July 31, 2014
32 mins read

እኛም የሚሊዮኖች አካል ነን። የአንድነት ጉዳይ ያገባናል – ግርማ ካሳ

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፣  ጊዜያቸዉን ወስደው ፣ በአንድነት ዉስጥ እየታየ ያለዉን በሌሎች ድርጅቶች ያልተለመደ፣ ዲሞክራሲያዊ ፉክክርን በመቀላቀል፣ የድርሻቸዉን ለማበርከት በርካታ ጽሁፎችን አስነብበዉናል። ለዚህም ያለኝን ምስጋና እና አድናቆት መግለጽ እወዳለሁ። ከርሳቸው ጋር በግል የተለዋወጥናቸው ሐሳቦች እንደተጠበቁ ፣ በአደባባይ ፣ በፌስ ቡክ ላቀረቡልኝ አንዳንድ ጥያቄዎች ግን ፣ እኔም በአደባባይ መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ።

«ምርጫ በአንድነት ዉስጥ ፤ ለአቶ በላይ ፍቃደ ድጋፌን እሰጣለሁ» በሚል ርእስ፣  የመምረጥ መብት ባይኖረኝም፣ እንደ ደጋፊ ሐሳቤን የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ፣ አቶ በላይን ኢንዶርስ ማድረጌ ይታወሳል።

«በላይ ጠንካራ መሆኑን እንዴት አወቁ ? በእርግጥ እርስዎ አሁን የያዙትን አቋም ቀደም ብለን እኛም ይዘን ነበር። ሆኖም በላይ ምክትል ሆኖ ከተመረጠ በኋላ፣ እኔ ሐሳቤን አንስቻለሁ። የተወሰኑትም እንዲሁ አደርገዋል። ምክንያቱም በስሩ የነበሩትን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ጉዳዮችን አንቀሳቅሶ መስራት አልቻለም። ለዚህም ይህ ትንሽ ነገር መምራት ካልቻለ ግዙፉን የአንድነት ፓርቲ ይመራዋል የሚል እምነት የለኝም። የእርስዎ ግምገማም መነሻዉን ባውቀው ደስ ባለኝ ነበር» ሲሉ ኢንጂነር  ዘለቀ ጥያቄ አቅርበዉልኛል።

በጣም ጥሩ፣ ወቅታዊና መጠየቅ ያለበትን  ጥያቄ ነው የጠየቁኝ። ኢንጂነር ዘለቀ ፣  ከስድስት ወራት በፊት፣ በላይ ብቃት አለው የሚል እምነት እንደነበራቸው አልሸሸጉም። «ምክትል ሊቀመንበር ከሆነ ጀምሮ ግን፣ ስራዉን አልሰራም» በሚል ነው ትችታቸው።

በላይን  ያለመምረጥም ሆነ፣ በላይ እንዳይመረጥ የመቀስቀስ ሙሉ መብት አላቸው። አቶ በላይ አንድ ትልቅ ድርጅት ለመምራት ራሱን እጩ ካደረገ፣ ጠንካራ ጥያቄዎች ሊቀርቡለት፣ ሊተች ይገባል። ኢንጂነር ግዛቸውም እንደዚሁ።

ኢንጂነር ዘለቀ፣  ከአንድነት ፓርቲ ጋር የተዋሃደው፣ የቀድሞ የብርሃን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ነበሩ። ሁለቱ ፓርቲዎች ሲዋሃዱ፣ ዉህዱን ፓርቲ ለመምራት እጩ ሆነው ከቀረቡ ሶስት እጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አመራር የነበሩ ዶር ንጋት፣ የተከበሩ ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ሁለተኛውና ሶስተኛ እጪዎች ነበሩ። በወቅቱ ኢንጂነር ግዛቸው «ፖለቲካ በቃኝ!  በመምህርነት አገሬን አገለግላለሁ» በሚል እራሳቸውን ያገለሉበትም ወቅት ነበር።

ዶር ነጋሶ ጊዳዳ  በጠቅላላ ጉባኤው ሲመረጡ ፣ ኢንጂነር ዘለቀ ፣ ከአንድ ተፎካካሪ የሚጠበቅ ግሩም ንግግር በማድረግ ከዶር ነጋሶ ጋር አብረው በጋራ እንደሚሰሩ አሳወቁ። በዶር ነጋሶ ካቢኔ ዉስጥም በመመረጥ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆነው መስራት ጀመሩ። እንግዲህ አንባቢያን ተመልከቱልኝ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ያለዉን የዲሞክራሲ ባህል።

