April 18, 2013
26 mins read

ትዳር ለምን ሰላም አልባ ይሆናል? መፍትሄውስ…

በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ መሆንዎን ማወቅ ይፈልጋሉ?

ከሊሊ ሞገስ

‹‹ጋብቻ ክቡር ነው መኝታውም ቅዱስ ነው››
ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ውስጥ ማከናወን ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ እና አብይ የሆነው ጋብቻ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ቁጥር ያላቸው ሙሽሮችን የምንመለከተው፡፡ ይሁን እንጂ በተመሳሳይ መልኩ ባማረና በደመቀ ስነ ስርዓት ባይሆንም፣ በቁጥር /በብዛት/ የበለጠው ቡድን ከፍተኛ የሆነ ሽልማት ያገኛል የተባለ ይመስላል ክቡር የሆነውን ጋብቻ ረግጠውና ጥለው ትስስራቸውን ለመበጣጠስ የየፍርድ ቤቱን ችሎት የሚያጨናንቁ ባለትዳሮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ሲሆን በሌላ በኩል የፈጠሩት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሚዛኑን ደፍቶ መፍታት ሳይችሉ በመካከላቸው ሰላም፣ ፍቅርና ደስታ ጠፍቶ እንዲያው ለይስሙላ አብረው የሚኖሩት ቁጥር ደግሞ ከተፋቱት የሚበልጠው ነው፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጠው ጥናታዊ መግለጫ ነው፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከተመሰረቱ ትዳሮች 1/3ኛው በጥንዶች መካከል እውነተኛ ፍቅር ሰላምና ደስታ በመጥፋቱ ትዳር በፍቺ ሊቋጭ ችሏል በማለት ሰሞኑን የገለፀው በተለያዩ የዓለማችን ክፍል በጋብቻ ዙሪያ ጥናት የሚያደርግ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት በዚሁ ጉዳይ /በጋብቻ/ ዙሪያ የሚያጠና ቡድን ከስድስት ጥንዶች /ባለትዳሮች/ መካከል ደስተኛና ሰላማዊ በመሆን የትዳር ህይወታቸውን ማስቀጠል የቻሉት /የቻለው አንዱ ትዳር መሆኑን ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡
እንግዲህ ይህ በገሀዱ ዓለም የሚታየው እውነታ ለሁሉም ባይሆንም ለብዙዎች የጋብቻችን ክቡርነት የመኝታውም ቅዱስነት ማርከስ ማለት አይደለም ትላላችሁ?
ይሁን እንጂ የጋብቻን ክቡርነት የመኝታውንም ቅዱስነት ጠብቆ መጓዝ የጥንዶቹ የውዴታ ግዴታ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህንን ግዴታ ለመወጣት ደግሞ ሰው ሆነን በመፈጠራችን የተሰጠን ትልቅ ብቃትና ፀጋ አለን፡፡ ነገር ግን ይህን ብቃታችን ተጠቅመን በጋብቻ ውስጥ መኖር ያለበትን ሰላም፣ ፍቅርና ደስታ እያጣጣምን ለመኖር ስላለንበት ዘመን እውነታ፣ ስለ እውነተኛ ፍቅር ምንነት እና ስለ ትዳር ጠንቅቀን ማወቅ ግድ ይለናል፡፡ ለዛሬ በዚህ ዙሪያ ጥቂት ለማለት ወደድን፡፡
መልካም ንባብ

በእርግጥም ሁሉም ጥንዶች /ተጋቢዎች/ በወግ በማዕረግ ተውበውና ተሞሽረው በደመቀ የሠርግ ስነ ስርዓት ትዳራቸውን መመስረት መፈለጋቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም እንደየአቅሙ ወይም እንደ ገቢ መጠኑ ወይም እንደየአስተሳሰቡ ከእወቁልኝ ካርድ እና በጣት የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ከማሳተፍ ጀምሮ አገር ጉድ የሚያሰኝ ድል ያለ ሠርግ በመሰረግ የትዳር ህይወቱን አንድ ብሎ ይጀምራል፡፡ ይሁን እንጂ እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ትልቁ ነገር የትኛውም አይነት የሠርግ ስነ ስርዓት በተጋቢዎች መካከል ዘላቂነት ያለው እርካታና የደስተኝነት ስሜት ለማምጣት ምንም አይነት አስተዋፅኦ እንደሌለው ወይም ለዘላቂ ደስተኝነታቸው ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የተደረገባቸውና ብዙ የተደከመባቸው ሠርጎች ተጋቢዎቹ /ጥንዶቹ/ የሽርሽር ጊዜያቸውን ሀኒሙኒያቸውን ሳይጨርሱ በመካከላቸው ሰላምና ደስታ እየራቀ ሲሄድ ይስተዋላል፡፡
ምንም እንኳ እውነታው ይህ ቢሆንም፣ ማንኛውም ትዳር ዘላቂነት ያለው ደስታ፣ ፍቅርና ሰላምን በውስጡ እንደያዘ ለሁልጊዜም መጓዝ ይችላል የሚሉት የዘርፉ ተመራማሪ ሊቃውንቶች፣ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ጥንዶቹ በተናጥልም ሆነ በጋራ ለትዳራቸው የጋራ ጥቅም በእውነተኛ ስሜትና ፍላጎት ሲያስቡና ሲሰሩ ነው ይላሉ፡፡ አክለውም ነገር ግን እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ጥንዶች ወደ ትዳር ህይወት ከመግባታቸው በፊት አንድ አስደሳች እና ማራኪ ትዳር ለመመስረት የሚጠይቀውን መስፈርት አስቀድመው ማሟላት የቻሉ እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡
በእርግጥ በባለ ትዳሮች መካከል ዘላቂነት ያለው አስደሳችና ሰላማዊ የትዳር ህይወትን ሊያስገኝ ወይም ሊያመጣ የሚችል አንድ አይነት የሂሳብ ቀመር ወይም መመሪያ ባይገኝም፣ ምናልባት በእውነታው ዓለም ውስጥ ያለ የየራስ መሻታቸውን ለማርካት ትዳሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካበረከተ በጥንዶቹ መካከል ቀጣይነት ያለው ደስተኝነትና ፍቅር ሊኖር ይችላል፡፡ ይህን እንደ መመሪያ ወይም ቀመር መውሰድ ሁላችንንም ሊያስማማ ይችላል፡፡ ማለትም አንድ ሰው በትዳሩ ወይም በትዳር አጋሩ ደስተኛ መሆን የሚችለው በትዳሩ ውስጥ የኑሮ እና የአጋርነት ዋስትና የማግኘት ፍላጎቱ፣ የሁልጊዜ ተወዳጅና ተፈቃሪ የመሆን ፍላጎቱ፣ በተጓዳኙ ዘንድ አስፈላጊና ጠቃሚ ሰው ስለመሆኑ እውቅና የማግኘት ፍላጎቱ /recognition/ እና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ሁሌም መርካት የቻሉ እንደሆነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ፍላጎቶችን ማሟላት በራሱ ፈታኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ እነዚህ ፍላጎቶች በተሟሉበት ሁኔታ ውስጥ በባለ ትዳሮች ሰላማዊና አስደሳች የፍቅር ሕይወት ላይ ጥላውን የሚያጠላው አሁን የሚታየው ዘመናዊ አኗኗር /Modern living/ የፈጠረው ችግር መሆኑ ይታመናል፡፡
ማለትም ዘመኑ በወለደው ዘመናዊ አኗኗር ውስጥ የተፈጠረው ያልተረጋጋ ኢኮኖሚ /የገቢና ወጪ አለመመጣጠን/ ከፍተኛ ውጥረትና ጭንቀት፣ የጊዜ እጥረት፣ የሰላም መጥፋት፣ ከፍተኛ የጥሎ ማለፍ ውድድርና ሌሎች ለዘመናችን ባለትዳሮች አስደሳች የትዳር ህይወት መጥፎ መሰናክል እንደሆኑ ይታመናል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወይም መሰናክሎች ለዘመናችን ባለትዳሮች ፈታኝ መሆናቸው የማይታበል ሀቅ ቢሆንም ማንኛውም ሰው በየዘመኑ የሚያጋጥሙትን አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች በጣጥሶ በድል በማለፍ ካሰበውና ካለመው ለመድረስ የሚስችል ተፈጥሯዊ ብቃት ባለቤት ስለመሆኑ የቀደሙትም ሆኑ የዘመናችን ስኬታማ ባለትዳሮች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ወጣቶች የግልም ሆነ የጋራ ፍላጎታቸውን የማሳካት ጽኑ እምነትና የተቀራረበ ስብዕና ወይም ስነ ልቦና ባለቤት ከሆኑ ዘላቂ ደስታ፣ ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት የትዳር ህይወት መምራት እንደሚችሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
እንግዲህ ስለ ትዳር ወይም ጋብቻ ስናነሳ በጥንዶቹ መካከል የሚፈጠረው ፍቅር መሰረታዊና ቀዳሚ ጉዳይ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ ስለ ፍቅር ወይም ስለ ፍቅር ትርጓሜ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት እንሞክር፡፡

ፍቅር
ፍቅር ማለት አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ጠንካራና የጠበቀ የግል ግንኙነት እንዲኖረው እና ያፈቀረውን ሰው ደስታና ደህንነት እንዲሁም ሌሎች ፍላጎቶች የማሟላት ብሎም የበለጠ የማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎትና ኃላፊነት እንዲያድርበት የሚስችል እውነተኛ ስሜት ማለት ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ ያለ ሰው የውዴታ ደረጃው፣ የጠለቀ ፍላጎት፣ የተቆርቋሪነት ስሜት እና ሌሎቹ መልካም ፍላጎቶችን በየጊዜው እየገነባ እና እያዳበረ ይሄዳል፡፡
ፍቅር ማለት ያፈቀሩትን ሰው መርዳት ወይም ማወቅ ማለት ነው፡፡ ከጠለቀ እውቀት፣ ከአስተዋይነት እይታ እና ከዳበረ ልምድ የፈለቀ ጥልቅ መረዳት፡፡ ያፈቀሩትን ሰው መረዳት ወይም ጠንቅቆ ማወቅ ማለት ስለ ግለሰቡ ስሜት፣ ፍላጎት፣ ባህሪ፣ ጉድለትና ሌሎች በቂ እውቀት ማግኘት ማለት ነው፡፡
ስላፈቀረው ሰው በቂ መረዳት ያለው አፍቃሪ፣ ያፈቀረውን ሰው ስሜት የሚጎዳ ድርጊት የመፈፀም አጋጣሚም ሆነ የሚያስቀይም ቃል የመናገር እድል አይኖረውም፡፡ በመሆኑም በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ ባሉ ጥንዶች መካከል የሚኖረው አለመግባባት /misunderstanding/ አነስተኛ ወይም ከቁጥር የማይገባ መሆን ይችላል፡፡
ፍቅር ማለት እምነት ወይም መተማመን ማለት ነው፡፡ ፍቅር ማለት ፍቅረኛሞች እርስ በእርሳቸው በሚኖራቸው ውህደት ወይም ቁርኝት፣ ታማኝነት እና ፍትሀዊነት ወይም ሚዛናዊነት ላይ እርግጠኝነት እንዲሰማቸው የሚያደርግ እምነት ወይም መተመመን ማለት ነው፡፡ ይህም አፍቃሪው ለተፈቃሪው የገባውን ቃል አክባሪነቱንና ታማኝነቱን ስለሚያረጋግጥ ተፈቃሪው በአፍቃሪው ላይ ሙሉ እምነትና መተማመን እንዲያሳድር ከማድረጉም ባሻገር የራሱንም ታማኝነትና እውነተኝነት ጠብቆ እንዲዘልቅ ያስገድደዋል፡፡ በዚህም ተፈቃሪዎች ሙሉ እና እውነተኛ የርስ በርስ መተማመን መፍጠር ይችላሉ፡፡
ፍቅር ማለት አንደኛው ለሌላኛው ቅድሚያ የሚሰጥበት እና አንድነትን በመፍጠር ወገናዊነቱን የሚያሳይበት መድረክ ነው፡፡ ያፈቀሩትን ሰው መሻትና ፍላጎት እውን ይሆን ዘንድ የራስን /የግልን/ ፍላጎት፣ ደስታና ስሜት አሳልፎ መስጠት ወይም መስዋዕት ማድረግ ጎልቶ የሚታይበት መድረክ ነው፡፡ ይህ መድረክም ተፈቃሪው የራሱን ስሜትና ፍላጎት ለአፍቃሪው አሳልፎ የመስጠት ዝንባሌና ፍላጎት እንዲያድርበት ያደርጋል፡፡ በዚህም ለተፈቃሪዎች የየግል ፍላጎትና መሻታቸውን አንደኛው ለሌላኛቸው አሳልፈው ለመስጠት ወይም መስዋዕት ለማድረግ ፈቃደኝነት እና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስችላል፡፡ እንግዲህ ይህ ደረጃ በደረጃ በጥንዶች መካከል የሚፈጠረው ህብረት ወይም አንድነት የሚገለፅበት የላይኛው እርከን ነው፡፡
ፍቅር ማለት በትልቅ ስሜት መዋደድ ወይም የፍቅርን ስሜት በተዋበና ባማረ መልኩ መግለፅ ማለት ነው፡፡ የፍቅር ስሜትን ወይም በግንኙነት የሚፈጠር ደስታና እርካታና ላፈቀሩት ሰው የሚገልፁበት ማራኪና ቀልብ ገዢ ድርጊታዊ እንቅስቃሴ ወይም አርት ማለት ነው፡፡
አፍቃሪው ከተፈቃሪው ሰው ጋር ሲገናኝ የሚተቃቀፍበት አስተቃቀፍ የወደደውንና የተመኘውን ገላ የሚደባብስበት አደባበስ፣ አብረው የእግር ጉዞ ሲያደርጉ /ሲንሸራሸሩ/ እጆቿን/ቹን የማይዝበት/የምትይዝበት አያያዝ፣ ወገቧን/ወገቡን የሚያቅፍበት/የምታቅፍበት አስተቃቀፍ፣ ከንፈር ለከንፈር የሚሳሳሙበት አሳሳም በቃ ምን አለፋችሁ አጠቃላይ እንቅስቃሴና ድርጊቱ/ቷ ውበትና አርት የተላበሰ መሆኑ የተፈቃሪውን ልብ በሀሴት ጮቤ ከማስረገጡ ባሻገር ተመሳሳይ ወይም የበለጠ ምላሽን እንዲሰጥ ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ በፍቅረኛሞች መካከል ያለውን ጥልቅ ፍቅር በተለየ መልኩ ማስኬድ የሚቻልበት ሂደት ነው፡፡
እንግዲህ በፍቅረኛሞች መካከል የሚፈጠረው እውነተኛ ፍቅር ማለት ከላይ እንዳየነው ሲሆን፣ ለትዳር ህይወት መቀዝቀዝ ምክንያት የሚሆኑ ተጨማሪ ነገሮችን ለማየት እንሞክር፡፡ ፍቅረኛሞች ደስተኛና ስኬታማ የትዳር ህይወት ለመምራት ሁለቱም ግለሰቦች በየግላቸው ፍቅር መስጠትና መቀበል ወይም ከላይ የተገለጡትን መግለጫዎች መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ ጥረት/ፍቅር መስጠት ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ማለትም አልፎ አልፎ አንዳንድ ተፈቃሪዎች ፍቅርን የመስጠት ብቃታቸው ወይም ስሜታቸው በእጅጉ የተጎዳ የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ ምናልባትም በአስተዳደጋቸው ወይም በሆነ ወቅት የደረሰባቸው በደል እንደ አስገድዶ መድፈር ያለ መጥፎ ጠባሳ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ምክንያት የተፈጠረባቸው ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ፍቅርን መስጠት እና መቀበል በተለይም ፍቅር የመስጠት/የፍቅር ስሜታቸውን መግለፅ ብቃትና ችሎታቸውን መልሰው ማምጣት የሚችሉበትን የስነ ልቦና ህክምና ከማግኘታቸው በፊት ወደ ትዳር ህይወት መግባት እንደሌለባቸው ይመክራል፡፡ ምክንያቱም ስኬታማ የትዳር ህይወትን ለመምራት ፍቅርን መስጠትና መቀበል ወይም ሌላውን የማፍቅር ፍላጎት መሰረታዊ በመሆኑ ነው፡፡
ሌላው ለትዳር መፍረስ ወይም ደስተኛ የትዳር ህይወት ላለመምራት ተጠቃሽ ምክንያት የሚሆነው ተፈቃሪዎች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት የሚመሰርቱት ፍቅር እውነተኛ ወይም ፍቅር የሚመስል ነገር ፍቅር ያልሆነ ጊዜያዊ ስሜት (infatuation) መሆን አለመሆኑ ለይተው ላያውቁ ወይም እውነተኛ ፍቅር መስሏቸው መጀመራቸው ነው፡፡ በእርግጥ አንድ በፍቅር ስሜት ውስጥ ያለ ‹‹ያፈቀረ ሰው›› የያዘው ፍቅር ከእውነተኛ ስሜት የመነጨ ፍቅር ይሁን ከተመለከተው አካላዊ ቁመና ወይም ከተፈጠረበት የወሲብ ስሜት የመነጨ የፍቅር ስሜት ይሁን በቀላሉ ለመለየት ያዳግተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ ፍቅር ማለት ከላይ ለማየት እንደሞከርነው፣ ያፈቀሩትን ሰው የማወቅ፣ የመተማመን፣ የመተባበር ወይም አንድነትን የመፍጠርና ሌሎች እውነታዎች በውስጡ የያዘና ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም እውነተኛ ፍቅር ረዘም ያለ ጊዜ የሚጠይቅ እንጂ በአንድ ቀን ወይም ሳምንት ወይም ወር ውስጥ የሚፈጠር አይደለም፡፡ በአይናችን አይተን ስለተማረክን ወይም በወሲብ ስሜት (መሻት) የሚፈጠር ፍቅር ብዙ ጊዜ ፍቅር የሚመስል ጊዜያዊ ስሜት ሲሆን ተፈቃሪዎች ወደ ትዳር ካመሩ አልፎ አልፎ ግንኙነታቸው ወደ እውነተኛ ፍቅር የመሸጋገር እድል ቢኖረውም በአብዛኛው ግን በሰላም እና ደስታ ማጣት ብሎም በመለያየት (በፍቺ) የሚደመደም ይሆናል፣ እንዲሁም ወሲብን (ከወሲብ መጣጣምና እርካታን) ብቻ መሰረት በማድረግ የሚመሰረት ጋብቻም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
በአጠቃላይ ለአንድ ትዳር ዘላቂ ሰላም፣ ደስታ እና እርካታ የጎላ ድርሻ ያለውን እውነተኛ ፍቅር ሁሉም እንዲኖረው የሚመኘው፣ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ የሚያጣጥሙት ቢሆንም ሀቁ ይህ ሊሆን የቻለው ከራሳችን ድክመት እንጂ ከእውነተኛ ፍቅር ባህሪ እና መገለጫ ወይም ተአምራዊነት አለመሆኑን ሁላችንም አምነን ልንቀበለው ይገባል፡፡ እንዲያውም ማወቅና መገንዘብ የሚገባን እውነተኛ ፍቅር ማለት ለሁሉም የሰው ልጅ የተሰጠ ተፈጥሯዊ ፀጋ እና በጊዜ ሂደት ውስጥ በቀላሉ ማግኘት የሚቻል ቅዱስ ነገር እንደሆነ ነው፡፡

በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ መሆን አለመሆንዎን ማወቅ ይፈልጋሉ?
እንግዲያውስ ከታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በጥንቃቄ መርምረው ይመልሱ

ከፍቅረኛዎት ወይም ከትዳር አጋርዎት ጋር አንድ ላይ በሚሆኑበት ወቅት ወይም በሆነ ርዕስ በሚነጋገሩበት ወቅት ወይም የሆነ ስራ በጋራ በሚያከናውኑበት ወቅት የደስታ ስሜት ይሰማዎታል?

ከፍቅረኛዎ ወይም ከትዳር አጋርዎ ጋር ረዘም ላለ ሰዓት በሆነ ጉዳይ በሚወያዩበት ወቅት እርስ በርስ ከመሰለቻቸት ውጭ መሆን ይችላሉ? መሰረታዊ ፍላጎቶቻችሁ በተቀራራቢ ወይም በተመሳሳይ ነገሮች ላይ ነው? ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ሀሳቦች /እና አላማዎች ይኖራችኋል? እርስ በርስ በጥልቀትና በእርግጠኝነት እንተዋወቃለን፤ ወይም ፍቅረኛዬን አውቀዋለሁ እረዳዋለሁ ይላሉ?

ከትዳር አጋርዎ የያዞት ፍቅር ከማንነታቸው እንጂ ከላይ ካዩት አካላዊ ውበት ወይም ካገኙት ወሲባዊ እርካታ ስላለመሆኑ እርግጠኛ ነዎት?

አልፎ አልፎ ለሚያጋጥማችሁ የሀሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች መፍትሄ ለመስጠት ወይም ወደ ጋራ ስምምነት ለመምጣት ተስማሚ /ተደራዳሪ/ ይሆናል?

አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ንትርክና ጭቅጭቆች የተሻለ መፍትሄ በማግኘት ይቋጫሉ?

አንድ ነገር ሲያስቡም ሆነ ሲያቅዱ እኔ በሚል ሳይሆን /እኔና ፍቅረኛዬ/ በሚል ስሜትና መንፈስ ነው?

ፍቅረኛዎን ወይም የትዳር አጋርዎን ሁሌም ለማስደሰት ይሞክራሉ?

ሰዎች በሚሰበሰቡበት ስፍራ ከፍቅረኛዎ ወይም ከትዳር አጋርዎ ጋር ሆነው መታየትዎ የኩራትና የደስታ ስሜት ይፈጥርቦታል?

በመካከላችሁ ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ ለተግባራዊነቱ በሙሉ አቅምዎ ይጥራሉ?

ልብ ይበሉ፡-
ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች መልስዎ ‹‹አዎ›› በትክክል የሚል ከሆነ በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ ለመሆንዎ ምክንያታዊ ማረጋገጫ አገኙ ማለት ነው፡፡
መልካም የትዳር ህይወት

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop