የፈሩት ይወርሳል የጠሉት ይነግሳል፤
ይኽ ንግር በኛ አገር እየሆነ ኑሯል፤
ዘመነ ግልንቢጥ ክፍ አዞ ያረባል፤
ባህር እየኖረ ከጤዛ ይጠጣል፤
ዙፋን ተቀራምቶ በጉልት ይቀናል፤
መቸስ ቅና ያለው ቅንቀን ይበላዋል፤
ወይ እንዳጋጣሚ! ‘ላንዱ’ ያልፍልታል፤‘ባንዱ’ ያልፍበታል።
በቀል ተጸንሶ መች ቂሙ ይረክሳል፤
ያሳደጉት ውሻ ዙሮ ይናከሳል፤
የዘመኑ እረኛም ቀበሮ ይሆናል፤
የሰው ቆዳ ለብሶ በአገር በግ ይፈጃል፤
የመንደር ተኩላው ጋጥ በረቱን ወሯል፤
ደቦ እየዘረፈ በአውጫጭኝ ያጉላላል፤
ሕዝብ እየገረፈ ጩኸቱን ይቀማል፤
የኛማ እንቆቅልሽ ‘ምን አውቅልሽ’ ይላል፤
ወይ እንዳጋጣሚ! ነባር ማንነቱ ወያኔ! ይባላል።
ውለታ፤ይሉኝታ ወሮታ መች ያውቃል፤
ቀን ሊወርስ ባመሻሽ ጥግጥግ ይይዛል፤
ንጉስ ያዘመቱት ‘ነጭ ለባሽ’ ይበዛል፤
ቤት ለእንግዳ ቢሉት እንግዳ ያደርጋል፤
በአባወራው እድር በአዳራሽ ያዝዛል፤
ጉርብትና ብሎም ሰው ካገር ይገፋል፤
ቀን የሰጠው ሸክላ ‘ባለእጁን’ ይሰብራል፤
እውስ አይዋጡት ‘ቀን መጤው’ ያይላል፤
ይህ ‘ጥቁር እንግዳ’ ውሎ አድሮ ‘ይነጣል’፤
ወይ እንዳጋጣሚ! ይኸን ሰው ማን ይሏል?
መንጋ እየተናዳ ተቧድኖ ተቋጥሮ፤
ወሰን ወንዝ ተሻግሮ ‘ሞፈር ዘመት’ ወሮ፤
የጥንት ባለርስቱን ጉዛሙን ሰው አስሮ፤
በምድር ገሃነም ‘ባዶ-ስደስት’ ቀብሮ፤
ትዳር ያጎፈየ ቃል ኪዳኑን ሰብሮ፤
የዘር ስብጥሩን በማሳው ቀይሮ፤
ቤት ባድማቸውን ሲነጠቁ ጓሮ፤
ባለም ላይ ግፋዓን ስላሰሙ እሮሮ፤
የሰውን ማንነት ስብዕና ደፍሮ፤
ማን አትበሉኝ ይላል? በማንነት ከብሮ።
ሰሜን፤ደቡብ፤ ምስራቅ ምዕራብ ሁሉ ወሮ፤
መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ኢትዮጵያን አጉሮ፤
‘አንድ ወገን’ በቁንጣን ሌላው ጦሙን አድሮ፤
ነፍስ እያስገበረ አንዱ በአንዱ ኑሮ፤
ይህ ዘመነ አጣብቂኝ ሰው አነባበሮ፤
አንዱ የእንጀራ ልጅ ኑሮ-ማዕዱ አሮ፤
ሌላው የስለት ልጅ ጠግቦ አነባበሮ፤
ይሆን? አጋጣሚ የድንገት ቀመሮ፤
ይኸ ተደማምሮ፤ ዙሮ፤ ዙሮ፤ ዙሮ፤
ግፉ ተነባብሮ ሲከብድ ለአእምሮ
የቁጥር ቅብጥርጥር ሳይባዛ በዜሮ፤
ለቆጡ ሲሻሙ ብብት እርቃን አድሮ
ገመና ሳይወጣ ይስማ ያለው ጆሮ፤
የበደለ እንዲክስ ይኖር ዘንድ ተፋቅሮ፤
አጋጣሜው ገጥሟል፤ ‘ጊዜና ዘንድሮ’።
የጎንቻው! 18.12.16