የትም ቦታ በሥራ ላይ መጋጨት፣ አለመስማማት አለ። ይሄ ደግሞ ብዙ ሊያስገርመን አይገባም። ያዉም ደግሞ አባላት አስተያየታቸዉን በግልጽ መናገር በሚችሉበት ድርጅት ዉስጥ ፣ ግጭቶች የተለመዱ ናቸው። የግድ አለመስማማቶች መፈጠር አለባቸው። ችግር የሚሆነው አለመስማማቶች፣ ወደ እህልና ግትርነት አምርተው መከፋፈልን ሲፈጥሩ ነው እንጂ። (ኢሕአዴግ ዉስጥ አለመስማማት ሲኖር የበላይ ሆኖ የሚወጣው ቡድን ሌላዉን ወይ እሥር ቤት፣ ወይም ስደት፣ ወይም ካለው ሃላፊነት አባሮ መዋረድ ልማድ እንደሆነ የምታወቅ ነው። የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እንደ ሮቦት በሉ የተባሉትን ማለት፣  ጻፉ የተባሉት መጻፍ፣ ግደሉ፣ ደብድቡ ሲባሉ ሕሊናቸዉን እና ኃይማኖታቸውን ሸጠው ሲገድሉና ሲደበድቡ ነው የምናውቀው።)

ኢንጂነር ዘለቀ በሥራ አስፈጻሚው ዉስጥ ሲሰሩ ከዶር ነጋሶ ጋር የመስማማት ችግር አጋጠማቸው። ከድርጅት ጉዳይ ሃላፊነታቸው ተነሱ። ነገር ግን ኢንጂነር ዘለቀ፣  አኩርፈው ፓርቲዉን ጥለው አልሄዱም። በምክር ቤት አባልነት አንድነትን ማገልገል ቀጠሉ።

ከስድስት ወራት በፊት አንድነት ፓርቲ መሪዉን እንደገና የሚመርጥበት ጊዜ መጣ። ዶር ነጋሶ ፣ የእድሜ ጉዳይ አይፈቅድልኝም በሚልና ሌሎች ምክንያቶች እንደማይወዳደሩ አሳወቁ። ሶስት እጩዎች ቀረቡ። የፓርላማ አባልና በወቅቱ የፓርቲው ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በወቅቱ የፋይናንስ ሃላፊ አቶ ተክሌ በቀለ እንዲሁም «ከፖለቲካ ወጥቻለሁ። በቃኝ » ብለው የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው።

 

በወቅቱ አገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ ያሉ በርካታ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች፣ አቶ በላይ ፍቃደ፣ ደርጅቱን እንዲመራ፣  እንዲወዳደር ጥያቄ አቀረቡለት። ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው  ሳይቀሩ «በላይ ድርጅቱን ለመምራት ብቃት፣ ብቻ ሳይሆን እውቀትና ብስለት ያለው ወጣት አመራር ነው » ሲሉ፣  በላይ ቢወዳደር እርሳቸው ወደ ዉድድሩ ይገቡ እንዳልነበረና ድጋፋቸውን ለበላይ እንደሚሰጡ ይናገሩ ነበር። በላይ «አንድ የአንድነት ተራ አባል፣ ከሊቀመንበሩ ያልተናነሰ መስራት የሚችል ነው። እኔ አገሬን እና ፓርቲዬን ለማገልገል የግድ ሊቀመንበር መሆን የለብኝም»  የሚል አስተሳሰብ ያለው፣ ለስልጣን እና ለወንበር የማይሸቀዳደም፣  እርጋታና ትህትና የተሞላበት ሰው ነው። በመሆኑም ኢንጂነር ግዛቸው ሁሉ ጠይቀዉት፣ ለመወዳደር ፍቃደኛ አለመሆኑ፣ የሚያሳየው የዚህን ሰው ትህትና ነው።

የማታ ማታ ኢንጂነር ግዛቸው የአንድነት ሊቀመንበር ሆነው ይመረጣሉ። አቶ በላይ ፍቃደን  እንዲሁም ከርሳቸው ጋር የተወዳደሩትን አቶ ተክሌ በቀለን ምክትል ሊቀመናብርት አድርገው በመምረጥ ስራ ይጀመራሉ። እርስ በርስ ሲፎካከሩ የነበሩ እንደገና አብረው መስራት ጀመሩ ማለት ነው።

ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ባዋቀሩት ካቢኔ  ከተካተቱት መካከል፣ በዶር ነጋሶ ከሥራ አስፈጻሚ እንዲወጡ የተደረጉት፣ በጠቅላላ ጉባኤውም የምክር ቤት አባል ሆነው በድጋሚ የተመረጡት፣  ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ይገኙበታል። ኢንጂነር ዘለቀ፣ በጣም ቁልፍና  ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ሃላፊነት ይሰጣቸዋል። የዉጭ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሆነው በኢንጂነር ግዛቸው ይሾማሉ። ከስራቸው ዉስጥ በዉጭ ያሉ የድጋፍ ማህበራትን ማሰባሰብና የበለጠ ማደራጀት አንዱና ዋናው ነበር።

የመኢአድ እና የአንድነት ዉህደት ሲጠናቀቅ አዲስ አመራር መኖር ስላለበት፣ የአንድነት ምርጫ በተደረገ በስድስት ወራቱ፣  እንደገና ምርጫ ማድረጉ የግድ ሆነ።

ዉጭ ባሉ ደጋፊዎች ዘንድ አዲስ አመራር የማግኘት ትልቅ ፍላጎትና ጉጉት አለ። ይሄም ኢንጂነር ግዛቸው ላይ ካለ ተቃዉሞ ሳይሆን፣ ኢንጂነሩ ከዘጠና ሰባት ጀምሮ የነበሩ እንደመሆናቸው፣ በቅንጅት ከዚያም አንድነት ዉስጥ ለነበሩ መከፋፈሎች  ተጠያቂ የሚያደርጓቸው ኢትዮጵያዉያን ጥቂት ባለመሆናቸው፣ በአጭሩ ኮንትሮቨርሻል መሪ በመሆናቸው፣ ለዉህዱ ፓርቲና ለትግሉ ከርሳቸው ሌላ አዲስ አመራር  ቢኖር በጣም ጠቃሚ ነው ከሚል አስተሳሰብ ነው።

በዚህም ምክንያት አንድነትም ሆነ ዉህዱ ፓርቲ በውጭ ያሉ ደጋፊዎቹን ከማብዛት አንጻር፣ አቶ በላይ ከስድስት ወራት በፊት የነበረዉን ዉሳኔ ከልሶ፣ እንዲወዳደር ዉጭ ያለው ደጋፊ ግፊት ማድረግ ጀመረ። ይሄ ደግሞ በየትም ዴሞክራሲ ያለ አሰራር ነው። (ትዝ ይለኛል እዚህ አሜሪካ አገር ጀነራል ኮሊን ፓወል፣ ለፕሬዘዳንት እንዲወዳደር፣  ብዙ ግፊት ከየአቅጣጫው ይቀርብለት እንደነበረ)

አገር ቤትም፣ አቶ በላይን በቅርበት የሚያወቁ፣ የጊዜዉን አሳሳቢነት፣ የትግሉን ወሳኝነት በማስመር፣  በነርሱ ዘንድ ያለዉን የአገር ቤት ሁኔታ ጠረቤዛ ላይ በማስቀመጥ፣  የድርሻቸውን ከፍተኛ ግፊት አደረጉ። አቶ በላይ፣ ሊቀመንበር ባይሆንም፣ ለአገሩና ለሕዝቡ ድሮም ሲሰራ የነበረ እንደመሆኑ፣ ፍቃደኛ ሆኖ፣ ሁኔታዎችን አመቻችቶ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀረበ። ይሄም ለብዙዎቻችን መልካም ዜና ሆነ።

