(እውነተኛ የወንጀል ታሪክ)
የደብረ ብርሃን ከተማ ከአዲስ አበባ 130 ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ ዛሬ…. ዛሬ የቀድሞ ዝናዋ ደብዝዞ… የድሮ ገናና ስማ ከስሞ ብዙ ባትጠራም ከዛሬ 540 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የመናገሻ ከተማ ነበረች፡፡ ከ1426-1460 ዓ.ም ድረስ ለ34 ዓመታት በነገሱት በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት የኢትየጵያ የመናገሻ ከተማ ወደ ነበረችው ደብረ ብርሃን ከተማ ሲጓዙ፤ ከተማዋ ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀር ወደ ቀን ተገንጥ ጠራ የምትባለውን አነስተኛ የገጠር ከተማ ያገኛሉ፡፡ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ሽፈራውና ታናሽ እህቷ ሙሉ ሽፈራው የተወለዱባት ናት ጠራ፡፡ ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬ የሁለቱም አክስት ናቸው፡፡ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ወደ ጠራ ሄደው ሲመለሱ ሁለቱንም የወንድማቸውን ልጆች ይዘው ነበር የመጡት፡፡ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ጥሩወርቅ ሽፈራው የአምስት ዓመት ልጅ ስትሆን ሙሉ ደግሞ ባልጠነከሩት እግሮቿ ድክ ድክ ማለት አልጀመረችም፡፡ እንደታዘለች ነበር የመጣችው፡፡ ያኔ ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬ የአንድ ልጅ እናት ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ጣሊያን ሀገር በመኪና አደጋ ልጃቸው ጆቫኒ ካማራና ከረሜሎ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ እዚህ አዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቢቀበርም እስካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ያሳደጓቸው ሁለቱ ወንድሞቻቸው ልጆች የዓይናቸው ማረፊያ… የእርጅና ዘመናቸው ተስፋቸው ነበሩ፡፡
ሁለቱ እህትማማቾች ያደጉትና ባይዘልቁበትም የተማሩት በአክስታቸው ቤት ነበር፡፡ ሁለቱም እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ በራሳቸውና በተለያየ ምክንያት ግን በትምህርታቸው ከዚህ በላይ አልዘለቁም፡፡ የህይወት እጣፈንታቸው የሚያመጣላቸውን እየጠበቁ እንደ እናትም አባትም ሆነው ያሳደጓቸውን አክስታቸውን መርዳት ጀመሩ፡፡
ሁለቱም እህትማማቾች አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ ይደጉ እንጂ ከተማ ውስጥ እንዳደጉ ልጆች አይደሉም፡፡ ከቤት ውጭ የሚያሳልፉት ጊዜ የለም፡፡ በቤተሰብ ቁጥጥር ነበር ያደጉት፡፡ ለቤተሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆን ለመላው ጎረቤትና የአካባቢ ሰው የሚመች ፀባይም ነበራቸው፡፡
ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት አካባቢ የዚያን ቤተሰብ የአኗኗር ሁኔታ የሚለውጥ ነገር ተከሰተ፡፡ ታላቅ እህትየው ጥሩወረቅ ሽፈራው ባል ለማግበት የምትፈልግ መሆኑን ለቤሰብና ለዘመድ አሳወቀች፡፡ እሷን ሆነው… እሷን ወክለው ሽምግልና ይቀመጡ ዘንድም ጠየቀች፡፡ በቤተሰብ ሽምግልና ከተቀመጡት ሰዎች ደግሞ አንዱ አጎቷ አቶ ተሾመ ምንዳዬ ነበሩ፡፡
ሽምግልና ተቀምጠው የወንድማቸውን ልጅ የሚያገባውን ሰው ተመለከቱ፡፡ በሁለቱ ተጋቢዎች መሀከል ያለውን ልዩነት ለመገመትም አልተቸገሩም፡፡ ‹‹እንዴት እስከ ዛሬ ትዳር ሳይመሰርት ቆየ?›› ብለው በውስጣቸው አሰቡ፡፡ አስበው አልቀሩም ጠየቁት፡፡ ‹‹….ከዚህ ቀደም ሚስት ነበረችኝ፡፡ ነገር ግን ኤርትዊ ስለሆነች ወደ ኤርትራ ሄዳለች፡፡›› የሚል መልስ እንደሰጣቸው ነው የሚናገሩት፡፡
ጥሩወርቅና ባለቤቷ የረጅም ጊዜ ትውውቅ አልነበራቸውም፡፡ አንዳቸው ሌላኛውን የሚያጠኑበት ጊዜም አልነበረም፡፡ በአጭር ጊዜ ትውውቅ ወደ ትዳር አመሩ፡፡ በቤተሰብ ሽማግሌ በአንድ ጎጆ ጥላ ስር ለመኖር ተስማሙ፡፡ ባለቤቷ የከባድ መኪና ሹፌር ነበር፡፡ ሁለቱ ተጋቢዎች ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ኑሯአቸው ጥሩወርቅ ባደገችበት በአክስቷ በወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬ ቤት ሆነ፡፡ ይህ ደግሞ ለአዲስ ተጋቢዎቹ ጥቅም ነበር፡፡ ለቤት ኪራይ የሚያስቡት ነገር የለም፡፡ ለቤት ኪራይ እዳ ከማሰብ ገላግሏቸዋል፡፡ ለጥሩወርቅ ደግሞ ያሳደጓትን አክስቷን አጠገባቸው ሆና ለመጦር አመቺ ሆኖላታል፡፡
ውሎ ሲያድር የጥሩወርቅ ባለቤት ከዚህ ቀደም ትዳር እንደነበረው ተሰማ፡፡ ሶስት ልጆች የወለደችለት ባለቤቱና ሶስቱም ልጆች እዚሁ አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ አካባቢ እንደሚኖሩ የጥሩወርቅ ቤተሰብ አወቀ፡፡ ቢሆንም ሁለቱን ተጋቢዎች ለመለያየት ጊዜው የረፈደ ነበር፡፡ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት መሆኑን የጥሩወርቅ ቤተሰብ ከቀን በኋላ ቢደርስበትም እንዲለያዩ ማድረግ ግን እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሆነባቸው፡፡ በዚህ ወቅት ጥሩወርቅ የመጀመሪያ ልጃቸውን ነፍሰ ጡር ነበረች፡፡ አሁን የስድስት ዓመት ታዳጊ የሆነውን አንተነህን ፀንሳ ነበር፡፡ አብረው እንዲኖሩ ከመፍቀድ ውጭ ለጥሩወርቅ ቤተሰብ የተለየ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡
እንዲያውም ይባስ ብሎ ጥሩወርቅ ነፍሰ ጡር እያለች ጠፋ፡፡ ባለቤቷ ነኝ ብሎ አብሯት መኖር ከጀመረና ከፀነሰች በኋላ ከቤት ጥሎ መጥፋቱ መላው ቤተሰቡን በጣም ነበር ያስቆጣው፡፡ ጥሩወርቅና ሙሉ ሽፈራው ለአቶ ጥላሁን ተክሌ የአጎት ልጆች ናቸው፡፡ አቶ ጥላሁን በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ሲገልፁ ‹‹….በመሀል ጠፍቶ ነበር፡፡ ነፍሰ ጡር እያለች ነበር የጠፋው፡፡ እንዴት ካስረገዛት በኋላ ይጠፋል? አልን፡፡ ተፈልጎ ነው የተገኘው›› ብለውናል፡፡
የመጀመሪያው ልጅ ከተወለደ በኋላ በቤት ውስጥ ሰላም ጠፋ፡፡ እነ ጥሩወቅን ከልጅነት ጀምሮ ያሳደጓቸው ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬ በሽምግልና የዕድሜ ዘመናቸው… በመጦሪያቸው ወቅት የባለትዳሮቹን ንትርክ ማድመጥ የዘወትር ልምዳቸው ሆነ፡፡ ለአመግባባቱ መንስኤ ነው የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ መሰረት በሌለው ቅናት አባወራው የሚፈጥረው ጭቅጭቅ ነበር ያንን ቤት ሰላም ያሳጣው፡፡ በከንቱ ጥርጣሬ በሚነሳ ቅናት የሚፈጠረው ጭቅጭቅ ጥሩወርቅን አስመረራት፡፡ ከምትቋቋመው በላይ ሲሆንባትም በተደጋጋሚ ያደገችበትን የአክስቷን ቤት ለቃ ለመውጣት ሁሉ ተገዳ ነበር፡፡ በሁለቱ ባለትዳሮች መሀከል በቅናት የተፈጠረው አለመግባባትና የዘውትር ጭቅጭቅ የነፍስ ዋጋ ያስከፍላል ብሎ የገመተ አንድ የቤተሰብ አባል ባይኖርም የሁኔታው እያደር መባባስ ግን የጥሩወርቅ ታናሽ እህትን ሙሉን በጣም አሳሰባት፡፡ ከጠራ የመጣችው አብራት ነው፡፡ በአክስታቸው ቤትም ያደጉት በአንድ ላይ ነው፡፡ በሁለቱ መሀከል የነበረው ፍቅር ከተለመደው የእህትነት ፍቅር የዘለለ ነበር፡፡ አንዳቸው ለሌላኛቸው የማይሆኑት ነገር አልነበረም፡፡ ሲዋደዱ ፍፁም ልዩ ናቸው፡፡ ሙሉ ሽፍራው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ እህቷ የመሰረተችው ትዳር ሰላም እንደነሳት በቅርበት ስለምታይ እሷንም የውስጧን ሰላም አሳጣት፡፡ ተረጋግታ በአንድ ልብ ትምህርቷን እንዳትከታተል አደረጋት፡፡ የእህቷ ባለቤት በጥሩወርቅ ላይ ምን ያደርስባት ይሆን?… የሚለው ነገር ነበር እረፍት የነሳት፡፡ ትምህርት ቤት ቁጭ ብላ የምታስበው ስለ እህቷ ነበር፡፡ ወደ ቤት ስትመለስ በሰላም የምታገኛት አይመስላትም፡፡ ዘወትር የሚታሰባትና የሚታያት በእህቷ ላይ የሚደርሰው ወይንም ይደርሳል ብላ የምትገምተው መጥፎ ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትምህርቷ ውጤት ላይ መጥፎ ተፅዕኖ አመጣ፡፡ ሙሉ ሽፈራው የእህቷ ነገር ሲያሳስባት… እያደር ሲያስጨንቃት ትምህርቷን ከዘጠነኛ ክፍል አቆመች፡፡ እህቷን ለመጠበቅ… የሚመጣውን ሁሉ ከእሷ ጋር ለመካፈል ብላ ከቤት መዋል ጀመረች፡፡
የሙሉ ትምህርቷን አቋርጣ ከቤት መዋል ግን ብዙም ለውጥ አላመጣም፡፡ ቅናት በሚፈጥረው ጭቅጭቅ ሁሌም ቤቱ ሰላም እንዳጣ ነው፡፡ ያሳደጓቸው ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬ ደግሞ ዕድሜያቸው እየገፋ ነው፡፡ በወር አንድ መቶ ሰላሳ ብር ብቻ ነው የጡረታ አበል የሚያገኙት፡፡ በ1967 ዓ.ም በወጣውና የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት የህዝብ እንዲሆን ባደረገው አዋጅ ከተወረሱባቸው ቤቶች ሰላሳ ሶስት ብር ብቻ የቤት አበል ያገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለሚያስተዳድሩት ቤተሰብ በቂ አይደለም፡፡ ሙሉ አንድ ነገር አሰበች፡፡ እናትም አባትም ሆነው ያሳደጓትን አክስቷን ለመጦር፣ ከራሷ አብልጣ የምትወዳትን እህቷንም ለመርዳት ሰርታ ገንዘብ ለማግኘት ፈለገች፡፡ እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ሄዳ ለመስራት ወሰነች፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ስትደርስ ሁለት ልብ ሆና ነው፡፡ ከምትወዳትና ከምትሳሳላት እህቷ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ለመሄድ መወሰኑ ከፍተኛ ሀሳብ ውስጥ ነበር የከተታት፡፡ ግን ደግሞ ያሳደጓትን አክስቷንና እህቷን መርዳት አለባት፡፡ የሁለተኛው ፍላጓቷ አየለ፡፡ የእህቷን ነገር እዚሁ ላሉ ዘመዶቻቸውና ለእግዚአብሔር አደራ ብላ ወደ ዐረብ አገር ለመሄድ ወሰነች፡፡ የመጀመሪያ እርምጃዋ ፓስፖርት ማውጣት ነበርና አወጣች፡፡ ግን እንዳሰበችው ሳትጓዝ ቀረች፡፡ የእህቷ ባለቤት ፓስፖርቱን ወስዶ ደበቀባት፡፡
የጥሩወርቅ ባለቤት ፀባይ እያደር በጣም እየባሰበት ሄደ፡፡ ማንም የቤተሰብ አባል ወደ ቤት እንዲመጣ አይፍልግም፡፡ በዚህም ምክንያት…. ጭቅጭቁን ጠልታ ከቤት ወጥታ ተከራይታ ለመኖር የተገደደች ሶስተኛ እህታቸውም አለች፡፡ በድንገት አንድ የቤተሰብ አባል ከመጣ ባለቤቷ ከሌላ ወንድ ሊያቃጥር የመጣ አድርጎ ነው የሚወስደው፡፡ በተለይ ደግሞ ሁለተኛው ልጅ ሱራፌል ሲወለድ ጭቅጭቅና ንትርኩ ባሰ፡፡ ለጭቅጭቁ መባባስ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹…ሁለተኛው ልጅ የእኔ አይደለም›› ማለቱ ነበር፡፡ እሱ ባለበት የጎረቤት ሰው ከመጣ ጸብ ነው፡፡ አንዳንዴ የቤት ስልክ ተደውሎ ከተዘጋ ‹‹…ውሽማሽ ነው የደወለው›› ብሎ ጸብ ያነሳል፡፡ ጥሩወርቅ እንደቀልድ የመሰረተችው ትዳር እንደ እሳት ያቃጥላት ጀመር፡፡ በሰቀቀን ከሰውነት ተራ ወጣች፡፡ የባለቤቷ ሁኔታ ሲያስመርራት ከቤት ወጥታ ትሄድ ነበር፡፡ ያኔ የነበውን ሁኔታ አቶ ጥላሁን ሲያስታውሱት ‹‹….እያደር ሲብስባት ሴቶች ጉዳይ ሄዳ አመልክታ ነበር፡፡ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ ተይዞም ነበር፡፡ ጥሩወርቅ ደግሞ ትንሹን ልጅ ይዛ እኔ ጋ ነበር የመጣችው፡፡ እሱ ግን አንድ ቀን መኪና ተከራይቶ ይጠብቃት ጀመር፡፡ ድንገት ልጇን ይዛ ስትወጣ አገኛትና ያዛት፡፡ ወደ ቤትም አመጣት፡፡ ሀገሯ ድረስ ጠፍታ ሄዳ ነበር፡፡ እሱ ነበር ያመጣት›› ይላሉ፡፡
