ሰማዕታት ሲታሰቡ።
ከሥርጉተ ሥላሴ 08.06.2014 (ሲወዘርላንድ – ዙሪክ)
ሰማዕታት ሲታሰቡ፤ ከቅርንጫፉ እ! ውጋት ነው። ከወገቡ እ! መጋኛ ነው። ከቋንጃው እ! ቁርጠት ነው። ከእጁ እ! ካንሰር ነው። ወያኔ ከሥረ መሰረቱ ነው መነቀል ያለበት። ስለምን የኢትዮጵያን ሉዕላዊ ህልውና አደጋ ላይ የጠላ ትውልድን ያሚያጠቃ ማነፌስቶ ስላለው። የወያኔ ማኒፌስቶ አንድን ዘር ብቻ መሰረት አድርጎ የተነሳ የጎጥ ማንፌስቶ ነው። ስለሆነም ነው ህልውናውን ለማቆዬት መሰል ተለጣፊ የጎጥ ድርጅቶችን ፈብርኮ የኢትዮጵያን ችግር ወስብስብ፣ ትብትብና ዳጥ ያደረገው።
በጎጥ ተመርቶ ለድል የበቃ፣ የህዝብን ጥቅም በእኩልነት ያስጠበቀ አንድም ሀገር ለናሙና ማቅረብ ፈጽሞ አይቻልም። የለም እንጂ – ቢኖርም እንኳን ለኢትዮጵያ እንደ ተፍጥሯዋ የራሷ አምክንዮዊ መንገድ ሊኖራት ይገባል። ልዕልት ኢትዮጵያ በኩረጃ ንድፍ ልትመራ የምትችል ሀገር አይደለችም። አሁን ኢትዮጵያ ሀገራችን ለዛውም በአንሳው ጎሳ ስብስብ ነው እዬተጎረደች ያለችው። የአንድ ጎጥ ድርጅት ማዕከሉ ጎጡ ብቻ ነው። ከዚህ የሚያልፍ ራዕይና አመለካከት የለውም። ሊኖረውም ፈጽሞ አይችልም። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሀገራዊ ሃብታት በሙሉ ይጠቀጠቃሉ – ይደፈጣጣሉ። ሃብታት ሲባል የሃብት ሃብት የሆነውን የሰለጠነውን የሰውን ልጅን ጨምሮ።
የሰውን ልጅ እኩልነት ማዕከል ያላደረገ አስተዳደር ደግሞ ትንፋሹ ጥፋት ነው። ጥፋቱ ምትክ የማይገኝለትን የህዝብና የሀገር ፍልሰት ምድረ – በዳነት ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደ ቤተ ሙካራ ጥንቸል ሁሉ ተሞክሮባታል። የዐፄ ሥርዐት ለዘመናት፤ የሶሻሊስት ሥርዐት ለ17 ዐመታት፤ ቋንቋን መሰረት ባደረገ ፌድራዚም የጎጥ አስተዳደር ደግሞ ለ23 ዓመታት። ሁሎችም ግን የህዝብን መከፋት ያደመጡ ባለመሆናቸው ሁልጊዜም ከስሜን እስከ ደቡብ፣ ከደቡብ እስከ ምስራቅ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለውን የህዝብ ችግር መፍታት አልቻሉም። ትናንትም እንባ ዛሬም እንባ …. ኑራቸው ሆኗል። የእንባና የደም መኖር። ቀረ የሚባል አንዳችም የሙከራ ጣቢያ፤ ሆነ ሥልት የለም። የቀረው ነገር „ሀገር አለኝ“ ማለት አፋፍ ላይ ያለበት ሁኔታ ብቻ ነው። በዘመነ ወያኔ – ስለትናንት የሚናገሩ ማናቸውም ሃብታት ተቀጥቅጠዋል፤ በፋስ ተፈልጠዋል፤ በገጆሞ ተከታትፈዋል። አፈሩም – ተፈጥሮውም – አዬሩም አልቀረለት። የትኛውም መሥሪያ ቤት ለመግባት የመጀመሪያው መጠይቅ ብሄረሰብህ ከዬት ነው? ዜግነትን ዘቅዝቆ ያንጠለጠለ – ደም የሚያዘንብ የመገለ ዘመን። የሁሉም ነገር ልኬታ መስፈሪያ ወቄቱ ጎሳ …. ጠቀራ! እንዲያውም በተገላቢጦሽ ኢትዮጵያዊነትን ለማወጅ ወንጀል የሆነበት የተኮደኮደ ዘመን፤ ኩፍትርትር የነቀዘ የጨቀጨቅ ወቅት፤ እጅግ የተማረረና ያለቀሰ ዘመን። ህም!
ከእንግዲህ በኋላ ለሁሉ መዳህኒት የሆነ የአቅም ጥሪት መሰብሰብ ግድ ይላል። የአቅም ምንጩንም ሚስጥር ለማግኘት ተግቶ መባተል። ይህ የአቅም ጥሪት አነሳው ብዙኃኑን ወይንም ብዙኃኑ አናሳውን ሊጨቁኑ ወይንም ሊድጡ የማይችሉበት ወጥ ሥርዓት መፍጠር ነው – ሥርዬቱ። የትርጉም ሥራ ለኢትዮጵያ ጠፍ ፍልስፍና ይመስለኛል። አቅብቅበው የሚጠብቁ ባዕዳን ስሜቶች አሉ። ቅስማቸው የሚሰበረው ከራሳችን – ከውስጣችን መነሳት ስንችል ብቻ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነት እኮ ከሰማዩ ፈጣሪ በስተቀር የትኛውም ፕ/ ሆነ ሳይንቲስት አንቦልቡሎ ወይንም ጠፍጥፎ ሊሠራው ከቶ የሚችል አይደለም። አንዷን ነገር ነጥለን አውጥተን የማን ነሽ? ማን ፈጠረሽ? መቼ ተገኘሽ? ብለን ብንመረምራት? ሃብትነቷ የሁላችንም መሆኑን በድፍረት አንገቷን ቀና አድርጋ በልበ ሙለነት ትነግረናለች።
ይህንን እርቀን – ከማንርቀው፤ ገፍተን – ከማንገፋው ወይ ካለባበሳችን፤ ወይ ከአመጋገባችን፤ ወይ ከጋብቻ ሥርዓታችን ብቻ አንዷን ዘለላ አንሱና ጠረጴዛ ላይ አስቀምጧት፤ እናንተም በክብር ወንበራችሁን ይዛችሁ ተቀመጡ። ተወያዩ! ጣዕሙ – ጠረኑ የሚውደው ባለቤትነቱ የእኔም – ያንችም – የእርሶዎም መሆኑን ነው። ሰውሰራሽን መጸሐፍ ማንበብ ይቻላል። መተርጎምም ይቻላል። በብዙ ጥልቅ ቅመም የተቀመረን – የነጠረ አንቱ የማንነት ተፈጥሮን ግን በእውነቱ አይቻልም። ይህንን ነው ወያኔ የተዳፈረው። ይህን ነው ደቁሶ አቃጥሎ አመድ ለማድረግ እዬታገለ ያለው። ይቻለዋልን? ወደ ራሳችን ተመልሰን ራሳችን እንጠይቅ። መልሱ አቅማችን ይለካል። መልሱ ትውልድን ታሪክን ሀገርን ይታደጋል ወይ ያከስላል። እራስን ማሸነፍ ድፍረትን ይጠይቃል። ራስን ሃቅ ማንተራስም ወኔን ይሻል። ራስን መሆን መቻልም ክህሎት ነው። እንደ እራስ ለመኖር መቁረጥም ቁሞ ያስኬዳል። አንገትን ቀና አድርጎ እኩል አፍሪካዊነትን ያጎናጽፋል፤ ልብን አደላድሎ ዓለምአቀፋዊነት ይሸልማል።
ስለሆነም ይህን መንገድ ለማግኘት በጎጥ ተደራጅቶ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ወይንም በዕምነት ተደራጅቶም የማይታሰብ ነው። አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ዘግቶ መኖርን እሰቡት። ይህ ለኑሮ አፍ ያለው መቃብር ነው – እፍን። የታሪኳ፤ የባህሏ፤ የቀለሟ፤ የሥልጣኔዋ፤ የተፈጥሮ ሃብታቷ፤ የእምነት ውርርሷ፤ የመልካዕ – ምድራዊ አቀማመጧ፤ የህዝቦቿ ሥነ-ልቦናዊ አመለካከት – ውበቷ፤ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የነበራት የባህል – የወግ – የልማድ የመልካም ጉርብትና ውርርሷ፤ የተፈጥሮዋ ጥልቅነት ተመርምሮ መነሻውም መድረሻውም፤ ጎጠኝነትን አላይህም አለስማህም የሚል የእንቢተኝነት መንፈስ መፍጠር ያስፈልጋል። እኩልነትን ያደመጠ፤ ማስተዋልን የሰነቀ፤ ሰብዕዊነትን ማዕከል ያደረገ፤ ነፃነትን የኳለ ኢትዮጵያዊ ንድፍ – ነድፎ ተግባራዊ ማደረግ ሲቻል ያን ጊዜ የተበተነ ሃሳብ፣ የተጎዳ መንፈስ፣ የቆሰለ አካል፣ የጎሳቀለ ህሊና ፈውሱ ይገኝለታል። በእያንዳንዱ ዜጋ ያለውን የታሰረ ፍላጎት ሊፈታ የሚችለው በበዚህ መንፈስ ስንሰባሰብ ብቻ ይሆናል። የኮሰሰ ወይንም የኮሰመነ ስሜትንም ወደ እራስ አስጠግቶ ሃብት ማድረግ የሚቻለው ያሰረንን ትብትብ እራሳችን በራሳችን ይፍታህ ስንለው ብቻ ነው። በዚህ ዙሪያ እኮ ብዙ አንደበቶች ታስረው ነው የሚታዩት ….
ከሞት በላይ ምን የከፋ ነገር አለ?! በተለይ ለአንዲት እናት ሀገር፣ ሆነ ለወለደች እናት ልጇን ከማጣት የበለጠ ምን መራራ አሳንጋላ ነገር አለ?! እጅግ ከመከራዎች ሁሉ ጎምዛዛው የልጅን መከራ ቆሞ ማስተናገድ ነው፤ በወያኔ መርዝ ይህንን እንኳን በእኩልነት ለማስተናገድ ተፈጥሮን የጋጠ ገጠመኝ ነው ያለው። ስለምን? መከራን መጋራትን ሸሽተናዋል። እንዲያውም በአንዱ መካራ ሌላው ያላጋጣል፤ በሌላው ጥቃት አንዱ ይስለቃል። ይህ ዛሬን ያሳድራልን? ይህ ነገን በብሩህ ተስፋ ያጫልን? እእ! እርግጥ ነው ለዚህ ተፈጥሮን የዘለለ ሰብእናን የጨፈለቀ የግዴለሽነት የመንፈስ ሆነ ዬበረሃማናት ባዕዳዊ ስሜት ወያኔ ጸንፆ ኮትኩቶ ያሳደገው ነው። ይበል እያለም ግርማ ሞገስ እልብሶ አሽሞንሙኖ የዳረው የኳለው መርዝ መሆኑ ይረደኛል። ግን ነገር ግን ይህ ለእኛ መዳኛችን ሳይሆን መጥፊያችን ነው። ይህን አሸንፈን ጥሰን የወጣን ዕለት ትንሳኤ ነው። በስተቀር ግን ከዚህ የባሰና የከፋ የተጋጋጠ እንዲሁም የደማ – በበቀል እርር ኩምትር ያለ ጥንዙል ነገ ከፊት ለፊታችን ያፋጠናል። እጅግ የምናፍቃችሁ ወገኖቼ የሀገሬ ልጆች – እኛም በዚህ ዙሪያ ወስጥ ወይንም ውጪ መሆናችነን ከራሳችን በላይ ሌላ የፖሊስ መርማሪ የለምና እንፈትሽ ….
ወያኔ ሌባ ነው። በዙ ነገራችን ቀምቶናል። ከሥር እንዲነቀል የሚያስፈልግበትም መሰረታዊ እውነት ከዚህ ይመነጫል ወያኔ እኛን ዘርፎናል። ሀገራችንንም አዋርዷል። ልዑላዊነቷን አስደፍሯል። ሽጧታል። ለነገም ተክፍሎ የማያልቅ የዕዳ ባለቤት አድርጓታል። በማወዕለ ንዋይ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም። የቤት ሥራችን የገዘፈና የገረዘዘም ነው። የዘረፈንን እኛነት ማስመሰለስ ደግሞ ከእያንዳንዱ በግል ከሁላችንም በጋራ የሚጠበቅ ግዴታ ነው። ለወያኔ ፓሊሲ አለመጠቃታችን ማወቅ የሚቻለው ፈተናውን ስናልፍ ብቻ ነው። ፈተናውን ለማለፍ እራስን ከጋለ ምጣድ ላይ አስቀምጦ እዬተገላበጡ መኮረጅ ነው፤ በትልቅ ብርት ድስት ውሃ አፍልተን ስሜታችን ጨምረን እንፈትሸው። ይመቻል? ይደላል? የሰርግ ሽርሽር ነውን? – በባሩድ በዬጊዜው የሚቃጠሉትን፤ በቤንዚን እዬነደዱ የሚያልቁትን፤ በስደት ሆነ በሀገር ውስጥ በሳንጃ የሚሸነሸኑትን፤ ከቀያቸው በግፍ የሚፈናቀሉትን ወገኖች የእኔ ነው አይደለም ብልን እራሳችን አፋጠን በምናገኘው ምላሽ ነገ እራሱን አምጦ ይወልዳል።
የትም ቦታ የሚቃጠለው ቤት፤ የትም ቦታ የሚፈሰው ደም፤ የትም ቦታ ለባዕድ ተቆርሶ የሚሰጠው መሬት፤ የትም ቦታ የሚገፋው ወገን የሥጋ ቁራጭ ነው። የደም ዘር ነው። ልንገፋው፣ አልሰማነም አላዬንም ብለን ልንሸሸው የምንችለው አይደለም። የትውልዱ አደራ እያነባ ይጠብቃል – እኛኑ፤ ግን መልሱን ፈርተነዋል። መድፈር ተስኖናል። ስለምን እኛ ያለነው በግል ጎጇችን እንጂ በአዳራሳችን ውስጥ አይደለምና።
የእንግዲህ ትግላችን በቅጣቱ ሰለባነት የሚጠዘጥዘን ስሜት አሻግረን ወያኔ ላይ በመጣል ብቻ ሳይሆን፤ ወያኔ በእኛ ላይ አቅም የሌለው መሆኑን በአይኑ እንዲይ ወስነና ቆርጠን ተግባር ላይ መገኘት ስንችል ብቻ ነው። ይህም ከተቀበርንበት አሸዋ ወጥተን ቁልጭ ባለ ግልጽ ፍላጎት መስመራችን ፈለግን ማግኘት ስንችል ብቻ ይሆናል – መፍትሄው። የእትዮጵያ ህዝብም ባልታዬው የጎሳ አስተዳደር አሳሩን ከፍሏል። በማያውቀው ዕይታ ፍዳውን ከፍሏል። ባልኖረበት ማንነቱ በመጤ ማንነት እንዲጫረስ እንዲፋጅ ተዶልቶበታል፤ ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንትነውን ባከሰላው የጎሳ አስተዳደር መስመር ያለውን ጉዞ ሁሉ በቃኝ ማለት ይኖርበታል። ይበቃዋል። ከዚህ በላይ ምን የፈተና ጊዜ አለ? እሳቱ እኮ ሁሉንም አዳረሰ። ይህ ሁሉ ጦስ የጎጥ ማኒፌስቶ የአመጣው መርዝ ነው። ሌላ የጎጥ ዘመን ናፍቆተኞችንም ፍላጎታቸውን የሚያመክንበት መንሹ ያለው በእጁ ነው። ከዚህ ሌላ እራሳቸውን ሰውረው በብሄረሰብ ወይንም በእምነት ተቆርቋሪነት ሰም የደም ነጋዴዎችንም መርምሮና ፈልፍሎ ለመለዬት ማንዘርዘሪያም የሚስፈልግበት እጅግ ፈታኝ የጠቆረ ወቅት ላይ እንገኛለን። ከማን ጋር ነኝ? የእኔ ነውን? እንዳቀርበኩት አቅረቦኛልን? ቅንነቴን አክብሮታልን? ግልጽነቴን አድምጦታልን …. ንጹሑን ውስጤንስ ጨፍሮበታል ወይንስ ቦታ መድቦለታል? …. በሁሉም አቅጣጫ በጥንቃቄ ከቋሳ በጸዳ ሁኔታ መመርመር የተጋባ ይመስለኛል። ዝንቅ ህይውት ለማህበራዊ ኑሮ ሸጋ ነው፤ ቀለማምም ነው። ኑሮ ያመርበታል – ጌጣማ። ለፖለቲካ አብሮነት ግን ….. እህህህ!
እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ዕይታ – በጎጥ የሚያስብ ሰው ሰብዕዊነትን ለመተርጎም አቅም ያንሰዋል። በጎጥ የሚየስብ ሰው ርህርህናን ለመተርጎም አቅሙ የሟሟ ነው፤ በጎጥ የሚያመልክ ሰው አህጉራዊ ዕይታዎችን ለማስተናገድ ሽባ ነው። በጎጥ የሚይ ሰው ዓለም ዓቀፋዊነትን ለመቀበል ደረጃው አይፈቅድለትም። በጎጥ የሚተነፍስ ሰው ዘመኑ ከሸለማቸው ሥልጣኔ ጋር ለመኖር ዳፍንት ይዞታል። ሌላው ቀርቶ በጎጥ የሚየስብ ሰው ከጎረቤቱ ቀርቶ ከትዳር አጋሩና ከልጆቹ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ሚያስችለው ተፈጥሮው ተፍቆበታል። በጎጥ ማሰብ ስለ ሰው ልጅ ኃላፊነት በማይሰማው የህልም አለም ግን ጉድጓድ ውስጥ መኖር ማለት ነው – እንደ እኔ። ይህ የእክሌ – ተከሌ በሽታ አይደለም። ተሸፍነን ከመጋረጃው በስተጀርባ የምናሽሞነሙነው ሰብዕናን አጋድሞ የሚያርድ የአብዛኞቻችን ገመናችን ነው። ዬቅርባችን ብቻ ነው ዓይናችን የሚፈቅደው። የአብዛኞቻን ችግር ይህ ነው። ከዚህ ጋር መፈታት መቻል ነው ስለ ነገ ራዕይ አለን ማለት የሚያስችለው ፍሬ ነገር። ቀን ደግሞ አድመኛ ነው። ትንሽ ነገር ብቅ ባደረገ ቁጥር ፈትለክ እያልን የአደባባይ ሲሳይ እንሆናለን። ተከድኖ የሚቀር ነገር የለም – አይኖርምም።
አውነት ለመናገር አብዛኞቹ ወጣቶች እኮ በጣም በልጠውናል። እጅግ ከእኛ በጣም ሩቅ ተጉዞው ነው ብሩሁን ቀን የሚያስቡት። ያስቸገርነው እኛ ቀደም ብለን የተፈጠረነው ነን። ይህም በመሆኑ እነሱ ያልበሉትን እዳ እንዲከፍሉ መደረጋቸው አልበቃ ብሎ የሚከፍሉትን መስዋእትንትም ዋጋ እያሳጣነው ነው። ያረመጠመጣል። እንደ እኔ ነገ በጎሳ በጎጥ ቲወሪ ፈጽሞ መታለም የለበትም ባይ ነኝ። ቲወሪው የሀገር ሉዕላዊነት፤ የህዝብን ክብርና ታሪክ የሚደረምስ አሲድ ነው። በጎሳ የተደራጀ አካል ጥላቻው በቀልን ያረገዘ ደም የጠማው ነው። በቀሉ ደግሞ አይደለም ነገን ዛሬን ክው አድርጎ የሚያድርቅ እጅግ ኋለቀር ኢሰብዕዊ መንገድ ነው። መማር – መሰልጠን – ማወቅ ማለት ከዚህ ኋላቀር አስተሳሰብ ጋር መፋታት ካልተቻለበት መማሩ ሥጦ ወይንም ውሃ ሲሄድበት የከረመ አለት ነው – ለእኔ።። መማር መብለጥ ነው፤ መቅደም ነው። መማር ለመልካም ነገሮች ሁሉ አብነትነት ነው። መማር ዓለምን አልፎ ፕላኔቶችን መመርምር ማለት ነው። መማር መሰልጠን ነው። ተፈጥሮን መተርጎም ማለት ነው። የሰው ልጅ ውበትን አድንቆ በውስጡ መኖር እንጂ የዚህ ተጻራሪ ሆኖ በአንድ እግር ተንጠልጥሎ መቆም መማር አይደለም። የጉም ሽንት ዓይነት ልበለው …. እራሱን መተርጎም የተሳነውም – ወይንም እራስን ለመተርጎም አስተርጎሚ ተበዳሪ እሳቤ – እንደ ሥርጉተ ማህይምነት በስንት እጁ ጣዕሙ –
እርግጥ ነው ወያኔ ከሥሩ እስኪነቀል ድረስ ተጓዳኝ የትግሉ ዘርፎች ይዘለሉ ማለት አይደለም። ወያኔ ያበቀላቸው እሾኾች ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ መነቀል አለባቻው። የተሟላና የተደራጀ የህሊና ሥራም መሰራት አለበት። በግንባር ያሉ ፈተናዎችን ከእግር እግሩ እዬተከተሉ እዬተነተኑ እርቃኑን ማስቀርት – ማደረቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዘላቂ ፍላጎትን ለማሟላት እራስን አሸንፎ በታቀደ፤ ህዝብን መሰረት ባደረገ፤ ነገ ከመምጣቱ በፊት ለምልሞ እንደሚጣ በሚያደረግ በተጠና መርኃ ግብር በቋሚነትና በተከታታይነት ሥራ ላይ መገኘት ያስፈልጋል።
ከውና – አንድ ነገር ወያኔ በለኮሰ ቁጥር ከዋናው ፍላጎት በመውጣት፤ ወይንም በደራሽ ችግሮች ላይ አትኩሮ ዋናውን ፍላጎት የሚሻውን ትኩረት ሆነ አቅም መንፈግ የተገባ አይደለም። ለአንድ መንገድ የተለያዩ ስልቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ተቀናጅተው አንዱ የዘለለውን ወይንም ያላዬውን ሌላው ክፍቶቹን እዬሞላ እዬተደጋገፉ እኛኑ ሊውጠን ካሰፈሰፈው የጠላት ሁለገብ ሴራ እራስን ማዳን ዬቅድሚያ ትንፋሻችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳችን ሊያርፍበት ዬሚገባው ዓይናማ አመክንዮ ሊሆን ይገባል እላለሁ። ለይደር የሚቀጠር ምንም ነገር የለም። አዳሩም ሞት ውሎም ሞት፤ አዳሩም ጥቃት ውሎም ጥቃት። አዳሩም ወርደት ውሎም ውርደት። ስለሆነም ሰቅስቆ ከሥሩ አረምን ማስወገድ፤ ማሳን አለስልሶ ቡቃዮዎችን ማስበል …. ከሁሉ በላይ የነፃነት ትግል ሰብዕዊነትን ይጠይቃል። ሰማዕታት ሲታሰቡም እራስን ከእሥር መፍታት በአጽህኖት አብዝቶ ይጠይቃል። በስተቀር የትውፊት ተደሞ ይታዘበናል። ። ልብ ያለው ሽብ። የኔዎች እኔ እንዲህ ታይቶኛል። ከክብሮቼ ጋር ውስጤን እንዲህ አውጥቼ ከመግለጽ በላይ ገነት የለም። አመሰግናችኋለሁ – በፍቅር። ኑሩልኝ።
እራሳችን የምናዳምጥበት አቅም አምላካችን ይስጠን። አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።