«አንዳንዶች ያኔ አልወዳደርም ብሎ አሁን ለመወዳደር ለምን ፈለገ ?» የሚል ጥያቄ አቶ በላይ ላይ ያነሱ አሉ። እንግዲህ መልሱን ከዚህ ጽሁፍ የሚያገኙ ይመስለኛል። ደግሞ እነዚህ ሰዎች፣  ለአቶ በላይ ይሄን አይነት ጥያቄ ሲያቀርቡ  «ኢንጂነር ግዛቸው ፖለቲካ በቃኝ ብለው በነበረበት ጊዜ፣ ከየት መጡ ሳይባል፣  እንደገና ሲወዳደሩ፣  «ለምን ? ምን ተገኝቶ ?» ብለው ጠይቀዋል ወይ ?  አንዳንድ አስተያየቶች ስንሰጥ፣  ትንሽ ደብል ስታንዳርድ ባይኖረን ጥሩ ነው።

ኢንጂነር ግዛቸው ራሳቸውም በተደጋጋሚ እንዳስረዱት ለሊቀመንበርነት ከስድስት ወራት በፊት የተወዳደሩት፣ ብዙዎች እንዲወዳደር ስለጠየቋቸውና ግፊት ስላደረጉባቸው እንደሆነ ገልጸዋል። « እኔ ተለምኜ ነው። አልፈልግም ነበር» ነበር ያሉት። እዚህ ላይ ምን ችግር የለኝም። ልክ ኢንጂነር ግዛቸው እንዳደርጉት፣ አሁን አቶ በላይ፣  ከደጋፊዎቻቸው የሚቀርብላቸውን ጥያቄ አስተናግደው ፣ ለመወዳደር ቢወስኑ ምኑ ላይ ነው ሐጢያቱ ? አስቡት ኢንጂነር ግዛቸው ከፖለቲካ ዉጭ ሆነው ሳለ ነው በአንዴ ዘለው ሐሳባቸው ቀይረው፣ ሊቀመንበር ለመሆን ብቅ ያሉት። አቶ በላይ ግን  አሁን የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር ነው። ከምክትል ሊቀመንበርነት ወደ ሊቀመንበርነት ለመሸጋገር ነው ራሱን እጩ ያደረገው።

አቶ በላይ እጩ ሆነ እንደቀረበ፣ የአብዛኞቻችን ግምት፣ ከጥቂት ወራት በፊት፣  ስለ አቶ በላይ የተናገሩትን ቃል አክብረው፣ ኢንጂነር ግዛቸው የዶር ነጋሶን ፈለግ በመከተል ራሳቸዉን ከእጩነት ያወጣሉ የሚል ነበር። ነገር ግን እንደገመትነው አልሆነም። ኢንጂነሩ ቃላቸውን ገልብጠው፣ ራሳቸውን ለእጩነት አቀረቡ። ያ ብቻ አይደለም፣ «በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ከስድስት ወራት በፊት ምርጫ ስለተደረገ ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሳይወዳደሩ በቀጥታ ነው ማለፍ ያለባቸው» የሚል ክርክር ይዘው የተወሰኑቱ፣  ያለ ምርጫ ኢንጂነር ግዛቸውን ለማስመረጥ ዘመቻ ጀመሩ። እነዚህ ወገኖች ያለ ኢንጂነር ግዛቸው ውስጣዊ ስምምነት፣ ኢንጂነር ግዛቸው ያለምርጫ እንዲሾሙ ለማድረግ ይከራከራሉ ብዬ አላስብም። በሌላ አባባል፣ ኢንጂነር ግዛቸው ራሳቸው፣ ሳይመረጡ በቀጥታ ለማለፍ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል ብዬ አስባለሁ።

ከነዚህ የ«ኢንጂነር ግዛቸው ይመረጡ» ዘምቻ አጧጧፊዎች አንዱ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ናቸው። ኢንጂነር ዘለቀ ፣ ኢንጂነር ግዛቸውን ለማስመረጥ በሚጽፉት፣ በሚያደርጉት እንቅስቃሴውች ሁሉ ምንም ቅሬታ የለኝም። ኢንጂነር ግዛቸው እንዲመረጡ በሥራ አስፈጻሚ ዉስጥ፣ በብሄራዊ ምክር ቤቱ፣  በጠቅላላ ጉባኤው እንዲሁም በአደባባይ የመቀስቀስ፣ የመሟገት ሙሉ መብት አላቸው። መብታቸውን ተጠቅመው፣ የዲሞክራሲ ባህሉን ለማሳደግ ለሚያደርጉት ጥረት አመሰግናቸዋለሁ።

እንደ ማንኛዉ የምርጫ ዉድድር፣ የምንደገፈውን ለማስመረጥ ስንል ፣ የማንደግፈው ለምን መመረጥ እንደሌለበት ማሳየቱ የተለመደና ብዙ ችግር የማይፈጠር ነው። ኢንጂነር ዘለቀም፣ ኢንጂነር ግዛቸው እንዲመረጡላቸው ፣ አቶ በላይ ለምን መመረጥ እንደሌለበት ያመላክታል የሚሉትን የራሳቸውን ምክንያቶች በማቅረብ፣  አቶ በላይ ብቃት የላቸዉም የሚለውን መከራከሪያቸውን ለመሸጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተገቢና ዴሞክራሲያዊ ነው።  አቶ በላይ ሆነ ደጋፊዎቻቸው፣ የአቶ ዘለቀን ትችና አስተያየት በመረጃና በሐሳብ መመከት እንጂ፣  ቅር መሰኘት ያለባቸው አይመስለኝም። እኔም፣ አቶ በላይን ኢንዶርስ እንደማድረጌ፣  ለምን የኢንጂነር ዘለቀ ረዲ መከራከሪያ ነጥብ፣  ዉሃ እንደማይቋጥር ለማሳየት ልሞከር። የኢንጂነር ዘለቀን ረዲ ሐሳቦች በሐሳቦች ለመመከት ማለት ነው።  (አስቡት እንግዲህ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች እንዲህ ባለ ሁኔታ ነው በሐሳብ በመፋጨት የሰለጠነ ፖለቲካ እያሳዩን ያሉት)

ኢንጂነር ዘለቀ፣ ስለ አቶ በላይ የብቃት ጉድለት ሲናገሩ፣ በአቶ በላይ ሥር ያሉ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ዘርፍ ኮሚቴዎች ሥራ አልሰሩም ከሚል ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ኮሚቴዎች ሥራ እየሰሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። ኮሚቴዎች ባላቸው አነስተኛ ሪሶርስ፣  የተቻላቸውን እያደረጉ እንደሆነ የሚገልጹ አንዳንድ መረጃዎች አሉኝ። ኢሕአዴግን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ አንድነት ከኢሕአዴግ ለምን እንደሚሻል የሚገልጹ አማራጭ ፖሊሲ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያሉ እንደሆነ ሰምቻለሁ። እንዲህ አይነቶቹን ሰነድ ማዘጋጀት ጊዜ ይወስዳል። ተራ ደብዳቤ አይደለም። ምሁራንን ማማከር፣ ምርምሮች ማድረግ፣ ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫዎች መመልክት ያስፈልጋል። (በቅርቡ የነዚህ ኮሜቴዎች የሥራ ዉጤት፣ በአዲሱ የውህዱ ፓርቲ አመራር ዘንድ ቀርቦ፣ ዉይይቶች ተደርጎበት ፣ ተሻሽሎ፣  ይፋ ሲሆን የምናየው ይሆናል)

አልሰሩም ብለን ደግሞ ብንቀበልም እንኳን ፣ የነዚህ ኮሚቴዎች ሃላፊዎችን የሾሙት ኢንጂነር ግዛቸው መሆናቸዉን መርሳት የለብንም። በአቶ በላይ የተሾሙ አይደሉም። ለኮሚቴዎቹ ድክመት ሃላፊነት መዉሰድ ያለባቸው ኢንጂነር ግዛቸው ናቸው። ኢንጂነር ዘለቀ አላስተዋሉትም እንጂ ትችት ያቀረቡት ኢንጂነር ግዛቸው ላይ ነው።

ሌላው ኢንጂነር ዘለቀ  በአቶ በላይ ስር ናቸው ያሏቸውን የኢኮኖሚ፣ የማህበረሰባዊና የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚቴዎች እንደጠቀሱት፣ ሌሎች እንደ ዉጭ ጉዳይ ያሉ ኮሚቴዎችን ቢጠቅሱ ጥሩ ይሆንም ነበር። እስከሚገባኝ ድረስ የዉጭ ጉዳይ ኮሚቴው፣ የሚጠበቅበትን ሥራ ሰርቷል ማለት አይቻልም። የዚህ ኮሚቴ ሃላፊ ደግሞ ፣ አቶ በላይን ሥራዉን አልሰራም ብለው የሚጽፉት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ናቸው።

አንድ ጠንካራ የአንድነት ደጋፊ ስለ ኢንጂነር ዘለቀ ሲጽፉ « ኢንጂነር ዘለቀ የዉጭ ጉዳይ ሃላፊነት ስራቸውን ትንሽ አይደለም ምንም አልሰሩም» ነበር ያሉት። እኝህ ደጋፊ ሲያክልም «ታዲያ እርሳቸው ምንም ሳይሰሩ ፣ ስንት ሥራ የሰራዉን፣ በወሬና በአሉባላታ ሳይሆ በስራዉ ዉጭ ሆነ አገር ውስጥ ባሉ ደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያለውን ፣ አንጋፋ የአንድነት አመራርን በአደባባይ ብቃት የለዉም ማለት ነውር ነው» ሲሉ ኢንጂነር ዘለቀ ስለ አቶ በላይ በሰጡት አስተያየት እንደማይስማሙ ገልጸዋል።

አቶ በላይ ፍቃደን፣ ለአንድነት ቅርበት የሌላቸው ወገኖች ላያውቋቸው ይችላሉ። የአንድነት አባላት፣ ደጋፊዎች፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል በቅርበት የሚከታተሉ ግን፣  አቶ በላይን በደንብ ያወቁታል። በተለይም ዉጭ አገር ባሉ የአንድነት ደግፊዎች ዘንድ አቶ በላይ እጅግ በጣም ተወዳጅ ነው።

አቶ በላይ ከሰሩት ጥቂቶቹን  ላካፍላችሁ ( ሌሎች የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ቀንጨብጨብ አድርጌ)

አቶ አንዱዓለም ወደ ቃሊት ከመወሰዱ በፊት ፣ የአንድነት ፎርም የሚባል ዝግጅት በየጊዜው ይቀርብ ነበር። በዚህ ፎረም፣  በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ዉስጥ የተለያዩ እንግዶች እየተጋበዙ ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ሃተታ ያቀርቡ ነበር። ከዉጭ አገርም በስካይፕ ምሁራን እየቀረቡ የሰላማዊው ትግል የሚያደግበትን የተለያዩ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል። የዚህ የአንድነት ፎረም ጀማሪና ዋና አዘጋጅ  አቶ አንዱዓለም አና አቶ በላይ ነበሩ። በዚህ ፎረም ከዉጭ እንደ ዶር መሳይ ከበደ፣ ዶር አክሎግ ቢራራ፣ ፕሮፌሰር ሰይድ፣ አቶ ብርሃነ መዋ፣ ጠበቃ ፍጹም አለሙ፣ አቶ ግርማ ሞገስ የመሳሰሉ ቀርበው የፖለቲካ ሃተታ አቀርበዋል። ከአገር ዉስጥም እንደ እስክንደር ነጋ፣ አሁን በ እሥር ቤት የሚገኙ ዞን ዘጠኖች  የመሳሰሉ ቀርበው ስልጣና ሰጥተዋል።

ሁላችንም መቼም የአንድነት ልሳን የነበረችውን የፍኖት ጋዜጣ እናስታወሳታለን። ይች ጋዜጣ መዉጣት እንድትጀመር  በዋናነት ያደረገው በላይ ፍቃዱ ነው። የጋዜጣው የኢዴቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢም ሆኖ አግልግሏል። ጋዜጣው በወያኔ መታተም ሳትችል ስትቀር ፣ አንድነት የራሱ ማተሚያ እንዲኖረው ለማድረግ ፣ ለዚህ ጉዳይ ከተቋቋመው የፍኖት ግብረ ኃይል ጋር በመተባባበር ገንዘብ እንዲሰበሰብ አድርጎ፣ የማተሚያ መሳሪያዉ ተገዝቷል። በኢትዮጱያ የመብራት ችግር ስለሌለና አገዝዙ የአንድነት ጽ/ቤትን የኤሌትሪክ መስመር ሆን ብሎ ብዙ ጊዜ ስለሚቆርጥ፣ ለማተሚያ ሥራ ጅኔሬተር በመግዛት የሕትመት ሥራው የሚጀመርበት ሥራ ለማፋጠን ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

