ከደረጀ የምሩ
1. ማውራት ያቁሙ፡- ‹‹መስማት ካለብን በላይ ማውራት ቢኖርብን ኖሮ ሁለት ምላስና አንድ ጆሮ ይኖረን ነበር!›› ማርክ ትዋይን በየትኛው አጋጣሚ ብዙ ከማውራት ብዙ ማዳመጥ የተሻለ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ሆነው ሰዎች በሚያወሩ ሰዓት ጣልቃ ገብተው ከማውራት ይልቅ ቢያዳምጡ ይመከራሉ፡፡ እርግጥ ነው ተናጋሪው ንግግሩን ሲጨርስና ያልገባዎት ነገር ካለ ቢጠይቁ ችግር የለውም፡፡
2. ራስዎን ለማዳመጥ ዝግጁ ያድርጉ፡- ዘና ይበሉና ሙሉ ትኩረትዎን በሰውየው ንግግር ላይ ያድርጉ በአዕምሮዎ ሌሎች ነገሮችን ከማሰብ ይቆጠቡ፡፡ የሰውን ልጅ አዕምሮ ጥቃቅን የሚባሉ ሀሳቦች ሳይቀሩ ሊቆጣጠሩት ይችላሉ፡፡ ‹ምሣዬን ምን ብበላ ይሻላል?›› ፣ ‹‹ስመለስ አውቶቡስ አገኝ ይሆን?››፣ ‹‹… ዝናብ እንዳይመጣ ብቻ!›› ወዘተ. አዕምሮን ለመጥመድ በቂ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ አብረውት ያለው ሰው ሲያወራ ትኩረትዎን በንግግሩ ፍሬ ነገር ላይ ለማድረግ ይጣሩ፡፡
3. ተናጋሪውን እያጨናነቁት የሚያወራልዎ ሰው ዘና ብሎና በግልፅነት እንዳያወራዎ ያግዙት አንገትዎን በመወዝወዝም ይሁን አንዳንድ ቃላትን ጣል በማድረግ ትኩረትዎ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ያረጋግጡለት፡፡ ተናጋሪውን ቢመለከቱም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አያፍጡበት፡፡
4. ተናጋሪውን አያቋርጡ ተናጋሪውን ሰው የሚረብሹና ትኩረቱን የሚስቡ እንቅስቃሴዎች ከማድረግ ይቆጠቡ፡፡ ለምሳሌ ያህል ወረቀቶች ማገላበጥ፣ በመስኮት አሻግሮ መመልከት ወይም ጥፍር መቁረጥን የመሳሰሉ ድርጊቶች ተናጋሪው ትኩረቱን እንዲያጣና ተደማጭነት ያጣ እንዲመስለው ሊያደርገው ስለሚቻል ይህን አመል ይተውት፡፡ ይኼ ብቻ አይደለም እርስዎም የንግግሩን ሀሳብ መረዳት ሊያዳግትዎ ይችላል፡፡
5. ይረዱ ነገሮችን ከእርስዎ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ተናጋሪው ከሚናገርበት አቅጣጫ ጭምር ለመረዳት ሞክሩ፣ ነገሮችን ከሌላ ሰው ቦታ ሆኖ ማዳመጥ መቻል ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እንዳለው ያስታውሱ፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን ተናጋሪው እርስዎ የማይስማሙበትን ሀሳብ ካነሳ ንግግሩን ሲጨርስ ጠብቀው የመከራከር መብትዎ እንደተጠበቀ ነው፡፡
6. ትዕግስተኛ ይሁኑ ተናጋሪው ለጥቂት ሰከንዶች … ወይም ከዛም ከፍ ላለ ጊዜ በዝምታ ተዋጠ ማለት ንግግሩን ጨረሰ ማለት እንዳልሆነ ይረዱ፡፡ ትዕግስተኛ ይሁኑና ተናጋሪው ተናግሮ እስኪጨርስ ይጠብቁት፡፡ መቼም ቢሆን መቼ የሰው ንግግር አያቋርጡ ወይም ሀሳባቸውን እንዲቋጩ አይጐትቷቸው፡፡
7. ሰዎችን አይገምግሙ እንደየሰው ባህሪ በንግግር ወቅት የሚታዩ ባህሪየትን በፀጋ ለቀመበል ይወስኑ፡፡ አንዳንዱ ሲናገር ቁጣ ቁጣ ይለው ይሆናል፡ ፡ ሌላው ሲናገር ይልጐመጐም ይሆናል፡፡ የእርስዎ ተግባር ማዳመጥ እንጂ የሰዎችን ጠባይ ማረቅ አይደለምና ትኩረትዎ በሰውየው ባህርያት ላይ ከማድረግ ይልቅ በንግግሩ ቁም ነገር ላይ ያድርጉ፡፡
8. ከቃላት ይልቅ ሀሳብን ይስጡ ብዙዎቻችን የመስማትና የማዳመጥን ልዩነት እንብዛም ላንረዳ እንችል ይሆናል፡፡ አንድ ሰው በሚናገርበት ወቅት በየተራ የሚደረድራቸውን ቃላት ሳይሆን ቃላቱ በህብረት የሚፈጥሩትን ሀሳብ ለመረዳት መሞከር የጥሩ አድማጭ መገለጫ ነው፡፡
9. የተናጋሪውን ገፅታ ይመልከቱ የአንድን ሰው ንግግር በቅጡ ለመረዳት የተናጋሪውን የፊትና የአካል ገፅታ መመልከት ወሳኝነት አለው፡፡ በፊቱ ላይ የሚያሳያቸው እንቅስቃሴዎችና የአይኑ እንቅስቃሴ ሁሉ ሀሳቡን በይበልጥ በመረዳት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በጆሮዋችን ብቻ ሳይሆን በአይናችንም እንሰማለንና (እንረዳለን)፡ ፡ ተናጋሪውን ተመልከቱና ቃላት ሊገልፃቸው ያልቻሉ የተናጋሪውን ስሜቶች ተረዱ፡፡
10. እርጠኛ ይሁኑ በመጨረሻም የተወራውን በትክክል ስለመስማትዎ ማረጋገጫ ለመስጠት አይሞክሩ ይልቁንም ወሬውን የተረዱበት መንገድ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ለራስዎ ያረጋግጡ፡፡