May 10, 2014
21 mins read

ምናባዊ ቃለምልልስ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር

ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ው/ልደታቸውን አስመልክቶ የተደረገ ምናባዊ ቃለ ምልልስ

ልማጠኛ (ልማታዊ ጋዜጠኛ)፡-
እሺ በቅድሚያ ጊዜዎን ሰውተው ስለውልደትዎ ለማውጋት እዚህ ያለሁበት ምናባዊ ስቱዲዎ ድረስ በመንፈስ ስለተገኙልኝ በፌስቡክና በመላው የሽሙጥ ማህበረሰብ ስም ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ እስቲ ያሉበትን ሁኔታ በአጭሩ ቢያስረዱ፡፡

መለስ፡-
ያለሁበት ሁኔታ ግልጽ ነው፡፡ በምድር ሳለሁ ለሰራሁት ስራ ጥሩም ሆነ መጥፎ ሂሳቤን በሙሉ ኦዲት እያደረኩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እዚህ እያንዳንዷ ነገር ሁሉ የራሷ አካውንት አላት፡፡ ያው ባላንሴ ዴቢት እና ላያቢሊቲ ብቻ ሆኖብኝ መጨነቄን ልትገምት ትችላለህ፡፡ ብዙ አታስገባኝ ወደሱ፡፡

ልማጠኛ፡-
እሺ ይተዉት እሱን፡፡ ዛሬ የልደትዎ ቀን ነው፡፡ በእርስዎ መወለድ ዓለም ምን ተጠቅማለች ብለው ያስባሉ፡፡ ምንስ ጉዳት ተከስቷል?

መለስ፡-
ዌል እንግዲህ በእኔ መወለድ ብዙ ጥቅም እና ጥቂት ጉዳቶች መከሰታቸውን በመረጃ ብቻ ሳይሆን በማስረጃም ጭምር ማሳየት እችላለሁ፡፡ ግን አንተ ማወቅ የፈለግከው ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረውን ነው ወይስ ስልጣን ላይ በአሚር ሙጫ ከተጣበቅኩ በኋላ ያለውን ጊዜ ብቻ ነው?

ልማጠኛ፡-
የወጣትነትዎና የትግሉን ዘመን ለጊዜው ይተዉት፡፡ ብዙም የሚያወያይ ነገር ላይኖረው ይችላል፡፡ በይበልጥ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ጊዜዎትን ነው ማወቅ የፈለግኩት፡፡

መለስ፡-
ይሁንልህ፡፡ እኔ ተወልጄና አድጌ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆንኩ ጀምሮ በርካታ ጥቅሞች ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከዋልኩት ውለታዎች አንዱ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት የሚባለውን ነገር በወሬ ደረጃ ማስተዋወቄ ነው፡፡ እምልህ… ተግባር ሌላ ነገር ነው፡፡ ግን እውን ባይሆንም እንኳ ሶስቴ የመብላትን ተስፋ ለድሆች መስጠት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ሶስት ቀን ባይችሉ እንኳ በሶስት ቀን አንዴ መብላት ላይከብዳቸው ይችላል፡፡ ኢንፋክት ከእኔ ጠቅላይነት በኋላ በአንድ ጊዜ ከ5 ሚሊየን ሰው በላይ ሲራብ አልታየም፡፡ ሁሌም ከ5 ሚሊየን እስከ 4 ሚሊየን 999 ሺ 999 ሰው ብቻ ነው ሲራብ የነበረው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እኔ ለፍቼና ላቤን አንጠፍጥፌ፣ ድንቅ የሚባል የኢኮኖሚ እውቀቴን በመጠቀም እንዲከሰት ባደረግኩት የኑሮ ሁኔታ የሰዎች የምግብ አምሮት እንዲጨምር አድርጌያለሁ፡፡ አፒታይት ማለቴ ነው፡፡ ዱሮኮ ስጋ በሳምንት ሶስቴ ወይ ሁለቴ ይበላ ነበር፡፡ ማንም አይናፍቀውም፡፡ አሁን ግን የፍቅር ዘፈን ተዘፍኖለት ‹‹ቁርጤ ቁርጠቴ›› ተዘምሮለት ነው የሚገኘው፤ በክብር.. ለዚያውም ደሞዝ ተጠብቆ! ህዝብ ይንቃቸው የነበሩት ጣፊያና አንጀት እንኳ ዛሬ አዲሳባ ላይ መበላት መጀመራቸው የኔ ውለታ ነው፡፡ ሸኾና ራሱ በእነሱ ቀንቶ ‹‹እኔስ መቼ ነው የምብበላው?›› የሚል ንቅናቄ ሊጀምር መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡

ልማጠኛ፡-
ለጊዜው አገሪቱ ውስጥ ያለው ህጋዊ ንቅናቄ የ‹‹ቐ›› ንቅናቄም ብቻ ነው ክቡርነትዎ፡፡ ለማንኛውም ይቀጥሉ እስቲ!

መለስ፡-
መልካም፡፡ እንደውም የስጋ ነገር ሲነሳ በግ ትዝ አለኝ፡፡ ዱሮ ትዝ ይልሀል በየሰፈሩ በአምስት ብር በሚቆረጥ ሎተሪ በግ እንደሽልማት ይደርስ ነበር፡፡ እንደውም ትዝ ይለኛል ገና ምኒሊክ ቤተ መንግስት እንደገባን አንዱ የበግ ሎተሪ ሲያዞር አዜብ አግኝታው የእኔ 6ሺ ብር ደሞዝ እስኪደርስ ከጓደኞቿ ተበድራ ገዝታ ነበር አልደረሳትም እንጂ፡፡ እሱን የበግ ሎተሪ ደርግ ነው ያስጀመረው ታውቅ ከሆነ፡፡ ያው ደርግ በበግ ሎተሪ አስጀመረ… እኔ ደግሞ በኢኮኖሚ ፖሊሲዬ በበዓል እንኳ የሚታረደውን በግ ሎተሪ አደረግኩት፡፡ አሁንኮ በግ ገዝቶ ማረድ ሎተሪ እንደማሸነፍ ሆኗል አሉ፡፡ በግ ተገዝቶ ሲገባ ሰፈር ውስጥ እንደሙሽራ ተጨብጭቦለት የሚገባ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ በዚህ ታዲያ ሌላው ቢቀር የበግ መብት ተቆርቋሪዎች ሁሉ ሳይደሰቱ ይቀራሉ ብለህ ነው? እንግዲህ የኔ ሌጋሲ ነው ይሄ!

ስኳርስ ቢሆን! ከእኔ በፊት የተናቀና በየወረቀቱ ተጠቅልሎ የሚሸጥ ‹‹ርካሽ›› ነገር አልነበረም እንዴ? ታምራት ላይኔ እንኳ ገና እንደገባን ስንቴ ሲልሰው ነበር! ዘይትም ቢሆን ያምስት አምስት ነበር ዱሮ፡፡ ዛሬ እቴ … እኔ ልመስገን እንጂ ስኳርና ዘይት ትንሽ ጠፋ ካለ ለትዳር ሽማግሌ እንደሚላከው ለቀበሌ ካድሬ አማላጅ ተልኮ ተለምኖ ነው በክብር በሰልፍ ቀብረር ብሎ የሚመጣው፡፡ አንዳንዱ እንደውም እንደዱሮው ትዳር ጠለፋ ምናምን ሁላ ይሞካክር ነበር፡፡

ልማጠኛ፡-
ክቡር ጠቅላይ… እስቲ ምግቡን ይተዉት ለጊዜው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ፡፡ ዜርፎር ስጋ ራሱ ከበላሁ ትንሽ ቆይቻለሁ፡፡ በጎመን ብዛት ቬጂቴሪያን ከሆንን ቆየን፡፡ አምሮቴን ከሚቀሰቅሱ ወደሌሎች ውለታዎችዎ ብናልፍ፡፡

መለስ፡-
ኦኬ! ከዩኒቨርሲቲ ሳንርቅ እንይ፡፡ ኮብልስቶን በማን ዘመን ነው ክብር ያገኘችው? ማንንም ጠይቅ! ወላ አውሮፓ ወላ አሜሪካ የከፍተኛ ትምህርት ቀመስ ባልሆኑ ሰዎች እጅ ስንት ዘመን ቅኝ ተገዝታለች? እኔ አይደለሁም እንዴ በዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እጅ ማእረግ አግኝታ እንድትስሰራ ያደረኳት? ‹‹የተማረ ይፍለጠኝ›› ብላ የተረተችው የኮብልስተን ንግስት ለዚህ ምስክር መሆን ትችላለች፡፡

ሌላው ደግሞ ዱሮ ኤለመንታሪ ትምህርት ቤት በመደዳ ግርፊያ የሚባል ትዝታ ነበረን፡፡ ሰክሮ የመጣ አስተማሪ ረበሻችሁ ብሎ በመደዳ ይገርፍ ነበር ተማሪውን፡፡ ያ የተማሪዎች ቋሚና የሚናፈቅ ትዝታ ሆኖ አልፎ ነበር፡፡ ያንን ትዝታ ለናፈቃቸው ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፓዮኔርነት አስተዋውቄያለሁ፡፡ አንድ ተቃውሞ ሲያነሱ ፌደራል ገብቶ በመደዳ የቀጠቀጣቸው በእኔ ዘመን ብቻ ነው፡፡ በዚህም የዱሮ ትዝታቸውን የማመንዠግ እድል አግኝተዋል፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችም የናፈቃቸውንና በፊልም ብቻ ይሰሙት የነበረውን የጥይት ድምጽ እንዲሰሙ አድርገናል፡፡ ቀላል ነው እንዴ ይሄ? እነሱምኮ ትንሽ አክሽን ትሪለር ምናምን ነገር ያስፈልጋቸዋል! ይኸው በቅርቡ እንኳ በአምቦና በሌሎችም ከተሞች የኦሮሚያ ከተሞች ተማሪዎችን የዚህ በረከት ተቋዳሽ ማድረግ የተቻለው በእኔ ሌጋሲ ነው፡፡ ስንቱ ተቀነጨለ በግርግር፡፡

ልማጠኛ፡-
እስቲ አሁን ደግሞ ወደተቋማት ይምጡልኝ፡፡ ተቋማት በእርስዎ ዘመን ምን ተጠቅመዋል ብለው ያስባሉ?

መለስ፡-
ብዙ ተጠቅመዋል፡፡ ለምሳሌ ማረሚያ ቤት ተቋምን ውሰድ፡፡ ወላ ቃሊቲ ወላ ቅሊንጦ ዱሮ ከሞላ ጎደል የወንጀለኞች ቦታ ነበር፡፡ አሁን ግን ለቦታው መሰጠት ከሚገባው ክብር አንጻር ምርጥ ምርጥ የሚባሉ ሰዎችን ከየአቅጣጫው በመምረጥ እንዲታሰሩበት አድርገናል፡፡ ዛሬኮ እስር ቤት ያልገባ የለም፡፡ እንደውም ‹‹የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው›› የሚል ተረት ሁላ ተጀምሯል ሰምተህ ከሆነ፡፡ እስር ቤት በቅርብ ታሪካችን እንዲህ አይነት ክብር አግኝቶ አያውቅም፡፡ ወላ ፖለቲከኛ፣ ወላ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ወላ ጋዜጠኛ፣ ወላ የሃይማኖት አባቶች የት ነው ያሉት ዛሬ? እስር ቤት አይደለም እንዴ? ኦፍኮርስ! ሌላው ቀርቶ በርካታ ባለስልጣናት እንኳ እየገቡ ነው በስኳር ጦስ፡፡

ደግሞ እስር ቤት ብቻ አይምሰልህ ክብር ያገኘው፡፡ አግአዚ ክፍለ ጦርስ ቢሆን አልተከበረም እንዴ? ዱሮ ማን ያውቀው ነበር? እኔ ነኝ ከወደቀበት አንስቼ በሺዎች በሚቆጠሩ እናቶችና አባቶች አፍ ያስገባሁት፡፡ በእርግማን መሆኑን አትይ ዋናው መነሳቱና ዝናው መናኘቱ ነው፡፡ ዱሮ ክፍለጦሩ ጥይት እንኳ የሚተኩሰው ልምምድ ላይ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ክብር ተሰጥቶት የትም ቦታ ተቃውሞ ላይ ቀይ ኮፍያውን ለብሶ ከች ይላል፡፡ ‹‹ተኩስ!›› ሲባል ብቻ በስናይፐር መቀንደብ ነው! ‹‹ቋ! ጧ! ጯ!›› ያረጋል እያነጣጠረ! ህጻን መምረጥ የለ አዋቂ! ይህን የመሰለ ዝና ታዲያ ከየት ነው የሚመጣው? አንድን ተራ ክፍለጦር ከሂትለር የ‹‹ፖግሮም›› ፖሊስ እኩል ዝና ማቀዳጀት ቀላል ነው እንዴ?

ለማእከላዊ ምርመራ ጣቢያም ሆነ የአገር ፍቅር ለሚለበልባቸው ገራፊዎቹ የዋልኩት ውለታም የሚረሳ አይደለም፡፡ በደርግ ዘመንኮ ገራፊዎች በግልጽ ስለሚገርፉ ብዙ ወቀሳ ይደርስባቸው ነበር፡፡ በእኔ ዘመን ግን ህጋዊ ሽፋንና ጠለላ አግኝተዋል፡፡ የጸረ ሽብር ህጉ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ የግርፋት ጊዜያቸው አጭር ነበር በፊት፡፡ እኔ ነኝ ከብዙ ጥረት በኋላ በፍርድ ቤት ፈቃድ ለ4 ወራት ያክል በነጻነት መግረፍ እንዲችሉ ያመቻቸሁት፡፡ ትቢተኛ ዳኞችን እንኳ እኔ ነኝ ‹‹እንዳላየ ሆናችሁ እለፏቸው፤ ተባበሯቸው፤ ህጋዊ ሂደቱን አሳልጡላቸው›› ብዬ አስጠንቅቄ ቀና ብለው እንዳያዩዋቸው ያደረኩት፡፡ ማንም ተራ ዳኛኮ የማእከላዊ ገራፊን እንደዱሮው ሊናገረው አይችልም፡፡ መገልመጥ ቀርቶ በዓይኑ ቂጥ ሊያየው አይችልም፡፡ ተቋማዊ መከባበሩ ሰፍኗል፡፡ በዚህ ምን ያክል እንደሚደሰቱ ገምት፡፡ ተቋማዊ ነጻነት ያለውን አስፈላጊነት የሚረዱ ሁሉ ሲያመሰግኑኝ ይኖራሉ በዚህ!

ልማጠኛ፡-
እስቲ ለህዝቡ የዋሉለት ካለም ቢጨምሩልን፡፡

መለስ፡-
ለሀዝቡ በዋነኝነት ዋልኩት ውለታ ለአገሩ መሞት እንዲችል ማድረጌ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ክብር ነው ያው፡፡ የተለያዩ ጭቆናዎችን በማድረግ ሰዎች በግልም በቡድንም ለትግል እንዲነሳሱና በሂደቱም ለአገራቸው ነፍሳቸውን እንዲሰጡ አመቻችተንላቸዋል፡፡ ይሄ ደብል ጥቅም ነው ያለው፡፡ ለህዝቡም ለአገር የመሞትን ክብር እንደሚያቀዳጅ ሁሉ ለፌደራልና አግአዚም ነጻ የሰው ዒላማ ይሰጣቸዋል፡፡ ውትድርና ስትሰለጥን ያው መተኮስ ሊያምርህ ይችላል፡፡ ይህ አምሮት ባለፈው ጎንደር ላይ አንዱ ፌደራል አስራ ምናምን ሰው እንደገደለው በህገወጥ መልኩ ከሚተገበር የሰላማዊ ተቃዋሚ አጋጣሚ ሲገኝ እንደ97ቱ፣ እንደአኙዋኩ፣ እንደጋምቤላው፣ እንደደሴው፣ እንደጎንደሩና ትግራዩ፣ እንደሱማሌ ክልሉ፣ እንደአሳሳውና ኮፈሌው፣ እንደአምቦው ወዘተ በህጋዊ መልኩ ቢተገበር ይሻላል ከሚል መነሻ ነው የተነሳነው፡፡

ሌሎችንም አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፡፡ ለምሳሌ በባድመ ጉዳይ እንደቀልድ ከኢሳያስ ጋር በርጫ ላይ የፈጠርናትን ጨዋታ የምር አድርገናት ‹‹ለምን ፉል ፍሌጅድ ጦርነት አድርገነው በኋላ አንሸማገልም›› በሚል ተነጋግረን በኢትዮጵያ በኩል ወደ 70 ሺ ሰው አካባቢ ለእናት አገሩ የመሞት እድል ፈጥረናል፡፡ መሬቱን ያው ጦርነቱ ሲያልቅ መልሰንለታል ለኢሴ፡፡ ይህ ለህዝብ ከዋልኳቸው ውለታዎች አንዱ ነው፡፡

ልማጠኛ፡-
ብዙ ውለታ ነው የጠቀሱልኝ፡፡ ይህ ሁሉ ውለታ በእርስዎ ሞት መቋረጡ በእርግጥም አሳዛኝ ነው፡፡ እንዳልኩዎት…

መለስ፡-
ኖ! ኖ! አትሳሳት! እኔ በበሞቴ የተቋረጠ ውለታ የለም! አሁንምኮ እነዚህ ነገሮች ቀጥለዋል፡፡ በኔ ሌጋሲ አይደለ እንዴ አገር እየተገዛ ያለው! እነ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እና ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሁሉ በእኔ ሌጋሲ አይደል እንዴ እየተንደላቀቁ ያሉት?

ልማጠኛ፡-
ሁለቱ አይለያዩም ጌታዬ? አቶ ሐይለማርያምኮ ጠቅላይ ሚኒ…..

መለስ፡-
አይለያዩም ባክህ! ጆብ ስፔሲፊኬሽናቸው ሁሉ አንድ ነው!

ልማጠኛ፡-
በመጨረሻ የሚጨምሩት ነገር ካለ እድሉን ልስጥዎት፡፡

መለስ፡-
ብዙ የምለው እንኳ የለኝም፡፡ ህዝቡን ብቻ ማመስገን ነው የምፈልገው፡፡ እንደአንድ ጣኦት ልመለክ የምችልበትን እድል ለማመቻቸት ለሚደክሙት ካድሬዎችም ሰላምታ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ እዚህ ፌስቡክ ላይም የተወሰኑት እየሰሩት ያለውንም ስራ አይቻለሁ፡፡ ምንም አይልም፡፡ ትንሽ ብቻ አንዳንዴ እያበዙት ጥርስ እያስነከሱብኝና የማንም መቀለጃ እያረጉኝ ከመሆኑ በስተቀር ጥሩ እየለፉ ነው፡፡ ምኞታቸው ተሳክቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ እመለካለሁ የሚል ተስፋ ባላደርግም እታገሳለሁ፡፡ ይብቃን ለዛሬ፡፡

ውይ ረስቼው! ሜሮን ጌትነትንም ሰላም በልልኝ በናትህ፡፡ እሷ ልጅ ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ በሌጋሲዬ ስም ያልተመለሰ ጥያቄ ሁሉ ነጥብ ትሰጣለች አሉ! ለካ ለልማታዊ አርቲስቶችም ብዙ ውለታ ውያለሁና!

ልማጠኛ፡-
አመሰግናለሁ አቶ መለስ!

መለስ፡- አመሰግናለሁ! ሙድህ ከጣመኝ ወደፊትም ብቅ እያልኩ ቃለ መጠይቅ ልሰጥህ እችላለሁ!
===================================

(ማሳሰቢያ፡- ይሄ ቃለ መጠይቅ ምናባዊ ነው፡፡ ዓላማው መለስ በስልጣኑ ከሰጠው ጥቅም ይልቅ በጨቋኝ ስርአቱ ያዘነበብን ጉዳት በጣም እንደሚከፋ ማሳየት ነው፡፡ መለስ አንዳችም ጥሩ ነገር አልሰራም ለማለት አይደለም፡፡ ጥሩ ነገሩ በ99.6 በመቶ ተጋኖ በኢቲቪና አንዳንዴም በፌስቡክ አሰልችቶናል፡፡ ጭቆና የቀደመ በጎ ስራን እንደእሳት ይበላል፤ ለዚህ አትጠራጠሩ፡፡ የመለስ ልደት በዓል ለሆነላችሁ የስርአቱ ተጠቃሚዎችና ቅልብ ካድሬዎች ደግሞ ሙት በመውቀስ ጽንፍ ረግጬ ከሆነ ይቅርታችሁን እለምናለሁ፡፡ አንድ ቀን እንደምትወለዱ ተስፋ በማድረግ! መልካም ልደት!)

‹‹ያለምንም ደም››
‹‹ሌጋሲው ይቅደም!›› ቂቂቂ

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop