ከሥርጉተ ሥላሴ 25.04.2014 (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)
ይህ የሁሉም ሰው ናፍቆት ስለሚሆን ሁላችንም የሚያስማማን ይመስለኛል። ለምን ይመስለኛል እንዳልኩ ባይገባኝም። ነፃነት ፍለጋ ለሌላው ከመማሰን በፊት አንድ ሰው መጀመሪያ እራሱን አስሮ ከተቀመጠበት ትብትብ እግዚአብሄር ይፍታህ ማለት አለበት። ወይንም አቅም ከሌለው አባቶችን „ይፍቱኝ“ ማለት በስተቀር ትርፉ የውርንጫ ድካም ነው።
ዬዬትኛውም የትግል ዓይነት ማሸነፍ ያለበት በቅድሚያ እራሱን ነው። ለሚያምኑበት ነገር ወይንም ድርጊት እራስን ከእግር ብረት አውጥቶ ተግባርን አሃዱ ማለት ያባት ነው። ቀደምቶቹ ያስተማሩን ትውፊታችን ይህ ነው። ድርጊታቸው በቋሚነት የሚስብከውም ይኽንኑ ነው። እኛ ግን ተላልፈነዋል ወይንም የነፃነት ትርጉሙ ጠፍቶብናል።
ከዚህ በላይ በእኛ ላይ ነፃ ያልሆነውን መንፈስ ደግሞ በሌላው ላይ መጫንም ሌላው መራራ አምክንዮና ወንጀል ነው። ዬውልግድ መንገድ።
ለምሳሌ – አንድ ሰው ማይክ ሲይዝ ሊነግርን የሚፈልገው የሌሎችን ፍላጎት ሳይሆን የራሱን እንቅጯን ውስጡን፤ እምነቱን፤ ወይንም ፓርቲ ካለውም የፓርቲውን ጭብጥ አቋም ሊሆን ሲገባ ሻታ ሲዞር „ሀ“ንም „ለ“ንም „ሐ“መርንም እንዳይገፋው ጤናው በታወከ አጣብቂኝ ውስጥ መንፈሱን እግር ከወርች አስሮ ስለ ነፃነት ይሰብካል። መጀመሪያ እኛው ነፃ እንውጣ።
ስንጽፍም መንፈሰ – ብራና ሆነ ቀለም ነፃ ሳይወጣ እሩቅ ተጉዘን – ስለ ነገ ራዕይ፤ ስለ ዴሞክራሲ፤ ስለ መብትና ግዴታ፤ ዋው! አልፈንም ስለ አንድ ፓርቲ ድርሻና ተልዕኮ ፖለቲካዊ ትንታኔ እንገባለን። ቀለሙ ያረፈበት ብራና ሲጻፍም — „በዚህ እንዳይታይብኝ፤ እንዲህ እንዳይተረጎምብኝ፤ ከዚህኛው ፓርቲ ፕሮግራም ጋር እንዳይቆራኝብኝ „ ወዘተ ከዬትም ጋር ከማንም ጋር ይገናኝ። እምነቴን ያሰፈረው ብራናዬ በነፃነት ፍላጎቱን ለታዳሚዎቼ ቁልጭ አድርጎ በድፍረት ሊናገር ወይንም ሊያብራራ ይገባል። በዚህ ዙሪያ የሚነሱትን ማናቸውም ጠረባዎች ሆነ ጫናዎች፤ በተጨማሪም ዱላዎችንም ፍላጎቴ ሆነ መንፈሴ እስመችቶ መሸከም ደግሞ ግድ ይለዋል። ይህ ጤነኛ መንፈስ ነው። ስለምን? ውስጤ ደሙ ጠርቷላ!
አንደኛ እራሴን አላፈንኩትም፤ ከወያኔ ከምጠብቀው ነፃነት በፊት እኔ እራሴ ነፃነቴን አውጄ እራሴን በግልጽነት ከዞግ አስተዳደር ምኞት ነፃ ወጥቻለሁ። ሁለተኛ ታዳሚዎቼን ስርክርክ ባላ ፍላጎት ግዜያቸውን ስላልተሻማሁ በእነሱ የውሳኔ አቋም ላይ ግልጽ የሆነ፣ ከተጽእኖ የጸዳ ነፃነት አበርክቻለሁ። በሌላ በኩል ልቤ ውስጥ የሚጉላላውን እብጠት ስላፈነዳሁት መግሉ ፈሶ ተፈውሻለሁ። በተጨማሪም አለፍ ብዬ ሰለሌሎች ሀገራዊ ጉዳይ ለመናገርም …. ጤናማ ቀለሜ ልዩ አቅምና ኃይል ፈጥሮልኛል። ግልጽነት – ቀጥተኝነት – መድህንነት፤
ያው እኔ የሚቀናኝ ሆነ ደስ ብሎኝ የምሟገተው ከተክሌሻ ጋር ስለሆነ እንደ ምሳሌ ማንሳት የምሻው ከሱ ጹሑፍ ነው። ያን ያህል ብሄራዊ ተቆርቋሪነት የዘከረ፤ የማስታወቂ ተግባሩን በብቁ ኃላፊነት የተወጣ ብራና እና ኮቢ —- ወርቅ እርእስ፣ ብቁ ሙያዊ ትንተና፣ ሸበላ ብዕር፤ ግን እንዲህ ሲል ወረደ „የአንድነት የሶስት ወር ዘመቻ ለመርዳት በውጭ አገር የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ኢትዮጵያዊያን ቃል እየገቡ ነው፡፡ መቼም ሲያትል ጎንደሬ ይበዛል፤ ጎንደርን ወስዷል፡፡” ሲያትልብቻነውንጎንደሬያለው? https://zehabesha.info/archives/28998
አሁን ይህ አገላለጽ እራሱም ነፃ አልወጣም – ከወያኔ የጥቃት ሰለባም አልዳነም። በሌላ በኩል ሲያትል ባሉ ደጋፊ ሆነ በማይደግፉ አባላት ዙሪያም ሰፊ ተጽዕኖ ያሳድራል። አይደለም ለዛሬ ለነገም። ቅንነታዊ ተሳትፎ እንዲህ በመንደር ቀፎ ፍላጎት ጎርጉሮ መጠቅለል ለምን አስፈለገ?! አልገባኝም – እንዲገባኝም አልፈቅድም።
ነገሩ እጅግ ረቂቅ ነው። እንዲህ በድረስ ድረስ ቋንቋ ሊገለጽ የሚችል አይደለም። እርግጥ በጎንደር ዙሪያ ልቤን ሞልቼ ብዕሬን የማናግርበት ቀን ይኖረኛል። በጣም መረጋገጫ ሆኗል። ልኩንም አልፏል። ወያኔ እንደ አደስ የሚደቁሰው ላይበቃ። ትንሽ የጀመርኩት ሥራ ተግ ሲልልኝ እመለስበታለሁ። የሆነ ሆኖ፤ ታናሼ ተክሌሻ እንዴት እንዳዬው አላውቅም እንጂ እሱ ያለበት ቶረንቶ እኮ እነማን እንዳሉበት የጥናት ሥራ ቢሰራ ፍሬውን ማግኘት ይችላል። የኢትዮጵያ መሬት በባንዳ ጣሊያን ፍላጎት አስፈጻሚ፣ በሙጃው ወያኔ በትናንሽ አጥቢያዎች መሸንሸኑ አልበቃ ብሎ ባደገው በታላቁ አሜሪካ፤ ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር የመንደር ቅዬሳውን እንዲህ አና ብለን እናጦፈዋለን።
ስለዚህ እኛ እራሳችን ነፃ ሳንወጣ፤ የፍላጎታችን በትረ መነሻን ሳንረዳ ነው ለሌለው ነፃነት የምንታገለው። መጀመሪያ ነገር ጠላታችን የሚፈልገውን ነገር ማደረግ እኮ ቁልጭ ያለ ልዩ ሽልማትም – ድጋፍም ነው ለጠላት ወረዳ። ጠላታችን የማይፈልገውን ነገር ተጋፍቶ ማደረግ ደግሞ የጠላታችን አናት ድምጽ በሌለው መሳሪያ ወንፊት በማደረግ የወገንን ጦር በስንቅም በትጥቅም በብቃት ማደራጀት ነው።
የምናፍቃችሁ የሀገሬ ልጆች „ልባምነት“ ጉደለን። እኔ የምፈልገው ብዕር፣ እኔ የምፈልገው ድምጽ፣ እኔ የምፈልገው ሚዲያ፣ የወያኔን ጭንቅላት ክፍት አድርጎ ቦንቡን አጉርሶ እንደ ነበረ የሚከድን፤ ክድን አድርጎ ዞር ሲል ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ከወያኔ አንጎል የተቀበረው ቦንብ ከውስጡ ፈንድቶ ብትንትን እንዲያደርገው ነበር። ግን አልሆነም። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆነ – ነገርዬው።
ወያኔን የሚያስጨንቅ „የደም ዕንባ ብሄራዊ ጥሪ“ ሰልፍ እንደራጃለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለፍላጎቱ አደግድገን ሰፈር እንቆጥራለን። ለጫካ ተመክሮ እንሰግዳለን። ወያኔ የካቲት ላይ ያው ለመስረቅ፤ ወረራም ተፈጥሮው ስለሆነ ጎንደርና ወሎ ያው የለመደበትን የኪስ ማውለቅ ተግባሩን ይከውን ነበር። ተገዶ ሲለቅ ወረራ ባደረገባቸው ቦታዎች የመጀመሪያ ተጠቂው ብላክቦርድና ትምህርት ቤት ነበር። ልጆች ታዳጊዎች እንዳይማሩ። አንድ የገጠር ት/ቤት በ5 ዓመትም አይገነባም። በፈረሰው ሙሉ ግድግዳ ላይ ደግሞ አስተውሉ በአይነምድሩ “ማሌሊት ያሸነፋል“ ብሎ ይጽፍ ነበር። ይህ በአይኔ በተደጋጋሚ ያዬሁት ሃቅ ነው። ይህ እንዲመራን መፍቀድ ውርደት ሳይሆን ውርዴ ነው ለእኔ። ለማንኛውም አንድነትን ለመደግፍ የገንዘብ ድጎማ ለማድረግ መንደር ምስረታው ቶረንቶ ላይ ጦፈ //// ጎንደሬው – ለጎንደር፤ ጎጃሜ – ለጎጃም፤ ወለጌው – ለወላጋው ወዘተ ….
ወገኖቼ – ህመሙ ጠልቆ ሊያርመጠምጠን የሚችለው ከቶ ምን ሲሆን ይሆን? በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ መሬት አጥቢያ የወያኔ የቋሳ እርምጃ ይገለጽበታል። እንደ ጥንቸል ወገኖቻችን የመከራ ቤተ ሙከራ ሆነዋል። የወያኔ ህዝብን በግፍ ማማስ ያልነካው አካበቢ የለም፤ ገጀሞው ያልከተከተው – መጥረቢያው ያልፈለጠው – ጦሩ ያልሰነጠቀው – ፍሉ ያልቀቀለው – አውሎው ያለንገላተው ዜጋና አካበቢ ፈጽሞ የለም። ጥቃቱ ሊያንስ ወይንም ሊበረክት ይችላል። ግን ለዜጎቹ ኃላፊነትም የማይሰማው፤ የሙሴነት አቅም የሌለው፤ ሥልጣኔ የተነነበት የጎሳ አስተዳደር ነው ያለው። ለዚህ ቢያንስ መነሻ ፍላጎታችን ማወቁ የማጥቂያ መንገዳችን ለመለዬት ባስቻልን ነበር ግን ዛሬም አልሆነም።
እኔ ጋንቤላ – ሙያሌ – አፋር – ሴሩ – ጎሬ – ሚዛን ወዘተ ያለው ወገኔ እንግልት እንዲያርመጠምጠኝ ካልፈቀድኩለት እንደ ተኛሁ ነው። ለዛውም ደመመን ተጭኖኝ። ቢያንስ በመንፈስ በነፃነት ሀገር ልቆና በልጦ መገኘት እንዴት ይነሰን?! እንዴት ያቅተን?!
ከዛ ቀንበጥ የ30 አመት ወጣት ረ/ አውሮፕላን አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ተገኘ እኮ የተማርነው ኮሽታ ሳይኖር፤ መርዝን አንቦልቡሎ አጉርሶ ነፃነቱን ጠላቱን አስገድዶ ያወጀ ብቁ ድርጊት ነው። አሁን በጀግና ፊት ምራቅ አጋዚ አይተፋም፤ ተዘቅዝቆ አይገረፍም፤ በአረም ጀሌ ከፍና ዝቅ የለም። ባዶ እጁንም አይደለም ጀግና ነፃነቱን ያረጋገጠ። ነፃነቱን የተጋፈውን ዘረኛ አንባገነን በዓለም አደባባይ እንደ ጀግናው ዘራዕይ ደረስ የጠላቱን ፍላጎት አዋርዶ ከመንፈሱ ጉሩቦ ላይ ቆሞ ረግጦም፤ ባዶነቱን እርቃኑን አስቀርቶ፤ በእጁ በገባ መሳሪያ ጊዜ ሳያጠፋ በፍጥነት „ ከጣሊያን እጅ አዙር ቅኝ ግዛትነት፤ ከወያኔ ብቀለና ትቢተኝነት እራሱን ነፃ ሲያወጣ በድል ሞሽሮ ነው“ የጠላቱን አከርካሪ እንኩት አድርጎ ደፍሮ ነው። ይህ ነው የነፃነት ትግል። እራሱን ነፃ ያወጣ ነፃነት ….. ይላችኋል እንዲህ ይገለጻል።
መከወኛ — ግን ሰው ስለምን በነፃነት ሀገር ተሸማቆ እራሱን ፍላጎቱን አስሮ ወይንም ቀፍድዶ ይኖራል?
የኔዎቹ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ።
* ልንረሳ ስለምንችል አትድከሚ፤ አስተውሽን ብላችሁ ኢሜል ለላካችሁልኝ ውዶቼ ከልብ አመሰገንኩ። እንዳላሰለቻችሁ በማለት ነበር የ24.04.2014ትን — www.lora.ch. ወይንም www.tsegaye.ethio.info Aktuell Sendung Radio Lora በዚህ ታገኙታላችሁ። ከእኔ ጋር በመሆናችሁም በልቤ ውስጥ አተምኳችሁ – ክብረተቼ!
እኩልነትን ያደመጠ – ኢትዮጵዊነት ብቻ የመፍትሄ መንገዳችን ነው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።