የአምስቱ አመት ፓላን በሚል ሰፊ ሰነድ መዘጋጀቱ ይታወቃል። ይህ ሰነድ ለድጋፍ ድርጅቶች ተልኮም አንብበነዋል። ይህን ሰነድ ካዘጋጁት ወገኖች መካከል አንዱ አቶ በላይ ነው። (ምናልባትም ኢንጂነር ዘለቀ ያኔ የአንድነት አመራር ስላልነበሩ ላያውቁት ይችሉ ይሆናል)

የአንድነት ፓርቲ ተቀባይነት ከፍ ካደረጉት እንቅስቃሴዎች መካከል በዋናነት እና በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ነው። ይህ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ፣  ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከፖለቲካው ወጥቻለሁ ባሉበት ወቅት፣ የተከበሩ ዶር ነጋሶ አንድነትን ሲመሩ ፣ የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት የተሰኘዉን የመጀመሪያዉ ዙር እንቅስቃሴ ፣  ከሚመሩትና ከሚያስተባብሩት አመራር አባላት መካከል በዋናነት የሚቀመጠው በላይ ነበር።

የተለያዩ ጉዳዮች ሲነሱ፣ በራዲዮኖች ፣ ቴሌቭዥኖች፣  ፓልቶክ ክፍሎች በመቅረብ፣ የአንድነት ደጋፊዎች በሚያዘጋጁት ዝግጅቶች ላይ በስካይፕ በመገኘት፣ የአንድነት ራእይና ተልእኮ በሚገባ የገለጹ፣  ጠንካራ የአመራር አባል ናቸው። እስቲ አቶ በላይ አንድ ወቅት ፣ አሁን በማእከላዊ ከሚገኘው፣ ሌላው አንጋፋ የአንድነት አመራር ጋር በኢሳት ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንስማ። ረጋ ያለ፣ ማሳመን የሚችል፣ የሚናገረዉን የሚያወቅ አመራር እንደሆነ እናያለን።

እንደ እኔ ግምት፣  ትግሉ በአሁኑ ወቅት አዲስ ፣ የበሰለ፣ ባጌጅ የሌው አመራር ይፈልጋል። ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ እየተመለስን መጎተት አንፈልግም። በድጋሚ የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምጻቸውን ለአቶ በላይ ፍቃደ እንዲሰጡ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

አገር ውስጥ ባሉ በከፊል ፣ ዉጭ ባሉ ደጋፊዎች ዩናኒመስሊ ማለት ይቻላል የማይደገፉ፣ ኮንትሮቨርሻል የሆኑ ሊቀመንበር መርጠው፣  አንድነት ሆነ ዉህዱ ፓርቲ ትግሉን ወደፊት ለማስኬድ ያለዉን ብቃት እንዳያሽመደምዱ እመክራለሁ።

እኔም ሆንኩኝ ሌላው ተራ ደጋፊ፣ አስተያየት መስጠት እንጂ መራጮች አይደለንም። የአንድነት፣ የዉህዱ ፓርቲ፣ የትግሉን አቅጣጫ የሚወስኑት አገር ቤት ያሉት፣  የጠቅላላ ጉባኤ ተወካዮች የሆኑት እንደ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ናቸው። በሥራቸው አልገባንም። እነርሱን ለማዘዝና ለመጫን መብትም የለንም፤ አልሞከርንምም። ነገር ግን  አንድነት፣  የሚሊዮኖች ንቅናቄ የሚመራ፣  ሚሊዮኖች እያሰባሰበ ያለ እንደመሆኑ፣  «እኛም የሚሊዮኖች አካል ነን። የአንድነት ጉዳይ ያገባናል» በሚል ነው አስተያየት የምንሰጠው።

በዚህም አጋጣሚ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ከዚህ በፊት የተናገሩትን  ቃል አክብረው፣ አመራሩን ለአዲሶች በማስረከብ የዶር ነጋሶን ጊዳዳ ፣ የዶር ኃይሉ አርአያን፣ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ .. ፈለግ እንዲከተሉ በድጋሚ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

 

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop