***** (ዜና መዋዕል)27/8/06
የሰሞኑን የአዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞና ግድያ በሚመለከት እንደ አንድ ግፍንና በደልን እንደሚጠላ ዜጋ ጥልቅ ሃዘን ይሰማኛል፡፡ ነገሩ በኛ ሀገር ሆነና ነው እንጅ ስልጣን የሚያስለቅቅና በግድያው የተሳተፉትንም በህግ የሚያስጠይቅ በሆነ ነበር፡፡ በየትኛውም ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን የሚያቀርብ ዜጋ እንኳን ሞት ድብደባም አይገባውም፡፡ ረብሻና ሁከት ፈጣሪዎች እንኳ ሲያጋጥሙ በሰለጠነ መንገድ በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ማቅረብ ተገቢ ነበር፡፡ ይህ ግን በኛ ሀገር ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ ከግጭቱ ባሻገር ግን ሰከን ብለን ልናነሳቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፤ እኔም በዚህ ጽሁፍ የማተኩረው በዚሁ ነው፡፡
ከ85% በላይ የሆነው ህዝብ ኋላ ቀር በሆነ የግብርና ዘዴ ህይወቱን በሚመራባት ሀገራችን የከተሜነት ወይም የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ መስፋፋት ጠቀሜታው አሌ የሚባል አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ አካባቢዎችም ከአ/አበባ በረከቷንም ሆነ ርግማኗን መካፈላቸው አልቀረም፡፡ በተለይም ከከተማዋ መስፋት ጋር በተያያዘ በዙሪያው ያሉ የኦሮሚያ ገበሬዎች ይዞታቸውን ባልተጠናና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እየሸጡ እርሻቸውን እያጠበቡ፤ ከተሞቹም ለዘላቂ ልማት አመቺ ባልሆነ መንገድ እየተስፋፉና ከአ/አበባ ጋር እየገጠሙ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ገበሬው ባለችው ጥሪት የሚያስተምራቸው ልጆቹን አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ተስፋፍተው ካልቀጠሩለት ስራ አጥ ልጁ ተመልሶ የእሱኑ መሬት እየተቀራመተ ድህነቱን ማባባሱ አይቀርም፡፡
በመሆኑም በማስተር ፕላኑ በዙሪያው ያሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወደ አ/አበባ ተካለሉም አልተካለሉ ይህንን የከተሜነት ወይም የኢንዱስትሪና አገልግሎቱን ዕድገት ታሳቢ አድርጎ በቅንጅት መስራቱ ለኔ በግሌ ጥቅሙ እንጅ ጉዳቱ አይታየኝም፡፡ ነገር ግን ከቀደመው የመንግስት አፈፃፀም ግድፈቶችና ከአጠቃላይ የስርዓቱ ችግር ስንነሳ የምንቃወምባቸው በቂ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡
ምንም እንኳ የጋራ ማሰተር ፕላኑ ለውይይት በቀረበበት ወቅት የኦሮሚያ ካድሬዎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በህገ መንግስቱ መሰረት ክልሉ ከአ/አበባ ሊያገኛቸው ስለሚገባው ጥቅሞች ቢሆንም በቀጣይ ባለድርሻ አካላት ይወያዩበታል መባሉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ፡-
1- ባለድርሻ አካላት ተወያይተው የጋራ ማስተር ፕላኑ ይቅር ቢሉ እንኳ መንግስት ከማድረግ ወደኋላ የማይልና የሚስማሙለትን ብቻ መርጦ የሚያወያይ፣ ውሳኔውንም የሚያስደግፍ መሆኑን ከቀደመው የመንግስት አካሄድ የምንረዳ መሆኑ፤
2- ገበሬዎቹም በልማት ስም ሲነሱ የሚሰጣቸው ካሳ በዘላቂነት ህይወታቸውን ለመምራት የማያስችላቸው መሆኑ፤
3- ስርዓቱ ለገበሬው ዝቅተኛ ካሳ ከፍሎ በከፍተኛ የሊዝ ዋጋ የሚሸጠው መሬት ገንዘቡ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መንገድ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም መዋሉን እንድንጠራጠር የሚያደርገን የመንግስት ባለስልጣናት ሃይ ባይ ያጣው ዘረፋና ሙሰኝነት፤
4- እንዲሁም መሬቱን በፍትሃዊነት ሀገርና ህዝብን ለሚጠቅሙ ሳይሆን የስርዓቱን ደጋፊዎችና ተጠቃሚዎች የኢኮኖሚ የበላይነት ለማስቀጠል ሲባል በአሻጥር እነዚሁ ልማታዊ ተብዬ ባለሀብቶች የሚቃረጡት መሆኑ ጥያቄ እንድናነሳ ከበቂ በላይ ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡
ጥያቄውን የምናነሳበት መንገድና ዘዴ ግን የምንፈልገውን ምላሽ ለማግኘት ያለንን ዕድል ይወስናል፡፡ ጉዳዩን የአንድ ብሄር ችግር አድርገን የምናነሳው ከሆነ ትልቁ ችግር እዚያ ጋ ይጀምራል፡፡ ሲጀመር በጋምቤላ ነዋሪዎቹ እየተፈናቀሉ ከህንድና ከአረቢያ የመጡ ኢንቨስተር ተብየዎች ከነፃ ባልተሸለ ዋጋ መሬቱን ሲነጥቁት አብረነው ስላልጮህን ዛሬ አብሮን ላይቆም፤ አማራው ህይወቱን መስርቶ ተረጋግቶ ሲኖርበት ከነበረው ቀዬ አማራ በመሆኑ ብቻ ሲፈናቀልና ከክልላችን ውጣ ሲባል የአማራው ችግር ብቻ አድርገን በማየታችን ዛሬ አብሮን ላይቆም ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገዢዎቻችን (ይቅርታ መሪዎቻችን ወይም አስተዳዳሪዎቻችን አልልም) እስካሁን ሲጠቀሙበት ለነበረው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው መጠቀሚያ መሆናችንን ነው፡፡ በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ለያይቶ የሚያጠቃን ስርዓት ዋናው ዓላማ ተባብረን እንዳንቆምና መብቶቻችንን እንዳንጠይቅ ነው፡፡
ይህ ደግሞ ተሳክቶላቸዋል፡፡ በሰሞኑ ተቃውሞ እንኳ ብሄር ለይቶ ከመቋሰሉ በተጨማሪ ጥያቄውን ሌላ መልክ ለማላበስ ምንም እንኳ ጥያቄውን ያነሱት ተማሪዎች ዓላማቸው ነበር ብለን ባንገምትም እሱን ታከው በአንዳንድ ቦታዎች ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱት፣ ንብረት ያወደሙትና የዘረፉት የራሳቸው ግብ እንደነበራቸው መካድ አይቻልም፡፡
ወደ እውነታው ስንመጣ ሱሉልታና ጫንጮ ለሚኖረው ኦሮሞ ባሌና ሐረር ከሚገኘው ኦሮሞ የሰሜን ሸዋ አማራ በባህልም በእምነትም ይቀርበዋል፡፡ አብሮ የኖረውን ሕዝብ አማራ ስላልሆነ ብቻ ሲጠቃ ዝም ይላል ማለት አይደለም፡፡ ኦሮሞውም አማራ ሲጠቃ ዝም አይልማ፡፡ ምናልባት ራሱን የተማረ ብሎ ከሚጠራውና በተግባር ግን ካልተማሩት አባቶቹ ካነሰው እንዲሁም ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍና ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት ሆዳቸውን ለመሙላት ከሚያስቡ ደም አፍሳሾች ውጭ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቻችሎ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ የሚኖር መሆኑን አንዱ ካንዱ ተጋብቶ ወልዶን ስላሳደገንና አብረንውም ስለምንኖር እናውቀዋለን፤ ይህንንም ለመረዳት ነጋሪ አያሻንም፡፡
ስለሆነም የሕዝቡን የመብት ጥያቄ በጠባብ ብሄርተኝነትና ጽንፈኝነት ተመርቶ ከማጥበብ ይልቅ፡-
– የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣
– በማንኛውም ቦታ ሰዎች ያለአግባብ እንዳይፈናቀሉና አስፈላጊ ከሆነም ፍትሃዊና ተገቢ ካሳ እንዲያገኙ፣
– በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሕዝቡን የስልጠን ባለቤትነት እንዲያከብርና ህገመንግስታዊ መሰረት የሌላቸውን አፋኝ ህጎቹን እንዲያሻሽል፣
– የስርዓቱ ብልሹ አስተዳደር እንዲሻሻል ካልሆነም ስልጣን እንዲለቅና
– ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖርባት ለሁላችንም የምትመች ሀገር እንድትኖረን ተባብረን በጋራ መቆምና መታገል ይገባል፡፡
ከሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ሌላውን ከማግለልና ከጥላቻ ፖለቲካ ከጥቂት አውቅልሃለሁ ባዮች ውጭ እንደሕዝብ የምንጠቀመው ስለሌለ በተለይ የተማረውና የሚማረው የህብረተሰቡ ክፍል ይህን ነቅቶ ሊከላከለው ይገባል፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!