በሁለቱ መሀከል የነበረው አለመግባባት ተወግዶ ትዳራቸው ሰላም እንዲሆንና በፍቅር ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ለበርካታ ጊዜ ሽማግሌዎች ሽምግልና ተቀምጠዋል፡፡ ግን ሽምግልናው መፍትሄ አላመጣም፡፡ በተደጋጋሚ ለሽምግልና የተቀመጡት አቶ ተሾመ ምንዳዬም ‹‹….በትዳራቸው መሀከል ለነበረው ያለመግባባት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እሷ አትነግረኝም፡፡ ግን ሲከፋትና ሲብስባት ሮጣ እኔ ጋ ነበር የምትመጣው፡፡ ቤቱን ይረብሻል፡፡ እንዲሁ ቁጭ ብሎ ነው የሚያድረው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ ምክንያት በሌለው ቅናት ነው፡፡ ቤት የመጣ ዘመድ ሁሉ የእሷ አቃጣሪ ይመስለዋል፡፡ ቤት ሰው እንዲመጣ በፍፁም አይፍልግም›› ነው ያሉን፡፡
የመጀመሪያው ልጃቸው አንተነህ ትምህርቱን ጀምሯል፡፡ ታናሽየው ሱራፌልም ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር መዋዕለ ህፃናት ነው የሚውለው፡፡ አባታቸው ግን እንደ አባትነት የትምህርት ሂሳባቸውን አይከፍልም ነበር፡፡ የልጆቹ የወር የት/ቤት ሂሳብ የእናታቸውና የቀሪ ዘመዶች ኃላፊነት ነበር፡፡
መጋቢት 26/2000 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ጥሩወርቅና ባለቤቷ መጨቃጨቅ ይጀምራሉ፡፡ ከወትሮው የተለየ ምክንያት አልነበረም የጭቅጭቁ መንስኤ ተነጋግረው መግባባት… ችግሩን ተወያይቶ መፍታት አልቻሉም፡፡ በትዳር ሰባት ዓመት ኖረው… ሁለት ልጆችን ወልደው ፀባይ ለፀባይ ተግባብተው፣… ባህርይ ለባህርይ ተጠናንተው ሰላም መፍጠር አልቻሉም፡፡ ጥሩወርቅ ሁኔታው እያደር ቢብስም የምታደርገው ነገር አልነበረም፡፡ ዕድሜያቸው ከሰማኒያ ዓመት በላይ የሆናቸው አክስቷ በዚያው ቤት ውስጥ አሉ፡፡ እሳቸውን አክብሮ እንኳን ጭቅጭቁን አልተወውም፡፡ ባለቤቱንና የልጆቹን እናት ብቻ ሳይሆን መላው የቤተሰብ አባል ሰላም አጣ፡፡ ልጆቹም በለጋ የዕድሜ ዘመናቸው በወላጆቻቸው መሀከል የሚሆነውን ሁሉ እያዩ፤ የሚነጋገሩትንም እየሰሙ ነበር፡፡ አክስታቸው ወ/ሮ ዘነበችም በመጦሪያና በማረፊያ ዕድሜያቸው ሊሰሙትና ሊያዩት የማይፈልጉትን ነገር እያዩና እየሰሙ ነው፡፡ የጥሩወርቅ ታናሽ እህትም ሙሉ የሚሆነውንና ሊፈጠር የሚችለውን በስጋት እያየች እየጠበቀች ነው፡፡ አንድ ጎረቤታቸው ነበሩ የእዚያን ዕለት ያስማሟቸው፡፡ ለጊዜው ነገሩ የበረደ… እርቀ ሰላም የወረደ ነበር የመሰለው፡፡ ጎረቤትየውም እንደ ጉርብትናቸው አስማምተዋቸው ሄዱ፡፡ የቤተሰቡም አባላት ሌሊቱ የሰላም ይሆን ዘንድ በየልባቸው እየተመኙ በየአልጋቸው አረፍ አረፍ አሉ፡፡
ሌሊት 10 ሰዓት፣ ሁሉም በየቤቱ የሰላም እንቅልፍ ተኝቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሰማይ ጥቁር ካባውን ለብሷል፡፡ በየመንደሩ ከሚሰማው የውሾች ጩኸት በስተቀር መንደሩ ፀጥ እንዳለ ነው፡፡ ሁሉም የሰላም እንቅልፍ ተኝቷል፡፡ እነ ጥሩወርቅ የተኙበት ክፍል ውስጥ ግን ሰላም አልነበረም፡፡ የጥሩወርቅና የባለቤቷ የመኝታ ክፍል ውስጥ በዚያ ውድቅት ሌሊት ግርግር ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ላይ የተኙትን አዛውንቷን ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬንና ሙሉ ሽፈራውን ከእንቅልፋቸው ቀሰቀሳቸው፡፡ አዛውንቷ በከዘራቸው እየተደገፉ ከሙሉ ጋር ወደ በረንዳ ይወጣሉ፡፡ ሌሊቱ ብርዳማ ቢሆንም ቀጥሎ ምን ይፈጠር ይሆን?… የሚለው ስጋት ብርዱ እንዳይሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡ ሁለቱም ህፃናት ሰማይና መሬት ባልተላቀቁበት… ፍጥረት በሙሉ በሰላም በእንቅልፍ ዓለም ባሉበት ሰዓት በቤት ውስጥ የተፈጠረው ነገር ከእንቅልፋቸው ቀስቅሷቸዋል፡፡
ምን እንደሚያደርጉ ወደየት እንደሚሄዱ ግራ በተጋቡበት ሰዓት ጥሩወርቅ ወደ ውጭ ትወጣለች፡፡ ባለቤቷና የሁለት ልጆቿ አባት ደግሞ ከኋላ ተከትሏታል፡፡ ሁለቱ ልጆች ደግሞ ደብዛዛ ቢጫ ቀለም ከተቀባው ሳሎን ውስጥ ሆነው የሚሆነውን ሁሉ እያዩ ነው፡፡ የስድስት ዓመቱ ህፃን አንተነህ፤ አባቱ እናቱን ተከትሎ ወደ ውጭ ከመውጣቱ በፊት ሳሎን ውስጥ የነበረውን ስልክ ገመድ እንዳላቀቀው ይናገራል፡፡
ጥሩ ወርቅ ውደ ውጭ ወጣች፡፡ በረንዳ ላይ አክስቷንና እህቷን ተመለከተች፡፡ በቀኝ በኩል ያለው ቆርቆሮው የአጥር በር ዝግ ነው፡፡ ወደ ግራ በሩ የተከፈተ ኩሽና አለ፡፡ ጣራዋም… ግድግዳዋም ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነው ኩሽና ነበር ለጊዜው ማምለጫ መስሎ የታያት፡፡ ገባች… ከውስጥ ደግሞ ሌላ የጣውላ በር አለ፡፡ እሱንም አልፋ ገባች፡፡ ወደ ሌላ ቦታ መሄጃ ማምለጫ ግን አልነበረውም፡፡ ለሰባት ዓመት ያህል አብራው በትዳር የኖረችው ሁለት ልጆችን የወለደላት ሰው ተከትሏት ገብታል፡፡ በእጁ ላይ ደግሞ ሽጉጥ አለ፡፡ ‹‹…እባክህ አትግደለኝ!… ልጆቼን ላሳድግበት›› ስትል ተማፀነችው፡፡ ይህንን ተማፅኖዋን በረንዳ የነበሩት አክስቷ፣ እህቷና ልጆቹ ይሰሙ ነበር፡፡
ተማፅኖዋ ልቡን አላራራውም፡፡ ያሰበውንም ከመፈፀም አላገደመው፡፡ እየተማጸነችው… እንዳይገድላት እየለመነችው ተኮሰባት፡፡ የተኮሳት የመጀመሪያ ጥይት ግንበሯ ላይ መታት፡፡ እንደገናም ተኮሰባት፡፡ በአካባቢው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባለት ነበሩ፡፡ የጥይት ድምፅ የተሰማበትን አካባቢ ለመለየት አልተቸገሩም፡፡ በፍጥነት ነበር ከቦታው ደርሰው የጥይት ተኩስ የተሰማበትን ጊቢ የከበቡት፡፡ በቦታው የደረሱት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባላት የሙሉ ሽፈራውን የድረሱልኝ ጩኸት ይሰማሉ፡፡ በሩን እንድትከፍትላቸውም ይጠይቃሉ፡፡
ቀደም ሲል የተሰማቸው ተኩስ ድምፅ በእህቷ ላይም ምን እንዳስከተለ የማታውቀው ሙሉ በሩን ለፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አባላት ልትከፍት መራመድ ስትጀምር ከኋላዋ በተተኮሰ ጥይት ተመታ ትውድቃለች፡፡ ወዲያው ነበር ህይወቷ ያለፈው፡፡ በድጋሚ የተሰማው የተኩስ ድምፅ በቤት ውስጥ ላሉት በሙሉ የማይመለስ ነበር የመሰለው፡፡ ተጨማሪ አደጋ በሌሎች ላይ እንዳይደርስ የፌዴራል ፖሊስ አበላት በሩን ሰብረው ለመግባት ሲሞክሩ ‹‹እንዳትገቡ! አለበለዚያ ራሴን አጠፋለሁ›› ይላል፡፡ እነሱም በተጠንቀቅ ሆነው ‹‹ራስህን አታጥፋ፡፡ እጅህን ስጥ›› ይሉታል፡፡ አሁን በማረሚያ ቤት ያለው ተጠርጣሪም እጁን ይሰጣል፡፡
ታናሽየዋ ሙሉ ሽፈራው ወዲያው ህይወቷ ሲያልፍ ጥሩወርቅ ግን በህይወት ነበረች፡፡ በቦታው በደረሱት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባለትና በአካባቢው ሰው ትብብር ወ/ሮ ጥሩወርቅ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ትወሰዳለች፡፡ የተመታችው ጭንቅላቷ ላይ ነበር፡፡ የህክምና ባለሙያዎች ህይወቷን ለማትረፍ የተቻላቸውን ያህል ቢያደርጉም በማግስቱ ሁለት ጨቅላ ህፃናትን ትታ ይህችን ዓለም በሞት ተለየች፡፡ ሰላም ያልነበረው ትዳር ቅናት በፈጠረው ስሜት የተፈጠረው ጭቅጭቅ የሁለት እህትማማቾችን ሕይወት እስከፍሎ ሁለት ጨቅላ ህፃናትን ያለ አሳዳጊ አስቀርቶ በአሳዛኝ ሁኔታ አበቃ፡፡ ከተወለዱባት ከጠራ መንደር አብረው እንደመጡ ሁሉ አብረው ይህችን ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
የስድስት ዓመቱ አንተነህ ወላጅ እናቱን አጥቷል፡፡ አባቱ ደግሞ በነፍስ ግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በማረፊያ ቤት ነው፡፡ በልጅ አንደበቱ የመጨረሻውን ሌሊት ሲናገር እንባ እያነቀው ነበር፡፡ ‹‹…መጀመሪያ እናቴን ተኝታ እያሰቃያት ነበር፡፡ እሷ ወደ ኩሽና ስትሄድ ተከትላትና ተኮሰ፡፡ ሙሉ ፖሊሶች መጥተው በሩን ልትከፍትላቸው ስትል አትክፈቺ አላት፡፡ ልትከፍትላቸው ስትል ግን በጥይት መታትና ወደቀች፡፡ እባክህ ልጆቼን ላሳደግ አትግደለኝ እያለችው እናቴንም ገደላት›› ብሎናል እንባ እያነቀው፡፡
አቶ አጥናፍ ሰገድ ነጋሽ የተባሉት የ‹‹ቲ-ሩም›› ባለቤት ባደረጉት እርዳታ የሁለቱ እህትማማቾች የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ፡፡ ዛሬም አቶ አጥናፍ ሰገድ ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬን በአንዳንድ ነገር ቢረዷቸውም የሁለቱ ህፃናት የነገ ህይወት መላ ቤተሰቡን እያሳሰበ ነው ያለው፡፡ ወ/ሮ ዘነበች አሁን ከጡረታና ከቤት አበል የሚያገኙት አንድ መቶ ስልሳ ሶስት ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ደግሞ ራሳቸውን ጨምሮ ለሁለቱ ህፃናት የሚበቃ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ እንኳን ለልጆቹ ለራሳቸውም አብስሎ የሚያበላቸው ሰው ይፈልጋሉ፡፡ ዕድሜያቸው ገፍቷል… አቅምም የላቸውም፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሰን ጥዋት ላይ ስንሄድ አቶ ጥላሁን ተክሌን ለአዛውንቷና ለሁለቱ ልጆች ቁርስ ለመስራት ጉድጉድ ሲል ነበር ያገኘነው፡፡ የልጆቹን የወደፊት ህይወት በተመለከተም ሲናገር ‹‹እነዚህ ልጆች እናታቸውን አትጠዋል፡፡ ግን ማደግ… መማር አለባቸው፤ እሷ እንዳታስድጋቸው አቅሟ ደካማ ነው፡፡ እኔ እየመጣሁ ነው አንዳንዴ የምረዳቸው፡፡ ልጆቹ ነገ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው የሚያሳድጋቸው ድርጅት ብናገኝ ደስተኛ ነኝ›› ብሏል፡፡
በትዳር ጓደኛሞች መሀከል የሚፈጠርን ያለመግባባት በሰላም ለመፍታት ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን አንተነህና ሱራፌልን የሚያሳድጋቸው፣ ወ/ሮ ዘነበች ምንዳዬንም የሚጦራቸው የለም፡፡ የሁለት እህትማማቾችን የህይወት ዋጋ ያስከፈለው ትዳር በሌሎችም ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ በነፍስ ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብም በማረሚያ ቤት ሆኖ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ነው፡፡
የሁለት እህትማማቾችን ህይወት የበላ ትዳር
Latest from Blog
\በጎንደር እና ወታደራዊ ውጥረት / ፋኖ በላሊበላ ኤርፖርት ዉጊያ/ ባለሃብቱ በአዲስ አበባ ታሰሩ የቀድሞው መከላከያ አመራር ፋኖን ሸለመ || ሻ/ቃ ዝናቡ ስላወቅሁ ደስ ብሎኛል || ጥር 7 አዲስ ቪዲዮ
በጎንደር እና ወታደራዊ ውጥረት / ፋኖ በላሊበላ ኤርፖርት ዉጊያ/ ባለሃብቱ በአዲስ አበባ ታሰሩ
አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ
አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም
ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ
የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ
ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ አንድ አባውራ ምንነቱ ያልታወቀ እህል ከገበያ ገዝቶ ለሚስቱ አምጥቶ ሰጣት አሉ፡፡ ከሰጣትም በኋላ ሚስቱ ያንን እህል ፈጭታ ቂጣ ላርግህ ብትለው፣ እንጀራ ላርግህ ብትለው፣ ገንፎ ላርግህ ብትለው … ምን አለፋህ
ወሰንየለሽ ኦሮሙማዊ ዕብደት!!
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን
የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ
ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?
የቀጠለው ውጊያና የፋኖ ድሎች / የግብፅ ፣ሶማሊያ ፣ኤርትራና ሱዳን ውሳኔ / “የህወሓት መከፋፈል ገደለን “|EN
የቀጠለው ውጊያና የፋኖ ድሎች / የግብፅ ፣ሶማሊያ ፣ኤርትራና ሱዳን ውሳኔ / “የህወሓት መከፋፈል ገደለን “|EN
ከሃይለገብርኤል አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ
የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’
ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም January 10, 2025 በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና