የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በኢትዮጵያ ቡና፣ በቅዱስ ጊዮርጊስና በተጫዋቹ አበባ ቡታቆ ላይ የገንዘብና የጨዋታ ቅጣት መጣሉን የሃገሪቱ መንግስታዊ ሚዲያዎች ዘገቡ። በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመለስ ዋንጫ የካቲት 17 ቀን 2005 በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ፣ ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት በተጫወቱበት ዕለት የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የጨዋታ አመራሮችን ሪፖርት በመመርመር ቅጣቱን መወሰኑን ኮሚቴው አስታውቋል ያሉት መንግስታዊው ሚዲያዎች በዕለቱ በቀኝ ጥላ ፎቅ የነበሩ የኢትዮጵያ ቡና አርማና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊስንና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ደጉ ደበበን፣ አሉላ ግርማን እና አበባው ቡታቆን እንዲሁም የፌዴሬሽኑን ስም በመጥራት አስፀያፊ ስድብ ተሳድበዋል እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጠባባቂ ተጫዋቾች በሚያሟሙቁበት ወቅት የውሃ ፕላስቲክ እና ድንጋይ ወርውረዋል በሚል ኮሚቴው መክሰሱን ዘግበዋል።
ክለቡ በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎቹ ለፈፀሙት ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ በመገኘቱ የሃምሳ ሺህ ብር እና በሜዳው የሚያደርጋቸውን ሁለት ቀጣይ ጨዋታዎች ያለተመልካች እንዲጫወት ተወስኖበታል ያለው ዘገባው ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ስድብና ነቀፋ የተሰነዘረበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አበባው ቡታቆም ለደጋፊዎች ክብር ሰጥቶ በትዕግስት ማሳለፍ ሲገባው የኢትዮጵያ ባህል ባልሆነ መልኩ በሰውነት ምልክት ደጋፊን በመሳደቡ፤ ለተጨማሪ ረብሻም ምክንያት በመሆኑ አምስት ጨዋታና አንድ ሺህ ብር እንዲቀጣ ሲወሰን ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በዕለቱ ደጋፊዎቹ አስፀያፊ ስድብ መሳደባቸውን፤ እንዲሁም የካቲት 15 ቀን 2005 የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ክለብ ከደደቢት የሴቶች ክለብ ጋር በተጫወቱበት ዕለት ዳኞችን አስነዋሪ ስድብ በመሳደባቸው 40 ሺህ ብር እንዲቀጣና ቀጣይ አንድ ጨዋታውን ያለተመልካች እንዲጫወት ነው የተወሰነው።
ይህን ቅጣት ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ደጋፊዎቻችን ለስድብ ያነሳሳው ተጫዋቹ እንደሆነ በመናገር የተጫዋቹ ቅጣት በቂ አይደለም፤ በክለባችን ላይ የተጣለው ቅጣትም ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ፀሀፊ አቶ ንዋየ በየነም አጥፊውን በትክክል ለይቶ መቅጣት ሲገባ ለማቻቻል ሲባል የተወሰነ ቅጣት ነው ብለዋል፤ ክለባቸው ጥፋት የፈጸሙ ተጫዋቾችና ደጋፊዎቹንም በስፖርት ማህበሩ መመሪያ መሰረት እንደሚቀጣም ነው መናገራቸውን የዘገቡት መንግስታዊው ሚዲድያዎች ክለቦቹ ይግባኝ መጠየቅ እንደሚችሉ ተዘግቧል።