March 13, 2015
26 mins read

Health: ስለ ወንዶችም ሆነ ሴቶች ስንፈተ ወሲብ ከባለሙያ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

በርካታ ባለትዳሮች በግልፅ ለመንገር ባይፈልጉም ከሁለቱ አንደኛው ከወሲብ የሚገኘውን ደስታ በመንፈጋቸው ሳቢያ ለዘመናት የገነቡትን ትዳር የጠዋት ጤዛ ሲያደርጉት አይተናል፡፡ ምንም እንኳን የስንፈተ ወሲብ ችግር ሳይንሳዊ ምክንያትና መፍትሄ ያለው ቢሆንም፤ ችግሩን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ግልፅነት ባለመኖሩ ትዳሮች ፈርሰዋል፡፡ ቤተሰብ ተበትኗል፡፡ ጥያቄው ያለው መፍትሄ ባለው ችግር ለምን ትዳሮች ይናጋሉ? ለምንስ ፍቅረኞች ወደ መለያየት ያመራሉ? የሚለው ላይ ነው፡፡

በቦስተን አካባቢ ባሉ ነጮች ላይ የተጠና ጥናት እንደሚያመላክተው 30 ሚሊየን የሚደርሱ ወንዶች የስንፈተ ወሲብ ችግር አለባቸው፡፡ ጥናቱ ጨምሮ እንዳረጋገጠው የወንዶች እድሜ በጨመረ ቁጥር ችግሩ የበለጠ እየሰፋ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ በጥናቱ ከተካተቱት የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 40 ዓመት ከሞላቸው ወንዶች 40 በመቶ የሚሆኑት እንደዚሁም 70 አመት ከሞላቸው ደግሞ በ70 በመቶዎቹ ላይ የስንፈተ ወሲብ ችግር ታይቶባቸዋል፡፡ የተለያዩ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች ተለያይተው ሲጠኑ ደግሞ፤ ለምሳሌ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከሌለባቸው በሶስት እጥፍ የስንፈተ ወሲብ ተጠቂዎች መሆናቸውን በቦስተን በተደረገው ጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህ ጥናት የስነ ልቦና ችግሮችና ውጥረቶች በሚበዛባቸው በአፍሪካና በኤዥያ ሀገሮች ቢሰራ የስንፈተ ወሲብ ችግር ምን ያህል የዓለም ችግር መሆኑን እንደሚያሳይ የአሜሪካዎቹ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ በዚህ አምዳችን በስንፈተ ወሲብ (Sexual Dysfunction) ምንነት፣ መንስኤ፣ ምልክቶችና አማራጭ የህክምና መፍትሄው ዙሪያ የሚያተኩር የባለሙያ ትንታኔን እናቀርባለን፡፡ ሙያተኛው አንድ የኩላሊት፣ የሽንት ቱቦ፣ የፊኛና የወንድ ብልት ዘር ፍሬዎች ስፔሻሊስት ቀዶ ሐኪም ናቸው፡፡

የስንፈተ ወሲብን ምንነትና በሁለቱም ፆታዎች በምን መልኩ እንደሚገለፅ በመጠኑ ብናየው?

ስንፈተ ወሲብ (Sexual Dysfunction) የምንለው በተለያዩ ምክንያቶች በሁለቱም ፆታዎች በኩል ወሲብ ለመፈፀም የሚያስችሉ ችግሮች ሲከሰቱ ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ደግሞ አግባባዊ (የሚያረካ) የወሲብ ግንኙነት አለመፈፀም አልያም በሚደረገው የወሲብ ግንኙነት አለመርካት (ጥሩ ውጤት አለማግኘት) ማለት ነው የስንፈተ ወሲብ ችግር የሚባለው፡፡
እንዴት ይገለፃል? ለሚለው ለግብረ ስጋ ግንኙነት ስሜት ማጣትና ከግንኙነቱ እርካታ አለማግኘት በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀሚያ አካላት አለመነሳሳትን በተመለከተ በአብዛኛው በወንዱ ላይ ይታያል፡፡ ፍላጎት ማጣት፣ ከግንኙነት በኋላ እርካታን አለማግኘት (የእርካታ መጨረሻ ላይ አለመድረስ) ብዙውን ጊዜ የሴቶች ችግር ነው ማለት ይቻላል፡፡

ለችግሩ መፈጠር መንስኤዎች ምንድናቸው?

የስንፈተ ወሲብን መንስኤ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ብለን በሁለት ትላልቅ ጎራዎች ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡ አካላዊ ስንል ከግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀሚያ አካሎች ለውጥ፣ በደም ውስጥ ካሉ ንጥረ ነገሮች መዛባት፣ ከአዕምሮና ከህብለሰረሰር የሚነሱ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እንደዚሁም ከልብ የሚነሱ ደም ስሮች በአግባቡ ወደ ብልት ሄደው የደም ዝውውሩን ውጤታማ ማድረግ ባለመቻላቸውና ብልትን እንዲቆም የሚያደርጉ ነርቮች ባለመስራታቸው የስንፈተ ወሲብ ችግር ይመጣል፡፡ ሌላውና ከአካላዊ ምክንያት ጋር የሚያያዘው ስሜት ቀስቃሽ ንጥረ ነገሮች (ሆርሞኖች) በሚፈለገው መጠን በሰውነት ውስጥ አለመኖር፣ ስሜት ቀስቃሽ ንጥረ ነገሮች በሚፈለገው መጠን እንዳይሰሩ የሚያደርጉ ሌሎች የሆርሞን አይነቶች በሰውነት ውስጥ በብዛት ሲከሰቱ፣ በብልት ላይ የተለያዩ አደጋዎች ሲደርሱ፣ በብልት አካባቢ በሚሰሩ ቀዶ ህክምናዎች ምክንያት በብልት አካባቢ ያሉ ነርቮችና ደም ስሮች ሲጎዱ ለስንፈተ ወሲብ ችግር መጋለጥን ያመጣሉ፡፡ በተጨማሪም ለሌሎች በሽታዎች መፈወሻ ተብለው የሚሰጡ ለምሳሌ ለደም ግፊት፣ ለጨጓራ፣ ለኮሌስትሮል፣ ለሽንት ማሸኛ፣ ለአዕምሮ ህመሞችና ለሌሎችም በሽታዎች የሚሰጡ መድኃኒቶች ችግሩን የማምጣት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በአጠቃላይ 25 በመቶ የወንዶች ስንፈተ ወሲብ ለሌሎች በሽታዎች በሚሰጡ መድኃኒቶች የሚመጣ ነው፡፡ ከስነ ልቦና አንፃር ደግሞ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ጫና፣ ውጥረትና ቀደም ሲል በነበረ የወሲብ ታሪክ ጥሩ ያልሆነ ክስተት ከነበረ ለምሳሌ በቅርብ ዘመዶችም ሆነ በሩቅ ሰዎች ተገዶ መደፈር ከነበረ ወሲብን መጥላት ይኖራል፡፡ በወሲብ መፈፀሚያ ቦታዎች አካባቢ ምቾት ማጣት፣ ከማይፈልጉት ሰው ጋር መኖር (ወሲብ መፈፀም) የወሲብ ስሜት አልባነትን ያመጣል፡፡ እንደዚሁም በአንድ ወቅት በሆነ ምክንያት ወሲብ ያለመፈፀም ችግር ገጥሞት ከነበረ ሁል ጊዜም ችግሩ አለብኝ ብሎ መጨነቅ ወደ ስንፈተ ወሲብ ችግር በቀጥታ የሚገፋ ሁኔታ ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ መንስኤዎችን ስናየው አካላዊ ወይም ከበሽታ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ስንፈተ ወሲብ በአብዛኛው ከ40 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ የሚታይ ነው፡፡ በተለይም ከስነ ልቦና ጋር በተያያዘ ችግር ይበልጥ የሚጠቁት ወጣቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከስነ ልቦናዊ ምክንያቶች ጋር የተያያዘው የስንፈተ ወሲብ ችግር ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ከ40-80 በመቶ የሚሆነው የስንፈተ ወሲብ ችግር በቂ የሆነ አካላዊ ምክንያት ያለው ነው፡፡ ከላይ በመንስኤነት ከተገለፁ ጉዳዮች በተጨማሪ የሚገልፀው አብዝቶ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ሐሺሽ እና ለመዝናኛነት ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች ችግሩን በማምጣት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡

ስንፈተ ወሲብን በማምጣት ወይም በማባባስ በኩል አስተዋፅኦ ያላቸው የጤና ችግሮች ካሉ ቢገለፁልኝ?

– ኢንፌክሽን
– የልብ ህመም
– የጉበት ህመም
– የኩላሊት ህመም
– የስኳር እና
– የደም ግፊት በሽታዎች እንደዚሁም
– የኮሌስትሮል ከፍ ማለት
– የጡንቻ መኮማተር (በተለይ በሴቷ)
– የደም ስር ችግሮች
– የነርቭ ህመም እና
– ሰውነትን የሚያንቀጠቅጥ ህመም (ፓርኪንሰንስ ዲዝዝ) ከላይ የገለፅኳቸው የጤና ችግሮች በአንድ በኩል ስንፈተ ወሲብን ያስከትላሉ፡፡ በሌላም በኩል ቀደም ሲል የተከሰተን ስንፈተ ወሲብ ያባብሳሉ፡፡

ስንፈተ ወሲብ መኖሩን ፍንጭ ከሚሰጡ ምልክቶች ዋና ዋና የሚባሉትን ብናያቸው?

– የወሲብ ፍላጎት ማጣት
– የወሲብ መፈፀሚያ አካላት ዝግጁ አለመሆን (አለመቆም)
– በተለይም ሴቶች ወንድንም ሆነ ወሲብን መጥላት
– ብልት ቶሎ ተልፈስፍሶ መውደቅ ወይም መርገብ
– ወሲብ በሚፈፀምበት ወቅት ህመም መኖር
– የሴት ብልት ጡንቻ መኮማተርና በሁለቱም ላይ ህመም መፍጠር
– ሴቶችን ለግንኙነት ዝግጁ የሚያደርግ ፈሳሽ በበቂ መጠን አለመኖር
– እርካታ ላይ አለመድረስ

ፈጥኖ እርካታ ላይ መድረስ በሳይንስ እንዴት ነው የሚታየው?

ፈጥኖ የዘር ፍሬን ማፍሰስ ችግር ያለባቸው በቁጥር ቀላል የማይባሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ ዋናዋና የምንላቸው ምክንያቶች አንደኛው ለወሲብ ጉጉ ከመሆን የሚመነጭ ችኩልነት፣ ሁለተኛ ከአሁን አሁን የዘር ፍሬዬ ፈሰሰ ብሎ መጨነቅ፣ ሶስተኛ ራሴንም ሆነ ተቃራኒ ፆታዬን ማርካት አልችልም ብለው በተደጋጋሚ ስለሚያስቡ ስሜታቸውን ነፃ አድርገው ለመጋራት መቸገራቸው አራተኛው ከነርቭ ወይም ከብልት አፈጣጠር ጋር የተያያዘ ምክንያት ነው፡፡

የብልት ማነስ (መስፋት) ከስንፈተ ወሲብ ጋር ይገናኛል?

የብልት ጉዳይ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ስንፈተ ወሲብ ደግሞ በቂ የሆነ አካላዊ አልያም ስነ ልቦናዊ ምክንያት ያለው የጤና ችግር ነው፡፡ ስለዚህ የብልት ማነስ ወይም መስፋት ከስንፈተ ወሲብ ጋር የሚያያዘው ነገር የለም፡፡
አንድ ወንድ የዘር ፍሬ በማፍሰስ ብቻ ትክክለኛውን የወሲብ ድርጊት ፈፅሟል ማለት ይቻላል?
የዘር ፍሬ እኮ ምንም አይነት ግንኙነት ሳይደረግ የሚፈስበት ሁኔታም አለ፡፡ ስለዚህ የዘር ፍሬ መፍሰስ በራሱ ለውጤታማ የወሲብ ግንኙነት ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ የአንድ ሰው ወሲባዊ ግንኙነት ጥሩ (ውጤታማ) ነው የሚባለው ወሲብ ከመፈፀሙ በፊት ያለውን ስኬታማ የፍቅር ጨዋታን ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡ በተጨማሪም ጥሩ የወሲብ ግንኙነት ተደርጓል ለማለት ሁለቱም ፆታዎች የመጨረሻው እርካታ ላይ መድረሳቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

ለስንፈተ ወሲብ ችግር ተጠቂ የሆነው ግለሰብ በተጣማሪው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምንድነው ይላሉ?

የሚያስከትለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንድ ግለሰብ ስንፈተ ወሲብ ውስጥ ማለት የእሱ ተጣማሪም የችግሩ ተጠቂ ናት ወይም ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ወደ ምን ያመራል ብንል ትዳርን ወደ ማፍረስና ወደ ብጥብጥ ነው የሚያመራው፡፡ ብጥብጡም ሆነ ትዳር መፍረስ የቤተሰብ መፍረስን ያከስትላል፡፡ በትዳር ውስጥ የተገኙ ልጆች ካሉም ይበተናሉ፡፡ በአካልና በስነ ልቦና ጤና የሚጎዱም ይሆናሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ህፃናቱን የሚረዳቸው ከሌለ የማህበረሰቡ ችግር ሆኑ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ በብዙ ሺህ ሰዎች ሲከሰት ደግሞ ችግሩ የግለሰቦች መሆኑ ቀርቶ የሀገር ይሆናል፡፡ የአሉታዊው ተፅዕኖ አንዱ ገፅታ ይሄው ነው፡፡ ሌላኛው ገፅታ ደግሞ የችግሩ ተጋላጭ በሆነው ግለሰብ ላይ የሚደርሰው ነው፡፡ የስንፈተ ወሲብ ችግር ያለበት ሰው በስነ ልቦና ህመም የተጎዳ ነው፡፡ ራሱን ይጥላል፡፡ የዝቅተኝነት ስሜትን ያሳዳራል፤ ይህች ዓለም ለእኔ የተፈጠረች አይደለችም ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ በመሄድ በራሱም ሆነ በአካባቢው ባሉ ሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ እስከ መገፋፋት የሚሔድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ሌላው ቢቀር ችግሩ እንዳለበት እንኳ አሜን ብሎ ለመቀበልና መፍትሄውን ባሉት አማራጮች ሁሉ ለመፍታት ፈቃደኝነትን ሊያጣ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ችግሩ አለብህ ብለው ሊነግሩት ከሚፈልጉት ሰዎች ጋር ሁሉ ፀብ የሚጭር ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ችግሩ ያለበት ሰው ከህይወት ጣእምን ያጣ ስለሚመስለው ሁልጊዜ ደስተኛ አይሆንም፡፡ በድብርትና በጭንቅት የተዋጠ የመሆን እድሉ ሰፊ ይሆናል፡፡

ችግሩ መኖር አለመኖሩን ለመለየት የሚያስችሉ ምርመራዎችስ?

ስነ ልቦናዊ ችግር ያለባቸውን ከዕድሜያቸውና ከሚሰጡን ታሪክ ተነስተን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ የችግሩ መንስኤ ከስነ ልቦና ውጪ አካላዊ ነው ብለን ካሰብን የተለያዩ ምርመራዎችን እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ችግሩን ያመጣው በሽታ ነው ብለን ካሰብን በሚጠረጠሩ በሽታዎች ዙሪያ የላብራቶሪ ምርመራዎችን እናደርጋለን፡፡ የሆርሞን እጥረት (መዛባትን) ለማረጋገጥም የተለያዩ ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡ እንደዚሁም በአካላዊ ምርመራ ችግሩ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ የስነፈተ ወሲብ ችግር መኖር አለመኖሩን የሚያረጋግጡ ምርመራዎች በሀገራችን በበቂ ሁኔታ ይሰራሉ፡፡ ውጤታማም ናቸው፡፡

ህክምናውስ?

የችግሩ መንስኤ በእርግጠኝነት ስነ ልቦናዊ መሆኑ ከተረጋገጠ ስነ ልቦናዊ ችግሩን መፍታት ላይ እናተኩራለን፡፡ ለምሳሌ ፈጥኜ እርካታ ጥግ ላይ እደርሳለሁ የሚል ከሆነ የዘር ፍሬውን ማዘግየት የሚችልበትን ዘዴዎች በማማከርና በማሰልጠን የማረጋጋት ስራዎችን እንሰራለን፡፡ ስነ ልቦናው ችግሩ የገዘፈና ስር የሰደደ ከሆነ ለተጨማሪ የማማከር ስራ ወደ ስነ ልቦና ሙያተኞች እንልከዋለን፡፡ በሌላ በኩል በሌሎች በሽታዎች ተብለው ከሚወሰዱ መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ ችግሩ የመጣና የሚወስዱትን መድኃኒቶች ማቆም የሚቻል ከሆነ መድኃኒቶችን ከመውሰድ እንዲታቀብ ይመከራል፡፡ ነገር ግን የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ማቆም የማይቻላቸው ከሆነ ከተቻለ መድኃኒቶች የሚቀየሩበትን ሁኔታ እንፈልጋለን፡፡ ካልተቻለ ግን ከገጠመው ስንፈተ ወሲብ ጋር ተስማምቶ የሚኖርበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ተገቢውን ምክር እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የስንፈተ ወሲብ ችግርን የሚያስተካክሉ በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ የመድኃኒት ገበያ በርካታ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ መድኃኒቶችን መውሰድ ያለባቸው በዘፈቀደ ሳይሆን በሐኪሞም ትዕዛዝ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከሌሎች አማራጭ ህክምናዎች ደግሞ የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
– የሆርሞን እጥረት ላለባቸው ሰዎች የሆርሞን መተኪያ ህክምና መስጠት
– በብልት ላይ በመግጠም ብልት እንዲቆም በማድረግ ወዲያው የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም የሚያስችል (vaccum device)
– ግለሰቡ በግብረ ስጋ ግንኙነት በተዘጋጀበት ወቅት ብልት ላይ የሚወጉ መድኃኒቶች አሉ
– በሽንት ቧንቧ ወደ ውስጥ የሚከተቱ መድኃኒቶችን መስጠት
– በቀዶ ህክምና የተፈጠረውን ችግር ማሰተካከል
– ደም ስሮችን በቀዶ ህክምና ማስተካከል

ከአማራጭ ህክምናዎች የበለጠ ውጤታማው የትኛው ነው?

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በአፍ የሚወሰዱ መድኃኒቶች የስኳርና ሌሎች የጤና ችግር በሌለባቸው ሰዎች ላይ ከ70 እስከ 90 በመቶ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የስኳር በሽታ ባለባቸው ሰዎች ደግሞ መድኃኒቶቹ ከ50 እስከ 60 በመቶ ውጤት ይገኝባቸዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከሙያው ጋር ቅርበት የሌላቸው ሰዎች ለስንፈተ ወሲብ ችግር መድኃኒት ሲያዝዙ ይታያል፡፡ አልፈው ተርፈውም የሆርሞን ህክምና ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ የሆርሞን ህክምናን ለመስጠት መታየት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ካንሰር ላለበት ሰው የሆርሞን ህክምና ቢሰጠው ካንሰሩን በከፍተኛ ሁኔታ ያባብሰዋል፡፡ ስለዚህ ለስንፈተ ወሲብ የሚሰጠው ህክምና ሌላ ችግር እንዳያስከትል በጥንቃቄና ታስቦበት ሊሰራ የሚገባው ህክምና ነው፡፡

ከስንፈተ ወሲብ ጋር በተያያዘ ሙያዊ ምክርዎትን ያክሉበትና ውይይታችን እንቋጨው?

በፍቅርም ሆነ በትዳር ውስጥ ያሉ ጥንዶች መገንዘብ በሚገባቸው ለግንኙነታቸው መነሻም ሆነ መድረሻ አልያም ብቸኛው ጣዕም ሰጭ ወሲብ መፈፀም ብቻ ነው ብለው ድምዳሜ ላይ መድረስ የለባቸውም፡፡ ከወሲብ ይልቅ በቅድመ ወሲብ ወቅት የሚፈፀመው የፍቅር ጨዋታዎች የበለጠ ጣዕም ሰጭና ጠቃሚ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ስለ ፆታዊ ግንኙነት የሚኖራቸውን እውቀት በእየዕለቱ ማሳደግን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ይህ የፍቅር ጨዋታ ጭንቀትንም ሆነ ወሲብ በአግባቡ የመፈፀም ብቃት የለኝም የሚለውን የፍርሃት ስሜትን የማጥፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
በተፈጠረው ችግር ዙሪያ በግልፅ መነጋገርና አንዱ አንዱን ለመርዳት እንዲሁም በጋራ መፍትሄውን ለማፈላለግ ፈቃደኝነት ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ ችግሩ በሴቷም ሆነ በወንዱ ይድረስ ብጥብጥ ከመፍጠር ይልቅ እንዲህ አይነት ችግር ይፈጠራል፣ ምንም ማለት አይደለም፣ ያለወሲብ መኖር እንችላለን ወዘተ… የሚሉ የማበረታቻ ቃሎችን ለተቃራኒ ፆታ መስጠት ያስፈልጋሉ፡፡ በሁለቱ መረዳዳት ችግሩ የማይፈታ ከሆነ ወደ ባለሙያ ሄደው በችግሩ ዙሪያ በግልፅ መነጋገርና መፍትሄ መፈለግ ይኖርባቸዋል፡፡
ጭንቀትን፣ ድብርትን፣ ውጥረትንና መሰል ስነ ልቦናዊ ችግሮችን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ አልኮል ከመጠጣት፣ ሲጋራና ሀሽሽን ከማጨስ መታቀብ እንደዚሁም የውስጥ ጤና ችግሮች ካሉ በወቅቱ መታከምም ተገቢ ሆናል፡፡ በአጠቃላይ የስንፈተ ወሲብ ችግሩ ከመድኃኒት ጀምሮ እስከ ቀዶ ህክምና የሚዘልቅ የህክምና መፍትሄ ያለው በመሆኑ ጥንዶች ትዳራቸውም ሆነ የፍቅር ግንኙነታቸውን ቀውስ ውስጥ ከመክተት በፊት ተረጋግተው ለመፍትሄው በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በትዕግስት ጥረት ማድረግም አለባቸው፡፡

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop