን ሁለት ማህበራዊ ተቋማት ትርጉማቸውን እና እርስ በርስ ሊኖራቸው የሚችለውን ግንኙነት በጥልቀት መረዳት ያሻል፡፡

በጥቅል ትርጉሙ ሀይማኖት/Religion የምንለው ሰዎች በጋራ ተሰባስበው ሥርአተ አምልኮታቸውን የሚፈጽሙበት የተደራጀ ስርአት ወይም ተቋም ማለት ነው፡፡ በሌላ ጎኑ የግለሰቦች የተናጥል የእምነት ደረጃና ጽናት ወይም በግል የሚያደርጉዎቸው ተግባራት እና የህይወት ፍልስፍናቸው መንፈሳዊነት / Spirituality በመባል ይገለጻል፡፡በአንድ ሀይማኖት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ ጥንካሬ እና የእምነት ደረጃ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው መንፈሳዊነት የግለሰብ ጉዳይ ሲሆን ሀይማኖት ግን የቡድን ወይም የጋራ ጉዳይ የሚሆነው፡፡ነገር ግን ሁለቱን ሙሉ ለሙሉ ነጣጥለን ማየት አንችልም፡፡ የሀይማኖት/የተቋሙ ጠንካራ መሆን ወይም መድከም ፡ በስሩ ባሉ ግለሰቦች ህይወት እና መንፈሳዊነት ላይ እንደሁኔታው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ እረኛው ጠንካራ ካልሆነ በጎች በተኩላ እንደሚበሉ ሁሉ፤አንድ ሀይማኖት እንደ ተቋም ጠንካራ አደረጃጀት ከሌለው በግለሰቦች መንፈሳዊ ስኬት ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በተቃራኒው፤ በተዘዋዋሪ መንገድ የግለሰቦች የእምነት ደረጃና እንቅስቃሴ በጥርቅሙ/Collectively የተቋሙ ተልእኮ ውጤታማ እንዲሆን ወይም እናዳይሆን በማድረግ ረገድ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህም በሁለቱ መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳለ እንረዳለን፡፡ ለዚህ ነው ለሁለንተናዊ ሰኬት ሲባል ግለሰቦች በምነታቸው ሲደክሙ ሀይማኖቱ/ተቋሙ መዋቅሩን ወይም ቀኖናውን ተጠቅሞ ምዕመኑን እንደሚያፀና/ችግሩን እንደሚፈታለት ሁሉ፤በግለሰቦች ወይም በሀይማኖት አባቶች ስህተት ምክንያት ተቋሙ ችግር ውስጥ ሲዘፈቅም ምዕመናን እንዲሁ እየተከታተሉ ሊተቹ እና ብልሽቱን ሊያርሙ ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ግን መጨረሻው አብሮ መጥፋት ነው፡፡

ሁለተኛው ማህበራዊ ተቋም ፖለቲካ ሲሆን፤ በግርድፉ ፖለቲካ ማለት በአንድ ቡድን ውስጥ ወይም ከዛ በላይ በሆኑ ቡድኖች/ሀይሎች መካከል ውሳኔ ለመወሰን እና ለማስፈጸም የሚደረግ ሂደትና ትግል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት የተለያየ አመለካከት ባላቸው ግለሰቦች ፣ቡድኖችና ሀገራት መካከል ሀይል /Power ወይም ሥልጣን/Authority ለማግኘት የሚደረግ ፍትጊያ ፖለቲካ ነው፡፡ የተለያየ አተያይ/አመለካከት ባለበት ቦታ ሁሉ ፖለቲካ አለ፡፡ ሰው ደግሞ የተለያየ ባህሪ ያለው ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ይህን ተከትሎ የሚመጣ የፍላጎት አለመጣጣም/ፍትጊያ አለ፤ ይህ ሚጠቁመን ሰው ባለበት ቦታ ሁሉ ፖለቲካ እንዳለ ነው፡፡ በቤተሰብ፣ በእድር ፣በማህበራት፣በሀይማኖት ተቋማት፣በፓርቲና መሰል ስብስቦች ውስጥ ሁሉ ፖለቲካ አለ፡፡ በምንም አይነት መለኪያ የሀይማኖት ተቋማትና አማኞች ከፖለቲካ ነጻ ናቸው ማለት አንችልም፡፡ ፖለቲካ ጥላ ነው ፡ ሰው ባለበት ሁሉ ፖለቲካ አለ፤ ሸሽተን (ፖለቲካና ኤሌክትሪክ በሩቁ ነው ብለን) አናመልጠውም፡፡ ምናልባት ቃሉን በትክክለኛው መንገድ ለመረዳት እንቅፋት የሆነብን ፖለቲካ የሚለው ቃል ባዕድ መሆን ከሆነ፤በእውነትና ሀሰት ወይም በተለያየ አመለካከቶች መካከል የሚደረግ ፍትጊያ ብለን ለኛ በሚገባን መንገድ መግለጽ እንችላለን፡፡ ፖለቲካ ወይም የእውነትና ሀሰት ፍትጊያ ሁል ጊዜ ይኖራል፡፡እኛም ምርጫችን ሁለት ነው፤ወይ ከእውነት ጋር ወግኖ ሀገርን እና ሀይማኖትን ከጥፋት መታደግ፤አለያም ከሀሰትጋር አብሮ ሀገርና ሀይማኖትን ገደል መስደድ፡፡

ሀይማኖት እና ፖለቲካ እንደ ተቋም

ከላይ በመግቢያየ እንደገለጽኩት ሀይማኖትና ፖለቲካ ለአንድ ማህበረሰብ ብሎም ሀገር ጤናማ እና ውጤታማ መሆን ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ የማህበራዊ ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ለራሳቸው ሰፍረው ያዘጋጁት ወይም የተዘጋጀላቸው የየቅል ስራዎችና ተግባራት ቢኖራቸውም ፍጹም ያልተለያዩና እርስ በርስ በበጎ ወይም በመጥፎ ጎኑ ሊመጋገቡ ወይም ሊጎዳኙ የሚችሉ ናቸው፡፡ መቼም ቢሆን በየትኛውም ሀገርና ህዝብ ውስጥ ሀይማኖትና ፖለቲካ ሳይገናኙ ለየቅል ተጉዘው አያውቁም፡፡ በርግጥ የግንኙነቱ አይነትና ደረጃ ሊለያይ ይችላል፡፡ እንዲሁ ግንኙነቱ ለሁለንተናዊ ማህበራዊ ትስስር የሚረዳ ጠቃሚ ፤ ወይም የማይረዳ ጎጂ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ሀይማኖትና ፖለቲካ ተጎዳኝ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው፡፡ የመንግስትና ሀይማኖት መለያየት / Separation of state and religion የሚለው የዲሞክራሲ ስርአት መርሆ የሚገልጽልን በዲሞክራሲ ስርአት ውስጥ መንግስታዊ ሀይማኖት እንደሌለና ግለሰቦች የፈለጉትን ዕምነት የመከተል መብት እንዳላቸው እንጂ፤ ፖለቲካና ሀይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ ማሳያ አይደለም፡፡ በተጨማሪም መንግስተና ፖለቲካ የሚሉት ቃላት የተለያየ ትርጉም እንዳላቸው ልብ ይሏል፡፡

ብዙ ምሁራን የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት በተመለከተ ብዙ አትተዋል፡፡ ጥቂቱን ለመግለጽ ያህል Karl Marx እና የሱ ሀሳብ አቀንቃኞች (Neo-Marxist) በጥቅሉ ሀይማኖትን የገዢው ቡድን መሳሪያ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ለነዚህ ሰዎች ሀይማኖት ሰዎችን መጨቆኛና ማደንዘዣ መሳሪያ ነው ፤ ይህንንም ለመግለጽ Karl Marx “ Religion is opium of the people / ሀይማኖት ህዝብ ማደንዘዣ ዕፅ ነው” የሚል ሀረግ ተጠቅሞ ነበር፡፡

ይህን ሀሳብ የሚወቃወሙ ሌሎች ምሁራን ደግሞ የሀይማኖትን ተቋማዊ እሴቶች በማንሳት ለማህበረሰብ አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆኑ የሚያትቱ አሉ፡፡ በተለይ ሀይማኖት ስነምግባርን/ ethics ለማህበረሰቡ በማስተማር ፤ ማህበራዊ ችግሮችን በሀይማኖታዊ አስተምሮዎች በማካተት እና ችግሮችን በመቅረፍ እና የእርስበርስ መተሳሰብና ትስስርን/solidarity በማጠናከር ለሁለንተናዊ ማህበራዊ ሰላምና መረጋጋት ያለውን ጉልህ ሚና ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ ፖለቲካው የተረጋጋና ሀገርም ሰላም እንዲሆን ሀይማኖት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን እና በዚህ ዙሪያ ያሉ ሌሎች እሳቤዎችን ስንቃኝ በጥቅሉ በሀይማኖትና ፖለቲካ መካከል ሊኖር የሚችለው ጉድኝት በሶስት መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡-

የመጀመሪያው ገጽ ፡ የሀይማኖት ተቋማት በፖለቲካው ላይ ፍጹም የበላይ ሊሆኑና የፖለቲካውን/የማስተዳደሩን ስራ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ እንደምሳሌ ያሁኑዋን ኢራን ወይም በፊውዳሊዝም ስራት ወቅት የሀይማኖት ተቋማት የነበራቸውን ዐብይ ሚና መውሰድ ይቻላል፡፡
ሀይማኖትና ፖለቲካው ሳይጠፋፉ በተአቅቦ አዎንታዊ ማህበራዊ ፋይዳ ባለው መልኩ በጋራ ለሁለንተናዊ ሰላምና አንድነት እየሰሩ ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ እንደምሳሌ በሩሲያና በእስራኤል የሀገር አንድነታቸውን ፣ታሪካቸውን እና ሰላማቸውን በማስጠበቅ ረገድ ፖለቲካውና ሀይማኖቱ እንዴት እየተናበቡ እንደሚሰሩ ማስተዋል ይቻላል፡፡
ሥስተኛው ገፅ፡ ፖለቲካው በማን አለብኝነት ስሜት የሀይማኖት ተቋማትን ሊደፈጥጥ እና በማስገደድ የፖለቲካው መሳሪያ አድርጎ ሊጠቀምባቸውና ፤ ለፖለቲካው እንዲመቹ አድርጎ ሊያዘጋጃቸው ወይም ሊያድሳቸው ይችላል፡፡ እንደምሳሌ እሩቅ ሳንሄድ አሁን በኢትዮጵያ ውስት ያለውን ሁኔታ ማስተዋል በቂ ነው፡፡
በርግጥ በሀይማኖትና ፖለቲካው መካከል የሚኖረው ግንኙነት ፡ ጥልቀትና ጥንካሬ እንዲሁም ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ እንደማህበረሰቡ ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ አለም በአሁኑ ወቅት ግለኝነት/Individualism በመንገሱ ፤ ማህበራዊ ትስስር በመላላቱ እና የህይወት ፍልስፍና ከሀይማኖት/መንፈሳዊነት ይልቅ በሣይንሳዊ አመክንዮዎች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ሀይማኖት እንደ ተቋም ያለው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ በነዚህ ሀገራት ሀይማኖት እንደተቋም ከፖለቲካው ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ብዙም ትኩረት የማይሰጠውና ማህበራዊ ፋይዳውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሶስተኛው አለም ሀገራት፡ ሀይማኖት / መንፈሣዊነት ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን በለት ተለት የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያለውና ማህበራዊ ፋይዳውም የትየለሌ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሀይማኖትና ፖለቲካው እንደ ተቋም እርስ በርስ የሚኖራቸው የሁለትዮሽ የጉድኝት አይነትና ደረጃ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠውና ለአንድነት፡ ሰላም እና ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ እንድምታ ያለው ነው፡፡ በሌላ አባባል የነዚህ ተቋማት የግንኙነት አይነትና ደረጃ ለመልማታችን ወይም ለመጥፋታችን ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህም ነው እያንዳንዱ ዜጋ ወይም አማኝ አያገባኝም ሳይል ሀላፊነት በተሰማው መልኩ እነዚህ ተቋማት እርስ በርስ ሳይጠፋፉ በተአቅቦ በበጎ ጎኑ እየተመጋገቡ ለሁለንተናዊ ሰላም፡ ነጻነትና ፍትህ በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ የሚኖርበት፡፡

ሀይማኖት እና ፖለቲካ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም በፊውዳሉ ስርአት ፡ ሀይማኖትና ፖለቲካ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ነበሩ ማለት እንችላለን፡፡ ክርስትና በ4ኛው ክፍለ ዘመን በይፋ የመንግስት ሀይማኖት ከሆነ ጀምሮ በመሀል ከነበሩት የዮዲት ጉዲትና የግራኝ አህመድ ግዜ ውጪ እስከ ደርግ መምጣት ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዎህዶ ቤተክርስቲያን/ክርስትና የመንግስት ሀይማኖት ሆኖ ቆይቶአል፡፡

በዚህ ረጅም የታሪክ ሂደት ውስጥ ቤ/ክ ከፍተኛ ስልጣን እና ሀይል የነበራት ሲሆን እኩል ግብርም ይገባላት ነበር፤ ሲሶ ለነጋሽ ፡ ሲሶ ለቀዳሽ ፡ ሲሶ ለአራሽ እንዲሉ፡፡ ለቤተክርስቲያን የማይመች ንጉስ ሲነሳም ህዝቡን በማስተባበር እና በማሳደም የንግስና እድሜው እንዳይረዝም የማድረግ ሀይል ነበራት፤ ለምሳሌ የመጨረሻው የዛግዌ ስርወ መንግሰት ንጉስ ይተባረክ ተወግዶ ሰሎሞናዊ ስርወ መንግሰት እንዲመለስ እና በ 1270 ይኩኖ አምላክ እንዲነግስ በማድረግ በኩል የቤ/ክ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ በተጨማሪም በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የነበረውን ታሪክ ማስታወስ ይቻላል፡፡

ህዝቡን በማስተዳደር እና ኢትዮጵያ አንድነቷን እና ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቆይ በማድረግ በኩል ቤ/ክ ያላትን ሃይልና ተደማጭነት በመረዳት በሚገባ የተጠቀሙበት ነገስታትም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል ታላቁና ብልሁ መሪ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ በአድዋ ጦርነት ወቅት ለድል ካበቋቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ፡ ቤ/ክ በዘመቻው ወቅት የነበራት ጉልህ ሚና ጭምር ነው፡፡ በ1953 ዓ.ም የታህሳስ ግርግር በመባል የሚታወቀው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲከሽፍና ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የግዛት ዘመናቸው ለጊዜውም ቢሆን እንዲራዘም በማድረጉ ረገድ በወቅቱ የነበሩት ፓትሪያርክ የተጫወቱትን ሚናም ማስታወስ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በደርግ ዘመን፡ የሀይማኖት ተቋማት ከመንግስት ጋር የነበራቸው ይፋዊ ቁርኝት የተበጠሰ ሲሆን ፡ ደርግ እከተለዋለው በሚለው የሶሻሊዝም ርዮተ አለም ምክንያት የሀይማኖት ተቋማት እንዲደክሙና ተደማጭ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የሀይማኖትና ፖለቲካ ግንኙነት ስንቃኝ፡ እንዳለመታደል ሆኖ ተመጋጋቢ የሆነ ለሁለንተናዊ ሰላም የሚረዳ የተአቅቦ የሁለትዮሽ ግንኙነት ሳይሆን፤ የፖለቲካው ፍፁም የበላይነት ያለበትና የሀይማኖት ተቋማትን የሚደፈጥጥ ብሎም የሚበዘብዝ በመሆኑ እጅግ አደገኛና ማህበረሰቡን እና ሀገሪቷን ውስብስብ ወደሆነ ማጥ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ስርአት ፡ እንደኛ ባለው ታዳጊ ሀገር ውስጥ የሀይማኖት ተቋማት የህዝቡን የለት ተለት ኑሮ በመምራት ፡ በመግራትና በመተርጎም በኩል ያላቸውን የላቀ ሚና አስቀድሞ የተረዳው ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው ስርአቱ ከመነሻው የሀይማኖት ተቋማት ላይ አይኑን በመጣል ፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መልኩ ጣልቃ በመግባት ለመቆጣጠር እና ለስርአቱ በሚጠቅም መስመርና አካሄድ ውስጥ ለማስገባት የሞከረው እና እየሞከረ ያለው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ስርአት የሀይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠርና ለመበዝበዝ የሚሞክረው በዋናነት ለሁለት አላማዎች ሲል ነው፡-

ፖለቲካዊ አላማ፤ የሀይማኖት ተቋማትና የሀይማኖት አባቶች ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም የመንግስትን ፕሮፓጋንዳና እሳቤ በቀላሉ በህዝብ ላይ ለመጫን እና ለማስረጽ ብሎም ህዝቡ ለሚደርስበት ግፍ ጠያቂ እንዳይሆን በማድረግ ያለጫና እና ያለገደብ ለመግዛት ሲሆን
ኢኮኖሚያዊ አላማ፤ የሀይማኖት ተቋማት ያላቸውን ሰፊ የተፈጥሮ እና የፋይናንስ አቅም ያለከልካይ በመዝረፍ የስርአቱን ኢኮኖሚያዊ ጡንቻዎች በማፈርጠም መደላደልን ለመፍጠር ነው፡፡
ይህ ስርአት የሀይማኖት ተቋማትን የሚቆጣተርበት እና ጣልቃ የሚገባበት መንገድ ሁለት አይነት ነው፡፡ የመጀመሪያው Bryan S. Turner በ 2013 እንደጠቀሰው Upgrading (Partial Secularisation) የሚባል ሲሆን፤ ይህ ማለት መንግሰት በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት እንቅፋት ይሆኑኛል የሚላቸውን አስተሳሰቦችን/አስተምህሮዎችን የሚያጠፋበትና በአዲስ የሚያዘምንበት /modernize የሚያደርግበት መንገድ ነው ፡፡ በዚህ ረገድ ስርአቱ በተለይ የእስልምና ሀይማኖት ላይ ጣልቃ በመግባት የፈፀመውን ደባ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሁለተኛው መንገድ (Serawit Bekele Debele, 2018) እንደጠቀሰው Cooptation የሚባል ሲሆን ፤ ይህ ማለት መንግስት በእጅ አዙር የሀይማኖት ተቋሙን የሚቆጣጠርበት እና የኔ የሚላቸውን ግለሰቦች/ የሀይማኖት አባቶች በመሾም ፡ የፈለገውን የሚፈጽምበት እና ጣልቃ የሚገባበት መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ማስረጃ የሚሆነን ከመነሻው መንግስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ላይ የፈፀመው እና እየፈፀመ ያለው ደባ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ አስተምህሮ መሰረት፡ ቤተክርስቲያን ረቂቅ የሆነች የአምላክ/የክርስቶስ ህያው አካል እንጂ ተቋም አይደለችም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅድስት ቤተክርስቲያን በራሷ አታጠፋም ወይም አትበድልም ወይም በሌላ የውስጥ ወይም የውጭ አካል አትበደልም፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያኑዋ ስራዎን ለመስራት በመተዳደሪያ ህጓ (ቃለ ዐዋዲ) መሰረት ያዘጋጀቻቸው በሰዎች የሚመሩ የአስተዳደር መዋቅሮች/ተቋማት (ለምሳሌ ቤተክሀነት፣ቅ.ሲኖዶስ እና ሌሎች በተዋረድ ያሉ የአስተዳደር አካላት) ሊበድሉ ፡ በውጭ አካል ተጽእኖ ስር ሊወድቁና ሊበላሹ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ተበላሽተዋል እናስተካክላቸው ስንል እነዚህን የአስተዳደር አካላት እንጂ፡ ረቂቅ የሆነችውን ቅድስት ቤ/ክ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡

በዚህ መንፈስ አሁን ያለውን ችግር ስንዳስስ፡- መንግስት በሚያሳዝን ሁኔታ ሰላዮችን መነኩሴ በማስመሰል ገዳም እና በሌሎች የቤ/ክኑዋ መዋቅሮች ውስጥ በማስገባት ለሀገር የሚፀልዩ እውነተኛ አባቶችን የማሸማቀቅ ብሎም መነኮሳትን አስሮ የማንገላታት ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም ምክንያት ባሁኑ ጊዜ ጳጳሳት ሳያውቁአቸው በካድሬዋች የሚሾሙ ያልተማሩ /ጨዋ ሰላይ-ዲያቆን ፤ ሰላይ-ካህን እና ሰላይ-መነኪሴዎችን በሚያሳዝን ደረጃ ማስተዋል ተጀምሯል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያኑዋን የአስተዳደር መዋቅር ከማበላሸት ባለፈ ፡ የቤተክርስቲያኑዋ ታሪክና ህልውና ላይ የተቃጣ ትልቅ የጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ በተጨማሪም የስርአቱ ካድሬዎች ከቤተክርስቲያኑዋ ዋና ዋና (መንፈሳዊ ጣዕም ያልገባቸው እና አለማዊ ከሆኑ) መሪዋች ጋር በመመሳጠር የቤተክርስቲያኑዋን አስተዳድር አካላት በሙስና በማንቀዝ ፡ ያለከልካይ የምዕመናኑን ሃብት ሲዘርፉና ሲካፈሉ ኖረዋል፡ አሁንም ይኸው ድርጊት እየተፈጸመ ይገኛል፡፡

በዋነኛነት አሁን ባለው ስርአት አማካኝነት ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ደባና የተጋረጡባትን አደጋዎች በአራት ከፍለን ማየት እንችላለን፡-

ምዕመኑ ከድሀ መቀነቱ እየፈታ የሚሰጠው አስራት፣ ምፅዋትና ቀዳምያት፡ በአልጠግብ ባዮች ያለማቋረጥ እየተዘረፈ ይገኛል፡፡ በዚህ ድርጊት ምክንያት መንፈሳዊ ህይወታቸውን የጎዱና እየጎዱ ያሉ ምዕመናን ቁጥር እየጨመረ መቷል፡፡
በሂደት የቤተክርስቲያኑዋን ስርአት ሊያናጉ የሚችሉ የቀኖና እና የስርአት ጥሰት በቤተክርስቲያኑዋ በተሰገሰጉ የመንግሰት ካድሬዎችና በውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው እየተፈፀመ ይገኛል፡፡
በጣልቃ ገቦች እና ተባባሪዎቻቸው በየጊዜው በሚፈፀሙ አፀያፊ እኩይ ድርጊቶች ምክንያት፡ ምዕመኑ ለአባቶችና ካህናት የሚሰጠው ግምት እና ያለው አክብሮት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸረሸረ የመጣ ሲሆን ፤ ይህም በጊዜ ሀይ ካልተባለ እጅግ አደገኛ መዘዝ የሚጎትት ነው፡፡ ምዕመኑ ከተማረው ቃለ እግዚአብሔር ጋር የሚጣጣም ድርጊት ከአባቶችና ከሀይማኖት መሪዎች ካላገኘ ተስፋ በመቁረጥ ስለሚሸሽ ፡ አሁን በምዕራብ ሀገራት በሚገኙ ቤተክርስቲያናት ውስጥ የምናየው የአማኝ/የሰው ድርቅ እንዳይመጣ በእውነቱ መፍራት እና መስራት ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ የቤተክርስቲያኑዋን መሰረታዊ ተልዕኮ የሚፃረር በመሆኑ፡ ከምንም በላይ የነፍስ/የበጎች መጥፋት ግድ የሚለው አባት ይቺ ቤ/ክ ያስፈልጋታል፡፡
በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት ቤ/ክዋ በፖለቲካው ቀጥጥር ስር ወድቃለች፤ ይህም በመሆኑ ምክንያት ለሀገር አንድነት፣ ልማትና ሰላም የሚጠቅሙ ድርጊቶችን ነጻ ሆና በራሷ ተነሳሽነት ማከናወን አልቻለችም፡፡ አንደበቷ በስርአቱ ተሸብቦ ፡ በችግር ጊዜ እንኳን ለምዕመናን የሚሆን መልዕክትና አዋጅ ነፃ ሁና ማስተላለፍ አልቻለችም ፤አገራዊ አስተዋጽኦዋና ፋይዳዎ በስርአቱ ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መቷል ፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፤ነገር ግን ይህን አንገብጋቢ ችግር በመረዳት ለመፍትሄው ሚንቀሳቀሱ ዜጎች/ምዕመናን ቁጥር በሚያሳዝን ደረጃ እጅግ አናሳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

መፍትሄዎች

እንግዲህ ሀቁን ከመረመርነው ፡ የኢ.ኦ.ተ.ቤ ያለችበት ሁኔታ እና እያጋጠማት ያለው መራር ሀቅ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ናቸው፡፡ ለዕምነታችን እና ለሀገራችን ቀናኢ እንድንሆን እና በመከራ ውስጥ ቢሆን እንኳን ለእውነት እንድንወግን እና ሀሰትን እንድናወግዝ የሚመክሩ ብዙ ሀይማኖታዊ ጽሁፎችና ማስረጃዎችን አንድ ሁለት ብሎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህን የእውነተኛ አማኝ መለኪያ የሆኑ ሀይማኖታዊ ፅሁፎች ባናውቃቸው እንኳን፡ ለሀይማኖታቸው እና ለሀገራቸው ሰማዕትነት ከፍለው ያለፉ ቅዱሳን አባቶቻችንን ታሪክ መለስ ብሎ መቃኘት በቂ ይሆናል፡፡ በታሪክ ሂደት ውስጥ ስንመለከት እቺ ቤ/ክ ለሀይማኖታቸው እና ለሀገራቸው ሲሉ ሰማዕትነትን የከፈሉ ዕልፍ ቅዱሳን አባቶችና ምዕመናን ያለፉበት አኩሪ ታሪክ ያላት ቤ/ክ ናት፡፡ እሩቅ ሳንሄድ በ 1928ዓ.ም ለሀገር አንድነት እና ለእምነት ነፃነት ሲሉ ሰማዕትነት ከተቀበሉት ቅዱስ አባታችን አቡነ ጴትሮስ እንኳን ብዙ መማር እንችላለን፡፡

በእውነቱ የአሁኑ ትውልድም ሀቁን በመመርመር እና በመረዳት ብሎም ከታሪክ በመማር፡ የቤ/ክ እና የሀገር መጎዳት ግድ ሊለው ይገባል፡፡ ወደነበርንበት የሞራል ልዕልና እና የእምነት ጥንካሬ መመለስ አለብን፡፡ በሰዎች ምክንያት የቤ/ክኑዋ አስተዳደር መዋቅር ወደ አልተፈለገ ጎዳና እየነጎደ ቢሆንም ቅሉ ፤ጠንካራ እምነት እና መንፈሣዊነትን የተላበሱ ምዕመናን ግን ቆርጠው ከተነሱ እና ለዕውነት መወገን ከቻሉ ስህተቱን ማረም ይቻላል፡፡ እንደ አባቶቻችን ለዕውነት የመቆም ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ በእርግጥ “ እውነት ስንናገር ሰው ጠላን ፡ ውሸት ስንናገር እግዜር ጠላን” እንዲሉ አበው ፤ለዕውነት በመወገናችን እና ለሀገርና ለሀይማኖት ነጻነት በመቆርቆራችን ምክንያት፡ ልንጎሳቆል እና መከራ ልንቀበል እንችላለን፡፡ ይህ ግን ለሀገርና ለሀይማኖት ሲባል የሚከፈል መሰዋትነት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ እንግዲህ ይህ መሰለኝ የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት እና አማኝነት መለኪያው፡፡

ወገኖች ተቋሞቻችንን እንፈልጋቸዋለን፡፡ ለማህበራዊ መግባባት፣ ለሀገር አንድነትና ሰላም ከፍተኛ እንድምታ ያላቸውን ተቋሞቻችንን ማንም እንዲነጥቀን አንፍቀድ፡፡

እግዚአብሔር ሀገራችንን እና ሀይማኖታችንን ይጠብቅ !

ሰሎሞን ጌጡ ከኑረንበርግ

[email protected]

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop