May 16, 2014
41 mins read

የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀው የጋራ ልማት ፕላንና ያልተቀናጁ ጥያቄዎች

በ  ሰለሞን ጎሹ
ሪፖርተር

 

125ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን ባለፈው ዓመት ያከበረችው አዲስ አበባ ባልተቋረጠ ግንባታና ለውጥ ላይ ትገኛለች፡፡

ከነዘርፈ ብዙ ችግሮቿ የብዙ ሚሊዮኖችን ሕይወት እየደጎመች የምትገኘው አዲሰ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች እንዲሁም የፌዴራል ተቋማት መገኛ ስትሆን ከዘጠኙ የፌዴራል መንግሥቱ አባል ክልሎች አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም መቀመጫ ነች፡፡

የፌዴራል መንግሥቱንና የኦሮሚያ ክልልን የተለያዩ ፍላጎቶች ለማሟላት የምትጥረው አዲስ አበባ የአገሪቱ ወሳኝ አስተዳደራዊ፣ ኢንዱስትሪያዊ፣ የንግድ፣ የአገልግሎትና የገንዘብ ተቋማትን ፍላጎት ከራሷ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም በየጊዜው እየተዳፈኑ ቆይተው ብቅ በሚሉ ተግዳሮቶች መናጧ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

በቅርቡ ለውይይት የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን የአዲስ አበባንና የኦሮሚያን ልዩ ዞን የተለያዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደተዘጋጀ ቢገለጽም ባለፉት 19 ዓመታት በተለያዩ መልኮች ሲቀርቡ የነበሩና ተቀዛቅዘው የነበሩ ጥያቄዎችን መልሰው እንዲነሱ መቆስቆሱ ግን አልቀረም፡፡

በዋነኛነት ጥያቄዎቹ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 49 የተመለከቱ ናቸው፡፡ አንቀጽ 49 ስለአዲስ አበባ ከሚገልጻቸው አንኳር ነጥቦች መካከል አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ ከተማ መሆኗ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያለው መሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት መሆኑ፣ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወከሉ መሆኑ ይገኝበታል፡፡

ይሁንና በአንቀጽ 49(5) ላይ የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም እንዳሚጠበቅለት መገለጹና ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን መደንገጉ በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደት ወቅት ያስነሳው ውዝግብ አሁንም ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ እንዳለ ነው፡፡

‹‹ልዩ ጥቅም››፣ ‹‹የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም››፣ እና ‹‹የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች›› ምንነትና ወሰንን በተመለከተ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የመሰላቸውን ሲሉ ቆይተዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. የወቅቱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከአዲስ አበባ ኦሮሚያ ያላትን ልዩ ጥቅም የሚመለከት ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ እንደሚቀርብ ገልጸው ነበር፡፡ በወቅቱ የረቂቅ ሕጉን ወደ ሕግ መቀየር በጉጉት የጠበቁት ዜጎች ዓመቱ ሲጠናቀቅ የተባለውን አዋጅ የማዬት ዕድል አልገጠማቸውም፡፡ መንግሥትም ሕጉ በዚያ ዓመት ወይም በቀጣይ ዓመታት ለምን ሊወጣ እንዳልቻለ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ በመንግሥት ዝምታ መሐል አንቀጽ 49 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችም ተውጠው ነበር፡፡

አሁን ውዝግቡን ዳግም የቀሰቀሰው የአዲሰ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ልማት ፕላን ዙሪያ በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በምሁራን፣ በዜጎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ዘንድ የቅርብ ጊዜ ዋነኛ የውይይት አጀንዳ ሆኗል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምሁራንና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተጻፉ የምርምር ሥራዎች ግን የጋራ ልማት ፕላኑ ይዘት ሳይሆን የቆዩ አለመግባባቶች ጥያቄና ውዝግብ ማስነሳታቸውን ያመላክታሉ፡፡

የጋራ ልማት ፕላኑ ይዘት

የጋራ ልማት ፕላኑ ከ2006 እስከ 2030 ዓ.ም. ድረስ የአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ለተለያዩ የልማት ዘርፎች በተቀናጀ ሁኔታ እንዴት መሥራ እንደሚችሉ በዝርዝር ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ ፕላኑ ያካተታቸው የልማት ዘርፎች መካከል አካባቢና አረንጓዴ ማዕቀፍ፣ ከተማና የከተማ ዙሪያ ግብርና፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የማዕከላትና ገበያ ቦታዎች ዋና ዋና ግልጋሎቶች፣ ዋና ከተማ ማዕከል፣ ትራንስፖርት፣ የመንገድ መርበብ፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ የቤቶችና የማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ የሕንፃ ከፍታ፣ የታሪካዊ ግንባታዎችና ሥፍራዎች፣ ስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የኢኮኖሚ ልማት ፕላን፣ የከተማ መዋቅርና ዕድገት፣ መሬት አጠቃቀም፣ መልካም አስተዳደርና የከተማ ፋይናንስ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የአካባቢ ልማት ፕላን፣ አቅም ግንባታ ይገኙበታል፡፡

የጋራ የልማት ፕላኑ ለነዋሪዎች የኑሮ ደረጃ መሻሻልና ለአገራዊ ልማትና ዕድገት መሠረት እንደሆነ ለውይይት የቀረበው የፕላኑ ሰነድ ይጠቁማል፡፡ አዲስ አበባን ሌሎች ዓለም አቀፍ ከተሞች የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ፕላኑ ትልቁ መሣሪያ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን መሪ ፕላኑ የተዘጋጀው የአዲስ አበባን ዕድገት በአግባቡ ለመምራት ከአሥር ዓመታት በፊት በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ የዋለውን ፕላን በማስፈጸሙ ሒደት የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በአግባቡ ተፈትሸውና ተተንትነው እንዲሁም ቀጣዩ ዕርምጃ ምን መሆን እንዳለበት ስምምነት ከተደረሰ በኋላ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በትብብርና በጋራ የተዘጋጀው መሪ ፕላን በሒደት በሚፈጠር የከተማ ልማት ቀጠና የበለፀገ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በመፍጠር ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ይበልጥ የሚጎለብትበትና የውጭ ኢንቨስትመንትን በተሻለ ሁኔታ የመሳብ ዕድልን ለማስፋት እንደሚያስችልም ሰነዱ ያመለክታል፡፡

የከተማ ልማት ፖሊሲና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎችን መሠረት እንዳደረገ የተነገረው የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የኦሮሚያ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች የጋራ ልማት ፕላን ዝግጅት በሁለቱ መስተዳደሮች የጋራ ፍላጎትና ስምምነት የተከናወነ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ፕላኑ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በአካባቢው የኢኮኖሚ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ (የመንገድ፣ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ የባቡር መስመር)፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ልማት፣ ተደራሽ የሆነ የጋራ የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት፣ የመካከለኛና የከፍተኛ ኢንዱስትሪ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃና ልማት፣ የቱሪዝምና ቅርስ ጥበቃ ልማት፣ የቤቶች ልማት፣ እና የዘመናዊ የከተማና የገበያ ማዕከላት ልማትና ግንባታን በተመለከተ ሁለቱን አስተዳደሮች ለማስተሳሰርና ለማቀናጀት ሁሉን አቀፍ ልማት ለማምጣት ትኩረት አድርጓል፡፡

አዲስ አበባ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን የሚጠቁመው ሰነድ በሁለት አሥርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመለክታል፡፡ በዚህ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ብዛት የተነሳ የሚፈጠሩትን ክፍተቶች ለመሙላት፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶችና የኢንፍራስትራክቸር አቅርቦት እጥረትና ጥራት ማነስን በአፋጣኝ ለመቅረፍ መሪ ፕላኑ አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የመሪ ፕላኑ መሠረታዊ ጭብጥ ከላይ የተገለጸው ሲሆን በቀጥታ ንባብ የትኛውንም አካል የሚጎዳ ወይም ተጠቂ የሚያደርግ አይመስልም፡፡ ይህ ግን አስተያዬት ሰጪዎች ‘አዲስ አበባ ከኦሮሚያ መሬት ልትሰርቅ ነው’፣ ‘የኦሮሚያ ገበሬዎች ከፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሊፈናቀሉ ነው’፣ ‘የፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሊጠቃለሉ ነው’፣ እና የመሳሰሉ አስተያዬቶች ሁሉ ምንጫቸውን መሪ ፕላኑን ከማድረግ አላገዳቸውም፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አባላት ጭምር መሪ ፕላኑ በቂ ውይይት ሳይደረግበት መዘጋጀቱንና ፕላኑ የኦሮሞን ማንነት እንዳያጠፋና ገበሬዎቹን እንዳያፈናቅል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ በአዳማው ውይይት መግለጻቸው ሪፖርተርን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡም ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ማቴዎስ አስፋው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአዲሰ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ መናገሻ ለገጣፎና ለገዳዲ፣ ገላን፣ ዱከም እንዲሁም ሰበታ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች ጥብቅ ትስስር ያላቸው በመሆኑ ፕላኑን በጋራ ከአዲስ አበባ ጋር መሥራታቸው ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የኦሕዴድ አባላት ግልጽ ባልሆኑላቸው የፕላኑ ክፍሎች ላይ ጥያቄ ማቅረባቸው ኦሮሚያና አዲስ አበባ አልተግባቡም ሊያስብል እንደማይገባ ያስረዳሉ፡፡ በዕቅዱ አማካይነት ከተሞቹ ወደ ኢንዱስትሪ ማዕከላት መሸጋገራቸው ለከተሞቹ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያመለከቱት አቶ ማቴዎስ ከተሞቹ በሚያድጉበት ጊዜ ጉዳት እንዳያደርሱ የሚያስችልና ተደጋግፈው እንዲያድጉ የሚያደርግ ፕላን ጽሕፈት ቤታቸው ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

መሪ ፕላኑን በጥርጣሬ ያዩት አስተያዬት ሰጪዎች ግን የሚመጣው ፕላን የኦሮሞ ነባር ነዋሪዎችን መፈናቀል የሚያስቀር እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ለባለሀብቶችና ኦሮሞ ላልሆኑ ሰዎች የመኖሪያና የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ያለመ ፕላን ነው በሚልም ነባር የኦሮሞ ገበሬዎችን ከኦሮሞ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን እንዳይጠቀሙ ያደርጋል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ በፕላኑ የተነሳም በልዩ ዞኑ የነበሩ የኦሮሞ ባህላዊ ቅርሶችና እሴቶች እንደሚወድሙም ያመለክታሉ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም የፊንፊኔና ዙሪያዎች ከተሞችና የገጠር መንደሮች ወደ አዲስ አበባ መቀላቀላቸው እንደማይቀር ሁሉ ተንብዬዋል፡፡

እነዚህን ሥጋቶች ከመሪ ፕላኑ ጋር መያያዛቸው እንቆቅልሽ የሆነባቸው አስተያዬት ሰጪዎች ግን በአፈጻጸም ሒደት የነዋሪዎቹ መሠረታዊ መብቶች እንዳይነኩ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም የሥጋቶቹ ምንጭ መሪ ፕላኑ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ልዩ ጥቅም ያለው ድንጋጌ አተረጓጎም እንደሆነም ያስገነዝባሉ፡፡

‘የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም’ ላይ ያለው ክርክር

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የተደነገገው ‘የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም’ን በተመለከተ አስፈላጊ ባለድርሻ አካላት ግልጽ የሆነ አረዳድና ስምምነት ወይም መግባባት የላቸውም፡፡ ‹‹Constitutional Special Interest of ONRS in AACA: Present Status and Future Challenges›› በተሰኘ ርዕስ በጻፉት የምርምር ሥራ አቶ በትሩ ዲባባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም’ ጉዳይ አወዛጋቢነት የጀመረው ገና ሕገ መንግሥቱ በመረቀቅ ሒደት ላይ በነበረበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው አንዳንዶች ለኦሮሚያ ዕውቅና መስጠቱን በበጎ ጎኑ ሲያዩት ሌሎች ግን አገር የማፈራረስ ተፅዕኖ እንዳለው ገልጸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ግራ መጋባት፣ ጥርጣሬ፣ ፍርኃት፣ እና አለመረጋጋት እንደሚስተዋል አቶ በትሩ ያስገነዝባሉ፡፡

በእርግጥም የሕገ መንግሥት ጉባዔ ቃለ ጉባዔ ጥራዝ አራት ላይ የሰፈሩት አስተያዬቶች በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በቂ መግባባት እንደሌለ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ አቶ አዳሙ ደገፉ የተባሉ አስተያዬት ሰጪ ለምሳሌ ‹‹ከተማው ቢያድግ ለጥቂቶች ሳይሆን የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኑ የሁሉም የጋራ ሀብት ሆኖ ሳለ የኦሮሚያ ክልል የተለዬ ጥቅም ይገኛል ተብሎ መቀመጡ የተባለው ጥቅም ግብርም ሊሆን ስለሚችል እንዲህ ዓይነት ድርድር የያዘን አንቀጽ ማስቀመጡ አግባብ ስለማይሆን እንዲወጣ›› ማለታቸው ሰፍሯል፡፡ የያኔው የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት ኮሚቴ አባልና የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን ደግሞ ‹‹የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የሚያገኘው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጠ የምትገኝ በመሆኗ እንደሆነና የከተማው መስፋት አርሶ አደሩን የሚነካ ከመሆኑም ሌላ ቀደም ሲል እንደተባለው በተፈጥሮ ሀብትና በመሳሰሉ ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ለሁለቱም የልማት እንቅስቃሴ የሚበጅ ነው›› ማለታቸው ተገልጿል፡፡ አቶ ተሰማ ጋዲሳ የተባሉ አስተያዬት ሰጪ ደግሞ አዲስ አበባ ያለችበት መሬት የኦሮሚያ መሆኑን ጠቅሰው ‹‹አዲስ አበባ የኦሮሚያ እምብርት በመሆኗ የክልል ምክር ቤት ሌላ ውሳኔ ካልወሰነ በስተቀር የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳትሆን የክልል ርዕሰ ከተማም በመሆኗ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይጠበቃል ሲባል በጽሕፈት ቤት አቅርቦትና በመሳሰለው እንጂ እንደተባለው ግብር የመሰብሰብ ጉዳይ አንቀጹን አዛብቶ ከመረዳት የሚመነጭ ትንቢት ነው›› ማለታቸውም በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በተለያዩ አፅናፎች ላይ ያሉ አቋሞች ቢንፀባረቁም ውይይቱ በቂ ነው ተብሎ ወደ ቀጣዩ አንቀጽ መሸጋገራቸውም በቃለ ጉባዔው በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

አቶ ወንድዎሰን ዋኬኔ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕገ መንግሥት መምህር ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው የሕግ ክፍል ኃላፊም ናቸው፡፡ ‹‹Self Governing Addis Ababa, the Federal Government & Oromia: Bottomlines & Limits in Self Government›› በተሰኘ ርዕስ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ላይ የምርምር ሥራ የጻፉ ሲሆን ‹‹ልዩ›› ጥቅምን ለኦሮሚያ ለመስጠት ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች እንዳሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አንደኛው ከአዲስ አበባ አቀማመጥ ማለትም በኦሮሚያ ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ ነው፡፡ አቶ ወንድዎሰን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) ባይኖር አዲስ አበባ የኦሮሚያ አንድ ከተማ ትሆን እንደነበር የጠቆሙ ሲሆን ሌሎች ክልሎች ይሄን ‘ልዩ’ ጥቅም እንደማያገኙ አመልክተዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር የነበራት ታሪካዊ ቁርኝት ነው፡፡

አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መገኘቷ በግልጽ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረ ሲሆን ታሪካዊ ቁርኝቱ ግን በግልጽ ዕውቅና ባለመሰጠቱ የኦሮሚያ ባለቤትነት ላይ የሚነሳው ጥያቄ አወዛጋቢ ሆኖ እንድቀጥል በር ከፍቷል፡፡ አቶ ጌታሁን በንቲ ‹‹A Nation without a city [a Blind Person without a Cane]: The Oromo Struggle for Addis Ababa›› በተሰኘ ርዕስ በጻፉት የምርምር ሥራ አዲስ አበባ (ወይም በኦሮምኛ ‘ፊንፊኔ’) ገና ስትቋቋም ጀምሮ የነባር የኦሮሞ ነዋሪዎችን በማፈናቀልና ወደ ከተማው ልማት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ሕይወት፣ በፖለቲካና በባህል ረገድ እንዲቀላቀሉ ባለማድረግ የተሞላ ታሪክ እንዳላት አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች ፀሐፊዎችም በአሁኑ አዲስ አበባ የጉለሌ፣ ኤካ፣ ገላንና አቢቹ የተሰኘ ጎሳዎች ይኖሩ እንደነበርና ያለፍላጎታቸው ከቀያቸው ተፈናቅለው አዲስ አበባ እንደተስፋፋች ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን ‹‹ልዩ ጥቅም››ን መረዳት የሚገባው ይሄንን የተዛባ ታሪካዊ ግንኙነት ለማስተካከል በሚደረግ ጥረት ዓውድ ውስጥ ሊሆን እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላ የ‹‹ልዩ ጥቅም›› ውዝግብ መጀመሪያ የተከሰተው በ1995 ዓ.ም. የክልሉ መንግሥት የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ወደ አዳማ እንዲዛወር ውሳኔ በወሰነበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ውሳኔ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ አይደለም›› ያሉ ተቃዋሚዎች ከመንግሥት ጋር የተጋጩ ሲሆን በ1997 ዓ.ም. ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ቅንጅት አዲስ አበባን ማሸነፉን ተከትሎ ግን የኦሮሚያ መንግሥት መቀመጫ ተመልሶ አዲስ አበባ እንዲሆን መደረጉ ጊዜያዊ እፎይታን ቢያመጣም የአንቀጽ 49(5) ትርጉምን አሻሚነትና ተለዋዋጭነትን ግን ያረጋገጠ አጋጣሚ ነበር፡፡

አቶ ፀጋዬ ረጋሳ ‹‹Issues of Federalism in Ethiopia: Towards an Inventory of Legal Issues›› በተሰኘ ሥራቸው ‹‹ልዩ ጥቅም›› ስለ ኦሮሚያ ባለቤትነት ወይም ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ስላላት የቦታ ቅርበት ብቻ የተሰጠ ስለመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ታሪካዊ ቁርኝትን ሕገ መንግሥቱ ቢጠቅስ ኖሮ ክልሉ የአዲስ አበባ ባለቤት ስለመሆኑ ማንሳት ቢቻልም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ውስጥ ስለመገኘቷ ብቻ በመጠቀሱ በከተማው እንግዳው ኦሮሚያ ይሁን ወይም የአዲስ አበባ አስተዳደር ይሁን እንደማይታወቅ አስረድተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ፌዴራል መንግሥቱ ሦስተኛ ባለጉዳይ ቢሆንም ሕገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥቱ የራሱ የሆነ ግዛት እንደሌለው በግልጽ በመደንገጉ የባለቤትነት ጥያቄው እንደማይመለከተው ጠቁመዋል፡፡

አቶ በትሩ ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባን እንደ ነፃና ራሷን የቻለች ከተማ ወይም ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አካል አድርጎ ባለመደንገጉ ማውራት የሚቻለው ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ስለምታገኘው ጥቅም እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡ የኦሮሚያ ጥቅም በማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ በተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀምና በጋራ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲሁም መሰል ጉዳዮች የተገለጸ ቢሆንም እያንዳንዱ ክፍል በራሱ ሲተረጎም የተወሳሰበ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ወንድዎሰን ስለ ኦሮሚያ ‹‹ጥቅም›› ሲወሳ ትልቁ ጉዳይ የአዲስ አበባ ያልሰከነ የድንበር መስፋፋት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ይህ ከፊንፊኔ ልዩ ዞን ጋር በተገናኘ የኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች ከአዲስ አበባ ሊያገኙ በሚችሉት እንደ ትምህርትና ጤና ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚገለጽ ቢሆንም በአግባቡ ካልተመሩ ግን የኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች ተጎጂም ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ አበራ ደገፋ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ሲሆኑ በ1999 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ‹‹ልዩ ጥቅም›› ላይ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥ ጠይቆ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ስለሆነ ትርጉም ኢያሻውም የሚል ምላሽ እንደተሰጠው አስታውሰዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሀብት አጠቃቀምንና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ከጠቀሰ በኋላ ሌሎች ጥቅሞች ማለቱን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ኦሮሚያ በአዲሰ አበባ ላይ የማንነት አሻራ የሚጥሉ የባህል ማዕከላትና የቋንቋ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ቢኖርባትም ይህ ተግባራዊ ባለመደረጉ ‹‹ልዩ ጥቅም›› በኦሮሚያ መንግሥት መቀመጫ ብቻ መገደቡን ገልጸዋል፡፡ አቶ አበራ ‹‹ልዩ ጥቅም›› አዲስ አበባ ከተማዋን የተመለከተ ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ስትወስን ከኦሮሚያ ይሁንታ ማግኘት መቻሏን እንደሚያካትም ተከራክረዋል፡፡

ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ዙሪያ ተቀዳሚ ተመራማሪ ሲሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) ላይ ሦስት ተዋንያን (ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባና ፌዴራል መንግሥት) እንዳሉ አስታውሰው ብዙ ጊዜ በክርክሩ ‹‹ልዩ ጥቅም›› የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ግንኙነት ተደረጎ መወሰዱ አግባብ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ፌዴራል መንግሥቱ አገሪቱን ይወክላል፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር ነዋሪዎቹን ይወክላል፤ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ ኦሮሞዎችን ይወክላል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊነቱ ተጠብቆ እንዲቆይና ኢትዮጵያን እንዲመስል የማድረግ ኃለፊነት አለበት፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር አዲስ አበባዊ ማንነት መፍጠር አለበት፡፡ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ የኦሮሚያን ልዩ መብት የሚያንፀባርቅ ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ነገር ግን ከሦስቱ ተዋንያን የአንዱ ብቻ ሊንፀባረቅ አይገባም›› በማለትም አስረድተዋል፡፡

ዝርዝሩ ሕግ ወዴት ገባ?

መንግሥት ዝርዝር ሕጉን ቢያወጣ ኖሮ ውዝግቡ ይቆም ነበር የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ ይሁንና ከ20 ዓመታትም በኋላ ዝርዝር ሕጉ የት እንደገባ ያልታወቀው የፌዴራል መንግሥቱ ዝርዝር ሕጉን ብቻውን መወሰን ስለማይችል እንደሆነ በመግለጽ ተጠያቂው ፌዴራል መንግሥት ብቻውን እንዳልሆነ የሚያመለክቱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል በፌዴራል ደረጃ፣ በአዲሰ አበባ ደረጃና በኦሮሚያ ደረጃ አስተዳደሩን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ስለሆነ የፓርቲ መስመርና የፖለቲከኞች ስምምነት ስላለ ነው እንጂ መድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ቢጠናከር ሕጋዊ መስመር መከተል አማራጭ አይሆንም ነበር በማለትም የሚከራከሩ አሉ፡፡

አቶ ወንድወሰን ዋኬኔ ዝርዝር ሕጉን የሚወስነው ማን እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ባለማስቀመጡ ሦስቱንም ባለድርሻ አካላት በእጩነት መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመው በ2001 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ሊያረቅ ያሰበው ሕግ ሳያሳካ የቀረው ሦስቱ ባለድርሻ አካላት መግባባት ባለመቻላቸው እንደሚመስላቸው አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ አስተዳደር የተሻሻለው ቻርተርና የኦሮሚያ ክልል ደንብ ቁጥር 115/2000 ዓ.ም ከ‹‹ልዩ ጥቅም›› ጋር የተገናኙ ድንጋጌዎችን ስለመያዛቸው ግን ያመለክታሉ፡፡ በአዲሰ አበባ ቻርተር አንቀጽ 62 እና 62 ላይ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ አስተዳደሮች የጋራ ጉዳያቸውን በመመካከርና በስምምነት እንዲፈቱ ወይም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ ሕግ እንዲዳኙ ይደነግጋል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ ዝርዝር ሕግ በሦስቱም አካላት ተነሳሽነትና ስምምነት ሊወጣ እንዳልቻለ አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

አቶ አበራ በተመሳሳይ መልኩ ዝርዝር ሕጉ ላለመውጣቱ ጥፋተኛ ከመሆን የሚያመልጥ ባለድርሻ እንደሌለ ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን ሕጉ ባለመውጣቱ ዋነኛ ተጎጂ የኦሮሚያ ክልል መሆኑን ግን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ትልቁ ችግር የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ድንበር ባለመታወቁ ኦሮሚያን ክልል ማድረግና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ሙሉ በሙሉ መጠቀም አልተቻለም፡፡ ድንበር ስላልተቀመጠ አዲሰ አበባ አስተዳደር ኦሮሚያ ላይ ውሳኔ እየሰጠ ነው፡፡ የኦሮሚያ ማንነት ጥያቄ በውል ካለመታወቁም በላይ ኦሮሚያ ክልል መሆኑ እየቀረ ነው›› ሲሉም አቶ አበራ አክለዋል፡፡

ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ ዝርዝር ሕጉን ለማውጣት በቅድሚያ ሦስቱም አካላት በሚገባ ተወያይተው ሊግባቡ እንደሚገባ አመልክተው የጋራ መግባባት ካለ ሕጉን ከመውጣት የሚያግደው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ልዩ ዞንና መሪ ፕላኑ

ከላይ እንደተገለጸው መሪ ፕላኑ የልማት ዕቅድ በመሆኑ በራሱ ውዝግብ የማይፈጥር ቢሆንም አሁን እየተደረጉ ያሉት ውይይቶች ግን መሪ ፕላኑ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን ይጎዳል በሚል ርዕስ ላይ ይሽከረከራሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በክልል ደረጃ ያደራጃቸውን አካላት ድንበር በግልጽ ያካለለ ባለመሆኑ በድንበር ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ የገቡት አዲስ አበባና ኦሮሚያ ብቻ ባይሆኑም ይሄ መሪ ፕላን የተዘጋጀው ግን በኦሮሚያ ይሁንታ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በመሪ ፕላኑ አማካይነት አዲስ አበባ የመስፋፋት ዕቅድ የሌላት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አቶ ወንድወሰን በኦሮሚያ ክልል ደንብ ቁጥር 115/2000 ዓ.ም. አማካይነት የድንበር ማካለል ውዝግቡ መቆሙን ይጠቁማሉ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች የሕዝብ ቁጥራቸውና እንቅስቃሴአቸው ባደገ ቁጥር የአጎራባቾቻቸውን ድንበር መግፋታቸውና ጥቅማቸውን መንካታቸው የተለመደ ቢሆንም የልዩ ዞኑ ማቋቋሚያ ደንብ ዋነኛ ዓላማ ግን ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን ግንኙነት በቅንጅት መምራትና መርህን ባልጠበቀ መልኩ አዲስ አበባ የምታደርገውን መስፋፋት መግታት በመሆኑ ከደንቡ በኋላ አሁን አዲስ አበባ እንደ ልቡ ይስፋፋል ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡ መሪ ዕቅዱ ሕጋዊና ዘላዊ ውሳኔ ስለማስተላለፉ መናገር ቢከብድም አቶ ወንድወሰን ከጋራ የልማት እንቅስቃሴው ኦሮሚያ ትጎዳለች ብሎ ማሰብ ከባድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ የአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ መስፋፋት በራሱ ችግር እንዳልሆነ ጠቁመው ከመስፋፋቷ ግን ኦሮሚያ ተጠቃሚ ስለመሆኗ ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የገጠር ከተሞች እንደነበሩ አስታውሰው በመሪ ፕላኑ እነዚህን ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር በማስተሳሰር ኢንቨስትመንት እንዲስቡ በማድረግ ተጠቃሚ ለማድረግ ማሰቡ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ተከራክረዋል፡፡ ነገር ግን በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎቹ የኦሮሞ ገበሬ ይፈናቀላል በማለት ስለሚቀርቡ ቅሬታዎች የተጠየቁት ዶ/ር አሰፋ ለገበሬዎቹ የሚሰጠው የካሳ ክፍያ ሕይወታቸውንና ቤተሰባቸውን ሊቀይርና መልሶ ወደ ጎዳና ሊያስወጣቸው በማይችል መልኩ እንዲፈጽም መንግሥት በልማት እንዲታቀፉና የከተማ ሕይወት እንዲላመዱ የሚያደርግ ፖሊሲ ሊኖረው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ለሪፖርተር አስተያዬታቸውን የሰጡ ዜጎችና ምሁራን መሪ ፕላኑ የቆሰቆሳቸው ጥያቄዎች ከፕላኑ የተነሱ ባይሆኑም በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ካልተሰጣቸው የሕዝቡን ተሳትፎ በሙሉ ስሜት ማግኘት ስለማይቻል ትኩረት እንደሚያሻቸው ግን መክረዋል፡፡

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop