ከአንዷለም አስራት [email protected]
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ የማከብራቸውና የሶስት አፋኝ መንግስታትን ጭቆና ከህዝብ ጫንቃ ላይ ለማንሳት እየታገሉ ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እና የአረና ትግራይ አባል የሆነው አብርሃ ደስታ የትግራይ ህዝብ የወያኔ አገዛዝ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ለማስረዳት የሞከሩት ስህተት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ አገልግሎት፣ በመሰረተ ልማትና በልማት ባለፉት 23 አመታት በአንጻራዊነት ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሆነ ለማስረዳት እሞክራለሁ። ይህን ስል የትግራይ ህዝብ አልፎለታል ፤ በልጽጓል፤ ከድህነት ወጥቷል እያልኩ ሳይሆን ህዋሃት በሚያደርገው በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ አድልኦ ምክንያት ከሌሎች ክልሎች የተሻለ የስራ እድል ተፈጥሯል ፤ የተሻሉ የአገልግሎት ተቋማት አሉ፤ እንዲሁም ከፍ ያለ የገንዘብ ፍሰት አለ ይህም የሆነው የሌሎችን ክልሎች ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ነው የሚለውን ለማስረዳት ነው። ከመጀመሪያው ማስረገጥ የምፈልገው ግን ለወያኔ ወንጀሎች የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።
1. በፖለቲካ
ወያኔ በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው ፣ የወያኔን ዓላማ የማይደግፍ ትግረኛ ተናጋሪ በጣም ጥቂት እንደሆኑ ይታዎቃል፡፡ አብዛኛዎቹ ትግርኛ ተናጋሪ የህዋሃት ተቃዋሚዎች አላማውን ሳይሆን ግለሰቦቹን የሚጠሉ መሆናቸው የታዎቀ ነው፡፡ እነ ገብሩ አስራት ፣ ስየ አብርሃ ፣አረጋዊ በርሄ የመሳሰሉት ከወያኔ የተለዩት አላማውን ጠልተው ሳይሆን መለስ ዜናዊና መሰል አምባገነኖችን በመጥላት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አንጋፋው ገብረ መድህን አርአያ ግን የወያኔን አላማ የማይቀበል እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ሁኖም የሁሉንም ትግርኛ ተናጋሪዎች የፖለቲካ አቋም አውቃለሁ ብየ አልታበይም ሌሎችም የወያኔን እኩይ ተግባር የማይደግፉ ይኖሩ ይሆናል ግን አብዛኛው ደጋፊ መሆኑ አሊ አይባልም።
ስለዚህም ወያኔ የትግርኛ ተናጋሪ ምሁራንን ሙሉ አቅም በሁሉም የስራ መስኮች ይጠቀማል፣ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ በክልል ከተዋቀረችበት ጊዜ ጀምሮ የትግራይ የተለያዩ ቢሮዎች በአንጋፋና የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው የቢሮ ሃላፊዎች ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚሁ ምሁራንም የውስጥ ነጻነታቸው የተጠበቀ በመሆኑ በሙሉ አቅም ይሰራሉ፡፡ በተቃራኒው የሌሎች ክልሎች ተዎላጅ የሆኑ አብዛኛዎቹ ምሁራን የወያኔን አላማ ከመጀመሪያው የተጸየፉ በመሆናቸውና ወያኔም ገና ከጅምሩ በጣላቻና በጥርጣሬ ስላያቼውና እንዲጠጉ ስላልፈለገ በተለጣፊ ድርጅቶች መዋቅሮቹ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ በዚህም ምክንያት በሌሎች ክልሎች ከክልል አስተዳዳሪዎች ጀምሮ ትምህርትም ፣ብቃትም፣ ልምድም የሌላቼውና ጠርናፊ ወያኔዎች ሲጠሩዋቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ ፣ ታማኝነታቼውንም ለማሳየት የተሻለ ነገር ከመስራት ይልቅ በሚገዙት ህዝብ ላይ ቀንበር የሚያጠቡ ደካሞች ክዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ስልጣን ተሰግስገውበታል፡፡ ለዚህ አለምነው መኮንን አይነቶችን እንደምሳሌ ማየት ይቻላል፣ አለምነው መኮንን መለስ ዜናዊን ያመልክ እንደነበር ይነገራል ፣አለቆቹ የመለስን ራእይ ማስቀጠል ሲሉ ሰምቶ እሱም ራሱን ጭምር አይሰድቡ ስድብ ሰደበ፡፡
ስለዚህም ትግራይ የተሻለ ትምህርት፣ ልምድ፣ ብቃት፣ ዝግጁነት እና ሙሉ ስልጣን ባላቸው ሰዎች የሚተዳደር ክልል እና ህዝብ በመሆኑ ተጠቃሚ ነው፡፡
በአንጻራዊነት መልካም አስተዳደርም አለ ማለት ይቻላል፤ ፖለቲካውን እስካልነካ ድረስ ማንኛውም ትግራዊ በትግራይ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም አቅሙ የፈቀደውን ይሰራል። አሁን ያለው የፖለቲካ ስርአት ቢቀየር የትግራይ ህዝብ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ምናልባት አምልካከታቸውን ቀይረው ዲሞክራቶች ይሆናሉ ብለን እናስብ እንደሆነ እንጅ የተለዩ ሰዎች ያገኛል ብየ አላስብም ፤ ምክንያቱም የአረናና የህዋሃት ልዩነት የግለስቦች ጸብ ብቻ ነው ብየ አስባለሁ።
በኢኮኖሚ
ሀ. በኢትዮጵያ በጣም ሀብታሙ ድርጅት ኢፈርት ነው፣ ኢፈርትም ትግራይ ውስጥ ከሃያ በላይ ግዙፍ ድርጅቶች አሉት፣ የነዚህ ድርጅቶች ክፍተኛ ገቢ የት እንደሚገባ መረጃው ባይኖረኝም እነዚህ ድርጅቶች ግን በጣም ብዙ የስራ እድል ትግራይ ውስጥ ከፍተዋል፣ ብዙ የትግራይ ወጣቶች በትግራይ ውስጥም ሆነ ከትግራይ ውጭ የዚህ ህገውጥ ድርጅት ተቀጣሪ በመሆን የሌሎች ክልሎች ወጣቶች ያላገኙትን እድል አግኝተዋል፡፡ በነገራችን ላይ የኢፈርት የገንዘብ ምንጭ በጦርነቱ ወቅት ከወሎ፣ ከጎንደር፣ ከጎጃምና ከወለጋ አካባቢዎች የተዘረፈ ገንዘብና እንዲሁም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ በትእዛዝ የተወሰደና ከጊዜ በኋላ እንዲሰረዝ የተደረገ ብድር ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች የሌሉ በርካታና ብዙ ቢሊዮን ብር ኢንቭስት ያደረጉ ድርጅቶች የስራ እድል ሲፈጥሩ የክልሉ ህዝብ አልተጠቀመም ማለት አይቻልም።
ለ. ህወሃት በጠባብ አላማው ከጎንደርና ከወሎ በጣም ሰፊ ለም የእርሻ መሬት ዘርፏል፣ ይህንንም የእርሻ መሬት ለአባላቱና ሌሎችም የትግራይ ተዎላጆች ብቻ አከፋፍሏል፣ እንዲሁም በርካታ የትግራይ ገበሬዎች በነዚህ ለም መሬቶች ሰፍረዋል፣ እነዚህ መሬቶች ቀደም ሲል በሌሎች ሰዎች የተያዙና የሁመራ አካባቢ ደግሞ የመንግስት እርሻ የነበረ ነው፡፡ ይህንኑ የዘረፈውን መሬት ህጋዊነት ለማረጋገጥ ይመስላል ወያኔ በተለይ በወልቃይት አካባቢ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አካሂዷል፣ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ታፍነው ተወስደው የደረሱበት አይታዎቅም፡፡ በነዚህ መሬቶች መወሰድ ምክንያት በርካታ የጎንደር ስዎች ተፈናቅለዋል፤ ተጎድተዋል፡ የትግራይ ሰዎች ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅመዋል።
ከዚህ ጋር የተያያዙ በተለይ በሁመራ አካባቢ የተደረጉ ሶስት ነገሮችን ልጥቀስ፤
በተፈጥሮ በተራቆቱ የጎንደርና የወሎ አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎች በቂ የእርሻ መሬት ስለሌላቸውና በለም አካባቢዎችም መስፈር ስለማይፈቀደላቸው ወደሁመራ አካባቢ እየሄዱ በቀን ሰራተኛነት ህወሃትን ያገለግላሉ፣ እነዚሁ ድሆች ከደጋው አካባቢ የመጡ፡በመሆናቸው ለወባና ሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ ይጋለጣሉ፣ መጀመሪያም እንደሰው የማይቆጥሯቸው የትግራይ ባለሃብቶችም ሲታመሙ አውጥተው ይዎረውሯቸዋል በርካቶችም በዚህ ሁኔታ ይሞታሉ፡፡ ይህን ሪፖርት ያደረገው በጊዜው በቦታው እርዳታ ይሰጥ የነበር የ MSF ሰራተኛ ፈረንጅ ነው። በጊዜው ሰው እንዴት በሰው ላይ እንደዚያ እንደሚጨክን በግርምት ያውራ ነበር። እንደዚህ አይነት ሰዎች ወደሁመራ ለስራ መሄድ በደርግ ጊዜም የነበረ ሲሆን በዚያን ጊዜ ግን በቂም ባይሆን እንደሰው ህክምና የማግኘት እድል ነበራቸው፡፡
ሌላው ባለፈው አመት በሚድያ እንደተነገረው በህዋሃት ካድሬዎች ደባ የቀን ሰራተኞቹ የወሎና የጎንደር በሚል በቡድን ተከፋፍለው ለሳምንታት ሲጨራረሱ የአካባቢው ፖሊስም ሆነ የወያኔ የመከላከያ ሰራዊት ግጭቱን ለማስቆም አጥጋቢ እርምጃ አልወሰዱም፡፡
ሶስተኛውና ከአመት በፊት ከስፍራው ከመጣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረ ወጣት የተገለጸው የቀን ሰራተኞቹ የሰሩበት ደመዎዝ ተከፍሏቸው ከወያኔ እርሻዎች ሲወጡ በቅርብ ርቀት በሽፍቶች በተደጋጋሚ መዘረፋቸው ነው፣ በኋላ የቀን ሰራተኛ የነበረው ይህ ወጣት ያረጋገጠው ነገር ቢኖር ግን በሽፍታ መልክ መልሰው የሚዘርፉትም ቀደም ሲል ደመወዝ ከፋይ የነበሩት የእርሻዎቹ ባለቤቶች የሆኑት የህዋሃት ካድሬዎች ናቸው፡፡
በሶስቱም መንገድ የህዋሃት ካድሬዎች በነጻ ጉልበት ስራቸውን ያሰራሉ፡፡ ድሆቹ ገበሬዎች ደግሞ ወደቤተሰባቸው የመመለስ እድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ብዙዎቹ በበሽታና በእርስ በርስ ድብድብ ያልቃሉ ቀሪዎቹም በተደጋጋሚ የሰሩበት በቀጣሪዎቹ ስለሚዘረፍ ወያኔ ያዘጋጀላቸውን የባርነት ኑሮ ይቅጥላሉ።
ሐ. በኢትዮጵያ የወታደራዊ (90% በላይ የኢትዮጵያ ጀኔራሎቹ ትግርኛ ተናጋሪዎች ናቸው)፣ የደህንነት፣ የጉምሩክ፣ የኢምባሲ፣ የቴሌ፣ የመብራት ሃይል፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር በተለይ በክፍለ ከተማና በወረዳ (አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ትግርኛ ተናጋሪዎች ናቸው) ፣የአየር መንገድ፣ የፖስታ ቤት፣ የስኳር ፋብሪካዎችና ሌሎችም በፌደራል መንግስት ስር የሚተዳደሩ መስሪያ ቤቶች ቁልፍ ቦታዎች በአብዛኛው የተያዙት በትግርኛ ተናጋሪዎች ነው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የእርዳታ ድርጅቶች የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ትግርኛ ተናጋሪዎችን በብዛት እንዲቀጥሩ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚመጡት ከትግራይ ነው ስለዚህም ትግርኛ ተናጋሪዎች ከሌላው ክልል ተወላጆች የበለጠ የስራእድል አላቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ አዲስ አበባን የሰማይ ጠቀስ ፎቆች ባለቤት ያደረጓት ጀኔራሎች ትግራይ ውስጥ ምንም ኢንቭስት አያደርጉም አይባልም፡፡ የየመስሪያቤቶቹን ቁንጮ ስልጣን የያዙት ትግረኛ ተናጋሪዎች በክልላቸው ኢንቨስት አያደርጉም ማለት ዘበት ነው። በአንድ ወቅት “አዲ በግዲ” ተብሎ ሁሉም ከትግራይ ውጭ የሚኖር የክልሉ ተዎላጅ በትግራይ ከተሞች ቤት እንዲሰራ ተደርጎ እና በርካታ ቤቶች ተሰርተው ተከራይ ጠፍቶ እንደነበር ይታዎሳል።
መ. የትግራይ ተወላጆች በፈደራል መንግስትና በሌሎችም ቦታዎች ባላቸው ስልጣን ተጽኖ በማድረግ በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ ፕሮጄክት እንዲኖራቸው ይታዘዛሉ አንዳንዶችም ፕሮጄክቶቻቼው በቀና መንገድ እንዲሄዱላችው ቀድመው ትግራይን ይመርጣሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ትግራይ ውስጥ ቅርንጫፍ የሌለው፡የውጭም፡ሆነ የአገር በቀል ድርጅት ጥቂት ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ትግራይ ውስጥ ደግሞ ማንም የውጭ ሆነ የአገር ውስጥ ድርጅት የሌላ ክልል ተወላጅ መቅጠር አይታሰብም ቋንቋ እንደምክንያት ይቆጠራል፤ በተቃራኒው የትግራይ ተዎላጆች በሌሎች ክልሎች ውስጥ በብዛት ይሰራሉ።
2. በማህበራዊ አገልግሎት
የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲወዳደር የተሻለ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ያገኛል፣ በምሳሌ ላስረዳ ወያኔ ብዙ ያዎራለትን የጤና አገልግሎት ብናይ በ2000 አ. ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሪፖርት በትግራይ ለሚኖር 4.5 ሚሊዮን ህዝብ 15 ሆስፒታሎችና 123 ጤና ጣቢያዎች ይህም ለ304333 ህዝብ አንድ ሆስፒታልና ለ37113 ህዝብ አንድ ጤና ጣቢያ ሲሆን በአማራ ደግሞ ለ20.1ሚሊዮን ህዝብ 20 ሆሰፒታሎችና 183 ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ፡ ይሕም አንድ ሆስፒታል ለ1ሚሊዮን ህዝብ እና አንድ ጤና ጣቢያ ለ110636 ህዝብ ይደርሳል፡፡ ይህ ቁጥርን በሚመለከት ሲሆን በአማራ ክልል ያሉት ሆሲፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በመስፈርቱ መሰረት የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ ሳይሆኑ የተሾሙ ናቸው [የተሾሙ ማለትም በወያኔ ሹመት ብቃት ስለማይጠይቅ ያለብቃታቸው ለፖለቲካ ጠቀሜታ የተሰየሙት ጤና ድርጅቶችና ትምህርት ቤቶች የተሾሙ ይባላሉ]በዚህ በወያኔ ዘመን የሚአርጉ ድርጅቶችም እንዳሉ ስነግራችሁ የቀልድ ይመስላችሁ ይሆናል፣ የአረጉ ማለት ያልተሰሩ ግን እንደተሰሩ ተደርገው ሪፖርት የሚደረጉና እንደተሰሩ ተደርጎ የወጣው ገንዘብም በየደረጃው የሚወራረድ ማለት ነው፡፡ ከጥቅሙ ተካፋይ ያልነበረ ተቆጣጣሪ ሲመጣ ድርጅቱ ማረጉ ይነገረዋል፡፡
3. በመሰረተ ልማት
ትግራይ በመሰረተ ልማት ማለትም በመንገድ ፣ በቴሌኮሙኔኬሽን ፣ በመብራት ከሌሎቹ ክልሎች በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በቅርቡ ሪፖርተር የሚገርም ዜና አውጥቷል አንድ ትግራይ ውስጥ ለሚሰራ መንገድ ሱር ኮንስትራክሽን የ2ቢሊዮን ብር ውል ፈረመ የመንገዱ ርዝመት 53ኪሚር ሲሆን ለአንድ ኪሎ ሜትር 40ሚሊዮን ብር ይከፈለዋል፡፡ እስካሁን በአገሪቱ ለኮንትራክተር የተሰጡ መንገዶች በኪሎሜትር ከ20ሚሊዮን አይበልጥም ነበር ይላል፡፡
4. በልማት
ባለፉት 23 አመታት ትግራይ ውስጥ በአድዋ፣ አዲግራት ፣ መቀሌ ፣ ማይጨው በርካታ ፋብሪካዎችና የአገልግሎት ሰጭ ትቋማት ተሰርተዋል እነዚህም ድርጅቶች ለብዙ ሰዎች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
ከዚህ በላይ የቀረቡት መረጃዎች የሚያሳዩት ትግራይ ውስጥ የተሻለ መሰረተ ልማት ፣ ማህበራዊ አገልግሎትና በጣም የተሻለ የሰራ እድል መኖሩን ነው፡፡ ወያኔ ማእከላዊ መንግስቱን በመቆጣጠሩ ለወጣበት ክልል ልጆች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ወያኔ ለትግራይ ወጣቶች ያመጣላቼው ግን የተሻለ የስራ እድልና ገንዘብ ብቻ አይደለም፤ በየሄዱበት በጥርጣሬ መታየትን በአንዳንድ ቦታም መጠላትን ጭምር እንጅ።
ይህ የወያኔ አንድን ክልል ለብቻው ሌሎችን ክልሎች በሚጎዳ መልኩ ለማሳደግ የሚደረግ ጥረት ፍሬ እያፈራ ነውን? የሚል ጥያቄ መጠይቃችን አይቀርም። መልሱ አዎ የትግራይ ህዝብ የተሻለ የትምህርት ደረጃ ፤ ዝቅተኛ የስራ አጥ ቁጥርና በተለይ በህጻናት ሞት ዝቅተኛ መጠን አስመዝግቧል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 በአሜሪካ የእርዳታ ድርጅትና በማእከላዊ ስታቲስቲክስ ድርጅት በተደረገ የህዝብና የጤና ጥናት (Demographic and health survey) መሰረት ክጥናቱ በፊት ባሉት 12 ወራት ውስጥ ምንም ስራ ያልሰሩ ወይም ያልተቀጠሩ ሴቶች በመቶ ሲለካ በትግራይ 24.8%፣ በአማራ 38.4%፤ በኦሮሚያ 43.9% ና በደቡብ ህዝቦች 44.8% ነበር። በተመሳሳይ ጥናት መሰረት በእርግዝናቸው ጊዜ በሰለጠነ ባለሙያ ምርመራ የተደረገላቸው እርጉዞች በመቶ የሚከተለውን ይመስል ነበር፤ ትግራይ 50.1% ፤ አማራ 33.6% ፤ ኦሮሚያ 31.5% ፤ የደቡብ ህዝቦች 27%. ከዚህ ላይ የትግራይም ሽፋን ቢሆን በቂ ነው ማለት አይደለም ግን ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲውዳደር ከፍተኛ ነው።
በተመሳሳይ ጥናት መሰረት ክትባት የተከተቡ ህጻናት በመቶ ትግራይ 73.4%፤ አማራ 38.4%፤ ኦሮሚያ 26.8% ና ድቡብ ህዝቦች 38.1% ነበር።
በዚሁ ጥናት መሰረት ከአንድ አመት በታች የሆኑ ህጻናት ሞትና (IMR) ከአምስት አመታት በታች ባሉ ህጻናት የሞት መጠን በሚቀጥለው ሰነጠረዥ ቀርቧል
ከዚህ በላይ እንደሚታየው ትግራይ በሁሉም መለኪያዎች የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትግራይ በ 2005 የደረሰበት ደረጃ ሌሎቹ ክልሎች በ2011 ማለትም ከ5 አመታት በኋላም አልደረሱም ፤ በሌላ አነጋገር ሌሎቹ ክልሎች ትግራይ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ከ7-8 አመታት ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ውስጥ አንድ ቀልድ አለ እሱም ቀደም ሲል አንድ ወጣት ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ? ሲባል ፓይለት ፤ ዶክተር ማለት የተለምደ ነበር፤ ያሁኑ ወጣቶች ግን ምን መሆን ትፈልጋለህ ሲባሉ ቶሎ ብለው “ትግሬ” ይላሉ። አሁን ባቋራጭ ሀብታም የሚያደርገው ፓይለትነት ወይም ዶክተር መሆን ሳይሆን ከገዥ ጎሳ መወለድ በመሆኑ ነው።
ለማጠቃለል ያህል በሁሉም መስፈርቶች የትግራይ ክልልም ሆነ ግለሰብ ትግርኛ ተናጋሪዎች የወያኔ ከፋፍለህ ግዛ ስርአት ተጠቃሚዎች እየሆኑ ነው ይህም እንዲቀጥል ወያኔ ሌሎች ክልሎች ብቃት ባላቸው ሰዎች እንዳይተዳደሩና ለእድገት ጥረት እንዳያደርጉ ሌሊት ከቀን ተግቶ ይሰራል። የክልል ፕሬዘዳንቶችን ይሽራል፤ ይሾማል፤ ይቆጣጠራል። ህዝብን ከህዝብ ያጋጫል ፤ ያፈናቅላል። ሲፈልግ አመጽ ያስነሳል፤ አመጹን ልቆጣጠር በማለት ይገድላል ፤ ያስራል፤ ከስራም ያፈናቅላል።
የዚህ ሁሉ ግፍ ቁናው ሞልቶ ዶክተር መረራ በተደጋጋሚ እንደሚሉት የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ሳይበላ ሊታሰበብት ይጋባል እላለሁ።
ቸር ይግጠመን።